ከቅድመ አክሱም እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ በየትኛውም የኢትዮጵያ አስተዳደራዊ ታሪክ ውስጥ ወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት የበጌምድር እንጅ የትግሬ ግዛት አልነበሩም፡፡ ለሁለቱ ሕዝቦች ተከዜ ተፈጥሯዊ ድንበር ነው፡፡
ወያኔ ተከዜን ተሻግሮ ወልቃይት ላይ የፈፀመው ወረራ በሁለት መሰረታዊ ምክንቶች ነው፡-
1ኛ. በወያኔ ለታለመችው የ “ታላቋ ትግራይ ሪፐብሊክ” የምግብ ዋስትና የሚያረጋግጥ
ለም መሬት በመፈለግ፤
2ኛ. ለወደፊቷ በ“ሀገርነት” ለታጨችው ለ “ታላቋ ትግራይ” ከቀሪው ዓለም ጋር
የየብስ የመውጫና የመግቢያ ስትራቴጂያዊ በር ለማግኘት በመፈለግ የተፈጸመ
ወረራ ነው፡፡
በዚህ ጽሁፍ የወልቃይትን ጉዳይ ከተከዜ-አጥባራ ፖለቲካና ከቀይ ባህር ጂኦ-ፖለቲካ ጋር አስተሳስረን እንመለከታለን፡፡ እግረ-መንገዳችንንም ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ጂኦ-ፖለቲክስ ተዋናይ መሆን ስለምትችልባቸው ስትራቴጂዊ ጉዳዮች ምክረ-ሀሳቦችን እናቀርባለን፡፡ ይህን የሚሰማ ‹መንግሥት› ከጠፋም እንደአማራ እንዴት መቆም እንዳለብን በሦስት መስመር የትግል አደራችንን እናሰፍራለን፡፡
መልካም ንባብ…!
ከጂኦ-ፖለቲካል ጠቃሜታ አኳያ በቀይ ባህር ላይ የሚገኘው ‹ባብ ኤል መንዳብ› አልያም የ‹ሀርመዝ› የባህር ወሽመጥ ለኃያላኑ ሀገራት ያለውን ትርጉም ያህል ወልቃይት ለእኛ ለአማሮች ብቻ ሳይሆን ለመላ ኢትዮጵያዊያንም የላቀ ዋጋ አለው፡፡ ቃብቲያ ላይ ያለው ‹ፓርክ›፣ ፓርክ ብቻ አይደለም፤ ከብዝሃ ህይወት ሀብቱ ባለፈ ከሽሬም ይሁን ከሽራሮ የሚነሳን ተስፋፊ ኃይል ገድበን የምንይዝበት መስመር ነው።
ወልቃይት በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጡ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ኤርትራ የሚገናኙበት ቦታ ነው:: አካባቢው በቀጠናዊ ፖለቲካ እጅግ ወሳኝና ጠቃሚ (Geo-Strategically Vital) አካባቢ ነው። ከምፅዋና ፖርት ሱዳን ጋር በቀላሉ እንድንገናኝ ማድረግ የሚያስችለን ይህ አካባቢ ፀጋው ተቆጥሮ አያልቅም። ለምና ሰፋፊ እርሻ ቦታዎች ያሉበት ይህ አካባቢ፣ ከሰብል ምርት ባሻገር ከፍተኛ የማእድን ክምችት አለው።
ወልቃይት-ጠገዴ በሦስት የአየር ጠባይ የሚከፈል ሲሆን፤ ቆላማው አከባቢው 75% ይሸፍናል። እንዲሁም ወይናደጋ 15% እና ደጋ 10% የአካባቢውን የአየር ጠባይ ይሸፍናል። የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ይፋዊ ባልሆነ ጥናቱ አጠቃላይ የወልቃይት ጠገዴን የመሬት ሰፋት በሄክታር 1,380,127.84 ያደርሰዋል።
**
ወልቃይት ጠገዴ አመት ሙሉ የሚፈሱ ትላልቅ ወንዞች ባለቤት ነው። ወልቃይት ጠገዴን ከትግራይ በግልፅ የሚለየውና ተፈጥሯዊ ደንብር የሆነው ተከዜ ወንዝ አመቱን በሙሉ የሚፈስና ከኢትዮጵያ ታላላቅ ወንዞች መካከል አንዱ ነው። ከተከዜ በተጨማሪ ሩዋሳ፣ ባህረ ሰላም፣ ካዛ፣ ቃሌማ እና ሞኮዞ የሚባሉ አመት ሙሉ የማፈሱ ወንዞች ይገኙበት።
በቃብቲያ ብሔራዊ ፓርክ የሚገኙት 42 አይነት አጥቢ፣ 163 የወፎች ዝርያዎች፣ 9 ተሳቢ እንሰሳት፣ ያልተጠኑ የተለያዩ የአሳ ዝርያዎች እና ከ400 በላይ ዝሆኖች ይኖሩበታል። ዝርያቸው የተለያዩ አንበሳና ነበርም በፓርኩ ውስጥ ይገኛሉ፡፡
የወልቃይት ጠገዴ መሬት ለእርሻ በጣም አመቺ ስለሆነ የተለያዩ አዝርእቶች በአካባቢው ይበቅላሉ። እንደነ ሰሊጥ ጥጥ፣ እጣን ለውጭ አገር ኤክስፖርት በማድረግ ለሀገር ኢኮኖሚ ማደግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው። ወርቅ፣ ኦፓል፣ የድንጋይ ከሰል፣… ሌሎች ማዕድናትም በአካባቢው ይገኛሉ።
***
ዋጋየ ለገሰ በፍትሕ መጽሔት የተከዜ ፖለቲካን ባስመለከት ባስነበበን አንደኛው ዝነኛ ትንታኔው ላይ በጥቁር አፈር የበለጸገውን ወልቃይት-ጠገዴን በአለም ካርታ መሰል ሀብት በሌሎች ሀገራ በቀላሉ ፈልጎ ማግኘት የሚቻል አይደለም ሲል ይገልፀዋል። “ይህ ቦታ የአፍሪካን የግብርና ታሪክ የቀየረ” እንደሆነ በውጭ ጸሐፍት ሳይቀር ተመስክሮለታል፡፡ ይህ መረጃ ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት የቦስተን ዩኒቨርሲቲው ተመራማሪ James C. McCann ባቀረበው ጥናት Frontier agriculture, food supply, and conjuncture: a revolution in Dura on Ethiopia’s Mazega 1898-1930 በሚለው ጥናት ውስጥ ያገኛል።
ወልቃይት-ጠገዴ እንደሀገር የግብርና አቢዮት ማስነሳት የሚቻልበት ፖቴንሻል አካባቢ ነው፡፡ ባህር የሚሻገር ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትንቅንቅ የሚታይበት ጥቁር አልማዝ የተከማቸበት አካባቢ ነው፡፡ እስከ ቀይባህር በተዘረጋ መረብ ጸጋው ጦር ሲያማዝዝ ኑሯል፡፡
“ማዘጋ ወልቃይትና ቀፍታ ሁመራን አካልሎ፤ እስከ አቆርዳትና ከሰላ የተዘረጋ ለም መሬት ነው” እንደሆነ ይገለጻል፡፡ አብላጫው መዘጋ መሬት ግን መገኛው ወልቃይትላይ ነው፡፡ ዋጋየ ለገሰ ከፍ ሲል በጠቀስነው የተከዜ ፖለቲካ ትንታኔው ላይ፡- ከዛሬ 150 አመታት ጀምሮ በቀይ ባህርና በሜዲትራኒያን በኩል የተሻገረ ከፍተኛ የሆነ የምግብ ምርትና የጥጥ ምርት ፍላጎት ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ጫፍ ሰተት ብሎ ገብቷል ይለናል። የተከዜ አጥባራ ተፋሰስም ምቹ ማረፊያው ስለመሆኑ ይሞግታል። በዚህም ሳቢያ በርካታ ፖለቲካዊ ክስተቶች ተከናውነዋል። እየተከናወኑም ይገኛሉ የሚለን ተንታኙ፤ የሱዳን እና የኢትዮጵያ የድንበር ውዝግብና ፍጥጫም ሆነ የወያኔ የግዛት ተስፋፊነትና በላዔሰባዊ ማንነት መዘጋን ጨርሶ ከመጠቅለል ጋር የሚያያዝ ስለመሆኑ በምክንያት ይሞግታል፡፡ የ‹‹ታላቋ ትግራይ ሪፐብሊክ›› ቅዠት ዋና ምንጩ ይሄው ቀጣና ነው፡፡
የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ፖለቲካም በወልቃይት መዘጋ በኩል ሲያደባ ውሎ ያድራል፤ የግብጽ ወታደራዊ ድጋፍና ስለላ በዚህ አካባቢ ተደጋግሞ ቢታይ ላያስገርምም የሚችለው በዚህ የተነሳ ነው፡፡ አባይን መቆጣጠር አንድ ጉዳይ ሆኖ በቀጣይ በአካባቢው ከውሃ የተሻገረ የተፈጥሮ ሀብት ቅርምት ፍላጎት ብታሳይ ከፈርዖናዊያን የሚጠበቅ ነው፡፡ እንደሕዝብም ሆነ እንደሀገር መበርታት ካልቻልን በወልቃይት የሚገባ የበዛ ዓለማቀፋዊ የጥፋት ወጥመድ አለብን። ወልቃይት የአማራ በር ብቻ ሳትሆን የኢትዮጵያም ስስ ብልት ናት።
እንዳለመታደል ሆኖ የምንኖርበት ቀጣና የአደጋ ማዕከል ነው፡፡
ባለፉት ስድስት ዓመታት ብቻ (2016-2021) የተከናወኑ ዐበይት ክንውኖችን ስንመለከት፡-
ለአጭር ጊዜም ቢሆን ኢራን በኤርትራ ዳህላክ ወደብ ወታደራዊ ማረፊያ ተከራይታ የየመን ጦርነት ላይ እጇን ለማስገባት በቅርበት ተጠቅማበታለች፡፡
በጅቡቲ ወታደራዊ ማረፊያቸውን ያደረጉ ኃያላን ቁጥር በሦስት እጥፍ ጨምሯል፡፡
ሳውድ ዓረቢያ በጅቡቲ ወታደረዊ ማረፊያ ለመገንባት ስምምነት ላይ ደርሳለች፡፡
ግብጽ የቀይ ባህር ተዋሳኝና አቅራቢያ ከሆኑት ሱዳን፣ ጅቡቲ፣ ኬኒያና ዩጋንዳ ጋር የጦር ስምምነት አድርጋለች፡፡
ቱርክና ኳታር የሱዳን ጥንታዊ የሱአኪን ደሴት ወደብ ለማልማት 4 ቢሊየን ዶላር በጋር በጀተዋል፤ የመጀመሪያው ምዕራፍ 500 ሚሊየን ዶላር ወጭ ተደርጎበታል (ከወደብ ግንባታው ጎን ለጎን ሱአኪን ደሴት በሊዝ ተዛውራ፣ የቱርክ ወታደራዊ ቃኝዎች ለመጪዎቹ ዘጠና ዘጠኝ ዐመታት የሀገራቸውን ሰራዊት በቦታው ላይ እንዲሰፍር ለማድረግ ለመረጃ ቅኝትና ቅድመ-ጥናት ከከተሙ አራተኛው ክረምት እየመጣ ነው)
