October 27, 2020
46 mins read

አቅጣጫችንንና ግባችንን የሳትነው መሠረታዊ ምክንያታችንን የሳትን እለት ነው – ጠገናው ጎሹ

October 25, 2020
ጠገናው ጎሹ

ምክንያት (cause) ውጤትን (effect) ያስከትላል ። ለምን? ለሚለው ጥያቄ የምንሰጠው መልስ የምክንያትን ምንነት ሲገልፅ ምን ተገኘ? ለሚለው ጥያቄ የምንሰጠው መልስ ደግሞ የውጤትን ምንነት ይነግረናል ። ከምክንያት ተነስተን ውጤት (ግብ) ላይ ለመድረስ ለምንከተለው አቅጣጫና አካሄድ የምንሰጠው መልስ ደግሞ እንዴት? የሚልውን ጥያቄ ይመልስልናል ።

የውጤት (effect) ስኬታማነት ወይም ውድቀት የሚወሰነው ወይም የሚለካው በምንነሳበት መሠረታዊ ምክንያት እና በምንከተለው አቅጣጫና የማስፈፀሚያ ስልት (ዘዴ) ትክክለኛነት ወይም ስህተት ፣ ጥናካሬ ወይም ልፍስፍስነት ፣ ጥራት ወይም ግብስብስነት ፣ ዘላቂነት ወይም በአጭር ቀሪነት ፣ ወዘተ ላይ ነው።

ስኬታማ ውጤት የተነሳንበትን ምክንያት እና የምንከተለውን አቅጣጫና የአፈፃፀም ስልት ትክክለኛነት በመግለፅ (በማንፀባረቅ) ላይ ብቻ የሚወሰን ሳይሆን የማያቋርጥ ጥረታችንን የሚያግዙ የተሞክሮ እሴቶችን (ግብአቶችን ) በመጨመር የላቀ ውጤት ባለቤቶች እንድንሆን አስተዋፅኦ እስከ ማድረግ የሚዘልቅ ነው ።

በተቃራኒው ስኬታማ ያልሆነ ውጤት ቀድሞውንም ትክክለኛነት ያልነበረውን ምክንያትና አካሄድ ይበልጥ በማባባስና በማወሳሰብ ለባሰ ውድቀት ይዳርጋል።

በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ከተሳሳተ ምክንያታዊነት ከተነሳን የምንሄድበት አቅጣጫም ሆነ የምንደርስበት ውጤት የተሳሳተ እንጅ ከቶውንም ትክክለኛ ሊሆን አይችልም።

በሌላ በኩል ግን በምንነሳበት ትክክለኛ ምክንያት እምነትና መርህ ላይ ፀንተን ከቆምን እና ትክክለኛውን አቅጣጫ ከተከተልን የምንደርስበት ግብም (ውጤትም ) የሰመረ ነው የሚሆነው ።

የእነዚህ ሁለት የተለያዩ (ተቃራኒ) ምክንያቶች፣አካሄዶችና ግቦች ሎጅክ ቀላልና ግልፅ ስለሆነ ብዙም የሚያጠያይቀን አይሆንምና አለመታደል ወይም መርገምት ሆኖብን ሳይሆን በእኛው በእራሳችን አስከፊ ውድቀት ምክንያት ከተነሳንበት የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ

ሥርዓት ለውጥ ሃዴድ እየተንሸራተን ተመልሰን የሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖች ሰለባ ወደ ሆንበት እንቆቅልሻችን ልለፍ።

ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ተጠናውቶን የኖረውን ክፉ የፖለቲካ ካንሰር ስያሜውን በመቀየር ማለትም ህወሃት/ኢህአዴግን ኦዴፓ/ብልፅግና በማለት ፣ የካንሰሩ ምንጭ የሆነውን ህገ መንግሥት ተብየ አይደፈሬ በማድረግ ፣ የካንሰሩ አስተላላፊና አስፋፊ የሆኑ ተቋማትን በነበሩበት በማስቀጠል፣ የካንሰሩ ተሸካሚ የሆኑ ባለሥልጣናትን (ካድሬዎችን) እንደ ጉልቻ በመቀያየር እና ከዚሁ ክፉ ልክፍት አትራፊ የሆኑ ባለሃብት (ኢንቨስተር) ተብየዎችን አጋር በማድረግ የቀጠለውን ሥርዓት ከምር ታግሎ ከማስወገድና የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር እውን ከማድረግ ይልቅ መሠረታዊ ባህሪውንና ተግባሩን ካልቀየረ የፖለቲካ ካንሰር ጋር ተመልሰን የመለማመድ አባዜ ውስጥ እራሳችንን ከማግኘት የከፋ እጅግ አሳፋሪና አደገኛ እንቆቅልሽ የለም።

እናም የገንዛ እራሳችንን ተደጋጋሚና ልክ የሌለው ውድቀት ማቆሚያ በሌለው የሰበብ አስባብ ድሪቶ ለመከላከል ከመሞከር እጅግ ክፉ ልማድ ወጥተን በቀጥታና በግልፅ ለመነጋገር ፈቃደኞችና ዝግጁዎች ሆነን መገኘት የትክክለኛ መፍትሄ ፍለጋ አንዱ አካል ነውና በዚሁ እሳቤ መሠረት አብረን እንደምንዘለቅ ተስፋ እያደረግሁ ልቀጥል።

