March 26, 2021
46 mins read

አንድነት፤ አንድነት ስንል አምሳ ዓመት ሊሆን ነው—ለመተባበር ዘውጋዊ ፖለቲካን የማስወገድ ቆራጠኛነት ያስፈልጋል – አክሎግ ቢራራ (ዶር)

አክሎግ ቢራራ (ዶር)

ክፍል አንድ

እኛ ለኢትዮጵያና ለመላው ሕዝቧ ቆመናል የምንለው ሁሉ አንድነት፤ አንድነት፤ ህብረት፤ ህብረት ስንል ወደ አምሳ ዓመት በመሸጋገር ላይ እንገኛለን። ውጤቱ ግን የዚህን ያህል ማራኪ አይደለም። የፖለቲካ ባህላችን ድርጅትን ፈጥሮ መከፋፈል፤ ማጥፋት፤ መተካትና መጠላለፍ እየሆነ አንዱ ሌላውን በመተቸት ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላ ትውልድ እንሸጋገራለን። ባለፉት ሶስት ዓመታ በአንድ በኩል ተስፋ ሰጭ፤ በሌላ በኩል አድካሚ የፖለቲካ፤ የማህበረሰብና የመነፈስ ባህርይ ለውጥ መታየቱ አያከራክርም።

ማህበረሰባዊና የልማት ለውጥ ስኬታማ ሊሆን የሚችለው በመጀመሪያ ብሄራዊ መግባባት፤ እርቅና ሰላም መሰረት ሲይዝ ነው። በተለይ፤ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሞችና ሉዐላዊነት ላይ ምንም አይነት ብዢታ የሌለበት ቅድመ ሁኔታ ወሳኝ ነው። ለዚህ ዋና ማነቆ ሆኖ የማገኘው ህወሓትና ራሱ ተነባክቦ የፈለፈላቸው የዘውግ ፖለቲካ አቅንቃኞች ናቸው።

ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሚባሉት የኢትዮጵያዊያን መለያ የነበሩ ወሳኝ እሴቶች ተሸርሽረዋል፤ ወድመዋል ለማለትም የሚያስደፍሩ ሁኔታውች በየቀኑ ይታያሉ። እልቂትና ውድመት የተለመዱ ክስተቶች ሆነዋል። የኢትዮጵያ ዋናና መሰረታዊ ችግር የውስጥ የፖለቲካ ሂደትና አመራር ችግር ነው። ወጣቱ ትውልድ ይህንን አጥፊና አውዳሚ ችግር በሚገባ አልተረዳውም።

በንጉሠ ነገሥቱ ወቅት የነበረው ትውልድ ከራሱ በላይ ለአገሩና ለወገኖቹ የሚያስብ ነበር ለማለት እደፍራለሁ። የብሄረሰብ ፖለቲካ መሰረት የያዘው በዚያ በእኔ ትውልድ አካባቢ ቢሆንም የተባባሰውና ለኢትዮጵያ ህልውና አደገኛ የሆነው ግን በአሁኑ ትውልድ ነው። የኢትዮጵያ ምሁራንና ልሂቃን ባህል ሁለት ወሳኝ የሆኑ ገጽታዎች አሉት።

አንድ፤ ሳይሰለቹ ስለ አገር ወይንም ስለ ቡድን ጉዳይ መነጋገር እና

ሁለት፤ ተነጋግሮ በአንድነት ለመስራት አለመቻል/ቆርጦ ለመነሳት አለመድፈር።

የትንሽ የኪስ ዘውድ አበሳ

ሁለተኛውን ባህርይ በሚመለከት ሁለት ምሁራን ጓደኞቸ በተደጋጋሚ የሚጠቅሱት ብሂል አለ። “እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ምሁር፤ ልሂቅና ሌላ በኪሱ ትንሽ ዘውድ እየያዘ የሚዞር ይመስላል።” ለኢትዮጵያ የምንከራከረው በቡድን እንጅ በአገራዊ ህብረትና በመናበብ አይደለም።  የዚህ አሉታዊ ውጤት ምንድን ነው?

መልሱ የእኛ መከፋፈል ለውጭ ኃይሎች፤ ለህወሓታዊያንና ለኦነጋዊያን የሕዝብ ግንኙነቱንና የዲፕሎማሲውን ቦታ እንድለቅላቸው ተገደናል። ህወሓታዊያን በዝቅተኛ $30 ቢሊየን ከኢትዮጵያ ድሃ ሕዝብ ሰርቀውና ወደ ውጭ አሽሽተው ዛሬ የበላይነቱን ይዘውታል። ትርክቱን ለውጠውታል። እኛ ብንተባበርና በቀን ለቡና ከምናወጣው በነፍስ ወከፍ ሶስት ዶላር ለመለገስ ብንችል፤ ህወሓቶችና አጋሮቻቸው የሚያካሂዱትን ትርክት ለመቀየር እምቅ አቅም አለን።

