እግዚአብሔር ሰይጣንን ውደድ ወይም ቀኝህን ሲመታህ ግራህን አዙርለት አላለም! – በላይነህ አባተ

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

ክቡር ቹንዋ አቼቤ ነገሮች ፍርክስክስ አሉ(Things Fall Apart) በሚለው መጽሐፋቸው፤ ክቡር ዴዝሞን ቱቱም በአንድ ወቅት ንግግራቸው የሳጥናኤልን ተግባራት የሚፈጽሙ ቁማር ተጫዋቾች የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል ለማጭበርበር እንዴት እንደሚጠቀሙበት ለማሳየት እንዲህ ብለው ነበር፡፡

“አውሮጳውያን ሰባኪዎች ወደ አፍሪካ በመጡበት ዘመን እነሱ መጽሐፍ ቅዱስ እኛ ደሞ መሬት በእጃችን ነበረን፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የያዙት ሰባኪዎችም አይናችሁን ጨፍኑ እንጸልይ አሉን፤ እሽ ብለን አይናችንን ጨፍንና ጸለይን፡፡ ከጸሎቱ በኋላ አይናቸንን ስንገልጥ ከእኛ እጅ የነሱ መጽሐፍ ቅዱስ ተነሱ እጅ ደሞ የእኛ መሬት ገብቶ አየን፡፡”

አሁን ደግሞ ዘር በማጥፋት የሳጥናኤል ወንጀል የተሰማሩ ግልገል ቁማር ተጫዋቾችና መሰሪ ሳባኪ ካድሬዎቻቸው መጽሐፋችሁ “ ጠላትንህን ውደድ፤ ቀኝህን ሲመታህም ግራህን አዙርለት” ስለሚል ስንጨፈጭፋችሁም፣ ስናስራችሁም፣ ስንገርፋችሁም፣ ስናሰድዳችሁም ውደዱን፣ ቀኝ ጉንጫችሁንም ስንጠፈጥፋችሁ ግራችሁን ስጡን እያሉ ዘልዛላን ሊያጃጅሉ ይሞክራሉ፡፡

እንደሚታወቀው ሳጥናኤል እግር ኖሮት ሲንቀሳቀስ፣ ምላስ ኖሮት ሲሰብክ ወይም እጅ ኖሮት ቁማር ሲጫወት አይታይም፡፡ ሳጥናኤል መኖሩ የሚታወቀው እግዚአብሔር ቅዱሳንን ለበጎ ነገር ሲጠቅምባቸው እንደሚስተዋለው ሳጥናኤልም እርጉማንን ለእርኩስ አላማ በመሳሪያነት ሲጠቀምባቸው ነው፡፡

ሳጥናኤል እንደ ውቃቢ የሚጋልበው ሰው “ሳጥናኤል ነኝ!” እያለ ወይም የሰይጣንን ቋንቋ እየተናገረ አይመጣም፡፡ ሳጥናኤል ቤቱን የሰራባት ሰው ሰይጣን መስሎ ወይም የሰይጣን ስብከት እየሰበከ ቢመጣ እንኳን የሚከተለው የሚሰማውም ጤናማ ሰው ስለማያገኝ ለማሳሳት የቅዱሳንን ቃል እየተናገረ ይመጣል፡፡ ለምሳሌ ሊያጠቃው የፈለገውን አማኝ እግዚአብሔር “ግራህን ሲመቱህ ቀኝህን ስጥ! ጠላትህንም እንደ ራስህ አድርገህ ወደድ” ብሏል እያለ ያጃጅላል፡፡

አማኝ ሆይ! እግዚአብሔር በማቴዎስ ወንጌል 5፡ 39-40 “…ቀኝ ጉንጪህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት” ያለው ሰው ሲመታህ እንጂ ደምህን ለመጠጣት ሰይጣን ሲወግርህ አለመሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ሰው ማለትም በህሊና የተሸፈነ አይምሮ ያለው ፍጡር እንደ ሆነ ዘፍጥረትም ሆነ ተፈጥሮ ያስረዳል፡፡ በህሊና የተሸፈነ አይምሮ ያለው ሰው ቅኝ ፊትህን ሲመታህ ግራህን ስታዞርለት በትግስትህ፣ በእምነትህና በሰውነት ብቃትህ ተመስጦ ተእግርህ ሥር ተደፍቶ እያለቀስ ተልቡ ይቅርታ ይጠይቃል፤ በሰራው ግፍ ተጸጽቶም ምናኔና ሱባኤ ይገባል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ‘‘ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች!!’’ በኒቆዲሞስ (ከሀገረ ኢትዮጵያ)