የተነሳንበት የለውጥ ፍለጋ መሠረታዊ ምክንያት ባለጌና ጨካኝ የጎሳ/የመንደር/የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ነጋዴ ገዥ ቡድኖች የተከሉትን እጅግ መርዘኛና አደገኛ ሥርዓት አስወግዶ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ማድረግ ሆኖ ሳለ ተመልሰን የዚያው ሥርዓት ውላጆችና አገልጋዮች የሆኑ ሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞች የተረኝነት ወጥመድ ውስጥ ሰተት ብለን ከገባንና ለመግለፅ የሚያስቸግር ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ሰለባዎች ከሆን ሁለት ዓመታት በላይ አስቆጠርን ። በመሠረታዊ የፍትህና የነፃነት ፍለጋ ተጋድሎ ሂደት ክፍሎቸ (ምእራፎች) ማለትም በምክንያት፣ በተግባራዊ ያፈፃፀም አካሄድና በውጤት (በግብ) መካከል መኖር የሚገባውን ጤናማና ዘላቂ መስተጋብር ጠብቆ ማስኬድ ያለመቻላችን ውድቀት ያስከተለውንና እያስከከተለ ያለውን አጠቃላይ (ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ ፣ ሞራላዊ፣ ሥነ ምግባራዊ ፣መንፈሳዊ) የትውልድ ቀውስ የማይገነዘብ ጤናማና ቅን ህሊና ያለው የአገሬ ሰው የሚኖር አይመስለኝም።

ኢህአዴግን ብልፅግና ብሎ በመሰየም እና ካድሬዎቻቸውን እንደ ጉልቻ እያቀያየሩ በመሾም ወይም በመመደብ ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በንፁሃን ዜጎች የቁም ሰቆቃና ደም ተዘፍቀው የኖሩበትን አስከፊ የፖለቲካ ሥርዓት ተሃድሶ (reform) በሚል የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ ጨዋታ ማስቀጠል ባይችሉና በምትኩ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር

እውን ቢሆን ኖሮ የዝርፊያና የሙስና ህይወታቸው ሲቋረጥ እና እነርሱ በአፍ ጢሙ የደፉት ፍትህ ትክክለኛውን ትርጉም አግኝቶ በህዝብ ፊት ቆመው ሲጠየቁ እየታያቸው ከአስከፊ ቅዠት ጨርሶ መላቀቅ የማይችሉ ፖለቲከኞችን (ኢህአዴጋዊያንን/ብልፅግናዊያንን) “የለውጥ ሃዋርያት ወይም የዘመናችን ሙሴዎች” ያልን እለት ነው በተነሳንበት መሠረታዊ ምክንያት ላይ የበረዶ ውሃ የቸለስንበት። ይህን አይነት ልክ የሌለው ደጋግሞ የመውደቅ (የመክሸፍ) አስከፊ የፖለቲካ ማንነት እንኳን የነፃነትና የፍትህ ሥርዓት ፈላጊ ነኝ የሚል ትውልድ የአያሌ ንፁሃን አርበኞች ዜጎቿን አፅም በውስጧ የተሸከመች እናት ምድርም ትፀየፈዋለች ።

ይህ የአሁኑ ወጣት ትውልድ ከተነሳበት መሠረታዊ ምክንያት ማለትም ዴሞክራሲያዊትና የበለፀገች አገር እውን የማድረግ ዓላማ እየተንሸራተተ የሸፍጠኛና ጨካኝ የጎሳ/የመንደር/የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ልክፍተኛ ገዥቡ ድኖችና ቢጤዎቻቸው ሰለባ የሆነ እለት ነው የእድሜውን ወርቃማ ዘመን በእጅጉ ያበላሸው። በእጅጉ ልብ የሚሰብረው ደግሞ የእራሱን እጣ ፈንታ ማበላሸቱ ሳያንሰው ባለጌና ግፈኛ ገዥ ቡድኖችና ፖለቲከኞች በልክፍታቸው አስክረው (አሳብደው) የገንዛ እራሱን ንፁሃን ወገኖቸ በሃይማኖታዊ እምነትና በብሄረሰብ ማንነታቸው እየለየ በአሰቃቂ ሁኔታ ጨፍጭፎ በአስከሬናቸው ላይ እንዲሳለቅ በማድረግ ህሊና ከሚባል ልዩ ስጦታ ጋር ከተፈጠረው ሰብአዊ ፍጡር በታች ብቻ ሳይሆን ከደመነ ነፍስ እንስሳት በታች ሲያውሉት ከምር ለምንና እንዴት? ብሎ ለመጠየቅ አለመቻሉ ወይም አለመፈለጉና የሚበጀውን አለማድረጉ ነው ።

