April 2, 2021
26 mins read

የችግሩን ሰንኮፍ ከስሩ ሳይነቅሉ በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ግድያ፤ መፈናቀልና የንብረት ውድመት ማስቆም አይቻልም!!!

መሰረት ተስፉ ([email protected])

ሁላችንም እንደምናውቀው በአማራ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት ሊካድ የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ይህ ጥቃት የተጀመረው ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ስልጣን በያዘ ማግስት ቢሆንም የአማራ ህዝብ በተለይ ከሌሎች ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር ሆኖ በመታገል ህወሃትን ካስወገደበት 2010 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ሶስት አመታት እየደረሰበት ያለው መፈናቀልና ግድያ ተባብሶ መቀጠሉን እየታዘብን ነው። እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ጭፍጨፋውና ጥቃቱ በዋነኛነት ኢላማ ያደረገው አማራን ነው ለማለት እንጅ በሂደቱ የሚጎዱ የኦሮሞም ይሁን የሌሎች ብሄሮች ንፁሃን የሉም ማለት አይደለም።

በዚህ ሁሉ ሂደት እጅግ የሚገርመው ነገር ቢኖር በዋነኛነት በአማራው ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ግድያ ለማውገዝና ለመከላከል የመንግስት መዋቅሩ እያሳየው ያለው የቁርጠኝነት ማነስ ነው። በእርግጥ አልፎ አልፎም ቢሆን በመንግስት የፀጥታ አካላት እየተወሰዱ ነው የሚባሉትን እርምጃዎች በዜና መልክ እየሰማን ነው። ነገር ግን እነዚህ በመንግስት እየተወሰዱ ነው የሚባሉ  እርምጃዎች በቂ ናቸው ብሎ መውሰድ አይቻልም። ምክንያቱም ተጠቂዎቹ ራሳቸው የፌዴራልም ሆነ የክክል የፀጥታ አካላት በአከባቢው አይኖሩም፤ ቢኖሩም ተገቢውን የመከላከል እርምጃ አይወስዱም እያሉ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ሲገልፁ መስማት የተለመደ ነው።

ምናልባት ወደፊት የፀጥታ አካላቱ ስራቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይችላሉ ብለን ብንወስድ እንኳ በወታደራዊ መንገድ ብቻ የዜጎችን ግድያ፣ መፈናቀልና ንብረት ውድመት በቋሚነት ማስወገድ የሚቻል አይመስለኝም።  ይልቁንም የችግሩን መሰረታዊ ምንጭ ፈልጎ በማድረቅ ነው ዘለቄታዊ የሆነ መፍትሄ ማምጣት የሚቻለው ብየ አስባለሁ። የችግሩ ሁሉ የሰንኮፍ ስር ደግሞ በተለይ አማራን በተመለከተ ያለው የተንሸዋረረ አስተሳሰብ ወይም አመለካከት እንደሆነ ግልፅ መሆን ይኖርበታል። በነገራችን ላይ አማራ እያልኩ ስገልፅ ለፅሁፌ እንዲያመቸኝ እንጅ አገውኛ ቋንቋ ከመናገሩ ባሻገር በስነልቦናው ከአማራ ጋር ምንም ልዩነት የማይታይበትን የአገው ህዝብም እያልኩ እንደሆነ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ።

