ፓስተር ቢንያም ከእስር በመፈታቱ ደስ ብሎኛል። ተገቢም ነው። ይህ ሰው እንደ ሃይማኖት አባት ልጆቹን ሃይ ያለ ሰው ነውና ሲጀመር እስራት አይገባውም ነበር።
በመስቀል አደባባይ ጉዳይ ዛሬ ሲኖዶስና የአዲስ አበባ አስተዳደር ቀጠሮ ይዘው እንደነበር ሰምተናል። ይሁን እንጂ ስብሰባው ሳይካሄድ ቀርቷል ሲሉ እየሰማን ነው። ጎበዝ ሃገራችን በብዙ መከራ መሃል እየተለበለበች ያለች ሀገር ናት። በዚህ ጊዜ ሁላችንም ግጭትን የሚጠምቁ ሃይሎችን መታገል አለብን። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው በስቃይ ላይ ስቃይን ለሃገራችን በምንም አይነት አንሻም። ስለሆነም መንግስት በተለይ የሃይማኖት ነክ ጉዳዮችን በጥንቃቄ መያዝ አለበት። የሃይማኖት ተቋማትን ማክበር አለበት። የኦርቶዶክስ የመስቀል አደባባይ የይዞታ ጥያቄ ለምን እንደሚወሳሰብ ምንም አይገባኝም። ይህ ጥያቄ መንግስትን ሊከብደው በፍፁም አይገባም። ሌላው ሁሉ ቢቀር ለብዙ ጊዜ ይህቺ ቤተክርስትያን ደመራዋን መስቀሏን ስታከብርበት ስለቆየች በሚለው ሂሳብ ብቻ ማዘጋጃ ቤት የይዞታ ማረጋገጫዋን ከነ ሙሉ ክብሩ ፓትርያርኩ ቢሮ ድረስ አምጥቶ መስጠት ይገባዋል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ያ ቦታ የኦርቶዶክስ ሆኖ እንደኖረ የታወቀ ነውና መንግስት ግጭቶችን ጠማቂ መሆን የለበትም። ጠብ ያለሽ በዳቦ መሆን ጥሩ አይደለም። አዲስ አበባ ሰፊ ነው። አደባባይ ሞልቱዋል፣ መስራት ይቻላል፣ መንግስት ለመስቀል አደባባይ በጣም አይጓጓ።
ከንቲባዋም የእነዚህን አባቶች ጥያቄ አክብረው በዚያው በፓትርያርኩ ፅህፈት ቤት ቢያናግሩ ከተገቢ በላይ ነው። አባቶች ተገቢውን ክብር ይሻሉ። አሁንም ሁኔታውን ማርገብ ይገባል። ነገር ከማጦዝ መንግስት በፍጥነት ሰርተፍኬቱን አዘጋጅቶ ለኦርቶዶክስ ቢያስረክብ ደግሞ ጥያቄው አለቀ ማለት ነው።
የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሄርን ለአግዚአብሄር እንደተባለው የቤተክርስቲያንን ለቤተክርስቲያን ማስረከብ ይገባል።
የእኔን የግል ታሪክ ላውጋችሁ። እኔ በግሌ ከልጅነቴም የፕሮቴስታንት አባል ነኝ። አያቴ፣ ዘመዶቼ በሙሉ ቀሳውስት ናቸው። በተለይም አያቴ መምሬ በየነ በድሉ የታወቁ ቄስ እንደነበሩ ስሰማ ነው ያደኩት። ታዲያ እኚህ አያቴ ዘወትር ይፀልዮበት የነበረ አንድ የብራና መፅሃፍ እኛ ቤተሰብ ጋር ይኖር ነበር። ይህ የብራና ዳዊት በ17ኛው ክፍለ ዘመን የተፃፈ ነው ብየ እገምታለሁ። ሁል ጊዜም ይህንን መጽሃፍ ለቤተክርስቲያን መስጠት