ጥቂቶች በፈፀሙትና ባስፈፀሙት ለምን ትውልድ ይተቻል? የሚል ጥያቄ ሊነሳ እንደሚችል እገነዘባለሁ ። አዎ! በገዥው ቡድን ውስጥና ከገዥው ቡድን ውጭ የሚገኙ ቀጥተኛ አስፈፃሚና ፈፃሚ ቡድኖችና ግለሰቦች ቁጥር ከህዝቡ ቁጥር አንፃር ጥቂት መሆናቸው አያወዛግበንም። የእነዚህ ልክና ማቆሚያ የሌለው እብደት በአገር (በህዝብ) ላይ ያስከተለውንና እያስከተለ ያለውን በአንደበት ወይም በብእር ለመግለፅ የሚያስቸግር መከራና ውርደት በዓይን በብረቱ እያዩ በተደራጀና በተቀናጀ እንቅስቃሴ አለማስቆም ወይም በራስ ህይወት ላይ እስከሚፈፀም መጠበቅ ወይም ከገዥ ቡድኖች የሸፍጥና የሴራ ተሃድሶ ልትገኝ የምትችለዋን የውርደት ፍርፋሪ ተስፋ በማድረግ ዝምታን መምረጥ ግን ቢያንስ የትክክለኛ ሰብአዊ ፍጡርነታችን መለኪያ አንዱ ከሆነው የሞራል እሴት አንፃር ፈፅሞ ተቀባይነት የለውም ። ከተጠያቂነትም አያድንም ። ምክንያቱም የሞራል ጥያቄ በጥሩውና በመጥፎው ወይም በሚጠቅመውና በሚጎዳው ወይም በሚያፀድቀውና

በሚያስኮንነው ወይም በፍትሃዊነትና በኢፍትሃዊነት ወይም በነፃነትና በባርነት ፣ወዘተ መካከል ያለውን ልዩነት አውቆ የሚበጀውን መምረጥና ማድረግ የመቻል ወይም ያለመቻል ጥያቂ ነውና ። ይህ ግዙፍና መሪር ውድቀት የሚመነጨው ደግሞ ወይ የምንነሳበት ምክንያት የተሳሳተ ሲሆን ወይም ደግሞ ከተነሳንበት መሠረታዊና ትክክለኛ ምክንያት እየተንሸራተትን የሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖችና ቢጤዎቻቸው ሰለባ ስንሆን ነው። በአገራችን እየገጠመን ያለው ከሁለቱም የሚመጣ ከባድ ፈተና ነው።

የፖለቲካ ባህላችንና ታሪካችን ከአንደኛው የጎሳ/የመንደር/የቋንቋ አጥንት ስሌት ፣ የብልግና፣ የግፍ፣ የሸፍጥ፣የሴራ ፣ የሙስና፣ ርካሽ የግል ወይም የቡድን ዝና ልክፍት፧ ወዘተ አገዛዝ ወደ ሌላኛው ተመሳሳይ ወይም ይበልጥ አስከፊ አገዛዝ ከመተላለፍ ክፉ አዙሪት መውጣት ካለበት የብልግና ፖለቲካ ጨዋታቸውን ብልፅግና በሚል ተደመሩ የሚሉንን የኢህአዴግ ፖለቲከኞች “የለም አካፋ አካፋ እንጅ የወርቅ ማንኪያ አይደለምና በቃችሁ” ማለትና ለዚሁ የሚመጥን ትግልን ማስቀጠል የግድ ይለናል።

አዎ! አገርን እንደ አገር የማስቀጠልና እና የተነሳንበትን የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ እውን የማድረግ ራእይና ግብ ከምር የሚያሳስበን ከሆነ እስከዚህ ድረስ ነው በግልፅና በቀጥታ መነጋገር ያለብን። በቀጥታና በግልፅ መነጋገርን ደናቁርትና ሸፍጠኛ ገዥ ቡድኖችን እና ቢጤዎቻቸውን እንደ መሳደብ እና አገርን አደጋ ላይ እንደመጣል መቁጠር የጀመርን እለት እኮ ነው አገርን እንደ አገር ለማቆየት ብቻ ሳይሆን የነፃነት፣የፍትህና የሁለገብ እድገት አገር ለማድረግ የሚያስችሉ የታሪክ ፣የእውቀትና የሞራል እሴቶቻችንን በአፍ ጢማቸው የደፉናቸው። ለዚህም እኮ ነው ከተነሳንበት መሠረታዊና ትክክለኛ ምክንያት እጅግ በሚያሳዝን አኳኋንና ድግግሞሽ እየተንሸራተትን የሸፍጠኛ፣ሴረኛና ግፈኛ ገዥ ቡድኖች ሰለባ በመሆን በግፍ የተገደሉ እጅግ አያሌ ቁጥር ያላቸውን ንፁሃን ወገኖች ወደ መቃብር በመሸኘት እኛም የቁም ሙቶች እየሆን የቀጠልነው። መቸም ልክ የሌለውንና ማቆሚያ ያላበጀንለትን የገንዛ ራሳችንን ውድቀት ፊት ለፊት ከመጋፈጥና የሚበጀንን ትርጉም ያለው የእርምት እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ የሰበብ አስባብ ድሪቶ እየደረትን ከግዙፉና መሪሩ ሃቅ የመሸሸግ ክፉ ልማድ ተጠናውቶን ነው እንጅ ለብዙ ዓመታት የኖርንበትና አሁንም እጅግ በአስከፊ ሁኔታ የምንገኝበት እውነታ ይኸው ነው ።

