March 20, 2013
10 mins read

ኢህአዴግ ተቃዋሚዎችን በኪራይ ሰብሳቢነትና በፀረ ዲሞክራሲያዊነት ፈረጀ

ኢህአዴግ ርዕዮተ ዓለሙን በሚገልፅበት “አዲስ ራዕይ” በተሰኘ መፅሔት የመጋቢት – ሚያዚያ 2005 ዓ.ም ዕትሙ ተቃዋሚዎችን በአስተሳሰብና በፍላጎት ደረጃ የኪራይ ሰበሳቢነት የተጠናወታቸው እና ፀረ-ዲሞክራሲያዊ ባህርይ የተላበሱ ናቸው አለ።

ቀደም ሲል አቶ መለስ ዜናዊ በዋና አዘጋጅነት ይመሩት የነበረውና በአሁኑ ወቅትም በግንባሩ ከፍተኛ አመራሮች የሚዘጋጀው አዲስ ራዕይ መፅሔት “ዲሞክራሲ፣ የአካባቢ ምርጫና የአገራችን ፈጣን ለውጥ” በሚል ርዕስ ባሰፈረው ሐተታ “የአገራችን የተቃዋሚ ኃይሎች በጥቅሉ በአንድ ቅርጫት ውስጥ አስገብቶ ባህርያቸውን ለማስቀመጥ የሚቻል ቢሆንም በመካከላቸው ያለውና ሊኖር የሚችለው ልዩነት ሲታሰብ ደግሞ በወቅቱ ከሚያራምዱት አቋምና ከሚጫወቱት ሚና በመነሳት ለያይቶ ማስቀመጥ ተገቢ ሆኖ ይገኛል። ለመነሻ ያህል ግን ሁሉንም የተቃዋሚ ኃይሎቻችንን የሚያመሳስለውንና ባህርያቸውንም በጋራ የሚወሰነውን ጉዳይ መመልከት ተገቢ ይሆናል። እንደማንኛውም ባልበለፀገና ለኪራይ ሰብሳቢነት በተመቸ ኅብረተሰብ ውስጥ እንደሚገኝ አብዛኛው ተቃዋሚ ሁሉ የአገራችን ተቃዋሚዎች አንድ ባህሪ አስተሳሰብና በፍላጎት ደረጃ ኪራይ ሰብሳቢነት የተጠናወታቸው መሆኑ ነው” ይላል።

ፅሑፉ አያይዞም “በብዙ ባልበለፀጉና የኪራይ ሰብሳቢነት የበላይነት ባለባቸው አገሮች በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ኪራይ ሰብሳቢ በመሆን አገሩንና ሕዝቡን በኪራይ ሰብሳቢነት አቅጣጫ ይመዘብራል። ይህን በመቃወም የሚደራጁ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ደግሞ በኅብረተሰብ ደረጃ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ሳይሆን በስልጣን ላይ ያለውን ዘራፊ መንግሥት አስወግደው ራሳቸውን ለምዝበራ በተመቸ ቦታ ለማስቀመጥ ይሻሉ። ከዚህ ለመገንዘብ እንደሚቻለው ገዢው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመንግሥት ሥልጣንን የሚፈልጉት አገር ለመለወጥ ሳይሆን ራሳቸውን ለመጥቀም ይሆናል። በሁለቱ መካከል የሚካሄደውም ትግል በአብዛኛው አንዱ ሌላውን በማጥፋት ላይ የተመሠረተ ይሆናል። ፈፅሞ መቻቻል የማይታይበትና በአንደኛው ኪሣራ ሌላው የሚያተርፍበት ወይም በአንደኛው አትራፊነት ሌላው የሚከስርበት የዜሮ ድምር ፖለቲካ የኅብረተሰቡ ፖለቲካዊ ሥርዓት መለያ ይሆናል”

አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ኢህአዴግ መራሹ መንግሥት ልማታዊ መሆኑን ምስክርነቱን የሚሰጠው ይኸው ጽሑፍ “በእኛ አገር የመንግሥት ሥልጣን ራስን (ግለሰብን) ለማበልፀግ ሳይሆን አገርን ለማልማትና ሕዝቡን ለመጥቀም ሲባል የተደራጀ ነው። ልማታዊ መንግሥታችንን ልማታዊ የሚያሰኘው አንዱና ዋንኛው መስፈርትም የመንግሥት ሥልጣን ራስን አለአግባብ ለማበልፀግ ሳይሆን ኅብረተሰቡን ለመለወጥና ለመጥቀም ሲል የሚጠቀምበት በመሆኑ ነው” ሲል ትንታኔውን ያቀርባል።

ተቃዋሚዎች ለምርጫ ያላቸው ፀረ-ዲሞክራሲያዊ አቋም እዚያው በዚያው የየድርጅቱን ውስጣዊ ፀረ-ዲሞክራሲያዊ ጥንቅር ያንፀባርቃል ብሏል። “ጉባዔዎች ወቅቱን ጠብቆ ማካሄድ፣ አባላት በነፃነት ሃሳባቸውን የሚገልፁበት ዕድል በሰፊው መክፈት፣ የአመራርን ተጠያቂነት ማረጋገጥ፣ ነፃና ግልፅ አሰራር ማስፈን ከተቃዋሚው ጎራ በተለይም በአመራሩ ዘንድ ባዕድ ነው። በዚህ ምክንያት ተቃዋሚው ኃይል በውስጡ ነፃ የኅሳብ ክርክርና ልዩነትን የማያስተናግድ፣ ስለዚህም ደግሞ ልዩነት አንስቶ መኖር የማይቻልበት ፀረ-ዲሞክራሲያዊ ድርጅቶች የበዙበት ሆኖ ይገኛል። ይህም እንደገና የተቃዋሚው ጎራ በልዩ ልዩ ሰባራ ሰንጣራ ምክንያቶች እንዲሰነጣጠቅና ልዩነት ሲኖር አንጃ መፍጠርን እንደተቀዳሚ አማራጭ እንዲወስዱ የሚያስገድድ ሁኔታ ላይ እንዲወድቁ አድርጓቸዋል” ሲል ይተቻል።