ኢትዮጵያ የገጠማትን ተግዳሮት፤ እኔ ብቻ ልምራ፤ እኔ ብቻ የእውቀት ምንጭ ነኝ፤ እኔ ብቻ ያልኩት ይሁን፤ እኔ ብቻ፤ እኔ ብቻና የእኔ ብቻ የሚለውን ጎጅ ባህል ያካትተዋል። የኢትዮጵያ ሁኔታ በጣም እንደተለወጠ የማይቀበሉ ግለሰቦችና ስብስቦች “በእኔ ብቻ ዓለም ይኖራሉ” ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም። የፖለቲካ ሳይንቲስቱና ህይወቱን በትግል ዓለም የኖረውና አሁንም የሚታገለው ዶር መረራ ጉዲና ለብልሹው የፖለቲካ ባህላችን ባህርይ “የቡዳ ፖለቲካ” የሚል ስያሜ ስጥቶታል። እኔ እንደሚገባኝ ከሆነ “የቡዳ ፖለቲካ” ባህሪይ፤ ጊዜ ወስዶና አስቦ ራስን ከመመርመርና ከመተቸት ይልቅ ችግሮችን ሁሉ በሌላ ማመካኘት ነው። አማራው ኦሮሞውን አንተ ነህ ቡዳ፤ ኦሮሞው አማራውን አንተ ነህ ቡዳ፤ ትግሬው ሁለቱንም እናነት ናችሁ ቡዳ ወዘተ እያለ ከታገለ አብሮነት እንዴት ይሳካል?

ህወሓት መንዝን ሲሻገር የአካባቢው የአማራ ሕዝብ “ህይወትና ኑሮ ከትግራይ ሕዝብ የማይለይ፤ በድህነትና በኋላ ቀርነት የተበከለ” መሆኑን አይቶ “ይኼን ሕዝብ እንዴት የትግራይ ሕዝብ ጠላት ነህ እንለዋለን” የሚል ውይይት እንደተደረገ አንድ ወዳጀ የዛሬ አስራ አምስት ዓመት አጫውቶኝ ነበር። ሜጀር ጀኔራል አበበ ተክለኃይማኖት “የተገኘውን ሰላምና እድገት የሚንድ የአመራር ዘይቤ በአስቸኳይ ይቁም” በሚል አርእስት ያቀረበው ትንተና በብሄርተኝነት፤ ጎሰኝነት ወይንም ጎጠኝነት ዙሪያ ባለፉት አርባ ዓመታት ተቋማዊ የሆነው “የቡዳ ፖለቲካ” ምን ያህል ስር ሰዶ አገሪቱን ለአደጋ፤ ሕዝቡን ለእርስ በእርስ ግጭት እንዳጋለጣቸው ያሳያል።

“የቡዳ ፖለቲካና” የዘውጋዊ ፖለቲካ የአንድ ሳንቲም ግልባጭ ናቸው። ህወሓት ያጠናከረው ዘውጋዊ ፖለቲካ እጅግ በጣም የሚዘገንን ውጤት አስከትሏል። ህወሓታዊያንና በራሳቸው አመለካከት የፈለፈሏቸው የዘውግ ግንባሮች የሚጋሩት ተመሳሳይ ባህል አለ። ይኼውም የእነሱ አጋርና ደጋፊ ያልሆነውን ሁሉ በጠላትነት መፈረጅ፤ መግደልና ማሳደድ ነው። “እኔ ብቻ ልብላ” ካልክ ሌላውን የማጥፋትና የማሳደድ መብት አለኝ ማለትህ ነው። ህወሓታዊያንና ኦነጋዊያን የሚያደርጉት ይህንኑ ነው።

በቅርቡ ብዙ የህወሓት ጀኔራሎችና ኮሎኔሎች ሞቱ ተብሎ ተዘግቧል። የሚዘገንነው ክስተት ግን መሞታቸው አይደለም። ህወሓቶችና ኦነጋዊያን ባለፉት አርባ ዓመታት በተከታታይ የሚዘገንኑ ዘውግና ኃይማኖት ተኮር እልቂቶች አካሂደዋል።

በማንኛውም አገር ጦርነት ሲካሄድ ሞት ሊከተል እንደሚችል ጠንቋይ አያስፈልግም። የሚዘገንነው ህወሓቶች የአስራ ስድስት በግጭቱ የሞቱ የጦር መኮንኖችን አንገት መቁረጣቸው ነው። በዜና የምንሰማው በሊቢያ፤ በኢራክ፤ በሶርያና በሌሎች ቦታዎች አልካይዳና መሰል ድርጅቶች የንጹሃንን ዜጎች አንገት መቁረጣቸውን ነበር። በሊቢያ ጽንፈኞች የኢትዮጵያዊያንን አንገት ቆርጠዋል። በማይካድራ፤ በቤኒ ሻንጉል ጉሙዝና በሌሎች አካባቢዎች አንገት ተቆርጧል። ህወሓታዊያን በቅርቡ የፈጸሙት ዘግናኝ የሚሆንበት ግን ለየት ያለ ይመስለኛል።

አብረዋቸው የኖሩትን፤ የበሉትን፤ የታገሉትን፤ ልጅና ቤተሰብ፤ ዘመደ አዝማድ ያላቸውን የራሳቸውን አጋር ግለስቦች አንገት የቆረጡበት ምክንያት ምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ ብዙ ጥናትና ምርምር የሚያስፈልገው ይመስለኛል። ኃይማኖት የሌላቸው ካልሆኑ በስተቀር፤ አንገት ስንቆርጥ ፈጣሪም ሊቆጣን ይችላል፤ የራሳችን ሕዝብ ይታዘበናል የሚል ስሌት አላሳዩም። የሰጡት መልእክት፤ ነገም እናንተን ልናርዳችሁ ዝግጁ ነን የሚል ነው። ከአልካይዳ/ ከአልሸባብ የሚለዩበት መስፈርት የለም። የሚያሳስበኝ፤ የህወሓታዊያንን ትርክት ሙሉ በሙሉ የሚደግፉት የምእራብ ዓለም መንግሥታትና ተቋማት ሚና ነው።