ሁላችንም እንገነዘበዋለን ብየ እንደማስበው ህወሃት ገና ከውልደቱ ጀምሮ አማራን እንደስትራቴጅያዊ ጠላት ፈርጆ ሲንቀሳቀስ ኖሯል። ኦነግም እንዲሁ በተመሳሳይ መንገድ የአማራን ህዝብ  እንደ ታሪካዊ ጠላቱ አድርጎ እንደሚንቀሳቀስ ይታወቃል። ሁለቱም በአማራ ላይ ያላቸውን የተንሸዋረረ አመለካከት በአገር ውስጥና በውጭ ሃገራት ባሉ ተወካዮቻቸው አማካኝነት አሰራጭተውታል፤ አሁንም በስፋት እየሰሩበት ይገኛሉ። ለምሳሌ ህወሃት በ1983 ዓ.ም ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ የአማራን ህዝብ የተለያየ ስም እየሰጠ ጠልቶ የማስጠላት ስራ በሰፊው ሰርቷል። ሲፈልግ ትምክህተኛ፣ ሲመቸው ጨፍላቂ ሌላ ጊዜ ደግሞ አህዳዊ የሚል ስም ሲለጠፍበት የነበረው የአማራ ህዝብ እንደሆነ ልንደብቀው የማንችለው ሃቅ ነው። በትግሉ ወቅትም ቢሆን ህወሓት በአማራ ህዝብ ላይ ያለውን ጥላቻ ከሚገልፅባቸው መንገዶች አንዱ በወቅቱ የነበሩት የኢትዮጵያ ሰራዊት አባላት (በእነሱ አጠራር የደርግ ጭፍጫፊ የሰራዊት አባላት)  ሁሉም አማራ እንደሆኑ አድርጎ በሃሰት በመቀስቀስ ህዝቡ ውስጥ እንዲሰርፅ ማድረግ ነበር። በዚህም ምክንያት ትግራይ ውስጥ አማራን እንደጨፍጫፊ አድርገው የሚያዩ ሰዎች ቁጥር ቀላል አልነበረም። ከዚህ የአመለካከት መንሸዋረር በመነሳት ህወሓት በአማራ ላይ ያደረሰውን በደል ልዘርዝር ብል የሚታወቅ ነገር መድገም ስለሚሆንብኝ ወደሱ አልገባም።

ኦነግም ቢሆን በተመሳሳይ መንገድ ነፍጠኛ፣ ተስፋፊና ሰፋሪ የሚሉ ስሞች በመስጠት የአማራን ህዝብ ጠልቶ ለማስጠላት ያልፈነቀለው ደንጋይ አልነበረም። አሁንም ይህን አቋሙን እንደቀየረ የሚያሳይ ፍንጭ አላየንም። በዚህ ምክንያትም ኦነግ የመንግስት ስልጣኑን ቢይዝ በአማራ ላይ ሊያደርስ የሚችለው ግፍ  ምን ይሆን ብየ ለማሰብ እንኳ ይደክመኛል።

የኦነግም ሆነ የህወሓት የተንሸዋረረ አስተሳሰብ ወይም አመለካከት በየራሳቸው አመራሮችና  አባላት ብቻ የታጠረ ሳይሆን ብልፅግና ፓርቲ ውስጥ ዘልቆ የገባ መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች መኖራቸውንም እያየን ነው። ለዚህም ነው በአንድ ፓርቲ ውስጥ ታቅፈው “ለፓርቲያችን አላማ መሳካት ስንል ህይወታችንን አሳልፈን እንሰጣለን” የሚሉት የብልፅግና ፓርቲ አመራሮችና አባላት ሳይቀር በአስተሳሰብ ወይም በአመለካከት መፈራቀቅ ምክንያት እርስ በርሳቸው እየተጓተቱ ንፁሃን እንዲጨፈጨፉ  አንድ ምክንያት እየሆኑ ያሉት።

አሁን አሁን ግልፅ እየሆነ እንደመጣው የኦሮሞና የአማራ ብልፅግናዎች በአመለካከት ደረጃ የሚለያዩባቸው ነጥቦች በቀላሉ የሚታለፉ አይደሉም። በህገመንግስቱ ረገድ ያላቸው አቋም የተለያየ እንደሆነ ይታወቃል። የኦሮሞ ብልጽግናዎች ከህገመንግስቱ ጋር ሞተን እንገኛለን የሚል አቋም ሲኖራቸው፤ የአማራ ብልፅግናዎች በበኩላቸው ህገመንግስቱ መሻሻል አለበት የሚል ጠንካራ ፍላጎት አላቸው።

የአዲስ አበባን ባለቤትነት በተመለከተም ሁለቱም ተቃራኒ ሃሳቦችን ያራምዳሉ። የኦሮሞ ብልፅግናዎች አዲስ አበባ የኦሮሚያ ናት የሚል አቋም ሲኖራቸው፤ የአማራዎቹ ደግሞ አዲስ አበባ የነዋሪዎቿ ናት የሚል እምነት ይዘው በፅናት ቆመዋል።