እንዳለብኝ አስብ ነበር። በመሆኑም እዚህ አሜሪካ እያለሁ ይህንን የብራና መጽሃፍ እንዴት ለቤተ ክርስቲያን መስጠት እንዳለብኝ ጠየኩ? አንዳንዶች ለምን ለቤተክርስቲያን ትሰጣለህ ለቦስተን ወይም ለሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ስጠው ይመራመሩበት አሉኝ። አልሰጥም አልኩ…….። ሽጠው ብዙ ገንዘብ ያወጣል አሉኝ………..። ይሄ አባባል ጨርሶ አናዶኝ ነበር። በሁዋላ ዋሽንግተን አካባቢ ያለ አንድ ወዳጄን ሳማክረው ከፓትርያርኩ ጋር ሊያገናኘኝ እንደሚችል፣ መፅሃፉን ለሳቸው መስጠት እንደምችል ነገረኝ። በእውነት ደስ አለኝ……..።
በዚሁ መሰረት ይህ ወንድም እየነዳ ወደ አቡነ መርቆርዮስ መኖሪያ ቤት ሄደን አገኘናቸው። ያን ጊዜ ፓትርያርኩ እዚሁ አሜሪካ ነበሩ። በውነት ፓትርያርኩን ሳገኝ ደስ አለኝ………። መናገር ባይችሉም ነገር ግን በፅሞና ያዳምጡ ነበርና እንዲህ ስል የመጣሁበትን ብርቱ ጉዳይ አስረዳሁ……..።
አባታችን ሆይ ዛሬ እዚህ የመጣሁት የአያቴን የመምሬ በየነን የብራና መፅሃፍ ለቤተክርስቲያን ልመልስ ነው። አያቴ ከዚህ አለም ከተለዩ ቆይተዋል። እኔ ከመወለዴ በፊት ነው የሞቱት ። ይሁን እንጂ ይህ መጽሃፍ ለረጅም ዘመን ከእኛ ቤተሰብ ቤት የቆየ ነው። አሁን የቤተክርስቲያን ቅርስ ነውና እባክዎ ልመልስ ነውና ይረከቡኝ……… ብየ እድሜ የጠገበውን የብራና መፅሃፍ ወደ ጳጳሱ ዘረጋሁ።
ጳጳሱ መፅሃፉን ተቀበሉኝና መጀመሪያ ከእንጨት የተሰራውን እድሜ የጠገበውን የመጽሃፉን ሽፋን አዩ። ቀጥሎ ቀስ ብለው እነሆ ገልጠው ማንበብ ጀመሩ..።። እኔም አይኖቼን በፊታቸው ላይ ተክየ የፊታቸውን መልዕክት ለማንበብ ጓጉቻለሁ። ከደቂቃ በኋላ አይኖቻቸው እንባ ሲያመጡ አየሁና የሆነ ነገር ፈንቅሎኝ አነባሁ……….። ይህቺ ፎቶው ላይ የምታዩዋት ምግብ አብሳያቸው ደግሞ ከፊት ለፊት ቆማ ስትከታተል ነበርና እሷም እንባዋን አፈሰሰች ። ሁላችን ተባረክንና መስቀል አስመውን ተለያየን። ደስ አለኝ። የቤተክርስቲያን ንብረት ለቤተክርስቲያን ያውም ለፓትርያርኩ በመስጠቴ በጣም ደስ አለኝ። የቤተክርስቲያን ቅርስ ከቤቱ በመግባቱ ደስ አለኝ።
ይህንን የግል ታሪክ የማወራው የቤተክርስቲያንን ለቤተክርስቲያን ማስረከብ የሚገባው መንግስት ብቻ ሳይሆን እኛም ዜጎችም መሆን አለብን ብየ ነው። የቤተክርስቲያንን ሃብት መመለስ ሊከብድ አይገባም ለማለት ነው። ይህቺ ቤተክርስቲያን በውነት የሃገር ባለ ውለታ ናት። ልትከበር ይገባል። መንግስት የይዞታ ካርታዋን በፍጥነት ለዚህች ቤተክርስቲያን እንዲሰጥ እንደገና በትሕትና እጠይቃለሁ።