ከጎሳ/ከቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ እናተርፋለን በሚል አደገኛ ቅዠት ውስጥ ከሚገኙት ገዥ ቡድኖችና ሌሎች ፖለቲከኞች በስተቀር ከቁም ስቃይ እስከ ህይወተ ህልፈት ዋጋ የተከፈለበት ትግል መሠረታዊ ምክንያት ጨርሶ ሊፀዳ በማይችል ፖለቲካ ወለድ ወንጀል

የበሰበሰውና የከረፋው ኢህአዴጋዊ ሥርዓት ተወግዶ በእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ (ሽግግርና ምሥረታ) እንዲተካ እንጅ የብስባሹና የክርፋቱ አካል በመሆን ጥርሳቸውን ነቅለው ያደጉና ያገለገሉ ሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞች (ካድሬዎች) ተሃድሶ (reform) በሚል ነፍስ ዘርተውበት ሌላ የአያሌ ዓመታት መከራና ውርደት እንዲያስቆጥሩን አልነበረም።

አዎ! መሠረታዊ ምክንያታችን የአንዱን የጎሳ/የመንደር/የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ልክፍተኛ የበላይነት እጅግ በባሰበት ሌላኛው ልክፍተኛ ተክተን በግፍ ህይወታቸውን ያጡትንና የሚያጡትን ንፁሃን ወገኖች የትም መድረስ ባልቻለና በማይችል የደም እንባ እየተራጨን ወደ መቃብር በመሸኘት እኛም የቁም ሙቶች ሆነን ለመቀጠል አልነበረም። ነገር ግን መሆን የለበትም ያልነው ሆነና ጋዜጠኛና ደራሲ አበራ ለማ ፦

“አምና ታች አምና ከነበርንበት

ይኸውና ዞረን ዞረን ግጥም አልንበት” በሚል ከገለፀበት ጊዜና ሁኔታ በባሰ አኳኋን ውስጥ እራሳችንን አግኝተነዋል ።

ጋዜጠኛና ደራሲ አቤ ጉበኛ ከግማሽ ምእተ ዓመት በፊት አልወለድምን ለመፃፍ ያነሳሳውን ምክንያት በሚገልፅበት መግቢያው ላይ ወደ ምድረ አሜሪካ በሄደበት በአንድ ወቅት ያጋጠመውን አጋጣሚ በምሳሌነት ይጠቅሳል። በአረፈበት ሆቴል ምግብ ቤት ውስጥ ኢትዮጵያዊነቱን ያወቁ አሜሪካዊት ወይዘሮ በጠየቁት መሠረት በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ሲነጋገሩ ለኢትዮጵያ ክብር እንደነበራቸው ከገለፁለት በኋላ “ነገር ግን የህዝባችሁን በርሃብ ማለቅ ከልዩ ልዩ ጋዜጦችና መፅሄቶች ሳነብ እጅግ አዘንኩ” ሲሉት የተሰማውን ስሜት ” ኢትዮጵያዊ የሆነን ሁሉ በየደረሰበት ቅስሙን ሲሰብረው ወደ ኖረው የሃገራችን መከራ ገባን” ሲል ይገልፀዋል ። አለመታደል ወይም መርገምት ሆኖብን ሳይሆን የምንነሳበትን ትክክለኛ ምክንያት (the right cause) ማለትም የነፃነት፣የፍትህ፣ የእኩልነት፣የአብሮነት፣ የሰላምና የጋራ ብልፅግና የፖለቲካ ሥርዓት እውን የማድረግ ዓላማ ደጋግመን በመሳታችን ይኸውና ከግማሽ ምእተ ዓመት በኋላም ከሰብአዊ ፍጡር በታች በሚያውል ፍፁም ድህነት (ምፅዋእት ለማኝነት) ውስጥ መገኘታችን አልበቃን ብሎ ሸፍጠኛና ግፈኛ የጎሳ/የመንደር/የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ገዥ ቡድኖችና መሰሎቻቸው ባጠመዱብን ወጥመድ ውስጥ ገብተን ማንነት ላይ ባተኮረ ፖለቲካ ወለድ ሰይፍ የሚሰየፉትን ንፁሃን ዜጎች ሬሳ በየእለቱ የመቁጠሩን ዜና ተለማምደናዋል ።

አዎ! እኛ በእነዚያ በግፍ ከመጨፍጨፍ አልፎ አስከሬናቸው በገንዛ አገራቸው አፈር ውስጥ እንዳይቀበር በተከለከሉ አያሌ ቁጥር ያላቸው ንፁሃን ወገኖች ምክንያት ሃዘናችን እንኳ ቅጥ አጥቶብን የዓለም መሳለቂያ ስንሆን ሸፍጠኛ፣ሴረኛና ጨካኝ የገዥው ቡድን ባለሥልጣናት እጅግ አሳሳች በሆነ አቀራረብ የሸፍጡና የሴራው ዋና ተዋናይ በሆነውና የግል የፖለቲካ ዝና (narcissit political personality) ልክፍት በተጠናወተው ጠቅላይ ሚኒስትር መሪነት የሚተወነውን የፓርክ (የመናፈሻ) ፣ የችግኝ ተከላ፣ የመንገድ ላይ ፅዳት ፣ የዳቦ እደላ፣ የፒኮክ ምስል ተከላ፣ ከአዲስ አበባ አሥመራ ለተደጋጋሚ ሽርሽር መመላለስ ፣ ለተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች አመራር ተብየዎች ስላቅና ስድብ የተቀላቀለበት ሌክቸር የመስጠት፣ የጳጉሜን ቀናት የህዝብን ቀልብ በሚስቡ ስያሜዎች ሰይሞ ሽር ጉድ የማለት ርካሽ የፖለቲካ ተውኔትን ካላደነቅን ስለ አገር እንደማናስብና እንደማያገባን ሊያስረዱን ሲሞክሩ መስማት ህሊናን ያቆስላል።

ይህ ለምንና እንዴት ሆነ (ይሆናል)? ምክንያቱም ተረኛ የጎሳ/የመንደር/የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ነጋዴ ገዥ ቡድኖች መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥን እውን ለማድረግ ግዙፍና መሪር ዋጋ የተከፈለበት መሠረታዊ ምክንያት ህወሃትን ከቤተ መንግሥት ፖለቲካ አራጊና ፈጣሪነት ማባረር እንደሆነ አድርገው ትኩረታችንን ከእነርሱ እጅግ እኩይና አደገኛ የተረኝነት ፖለቲካ ጨዋታ ላይ እንድናነሳ ሊያደርጉን ሲሞክሩ ለምንና እንዴት ብለን አልሞገትናቸውም። እንዲያውም ይባስ ብለን የትም ቦታና ጊዜ ለሚፈፀም ወንጀልና ኮሽታ ሁሉ ተጠያቂው ህወሃት ነው ከሚል እጅግ ደምሳሳና የወረደ የፖለቲካ ጨዋታ መረባቸው ውስጥ ሰተት ብለን ገባንላቸው።

ህወሃት በበላይነት እየመራ በፈፀመውና ባስፈፀመው ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ልክ ሊጠየቅ አይገባውም ብሎ የሚከራከር ባለ ጤናማ ህሊና የአገሬ ሰው የሚኖር አይመስለኝም። በሌላ በኩል ግን ህወሃት በሚፈልገው ቅርፅና ይዘት ጠፍጥፎ የሠራቸው የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ፖለቲከኞች ሲያስፈልግ እንደ ደመ ነፍሱ አጋሰስ የሚጫነባቸውን ሁሉ አግበስብሰው በማጓጓዝ ፣ ሲያስፈልግ ደግሞ መብት የሚጠይቁ ንፁሃንን የቁም ስቃይ አሳዩልን ሲባሉ ገልብጠው በመግረፍ እና ባስታጠቋቸው ገዳይ መሣሪያ ግደሉ ሲሏቸው በመግደል መሉ ተሳትፎ ማድረጋቸው እየታወቀ ከልብ የመነጨና ወደ ተግባር የሚለወጥ ሳይሆን በለየለት የሸፍጥና የሴራ ካባ የተጀቦነ ይቅርታ ስለጠየቁ ከተጠያቂነት ነፃ ናቸው ብሎ የሚያምንና የሚከራከር ባለጤናማ ህሊና የአገሬ ሰው የሚኖር አይመስለኝም።

ከተነሳንበት መሠረታዊና ትክክለኛ የነፃነትና ፍትህ ሥርዓት ለውጥ እውን የማድረግ ምክንያት ወይም ዓላማ እየተንሸራተትን ወደ መጣንበት ክፉ አዙሪት ከሚዘፍቁን ምክንያቶች አንዱ በዚህ ረገድ ያለብን የአስተሳሰብና የአቋም ሽባነት ወይም ክሽፈት ነው።

አዎ! ከፍተኛና መሪር ዋጋ ያስከፈሉ ህዝባዊ እምቢተኝነቶች መሠረታዊ ምክንያት ከላይ እስከታች ለመግለፅ በሚያስችግር ሁኔታ በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የተዘፈቀው ፣ የበሰበሰውና የከረፋው ሥርዓተ ህወሃት/ኢህአዴግ እንደ ሥርዓት ተወግዶ ሁሉን አቀፍ በሆነ የጋራ ምክክርና መግባባት ላይ የሚመሠረት ዴሞክራሲያዊ የሽግግር ሥርዓት እውን እንዲሆን እንደነበርና አሁንም እንደሆነ የሚክድ የነፃነት፣ የፍትህ፣የእኩልነትና የጋራ ብልፅግና ሥርዓት ፈላጊ ኢትዮጵያዊ ይኖራል የሚል እምነት የለኝም። እናም ከዚህ እጅግ መሠረታዊ የሥርዓት ለውጥ እምነትና መርህ እየተንሸራተትን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በንፁሃን የቁም ስቃይና ደም የፖለቲካና የሞራል ሰብእናቸው የቆሸሸ (የተመረዘ) ሸፍጠኛና ሴረኛ ኢህአዴጋዊያን/ብልፅግናዊያን ሰለባ የሆን እለት ነበር ትክክለኛ አቅጣጫችንን የሳትነውና እውን እናደርገዋለን ያልነውን ግባችንን በአፍ ጢሙ የደፋነው።

በእውነት ስለእውነት እንጠያየቅ ካልን የእራስን ትክክለኛ የነፃነትና የፍትህ ሥርዓት ፍለጋ ትግል ምክንያት እና ራዕይ በሸፍጠኛና ሴረኛ የኢህአዴግ/የብልፅግና ፖለቲከኞችና ካድሬዎች እጅግ አደንዛዥ ዲስኩርና ተውኔት ተማርኮ ከማስረከብ የባሰ ምን አይነት ክፉ የፖለቲካና የሞራል ውድቀት ይኖራል?