ጽሑፉ፤ 33 ድርጅቶች ሆነን ተሰባስበናል በማለት ራሱን አግዝፎ ለማቅረብ ሲሞክር ቆይቷል ያለውን ቡድን በምርጫው ለመሳተፍ ፍላጎት እንደሌለው እየታወቀ ከጅምሩ ቅድመ ሁኔታዎች በማብዛት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ያላደረገው አልነበረም ሲል ወቅሶታል። “አንድ ጊዜ በምርጫ ቦርድ ሲያሳብብ፣ ሌላ ጊዜ በገዢው ፓርቲ ላይ ክስ ሲደረድር ከከረመ በኋላ የምርጫው መጀመር ሲታወጅ፤ ለመመዝገብ ፍላጎቱም ዝግጁነቱ እንደሌለው በግላጭ አሳይቷል” ብሏል።

አዲስ ራዕይ በዚሁ ዕትሙ “ዘጠነኛ ድርጅታዊ ጉባኤያችንና ስትራቴጂያዊ ፋይዳዎች” በሚል ርዕስ ባሰፈረው ፅሑፍ በራሱ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር በመሬት ዝርፊያ፣ ግብር ባለመክፈል፣ የመንግሥት ገንዘብ በመመዝበር፣ በአድሎ እና በሙስና መልኮች መከሰቱን ያረጋግጣል። እነዚህ የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች ለመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት ሲሆኑ መቆየታቸውን ጠቅሶ በዚህ ድርጊት ዋንኛ ተጎጂው ምልዐተ ሕዝቡ ነው ብሏል።

ከኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች ጋር በተያያዘ ሕዝቡ በሁለት መልኩ ተጎጂ ሆኗል ይላል። “በአንድ በኩል ሰርቶ የመበልፀግ ዕድሉ ስለሚቀጭጭ በሌላ በኩል ደግሞ በተጨባጭ በሚፈፀምበት ምዝበራና አድልኦ ተጎድቷል” ሲል ይገልፃል።

በዚህ ሳምንት መጨረሻ በባህር ዳር ከተማ የሚካሄደው የኢህአዴግ 9ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ በአንድ በኩል ልማታዊ ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብና ተግባር በተነፃፃሪ ሰፊ የሕዝብ ንቅናቄ መልክ እየተፈፀመ የሕዝብን ተጠቃሚነት ባረጋገጠበት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኪራይ ሰብሳቢነት ላለመሞት በሚያደርገው መፍጨርጨር በሕዝብ ላይ ጉዳት ማድረስ በቀጠለበት፤ ነገር ግን ደግሞ ከምልዓተ ሕዝቡ ድሎቹን ለማስፋትና የተደቀኑበትን አደጋዎች ለመመከት በድርጅታችን ዙሪያ ተሰባስቦ በሚፋለምበት ወቅት የሚካሄድ ጉባዔ ነው ሲል ያሞካሸዋል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ለመጨረሻ ጊዜ በፓርላማ ተገኝተው የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ለማስወገድ መንግሥታቸው የገጠመውን ፈተና አስመልክተው ባደረጉት ንግግር “ወይ ኪራይ ሰብሳቢነት ያሸንፋል፣ ወይ ልማታዊነት ያሸንፋል” ሲሉ መረር ያለ መልዕክት ማስተላለፋቸው አይዘነጋም።¾

ምንጭ፡ ሰንደቅ ጋዜጣ ዛሬ ማርች 20 በአዲስ አበባ ታትሚ የወጣ

Latest from Blog

የኦህዴድ መራሹ ብልፅግና  መንግስት  በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል በንጹሀን  ዜጎች ላይ እየወሰዳቸው ያሉ የነፃ እርምጃ  ግድያዎች  መንግስት ያሰበውን የፖለቲካ ግብ ያሳካለታል  ወይ ? በኔ አመለካከት እነዚህ የንፁሃን ዜጎች  የጅምላ ግድያዎች  በሁለት በኩል እንደተሳለ ቢላዎ (double edge sword) ናቸው:: ፩- መንግስት እያሰላው

 የኦህዴድ መራሹ ጅምላ ግድያዎች ስሌት (ሸንቁጥ- ከምዕራብ ካናዳ)

January 24, 2025
እነዶ/ር ደብረፅዮን እና በጠ/ሚ ዐብይ አህመድ በተሾሙት የትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት መሪዎች እነጌታቸው ረዳ መካከል የነበረው አለመግባባት ተካርሮ ሰራዊቱን ወደውግንና አስገብቷል። የትግራይ ሐይል አዛዦች ትላንት ባወጡት መግለጫ ውግንናቸው ከእነዶ/ር ደብረፅዮን ጋር መኾኑን አስታውቀዋል።

በትግራይ የተፈጠረው ምንድነው?

January 23, 2025
የድሮ መሪዎች ያላደረጉትን ምሁር ጳጳሳቱ ያላስተዋሉትን ከፈረሰች ጎጆ ከባልቴት ቤት ገብቶ ክብሩን ዝቅ አድርጎ ውሀዋን ጠጥቶ ምግቧንም ተጋርቶ ያላለቀሰ ሰው ያንን ትይንት አይቶ ማን ይኖራል ከቶ? በዉሸት ፈገግታ ፊቱን አስመስሎ ፀሀይ የበራበት

ሰው በሰውነቱ – ከ ይቆየኝ ስሜ

Go toTop