አንገታቸው የተቆረጠው ግለሰቦች አልሞቱም፤ አሉ፤ ይመሩናል፤ ድርጅታችን አልተነካም ወዘተ ለማለት ከሆነ ድርጊቱ የሚያሳየው ግን የቡድኑን ኢ-ሰብ አዊነት ነው። በመቀሌ የትግራይ ዘውግ አባል ያልሆኑትን መኮንኖችና ወታደሮች መግደላቸውን አንርሳ። በማይካድራ ያካሄዱትን ጭካኔ የተሞላበት ጭፍጨፋ እናስታውስ። በተገላቢጦሽ ህወሓታዊያንና ደጋፊዎቻቸው በማይካድራ November 9, 2020 ህወሓት መራሹ ሳምሪ 1,200 ንጹህ አማራዎችን መጨፍጨፉን አምነስቲ ኢንተርናሽናልና የተባበሩት የሰብአዊ መብት ኮሚሽነሯ ከዘገቡት በኋላ ግፉ ተረሳ። ሌላም የማይካድ ወንጀል ተፈጽሟል። በአክሱም ከተማ ወገኖቻችን ተገድለዋል። ማንኛውም እልቂት ግፍ ነው። ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ግን በ November 28, 2020, በአክሱም ከተማ ለተካሄደው ግፍ ነው። ጭፍጨፋውን ለምን እየለያያችሁ ታቀርባላችሁ? ብለን የመጠየቅ ሃላፊነት አለብን። በማንኛውም መስፈርት ብንመራመረው ከጀርባ ያለው “ቡዳው” ህወሓት ነው። ምክንያቱም ጦርነቱን የጀመረው፤ በመላው ኢትዮጵያ እሳት እንዲቀጣጠል ያመቻቸውና የቀሰቀሰው ህወሓት ነው።

ህወሓታዊያን ለማንም ፍጥረት እርህራሄ የሌላቸው አረመኔዎች መሆናቸውን የሚያሳይ ድርጊት ነው። የራሱን ወገኖች አንገት የሚቆርጥ አካል ለማንም ኢትዮጵያዊ ምህረት ሊያሳይ አይችልም። በዚህ ላይ ብዢታ አታሳዩ።

እያወደሙ መልሶ ማቋቋም ከኢትዮጵያ አቅም በላይ ነው።

ህወሓታዊያን የትግራይን ሕዝብ ኑሮ አቃውሶታል። የትግራይ ሕዝብ የሚገለገልብትን አየር ማረፊያ በቦምብ ከጥቅም ውጭ አውድመውታል። የክልሉን ልማት በሃያ ዓመታት ወደ ኋላ ጎትተውታል። የራሱን ወገን አንገት የሚያርድና በድሃው ሕዝብ ባጀት የተሰራውን መሰረተ ልማት ቦምብ የሚያደርግ ቡድን እንዴት ለወገኑ ቆመ ሊባል ይችላል? ለራሱ ወገን ደንታ የሌለው ቡድን ለሌላው ኢትዮጵያዊ ህይወትና ደህነንት ያስባል ማለት ዘበት ነው። የውክልና ጦርነት እየተስፋፋ የሄደበት መሰረታዊ ምክንያትም ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው። ከጅምሩ ጸረ-ኢትዮጵያ የሆነ ቡድን ለኢትዮጵያ ዘላቂንትና ለመላው ሕዝቧ ደህንነት ያስባል ማለት ድንቁርና ነው።

ሜጀር ጀኔራል አበበ፤ የአማራውን ሕዝብ አሰቃቂ ሁኔታ እንዲህ በሚል አቅርቦታል። “የህወሓት ሠራዊት መንዝ/ ሸዋ በገባበት ጊዜ…ወደ ሠራዊቱ የተቀላቀሉት አዲስ ታጋዮች መንዝ ሲገቡ የሕዝቡ የኑሮ ሁኔታ ሊገባቸው አልቻለም። የሕዝቡ ኑሮ ከትግራይ ሕዝብ በምንም ሁኔታ የማይሻል ሆኖ ሲያገኙት አንዳንዶቹ ተዋከቡ። የአማራ ገዥ መደብንና የአማራን ሕዝብ መለየት አልቻሉም። “እንዴት ነው አማራ ጠላታችን ነው ያላችሁት፤ ተታልለን ነው የታገልነው” አሉ። በነባሮችና በአዲሶቹ መካከል የጦፈ ክርክር ተካሂዶ በመጨረሻ ተማመኑ። ህወሓት ሲያስተምራቸው የነበረው ግልጽ መሆኑ፤ እሱም፤ “የአማራ ገዥ መደቦች በአማራ ስም ሲነግዱም ለራሳቸው ካልሆነ ለአማራው ምንም እንዳልሰሩለትና አማራም እንደሌላው ሕዝብም እንደሚጨቆን” ተማመኑ። ይህም ሆኖ፤ “የቡዳው ፖለቲካ” ተባባሰ እንጅ አልተሻሻለም። ፕሮፌሰር መራራም የችግሩን እምብርት ደፍሮ አላወጣውም። ብሄርተኝነት ኢትዮጵያን ወደ ገደል አፋፍ እየገፋት ነው።

ኦነጋዊያንና ሌሎች የህወሓትን የተሳሳተ ትርክት መርህ ያደረጉት ሁሉ አልተማሩም። አሳሳቢው ግን፤ ሌሎቻችንም አልተማርነም። ሁለት ማስታወሻዎች ግልጽ እንዲሆኑ እመኛለሁ።