በኢትዮጵያ ታሪክ ረገድም የኦሮሞና የአማራ ብልፅግናዎች ያላቸው ተቃርኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በዚህ ረገድ ብዙዎቹ የኦሮሞ ብልፅግናዎች ለአማራ ያላቸውን ጥላቻ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ሲያንፀባርቁ ማየት እየተለመደ መጥቷል። ። ከነሱ ውስጥ ነጋ ጠባ አማራን በነፍጠኝነት፣ በጨፍላቂነትና በአሃዳዊነት የሚወነጅል ሃይል ቁጥር በርካታ ነው። ለምሳሌ የክልሉ ፕሬዚደንት የሆነው አቶ ሽመልስ አብዲሳ ሳይቀር ታሪካችን የሰረቀንን ነፍጠኛ ሰብረነዋል ብሎ በአደባባይ ሲደነፋ መስማት የተለመደ ሆኗል። ይህ ብቻ ግን አይደለም። ሃሳቡ ከየት መነጨ፤ ምን ያህሉስ ይደግፉታል የሚለውን ለጊዜው እንተወውና “…አማርኛን አዳክመን የራሳችን ቋንቋና ማንነት በሌላው ላይ ብልጫ እንዲኖረው እንተጋለን፣ ከዚህ በኋላ ኦሮሞ ወይም ኦሮሞ ያልፈቀደለት ካልሆነ ሌላ ማንኛውም ሃይል ወደስልጣን አይመጣም፣ ህወሓት ኢህአዴግን የመሰረተው ራሱን ለመጥቀም በማሰብ እንደነበረው ሁሉ እኛም ብልፅግና ፓርቲን የመሰረተነው የእኛን ጥቅም ለማስከበር ነው፣ ሶማሊኛን፣ ትግርኛንና አፋርኛን የፌዴራሉ የስራ ቋንቋ ያደረግነው አማርኛን ለማዳከም ነው…” የሚል የለየለት የሴራና የቁማር እቅድ ነድፈው እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ የሰማነውም ከራሱ ከሽመልስ አብዲሳ ነው።

ይህን እቅዳቸውን ተግባራዊ ለማድረግ እየተጠቀሙበት ያለው ስልት ማሳመንና ማደናገር (Convince or Confuse) የሚል እንደሆነም የገለፀልን ሽመልስ ራሱ ነው። እነሽመልስ ይህን የማሳመንና የማደናገር ስልት ተጠቅመው የሌሎች ክልሎችን ብልፅግናዎች ከጎናቸው ለማሰለፍ እየሄዱበት ያለውን እርቀት የሚያመላክቱ ተግባራትን መታዘብ ከጀመርንም ዋል አደር ብለናል። ይህን እያደረጉ ያሉት ደግሞ ያው የፈረደበትን አማራ አዳክመው በሃገሪቱ ላይ የበላይነት እንዲኖራቸው ያቀዱትን ድብቅ አጀንዳ ለማስፈፀም እንደሆነ ለመረዳት ከባድ አይደለም። ከዚህ በመነሳት የኦሮሞ ብልፅግናዎች ምናልባትም በከፋ ሁኔታ ህወሓትን ለመተካት እየታተሩ ነው ቢባል ስህተት የሚሆን አይመስለኝም።

ከዚህ ገፊ ምክንያት ተነስተውም ይመስላል ኦሮሚያ ብልፅግናዎች ኦሮሚያ ውስጥ በተለያዩ ጊዚያት በአማራ ላይ እየደረሰ ያለውን ጭፍጨፋ ለመከላከልና ለማስቆም ወኔ ሲያጥራቸው የምናያቸው። የኦሮሚያ ብልፅግናዎች ወኔ የሚያጥራቸው መሆኑን ለመረዳት ጃዋር ተከበብኩ ባለበት ወቅት፣ ከአርቲስት ሃጫሉ ግድያ በኋላ እና ሰሞኑን ደግሞ ምዕራብ ወለጋ ላይ እነሱ ነፍጠኛና ሰፋሪ በሚሏቸው አማራዎች ላይ በደረሱት ማንነት ተኮር ጭፍጨፋዎች ላይ የሰጡትን ምላሽ ማየት ብቻ በቂ ነው። በአማራው ላይ እየደረሰ ካለው ጭፍጨፋ በላይ የሚያመው ደግሞ የኦሮምያ ብልፅግናዎች አማራው በማንነቱ ተለይቶ እየተጠቃ መሆኑን ለማመን እንኳ ፍላጎት አለማሳየታቸው ነው። እንዲያውም አንዳንድ ጊዜስ አጥቂውንና ተጠቂውን አጃምለው በመውቀስ ጉዳዩን አድበስብሰው ለማለፍ ሲሞክሩም እየተመለከትን ነው። ይህ ደግሞ በአማራ ቁስል ላይ ሚጥሚጣ ከመነስነስ ተለይቶ የማይታይ አደገኛ መንገድ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል።

ኦሮሚያ ውስጥ ያሉ አማራዎችን እጣ ፋንታ አሳሳቢ የሚያደርገው ግን ጭፍጨፋው ብቻ አይደለም። አማራዎች ከመጨፍጨፋቸውና ከመጠቃታቸው በላይ እንደጥፋተኛ እየታዩ የግፍ ግፍ የሚፈጸምባቸው መሆኑን የሚያሳዩ አገላለፆችን መስማትም እጅግ በጣም አስደንጋጭ ነው። ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን በህይወት ለማቆየት ሲሉ ያለፍላጎታቸው ማንነታቸውን እየቀየሩ ያሉ አማራዎች ጥቂቶች አይደሉም የሚል ነገር መስማትም እንኳን ለተጠቂዎቹ ለሚሰማው ሰውም ይከብዳል።

በሌላ በኩል የሚገኙት የአማራ ብልፅግናዎች ደግሞ በየጊዜው ታሪክን ማዕከል ያደረጉ አጀንዳዎች ሲቀረፁላቸው  እነሱን ለማስተባበልና ታሪክ ፈፃሚዎቹን ለመከላከል ከሚያደርጉት ብልጭ ድርግም የሚል እንቅስቃሴ የዘለለ አመርቂ ስራ እየሰሩ ነው ብሎ መውሰድ የሚቻል አይመስለኝም። አሁን ላይ ለአማራና ለኢትዮጵያ ህዝብ ፍትሃዊ ጥቅሞች ምን እየሰራን ነው በሚሉ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ከማተኮር ይልቅ አያቶቻችን በሰሩት መልካም ስራ ለመኮፈስ ጥረት ማድረግ የአማራ ብልፅግናዎች መለያ ነው ቢባል ማጋነን አይመስለኝም። በእርግጥ የፌስቡክ አርበኛው ሁሉ እንደሚለው አካኬ ዘራፍ እያሉ ከሁሉም ጋር ይጋጩ የሚል እምነት በጭራሽ የለኝም። ነገር ግን ከሌሎች ጋር በጋራ ሃገር እንደሚመራ ሃይል የበኩላቸውን እየተወጡ ነው ለማለት የማቀርበው ማስረጃ የለኝም። በተለይ ሃገሪቱ ምን ላይ እንዳለች፣ ተቋማዊ አሰራር መኖር አለመኖሩን፣ ምን እቅድ እንደተነደፈ፣ እቅዱስ በምን ሁኔታ ተግባራዊ እየሆነ እንዳለ፣ ቋሚ የክትትልና የቁጥጥር እንዲሁም የግምገማ ስርዓት መኖር አለመኖሩን እውቀቱ አላቸው የሚል እምነት የለኝም። ይህ ቢሆን ኖሮ የአማራ ክልል ፕሬዚደንት በአማራ ላይ እየደረሰ ያለውን ተደጋጋሚ ጭፍጨፋ ለማስረዳት መድረክ እፈልጋለሁ የሚል ጥያቄ ባላነሳም ነበር። ስለአማራ ብልፅግናዎች የማልክደው ነገር ቢኖር ግን የህወሓትን ጥቃት መክተው ክልሉንም ሆነ ሃገርን ከሁለተኛ ዙር ከፋፍሎ የመግዛት ሙከራ ለመታደግ የተቀናጀና ውጤታማ የሆነ አመራር መስጠታቸውን ነው።

ስለችግሩ ሰንኮፍ ይህን ያህል ካልኩ መፍትሄን ይሆናሉ የምላቸውን ሃሳቦቼን ደግሞ እንደሚከተለው ለማቅረብ እሞክራለሁ። መጀመሪያና ከሁሉም በላይ የአማራ ብልፅግናዎች ከውንዜኝነት እሳቤ ወጥተው ራሳቸውን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መፈተሽና ማጠናከር ያስፈልጋቸዋል። ራሳቸውን ፈትሸው ካጠናከሩ  በኋላ የአማራን ህዝብ ፍትሃዊ ጥቅሞች ያለአግባብ ይፃረራሉ ከሚሏቸው ሃይሎች ጋር ግልፅ ውይይት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ለምሳሌ አማራዎች በተደጋጋሚ እየተጠቁባቸው ካሉ የክልል አመራሮች በተለይ ደግሞ ከኦሮሚያና ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ብልፅግናዎች ጋር ስሜታዊ ያልሆነ ግን መርህን በተከተለ አግባብ ፊት ለፊት በመነጋገር ችግሮችን ለመፍታት የሚችሉትን ሁሉ ማድረግ ይኖርባቸዋል። በዚህ ረገድ የኦሮሚያ ብልፅግና ውስጥ ያሉ አመራሮች ካላቸው ጥላቻ በመነሳት በየአደባባዩ አማራ ላይ እየለጠፉት ያለው የዳቦ ስም፣ ከዚህ ተነስተውም አማርኛን ለማዳከም እየሰራን ነው በሚለው  ድብቅ እቅድና አማራው ላይ እየደረሰ ያለውን ጭፍጨፋ ለማስቆም የሚያሳዩትትን ዳተኝነት በማስረጃ አስደግፈው ሊታገሏቸው ይገባል። በአዲስ አበባ፣ በህገመንግስቱ እና በታሪክ ላይ ያላቸውን ልዩነት በተመለከተም ሰላማዊና በሰከነ ፖለቲካዊ ውይይት እልባት እንዲያገኙ ቢያደርጉ ተመራጭ ይሆናል። የማይስማሙ ከሆነ ደግሞ ሁለቱም በሃገሪቱ ተቋማትና ህግጋት በመመራት ለጥያቄዎቻቸው መልስ መፈለግ እንጅ መሻኮትና በቁማር ህጎች መመራት ጠቃሚ እንዳልሆኑ መረዳት ጊዜው የሚጠይቀው ግዴታቸው እንደሆነ ሊገነዘቡ ይገባል።

ከዚህ ጎን ለጎንም የአማራ ብልፅግናዎች በሃገራዊዩ ብልፅግና ፓርቲ ውስጥ መርህን በተከተለ መልኩ ተፅዕኖ የመፍጠር አቅማቸውን ማጎልበት አለባቸው።  ይህን ማድረግ የሚችሉት ደግሞ ከፍ ብየ ለመግለፅ እንደሞከርኩት እንደሌሎቹ በድለላ፣ በማታለል፣ በማደናገርና በማስገደድ ሳይሆን በማስረጃ ላይ የተደገፈ ሃሳብ በማቅረብ፣ ተቋማዊ አደረጃጀቶችና አሰራሮች በቋሚነት ተግባራዊ እንዲሆኑ በማድረግና የተዛነፉ ሁኔታዎች ሲኖሩ ደግሞ መተክላዊ የሆነ ትግል በማካሄድ ነው። በዚህ መንገድ መጓዝ  ለአማራ ጥላቻ ያላቸውን ሃይሎች  ከሌሎች ጋር ሆኖ ለመታገልና ለማስተካከል እድል ይሰጣል። አሁን እንድምናየው ሁሉም በየፊናው ተበትኖ ችግር ሲደርስ ብቻ የሚያለቅስ ወይም የሚፎገላ ከሆነ ግን እታገልለታለሁ የሚለውን ህዝብ መብት ማስከበር ይቅርና ለራሱም መፃኢ ደህንነት ዋስትና ሊኖረው አይችልም።

