የካቲት 13 ቀን 2012 ዓም (21-02-2020)
በዚህ እርዕስ ላይ ለመጻፍ ያነሳሳኝ ምክንያቱ ግራ በሚለው የፖለቲካ አመለካከት፣አቋምና ዝንባሌ ላይ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ በሚባል ደረጃ በተለይም በአገራችን በኢትዮጵያ ውስጥ በህብረተሰቡ የሰፈነው ግንዛቤ የተሳሳተ መሆኑን በመረዳት እርማት እንዲደረግ ይረዳል በሚል ህሳቤ በመነሳት ነው።
ግራ የሚባለው የፖለቲካ አመለካከትና አሰላለፍ ለብዙሃኑ ጥቅምና መብት የተነደፈ ፍልስፍና መሆኑ ቀርቶ የጨካኞች፣ የገዳዮች፣የአምባገነኖች፣የጸረ አንድነቶች፣ብሔራዊ ስሜት የሌላቸው፣የአረመኔዎች፣የምግባረቢሶች፣ የምቀኞች፣ጸረ ሃይማኖትና የሁሉም ክፉ ነገር ተሸካሚ የሚያስፈራ የዲያቢሎስ ቡድን የሚሰገሰጉበት ዋሻ እንደሆነ ተደርጎ ይንጸባረቃል።ይህንን የተሳሳተ የጥላቻና የፍርሃት ወይም የሽብር ዘመቻ የሚያራግቡት የሕዝቡን መብት ገፈው በባርነት ደረጃ እረግጠው እያሰሩ ፣ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ወረራ የአገር ሃብትና ንብረት፣የተፈጥሮ ሃብትና ማዕድናትን በብቸኛ ባለቤትነት እዬመዘበሩ ለመኖር የሚሹ የአገር ውስጥና የውጭ ዘራፊዎች ናቸው።እነዚሁ ሃይሎች በሚነዙት የገንዘብና የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ጎን ለጎን ጥቅማቸውን የሚያስከብር፣ለሃገሩና ለክብሩ ደንታ የሌለው ቡድን ሥልጣን ላይ እንዲወጣ በማድረግ፣የመንግሥት ተቋማትን በመቆጣጠር ብዙሃኑ ተባብሮ በነሱ ላይ እንዳይነሳና የራሱንና ብሔራዊ ጥቅሙን እንዳያስከብር ሰጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛ ወይም በጎሳ፣በእምነት—ወዘተ ተከፋፍሎ እርስ በርሱ እዬተጫረሰ እንዲኖር በሚያቀብሉት የመሣሪያ ዕዳ ውስጥ እንዲነከር ያደርጉታል።ይህን በቅጡ ያልተገነዘበው ሰፊው ሕዝብ ለራሱ ጥቅምና መብት የቆመውን ፍልስፍና በተጻራሪ እያዬ ትጥቁን እንዲፈታ ተደርጎ እጣ ፈንታው ድህነት፣ስደት፣የእርስበርስ እልቂትና ጦርነት ሆንዋል።
በየአገሩ የተከሰተው አለመረጋጋት፣መፈራረስና ሰላም ማጣት የነዚሁ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱትና የዓለምን ሃብት በመዳፋቸው ያስገቡት የዘራፊዎች ገደብ የለሽ ስግብግብነት የወለደው ጭካኔ ውጤት ነው።ይህንን ሁሉ ወንጀል ሲፈጽሙ የሚያጭበረብሩበት ካባ ዴሞክራሲ የሚለው ስያሜ ነው።ለነሱ ዴሞክራሲ ማለት በፈለጉበት ቦታ በነጻ የሚዘርፉበትን ፍቃድና መብት የሚሰጥ ማለት ነው።በልማትና በእርዳታ፣በእምነት ነጻነት ስም የዘረፋ መረብ መዘርጋት ማለት ነው። እውነተኛው ዴሞክራሲ ደግሞ በብዙሃኑ ውሳኔና ፍላጎት፣ለብዙሃኑ ጥቅም የሚመሩበት እንጂ ለጥቂቶች ጥቅምና ውሳኔ የሚገለገሉበት ፍልስፍና እንዳልሆነ የፍልስፍናው ሊቆች የሰጡት አስተምሮና ሥራ ይመሰክራል። የግራ ፖለቲካ የብዙሃኑን ጥቅም ለማስከበር የተነደፈ ፖለቲካ እስከሆነ ድረስ እውነተኛው ሕዝባዊ ዴሞክራሲ ግራ ክንፉ የሚያራምደው የሶሻሊስት ወይም የህብረተሰብአዊ የፖለቲካ ፍልስፍና ነው ማለት ነው።
የግራ ፖለቲካ በሚለው አጠራር ላይ የሚንጸባረቀውን የተሳሳተ አመለካከት ወይም አስተሳሰብና ውዥንብር ለማረም የስያሜው መነሻ ምክንያት የሆነውን፣ ወቅትና ቦታውን የሚጠቁም የታሪክ ማስረጃ ማቅረቡ ግድ ይላል።
ግራ ወይም ቀኝ የሚለው አባባል በፈረንሳይ አገር የኢንዱስትሪ አብዮትን(Indutrial revolution)ምርትና የማምረቻ መሳሪያ ለውጥን ተከትሎ በተፈጠረው የህብረተሰብ እርከን ልዩነት ሳቢያ በተከሰተው የመደብ አሰላለፍ ፣በተለይም በማምረቻ መሣሪያው ባለቤትና ተቀጥሮ በሚሠራው ሠራተኛ መካከል የኤኮኖሚ ወይም የሃብት ኢፍትሃዊ ግንኙነት ያመጣውን ውዝግብ አስታኮ የተነሳ የፖለቲካ ፍልስፍና አመለካከት ነው።ይህ ፍልስፍና በሌሎቹም የከበርቴ ስርዓት በሰፈነባቸው አገሮች በመስፋፋት ዓለም አቀፋዊ ለመሆን በቅቱዋል።
በፈረንሳይ አገር በአሠሪውና በሠራተኛው መካከል የመብት መዛባትና መጣስ ሲጀምር ሰራተኛው ማጉረምረምና ብሶት ማሰማት ጀመረ። ያንን የመብት ጥሰትና የጥቅም ጥያቄ የሚያነሱ የሠራተኛው ተወካዮች በተደራጀና ባልተደራጀ መልኩ አድማ በመምታት ጥያቄያቸው መልስ እንዲያገኝ ትግል ጀመሩ።በወቅቱ የተከሰተው ችግር፣ድህነትና ጭቆና ከፋብሪካ ሠራተኛው ባሻገር የሌላውም ብዙሃን የጋራ ድርሻ በመሆኑ ሁሉም ብሶቱን የሚወጣበት መንገድ በናፍቆት ይጠብቅ ነበር።ይህ የመደብ አሰላለፍና ማህበራዊ ቀውስ የስርዓቱ ምርኩዝ የሆነውን የወታደሩን ክፍል ሳይቀር ሰልፉን ለይቶ እንዲቆም አስገደደው።ከዚያም ባለፈ
በጊዜው በትምህርት ደረጃቸው ከፍተኛ እውቀት ያላቸው ምሁራን ሚናቸውን እንዲለዩ አስገደዳቸው። በተለይም በህብረተሰብ፣በኤኮኖሚ፣በፍልስፍና፣በሕግ— መስክ የዳበረ እውቀት ያላቸውን በጎ አሳቢዎችና ተቆርቋሪዎችም ለችግሩ መፍትሔ ለመፈለግ ጥናትና ምርምር ለማድረግ ገፋፋቸው።ከጥናትና ምርምርም ባሻገር የሠራተኛው ትግል ተጠናክሮ መብቱን እንዲያስከብር የሚረዳ ድርጅታዊ መዋቅር እንዲፈጠር መመሪያና ምክር በማቅረብ ተባበሩ።ሶሻሊዝም የሚለውን ስያሜ የያዘ የፖለቲካ ፍልስፍና ነደፉ።ሶሻሊዝም ፣ሶሽያል ከሚለው ቃል ትርጉሙም ህብረተሰብአዊ/ብዙሃዊነትን/የሚያመለክት ስያሜ ነው።አንጥረኛው፣ ሠራተኛው፣ወታደሩ፣ አርሶ አደሩ፣ሙያተኛው መደብ እጅግ የላቀ ቁጥር ያለው የህብረተሰብ ክፍል አባል ነው።የዚህን ከፍተኛ ማህበረሰብ ጥቅምና መብት ለማስከበር የስርዓት አይነት ለመፍጠር የተነደፈ ፍልስፍና የሚከተል ማለት ነው።
በአሁኑ ጊዜ የከበርቴውን (የካፒታሊስቱን)ጥቅም ለማስከበር ደፋ ቀና የሚሉ ሃይሎች የፖለቲካ መስመር ወይም የለውጥ ሂደት በፍልስፍና ላይ የተመሰረተ መሆን አይኖርበትም፤በግለሰቦች ወይም በቡድን አባላት በጎ ፈቃድና ፍላጎት ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት ይላሉ።እራሱ ግለሰብም ሆነ ቡድን ፍላጎትና ዓላማውን ተግባራዊ ለማድረግ ንድፈ ራዕይ ከሌለው በደመነፍስ ህይወቱንና ኑሮውን መልክ ሊያሲዝ አይችልም።መነሻና መድረሻውን ካላወቀ እርባና ቢስ ይሆናል።ፍልስፍና አያስፈልግም የሚሉት ወገኖች እነሱ ጥብቅና የቆሙለትና የሚመሩበት የከበርቴ ፖለቲካ እራሱ ፍልስፍና መሆኑን አይገነዘቡም።ጥያቄው ለማን ጥቅም የቆመ ፍልስፍና ነው የሚለው ነው።የግራውን ወይም የሶሻሊስቱን ፍልስፍና ለመቃወም ሲሉ ከማይወጡበት የድንቁርና አሮንቃ ውስጥ ይገባሉ። የፖለቲካ፣የኤኮኖሚና ማህበራዊ ጥያቄ ደግሞ እንደዚሁ የሚመራበት ራዕይ ወይም ሳይንሳዊ ፍልስፍና ከሌለው በመሃል ውቅያኖስ ላይ አቅጣጫውንና መድረሻውን ለማወቅ የሚረዳው አመላካች ወይም ኮምፓስ የሌለው የሚዋልል መርከብ ማለት ነው።እጣ ፈንታውም መስመጥ ይሆናል።በግለሰቦች ደመነብስ ወሳኔና ፍላጎት የሚመራ ህብረተሰብ ለአምባገነን ስርዓት የተጋለጠ ይሆናል።አልፎ ተርፎም ለውድመትና ለአገር መፈራረስ ይዳርጋል። የከበርቴው ስርዓት ተጠሪዎች ዴሞክራሲ እያሉ ቢለፈልፉም ሕዝብ ያልመረጣቸውን ግለሰቦችና ቡድኖች በጉልበት ስልጣን ላይ እንዲቀመጡ ሲያደርጉ በታሪክ ተደጋግሞ ታይቱዋል።በእኛም አገር ውስጥ የሚታዬው ይኸው ነው።መጀመሪያ ህዋሃት/ኢሕአዴግ አሁን ኦህዴድ/ኢሕአዴግ ነገ ደግሞ ብልጽግና /ኢሕአዴግ።የስም ለውጥ በማድረግ እያወናበዱ መበዝበዝ!