በሶማሊያ ማህበራዊና ሰብዓዊ ዕርዳታዎችን ተገን በማድረግ ቱርክና ኳታር የማይናቅ የጂኦ-ፖለቲካዊ ሚና በሰፊው አሳይተዋል፤ በሰሜን ምስራቅ ሞቃዲሾ በምትገኘው ‹ሆብዮ› የወደብ ግንባታና ተያያዥ የኢኮኖሚ ትብብሮች እንዲሁም ወታደራዊ ድጋፎች እያደጉ መጥተዋል፡፡
ንብረትነቱ የተባበሩት አረብ ኢሜሬት የሆነው DP World እና እህት ድርጅቶቹ በሶማሌላንድ በርበራ ወደብ (51% ይዟል፤ እዚህ ላይ ኢትዮጵያም 19% ድርሻ አላት) እንዲሁም ፑንት ላንድ ቦሳሳ ወደብን በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ በኤርትራ አሰብ ወደብ (የየመን ጦርነት ከጀመረ በኋላ) ወታደራዊ ማረፊያ ገንብቷል፡፡
የአውሮፓ ህብረት በምዕራባዊ የህንድ ውቂያኖስ የነበረውን የባህር ላይ ደህንነት ክትትል በማስፋት ለአፍሪካ ቀንድ እና ለቀይ ባህር የተሰጠውን ክፍል በማካተት በ 2018 አጋማሽ ላይ የባህር ላይ ደህንነት ስትራቴጂ የድርጊት መርሃ ግብሩን አሻሽሏል፡፡
እ.አ.አ 2018 በገልፍና አካባቢው ሀገራት ለመጀመሪያ ጊዜ ‹የቀይ ባህር ፎረም› ተመሰርቷል፡፡ በፎረሙ አባል የሆኑ ሀገራት ሳወዲ አረቢያ፣ ግብጽ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ የመንና ጆርዳን ሲሆኑ፤ ፎረሙ በሳውዲ አነሳሽነት እንደተዘጋጀ ቢነገረም ዋነኛዋ የሀሳቡ ጠንሳሽ ግብጽ እንደሆነች የውሃ ጂኦ ፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ በተለይም በፎረሙ የቀይ ባህር ሰፊ ወሰን ባለቤት የሆነችው ኤርትራ አለመካተቷና ለሃያ ዓመታት በኢትዮ-ኤርትራ መካከል የቆየው ቁርሾ በዕርቀ ሠላም ከተፈታ በኋላ የፎረሙ ምስረታ መካሄድ አጀንዳውን ከሕዳሴው ግድብ ጋር ያገናኘዋል፡፡
ከዚህ በላይ በወፍ በረር ቅኝት የተመለከትናቸው ዐበይት ክንውኖች በቀይባህር ጂኦ-ፖለቲካ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ በመፍጠር ላይ ናቸው፡፡ በፔትሮ ዶላር የታጀበው የአረብ ሀገራት ፉክክር እያደገ መጥቷል፡፡ ‹በአፍሪቃ ቀንድ ላይ ታሪካዊ ባለቤትነት አለኝ› ብላ የምታምነው ግብጽ በበኩሏ ከዓባይ ውሃ ጋር በሚያያዘው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ኢትዮጵያን በማዳከም ላይ አተኩራለች፡፡
ከሰሞኑ ግብፃዊው ጋዜጠኛ ሉጥፊ ዘካሪያ ‹‹ህወሃት ወልቃይትን እንዲይዝ ግብፅ ያደረገችው ሙከራ ከንቱ ቀርቷል።” ሲል በአረበኛ ቋንቋ የሰጠው ትንታኔ ወደአማርኛ ቋንቋ ተተደርጉሞ አንብበናል፡፡ ሉጥፊ ዘካሪያ የተባለው ይሄው ግብፃዊ ጋዜጠኛ ወልቃይት ትግራይን ከሱዳን ጋር የሚያገናኝ ብቸኛ ኮሪደር እንደሆነ በመግለጽ፣ ወልቃይትን በህወሃት ቁጥጥርና ስር እንዲሆንና በሱዳን በኩል የሚያስፈልገውን ማንኛውንም አይነት እርዳታ በማቅረብ የኢትዮጵያን መንግስት በማዳከም፣ የግድቡን ስራ በማስተጓጎል ያደረግነው ሙከራ ሁሉ ሳይሳካልን በከንቱ ቀርቷል ሲል የገዛ ሀገሩን (ግብፅ) ሴራ አጋልጧል፡፡
ግብፅ፣ ይሆንልኛል ይሳካልኛል ብላ የሄደችባቸው መንገዶች ሁሉ ቀድመው ተዘግተው ይገኛሉ። ሀሳብ ውጥናችን ድካማችን በሙሉ ፍሬውን ይቅርና ትንሽ እንኳን የተስፋ ልምላሜ ሳናይበት በኢትዮጵያውያን አረም ተውጦ በእንጭጩ ቀርቶብናል ሲል በፀፀት የተሞላ የሀገሩን ሽንፈት አውጇል። አሁንም ቢሆን ግብፅ በዚህ ጉዳይ ላይ ጨርሳ ተስፋ ትቆርጣለች ማለት አይደለም፡፡ ጊዜና ወቅት ጠብቃ መመለሷ አይቀርም፡፡ ወያኔ ድርጅታዊ ህልውናው እስካልሰመ ድረስ የካይሮ የሳሎን ውሻ ሆኖ ማገልገሉ ይጠበቃል፡፡
በሌላ በኩል ጅቡቲ የጦር ሰፈሮችን ለኃያላኑ በማከራየት በዓመት 300 ሚሊየን ዶላር ገቢ ማግኘት ጀምራለች፡፡ አገሪቱ የጦር ሰፈር እንዲያቋቁሙ የፈቀደችላቸው ኃያላን ተጻራሪ ፍላጎት ያላቸው በመሆኑ አንዳንድ ጸሐፍት ሦስተኛው የዓለም ጦርነት የሚጀመረው በጅቡቲ ሊሆን ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ያካፍሉ ጀምረዋል፡፡
በዓለም የፖለቲካ አደባባይ ይህ ሁሉ ዐበይት ክንውን ሲታይ ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ጂኦ-ፖለቲካ ከመገለሏም በላይ በአቅራቢያዋ ወታደራዊ ማረፊያ የገነቡት ኃያላን (ከቻይና በስተቀር) ቀይ ባሕር ላይ ያላቸው ፍላጎት የሚሳካው ኢትዮጵያ ስትዳከም እንደሆነ የሚያስመስል ጣልቃ ገብነት በማሳየት ላይ ናቸው፡፡
በአፍሪቃ ቀንድ ትልቁ ፈተና የጠንካራ መንግሥት አለመኖር ነው!
የሶማሊያ እንደ አገር የመቆም ሙከራ እና ተራዛሚው የአልሸባብ የሽብር ጥቃት፣ የደቡብ ሱዳን እንደ አገር የመቆም ፈተናዎች መብዛት፣ የሱዳን ውስጣዊ የፖለቲካ ቀውስ እየተባባሰ መሄዱ እና ለውጪ ጣልቃ-ገብነት ተጋላጭነቱ መጨመሩ፣ ውሎ ያደረው የሱዳን እና የደቡብ ሱዳን በ‹‹አቢዬ›› ግዛት የይገባኛል ፍጥጫ እንደቀጠለ መሆኑ፣ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በሱዳን መደፈር እና ኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶቿ እጃቸውን ባስገቡበት የህልውና ጦርነት መታመሷ፣ ኤርትራ በተዳከመ ኢኮኖሚ ውስጥ ከመግባቷ በላይ፤ ከሌሎች ጎረቤቶች በተለየ ሁኔታ፣ የኢትዮጵያ መፃዒ ዕጣ-ፈንታ የበዛ ተጋሪ ሆና መገኘቷ፤ እንዲሁም 7ዐ% የዓለም ነዳጅ የሚተላለፍበት የቀይ ባህር ስትራቴጅክ አካባቢ በተቀናቃኝ አገራት ፉክክር ውስጥ መውደቁ እና በሁሉም የቀጣናው አገራት መካከል የድንበር ንትርኮች መኖራቸው… ዛሬም ድረስ በአካባቢው “የወሰን ጉራማይሌ” (A Frontier mosaic) እንዲታይ አድርጓል፡፡
ይህ ደግሞ ለኮንትሮባንድ፣ ለጦር መሳሪያ፣ ለአደንዛዥ ዕጽ፣ ለሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ስደት ቀጣናውን ምቹ መረማመጃ እንዲሆን አስገድዶታል፡፡
እነዚህን ክፍተቶች ተከትሎች የአፍሪካ ቀንድ ከራሱ ምክንያቶች በዘለለ፤ የዓለም ፖለቲካል-ኢኮኖሚ ተፎካካሪ ኃይሎች የውክልና ጦርነት መፋለሚያ ሜዳ ይሆን ዘንድ ተገድዷል፡፡ ለዚህ ሁሉ ውስብስብ ችግር ሥረ-ምክንያቱ ደግሞ በቀጣናው የጠንካራ መንግሥት አለመኖር ሲሆን፤ አገራቱ ‹የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው› በሚል ብሂል ዛሬም የሚጓዙ መሆናቸው ደግሞ ሁኔታዎችን አወሳስቧቸዋል፡፡
በየዐመቱ የአገራቱን መንግሥታዊ ጥንካሬ በመመዘን ደረጃ የሚያወጣው “FUND FOR PEACE (FFP)” በFragile States Index በተከታታይ አምስት ዐመት ሪፖርቶቹ አገራቱን የፍርሰት ጠርዝ ጠቋሚ ምልክቶች ውስጥ አስገብቷቸዋል፡-
አገራት | 2017 | 2018 | 2019 | 2020 | 2021 |
ኢትዮጵያ | High Alert | Alert | Alert | Alert | Alert |
ኤርትራ | Alert | Alert | Alert | Alert | Alert |
ሶማሊያ | Very High Alert | Very High Alert | Very High Alert | Very High Alert | Very High Alert |
ጅቡቲ | High warning | High warning | High warning | High warning | High warning |
ሱዳን | Very High Alert | High Alert | High Alert | High Alert | High Alert |
