የኢትዮጵያን ምድር ደሙ ሸፍኖታል፣
ልጆቹ በጅቦች በጭራቅ ታርደዋል፣
ታርዶ ግን አይቀርም አማራ ይነሳል!
መቃብር ፈንቅሎ መንበር ላይ ቁጪ ይላል!
በራሱ ተከብራ በእርሱ ኖራ ኮርታ፣
ኢትዮጵያ ሆነች የአማራ መስቀያ፣
የደሙ መፍሰሻ ምድረ ጎልጎታ!
ሰቀልነው ብለዋል በብአዴን አስረው፣
ዳሩ ግን አማራ ዳግም ሕይወት አለው፡፡
ክዶ ያስገደለው ስሞ ከርስቶስን፣
ይሁዳ እንደሞተው ሰልቅጦ ዲናሩን፣
ክትፎ ትን ብሎት ጠፊ ነው ብአዴን፡፡
የእየሱስን እድሜ ግፍ ጽዋ ጨልጧል፣
ገደልነው ቀበርነው ብለው ፎክረዋል፣
ነገር ግን አማራ ወደ ላይ ይወጣል፣
እንደ መድፍ ሮኬት ሽቅብ ይተኮሳል!
ልክ እንደ ክርስቶስ በአንቀልባ ተሰዷል፣
ተሰፈር መንደሩ በሙርጅ ተጠርጓል፣
እንደ ማርያም ጠላት ተመንበር ተነቅሏል፣
በጦር በገጀራ ተወግቶ ተገሏል፣
ዳሩ ግን አማራ በሳልስት ይነሳል፣
ወደ ሰማይ ጉኖ ተቦታው ቁጪ ያላል፡፡
ሄሮድስ እየሱስን በጣም ስለፈራው፣
ዘመቻውን ሲያውጅ አፍኖ ሊገለው፣
ህጻን ወንድ ልጆች ይረሸኑ እንዳለው፣
አማራን እንደ ነብር እንደ አንበሳ ፈርተው፣
ተማህጸን ጽንሱን እየገደሉት ነው፡፡
አብ ልጁን በምድር ፈተና እንደሰጠው፣
አማራንም አምላክ እየሞከረው ነው፡፡
መቃብርን ፈንቅሎ ወልድ እንደተነሳው፣
አማራም ፈተናን በጥሶ አላፊ ነው፡፡
ፍትፍት አጉራሹን ሕዝብ የከዳሃው ባንዳ፣
አገር ገንቢውን ሕዝብ የሸጥከው ይሁዳ፣
ብአዴን የተባልክ እርጉም ወለወልዳ፣
ሰላሳ ዲናርህን ለዘላለም ብላ!
ታረብ ተምራቡ እየዶለትክ ደባ፣
ተእጅ አዙር ቀኝ ገዥ እየፈተልክ ሴራ፣
አማራን ለመቅበር ሌት ተቀን ብትሰራ፣
ዳግም ላይሸወድ ቀጥ ይላል አማራ!
ክርስቶስ ንጉስ ነኝ የሚል ቃል ሳይወጣው፣
ፈሪስ ለቄሳሩ ዋሽቶ እንዳቃጠረው፣
ባንዳና ኸርማን ኮን አማራን የሚያማው፣
ንጉስ ታልሆንኩ ብሏል አማራ እያለ ነው፡፡
የዚህ ዓይነቱ ሸውክ ደባውና አላማው፣
አማራን መስቀል ላይ በምስማር መምታት ነው፡፡
አማራ በቅኔህ ሁሌ እንደምትለው፣
ለዱሩ ጸጥታ ነብሩ ቢታገሰው፣
ፍየል በምላሱ ላንቃውን ሞረደው፡፡
ታሪክ እንደሚያውቀው አማራ ጽኑ ነህ፣
ልክ እንደ ክርስቶስ ዘመንም ቢከዳህ፣
ቀጥቅጠን ገደልነው ቀብረነዋል ቢሉህ፣
ፈንቅለህ ተነስተህ ድል ትቀዳጃለህ፡፡
ለአገር ክብር ብለህ ብትታገሳቸው፣
እንደ አይጥ ቆርጥመው ተምድር ሊያጠፉህ ነው፡፡
አማራ ሆይ አንተም አምልካህን እርዳው፣
ወንድምህ ሲያጠፋ ምከረው ውቀሰው፣
ዳሩ ግን በመጥፎ በክፉ ዓይን አትየው፡፡
አማራ ጥፈቱ አንድ ብራና ነው፣
እንደ ጅል ቀዳደድህ መንደር አትጣለው፡፡
በአማራ ሰቆቃ እጅግ የረካኻው፣
ገለን ቀብረነዋል እያልክ የምትዝተው፣
በገነባት አገር ኑሮን የነሳሃው፣
ክፋትህ ተንኮልህ የሰዶማውያን ነው፣
ገሞራው ሲያነድህ አማራ እሚድን ነው፡፡
አያት ቅደመ አያቱ የሰጡት አደራ፣
ነፃነት ወይም ሞት የሚል ቃል ነውና፣
በጪራሽ አይኖርም ዝቅዝቅ ታይቶ አማራ!
እንደ ዘጽአት ሕዝብ ቢፈስ ቢፈናቀል፣
እንደ ሰማእታት ቢገረፍ ቢታሰር፣
እንደ ክርስቶስ እጅ ቢመታበት ምስማር፣
እንደ ጎን አጥንቱም ቢጨቀጨቅ በጦር፣
በብአዴን ታስሮ ተእንጨት ላይ ቢሰቀል፣
ገለነዋል ብለው ቢቆፍሩም መቃብር፣
ድንጋዩን ፈንቅሎ አማራ ይነሳል!
እንደ ቅዱስ በቅቶ ቃል ገብቶ መሐላ!
እንደ ድር አብሮ አግስቶ እንደ አንበሳ፣
ታሪክ ምስክር ነው ይነሳል አማራ!
ይነሳል! ይነሳል! ይነሳል!
በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
ጥር ሁለት ሺ አስራ ሁለት ዓ.ም.
እንደገና ጥቅምት አስራ ሶስት ዓ.ም.