ሳጥናኤል ቤቱን የሰራበት እርጉም ግን ግራ ፊትህን ስታዞርለት የበለጠ አውሬ ይሆንና ቆመህ እየሄድክ ዓይንህን በወረንጦ ይዘነቅርሃል፤ ማህጸን ሰንጥቆ ያልበሰለ ጽንስህን ያዋጣዋል፤ አንገትህን ይቆርጥሃል፤ እሬሳህንም እንደ ቅዱስ ጳውሎስና ጴጥሮስ ሬሳ ይዘቀዝቃል፤ተመሬትም ይጎትታል፡፡ በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር ቀሳውስትም ሆነ ምዕመናን ለሳጥናኤል እንዳይተኙ፤ ቀኝ ፊታቸው ሲመታቸው ግራቸውን እንዳያዞሩና እንዳይጠፈጠፉ ይልቁንም በመንፈስም ሆነ በአካል ጠንክረው እንደ ሙሴ፣ ኢያሱና ዳዊት እንዲታገሉ አዝዟል፡፡

በተመሳሳይ መንገድ እግዚአብሔር በሉቃስ 6፡27-28 “…. ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ” ያለው ለሰው ጠላት እንጅ ለሰይጣን ጠላት አለመሆኑን ልብ ይሏል፡፡ የሰይጣን ተከታይ ጭራቆች ያለምንም ተቃውሞ የክርስቶስን አማኝ ለማጥፋት ሲፈልጉ እነዚህን የቅዱስ መጽሐፍ ምዕራፎች አይናቸውን በጨው ታጥበው ይጠቅሳሉ፡፡ አንዳንድ በእምነትም ወይም በአይምሮ ያልበሰሉ በጎችም እውነት መስሏቸው የጭራቆችን ስብከት እየሰሙ ብ ኣ ኣ! እያሉ ይከተላሉ፡፡

እግዚአብሔር “ጠላትህን ውደድ!” የሚለውን ትዕዛዝ የሰጠው ግን በህሊና የተሸፈነ አይምሮ ያለው ጠላት ሲገጥም ብቻ ነው፡፡ “ጠላትህን ውደድ” የሚለው ትዕዛዝ መሰረትም በህሊና የተሸፈነ አይምሮ ያለው ፍጡር ጠላትህ ሆኖ ሳለ ስትወደውና መልካም ነገር ስታደርግለት በደግነትህና በእምነት ጽናትህ ተደንቆ ከአንተ ትምህርት ይወስዳል፤ በጾምና በጸሎትም ከአረመኔአዊ ባህሪው ተላቆ ለመለኮት ይንበረከካል የሚል ነው፡፡

በአምስቱ ዘመን ወረራ ፋሽሽቶች ሃይማኖትን ወይም የመጽሐፍን ቃል በጦር መሳሪያነት ሊጠቀሙበት ሞክረው ነበር፡፡ ለምሳሌ በላይ ዘለቀ ማርያምን እንደሚወድ በስለላቸው ተረድተው “በማርያም ይዤሃለሁ” የሚል መልእክት ይልኩለት ነበር፡፡ እርሱም የሰይጣን መለክት መሆኑን ተረድቶ “የእናንተ አገር ማርያም ታልሆነች የኔ አገር ማርያም የሰው አገር ውረሩ አትልም” እያለ ይመልስላቸው ነበር፡፡ የአምስቱ ዘመን ጭራቆች “ቀኝህን ሲመቱህ ግራህን ስጠው” የቁማር ስብከት በአያቶቻችን ብልህነት፣ እንደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ባሉ መነኩሳት ተጋድሎ፣ እንደ መላከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ባሉ በመላ አገሪቱ በተሰማሩ የካህን ፋኖዎችና አርበኞች ከሽፏል፡፡   

ተጨማሪ ያንብቡ:  በሰፊው የኦሮሞ ህዝብ እና ልጆች ላይ እየተፈፀመ ያለውን ግፍ በአጽንኦት እናወግዛለን!!!

የጥበብ መጀመሪያው እግዚአብሔርን መፍራት ነው፡፡ ቀጣዩ ደሞ ህሊና ያለውን የሰው ጥላት ህሊናውን ግጥጥ አድርጎ ተፋቀ የሰይጣን ወይም የጭራቅ ጠላት መለየት ነው፡፡ ህሊና ያለው ጠላት ሲገጥምህ ክርስቶስ እንዳዘዘው ውደደው፣ ቀኝ ፊትህን ሲመታህም ግራህን ስጠው፡፡ የሰይጣን ጠላት ወይም የሚጨፈጭፍ ጭራቅ ሲገጥምህ ግን እግዚአብሔር እንዳዘዘው እንደ ሙሴ፤ ኢያሱና ዳዊት በጽናት ታገለው፡፡ “የሰይጣን ጠላት ቀኝህን ሲመታህ ግራህን ስጠው ወይም ውደደው” በፊት አፍሪካን ሊቀራመቱ የመጡ ቀንዳም ቁማርተኞች አሁን ደግሞ ህልውናንም ሊነፍጉ የመጡ ቡችላ ቁማርተኞች ስብክት ነው፡፡ አመሰግናለሁ፡፡

 

ሰኔ ሁለት ሺ አስራ አራት ዓ.ም.

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share