የተነሳንበትን የነፃነት፣የፍትህ፣የእኩልነትና የጋራ ብልፅግ ሥርዓት እውን ከማድረግ ትክክለኛ ምክንያት (the right cause) ክፉኛ በመንሸራተታችን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ህወሃትን በአሽከርነት ሲያገለግሉ በንፁሃን የቁም ስቃይና ደም የተጨማለቀውን እጃቸውንና ህሊናቸውን በእውነተኛ የይቅርታ መንፈስ ለማደስ የሚያስችል እርምጃ በመውሰድ ለመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ዝግጁ ሆኖ ከመገኘት ይልቅ በይቅርታና እርቀ ሰላም ስም ቢሳለቁብን ለምን ይገረመናል?

በቀጥታና በግልፅ በመነጋገር ተገቢውን የጋራ መፍትሄ እውን ለማድረግ ካልቻልን ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ጥርሱን ነቅሎ ካደገበትና ካገለገለበት በጎሳ/በቋንቋ አጥንት ስሌት ላይ የተመሠረተ የብልግና ፣የጭካኔ ፣የሸፍጠኝነትና የሴረኝነት ሥርዓት ባገኘው ልምድ የመከረኛውን ህዝብ ስስ ሥነ ልቦና አሳምሮ በሚያውቀውና ይህንኑ ወደ ተዋጣለት የማታለያ ወይም የማደንዘዣ ተውኔትነት ቀይሮ በመጫወት የተካነ ጠቅላይ ሚኒስትር

በሚመራው ገዥ ፓርቲ (ብልፅግና ተብየ) እና መንግሥት ሥር ቀጣይ የመከራና የውርደት ዓመታትን ልናስቆጥር እንደምንችል ለመናገር ነብይነትን ጨርሶ አይጠይቅም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰሞኑ ለፓርላማ ተብየው (በመከረኛውና በደሃው ግብር ከፋይ ህዝብ ትክሻ ላይ የተጣበቀ ደም መጣጭ አካል ) ባቀረበውና ከሥራ ክንውን ይልቅ የርካሽ ፖለቲካ ፕሮፓጋንዳነት የተላበሰው ሪፖርት የእራሱን (የጠ/ሩን) እጅግ አደገኛ የፖለቲካ ሰብእና ይበልጥ ግልፅ አድርጎታል ። መቸም አይኔን ግንባር እና ጆሮየን ደግሞ ድፍን ያድርግልኝ የሚል የገዥው ቡድን አባል ወይም ግብረ በላ ወይም አድር ባይ ወይም እንደ ደመነፍሱ አጋሰስ ከከርሱ (ከሆዱ) መሙላት ውጭ ምንም ነገር የማይገደው ካልሆነ በስተቀር ለውጥ መጣ በሚል ዳንኪራ ረግጠን ሳናበቃ በአገራችን ውስጥ የሆነውንና እየሆነ ያለውን እጅግ ግዙፍና መሪር መከራና ውርደት የማይገነዘብና ህመሙ የማይሰመው የአገሬ ሰው ይኖራል ማለት ያስቸግራል ።

እናም አገር (ህዝብ) በእንዲህ አይነት ማቆሚያ ባልተበጀለት መከራና ውርደት ውስጥ በሚገኝበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ፓርክ (መናፈሻ) ፕሮጀክቱ “ገድልና” ይህን በማድረጉ ስለደረሰበት ትችት እና ስለ የተሃድሶው “አንፀባራቂ ውጤት” ሰፊ ጊዜ ወስዶ ሲደሰኩር (ሌክቸር ሲሰጥ) ትእግሥታችንን በእጅጉ ቢፈታተነንም የአገር ጉዳይ በመሆኑ ማዳመጥ ነበረብን። አዎ! እጅግ ብዙ ንፁሃን ዜጎች በብሄረሰብ ማንነታቸውና በሃይማኖታዊ እምነታቸው ምንነት ምክንያት ተለይተው በቁም ሰቆቃና በአሰቃቂ ግድያ ውስጥ የሚገኙበትን እውነታ እጅግ በሚያሳዝን የቅጥፈት አቀራረብ ደፍጥጦት ሲያልፍ ፣የአያሌ የአገሬ ገበሬዎችን ህይወት በቀጥታና የአገሬን ሸምቶ አዳሪ ህይወት ደግሞ በተዘዋዋሪ ከፍተኛ ሥጋት ላይ የጣለውን የአንበጣ መንጋ በስላቅ ጨርፎት ሲያልፈው ፣ ከኦሮሙማ (oromization) የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ ስትራቴጅ አንዱ የሆነውን የቋንቋ ጥያቄ ከጥያቄው መሠረታዊ መነሻ ውጭ አውጥቶ እርሱ በፈለገው መንገድ በመተርጎም “በማያሳስባችሁ አታስቡ” በሚል አይነት የሸፍጥ ምላሽ አልፎት ሲሄድ ከመታዘብ በላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩን አደገኛ የፖለቲካ ሰብእና እና ፍላጎት የሚነግረን የለም ።

ለነገሩ ከክስተቶች የትኩሳት መጠን ጋር አብረን የመሞቅና የመቀዝቀዝ ክፉ የፖለቲካ ልማድ ሰለባዎች የመሆናችን ነገር ፋታ አልሰጠን እያለ በመቸገራችን ከምር ልብ አላልነውም እንጅ የኦሮሚያው ገዥ የሽመልስ አብዲሳና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖለቲካ ጨዋታዎች የሸፍጡና የሴራው ፖለቲካ አካሎች እንጅ የተለያዩ አልነበሩም ። አይደሉምም። ሽመልስ የኦሮሙማን (oromization) የአጭር ፣የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ስትራቴጅ በአደባባይና ከአደባባይ በስተጀርባ በግልፅና በቀጥታ እየነገረ እንድንለማመደው ሲያደርገን

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግሞ በአደባባይ እየወጣ እውነተኛነትንና ቅንነትን የሚያንፀባርቁና ግልብ ስሜትን የሚያማልሉ ዲስኩሮችን በሰላ አንደበቱ እያዥጎደጎደና የመከረኛውን የዋህ ህዝብ ከንፈር እያስመጠጠ ለሽመልስ ሽፋን መስጠቱን ለመረዳት አዲስ አበባን ከልዩ ጥቅም ጥያቄ አልፎ ጠቅልሎ ለመቆጣጠር ከሚደረገው ጥረት ጀምሮ በመሬት ላይ እየሆኑ ካሉት እውነታዎች በላይ አስረጅ የለም።

በቤተ መንግሥት ርካሽ የፖለቲካ ጨዋታ አማካሪነት ሽር ጉድ የሚሉና የአድርባይነት ልክፍተኞች የሆኑ “ሰባኪያን/ሙሃዘ ጥበባት ” ታላቁን መጽሐፍ እንደሚመቻቸው እየተረጎሙ እና ከየሰፈሩ የሚቃርሙትን ተረትና ምሳሌ የሚያማክሯቸውን ሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞች በሚያስደስት መልኩ እያዘጋጁ “በጠቅላይ ሚኒስትራችን ድንቅ አመራር የአገር ትንሳኤ እውን ሆነ” የሚል አይነት በእጅጉ የወረደ ወይም የዘቀጠ ትርክት ሰለባዎች ለመሆን ካልፈቀድን በስተቀር መሬት ላይ ያለው መሪር ሃቅ ይኸው ነው።

የተነሳንበትን መሠረታዊ ምክንያት (የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ) በዴሞክራሲያዊ አርበኝነት ስሜትና የተግባር ውሎ እውን ለማድረግ ያለመቻላችን አሳፋሪና አስከፊ ውድቀት አቅጣጫችንን በማሳቱና በአንፃራዊነት ብሩህ ሆኖ የነበረውን የመድረሻችንን (የግባችንን) ራዕይ በእጅጉ በማደብዘዙ ይኸውና ሸፍጠኛና ሴረኛ ኢህአዴጋዊያን/ብልፅግናዊያን በለመዱት ወይም በሰለጠኑበት እኩይ የፖለቲካ ጨዋታ ተጠቅመው “ታሪካዊ የምርጫ ድል” ሊያበስሩን (ሊያረዱን ማለት ይሻላል) ከወራት በኋላ ቀጠሮ ይዘውልናል።

ለርካሽ ፖለቲካ ጨዋታቸው ከያሉበት ቦታና ሙያ አፈላልገውና እጅግ ሸፍጠኛና ሴረኛ በሆነ የፖለቲካ ሰብእናቸውና አንደበታቸው ሰብከው የምርጫ ቦርድ ተብየው አሻንጉሊቶቻቸው ያደረጓቸው ግለሰቦችም ( በዋናነት ወ/ት ብርቱካን መዴቅሳ ) ይህንኑ የትራጀዲ ( በእጅጉ አሳዛኝ) የፖለቲካ ድራማ “ታሪካዊ፣ ፍትሃዊና ነፃ” ለማድረግ ዝግጅታቸውን እያጧጧፉት እንደሆነ ያለምንም የህሊና ሃፍረት እየነገሩን ነው።

እናም እኛን በእጅጉ ሊያጠያይቀንና ሊያሳስበን የሚገባን ጉዳይ (issue) በተነሳንበት ትክክለኛ ምክንያት (the right cause) መሠረታዊ የምንነትና የእንዴትነት ጥያቄ ላይ ፀንተን ለመቆም ባለመቻላችን የምንሄድበት (የምንከተለው) አቅጣጫ ፈሩን የሳተ እና ሥራ ላይ የምናውለው የአፈፃፀም ስልት እራሱን ጠልፎ የጣለ በመሆኑ ልንደርስበት የምንፈልገው ግብም (ውጤትም) ገና ከጅምሩ በአስከፊ ሁኔታ የተጨናገፈ የመሆኑ መሪር እውነትነት ነው። በተተነሳንበት የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ ዓላማ ላይ ፀንተን ለመቆም ባለመቻላችን የምንከተለው አቅጣጫ እና