የአማራ ህዝብ በህጋዊ መንገድ ተደራጅቶ ፍትሃዊ መብቶቹን ሊያስከብር እንዲችል ሰፊ ስራ መስራትም እንደሁለተኛ መፍትሄ ሊወሰድ ይገባል። ድር ቢያብር እንዲሉ ከአንድ ሁለት ከሁለት ደግሞ ሶስት እያለ ሲቀጥል ጥንካሬም እየጨመረ እንደሚሄድ ለማንም ግልፅ ነው። ስለዚህ የጎጥ፣ የወንዝና የመንደር ልዩነቶችንና ሽኩቻዎችን አስወግዶ በየደረጃው እንደህዝብ መደራጀት ያስፈልጋል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ሁሉም ወጣቶች በፍፁም ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ  ክልላዊ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ስልጠናወች ቢወስዱ ለህዝቡ እድገትና ልማት አወንታዊ አበርክቶ እንደሚኖራቸው ማሰብም ይገባል። በነገራችን ላይ ይህ ዘዴ በሃገር አቀፍ ደረጃም ተግባራዊ ቢሆን ጠቀሜታው የጎላ እንደሚሆን እገምታለሁ።

በአማራ ላይ ያለማቋረጥ እየተፈፀሙ ያሉትን ጭፍጨፋዎችና ጥቃቶች የሚመራቸው፣ የሚያስተባብራቸውና ተግባራዊ የሚያደርጋቸው ማን እንደሆነ ለማወቅ የሚያስችል ገለልተኛ የሆነ ጥናት እንዲደረግ መታግልም ሊታለፍ የማይችል መፍትሄ እንደሆነ መረዳት ጠቃሚ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞም ተጠያቂነት እንዲኖር ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል።

ከክልሉ ውጭ ያሉ የአማራ ተወላጆችን አደረጃጀት፣ እየደረሰባቸው ያለውን ጥቃት፣ ጥቃቱን የሚያደርሱትን አካላትና ምክንያታቸውን በአጠቃላይም ደህንነታቸውንንና ፍትሃዊ ጥቅሞቻቸውን በጥናት ላይ ተመስርቶ የሚከታተልና የሚያስጠብቅ በሰው ሃይልም ሆነ በቁሳቁስ የተሟላ አካል ማቋቋም እንደሚያስፈልግም መረሳት የለበትም።

ከዚህ ባሻገር ያሉ ሌሎች የመፍትሄ ሃሳቦች ለማመንጨት ይቻል ዘንድ ደግሞ የአማራ ሙህራንና ፖለቲከኞች ቁጭ ብለው መምከር ይኖርባቸዋል። የአማራ ምሁራንና ፖለቲከኞች ስል የአንድነት ሃይሎችና ብሄርተኞች ነን የሚሉትን ሁሉ ይጨምራል። የሙህራኑና የፖለቲከኞቹ ምክክር በየተወሰኑ ጊዜያት የሚካሄድ ሆኖ በእቅድ ሊመራ ይገባል።  ለምሳሌ ምክክሩ በየሶስት ወሩ ወይም በየስድስት ወሩ ሊሆን ይችላል። የዚህ ምክክር አላማ በአማራ ህዝብ ፍትሃዊ ጥቅሞች ዙሪያ ያሉትን ችግሮች ማንጠር፤ መፍትሄዎችን ማስቀመጥና  የተቀመጡ መፍትሄዎች ተግባራዊ መሆናቸውን መከታተልና መቆጣጠር ቢሆን የመረጣል እያልኩ  ላዛሬው ሃሳቤን እዚህ ላይ አጠቃልላለሁ።

ቸር እንሰንብት!

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop