February 17, 2020
56 mins read

በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ፣ በናይል ተፋሰስ የውሃ ፓለቲካ እና በአፍሪካ ቀንድ ጂኦፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የተደረገ ቃለመጠይቅ – ፕሮፈሰር ተስፋዬ ታፈስ

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአፍሪካና ኦሪየንታል ጥናትና ምርምር ተቋም

የጂኦፖለቲክስና የአፍሪካ ጥናት መምህርና ተመራማሪ

የዛሬው እንግዳችን ፕሮፌሰር ተስፋዬ ታፈሰ ትውልዳቸው ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ቢሾፍቱ ከተማ ሲሆን፣ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በጂኦግራፊ እና የሁለተኛ ድግሪያቸውን በጂኦፖለቲክስ የትምህርት መስክ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አግኝተዋል፡፡ የዶክትሬት ድግሪያቸውን ደግሞ ጀርመን ሀገር ከሚገኘው ኦስናብሩክ ዩኒቨርስቲ በጂኦፖሊቲክስ እና ሶሻል ጂኦግራፊ የትምህርት መስክ ተቀብለዋል፡፡ አሜሪካን አገር ከሚገኘው ዩኒቨርስቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ ሎስ አንጀለስ እና በጀርመን በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ጎብኚ ፕሮፌሰር በመሆን አስተምረዋል፡፡ በሴኔጋል ዋና ከተማ ዳካር በሚገኘው የአፍሪካ የማህበራዊ ሳይንስ ጥናትና ምርምር ካውንስል (CODESRIA) የምርምር ክፍል ኃላፊና ተመራማሪ በመሆንም ሰርተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በማህበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ የአፍሪካና ኦሪየንታል ጥናትና ምርምር ተቋም የጂኦፖለቲክስና የአፍሪካ ጥናት ፕሮፈሰር ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር ተስፋዬ አምስት መጻህፍትን በታዋቂ አታሚዎች አሳትመው ለንባብ ያበቁ ሲሆን፣ በተለያዩ ጉዳዮች በተለይ ደግሞ በናይል ተፋሰስ የውሃ ፓለቲካ ጋር በተያያዘ መጽሀፍ በማሳተም፤ የተለያዩ ጹሁፎችን በመጻፍ ይታወቃሉ፡፡

እኛም ከ25 ዓመታት በላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመምህርነትና ተማራማሪነት ካገለገሉትና አሁንም እያገለገሉ ካሉት ከእኚህ አንጋፋ ምሁር ጋር በአፍሪካ ቀንድ ወቅታዊ ሁኔታ፣ በናይል ተፋሰስ የውሃ ፓለቲካ እና በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ቆይታ አድርገን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡

አዲስ ልሳን፡- የጋዜጣችን እንግዳ ለመሆን ፈቃደኛ ስለሆኑ እናመሰግናለን፡፡

ፕሮፌሰር ተስፋዬ፡-ይኼን ዕድል ስለሰጣችሁኝ እኔም አመሰግናለሁ፡፡

አዲስ ልሳን፡- ወቅታዊውን የአፍሪካ ቀንድ ሁኔታ እንዴት ይመለከቱታል?

ፕ/ር ተስፋዬ፡- በመጀመሪያ የአፍሪካ ቀንድ ስንል ምን ማለት ነው የሚለውን ትርጉም መስጠቱ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ የአፍሪካ ቀንድ አራት ዋና ዋና ሀገሮችን የያዘ ነው፡፡ እነርሱም ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያና ጅቡቲ ናቸው፡፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና ጂኦግራፊ ተዛማጅ የሆኑት ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያና ኡጋንዳም በዚህ ሥር ሊካተቱ ይችላሉ፡፡ የአፍሪካ ቀንድ እንዳለመታደል ሆኖ በብዙ ችግሮች የተተበተበ ነው፡፡ በስደተኞች፣ በተፈናቃዮች ብዛት፣ በእርስ በእርስ ጦርነት፣ በአካባቢ መራቆት፣ በድርቅ፣ በረሃብ፣ በሽብርና በባህር ላይ ውንብድና ብዙ ጊዜ ይጠቀሳል፡፡ እነዚህ ሁሉ መጥፎ ነገሮች እያሉ ደግሞ ስትራቴጂካሊ በጣም ጠቃሚ የሆነ አካባቢ በመሆኑ የአሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት እና ቻይና የመሳሰሉ ኃያላን ሀገራትን ትኩረት መሳብ ችሏል፡፡

የቻይና በቀጠናው መከሰት አዲስ ነገር ነው፡፡ ጅቡቲ ላይ የጦር ሰፈር መስርተዋል፡፡ ይሄ አንድ ትልቅ ክስተት ነው፡፡ ምክንያቱም ቻይና በፊት ብዙም ከአካባቢዋ የምትርቅ አገር አልነበረችም፡፡ የአውሮፓ ህብረት ደግሞ ለኤርትራ ለብዙ ጊዜ ጀርባውን ሰጥቶ ቆይቶ አሁን የፍልሰትና የስደት ምንጭ ስትሆን ሳይወዱ በግድ እያነጋገሯቸው ነው፡፡ ስደቱን ለማቆም ኤርትራን እየረዱ ነው ያሉት፡፡ ይኼ ሌላ ወቅታዊ አዲስ ክስተት ነው፡፡

ትንሿ ሀገር ዩናይትድ አረብ ኤምሬቶች አዲስ ሀይል ሆነው በአካባቢው ብቅ ብለዋል፡፡ በጣም በሚገርም ሁኔታ አሰብ ላይ ወታደራዊ የጦር ሰፈር መስርተዋል፡፡ ከዚያ ሆነው ነው በሚያሳዝን ሁኔታ የመንን እየደበደቡ ያሉት፡፡ ቱርኮች ደግሞ ወደ ሶማሊያ ገብተው ‹‹ቱርክሶም›› የሚባል ወታደራዊ ካምፕ መስርተዋል፡፡

ለምንድነው እነዚህ ሀገራት ወታደራዊ የጦር ሰፈር በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የገነቡት? የሚለው ጥያቄ ብዙ ምክንያቶች አሉት፡፡ አንደኛ የጅቡቲ ስትራቴጂካዊ አቀማመጧ በተለይ ባብል ኤል መንደብ የጅቡቲ ድንበር ላይ መሆኑ ነው፡፡

ሁለተኛው በአካባቢው እየተስፋፋ የመጣው የባህር ላይ ውንብድና (piracy) የዓለምን የንግድ እንቅስቃሴ እያወከ ስለሚገኝ ነው፡፡ በዚች ጠባብ መስመር ላይ በቀን ከ3 ሚሊዮን በርሜል በላይ ድፍድፍ ዘይት ይተላለፋል፡፡ የመርከቦች እገታም ብዙ ጊዜ አለ፡፡ እያንዳንዱ ሀገር የራሱ መርከቦች በሰላም እንዲንቀሳቀሱ ስለሚፈልግ ነው በአካባቢው የጦርሰፈር መገንባት ፍላጎታቸው ያሳደረባቸው፡፡ ሌላውና ሶስተኛው በአካባቢው እያደገ የመጣውን ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነት ለመቆጣጠር ነው፡፡ አልቃይዳ፣ አልሸባብ፣ ኢስላሚክ ስቴት ለመሳሰሉ አሸባሪ ድርጅቶች ምቹ የሆነ አካባቢ ስለሆነ የዓለም አቀፍ ሀይሎች ይኼን ለመቆጣጠር ወደ ጅቡቲ ገብተዋል፡፡

አዲስ ልሳን፡- ኃያላኑ ሀገራት በጅቡቲ እና በቀይ ባህር አካባቢ ወታደራዊ የጦር ሰፈሮችን እያቋቋሙ መሆኑ በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና እና በኢትዮጵያ ላይ ምን አይነት ተጽዕኖ ይኖረዋል?

ፕ/ር ተስፋዬ፡-የአፍሪካ ቀንድ በስትራቴጂክ ጥቅሙ ምክንያት የብዙ ኃያላን ሀገራትን ቀልብ ገዝቷል፡፡ ለምሳሌ የቀድሞ የጅቡቲ ቅኝ ገዥ ፈረንሳይ FFDj የሚባል የጦር ሰፈር አላት፡፡ ከ9/11 የሽብር አደጋ በኋላ አሜሪካኖችም ፍላጎት አሳድረው፣ የአሜሪካ ባህረ ሀይል ሰፈር (ካምፕ ሌሞኒየር) ተመስርቷል፡፡ ጣሊያኖችም የጣሊያን ብሔራዊ ወታደራዊ ድጋፍ የሚል ሰፈር አቋቁመዋል፡፡ ጃፓኖች ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ወደ ሌላ አካባቢ የሚገቡ አልነበሩም፡፡ አሁን ግን የጃፓን የራስ መከላከያ ኃይል ብለው ከህንድ ጋር በጥምር የጦር ሰፈር ከፍተዋል፡፡ ስለዚህ ከፈረንሳይ ሌላ አምስት ሀገሮች ወታደራዊ የጦር ሰፈር አላቸው ማለት ነው፡፡ ጅቡቲን የምታክል ትንሽ ሀገር እነዚህ ሁሉ ኃይሎች ሰፍረውባታል፡፡

ኤርትራ ላይም ሶስት ሀገራት ወታደራዊ የጦር ሰፈር አላቸው፡፡ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ኢራን አሰብ ላይ የጦር ሰፈር ገንብተዋል፡፡ እስራኤል ዳህላክ ደሴት ላይ የመርከብ ማሳረፊያ በሚል ወታደራዊ የጦር ሰፈር መስርታለች፡፡ ሳውዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችና ግብጽ በአንድ በኩል፣ ካታርና ቱርክ በሌላ በኩል ተጽዕኗቸውን ለማሳደግ ይፈልጋሉ፡፡ አካባቢው የውድድር ሜዳ እየሆነ መጥቷል፡፡

በኢትዮጵያ ላይና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የሚያመጣውን ተጽዕኖ ከአዎንታዊ ጎኑ ብንጀምር የእነዚህ ኃይሎች በአካባቢው መኖር የሀገራችንና የአፍሪካ ቀንድን በተወሰነ መልኩ ከሽብር ጥቃት ሊያድን ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም ብዙ ችግር ያለበት አካባቢ በመሆኑ አልቃይዳ እና አልሸባብን የመሳሰሉ የተለያዩ ሀይሎች ችግር ሊፈጥሩ ስለሚችሉ የእነዚህ ሀይሎች መኖር ተጽዕኖውን የሚቀንሰው ይመስለኛል፡፡

በአሉታዊ ጎኑ ደግሞ አፍሪካውያን ያልሆኑ ሀይሎች ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ጅቡቲና አካባቢው መስፈራቸው ያሳስባል፡፡ የቀዝቃዛው ጦርነት አይነት ማለትም ቻይና ከአሜሪካ፣ ሳውዲና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ከኳታር አይነት ፍጥጫ፡፡ የነዚህ ሁሉ  ኃይሎች እዚህ አካባቢ መረባረብ የአፍሪካ ቀንድን የውድድርና የፍጥጫ ሜዳ አድርጎታል፡፡ ይሄ የራሱ የሆነ ተጽዕኖ ይኖረዋል፡፡ ጅቡቲና አካባቢው ላይ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ለኢትዮጵያም ይተርፋል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ በዚህ ልትጎዳ ትችላለች የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡

አዲስ ልሳን፡- ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ምን ማድረግ አለባት?

ፕ/ር ተስፋዬ፡- ሁሉንም ነገር ነቅቶ ከመጠበቅ ሌላ ምንም አማራጭ የለንም፡፡ ጅቡቲ ራሷን የቻለች ነጻ ሀገር ነች፡፡ የምትፈቅደውም፤ የምትከለክለውም ራሷ ናት፡፡ ነገሮች ጥሩ ሆነው ጅቡቲ ከኢትዮጵያ ጋር፣ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ኮንፌደሬሽን አይነት ነገር ቢፈጥሩ፣ በፖለቲካና ኢኮኖሚ አንድ ላይ እየተናበቡ ይሰራሉ፡፡ አሁን ግን ጅቡቲ የፈቀደችውን ኢትዮጵያ አይሆንም ልትል አትችልም፡፡ ወደፊት የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ኮንፌደሬሽንና ቀጠናