March 17, 2014
23 mins read

የታሪክ ጥናት አብነት -የታሪክ ትምህርት ተግዳሮት

(በካሣሁን ዓለም-አየሁ )
ታሪክ ማጥናት አያሌ ጠቀሜታዎች አሉት ።ታሪክን የምናጠናው በተለያዩ ምክንያቶች ነው ።ለታሪክ ማጥናት የመጀመሪያው አስባብ የአእምሮን እድገት ለመለኮስ ግልጋሎት መዋሉ ነው ።ታሪክ ማዕምራዊ ብስለትን ያነቃል።ሁለተኛው ምክንያት ደሞ፣ ለመልካም ዜግነት መሰረት መጣል ነው ።ሶስትም፣ ምግባራዊ ግዴታዎችን ለመፈፀም በብርቱ ያግዛል።በአራተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው የታሪክ ጥናት ዞግ ታሪክ ባህልን ለመገንዘብ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ነው።በመጨረሻም፣ ታሪክ ለዉጥን ለማገናዘብ አስፈላጊነቱ መጉላቱ ።
አሜሪካዊው የታሪክ ምሁር ዋልተር ማክዱጋል ታሪክን መረዳት ለምን እንደሚጠቅም ባስተነተነበት የምርምር ወረቀት ላይ፣ ሶስት አበይት ምክንያቶችን እንደመደምደሚያ አቅርቧል ፣እንዲህም ይነበባል ። ” የታሪክ ትምህርት የአንድን ሀገር ህዝብ አእምሮአዊ እድገት የሚያነቃቃ፣አስፈላጊ የሆነዉን የዜግነት ድርሻ ለመትግበር የሚያተጋ እና ስነ-ምግባራዊ አገልግሎት እንዲወጡ የሚያዘጋጅ ግዙፍ መሳሪያ ነው ።” ታሪክ የወጣቶችን ሕሊና በምክንያት እንዲመራ የሚገራ ፣የሰው ልጆችን ህይወትና አኗኗር ጥልቀት፣ስፋት፣ክብረት(ሪችነስ) ለማድነቅ የሚያስችል ፣ስለ ሰው ልጅ አሳዛኝ የኑሮ መዋዕል የሚያስገነዝብም ትዉስታ የሚያድል ኃይል ነው።የታሪክ እዉቀት በሌሎችም ስነ- እውቀታት(ዲስፕሊንስ) ለምሳሌ ስነፅሁፍ፣ስነ -ልሳን፣ ስነ-ፍጥረት(ሳይንስ ) ፣ነገረ- መለኮት(ትዎሎጂ ) ፣ስነ- ሰብ(አንትሮፖሎጂ )፣ስነ-ሕብረተ ሰብ(ሶስዮሎጂ ) ፣ስነ -ቅሪት ቁፋሮ(አርኬዎሎጂ )፣ፍልስፍና፣ስነ -ህንፃ(አርኪቴክቸር) ወዘተ መሰረት የሚሆን የሚጣጣም አውድ እንደሚፈጥር ለግንዛቤ ከበቃ ሰንበትበት ብሏል ።ታሪክ የማንኛዉም ዘርፈ- ትምህርት ማዕምራዊ ግብዓት፣የአስተምህሮዎች መሰረት መሆኑን በምርምር የተራቀቁ በሰሎች በአፍም በመፅሃፍም ሲያውጁ ነው ዘመናት የተቆጠሩት ።
አሜሪካዊው የስነ- ትምህርት ተጠባቢ ሊኔ ማንሰንም በበኩሉ ስለ ታሪክ እዉቀት ፋይዳ ሲናገር ፣ “ታሪክ ስላለፉት ሁነቶችና ሰብእናዎች እርባና በማስተማር፣ ከራሳችን ህይወትና አኗኗር ጋር በማዛመድ አስተያይተን ይዞታችንን የምናበለፅግበትን መንገድ ለመቀየስ ያግዛል።ሰዎች በሃላፊው ዘመን የሰሩትን የፈፀሙትን በማወቅ ፣የራሳችንን አኗኗር በሰፊ ማዕቀፍ ዉስጥ እያስተዋልን በመመጪ ዘመን ማድረግ የምንችለዉን እንድንተልም የሚያበቃ የጥበብ አቅል ያድለናል።”ብሎ ያሰምርበታል ።ማንሰን ለትንታኔው ማሳረጊያ ያደረገው አረፍተ -ነገር እጅጉን ቀልብ የሚስብ ነበር ፣ ” ካለ ታሪክ እዉቀት ፣ አለምህ በጣም ትንሽ ናት። ” ያለው የብዙሃኑን ትኩረት ማርኩዋል ።ይህም የታሪክን ትምህርት ሁለንተናዊ ረብ ፣ታሪክ መማር ማጥናት የሚኖረዉን ታላቅ ቁብ ለፅድቅ የሚያበቃ ሆኖ እናገኘዋለን ።

የታሪክ ትምህርት አቀናቃኞች የታሪክን ስነ-ዜጋዊና ምግባራዊ አገልግሎት በተመለከተ እንዳብራሩት ከሆነ፣ የታሪክ ትምህርት ምናልባትም ከማንኛዉም የትምህርት ዘርፍ በበለጠና በላቀ ሁኔታ፣ ሰዎች እንዴት ኃላፊነት የሚሰማቸው ሆነው እንደሚቀረፁ፣እንደምን በህብረተሰቡ ዉስጥ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ ዜጎች ሆነው እንደሚታነፁ ያስተምራል።ለዚህ ነው እውቁ የታሪክ ተመራማሪ ማክዱጋል ታሪክ “በዘመናዊ ስርዓተ – ትምህርት ዉስጥ ያለ/የሚገኝ ሃይማኖት ” ነው እስከማለት ርቆ የሄደው ።

ለግላጋዎቹ ወሬዛዎች በሚኖሩበት ሀገር የተገነቡትን እሴቶች ሲማሩ፣ሁነኛ አምሳሎችን (አይድያልስ) ለመጠበቅና ለማስከበር የተደረጉትን ጦርነቶች ሲረዱ ፣የተለያዩ መሪዎችን ድል አድራጊነትና ሽንፈት ሲያጠኑ የራሳቸው ህብረተሰብ እንዴት እንደተበጀና መልክ እንዳበጀ እንዲሁም የነሱ ሚና በዚህ ዉስጥ ምን እንደሆነ በተሻለ መንገድ ደህና አድርገው ይረዳሉ ፣ይገነዘባሉ ።
የታሪክን እውቀት ግንዛቤ መታጠቅ ፣የታሪክን ውል ማስተዋል ማጥበቅ ወጣቶች ያለፉትን ግለሰቦችና ህብረተሰቦች አሳዛኝ ስህተት የሚማሩበትን አጋጣሚ ሁኔታ ሲያዘጋጅላቸው ፣ተመሳሳይ ስህተቶች እንደገና እንዳይሰሩና እንዳይከሰቱ የሚከላከሉበትን አመቺ ምህዳር ያደላድልላቸዋል።
ከዚህም ባሻገር የታሪክ ግንዛቤ ፣ወጣቶች ከቀደሙት ታላላቅ ሰዎች ዉሎ መንፈስ ተምሳሌት ተዉሰው ትላልቅ ህልሞች እንዲያልሙ ያነቃቃል።ባለፉት ግዙፍ ሰብናዎች ገድል አርአያነት ተገርተውና ተቃኝተው በሕይወታቸው ዉስጥ ድንቅና እፁብ ነገሮችን እንዲከዉኑ ዉስጣዊ ኃይል ለማፍለቅ ያበቃል ያጠረቃል ። የታሪክ ምርምር ሊቁ ማንሰን አክሎም ሲያትት ፣” ወደአለም የሚወስዳቸዉን የሚያደርሳቸውን አስፈላጊ እዉቀት የሚቸራቸው የሊበራል አርቶች እዉቀት ነው ።እናም ታሪክን ማጥናት የብልህ ምርጫ ነው ።” ሲል የታሪክን ትምህርት ንዑድነት ያደመቀበት ቀለም በእማኝነት የፀደቀ ብሂልነትን ተክኖ ዘልቁዋል።
በዚህ ፀሐፊ አገማገም፣ የታሪክ ጥናት ባህልንም ለመረዳት ያለው ጠቀሜታ እጅጉን የጎላ ነው ።የታሪክ እዉቀት ባህልን ለመመርመርና ለመተንተን በቁልፍ መሣሪያነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል ።ጠለቅ ዘለቅ ያለ ታሪካዊ ግንዛቤ ሳይጨብጡ ባህልን ለመግለፅ የሚደረግ ሙከራ “ሳያጣሩ ወሬ፣ ሳይገሉ ጎፈሬ” ይሆናል ትርፉ ።ወደሁዋላ መለስ ብለው ታሪክን ካልዳሰሱ ፣የታሪክ መዛግብትን አገላብጠው ካልከለሱ የተለያዩ ባህሎችን መገንዘብ አዳጋችም አታካችም ነው የሚሆነው ።አንድን ባህል ጠንቅቆ ለማወቅ ከሁሉም የሚልቀው ሁነኛ አቀራረብ ባህሉ የተመሰረትበትን ፣ባህላዊ ገፅታው የተንሰራፋበትን አካባቢ ታሪክ በማጥናት ነው ።ስለ ባህል የሚያጠኑ በሳል ተጠባቢዎች እንደሚያስተምሩን ፣ባህል አጠቃላይ(ጀነራል ) እና ልይ ወይንም ዉሱን(እስፐስፊክ ) ተብሎ የሚደለደል ሲሆን ፣ሁለቱንም ባህላዊ ምዳቤዎች በቅጡ ለመረዳት የታሪክ እዉቀት እገዛ በፍጡነ-ረድኤትነት የሚስተዋል ሆኖ ይገኛል ።ታሪክ አጠቃላዩን ሃገራዊ ባህል የምናነፅርበት ፣ልይና ዉሱን የሆነዉን ግላዊና አካባቢያዊ ክበበ-ባህል የምናስተዉልበት መነፅር ሆኖ ያገለግላል ።እንዲህም ሲሆን ፣ታሪክ ለመልካም ዜግነት እዉንታ መሰረት የሚሆነዉን የራስን ልይና ዉሱን እንዲሁም አካባቢያዊ ባህል ጠንቅቆ ለማወቅ፣ የሀገርን የመንግስትን ስርወ- ታሪክ ልብ በማለት ብሔራዊ (ናሺናል )፣ሃገረ መንግስታዊ (እስቴት )፣እና አካባቢያዊ (ሎካል) ሆነው የፀኑ ሕግጋትን ፣ወጎችን ፣ልማዶችን ፣ግዕዛትን (ኖርምስ )፣ትዉፊቶችን ወዘተ ለመተዋወቅና ለመለማመድ አመቺ ጎዳና ይጠርግልናል።
በሌላም በኩል የታሪክ ጥናት እርባና ከሚገለጥባቸው የአተያይ ዘዌዎች(አንግልስ ) አንዱ ለዉጥን ለመረዳት የሚፈይደው ፋይዳ ገሃድነት ነው ።ለውጥ ከያንዳንዱ እለት ህይወት ማህፀን ዉስጥ የሚፈለቀቅ የሕይወት ዘር ነው ። ለዉጥ የህይወትም ቅመም እንደሆነ የሚያወሱ ሃታትያን በርካታ ናቸው ።የህልዉናን ፍሰት ለማስመር ለዉጥን በቅጡ ማየት፣መመርመርና መፍትሄ መሻት ወይ መላመድ ተፈጥሮአዊ ሕግም ጭምር ነው። ” ታሪክ ራሱን ይደግማል “ሲባል ስንሰማ አድገናል።ኖረናልም ።ታሪክ ራሱን ሲደግም ለማስተዋል የታደልንም በአሀዝ እንገዝፋለን መቼም ።ታሪክን ማጥናት እንዴት ለዉጥን በአግባቡ ማጤንና መወጣት እንደሚገባን ያስተምረናል ።ለዉጥ ሲከሰት ዞር ብሎ ኃላፊዉን ጊዜ መመልከት እጅግ ብልህነት ነው።ለዉጡ በተሸኘው ዘመን የነበረዉን ሁኔታ መፈተሽ፣እኛም ሆነ በቅርብ የምናውቃቸው ወይም ታሪካቸዉን የሰማንላቸው ሰዎች፣ቡድኖችና ሰብአዊ ስብስቦች ፣ማህበረሰቦች ፣ህዝቦች ፣ሀገሮች ወዘተ እንዴት ለዉጡን በማስተናገድ ተሻግረን /ተሻግረው ማለፍ እንደቻልን/እንደቻሉ ልብ የምንልበትን አስተዉሎት ይለግሰናል።ይህንንም አስተዉሎት ለገዛ ራሳችን ህይወት አርአያ ምሳሌ አድርገን ልንገለገል እንችላለን ።ከዚህም በተጨማሪ ፣ታሪክ ለዉጥን በወርደ -ስፉህ(ላርጅ ስኬል ) መልኩ አብራርቶ ለማስተንተን አቅል ይቸራል።ለምሳሌ አንድ ሰው ለምን የኑሮ ዉድነት እንደተከሰተ ፣የኑሮ ዋጋው ንሮ ስለምን ህዝቡን በችግር እንዳባዘተ ለማወቅ ቢሻ ፣ታሪክን ዳግም በመፈተሽ የምጣኔ ሃብታዊዉን ዝቅጠትና ድቀት ገፅታ ሊቃኝ፣መንስኤዎቹንና የስፍነቱን መጠን መርምሮ ሊያገኝ አይሳነዉም።ይህም በታሪክ የተፈሸነ፣በታሪክ ተዳውሮ የተሸመነ ግኝት አሁን ባለንበት ወቅት በቃሪያ ጥፊ እሚያጮለንን ዉጥንቅር ፣እግር ከወርች ቀይዶ አላላውስ ያለልን ዉንክርክር ድንግርግር በወጉ ሊያመላክተን ይበቃል።
ከላይ ለማሳየት እንደተሞከረዉና ሁላችንም እንደምናውቀው የታሪክ ትምህርት እንደው ታሪክን ለማተት ብቻ የሚሰጥ ትምህርት አይደለም ። ታሪክ ብዙ እጅግ ብዙ ነገሮችን ያስተምረናል ።ታሪክ የትውልድን አእምሮ በማንቃት ፣የወጣቱን ሕሊና በቁም ነገር በማጠርቃት ወደ ብስለት ያሥገሰግሰዋል።እርምጃዉን ያፋጥናል ።የታሪክ እዉቀት የመልካም ዜግነት መስረት ፣የዜግነት ግዳጅን በስኬታማ መልኩ ለመወጣት የሚያስችል ፣የግንዛቤ አብነት የሚያድል ሲናዊ ክህሎት ያላብሳል።ከዚህም ተያይዞ ፣ታሪካዊ እዉቀት ያለንበትን ማህበረሰብና ሕብረተ -ሰብ ወግና እድር ፣ትውፊቶችና ግዕዛት፣ፍቁዶችና አይነኬዎች ጠንቅቀን፣ ድረ-ገብ ባህርያት አዳብረን በምግባረ -ሰናይነት ኑባሬያችንን እንድናስመሰክር ኮትኩቶ አሳዳጊያችን ነው ።ወደ ባህላዊው ዳራ ስንዘልቅም፣የታሪክ እዉቀት ባህልን በጥራት በምልዓት ለመገንዘብ አይናችንን በሚከፍትልን የብርሃን ዘሐ ይመሰላል ። ታሪክ ማጥናት በእለት ተዕለት ሕይወታችን፣በዙሪያችን በሚፈጠሩት ለዉጦች መሃል እንዴት መኖር እንደምንችል ፣እንደምን የለዉጡን ማዕበል ዋኝተን እንደምንሻገር የሚያግዘንን ኃይል ያስታጥቀናል።
ታሪክን የሸመገለው ዘመን አስታዋሽ ፣ያልሰለጠነና ሁዋላ ቀር ትዉልድ ትዝታ ቀስቃሽ ብቻ አድርጎ መመልከት በራሱ ካለመሰልጠን የሚመጣ ግድፈት ሆኖ የሚታይ ነው ። ጥበባዊ በረከት ይደርጅለትና በሳሉ ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን ፣
“የት ጋ እንደሆን ይታይ የኛ ጥበብ መሰረቱ ፣
የሁዋላው ከሌለ የለም የፊቱ ።
ሳይራመድ በታሪክ ምንጣፍ ፣
ሰው አይደርስም ከዛሬ ደጃፍ።”
ያለው የብዙዎችን ትኩረት የማረከው በዋዛ አይደለም ።ታሪክ የትላንት መሰረታችን ከዛሬ ይዞታችን ተነፃፅሮ፣ ነገያችን በተራዘመ አተያይ ታልሞ፣ ተተልሞ የሚገራበት ወደረኛ የኑባሬ ጉባኤችን ነው እኮ። ታሪክ የምንነታችን ፣የእንዴትነታችን ፣የማንነታችን የከየት ወዴት አሻራችን ነዉና ልናውቀው ልንጠብቀው ይገባል።
ታሪክ ሊከበር ይገባል ።ታሪክ ከምናብ ተፈልቅቆ ፣በግለሰባዊ የፈጠራ ግፊት ብቻ ተጨምቆ የሚነገር ተረት ፣የሚፃፍ የፈጠራ ድርሰት /ወግ አይደለም ።ወይም ቡና በአቦል ተቀድሶ በበረካ እስኪያሰልስ እርስ በርስ የሚተጋተጉበት ተረብና የነገር ጉሸማም አይሆንም ፣ከቶም ቢሆን። ታሪክ አግቦና አገም ጠቀምም አይደለም ።ያለ የነበረን የዘመን ዉሎና አዳር ፍርድ ሳያዛቡ ገልፀው ፣ግራና ቀኝ አይተው ያለአድልዎ በይነው ተንትነው ፣ለመጪው ትዉልድ ቅርስ ማስተላለፍ ነው። ታሪክን ማዛባት ፣የተወናከረ ታሪክ ማስተማር ፣ማስራጨት ማስተጋባት ያስጠይቃል ።ያጠያይቃል።ታሪክንም እንዳይማሩ መከልከል ማገድ፣የታሪክ ትምህርትን ቢጋር ከሥርዓተ ትምህርቱ ደልዞ መፋቅ ፣ከፍተኛ ትምህርት ተቁዋማት፣ዩኒቨርስቲዎች የታሪክ ትምህርት እንዳያስተምሩ በመግለጫና ሰርኩላር ማገድ ሃገርን መግደል መሆኑ ሊጤን ይገባል።ሀገራችን በአያሌ አይ-አዎዎች (ፓርዶክሥስ ) አየታመሰች ነው ።ግብርና -መር የኢንዱስትሪ እድገት ለእዉንታ የሚያበቃ የምጣኔ ሀብት ፖሊሲ መታወቂያ ዉሌ ነው ያለው መንግስት፣ ከትምህርት አይነቶች ማዕድ እርሻና ከብት እርባታዉን አካቶ የሚያቅፈዉን የግብርና ትምህርት ድራሹን ካጠፋ ሰንብቷል ።በዚህም የገበሬው ልጅ ወላጆቹን እንዳቅሙ ሊመክር የሚያስችለው አንዳች እይታ እንዳያጎለምስ ድድር ግርዶሽ ጋርዶበታል፣ትንሽም ቢሆን ምርት ማሳደጊያ ምክርና አስተያየት እንዳይሰነዝር ዕድል ነፍጎታል።የታሪክ ትምህርት ወቅታዊ ተግዳሮትም በመፃኢ እኛነታችን ላይ የሚቆልለው አስከፊ ጫና የትየለሌነቱ ካሁኑ ይታየኛል።በረከት ስምዖን ድርሰት የተለማመደበትንና ፣እስከዛሬም ፈውስ ባላገኘለት የንክነት (ንዩሮሲስ ) ሕማሙ መዳፍ ስር ተጨብጦ፣ ፍርሃትና ጭንቀት ተልትሎ በከታተፈው ፣ እብድ እንደያዘው በሶ በነፋስ ተበታትኖ በተዘራ መንፈስ የጫረዉን “የሁለት ምርጫዎች ወግ” ነው የታሪክ አባሪ የምናደርገው ?ተዋደው ተዛምደው ፣ተፋቅረው ተከባብረው የኖሩትን ህዝቦች በጎሳ ነቀርሳ ልክፍት አናቁሮ በማበላላት ፣ለኢሕአዴግ መንሰራፋት አመቺ መንገድ በክፋት ለመቀየስ፣ የሻቢያው ሰላይ ተስፋዬ ገብረአብ ህዝብን በህዝብ በማያባራ ግጭት ለማፋጀት የፃፈዉን “የቡርቃ ዝምታ” ብቻ ነው ታሪክ ብለን የምናወርሰው ?የኤርትራ ታሪክ ሟቹ መለስ ዜናዊ ደደቢት በረሃ ዉስጥ መሽጎ በፃፈው ብቻ ተወስኖ መቅረት አለበት ?የጅማ አባጅፋርን ቤተ- መዘክር ትተን ነው የአኖሌን ሃውልት የምናስጎበኘው ?መምህር ወልደኪዳን በሚያሳዝን ቅጥፈት የደጎሱትን የተንሻፈፈ ተረት ነው ለልጆቻችን አደራ የምናኖረው ? ታዋቂ ምሁራንንና ተመራማሪዎችን ያፈራው ፣በበርካታ ሺዎች የሚሰሉ አፍሪቃዊ የታሪክ ባለሙያዎችን አሰልጥኖ ወግ ማዕረግ ላለው አላማ ያደረሰው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ለመዘጋት መቃረቡ ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት ነቢይነትን አይጠይቅም ።እጅግ አሳዛኝ ሁነትነቱ ከማንም የተሰወረ አይደለም ።ሁላችንንም ሊያሳስበን ግን ይገባል። አሁን ነው ስለ ታሪክ ማሠብ ። የዛሬን ቱማታ ብቻ ሳይሆን ነገንም ቆም ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው።መንግስት በታሪክ ትምህርት ላይ የተከሰተዉን ችግር አስተዉሎ አሰብ እንዲያደርግ ጊዜው ትልቅ ጥያቄ ደቅኖበታል።እንዴት እንደሚዳኘው ከርመን እናየዋለን ።የነገ ሰው ይበለን ።

Latest from Blog

ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
Go toTop