ደቡብ ሱዳን | Very High Alert | Very High Alert | Very High Alert | Very High Alert | High Alert |
ምንጭ፡- FUND FOR PEACE (FFP) Annual Report 2017-2021
እንደ FFP የአምስት ዐመት ተከታታይ ሪፖርት ከሆነ፣ አገራቱ ለፍረሰት የቀረቡ ናቸው፡፡ በRobert I. Rotberg ‹‹The Failure and Collapse of Nation-States›› የሀገረ-መንግሥታት ውድቀት መለኪያዎች ከተመለከትናቸው የአፍሪቃ ቀንድ አገራት፣ ክሽፈትን የሚጋሩት ከአማካይ በላይ ሆነው ይታያሉ፡፡ በአመዛኙም በውጥረት የተሞሉ፣ በግጭት የታጠሩ፣ አደገኛ እና በተፋላሚ አንጃዎች መካከል የተካረረ ውጥረት ተስተውሎባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ሶማሊያ የመንግሥት ጦሮች ደግሞ፣ ከአንድ ወይም ከዛ በላይ ተቀናቃኝ ዐመጸኞች ጋር እየተፋለሙ ነው፡፡ የደቡብ ሱዳን ሁኔታም አስተማማኝ አይደለም፡፡ ጅቡቲ ‹የቀይ ባህር ቃፊር ነን› ባዮች ማዕከል መሆኗ የስጋት እንጂ፤ የሠላም ዋስትና የሚሆንበት ዕድል ከሰናፍጭ ቅንጣት ያነሰ ነው፡፡
በጥቅሉ፣ አሁንም በቀንዱ አገራት የሕዝብ አለመረጋጋቶች እና የተለያየ መጠን ያላቸው የማኀበረሰብ እምቢተኝነቶችን ጨምሮ፤ በመንግሥት እና መንግሥት ውስጥ ባሉ ቡድኖች ላይ ያነጣጠረ ሰፊ ተቃውሞዎች አሉ፡፡ በዚህ ረገድ ሱዳን፣ ሱማሊያ እና ኢትዮጵያ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ከፍተኛ በሆነ የወጣት ቁጥር ንረት (Youth bulge) የተወጠረው የአፍሪቃ ቀንድ፣ አገራቱ ጠንካራ መንግሥት የሌላቸው መሆኑ፣ ወጣቶችን ከግጭት እስከ ስደት የቀውስ ማረፊያ አድርጓቸዋል፡፡ አገራቱንም ክሽፈት የታሪካቸው አካል እንዲሆን አስገድዷቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳንን ለመሰሉት፣ ይህ ትኩስ ኃይል በማንኛውም መልኩ (በዘውግ፣ በሃይማኖት-አክራሪነት…) ለሚነሱ ግጭቶች ማገዶ ሲሆን ታዝበናል፡፡
ሌላው ነገር ደግሞ፣ በእነዚህ አገራት ከዐምዳዊ (Vertical) የግጭት መስመር አልፎ፤ የጎንዮሻዊ (Horizontal) ግጭቶችም መስተዋሉ ነው፡፡ በርግጥም የጠንካራ መንግሥት አለመኖር ፈተና ለሆነበት የአፍሪቃ ቀንድ፣ ወጣቶች በተለያዩ ቡድኖች ላይ በሚያሳድሩት ቅሬታና ቁጣ ለግጭት ቅርብ የመሆን ዕድላቸው ከፍተኛ ሆኖ ይታያል፡፡ ከዚህ የሚነሱ ፈተናዎች፣ ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በተቃርኖ የተሞላ ፍላጎትና ከተወሰኑ የምዕራቡ ዓለም ሀገራት ጫና ጋር ተደምረው፣ የወልቃይትን ጉዳይ ይበልጥ እያወሳሰቡት ይገኛል፡፡
እንደመፍትሔ ኢትዮጵያ የቀይ-ባህር ፖለቲካ ተዋናይ ሆና መገኘት አለባት!
የቀይ ባህር፣ ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች
የአካባቢውን ሠላምና ደህንነት በተመለከተ፡-
- የጋራደህንነት ቃል-ኪዳን (Collective Security) ጦር ማደራጀት ለቀጣናዊ ህብረቱና ለቀይ ባሕር ጅኦ-ፖለቲካ እግር መትከያ አንዱ ስትራቴጅ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የቀደመ የሀሳብ ስምምነት ያላቸው ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ሱማሊያ በባህር እና በየብስ የጋራ ጦር የማደራጀቱን ተነሳሽነት ቢወስዱ፣ የገልፍም ሆነ የምዕራቡ አገራት ተላላኪ መንግሥት የማቋቋም ሴራቸውን ለማምከን የሚችሉበትን ዐቅም እንዲፈጥሩ ያግዛቸዋል፡፡
- ሌላው ቀይባሕር ከኤርትራ ወሳኝነት ጋር መያያዙ ነው፡፡ በባሕሩ፣ ከሰሜን ወደ ደቡብ አንድ ሺሕ ኪ.ሜ የሚሸፍን ድርሻ ያላት ኤርትራ፣ የባሕር ላይ ደህንነት ሚናዋን ከፍ ያደርገዋል። በዚህም፣ ከዐረቡ ዓለም በቀይ ባሕር በኩል ለሀማስ የጦር መሳሪያ እንዳይደርስ በማገድ ከእስራኤል ጋር ሰፊ የትብብር ዐቅም መፍጠር ትችላለች፡፡ በተመሳሳይ ሶማሊያ የባሕር ላይ ውንብድና እና የሽብር ተስፋፊነት ቀዳሚ የስጋት በር መሆኗ፣ የጋራ ደህንነት ቃል-ኪዳኑ አንጻራዊ ዓለም ዐቀፋዊ ድጋፍ የማግኘት ዕድሉ እንዲጨምር ገፊ-ምክንያት ይሆናል፡፡
- ይህ ዐቅም ኢትዮጵያ፣ በአገር ውስጥም ሆነ በቀጣናው እንደ ስትራቴጅ በያዘችው የፀረ-ሽብር እና አክራሪነት ትግል፣ ከየብስ እስከ ባህር ኃይል ለማደራጀት አመችነትን ይፈጥራል፡፡ ሽብርተኝነትን ብቻ ሳይሆን፤ አክራሪነትን በመዋጋት በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ደረጃ ኤምሬቶች ስትራቴጅክ አጋር ናቸው፡፡ በተግባር እንደሚታየው ኤምሬቶችበቀንዱ ላይ ያላቸው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፡- የፀረ-ሽብር ዘመቻ፣ ንግድ፣ ቱሪዝም እና የሺአ እስልምና መሰባሰቢያ የሆነችው ኢራን በአካባቢው አገራት ተጽዕኖ እንዳይኖራት በማድረግ ላይ ያተኩራል፡፡ ከፀረ-ሽብር ዘመቻው እኩል በፀረ-እስላማዊ ወንድማማቾች ሚና ላይ ጉልህ ድርሻ ያላቸው መሆኑ፣ በአክራሪነት ትግል ዙሪያ ስትራቴጂያዊ አጋር ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ፣ ሽብርተኝነት እና አክራሪነት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው ለሆኑ አገራት በመልካም ጎኑ የሚታይ ነው፡፡
ከላይ በገች ሁኔታዎች የተመለከትናቸውን የተጽዕኖ ምክንያቶችን የመቀነሻ መንገድ አድርጎ መጠቀምም ይቻላል፡፡
የፖለቲካና ዓለም ዐቀፍ ጉዳዮች፡-
- ኢትዮጵያሶማሊያን በተመለከተ ስትከተለው የቆየችው (ቢያንስ በፖሊሲ ደረጃ) በሶማሊያ ከሠላምና መረጋጋት በዘለለ፤ ዴሞክራሲያዊ ሥርዐት እንዲሰፍን ማገዝ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በገቢር ወያኔ ያወሳሰባቸው ጉዳዮች እንደተጠበቁ ሁኖ፣ አሁን ባለው ሁኔታ ግን፣ የተረጋጉ የሶማሊያ አካባቢዎችን (ሶማሌ ላንድ እና ፑንት ላንድ ጨምሮ) በዚያው እንዲቀጥሉ ከማድረግ የተሻለ አማራጭ ያለ አይመስልም፡፡ ከአካባቢው ሊነሱ የሚችሉ ጥቃቶችን ለመከላከል ዐቅምን ከማሳደግ አኳያ፣ የጋራ ቃል-ኪዳኑ መፍትሔ ቢሆንም ቅሉ፤ ሁለቱ ራስ ገዞች ላይ የሚያዘው ፖለቲካዊ አቋም ጥንቃቄን ይጠይቃል፡፡
- የምስራቅ አፍሪቃ አገራት የልማት እና የፖለቲካ ተቋም የሆነውን ኢጋድን እና የአፍሪቃ ሕብረት ሚናን ማሳደግም ሌላኛው መንገድ ነው፡፡ በተለይ ኢጋድ፣ ከዐረብ ሊግ እና ከምስራቅ አፍሪቃ ማኀበረሰብ (East African Community) ጋር በመተባበር የሠላምና ደህንነት፣ የባህር ላይ ፀጥታ፣ የንግድና አካባቢያዊ ትስስር አጀንዳዎችን በጋራ መቅረጽ፣ መድረኮችን ማዘጋጀት፣ ለተፈፃሚነቱ አገራቱን ማስተባበርና ተቋማዊ ወዳጅነትን ማሳደግ ወሳኝ ተግባሩ እንዲሆን ይመከራል፡፡ በርግጥ ኢጋድ በቀደመ ድርጊቱ የትሕነግ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሆኖ ያገለግል ከመሆኑ ጋር በተያያዘ፤ እንዲሁም ጅቡቲ እና ኤርትራ ያለባቸው ቅራኔ ባለመፈታቱ፣ ኤርትራ በቅርቡ ወደ ኢጋድ የመመለስ ዕድሏ ጠባብ ይመስላል፡፡ ይህም ሆኖ፣ ባለብዙ መድረኮች መፈጠራቸው ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ጥቅሟን ለማስከበር ያግዛታል፡፡
- የአውሮፓሕብረት አባል አገራት በቀዳሚነት ይህን አካባቢ የሚመለከቱት ከስደት ጋር በተያያዘ ነው፡፡ የትኛውም ግጭት የሚያስደነግጣቸው በሚያስከትለው እልቂት ሳይሆን፤ ወደ አውሮፓ ሊጎርፍ የሚችለው ፍልሰተኛ መጠን ነው፡፡ ኢትዮጵያም ከሕብረቱ ጋር ካደረገችው ስድስቱ የትብብር መስኮች አንዱ፣ ፍልሰትን መከላከል መሆኑን ይጠቀሳል፡፡ ስለዚህም፣ ተደማጭነቷን ለማሳደግ ሕገ-ወጥ የሰው ዝውውር ላይ ጠበቅ ያለ ሕግ መከተሉ ዋጋዋን ያስወድደዋል፡፡ በግዛቷ የሚገኙ የስደተኞችን ካምፕ ቁጥርንም መጨመር፣ የሕብረቱ አባል አገራት ለኢትዮጵያ ሠላምና መረጋጋት የሚኖራቸው አስተዋጽኦ፣ ከራሳቸው ፍላጎት አኳያ እንዲቃኙት ያስገድዳቸዋል፡፡
- የቀይባሕር ጂኦ-ፖለቲካዊ ሁኔታና የትብብር መማክርት ምስረታን እውን በማድረግ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የቀይ ባሕርን ጉዳይ የሚከታተል ንዑስ ኮሚቴ ማደረጀቱ አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ከምንም በላይ በፖለቲካ ተፎካካሪዎች ዘንድ በብሔራዊ ጥቅሞች ላይ መግባባትን መፍጠር አስፈላጊ ነው፡፡
የኢኮኖሚ ትስስር፡-
- የቀጣናውን አገራትሊያስተባብራቸው ከሚችሉ ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ውስጥ ዋነኛው ኢኮኖሚ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከተለመደው የድንበር ንግድ ባለፈ፤ ለቀጣናው አገራት የኢንቨስትመንት ባንክ ማደራጀት፡- ውህደቱን ለማሳለጥ፣ ዐዳዲስና ዐቅም ያላቸው ቀጣናዊ ባለሀብቶችን ለማፍራት ይረዳል፡፡ ለስኬቱም ኢትዮጵያ ትልቁን ሚና መጫወት የሚጠበቅባት በመሆኑ፤ ዐዲሱ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ይህንን የተመለከተ ተልዕኮ ይኖረው ዘንድ ይመከራል፡፡
የውሉ ማሰሪያ
የወያኔን እጅ ብቻ ሳይሆን አንገት መቁረጥ!
ያለፉት ሦስት ዐሥርታቷ ኢትዮጵያ፣ ውስጣዊ አንድነቷ የሟሟና የመለያየት ዝግመት የተስተናገደባት ብትሆንም፤ በቀጠናው ወሳኝ ኃይል መስላ የታየችበት ነበር፡፡ በዚህ ላይ፣ ቀጠናዊ ሚናዋ እና አስፈላጊነቷ፣ ከአገር ወደ አንድ ቡድን የወረደበት ነው፡፡ ይህም፣ ትሕነግ፣ የአገሪቱን ቀጠናዊ ሚና በራሱ ጠቅላይነት ላይ ለማንጠልጠል አብዝቶ ያሴረው፣ በቀጣይም ብቸኛው የአካባቢውም ሆነ የኢትዮጵያ አዳኝ ኃይል መስሎ ለኃያላኑ አገራት ለመታየትና በእነሱ ድጋፍ ለተራዛሚ ዐመታት በበላይነት ሥልጣኑ ለመኖር ከነበረው ከንቱ ሕልም ጋር ይያያዛል፡፡
የሆነው ሆኖ፣ በአፍሪካ ቀንድ እና ቀይ ባሕር ቀጠና የኃያላኑ አጋር መስሎ የታየው የትግራዩ ስብስብ፤ በዚያው ልክ ለቀጠናው እረፍት ማጣት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በዚህ ቡድን የሥልጣን ዘመን አካባቢው እጅግ በተለየ መልኩ መጥፎ ስዕል የያዘ ክፍለ ዓለም ስለመሆኑም ምሁራኑ ይሞግታሉ፡፡
M.Mohamed Abshir እ.ኤ.አ በሚያዚያ 20/2021 “Ethiopia, Eritrea, Somalia, Djibouti: The constant instability in the Horn of Africa” በሚል ርዕስ ባስነበበው ቀጠናዊ ዳሰሳ፣ ያለፉት 30 ዐመት ለአፍሪካ ቀንድ አስከፊ ስለመሆናቸው አውስቷል፡፡ መረጋጋት የራቀው እና ተለዋዋጭ ማኀበረ-ፖለቲካ የተከሰተበት እንደነበረም ጠቅሷል፡፡ በአፍሪካ ቀንድ የታየውን ያህል የሰላም አስከባሪ ሠራዊት ስምሪት፣ በየትኛውም የዓለም ክፍል አልታየም፡፡ የቀጠናው ተፈናቃዮችም ቁጥር፣ ከየትኛውም የዐለማችን አካባቢ የላቀ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
በዚህ የቀጠናው ሂደት ውስጥ ዓለም በልኩ ያልተመለከተው ዋንኛው ነጥብ፣ የአብዛኛዎቹ ቀውሶች ጠማቂ ትሕነግ መሆኑን ነው፡፡ ለሁለት ዐመት ከኤርትራ ጋር ያደረገው እጅግ ደም አፋሳሽ ጦርነትንም ጨምሮ፤ በሶማሊያ የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረትን ለመዋጋት ሠራዊት ባዘመተበት ወቅት፣ ስምሪቱን ለቡድናዊ ጥቅመኝነት (በተለይ ለጦር መሳሪያ ዝውውር) በማዋሉ፣ ከቀጠናው ሰላም ይልቅ፤ ለቀውሱና አለመረጋጋቱ የአንበሳውን ድርሻ እንዲይዝ ያደርገዋል፡፡
M.Mohamed Abshir (2021) ‹‹የአፍሪካ ቀንድ ትልቁ ፈተና ከውስጥ የሚመነጭ ነው›› ይላል፡፡ ቀጠናውን በአጭር ሲገልጸው ‹‹ከራሱ ጋር ጦርነት የከፈተ›› በሚል ነው፡፡ ከብሔርና ጎሳ ብጥብጦች እስከ ታሪካዊ ቅራኔ አጀንዳዎች ቀጠናውን እያመሱት ይገኛሉ፡፡ በዚህ ውስጥ ተፈልጎ የማይጠፋው ደግሞ፣ የትግራዩ ግራ-ዘመም ማርክሲስት እና አሸባሪው ትሕነግ ነው፡፡ ለዚህም ነው፣ ፀሐፊው ‹‹የውስጣዊውን ሁኔታ ከእነ ዐውዱ የሚረዱት ራሳቸው ናቸውና፤ መፍትሔው ከውስጥ ሊመነጭ ይገባል›› ሲል ምክረ-ሀሳቡን የለገሰው፡፡
እኛም እንላለን፡- ያለፉት ሠላሳ ዐመት የቀጠናው ቀውስ ያበቃ ዘንድ፣ ሌሎችን መበጥበጥና ማሳነስ የበላይነቱና የተፈላጊነቱ መሠረት አድርጎ የሚመለከተው ትሕነግ፣ ከቀጠናው ሊወገድ የግድ ነው፡፡ መፍትሔው ከውስጥ እንዲመጣም፣ ውስጥ ያሉ ሕዝቦች እና አገራት ሊደመጡ ይገባል፡፡
በመጨረሻም፣ በትሕነግ ገላጋይነት የኖሩ መንግሥታት ፊት-ለፊት ለመተያየት ዕድል ማግኘት ጀምረዋል፡፡ አንድም ለ20 ዐመታት ከኤርትራ ጋር የዘለቀው ቅራኔ፣ ወደፊትም የሚቀጥል የቀጠናው ስጋት ነው፡፡ ሁለትም በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሕልውናው ያበቃ እና በሕዝቦች መካከል ደም-አፋሳሽ ጦርነት በመክፈት፣ የቀጠናውን ቀጣይ አለመረጋጋት ያራዘመ የግጭት ስጋት ደቅኗል፡፡ ከአዲስ አበባ እስከ አስመራ፣ ከጁባ እስከ ሞቃዲሾ የዚህ ኃይል መወገድ ‹የሰላማችን መንገድ ነው› እያሉ መሆኑም ምክንያታዊ ነው፡፡
ከዐሥር ዐመት በፊት፣ በትሕነግ ‹የእንደምስሳችኋለን› ማስጠንቀቂያ ዙሪያ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ፡-
‹‹እነሱ ማድረግ የሚችሉትን እያደረጉ ነው፡፡ እኛን ለማጥፋት አንዴ ሱዳን፣ አንዴ የመን፣ ጅብቲ እና ኢጋድ፣… ላይ ታች እያሉ ነው፡፡ እኛ ደግሞ እየተጓዝን ነው፡፡ እኛ እና እነሱ በተራዘመ ጊዜ፣ በረጅሙ መንገድ ላይ እዛው እንገናኝ ነው መልሴ›› ሲሉ መመለሳቸው፣ ከወቅታዊው ሁኔታ ጋር ተደምሮ ሲታወስ ለትንቢት የቀረበ ነው።
ዛሬ ፕሬዝደንት ኢሳያስ እንዳሉት እየሆነ ይመስላልና፡፡ ይህን ትንቢት የሚቀለብሰው ግን ዐቢይ አህመድ ኤርትራን የካደ ቀን ነው፡፡ አደገኛ ምልክቶችን እያየን ነውና ዐቢይ ኤርትራን ቢክድ ፈቅዶ የሚከተለው ኢትዮጵያዊ በዋናነት አንድም አማራ አይኖርም፡፡ ‹እንኳንም ዘንቦብሽ እንዴውም ጤዛ ነሽ› እንዲሉ ዐቢይ አህመድ በኢትዮጵያ በዋናነት በአማራ ሕዝብ የገጠመው የቅቡልነት ቀውስ በኤርትራ ክህደት ማግስት ከወንበሩ መነቀያ ምክንያት እንደሚሆንበት አያጠራጥርም፡፡
በመጨረሻም፣ ‹ጦርነቶች ሁሉ ሠላም ያመጣሉ› ማለት ባይቻልም፤ የወያኔ መቃብር መውረድ ግን፣ ከኢትዮጵያም በዘለለ፤ የቀጠናውን በጎ ዕድል ያለጥርጥር ያሰፋዋል፡፡
ወልቃይት ‹አማራነት በክብር ሊገለጽ ወይም አማራነት ዕዳ ሊሆን በምርጫ የቀረበበት ምድር› መሆኑን እንደአማራ መገንዘብ የግድ ይላል፡፡ ታሪክ ትልቅ ነገር ነው፤ ክብር መሠረታዊ ጉዳይ ነው፤ ህልውና መተኪያ የለውም፡፡ ስለሆነም ለታሪካችን፣ ለክብራችንን እና ከሁሉም በላይ ለህልውናችን ሁልጊዜም ዝግጁ ሆነን መገኘት ይጠበቅብናል፡፡ ከሌሎች አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ጋር ተባብረን የኢትዮጵያን ህልውና ለማስከር ሁልጊዜም ዝግጁዎች መሆን ይገባናል፡፡
እንደአማራ
~ ፈጽሞ አንዘናጋ!
~ ጠላቶቻችን ምን ያህል እንደሚጠሉን እና ሊያወርዱን እንደሚፈልጉ እንወቅ!!
~እንንቃ፣ እንደራጅ፣ እንታጠቅ!!!