በሶስቱም ስርዓቶች የከበርቴ አገሮች መንግሥታት እጆች አሉበት።ለተባባሪዎቻቸው የገንዘብ፣የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ድጋፍ እዬሰጡ አገራችንን ሊቆጣጠሩ የሚችሉበትን መንገድ ላለፉት 30 ዓመታት ሲያመቻቹ ኖረዋል፤አሁንም በማመቻቸት ላይ ይገኛሉ።ይህንን ዓለም አቀፍ የከበርቴውን መደብ የእጅ አዙርና ቀጥተኛ ወረራ ለመከላከል የግድ ህዝቡን ማእከል ያደረገ የፖለቲካ፣የኤኮኖሚና የማህበረሰብ ጥያቄዎችን ሊፈታ የሚችል ፍልስፍና መከተልና ሕዝቡን ማሰለፍ ይኖርብናል።የግዴታ ሶሻሊስት ወይም ኮምኒስት መባል አይኖርበትም፤የሕዝቡን መብት ለማስከበር እስከቻለ ድረስ ወሳኙ ሥራና ውጤቱ ነው።ለአገር ጥቅምና ሕዝቡ የሚሳተፍበት ስርዓት ከሆነ አገር ወዳድ ወይም ሕዝባዊ የሚለው ስያሜ በቂ ይሆናል።
ለግራው ወይም ለሶሻሊስቱ ፖለቲካ መስመር መሰረት የሆነው በ1871 እ.አ.አ. በፈረንሳይ አገር በፓሪስ ከተማ የተካሄደው ሕዝባዊ አመጽ ነው።ታሪኩ በአጭሩ ይህን ይመስላል።
በፈረንሳይ አገር በፋብሪካ ሠራተኞች፣በአርሶ አደሮች፣በወታደር ክፍል አባላትና በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ የፈጠረው የኑሮ ጫናና በመንግሥት አስተዳደር አለመርካት የተነሳ ፓሪስ ኮሚውን(Paris Commune) በመባል የሚታወቀውሕዝባዊ አድማ ለሶስት ወራት(ከ18 ማርች እስከ28 ሜይ 1871) የከተማዋን አስተዳደርና ስልጣን ለመያዝ ቻለ።ይህ የሥልጣን ባለቤትነት ግን ብዙም አልቆዬም።የተወገደው ሥርዓት እንደገና ሃይሉን አሰባስቦና ተጠናክሮ ያሶገደውን ሃይል በጉልበት አሶግዶ ከመንበሩ ላይ ተመልሶ ተቀመጠ።የዚህ ውድቀት ተመክሮ የሕዝቡን ጥያቄ በሚደግፉት በኩል የማህበረሰቡን ጥያቄ ለመፍታት የሚችል የተደራጀ ሃይል የፖለቲካ ፍልስፍና ይዞ መነሳት እንዳለበት እንዲገነዘቡ አደረጋቸው።ከጥቂት ዓመታት በዃላም እንደ ፖለቲካ ሃይል ሆኖ መሳፍንትና ባላባቶች ይቆጣጠሩት በነበረው ምክር ቤት(ፓርላማ) ውስጥ በ1789 እ.አ.አ. የስርዓቱ ተቃዋሚ ወኪሎች ተመርጠው ለመግባት ቻሉ።በፓርላማው ውስጥ ሲገቡ የተሰጣቸው መቀመጫ ከፓርላማው አፈጉባኤ/ሊቀመንበር መቀመጫ ወንበር በእስከ ግራ በኩል የነበረው ቦታ ነበር።ቀድሞ የነበሩት የመሳፍንቱና የባላባቱ ተወካዮች በቀኝ በኩል የነበረውን መቀመጫ ይዘውት ነበር።እንግዲህ ግራና ቀኝ የሚለው የፖለቲካ መስመር ስያሜ የሁለቱን ተቃራኒ ክንፎች አቀማመጥ ተከትሎ የመጣ ነው።እስከአሁንም ድረስ በአንዳንድ አገሮች የፓርላማ ወንበር አቀማመጥ ይህንኑ የተከተለ ነው።በተለይም በእንግሊዝ ፓርላማ ውስጥ በግልጽ ይታያል።ሌበር ፓርቲ በግራ፣ኮንሰርቫቲቩ በቀኝ ።
ይህ ብቻ ሳይሆን የግራ ፖለቲከኞች ወይም ሶሻሊስቶች መለያ የሆነው ቀይ ባንዲራም አነሳሱ ከፓሪስ ኮሚዩን ህዝባዊ አመጽ ጋር የተያያዘ ነው።አማጽያኑ በነበረው ባለሶስት ቀለም የፈረንሳይ ባንዲራ ፈንታ በዬህንጻውና በዬአደባባዩ ቀይ ባንዲራ እንዲውለበለብ አደረጉ።ከዚያም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የሶሻሊስቶችና በሶሻሊስቶች የሚመሩ አገሮች አርማ ለመሆን በቅቱዋል።የሚሰጠው ትርጉምም በመደብ ትግል ከተከፈለው መስዋዕትነት ጋር የተያያዘ መሆኑን የሚያበስር ነው።
የመሳፍንቱና የባላባቱ ስርዓት እዬሙዋሸሸና እዬተዳከመ ሲሄድ፣የምርት መሳሪያውና ግንኙነቱ ሲቀዬር፣የሳይንስ ምርምርና ግኝት እዬዳበረ ሲመጣ ህብረተሰቡ ለአዲስ አመለካከትና ባህል በቃ።ከግምታዊና ከሃሳባዊ ወደ ተጨባጭ እይታ አሻገረው።ይህንን ለውጥ ያበሰረው የኢንዱስትሪው ባለቤት አዲስ መጡ ክፍል የፖለቲካና የኤኮኖሚ ሃይል ሆኖ የስርዓቱ ባለቤት ሆነ።ውሎ አድሮ ይህም ስርዓት ከራሱ መደብ ውጭ ለሌላው ጥቅምና መብት የቆመ አልሆነም።እያንዳንዱ ስርዓት ሲፈጠር አብሮት የሚወለድ ተጠቃሚና ተጎጂ፣ደጋፊና ተቃዋሚ አካል ይዞ መምጣቱ አይቀሬ ነውና በዚህም የከበርቴ ስርዓት ሁሉም የህብረተሰብ አባል የጥቅም ግብግብ ውስጥ ገባ።የመደብ ትግሉ ተካረረ።
የከበርቴ መደብ፣አቅሙ እዬጎለበተ ከጎጆ አምራችነት የትላልቅ ማምረቻ መሣሪያዎች ባለቤትነት ሲሻገር ለጨመረው የምርት ብዛት የሚሆን ጥሬ ዕቃ ፍለጋ፣ከአገሩ ድንበር አልፎ የሌሎች አገሮችን ማሰስ ጀመረ።በጉልበት የቅኝ አገዛዝ መዳፍ ውስጥ አስገብቶ ዓይን ያወጣ ዘረፋ ሲያካሂድ በውስጥና በውጭ ተቃውሞ ተነሳበት። በወቅቱ ከመሳፍንቱና ከባላባቱ አንጻር ሲታይ ግራ ተብሎ የተመደበው የዘመኑ ተራማጅ ከበርቴ ከጊዜ በዃላ ጡንቻ አውጥቶ የሰራተኞችን፣ብሎም የሰፊውን ሕዝብ መብትና ጥቅም መዳፈር ሲጀምር ዓይንህን ላፈር ተባለ።ወረራ ባካሄደባቸው አገሮች ውስጥ የሚፈጽማቸው ወንጀሎች ፍጹም ጨካኝነቱን በግልጽ አሳዬ።ይህንን አይን ያወጣ ዘረፋና ወረራ የሚቃወሙ ተራማጅ የግራ ሃይሎች ትግላቸው ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው በማድረግ ፍልስፍናቸው ከድንበር ያለፈ ሆነ።ተቀባይነቱም እያደገ መጣ።የቀኝና የግራ የፖለቲካ አመለካከቶች ተጻራሪ የትግል ጎራዎች ሆነው እስከ አሁን ድረስ ዘልቀዋል።
በዓለም ላይ የሰፈነው የከበርቴ ስርዓት ለዘመናችን ችግር ፈጣሪ እንጂ ችግር ፈች አልሆነም።የዓለም ሕዝብን ለቀውስና ለጦርነት ዳረገው እንጂ ሰላም አላወረደለትም።ያለፉት ሁለት ታላላቅ የዓለም ጦርነቶች የዚሁ መዘዝ የፈጠራቸው ናቸው።አሁንም በያገሩ የሚካሄዱት ግጭቶች የዚያው ውጤቶች ናቸው።አሁን በዘመናችን አገራትን በቀጥታ ከመውረርና ወታደራቸውን ከማስጨረስ ለሆዱ ያደረ ባንዳ መንግሥት ሥልጣን ላይ ወጥቶ የወገኑንና የአገሩን ጥቅም አሳልፎ በመስጠት እንዲተባበር አድርገውታል።የአገርን ልዑላዊነትና አንድነት ለመፈታተን በሃይማኖትና በጎሳ የእርስ በርስ ትርምስ ውስጥ ማስገባት፣ደጋፊን እያጠናከሩ ተቃዋሚውንና አገር ወዳዱን ማጥፋት ስልታቸው ሁኖዋል።ይህን ሁሉ ሲያደርጉ ከሚሰጡት ምክንያት ዋናው ሕዝቡን ለሽብርና ለድህነት የዳረገው የግራ ወይም የሶሻሊስት ስርዓትና ፖለቲካ ነው የሚል ነው።ሕዝቡ ይህንን እንደ እውነት ተቀብሎ ለራሱ ጥቅምና መብት የተነሳውን ወገን በጠላትነት እንዲፈርጅና እንዲሸሽ ያላባራ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በስፋት ይሰራጫል። በዚህም ግራ የሚባለው ቃል ሲነሳ የሚበረግገው ቁጥሩ ቀላል አይደለም።ሌላው ቀርቶ የግራ አስተሳሰብ ዝንባሌ የነበረው ሳይቀር ውዥንብር ውስጥ ገብቶ በነጻነትና በልማት ስም ለጠባብ ጎሰኝነትና ለከበርቴው የዘረፋ ዘመቻ እጁን የሰጠው ቁጥሩ ቀላል አይደለም። የግራ ፖለቲካ ግን መመሪያና ዓላማው በቀኙ እንደሚወራበት ሳይሆን ከዚያ የተለዬ ነው።
በአጭሩ የግራ ፖለቲካ ሲተነተን ማህበራዊ ፍትህ፣ማህበራዊ ባለቤትነት፣ማህበራዊ ሰላም፣ማህበራዊ እኩልነት፣ማህበራዊ ጥቅም፣ማህበራዊ አብሮነት፣መተሳሰብ፣ከግለኝነትና ከራስ ወዳድነት የራቀ የጋርዮሽ ስሜት፣የጋራ ባህል፣የጋራ አገር፣የጋራ እምነት፣የጋራ ማንነት ማለት ነው።ለጋራ ችግር የጋራ መፍትሔ መፍጠር ማለት ነው።በጋራ ለተሻለ ኑሮ የሚበቁበት፣ከዕድገት ደረጃ ላይ የሚደርሱበት የፖለቲካ ጎዳና ማለት ነው።የግራ ፖለቲካ ጸረ ዘረኝነት፣ጸረ አምባገነንነት፣ጸረ ወረራና ዘረፋ ማለት ነው።የሰውን ልጅ እኩልነት የሚያምንና የሚያስከብር ፖለቲካ ማለት ነው።ህብረተሰቡ የተጋለጠበትን ድህነት፣በሽታ፣ ዘረፋ፣አምባገነንነት ዘረኛነት፣ጎሰኛነት፣ድንቁርናና ዃላቀርነት…ወዘተ ለማጥፋት የተነደፈ የፖለቲካ ፍልስፍና ማለት ነው።
የግራ ፖለቲካ በአውሮፓ የከበርቴ አገሮችም ጠንካራ መሠረትና ደጋፊ ያለው ፖለቲካ ነው።ለሰራተኛው መደብ፣ለብዙሃኑ ሕዝብ፣ለሴቱ፣ለስደተኛው፣ለሰው ሳይቀር ለእንስሳት መብት የሚታገለው የግራ ፖለቲካ መስመር ተከታዩ ነው።እንደ ከበርቴው የቀኝ ክንፍ ቢሆንማ ኖሮ አንድም የውጭ አገር ዜጋ በተለይም ጥቁር በአውሮፓና በሌሎቹም አገሮች ዝር አይልም ነበር።በግራው ክንፍ ትግል እኛም ኢትዮጵያውያኖች በሰላም ለመኖር ችለናል።የግራ ፖለቲካ ዓለም አቀፋዊ እንጂ በራስ ክልል ውስጥ የሚያምንና ገፊና ጎሰኛ ስሜትን የሚያዳብር አይደለም።ሌላውን አያፈናቅልም፣መብቱን አይገፍም።ሰብሳቢና አቃፊ ነው።የክልል አጥርና ገደብ ፈጣሪ ሳይሆን ድንበረቢስና ዓለምአቀፋዊ ነው።
የሰው ልጆችን ሁሉ መብት የሚያስከብር እንጂ መጣስን መመሪያው አያደርግም።መብት ሲባልም ማንኛውም ሰው የፈለገውን እምነት የመከተል፣ በፈለገበት ቦታ የመኖር ፣የመሥራትና ሃብት የማፍራት ፣ባህልና ቋንቋው ተከብሮለት ፣ከሌሎቹ ጋር ተከባብሮ እንዲኖር እንጂ እንዲነጣጠል አይፈቅድም።እያንዳንዱ በግል ተነሳሽነት ለራሱ፣ለቤተሰቡና ለህብረተሰቡ የሚጠቅም ሥራ እንዲሠራ ያበረታታል እንጂ አያቀጭጭም።ዕውቀትና የፈጠራ ችሎታ ወይም ውጤት የብዝበዛ መሣሪያ ወይም የንግድ ሸቀጥ ሳይሆን በቅድሚያ ዓላማው ለሕብረተሰቡ ጥቅም እንዲውል ነው።በተለይም ትምህርት፣መድሃኒትና የጤና አገልግሎት፣የመኖሪያ ቤት፣የምግብ አቅርቦት የሰው ልጅ ማግኘት የሚኖርበት የህይወት ጥያቄ ስለሆነ የትርፍ ማግበስበሻ ውድ ዕቃ እንዳይሆኑ ይከላከላል።ለሕዝቡ በቀላሉ የሚዳረሱበትን መንገድ ይተልማል።በብዙሃኑ ስቃይና መከራ ጥቂቶች እንዲንደላቀቁ አይፈቅድም።
ቀደም ሲልም ሆነ አሁን የግራውን ፖለቲካ ለማጨናገፍና ፈሩን ለማሳት በግራ ፖለቲካ ስም የሚንቀሳቀሱ ግን የግራ ፖለቲካ ጸር የሆኑ ሃይሎች መነሳታቸውን በታሪክ አይተናል።በኢትዮጵያም ውስጥ እንዲሁ።የተማሪውን አገር ወዳድና ለዴሞክራሲ ለውጥ የተደረገ እንቅስቃሴ ተከትሎ የመጣው የደርግ ወታደራዊ አምባገነን መንግሥትና በነጻነት ስም አገር ለመቆራረስ ጫካ ገብተው የነበሩ በውጭ ሃይሎች እርዳታ አሁን በሥልጣን ላይ የተቀመጡት የጎሳ ድርጅቶች የአገር ወዳዱ ጸር፣የዓለም አቀፉ ወረራ የከበርቴው ጉዳይ አስፈጻሚዎች ናቸው። እነዚሁ ጸረ ግራ ፣ጸረ አገርና ጸረ ሕዝብ የሆኑት ቡድኖች ተወካይ የሆነው አሁን ሥልጣኑን የያዘው መንግሥት ጠ/ሚኒስትር ተወልዶ ባላዬውና በማያውቀው ጊዜ በ1966 የተካሄደውን ሕዝባዊ ትግል ዓላማ ቢስ እንደሆነ፣ ወጣቱም(እናቼንፋለን፣እናሸንፋለን) ቼ እና ሼ በሚሉ በፊደላት ተራ ልዩነቶች የተጋደለ ከንቱ ትውልድ አድርጎ ተሳልቆበታል። ትውልዱን በጅምላ የስልሳው ትውልድ በሚል ስያሜ በደርግና በነጻ አውጭ ነን በሚሉ ጸረ ኢትዮጵያ ድርጅቶች የተፈጸመውን ወንጀል ሊያሸክመው ይሞክራል። ለሰው ሲል፣ለአገሩ እድገትና መሻሻል፣ለስርዓት ለውጥ አንድ ህይወቱን አሳልፎ ለመስጠት በተሰለፈና በሰጠ፣ከሞት ተርፎም በያገሩ የስደት ኑሮ የሚገፋውን አንጋፋ አገር ወዳድ የውግዘት ዒላማ አድርጎታል።
እንደ እውነቱ ከሆነ አንጋፋው ትውልድ ከአገሩ አልፎ ተርፎ ለሌሎች አገሮች ነጻነት ድምጹን ያሰማ ጀግና ትውልድ ነበር።የቬትናም ሕዝብ በናፓል ቦምብ ሲደበደብ፣የዚምባብዌ(የሮዴሽያ)፣የናሚቢያ፣የአንጎላ፣የደቡብ አፍሪካ፣የሌሎችም አገሮች ሕዝብ በነጮች የቅኝ አገዛዝ መከራውን ሲቆጥር አደባባይ ወጥቶ ተቃውሞውንና ለሕዝቡ አጋርነቱን የገለጸ ትውልድ ነው።ለማዳጋስካር ሕዝብ የእኩልነቱን ደረጃ በገሃድ ነጮች በሚቆጣጠሩት በራሳቸው ከተማ ያሳዬና ሕዝቡን ለትግል ያነሳሳ ትውልድ ነው።አንጋፋው ትውልድ ለጥቁር ሕዝብ ነጻነት ፊትአውራሪ የሆኑት ያባቶቹ ልጅ ነበር።
ትውልድ በጅምላ አይወነጀልም።በማንኛውም ትውልድ አጥፊና አልሚ አለ፣ይኖራልም።የስልሳው ትውልድ ውስጥ አሁን አገራችን ካለችበት መቀመቅ ውስጥ የከተቱዋት ጎሰኞች እንዳሉ ሁሉ ከስልሳዎቹ ወዲህ በተፈጠረው ትውልድም ውስጥ እንዲሁ ጎሰኞችና አገር አዋኪዎች አሉ።እንደውም ይባስ ብሎ ለአገሩ ደንታ የሌለው ትውልድ፣ሕዝብ የሚፈናቀልበት ትውልድ፣የአገር አንድነት ፈተና ውስጥ የገባበት ትውልድ፣የአገር ሃብትና ንብረት የሚቸበቸብበት ትውልድ፣ የሰው ልይ ተዘeዝቆ የሚሰቀልበት ትውልድ፣በቆንጨራ የሚከተፍበት ትውልድ አሁን ባለው ትውልድ ዘመን ነው።በዚህም ከንቱ ትውልድ ውስጥ ለአገሩና ለወገኑ ህይወቱን አሳልፎ የሰጠና የሚሰጥ ጀግና አገር ወዳድ ትውልድም እንዳለ መካድ አይገባም።
የየካቲቱን ሕዝባዊ ትግል የመራው የተማሪው/የወጣቱ ክፍል የተሰለፈውና ህይወቱን የገበረው
የዴሞክራሲ መብት ይከበር፣መሬት ላራሹ ይሁን፣ሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም፣ዳቦ ለተራበ፣ውሃ ለተጠማ፣የትምህርትና የሥራ ዕድል ለሁሉም…ወዘተ የሚሉ መርሆችን ይዞ እንጂ እንደአሁኑ ወጣት ጎሳ ለይቶ፣ ቆንጨራ መዞ ልጋደል፣አገር ትበታተን አላለም።የነበረው እይታ በክልል የታጠረ ሳይሆን ዓለምአቀፋዊ ነበር፤ነውም።
በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የግራ ፖለቲካ አራማጁን እርጉም የስልሳው ትውልድ እያሉ ፣ ሰይጣናዊ ስዕል እዬሳሉ ሕዝብ እንዲርቀውና እንዲፈራው፣በማድረግ እራሳቸውን እንደ በጎ አሳቢ የቀኝ ፖለቲካ አራማጆች ነን በማለት በአደባባይ የሚለፍፉtte፣ የቀኞቹን ድጋፍ ለማግኘት በኩራት የሚኮፈሱት ቡድኖች ሊያውቁት የሚገባው ነገር ቢኖር ሕዝቡ ለጥቅሙ የቆመለትን ሲረዳ አንቅሮ እንደሚተፋቸው ነው።
ሌላው ውንጀላ ደግሞ ሶሻሊስቶች ጸረ ሃይማኖት እንደሆኑ ተደርጎ የሚነዛው ፕሮፓጋንዳ ነው።እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ሶሻሊስቶች ከሃይማኖት ጋር ከሚለያዩበት ይልቅ የሚቀራረቡበት ነጥብ ይበዛል። አትስረቅ፣አትቀማ፣አትዝረፍ፣አትዋሽ፣በሃሰት አትመስክር፣አትግደል፣ሌላውን እንደራስህ ውደድ፣የሰው ልጅ በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረ እኩል ነው፤አንዱ ጌታ ሌላው ባርያ ሊሆን አይገባውም የሚሉት መሪ ቃሎች የነሱም መመሪያዎች ናቸው።ከዚያም በላይ እሹ፣ፈልጉ ታገኛላችሁ የሚለው መለኮታዊ ቃል ለሳይንስ ምርምርና ግኝት እውቅና የሚሰጥ በመሆኑ የሶሻሊስቶቹን እምነት አይጻረርም። ሶሻሊስቶች የሚቃወሙት ሃይማኖቱን ሳይሆን ለባለጸጋዎችና ጸረ ሕዝብ ሃይሎች ጠበቃና ዘበኛ ሆነው የተሳሳተ ትምህርት፣አሜን ብሎ እንዲቀበል የሚሰብኩትን የሃይማኖት መሪዎች ነው።በዚህም የተነሳ አደንዛዥ እጾች ይላቸዋል።
ልዩነት አለ ቢባል ሶሻሊስቶቹ የተፈጥሮን ትንሳኤና ሂደት የሚያዩበት መነጽር የተለዬ መሆኑ ነው።ባጠቃላይ የሰውን ልጅ አመጣጥ በተመለከተ የተፈጥሮና የሶሻል ሳይንስን መሰረት ያደርጋሉ። ተፈጥሮ ሳይለውጥ የኖረ አልፋና ኦሜጋ ፣ምንጩና ባለቤቱ የታወቀ አድርገው አለመቀበላቸው ነው።ሳይንስን እንደመሣሪያ ተጠቅመው መልስ ለማግኘት ጥረትና ፍለጋውን ይቀበላሉ።በተጨባጭ ማስረጃ ላይ የተደገፈን እውነትን እንጂ ግምታዊና ሃሳባዊ በሆነው ነገር ደምድመው እጃቸውን አጣጥፈው አይቀመጡም።ሃይማኖቶች ይኖራሉ ብለው ያላስተማሩትንና ያላወቁትን ፣በህዋው ወይም በጠፈር ዙሪያ ያሉትን የተፈጥሮ አካላት ሳይንስ ስለደረሰባቸው ሌላውንም የተፈጥሮ ሚስጥርና ምንነት ለማወቅ የጊዜ ጉዳይ ይሆናል እንጂ የሚሳን አይሆንም ብለው ያምናሉ። በአሁኑ ጊዜ ሃይማኖቶች ትምህርታቸውን ለመስጠት የሚገለገሉበት የሳይንስ ውጤት የሆነውም ራዲዮ ሲጀመር የሰይጣን ሥራ ተደርጎ ይወገዝ ነበር።
ሶሽያሊስቶች የአገራትንና የሕዝቦችን ግንኙነት እንደሚቃወሙም ተደርጎ ይሰበካል።እውነታው ግን ከዚያ የተለዬ ነው። አንዱ አገር የሌላውን አገር በመውረር፣ወይም ባልተመጣጠነ የጥቅም ሰንሰለት አንዱ ተጠቃሚ ሌላው ተጎጂ እንዳይሆን፣ የጌታና የባርያ ግንኙነት እንዳይኖር፣በመከባበርና በጋራ ጥቅም ላይ ፣ሰጥቶ መቀበል በሚል መርሆ ላይ ያረፈ ግንኙነት እንዲኖር የሚያደርግ እምነት ተከታዮች ናቸው።
የተሳካላቸው የግራ ፖለቲካ አራማጆች ሶሻሊስቶች አገራቸውን ለከፍተኛ እድገትና ስልጣኔ እንዳበቁ፣ከራሳቸው አልፈው ለከበርቴ አገር እንደተረፉም ዘወር ብለው ሊያጤኑት ይገባል።ዴሞክራሲ ሲባል የሁሉም አመለካከት የሚከበርበት ስርዓት ማለት ነውና በመከባበር ሁሉም የራሱን መንገድና መስመር የመከተል መብቱን ማክበር ለዴሞክራሲ ሕግ መገዛት ነው።
በአገራችን አንገቱን ደፍቶ፣ድምጹን አጥፍቶ የተቀመጠው የግራ ፖለቲካ መስመር ደጋፊ ደፍሮ መነሳት አለበት፤ጊዜው የሚጠይቀውን የሶሻሊስት የትግል መርሆ ይዞ መደራጀት ይኖርበታል።ቦታውን ለቀኙ ፖለቲካ ቡድን መልቀቅ አይኖርበትም።ሕዝብ እየተሰቃዬ፣የአገር ሃብትና ንብረት እዬተቸበቸበ፣እዬተዘረፈ፣አገር እዬጠፋ ዘመናዊ ባርነት በተንሰራፋበት ዓለም ተመልካች ሊሆን አይገባውም።ከጥፋት እራሱንና አገሩን ለማዳን ጊዜው አሁን ነው።ተወደደም ተጠላም ለሃገር ልዑላዊነት፣ለሕዝብ መብትና ጥቅም፣ለዴሞክራሲ መስፈን የሚታገለው የግራ ፖለቲካ አራማጅ ምንም እንኳን ከባድ ቢሆንበትም እጁን መስጠት አይኖርበትም፤የተከፈተበትን የፕሮፓጋንዳና የጥቃት ዘመቻ ለመቋቋምና አገሩን ከጥፋት ለማዳን በድፍረት ልዩነቱን አሶግዶ በአንድ ላይ መቆም ያለበት ጊዜው አሁን ነው።
አሁን በብዙ ስም የተደረደሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች በስም እንጂ በዓላማ የተለያዩ አይደሉም።ሁሉም የኔዎ ሊበራል የከበርቴውን የዘረፋ ዓላማና ፍላጎት የተቀበሉ ብሔራዊ ስሜት የሌላቸው፣የአቀባባይ ሰልፈኞች ናቸው።አማራጭ በሌለበት ሜዳ ለምርጫ መሰለፍ አገራችንንና ሕዝባችንን ለአደጋ ብሎም ለጎሰኞች ቅርጫ አሳልፎ መስጠት ይሆናል።ስለሆነም የምርጫ ሁኔታ ሳይሙዋላ፣ሰላምና መረጋጋት ሳይኖር፣በቂ ዝግጅት ሳይደረግ፣ምርጫ ማካሄድ ለጎሰኞቹ እውቅናና የፈለጉትን ለማድረግ የሚችሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር መፍቀድ ማለት ነው።ያ የሚፈልጉት ነገር ደግሞ ኢትዮጵያን ሙሉ ለሙሉ በመዳፋቸው ሥር ማድረግ አለያም የሚፈልጉትን አካባቢ ቦጭቆ የራስን አዲስ አገር መፍጠር ነው።የነጮቹም ፍላጎት ከዚህ የተለዬ አይደለም።በሥልጣን ላይ ያለው የጎሰኞች ቡድን እንዲኖር አለያም ኢትዮጵያ ፈራርሳ ደቃቃና ደካማ ክልልን እንደፈለጉ ለመቆጣጠርና ለመበዝበዝ የሚያስችላቸውን ስሌት አድርገው በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው።
ያለው አማራጭ ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስከብር፣የጎሳና የሃይማኖት አሰላለፍን ያልተከተለ፣ከሁሉም ማህበረሰብ ክፍሎች የተውጣጣ የሽግግር መንግሥት መመስረትና ለዴሞክራቲክና አስተማማኝ ምርጫ ሕግና ደንብ ተከትሎ ሕዝቡን ማደራጀት ነው።
በግራ ፖለቲካ ላይ ያለው ውዥንብር ይገፈፍ!!ሶሻሊስቶችም የታፈነውን ድምጻቸውን ለማሰማት ደፍረው ይውጡ!!አገራቸውንና ሕዝባቸውን ከተደቀነበት አደጋ ለማዳን ቆርጠው ይነሱ!!!
አገሬ አዲስ