አንድ፤ የተማሪው እንቅስቃሴ የተከፋፈለው ከላይ በተጠቀሰው ምክንያት፤ ማለትም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግር የመደብ እንጅ የብሄር ጭቆና፤ ጥላቻና ልዩነት አይደለም በሚለው ዙሪያ እንደ ነበረ አስታውሳለሁ። እኔም አንዱ ተከራካሪ ነበርኩ። አሽኮኮ ብሎ ያሳደገኝን  “አያ ውበትን” እየጠቀስኩ፤ የዐማራ ድሃ ገበሬ የኦሮሞውን ድሃ ገበሬ ሊጨቁን አይችልም በሚል ተከራክሬ ነበር።

ሁለት፤ ያለፈው የኢትዮጵያ ሕዝብ የኑሮ ታሪክ ሚዛናዊ በሆነ ደረጃ ቢመረመር፤ ተራው የአማራና የትግራይ ሕዝብ (ሃበሻ ተብሎ የሚጠራው) እንደሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጭቁን፤ ከቀዩ የሚሰደድ፤ ድሃና የገዢዎች ሰለባ መሆኑን የሚያስተጋባ ነበር። የህወሓት ነባሮች ይኼን ክርክር አያውቁትም ለማለት አይቻልም። “ሰፊው የአማራ ሕዝብ ለኋላቀርነት፤ ለድህነት እና ለብዝበዛ የተጋለጠ” መሆኑ፤ ልክ እንደ ትግራዩ፤ እንደ ኦሮሞውና ሌላው ሕዝብ ነጻነቱና “ዲሞክራሳዊ መብቱ የታፈነ” መሆኑ፤ ልክ እንደሌላው የኢትዮጵያ ድሃና የስራ እድል ያጣ ሕዝብ “የጦርነት ሰለባ” መሆኑ እና፤ ይኼ ሁሉ በመሬት የሚታይ ሁኔታ እየታወቀ የህወሓትና ሌሎች ነባሮች ለስልጣንና ለግል ጥቅም ሲሉ “ሌሎቹ ሕዝቦች በአማራ ሕዝብ ላይ ጥርጣሬ” ብቻ ሳይሆን የሚዘገንን ጥላቻ ተቋማዊ ማድረግ፤ የአማራን ብሄረሰብ ለይቶ ማጽዳትና ማጥቃት፤ ሆነ ብሎ ቁጥሩን መቀነስ፤ መሪዎች እንዳይኖሩት ተስፋ የሚሰጡትን ሲያብቡ ማሰር፤ እንዲሰወሩ ማድረግና በድብቅ መግደል፤ ከተፈጥሮ ኃብታቸው ማስወገድ እና በአማራው ሕዝብ ላይ በጅምላ “ጥርጣሬ” እንዲኖር ማድረጉ አሁንም ቀጥሏል። ይህንን ነው “የቡዳ ፖለቲካ” ብሎ መተቸት። ለዘላቂና ፍትሃዊ ልማት ዋና ጠንቅ ነው፤ ማነቆ ነው።

እንደዚህ ያለው የብሄር ጥላቻና አግላይነት ለሰላም፤ ለእርጋታ፤ ለአገር ሉዐላዊነትና ለሕዝብ አንድነት ጸር ነው። የአማራውን ሕዝብ የድህነትንና የኋላ ቀርነትን የማይካድ ደረጃ እኔ ሳልሆን፤ አልጀዚራ በማስረጃ ተደግፎ ሲያቀርብ እንዲህ ብሏል። “የአማራው ሕዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያና የአፍሪካ ሕዝቦች በበለጠ ደረጃ ፍጹም ደሃ፤ ኋላ ቀርና በበሺታ የሚሰቃይ ሆኖ አግኝተነዋል” ብሏል። ይህ “የቡዳ ፖለቲካ” ሰለባ የሆነ ሕዝብ በአሁኑ መንግሥት ያገኘው ጥቅም ምን እንደሆነ ህወሓቶችና ኦነጋዊያን መረጃ ማቅረብ ይኖርባቸዋል።

ዓለም ባንክ ስሰራ በነበርኩበት ወቅት፤ የፖሊሲው ምክትል ፕሬዝደንት ጅም አዳምስ፤ ከምርጫ 97 በኋላ ብዙ ግር ግር ስለነበረ፤ ለድሃው ኢትዮጵያዊ በቂ የሆነ ድጎማ ማድረግ አለብን ብሎ ተሟግቶ Safety Net program ተመሰረተ። በዚህ ፕሮግራም መሰረት ባለፉት ሃያ አመታት በትግራይ ክልል ብቻ ሁለት ሚሊየን የትግራይ ሕዝብ አባላት በየዓመቱ በድጎማ ብቻ ሲደገፉ ቆይተዋል። ህወሓቶች የሚለገሰውን የውጭ እርዳታ ለምን ተጠቅመው ይህ ሕዝብ ራሱን እንዲችል አላደረጉም የሚለውን ጥያቄ መጠየቅ አግባብ አለው። በተጻራራው ያደረጉትን ትኩረት ስጡት። አብዛኛውን የውጭ እርዳታ የነጠቁት፤ ቪላዎች የሰሩበት፤ የሰረቁት፤ ከአገር ያሸሹት እነሱ ናቸው። የህወሓት ከፍተኛ ባለሥጣናት በድሎት እየኖሩ የትግራይ ሕዝብ በደህንነት መረብ ድጎማ ሲሰቃይ ኖሯል። ዛሬ የዓለም ሕብረተሰብ “የአዞ እንባ” ሲረጭ ስመለከት ጥገኝነትን እንደ ተለመደ ነገር መቀበላቸውንና ለራሳቸው አጎብዳጅ የሆነን ቡድን እንደሚደግፉ እንድትረዱት እፈልጋለሁ። ህወሓት የውጭ ኃይሎች አገልጋይ ቡድን ነው።

ህወሓት ለመቀሌና ለአክሱም ሕዝብ የውሃ ጉድጓድ ለምን አልሰራም? የተሰራውን  መሰረተ ልማት ለምን አፈረሰው? የህወሓት የበላዮች ለምን ልጆቻቸውን በዘረፉት ኃብት እየደገፉ ውጭ ልከው በድሎትና በደህንነት እንዲኖሩ አደረጉ? የድሃውን ወጣት ለምን የእሳት እራት አደረጉት? በውጭ በሰላምና በድሎት የሚኖሩት ህወሓታዊያን ከአገር ተሰርቆ የወጣውን የሰላሳ ቢሊየን ዶላር ትርፍራፊ እየተጠቀሙና አቤቱታ አቅራቢዎችን እየተጠቀሙ ኢትዮጵያንና ጥሮ ግሮ የሚኖረውን ሕዝብ ከማስጨነቅ ይልቅ ለምን ይህንን ግዙፍ መዋእለንዋይ መልሶ ለማቋቋምና የተራበውን የትግራይን ሕዝብ ከድጎማ ድባብ እንዲላቀቅና ኮርቶና ደልቶት እንዲኖር አይደግፉትም?

አብሮና ተሳስሮ የመኖርን ትሥስር የደመሰሰው ህወሓት ነው። 

እንደ ብረት የተሳሰረ ሕዝብ ለመፍጠር ከተፈለገ ሁሉም የኢትዮጵያ ዜጎች በማንኛውም ኢትዮጵያ መብታቸው በሕግ የተጠበቀ መሆን ይኖርበታል። የመኖር፤ የመንቀሳቀስ፤ኃብት የማካበት መብታቸው መከበር አለበት። የዜግነት መብት ሊሸራረፍ አይችልም። የሚሸራርፉት የውጭ ኃይሎች የሚፈልጉት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ መሆኑን ትኩረት ስጡት። የትግራይ ኢትዮጵያዊያንም ሆነ የአማራ፤ የኦሮሞ ሆነ የሶማሌ የዜግነት መብታቸው የተከበረባት ኢትዮጵያን ለመመስረት ቆርጠንና ተባብረን ካልተነሳን በስተቀር ኢትዮጵያ የመበታተን እድሏ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። የምእራብ አገሮች ይህንን የመበታተን ሴራ እንደሚፈልጉት መሆኑን በሌላ ሃተታ ላይ አስስቤአለሁ። ይህ እንዳይሳካ የምንመኝ ኢትዮጵያዊያን በጋራ ሆነን ማድረግ ያለብን አስኳል ጉዳይ፤ የዘውጉ ሕገ መንግሥትና የክልሉ አጥር እንዲነሳ ማድረግ ነው። ራሳችን የፈጥረነውን የዘውግ ስርዓት ለማፍረስ ካልቻልን ፈረንጆቹን መተቸት በቂ አይደለም። 

ፈረንጆች ቢወዱም ባይወዱም፤ ቢክዱም ባይክዱም፤ ህወሓት የሰራቸው ወንጀሎች ሊካዱ አይችሉም። የተገረፈው፤ የተዋረደው፤ መንፈሱ በየቦታው የተነካው፤ የተዘረፈው፤ በተከታታይ ክህደት የተካሄደበት የኢትዮጵያ ሕዝብ የህወሓትን መሰሪነትና ተላላኪነት ያውቀዋል። ህወሓታዊያን  በኢትዮጵያዊነታቸው ያፍራሉ። ለፈረንጆችና ለግብጾች ታዛዢነትንና አጎብዳጅነትን ይመርጣሉ። ለምን?

የምእራብ መንግሥታት ሆነ ብለው ችላ ያሏቸው የህወሓት ክፋት፤ ጥፋትና ወንጀሎች ምንድን ናቸው?

  1. ራሱን የትግራይ ማርክሲስት-ሌኒኒስት ሊግ ብሎ ከሰየመ በኋላ ተፎካካሪዎቹን እያጥፋና እያሳደደ ራሱን የትግራይ ነጻ አውጭ ግንባር ወይንም ትህነግ ብሎ ሰየመ። ዋናው ዓላማው ከኢትዮጵያ ተገንጥሎ ታላቋን የትግራይን ሪፐብሊክ መመስረት ነበር።

 

  1. ለትግሉ አመቻች የሆነውን መርሃ ግብር (Manifesto) ያዘጋጀው የአማራው ሕዝብ፤ ልክ እንደ ፈረንጆቹ ቅኝ ገዢዎች ተመሳሳይ በሆነ ደረጃ ዋናው የትግራይ ሕዝብ ጠላት ነው ብሎ ፈረደበት። የአማራው ሕዝብ እንደ ማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ በመካከሉ በመደብ የተከፋፈለ መሆኑን ፋይዳ ቢስ አድርጎ አማራው በያለበት ተከታታይ ውርደትና ጥቃት እንዲካሄበት ፈረደበት፤ ወነጀለው፤ እንዲጋለጥ አደረገው፤ ወዳጆችና አጋሮች ገበየበት/ ገዛበት።

 

  1. ሀወሓቶች የራሳቸው የትግራይ ክልል ረዢም ታሪክ ያለው መሆኑንና ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አንድ አካል መሆኑን ቢያውቁትም፤ ለኢትዮጵያ ባላችው ጥላቻ የኢትዮጵያ ታሪክ ረዢም አይደለም። ኢትዮጵያን የመሰረቷት አጼ ምኒልክ ናቸው፤ ከእሳቸው በፊት ኢትዮጵያ የምትባል አገር የለችም ነበር። የኢትዮጵያ ታሪክ የመቶ ዓመታት ታሪክ ብቻ ነው ብለው አስተጋቡ። ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል አይደለችም ብለው ፈረዱ። ኢትዮጵያ የባህር በር እንዳይኖራት አመቻቹ። ይህ ከፍተኛ ክህደት ነው።

 

  1. ማርክሲስት ሌኒኒስት መሆናቸውን በተግባር ተርጉመው የማእከላዊውን መንግሥት ስልጣን ከያዙ በኋላ፤ የመንግሥት ስልጣን አስተዳደራቸውን አብዪታዊ ዲሞክራሲ እና ዲሞክራሳዊ መአከላዊነት በሚሉ የበላይነት ስልቶች ለአናሳ ዘውግ የበላይነትና ቁጥጥር አመች በሆነ ደረጃ ወሳኝ የሆኑትን ተቋማት ሁሉ በትግራይ ተወላጆች አስይዘው ኢትዮጵያን ለመቆጣጠርና ለሃያ ሰባት ዓመታት ለመግዛት ቻሉ። ይህንን ቅርስ ከህወሓት የወረሰው አካል የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ ለበላይነቱ ስለሚረዳው ዛሬም አልተቀየረም። ህወሓትን በሚመለክት ልቆጠብና አንድ ጥያቄ ላቅብ። የምእራብ አገሮች ኮሙኒስት ቻይናን፤ ሰሜን ኮርያን በአንድ ፓርቲ፤ የኮሙኒስት ማእከላዊነታቸው እየተቹ ለምን ይህንን ማርክሲስት ቡድን ደገፉት?

 

  1. ህወሓት በ 1991 የፖለቲካ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ሁሉም የአፍሪካ አገሮች በዘውግ መደራጀት አፍራሽ ነው ብለው የከለከሉትን መርህ ወደ ጎን ትቶ፤ በብሄርና በቋንቋ መለያዎች አጣምሮ፤ የመገንጠል መብትን ሕጋዊ አድርጎ፤ ኢትዮጵያን ገዛ፤ ድርጅታዊ ምዝበራ አካሄደ። ወንድም ወንድሙን እንዲጠራጠር፤ እንዲገድል አደረገ። ይህንን የከፋፍለህ ግዛው ስልታዊና ጸረ-ዲሞክራሳዊ ሕገ መንግሥት ነው ህወሓት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያወረሰው። የዪጋንዳው ፕሬዝደንት ሙሰቬየኒ ለኢትዮጵያ ተጨንቀው “ጥንታዊዋንና ታሪካዊዋን ኢትዮጵያን እየናዳት የሚገኘው የዘውግ ፖለቲካ ነው” ያሉት ትክክል ነው።

 

  1. አድናቆትን ያገኘው መለስ ዜናዊ የምእራብ አገሮችን፤ ተቋማትን፤ በተለይ የገንዘብና የእርዳታ ድርጅቶችን በከፍተኛ ደረጃ ማረካቸው። መድብለ ፓርቲ፤ የሜድያ ነጻነት፤ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ወዘተ እፈቅዳለሁ። የግል ኢኮኖኖሚውን አስፋፋለሁ፤ የሕዝብና የመንግሥት የነበሩትን ድርጅቶች ሁሉ የግል አደርጋለሁ የሚል ቃል ኪዳን ገባላቸው። የኢትዮጵያን ለም መሬት መቸርቸር ጀመረ። ኢትዮጵያ ከህወሓት መራሹ መንግሥት በፊት አግኝታ የማታውቀውን ግዙፍ እርዳታ ማግኘት ጀመረች። በየዓመቱ እጥፍ “አሃዝ እድገት” ተቀዳጀች ተብሎ ይመዘገብ ጀመረ። የህወሓት ባለሥልጣናት፤ ቤተሰቦችና ወዳጆቻቸው በህልማቸው አስበውት የማያውቁትን የገቢ መጠን አገኙ። ከሰላሳ ቢሊየን ዶላር በላይ የሚገመት የውጭ ምንዛሬ ከኢትዮጵያ ድሃ ሕዝብ ተዘርፎ፤ በሕገወጥ መንገዶች ወደ ውጭ አገሮች ተላከ። ዛሬ ኢትዮጵያን ለማጥቃት ይጠቀሙበታል። ይህ ነው፤ ህወሓትን የማፍያ ቡድን የሚያስብለው። ህወሓት የኢትዮጵያን ካዝና ባዶ ያደረገ ቡድን ነው። ሌላውን እንርሳውና የትግራይን ድሃ ሕዝብ እንኳን ከአሰቃቂ ድህነት አሮንቃ አላወጣውም።

 

  1. የኢትዮጵያ የውጭ እዳ መጠን ለምን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረሰ? የሚለውን ለመመለስ የሚቻለው የህወሓትን ማፊያ ባህርይና ስራዎች፤ በተለይ፤ ድርጅታዊ ምዝበራ ለመገንዘብ ሲቻል ብቻ ነው። የምእራብ ለጋስ መንግሥታትና አበዳሪ ድርጅቶች ይህንን አያውቁም ለማለት አልችልም፤ ያውቃሉ። ግን የሚያገኙት ጥቅምና አገልግሎት ስላለ፤ ሰላሳ ቢሊየን ዶላር ለነሱ ፋይዳ የለውም። አብዛኛው የውጭ ምንዛሬ ተመልሶ የገባው ወደ ራሳቸው አገሮች ነው። በአሜሪካ አገር እንኳን የተሰሩትን የኪራይ ቤቶች፤ ቪላዎች፤ ሱቆች፤ ለይተን ገና አናውቃቸውም።

 

  1. ህወሓት መራሹ መንግሥት ስልጣኑን ከያዘ በኋላ ኢትዮጵያ በዝቅተኛ ሲታሰብ አርባ ቢሌየን ዶላር እርዳታ አግኝታለች። አንድ አገር በውጭ እርዳታና ድጎማ ሊበለጽግ ቢችል ኖሮ ኢትዮጵያ ቢያንስ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች መካከል አንዷ ትሆን ነበር። ዛሬ ኢትዮጵያ በነፍስ ወከፍ ገቢና በማህበረሰባዊ ልማት መስፈርቶች ድሃና ኋላ ቀር ከሆኑት አገሮች መካከል አንዷ ናት። የህወሓትን ቢሊየኔሮችና ሚሊየኔሮችን በአንድ በኩል፤ በሌላ በኩል በትግራይ ብቻ በየዓመቱ ላለፉት ሃያ ዓመታት ብቻ በድጎማ የሚኖረውን ሁለት ሚሊየን ድሃ ሕዝብ አነጻጽሩትና ራሳችሁ ፍረዱ። የህወሓት ናፋቂዎች ህሊና ቢሶች ናቸው።

 

  1. የምእራብ አገሮችና አበዳሪ ድርጅቶችም መተቸት ያለባቸው በዚህ መስፈርት ነው። ድጋፋቸውን ማን ማረከው? ድጎማ ብቻውን አይሰራም። ድጎማውና ብድሩ በጥቂቶች ከተማረከ ደግሞ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ኪሳራ መሆኑ አይቀርም።

 

  1. የምእራብ አገሮችና ተቋማት ህወሓት ኢትዮጵያን ሰጥ፤ ለበጥ አድርጎ ሲገዛ በነበረበት ወቅት የፈጸማቸውን ግፎችና በደሎች ለምን ጊዜው እንደረሱት የማይገባው እትዮጵያዊና ለህሊናው ብቻ የሚገዛ ፈረንጅ ያለ አይመስለኝም”። ለምሳሌ፤ ምርጫ ዘጠና ሰባትን ተከትሎ በተከሰተው ሕዝባዊ እምቢተኛነት ብቻ አስር ሽህዎች ታስረው ነበር። የህወሓት አልሞ ተኳሾች የኦሮሞውንና የአማራውን ወጣት በገፍ ጨፍጭፈውታል። በአንድ ወቅት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በዓለም ደረጃ ጋዜጠኞችን፤ የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎችን በማሰርና በማሳደድ የመጀመሪያውን ደረጃ ይዞ ነበር። የአፈናና የጭካኔ ሕጎችን (Draconinan Proclamations) አውጇል ተብሎ ተከሶ ነበር። የአሜካ ምክርት ቤት H.R. 128 የተባለውን ውሳኔ ያወጣው ለምንድን ነበር? እንዴት ተረሳ? የኢትዮጵያ ሕዝብ ትንሽ መተንፈስ የጀመረው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶር ዐብይ አሕመድን መሪ እንዲሆኑ የኢህአዴግ አመራር ከመረጠ በኋላ መሆኑ ለምን ጊዜው ተረሳ?

 

  1. የምእራብ አገሮችና ተቋማት በይፋም ባይሆን ውስጥ ለውስጥ፤ ህወሓት የትግራይ ተወላጆችን ብቻ እየመረጠና እያሰለጠነ አብዛኛዎቹን የመንግሥት ተቋማት–ደህንነትና መረጃን፤ መከላከያን፤ ቴሌኮምን፤ መብራት ኃይልን፤ የውጭ ጉዳይና የዲፕሎማት መስሪያ ቤቶችን፤ አየር መንገድን፤ የአገር ውስጥና የውጭ ገበያ መስሪያ ቤቶችን፤ የከተማና የገጠር መሬት ድልደላ መስሪያ ቤቶችን፤ የግንባታና የመገናኛ ድርጅቶችን፤ ጉምሩክን፤ ከባድ እንዲስትሪዎችን ወዘተ በበላይነት መያዙ አስጊ ሁኔታ ፈጥሯል ይሉ አልነበረም? ዓለም ባንክ በነበረበርኩበት ወቅት ይህን ትችት እሰማ ነበር። እኔም ይህን አይን ያወጣ ዘውጋዊ አድልዎ ለኢትዮጵያ አደገኛ ነው እያልኩ እከራከር ነበር። የኢትዮጵያ ኢምባሲዎች ሙሉ በሙሉ በህወሓት ካድሬዎች ተይዘው እንደ ነበረ የአደባባይ ምስጢር ነው።

በትግራይ የተከሰተውን ቀውስ በተናጥል መገምገም አደገኛ ነው። የምእራቡ ዓለም መንግሥታትና ተቋማት ኢትዮጵያን ለመርዳት ፍላጎት ካላቸው ቢያንስ የሚከተሉትን ሃቆች ያስተናግዱ እላለሁ። ህወሓት፤

  1. ለትግራይ ክልል ሕዝብ ለሃያ ዓመታት ከጎኑ ሆኖ ተራውን ድሃ ወንድም/እህቱን በቅንነት በጨዋነት፤ በልዩ ልዩ ዘርፎች–አንበጣን ከመከላከል ጀምሮ በራሱ ወጭ መጠለያዎችን እስከ መገንባት ድረስ–ያገለግል የነበረውን የሰሜን እዝ አባላትን በዘውግ ለይቶ ጥቃት ፈጽሞበታል፤ ኢትዮጵያን ከድቷታል፤ የእዙን አባላት ገድሏል፤ አቁስሏል፤ ትጥቁን አስፈትቷል፤ ጫማውን አውልቆ እንዲሸሽ አድርጓል፤ የማቾቹን እሬሳ በየመንገዱ ጥሏል።

 

  1. የኢትዮጵያን የመከላከያ ኃይል ለማዳከም ባቀደው መሰረት፤ ከባድ መሳሪያዎችን፤ መገናኛዎችን፤ ስትራተጅክ ግንኙነቶችን አፍርሷል፤ ኢትዮጵያ ለውጭ ጠላቶች ጥቃት እንድትጋለጥ አድርጓል።

 

  • የጦር አውድማውን ውደ አማራው ክልል ለማስፋፋት ባለው እቅድ፤ የጎንደርንና የባህር ዳርን አየር ማረፊያዎች በሮኬት ደብድቧል፤ ንጹሃንን ገድሏል፤ ሃብት አውድሟል። ግጭቱን ቀጠናዊ ለማድረግ የአስመራን አየር ማረፊያ በሮኬት ደብድቧል፤ የኤርትራን ብሄራዊ ደህንነት ስጋት ውስጥ አስገብቷል።

 

  1. በማይካድራ በሚዘገንን ደረጃ ከ 1,200 በላይ የሚሆኑ አማራዎችን በዜግነት መለያቸው ምክንያት ጨፍጭፏል። ሳምሪ ለተባለው ላሰለጠነው የወጣት አጥፊ ቡድን መሳሪያና አመራር ሰጥቷል። አካባቢው ከህወሓት አስከፊ ቁጥጥር ነጻ ሲወጣ ወንጀለኛው ቡድን ወደ ሱዳን እንዲሸሽ አድርጓል። በአሁኑ ወቅት ራሱን መልሶ ለጥቃት በማዘጋጀት ላይ በሱዳንና በግብጽ ለሚደገፈው የህወሓት ጽንፈኛ ቡድን አጋር ሆኗል። በአክሱም ከተማ አሰቃቂ ጭፍጨፋ እንዲካሄድ ሁኔታዎችን አመቻችቷል፤ የእልቂቱ ተባባሪ ሆኗል።

 

  1. የትግራይ ሕዝብ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ እንዲነሳ ለማመቻቸት ባደረገው ስሌት መሰረት፤ በትግራይ አስሯቸው የነበሩትን “30,000 ወንጀለኞች ፈታ፤ ከእነዚህ 10,000 የሚሆኑት ታስረው የነበረው በመቀሌ ነው። እነዚህ ወንጀለኞች የት ሄዱ? ምን ይሰራሉ? በሌብነት፤ በዘረፋ፤ በማጅራት መችነት፤ ሴቶችን በመድፈርና በሌሎች የሁከት ፈጠራ ስራዎች ይሰማሩ አይሰማሩ እንዴት እናውቃለን? እነዚህና የህወሓት እርዝራዢዎች በአሁኑ ሠፊ ጥፋት ምን ሚና አላቸው?

 

  1. የክልሉ ድሃ ሕዝብ የሚገለገልባቸውን ተቋማት–አየር ማረፊያዎች፤ የኤሌክትሪክና የቴሌኮም መሳቢያዎች፤ የህክምና መገልገያዎች የመሳሰሉ–ሆነ ብሎ አወደማቸው። ሰብአዊ እርዳታ ያለ ምንም ስጋት እንዳይሰራጭ መሰናክል የሆነው ህወሓት አይደለም? የኢትዮጵያ መንግሥት 70 በመቶ የሚሆነውን ሰብአዊ እርዳታ እየሰጠ ለምን ይህን ሃቅ የሜድያ ሽፋን አይስጠውም? ማንን ለመጉዳትና ለመንቀፍ ታስቦ ነው?

ህወሓት፤ እነዚህንና ሌሎችን በኢትዮጵያ ታሪክ ተሰርተው የማያውቁ ግፎችንና በደሎችን ከፈጸመ በኋላ፤ “ከደሙ ንጹህ ነኝ” በሚል ትርክት የውጭ መንግሥታትንና ድርጅቶቻቸውን፤ ለዚሁ እኩይ ተግባር ያሰለጠናቸውን አክቲቪስቶች ኢትዮጵያን፤ በተለይ ዝነኛውን የኢዮጵያን መከላከያ ኃይል እንዲያወግዙ ቀሰቀሳቸው። ይህ ትርክት አሁንም በሰፊው ይካሄዳል።

እኔን እጅግ የሚያሳስበኝ የውጩ ትችት ሳይሆን፤ የህወሓትን ፈለግ የተከተሉ የአገር ውስጥ የዘውግ ጽንፈኛ ኃይሎች ናቸው። አንዳንድ በኢትዮጵያ ምክር ቤት የተነሱ ትችቶችና ፈር የለቀቁ ጥያቄዎች ውጭ ከሚተረከው በምንም ሊለዩ አይችሉም። ህወሓት እየፈረሰ ነው ቢባልም ተተኪዎች በኢትዮጵያ ላይ እያንዣበቡባት ይታያሉ።

ቀጣዩን በመጭው ሳምነት ይመልከቱ

 

March 26, 2021

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop