ቁጥር 2
ባይሳ ዋቅ-ወያ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓቢይ የፖሊቲካ ሥልጣኑን ከተረከቡ ወዲህ “መደመርና” “ይቅርታ” የሚባሉ የአማርኛ ቃላት ከምንጊዜም በላይ ገበያ ላይ የዋሉ ናቸው ብል ማጋነን አይሆንብኝም። በቁም ነገር ብቻ ሳይሆን፣ በቀልድም ብዙ ብዙ አባባሎች በማሕበራዊ ሚዲያው ላይ እየተለጠፉ አስቀውናል። በፋሲካ ጾም መባቻ ሰሞን፣ የአዲስ አበባ ዶሮዎችም ተደምረናልና ዘንድሮ ለዕርድ አንቀርብም ብለው መግለጫ ማውጣታቸውን ባንድ የፌስቡክ ገጽ ላይ ተለጥፎ አስቆን ነበር። ሌላም ሌላም እንዲሁ የሚያስቁ ምስሎችና አባባሎች ተለጥፈው የመደመርን ምንነት ለማስረዳት ይሞክሩ ነበር። ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ “መደመር” ሲሉ ምን ማለታቸው እንደሆነ በቅርብ ባሳተሙት መጽሃፋቸው በተለያዩ መድረኮች ገለጻ የሰጡበት ስለሆነ በዚያ ላይ ጊዜ ማባከን አስፈላጊ አይመስለኝም። በዚህ ጽሁፌ ለማተኮር የፈለግሁት ግን ከመደመር እኩል በየመድረኩ ተደጋግሞ በሰፊው የተነገረለት “የይቅርታ ፖሊቲካ” እና ተያያዥ በሆነው የፍትሕ ነጻነት ላይ ነው። ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረውና የወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው ቁጥጥር ሥር ከነበሩ ከስድሳ በላይ የሚሆኑት የቀድሞ ባለ ሥልጣናትና አንዳንድ ግለሰቦች ክሳቸው ውድቅ እንዲሆን መደረጉን ተከትሎ ዜጎች በየጎሬያቸው ሲያጉረምርሙ መስማቴ ደግሞ የኔንም “ጥያቄ” እንዳነሳ ገፋፋኝና ይህንን ለብዙ ጊዜ ልጽፍ አስቤ እስከ ዛሬ በቀጠሮ ያሳደርኩትን ጉዳይ ላካፍላችሁ ወሰንኩ። ኢትዮጵያ ውስጥ አንዳችም የመንግሥት ውሳኔ ግልጽ በሆነ (transparent) መንገድ ለዜጎች ስለማይደርስ ለዚህ ጽሁፌ መነሻውም መድረሻውም በቴሌቪዥን የሰማሁት አጭር መንግሥታዊ መግለጫ ብቻ መሆኑ እንዲታወቅልኝ ከወድሁ ላሳስብ እወዳለሁ። የኢትዮጵያ ጋዜጤኞችም ለጉዳዩ ከኛ ከተራው ሕዝብ የተሻለ ቅርበት ቢኖራቸውም፣ ስለጉዳዩ ያላቸው ዕውቀት ግን ከኛ የተሻለ እንዳልሆነ እገምታለሁ።
የይቅርታ ፖሊቲካ ምንድነው?
አብዛኛው ሕዝብ “ይቅርታን” “ግራ ጉንጭህን በጥፊ ለመታህ ቀኙን አዙርለት” ከሚለው ኃይማኖታዊ መሪህ ጋር ያያይዙታል። ባገራችን ውስጥ በተለይም ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት፣ የሥልጣን ወይም የሙያ ወንበራቸውን ያላግባብ በመጠቀም ሰፊውን ሕዝብ ሲያስሩ፣ ሲገርፉ፣ ሲያሰቃዩና ሲገድሉ የነበሩትን ወንጀለኞች “ያለፈው አልፏል፣ የሞቱትን ለመመለስ አይቻልም፣ ሕይወት ግን መቀጠል ስላለበት ይቅር ተባብለን ያለፈውን ፋይል በሙሉ ዘግተን አዲስ ምዕራፍ እንክፈት” ማለት ነው ብለው የደመደሙም አይጠፉም። “ይቅርታ” የሚለው የዶ/ር ዓቢይ መሪህም በዚሁ መንፈስ ሥራ ላይ ይውላል ብለው ተስፋ ያደረጉ እንዳሉ ይሰማኛል። ትንሽ ግራ የሚያጋባው ግን እሳቸው እየደጋገሙ “ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት” ስለሚሉና፣ ሕገ መንግሥቱ ደግሞ፣ ወንጀል የሠራ ማንኛውም ዜጋ በሕጉ (ወንጀለኛ መቅጫ) መሰረት ይቀጣል ስለሚልና ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦች ለፍርድ ቀርበው ተገቢውን ቅጣት ይቀበላሉ ማለት ስለሆነ፣ የዶ/ር ዓቢይ የይቅርታ ፍልስፍ ጽንሰ ሃሳብ ወንጀለኛን ይቅር ለማለት እንዳልሆነ ይታየኛል። እንግዲህ መነሳት ያለበት ዋናው ጥያቄ፣ የይቅርታው ፖሊሲው በአገሪቷ የፍትሕ ሂደት ነጻነትን አክብሮ በፍትሕ አፈጻጸም ውስጥ ጣልቃ ሳይገባ ሊተገበር ይችላል ወይ? የሚለው ነው።
ይቅርታ በመሠረቱ አንድ ሰው ስሕተት ከፈጸመ በኋላ ስሕተት መፈጸሙን አምኖ ከተጸጸተና ይቅርታ እንዲደረግለት ከጠየቀ በኋላ “የሰው ልጅ ሁሌም ከስሕተት ነጻ አይደለምና ይቅር ብዬሃለሁ” ብሎ ተበዳዩ አካል የሚወስደው ወሳኝ እርምጃ ነው። ይህ ዓይነት የግለሰቦች ይቅርታን የመጠየቅና ይቅር የማለት ባሕል ማሕበረሰቡ ከልምድ ባካበተው አብሮ የመኖር ሂደት ልምድ የመነጨ ሲሆን ወሳኙ ነገር የበዳዩ ግለሰብ በድርጊቱ ተጸጽቶ ይቅርታ የመጠየቅና የተበዳዩ ይቅር የማለት የሞራል የበላይነት መኖሩ ነው። የሰው ልጅን ግላዊ ባሕርይ የሚያጠኑ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ በማሕበረሰብ ውስጥ ትልቁ ችግር ይቅርታ መጠየቅና ይቅር ማለት ነው ይላሉ።
“በወዲያኛው ዓለም አምላክ ፊት ለፍርድ ስትቀርብ ይቅር እንድትባል በምድር ላይ የበደሉህን ሁሉ ይቅር በላቸው” የሚለው ሰማያዊው ሕግ እንዳለ ሆኖ ምድራዊው ሕግ ግን በሰው ልጆች መካከክልና እንዲሁም በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን ግንኙነት ሰላማዊና ጤናማ ለማድረግ ከማሰብና ሰዎች ደግሞ ለሚፈጸምባቸው ምድራዊ በደል እዚሁ በምድራችን ላይ በምድራዊው ሕግ ካሳ ስለሚፈልጉ ያንን ለማሟላት የወንጀለኛ መቅጫ ሕጎች ይደነገጋሉ። ዘመናዊው የማህበረሰብ አስተዳደርም ከዘመናት ተሞክሮ በኋላ በሶስት የተለያዩ ተቋማት ማለትም፣ የሕግ አውጪ (Legislative – ፓርላማ ወይም የሕዝብ ተወካዮች)፣ የዳኝነት (Judiciary) እና አስፈጻሚ (መንግሥት – Executive) በተባሉ ራሳቸውን ችለው በሚቆሙና አንዳቸው በሌላው ሥራ ጣልቃ እንዳይገቡ ታስቦ በተሠራ ተቋም መሠረት ተዋቀረው እናያለን። እነዚህ ሶስት የማህበረ ሰብ ተቋማት የሕጎች ሁሉ የበላይ በሆነው በሕገ መንግሥቱ መሠረት ታማኝነታቸው ለሕገ መንግሥቱ ብቻ መሆናቸውን ሕገ መንግሥቱ ራሱ በግልጽ ስላስቀመጠ የአሠራር ችግር ይኖራል ተብሎ አይገመትም። የሕገ መንግሥቱ ቃላትና መንፈስ (letter and spirit) ያላንዳች ማወላወል ከተከበረ ማለት ነው።
የሰው ልጅ በዚህች ምድር ላይ ለሚፈጽመው በደል፣ ማለትም ወንጀል በዚሁ በምድሪቱ ላይ ማሀብረሰቡ በደነገገው ሕግ መሠረት ተገቢውን ቅጣት ተቀብሎ ከኃጢያቱ ነጻ ይሆናል እንጂ “ይቅር ብዬሃለሁ” ወይም “ጉዳይህ በወዲያኛው ዓለም ይታይልሃል” ተብሎ በነጻ አይለቀቅም። ያ እንዳለ ሆኖ ግን መንግሥት የበዳዮችን የግል ሕይወትና የፈጸሙትን በደል እንዲሁም ሌሎች ተጓዳኝ ኩነቶችን አመዛዝኖ ቅጣታቸውን እንዲቃልልላቸውና በይቅርታ የእሥራትን ዘመን እንዲያሳጥርላቸው ለፕሪዜዴንቱ አቅርቦ ለማሳጠር ይችላል። በሕገ መንግሥታችን አንቀጽ 71 መሠረት “ምሕረት” የማድረግ ሥልጣን ያለው ፕሬዜዴንቱ ብቻ ነውና! ይህ ሁሉ ግን ሊሆን የሚችለው ሕጉ በሚፈቅደው መሠረትና ተበዳዩ ለፈጸመው በደል ተመጣጣኝ የሆነ ቅጣት አስቀድሞ በዳኛው ከተወሰነበት በኋላ ብቻ ነው። በሕገ መንግሥታችን መሠረት፣ ሕጉ ከሚፈቅደው ውጪ ግን ማንም አካል አንድን በዳይ (ወንጀለኛ) ይቅር ሊለውና የክስ ሂደቱን ሲያስቆም አይችልም።
ይህ እንዳለ ሆኖ፣ ፖሊቲከኞች በተለይም ኢትዮጵያን በመሳሰሉ ታዳጊ አገራት የሥልጣን ወንበር ላይ ያሉ መሪዎች (አስፈጻሚ አካላት)፣ አብዛኛውን ጊዜ ለራሳቸው የፖሊቲካ ነጥብ ለማግኘት ከማለት፣ የነዚህን ሶስት ማህበረሰባዊ አስተዳደር ተቋማትን ሕጋዊ አሠራር የሚያዳክምና ሕጋዊ ያልሆነ የጣልቃ ገብነት እርምጃ ሲወስዱ ይስተዋላሉ። የፖሊቲካ ነጥብ ያስገኛል ወይም የአንድን አኩራፊ ቡድን ፍቅርና አመኔታ መልሶ ያስገኛል ብለው ካመኑበት፣ በፍትሕ ሂደቱ ውስጥ ጣልቃ ገብተው በወንጀል ተጠርጥረው ቁጥጥር ሥር የዋሉትን ግለሰቦችን ክስ ሲያቋርጡና ተጠርጣሪዎችን ሲያስፈቱ ይታያል። ይህ ሕገ ወጥ አሠራር ባገራችንም አሳሳቢ በሆነ መልኩ ተገባራዊ እየሆነ ነው። በርግጥ ኢትዮጵያን በመሳሰሉ ታዳጊ አገራት ተቃዋሚ ወገንን (ፖሊቲከኞችን)ያላንዳች መረጃ በወንጀል አስከስሶ ለፍርድ አቅርቦና ለረጅም ጊዜ ያለፍርድ ማጉላላት፣ ብሎም ለረጅም ዘመን እሥራት መዳረግ የተለመደ ስለሆነ አንደኛው ወገን ያለፈቃዱ ከሥልጣን ወርዶ በሌላኛው ሲተካ፣ አዲሱ ባላሥልጣን ደግሞ በቀድሞ ሥርዓት የታሠሩ የፖሊቲካ እሥረኞችን ክስ አቋርጦ በነጻ መልቀቅን ባገራችን ከንጉሡ በኋላ የመጡት ተከታታይ መሪዎቻችን በተግባር ሲያውሉት አይተናል። ይህ እንግዲህ አብዛኛውንም ጊዜ የፖሊቲካ ተቃዋሚ ድርጅቶች አንዳችም ወንጀል ሳይሰሩ፣ ከመንግሥት የተለየ አስተሳሰብ በማስተናገዳቸው ብቻ እንደ ወንጀለኛ ተቆጥረው ለእሥር የተዳረጉ ስለሆነ የክሳቸውን መቋረጥና መፈታታቸውን እልልልል እያልን በደስታ ስንቀበል ኖረናል። ውሎም ቢያድር ፍትሕ በመጨረሻ ላይ ታሸንፋለች (justice prevails) የሚለው መሪህ በተግባር ስለተተረጎመልን መደሰታችን ትክክለኛ ነበር። ለወደፊትም፣ የተለየ አስተሳሰብ በማስተናገዳቸው ብቻ የወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው ቁጥጥር ሥር ያዋላቸውን ዜጎች መንግሥት ክሳቸውን ቢሠርዝና ለነጻነት ቢያበቃቸው እልልልልል እያልን እንቀበላለን።
ችግሩ ያለው ሌላ ቦታ ነው። አሳሳቢውና የዚህ ጽሁፍም ዓላማ የሆነው ጉዳይ ስለ ፖሊቲካ እሥረኞች ክስ መቋረጥና መፈታታቸው ሳይሆን፣ ከጥቂት ሳምንታት በፊት፣ መንግሥታችን በከባድ የሙስና ወንጀል ማለትም ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ያገሪቷን ሃብት ለግላቸው በማዋል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ወይም ደግሞ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት በገፍ የጣሱና በዚህም ተጠርጥረው ቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ እያለ ክሳቸው እንዲቋረጥ ማደረጉ ነው። ይህ በእጅጉ ሊያሳስበን ይገባል። ሁለት ገጽታዎቹን ማየት እንችላለን። ወይ ግለሰቦቹ ከመጀመርያውም ቁጥጥር ሥር የዋሉት እና የተጠረጠሩበት ወንጀል ከፊተኛው አገዛዝ ጋር በነበራቸው ቁርኝነት ምክንያት እንጂ አንዳችም ወንጀል አልሠሩም ሲሆን ሌላው ገጽታ ደግሞ አዎ በርግጥ በወንጀል ተጠርጥረዋል፣ ወንጀሉን ለመፈጸማቸውም በቂ ማስረጃ አለ፣ ግን ባገሪቷ የሰፈነውን አለመረጋጋት ለማርገብ ሲባል የተጠርጣሪዎቹን ክስ መሠረዙ አስፈላጊ ነው ተብሎ ታምኖበታል የሚለው ይሆናል። የተጠርጣሪዎቹ ክስ መሠረዝ በመጀመርያው ምክንያት ከሆነ፣ የዶ/ር ዓቢይ መንግሥት ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ክሳቸውን ሠርዞላቸው ከእስር ቤት እንዳስፈታቸው የፖሊቲካ እሥረኞች ዛሬም እልልልል ብለን መቀበል አለብን። በአንጻሩ ግን ግለሰቦቹ በርግጥም ወንጀል ፈጽመው እና ወንጀሉን ለመፈጸማቸው በቂ ማስረጃና መረጃ እያለ “ለሰላምና መረጋጋት” ተብሎ ክሳቸው ተሠርዞ ከሆነ፣ ይህ ዓይነቱ ድርጊት መንግሥት ራሱ እንደ አንድ ተቋም በሕዝብ ላይ እየፈጸመ ያለ አንድ ከባድ ወንጀል ነው ብሎ መደምደም ይቻላል። መንግሥት የወሰደው እርምጃ ወንጀል የሆነበት ምክንያት ደግሞ፣ መንግሥት ማለትም አስፈጻሚው (Executive) አካል በፍትሕ ሂደት (Judiciary) ሥራ ጣልቃ በመግባቱ ብቻ ሳይሆን፣ በቂ ማስረጃ ባለማግኘቱ የተጠርጣሪዎቹ ክስ እንዲሠረዝ ለዳኛው የማቅረብ ሕጋዊ መብት ያለው ብቸኛው አካል ዓቃቤ ሕጉ ብቻ መሆኑ እየታወቀ፣ በማያገባውና ሕገ መንግሥቱ ከፈቀደለት ሥልጣን ገደብ አልፎ የተጠርጣሪዎቹ ክስ እንዲሠረዝ በማድረጉ የሕግ የበላይነትን ስለጣሰ ነው።
የወንጀል ድርጊት ምንጊዜም ወንጀል ነው። የወንጀል ድርጊት ፈጻሚው ማንነትና በማሕበረሰቡ ውስጥ ያለው ቦታ ወይም ሥልጣን ግለሰቡን ከወንጀለኛነት ነጻ አያደርግም። ስለሆነም የወንጀል ድርጊት የፈጸመ ማንኛውም ግለሰብ ወንጀሉን ስለመፈጸሙ በቂ ማስረጃ እስካልጠፋና የመረጃው አለመገኘትንም ዓቃቤ ሕጉ ለዳኛው አቅርቦ ካላሳመነ በስተቀር፣ ተጠርጣሪው በማንኛውም መሥፈርት ከፍርድ ነጻ ሊሆን ወይም ክሱ የሚሠረዝበት ምክንያት ሊኖር አይችልም። ይህ ማለት ግን የወንጀል ድርጊት መፈጸማቸው ተረጋግጦ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ተገቢው ቅጣት የተበየነባቸው ሰዎች በመንግሥት ምህረት አይደረግላቸውም ማለት አይደለም። ተጠርጣሪው ከተፈረደበት በኋላ የወንጀለኛው ማንነት እና በማህበረሰቡ ውስጥ ያለው በጎ እይታ እንዲሁም ወንጀሉ የተፈጸመበትን ሁኔታና አካባቢን በማገናዘብ መንግሥት ይቅርታ ሊያደርግለትና በነጻ ሊለቅቀው ይችላል። ይህ የመንግሥቱ ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው።
ለአንዳንድ የፖሊቲካ ትርፍ ሲባል ብቻ በተለያዩ ከባድ ወንጀሎች ተጠርጥረው ክሳቸው በፍርድ ቤት ሲታይ የነበረውን ከስድሳ በላይ ግለሰቦችን ፋይል መንግሥት ሲያስዘጋ፣ ክሳቸው በምን ምክንያት እንደተሠረዘ ከፍርድ ቤቱም ሆነ ከመንግሥት የተሠጠ አንዳችም መግለጫ አልነበረም። ለማንኛውም ግን ያገሪቷ የፍትሕ ሂደት ለመጀመርያ ጊዜ ከፖሊቲካ ጫና ነጻ ሆኖ በነጻነት ይጓዛል የሚለው ተስፋችን ቢመነምን ማንንም ሊያስገርም አይገባም። በሕገ መንግሥታችን መሠረትም የተለያዩና አንዳቸውም ባንዳቸው ሥራ ጣልቃ እንዳይገቡ ተደርገው የተዋቀሩ የሕግ አውጪ (ፓርላማ)፣ የዳኝነት (Judiciary) እና አስፈጻሚ (Executive) ሆነው የተዋቀሩ ተቋማት አንዳቸው ባንዳቸው ላይ ጫና እያሳደሩ የፍትሕን ሂደት የሚያዛንፉ ከሆነ፣ ሕዝባችን ትናንት የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቱ በገፍ ሲጣስበትና የፍትሕ ሂደትን መዛባት ተቃውሞ ከዳር እስከ ዳር ተባባሮ የገረሰሰውን ሥርዓት፣ ዛሬ ያለው መንግሥት ደግሞ ተመሳሳይ የሆነ የፍትሕ ሂደትን የሚያዛንፍ ድርጊት ሲፈጽም አይቶ ዝም የሚል አይመስለንም። እጅግ በጣም አደገኛ የሆነ አካሄድ!
ሌላው ተጓዳኝ ነገር ደግሞ የወንጀል ድርጊት (የጅምላ የሰብዓዊ መብቶችን ጥሰትን ከመሳሰሉት በስተቀር) በመሠረቱ የሚፈጸመው በጅምላ ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ ነው። በቅርብ “በምህረት” የተፈቱትም ተጠርጣሪዎች እያንዳንዳቸው የየራሳቸው የክስ ፋይል የነበራቸውና በዳኛም ፊት ይቀርቡ የነበሩት ለየግላቸው በተሠጣቸው ቀጠሮ መሠረት በግለሰብ ደረጃ ነበር። ስለዚህ ዓቃቤ ሕጉ፣ “በቂ ማስረጃ ስላላገኘሁባቸው ክሳቸው ይሠረዝ” ብሎ ለዳኛው አቀረበ እንኳ ቢባል፣ ተጠርጣሪዎቹ በግለሰብ ደረጃ በቀጠሮአቸው ቀን ብቻ በየግላቸው ዳኛ ፊት ቀርበው የክሳቸውን መሠረዝና ብሎም በነጻ የመለቀቃቸውን መልካም ዜና ይሰማሉ እንጂ፣ በተለያየ መዝገብ የክስ ፋይል የተከፈተባቸውን ተጠርጣሪዎች ዳኛው ይሁን መንግሥት ማን እንደወሰን እንኳ በማይታወቅ ሁኔታ በጅምላ ክሳቸውን ሠርዞ አንድ ላይ በነጻ መልቀቅ ዓይን ያወጣ የማን አለብኝነት መንግሥታዊ ጣልቃ ገብነት ነው ብል ከእውነት የራቅሁ አይመስለኝም።
መርካቶ ላይ ኪስ በማውለቅ በተራ ሌብነት ወንጀል የተጠረጠሩትን ዜጎች ለፍርድ አቅርቦ በማስረጃ የተደገፈ ብይን ተሰጥቶባቸው ቅልንጦ ሲወርዱ ባየው ዓይናችን፣ ሥልጣናቸውን መከታ አድርገው የሰፊውን ሕዝብ ሃብት የዘረፉትን ወይም የተለየ አስተሳሰብ በማስተናገዳቸው ብቻ ዜጎችን ለእስር ዳርገው ሲያሰቃዩ የነበሩ ተጠርጣሪ ግለሰቦችን ክስ ውድቅ አድርጎ በነጻ እንዲለቀቁ የሚያደረግ የፍትሕ ሂደትን የሚያጨናግፍ መንግሥታዊ ውሳኔ ሲሰጥና ተጠርጣሪዎቹ በነጻ ሲለቀቁ ማስተዋሉ፣ አይተን የነበረውን የለውጥ ተስፋ ጭላንጭል አጨልሞብናል ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም። ሕዝቡም በመንግሥትና ብሎም በፍትሕ ሂደቱ ላይ ያለው እምነት በጥልቁ መሸርሸሩ አይቀሬ ይሆናል።
ምንም እንኳ አሁን ያለውን መንግሥት በፈቃዳችን መርጠን በትረ ሥልጣን ያስጨበጥነው ባይሆንም፣ የለውጡ ቡድን በጊዜው ሕዝብ ሕዝብ ይሸት ስለነበር በእልልታ ተቀብለነው ነበር። መንግሥት ስለሆነ ብቻ ከኛ የተለየ ወይም የላቀ መብት ነበረው ወይም ይኖረዋል ብለን አልገመትንም፣ መገመትም አልነበረብንም። አንድ በርግጠኝነት ከኛ የተለየ ነገር ይኖረዋል ብለን የገመትነውና መሆንም የነበረበት፣ መንግሥት በተለይም ዲሞክራሲያዊ ነኝ ብሎን ራሱን እስከ ጠራ ድረስ፣ “ከባድ ኃላፊነትን” ነው። ይህ ኃላፊነት ደግሞ የሚመነጨው መንግሥቱ ራሱ በፈቃደኝነት “እወክላችኋለሁ” “አገለግላችኋለሁ” ብሎ በራሱ ላይ የጫነው ኃላፊነት ስለሆነ ሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ ሕገ መንግሥቱ ባስቀመጠለት የሥልጣን ገደብ ውስጥ እኛ ዜጎች የምንፈልገውን ብቻ የማድረግ ግዴታ አለበት ማለት ነው። ይህ መብቱ ሳይሆን ግዴታው ነው። ለኛ ግን በሕገ መንግሥቱ መሠረት እንዲያገለግለን የማስገደድ መብታችን ነው። በተረፈ ግን ዛሬ መንግሥት (አስፈጻሚው አካል) ሥልጣን አለኝ ብሎ ሕገ መንግሥቱ ካስቀመጠለት የሥልጣን ኃላፊነት ውጪ በፍትሕ ሂደት ጣልቃ በመግባት፣ ለጊዜው በግልጽ ባልተነገረን ምክንያት በወንጀል ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸውን ግለሰቦች ክሳቸውን ሠርዞ በነጻ መልቀቅ ማለት ራሱን የቻለ ከባድ ወንጀል መሆኑንና ሌላ ጊዜ ደግሞ ሌላ መንግሥት ሥልጣን ላይ ሲወጣ በሕግ የሚያስጠይቃቸው መሆኑን ካሁኑ ቢያውቁትና ተመሳሳይ ወንጀል ከመፈጸም ቢቆጠቡ የሕዝቡን አመኔታ ለማግኘት ይበጃል ባይ ነኝ። እንዳለ የሚቀር ነገር የለም አሉ አምባሳደር ካሳ ነፍሳቸውን ይማርና! ዛሬ ሥልጣን ላይ ነኝ ብሎ ሕገ መንግሥቱ ከሚፈቅደው ውጪ ሕጉም የማይፈቅድውንና ሕዝቡም የማይወደውን ድርጊት መፈጸም ሌላ ጊዜ በሕግ ጥሰት ማስጠየቁ አይቀርምና ከወዲሁ ቢታሰብበት ጥሩ ይመስለኛል።
ለማንኛውም፣ አገራችንን ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው ብቻ እንዲያስተዳድሯት ፈጣሪ ለመሪዎቻችን አስተውሎትን ያብዛላቸው። በቸር ይግጠመን።
*******
ጄኔቫ፣ ማርች 20 ቀን 2020 ዓ/ም