እውን ለማድረግ የምንፈልገው ውጤት/ ግብ ተለያይተው የመውደቃቸው (falling apart) አሳዛኝ ሁኔታ ከምር ሊያስቆጣን እና ፈጣንና ውጤታማ የእርምት እርምጃ እንድንወስድ ሊያስገድደን ይገባል።

የትየለሌ መስዋእትነት የተከፈለበት ህዝባዊ እምቢተኝነት መሠረታዊው ምክንያት ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የኖርንበትን ዴሞክራሲ አልባ የመከራና የውርደት ሥርዓትን እንደ ሥርዓት ከሥሩ በመንቀል የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥን እውን በማድረግ እንደ አንድ አገር ህዝብ ተከብረን ፣ ተከባብረንና በጋራ በልፅገን ለመኖር እንደ ነበር ህሊናውን ሸጦ ለማደር ለማይፈቅድ የአገሬ ሰው ግልፅና ግልፅ ነበር ። አሁንም ነው ።

እናም የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ትግል በሸፍጠኛና ሴረኛ የኢህአዴግ/የብልፅግና ገዥ ቡድኖች እና በአክራሪ የጎሳ/የመንደር/የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ልክፍተኞች መጨናገፍ የለበትም በሚል በፍፁም ሰላማዊ ትግል በመቀጠላቸው የጠባቡ እስር ቤት ሰለባዎች ከሆኑት እና አሁንም የንፁሃን እሥር ቤት ከመሆን ባልተላቀቀችው ኢትዮጵያ የተለያዩ ቦታዎች እልህ አስጨራሽ ብቻ ሳይሆን የህይወት መስዋእትነት የሚጠይቅ ሰላማዊ ትግል ከሚያዳሂዱ ወገኖች ጋር ፀንቶ መቆምን ከመቸውም በላይ ግድ ይለናል።

አገርን በመምራት ቀዳሚ ሥልጣንና ሃላፊነነት ላይ የተቀመጠ ፖለቲከኛ ሳያውቀው የሚፈፀም አገራዊና የዜጎችን ሁለንተናዊ ህይወት አደጋ ወይም ሥጋት ላይ የጣለ ወይም የሚጥል ጉዳይ የሚኖር ይመስል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከተፈፀመውና እየተፈፀመ ካለው ፖለቲካ ወለድ መከራና ሰቆቃ (አስከፊ ወንጀል) ቢቻል ነፃ ለማድረግ ቢያንስ ደግሞ አቅልሎ ለማሳየት ቁጥራቸው ቀላል ባልሆነ ተማርንና ተመራመርን በሚሉ ወገኖች የሚደረተው እጅግ አሳፋሪ የድርሳን ድሪቶን ነውር ነው ሊባል ይገባል ።

በአንፃሩ የመማርን ወይም የምሁርነትን ትክክለኛ ትርጉምና ባህሪ ተላብሰው ኢትዮጵያን

በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ለሁለንተናዊ ውድቀት የዳረጋት ሸፍጠኛና ሴረኛ

የጎሳ/የመንደር/የቋንቋ አጥንት ስሌት የፖለቲካ ሥርዓት ተወግዶ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ

ሥርዓት እውን ይሆን ዘንድ ከምር የሚጥሩ ምሁራን ከተናጠል ወይም ከትንንሽ ቡድኖች

አልፈው ትልልቅ የጋራ ማህበራትን (ድርጅቶችን) በመፍጠር የላቀ በጎ ተፅዕኖ ፈጣሪ

ሃይሎች እንዲሆኑ አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ ያስፈልጋል። እንዲህ በማድረግ ነው በአድር

ባይነት ጭራውን የሚቆላውን ወይም ግፈኛ ገዥ ቡድኖች በሆዴ (በሥራዬ) ቢመጡብኝስ

በሚል መከራና ውርደት ተሸክሞ ለመኖር (መኖር ከተባለ) የመረጠውን ወይም በየጎሳው

የፖለቲካ ከረጤት ውስጥ ተጠርንፎ የባለጌና ግፈኛ የጎሳ/የመንደር/የቋንቋ አጥንት ስሌት

ፖለቲካ ነጋዴዎች የጥቅም ተጋሪ የሆነውን ምሁር ተብየ ወደ ትክክለኛ የመማር ትርጉምና ህሊናው እንዲመለስ ማድረግ የሚቻለው።

ታዲያ የዚህ ሁሉ ጥረት ወይም እንቅስቃሴ ዓላማ ከምንነሳበት የነፃነትና የፍትህ ፍለጋ ትግል መሠረታዊ ምክንያት በተደጋጋሚ በመንሸራተት የሸፍጠኛ፣የሴረኛና የግፈኛ ገዥ ቡድኖችና ቢጤዎቻቸው ሰለባ የመሆናችን አሳዛኝ ታሪክ አብቅቶ በጋራና ባልተገደብ አገራዊ ምክክርና ውሳኔ የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርንና ግንባታን እውን ለማድረግ መሆኑ ፈፅሞ ሊዘነጋ አይገባውም።

ይህ የሚሆንበት ጊዜ እሩቅ እንደማይሆን ያለኝን ተስፋ እየገለፅሁ አበቃሁ!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop