የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአፋር እና በአማራ ክልሎች ተስፋፍቶ በቆየው ጦርነት በአሸባሪው ትህነግ ወራሪ ኃይሎች የተከሰቱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በተመለከተ ከመስከረም ወር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ለአራት ወራት ያክል ያደረገውን ምርመራ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ ዛሬ ለብዙሃን መገናኛ ባቀረቡት በዚሁ ሪፖርት በጦርነቱ በተጎዱ በርካታ ቦታዎች በአካል በመገኘት በተደረገው ምርመራ መሰረት አጠቃላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን አስታውቀዋል።
ኢሰመኮ ከዚህ ቀደም ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት (UNOHCHR) ጋር በጣምራ ካደረጉትና በትግራይ ክልል ላይ ካተኮረው ሪፖርት ቀጣይ በሆነው በዚህ ሪፖርት፤ በተለይ ከሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የትግራይ ኃይሎች በአፋርና በአማራ ክልሎች በከፈቱት ወታደራዊ ጥቃት የፈጸሟቸውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን መርምሯል ብለዋል፡፡
የትግራይ ኃይሎች ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀልን እና በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ሊሆን በሚችል መልኩ የእገታ እና አስገድዶ መሰወር ተግባራትን የፈጸሙ መሆናቸውንም ዶ/ር ዳንኤል አብራርተዋል።
የትግራይ ኃይሎች በአፋርና አማራ ክልሎች የሚገኙ ቦታዎችን ተቆጣጥረው በቆዩበት ጊዜ መጠነ ሰፊ፣ ጭካኔ የተሞላበትና ስልታዊ የሆነ በተናጠል እና በቡድን የተፈጸመ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት በሴቶች፣ በሕፃናት ሴቶችና አረጋዊያን ሴቶች ላይ አድርሰዋ ብለዋል፡፡
ይህ ወራሪ ሀይል ፆታዊና ወሲባዊ ጥቃት የተጎጂዎችን እና የጥቃቱ ዒላማ የተደረጉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ሰብአዊ ክብር ለመጉዳት እና ለማዋረድ፣ በአብዛኛው በሴቶች ላይ በሙሉ ያለልዩነት፣ አልፎ አልፎም አጥቂዎቹ ሆነ ብለው ለጥቃቱ ዒላማነት በመረጧቸው ሴቶች ላይ ሆነ ተብሎ ታቅዶ በግፍና በጭካኔ፣ በግልጽ የበቀል ስሜት፣ በቡድን አስገድዶ በመድፈር፣ ድርጊቱን ሆነ ተብሎ በቤተሰብ ፊት ፈጽመዋል ነው ያሉት።
እነዚህ የትግራይ ኃይሎች ባዕድ ነገር በሴቶች ማኅፀን በመክተት ጭምር፣ በታጣቂዎቹ ኃላፊዎች ይሁንታ እና ዝምታ የተፈጸመ በመሆኑ፤ ስልታዊ በሆነ መንገድ ለጦርነት ዓላማ እንዳዋሉት የሚያስረዳ ነው ሲሉም ነው ያብራሩት።
የትግራይ ኃይሎች በቁጥጥራቸው ስር በገቡ የአፋር እና የአማራ ክልል አካባቢዎች ነዋሪዎችን ገንዘብ አምጡ፣ መረጃ አምጡ፣ የደበቃችሁትን መሳሪያ አውጡ፣ በሚሉና በመሳሰሉ ምክንያቶች በሲቪል ሰዎች ላይ በጭካኔ የመደብደብ፣ የማዋረድ እና የማሰቃየት ተግባር ፈጽመዋል ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ስር በነበሩ አብዛኛዎቹ አካባቢዎች በተደራጀ መልኩ የትግራይ ኃይሎች በመንግሥት አስተዳደር ተቋማት፣ የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት (በተለይ የጤና ተቋማት እና የትምህርት ተቋማት) ፣ በግል ንብረቶች እና በንግድ ተቋማት ላይ መጠነ ሰፊ ዘረፋ፣ ገፈፋ እና የንብረት ውድመት ፈጽመዋል ሲሉም ዶ/ር ዳንኤል አስታውቀዋል።
እንደ ኮሚሽነሩ ማብራሪያ፤ በአብዛኛዎቹ ምርመራ በተደረገባቸው አካባቢዎች የትግራይ ኃይሎች ሆነ ተብሎ በታቀደ፣ በተጠና፣ በተደራጀ መንገድ ስልታዊ የዘረፋና ገፈፋ ተግባር፣ በተለይም የሕክምና መሳሪያ ቁሳቁስ፣ ማሽኖችን እና የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን በመዝረፍና በመግፈፍ፣ በመኪና በመጫን ወስደዋል።
በአፋርና በአማራ ክልሎች በአጠቃላይ በ 2,409 የጤና ተቋማት ላይ ጥቃት፣ ጉዳትና ዝርፊያ በመድረሱ አገልግሎታቸው ተቋርጧል፡፡ በተጨማሪም 1,090 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ፣ 3,220 ትምህርት ቤቶች ደግሞ በከፊል መውደማቸውን አረጋግጠዋል።
በፋይናንስ ተቋማት በተለይም በ18 የንግድ ባንኮች 346 ቅርንጫፎች ላይ በቢሊዮን ብሮች የሚቆጠር ዘረፋ እና ውድመት ደርሷል ብለዋል።
የአዕምሮ ሕሙማን በትግራይ ኃይሎች የጥቃት ዒላማ ተደርገዋል ያሉት ዶ/ር ዳንኤል፤ የትግራይ ኃይሎች ወደ ተቆጣጠሯቸው ከተሞች ሲገቡ የአዕምሮ ሕሙማኑ በመንገድ ላይ በመገኘታቸው የመንግሥት ሰላዮች ናቸው በሚል ጥርጣሬ ተገድለዋል ሲሉም አብራርተዋል።
በዘላለም ግዛው
- የትግራይ ኃይሎች በአፋር እና በአማራ ክልል በወረራ ገብተው…
- ጭካኔ የተሞላበትና ስልታዊ የሆነ የአስገድዶ መድፈር በተናጠል እና በቡድን ፈጽመዋል፤
- ሕፃናት ሴቶችንና አረጋዊያንን ሳይቀር ደፍረዋል፤
- ባዕድ ነገር በማኅፀን በመክተት ሴቶችን አሰቃይተዋል፤
- የአዕምሮ ህሙማንን የመንግስት ሰላይ ናችሁ በሚል መግደላቸውን ማረጋገጡን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አስታውቋል።