የምዕራቡ ዓለም አስተሳሰብ ሊቀበለው የሚችል የዲፕሎማሲ ቋንቋ ምን ሊሆን እንደሚችል ማወቅ ይቸግራል። ከአሽዊዝ (Auschwitz) እልቂት በኋላ ዲሞክራሲን ለማስፈን፣ ሰብአዊ መብትን ለማስከበርና የሕግ የበላይነትን ለማስፈን በትብብር እንደሚሰሩ ቃል ገብተው ነበር። ከ85 ዓመት በኋላ ቃልኪዳናቸው ተግባራዊ ሳይሆን ጦርነትና ኢ-ሰባአዊነት የሰፈነባት፤ ሕግ አልባነት የነገሰባት የ21ኛው ክፍለ ዘመን ዓለምን አስረክበውናል። ቃላቸውን አጥፈው ዓለምን የሚቀውጡና የሚአምሱ ቀንደኛ መርጦ አልቃሾች እነርሱ ሆኑና አርፉት። በግፋበለው ፖልቲካቸው የሩስያን ትዕግስት አስጨርሶ ዩክሬን እንድትወረር ምክንያት ሆነዋል። የሩስያና ዩክሬን ጦርነት ከፍተኛ ውድመት አድርሷል፣ የንፁሐንን ሕይወት ቀስፏል፤ የዓለም ሰላምና ኢኮኖሚን አናግቷል፤ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ዩክሬናዊያንን ለስደት ዳርጓል። ይህ ሁኔታ እየተባባሰ እንደሚቀጥል ይገመታል።
እውነት ነው ለ85 ዓመታት አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ ከሰው ሰራሽ ቀውስና ጦርነቶች ነፃ ሆነው እስከ ዛሬ ዘልቀው ነበር። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ምዕራባዊያን ሰው ሰራሽ ቀውሶችንና ጦርነቶችን በድሃ ሃገራት ላይ በቀጥታና በተዛዋሪ እየፈበረኩ ግፍ ሲፈጽሙና ሲአስፈጽሙ ኖረዋል። ለዘመናት ከዳር ሆነው ሲቆሰቁሱት የነበረው እሳት ዛሬ ነበልባል ሆኖ እነርሱንም መለብለብ ሲጀምር ጩኸታቸው በረከተ።
አፍሪካን ፀረ ሰላም፤ ፀረ ዴሞክራሲ፤ ሕገ አራዊትና ጦርነት ናፋቂ እያሉ ሲሳለቁባት የነበረው ሁኔታ ከመቅጽፈት ታሪክ ሆነ። አፍሪካ የማናቸውም ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ቀውስ ምንጭ አርገው ሲኮንኗት የነበረውን ሁኔታ አፍሪካዊያን አይረሱትም። በሩዋንዳ የዘር ፍጅት፤ በሶማሊያ ቀውስ፤ በአንጎላና በኢትዮጵያ ጦርነት፤ በሱዳን የርስበርስ ፍጅት ወዘተ ያደረጉትን ውግዘት፤ የጣሉትን መአቀብ፤ የጠነሰሱትን መፈንቅለ መንግስት፤ የአሳዩትን ንቀትና ማግለል አፍሪካ አትረሳም። በፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካን ወንበር አልባ አድርገው ሲአወግዟት፤ ድምጿን በቬቶ ስልጣናቸው ሲአሽመደምዷት የኖሩትን አፍሪካ አትረሳም።
ተፈጥሮና የራሳቸው የምርምር ቤተ ሙከራ የወለደውን መቅሰፍት በአፍሪካ አሳበዋል። የኤድስ፤ ኢቦላ ወዘተ መነሻው አፊርካ እንደሆነ አርገው በመሳል አፍሪካን የስህተታቸው ማስተንፍሻ አርገዋት ኖረዋል። የሰዶሜ ስነምግባርን ዓለም አቀፍ ሕግ አርገው፤ ከእንስሳት ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነትን እንደ ተፈጥሮ ግዴታ እየሰበኩና እየፈጸሙ አፍሪካዊያንን አውሬዎችና ኋላ ቀሮች እያሉ ሲአፌዙ ብዙ ዓመት አለፈ።
የሰው ልጅ ከኮሚኒስትና ከወታደራዊ አምባገነንነት፣ ከሙስና እና ከሰብአዊ መብት ጥሰት ከሚደርስበት በደልና ሰቆቃ ለመከላከል አስገዳጅ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን ቀርፀው አፍሪካ እንድተፈርምና እንድትፈጽም አርገዋል። በአንፃሩ ያረቀቁትንና የፈረሙትን ሕግ እየተቃረኑ በአፍሪካ ላይ ያሻቸውን የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚና የፀጥታ ግፍ ይፈጽማሉ።
በአሜሪካ የሚመራው ዓለም ይህን ሕግ በወረቀት ላይ አስፍሮ ቢገኝም ተግባሩ ግን በተቃርኖ የበሸቀጠ ለመሆኑ ብዙ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል። የዴሞክራሲ መሲሐው ዓለም የመጀመሪያውን የኑክሌር ቦም በጃፓን ላይ አፈንድቶ በሰው ዘር ላይ እልቂት ፈጽሟል። አፍሪካን፤ ላቲን አሜሪካንና አስያን ቅኝ ግዛት በማድረግ ከሰው በታች አርገው ገዝተዋል፤ ንብረታቸውን ዘርፈዋል። ኢራክንና አፈጋሃኒስታንን በማንአለብኝነት ወረው አውድመዋል። ኢትዮጵያን እንደኢራክ ለማድረግ ዳር ዳር ይላሉ። ግፍቸውን እረስተው አፍሪካ ሩሲያን እንድታወግዝና ከዩክሬን ጎን ቆማ እንድትዋጋ ጥሪ ሲአቀርቡ አለማፈራቸው።
በተባበሩት መንግስታት አማካይነት ኢትዮጵያን የመሰሉ ድሃ ሃገራትን አስዘምተው ኮሪያን ከሁለት የመክፈል ሕልማቸውን እውን አርገዋል። ዛሬ ድረስ ኮሪያኖችን እርስበርስ ለማዋጋት የማይጠነስሱት ደባ የለም። የሶስተኛው ዓለም ጦርነት ከተነሳ ከኮሪያና ሊአጠፉህ ነው ተነስ፤ ታጠቅ፤ ዝመት በህብረት አውግዝ እያሉ የዓለምን ሕዝብ የሚማፀኑት።
ዓለምን ለማሳመን ሩስያ በዓለም ሕግ የተከለከሉ ክለስተር ቦምቦችን በዩክሬን ላይ በመጠቀም የጅምላ ፍጅት እየፈጠረች ነው ይላሉ። በአንፃሩ አሜሪካ እንደ ሩሲያ እና ዩክሬን ሁሉ የክላስተር ቦምብ መጠቀም የሚከለክለውን የዓለም አቅፍ ስምምነት ለመፈረም ፈቃደኛ አይደለችም። አሜሪካ በቬትናም እና ካምቦዲያ ጦርነቶች የክላስተር ቦምቦችን በተደጋጋሚ ተጠቅማለች። በ2009 ዓ.ም. ፕሬዚደንት ኦባማ የመን ውስጥ ክለስተር ቦምብ ተጠቅሟል። እ.ኤ.አ. በ2008 ተጠናቆ በ2010 ሥራ ላይ የዋለው ዓለም አቀፉ የክለስተር ቦምብ ማምረትና መጠቀምን የሚአግደው ሕግ መኖሩ እየታወቀ አሜሪካ ከየመን ጋር ለሚፋለሙት ሳውዲ አረቢያና መሰል ሃገራት የክላስተር ቦምቦችን ትሸጣለች።
ምዕራቡ ዓለም እና ጉደኛው አሜሪካ የአፊርካ ሕበረት ሃገራት በወልና በግል ሩስያን እንዲአወግዙ እና ከዩክሬን ጎን እንዲሰለፉ ኦፊሲአላዊ ጥሪ ያቀረቡበት ምስጢር ግልጽ ነው። ጥሪው ሰፊ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ አንድምታ ያለው መሆኑን አለማወቅ አፍሪካን ያስበላል። ለማንኛውም የአሜሪካ የድረሱልኝ ጥሪ የሚከተሉትን ዓላማዎች ግቡና መዳረሻው ያደረገ በማድረግ የተደረገ የዲፕሎማሲ ንግድ ይመስላል። እነዚሁም፤
- ሩስያንበጋራ ጭራቅ አስመስሎ በማወገዝ ከዓለም ማህበረሰብ መነጠልና ደጋፊ አልባ ሃገር ማድረግ፤
- ሩስያከአፍሪካ ጋር ያላትን የጠበቀ የኢኮኖሚ፤ የማህበራዊ፤ የፖለቲካና የሚሊታሪ ግንኙነት መረብ መበጣጠስ። በዚህም ከእጃቸው እያፈተለከችውን አፍሪካ አማራጭ አልባ አሃጉር በማድረግ አፍሪካን መልሶ በምዕራቡ ዓለም መዳፍ ስር ማስገባት፤
- አፍሪካንበመዳፋቸው ስር አድርገው በኢኮኖሚ መአቀብ እያስፈራሩ እንዳሻቸው የነርሱ ተገዥ በማድረግ የአዲሱ ቅኝ ግዛት (neo-colonialism) ሕልማቸውን በተዛዋሪ ተግባራዊ ማድረግ ቀዳሚ ዓላማዎቻቸው ናቸው።፤
ከሁሉ በላይ ግን ምዕራባዊያን ጦራቸውን ከዩክሬን ጎን አሰልፈው ሩሲያን መግጠም አይፈልጉም። ከገጠሙ ማሸነፍ የማይችሉት ጦርነት ውስጥ ገብተው ከአፍሪካዊያን ነፍስ በላይ ነው ብለው የሚሳሱለት ሕይወታቸውን መገበር አይፈልጉም። በአፈግሃኒስታን፣ ሶማሊያ፣ ዒራቅ፣ ሊቢያ፤ ሶሪያ፤ ኮርያ ፤ ቪየትናም፤ ካምቦዲያ ውዘተ የገበሩት ሕይወት፤ የደርሰባቸው ውርደት፤ ያስከተለባቸውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኪሳራ ጠንቅቀው ስለሚአውቁ ሌላ ስህተት መስራት አይፈልጉም። ስለዚህ ያላቸው አማራጭ አፍሪካዊያንን በገንዘብ ገዝቶ ከዩክሬን ጎን የማሰለፍ መርሃ ግብር ነድፎ መተግበር ምርጫቸው ሆኗል።
እንዲሁም እጅግ የሚአሳስባቸው ጉዳይ ቢኖር የራሳቸውን ሰው አሰልፈው በሩስያ ከተሸነፉ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካና የስነልቡና ኪሳራ እንደሚአስከትል ስለሚአውቁ ከዩክሬን ጎን ቆመው የመዋጋት ሞራሉም ሆነ ድፍረቱ የላቸውም። አሜሪካና ምእራቡ ዓለም በሩስያ ተሸነፉ ማለት ቀንደኛ ጠላታቸው ኮምኒዝም አሸናፊ ሆኖ ወጣ ማለት ስለሚሆን ውርደቱን አይፈልጉትም። በእብሪትና በውሸት የተሞላው ኩራታቸው፤ በጉራ ብቻ የገዘፈው ሃይላቸው፤ እንደጎረምሳ ያበጠው ጥጋባቸውና ትዕቢታቸው ከፍተኛ ውርደትን ተከናንበው በዓለም መድረክ ላይ መሳለቂያ መሆን ለነርሱ የሞት ሞት ነው።
ሶማሊያ ገብተው ከትዋረዱ በኋላ ለተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪ ሃይል ገንዘብ እየሰጡ የኢትዮጵያን ሰራዊት በመጠቀም ግጭት በሰፈነባቸው የአፊርካ ሃገራት እየላኩ ሰላም ለማስከበር እንደሞከሩት ሁሉ አሁንም አፍሪካዊያንን ተጠቅመው ሩሲያን እንዲዋጉላቸው መፈለጋቸው ጥርጥር የለውም። ለዚህ ነው አፍሪካን ከዩክሬን ጎን ተሰለፉ፤ ሩስያን አውግዙ የሚሉት። ጭብጡ ግን አንተም ጨካኝ ነበርህ ጨቃኝ አዘዘብህ እንደገና ዳቦ እሳት ነደደብህ ነው ነገሩ።
ስለሆነም አፍሪካ የምዕራቡን ዓለም ተንኮል ተረድታ የአሜሪካን ጥሪ ማምከን ይኖርባታል። አፍሪካዊያን ከዩክሬን ጦርነት ለመሸሽ ሲፈልጉ በቀለማቸው ምክንያት ከኪዬቭ እንዳይወጡ ባለስልጣናት አፍሪካዊያኑን እንደ ሰው ጋሻ (human shield) ሲጠቀሙባቸው ከጎናቸው ያልቆመ እና ያላወገዘ ዓለም በምን አመክንዮ ነው አፍሪካዊያን ሕይወታችሁን ለዩክሬን ገብሩ እያሉ የሚማፀኑት። መርጦ አልቃሿ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቿ አሜሪካስ እንዴት ዝም አለች። መልሱን እኔም እናንተም የምናውቀው ቢሆንም ተወያዩበት፤ ተከራከሩበት! የአፍሪካ ሕብረት ግን ለአሜሪካና ለምዕራቡ ዓለም ተንኮል እጅ መስጠት እንደሌለብት መስማማት ይጠበቅብናል።
ሰማነህ ታ. ጀመረ
ኦታዋ፤ ካናዳ
መጋቢት 1 ቀን 2014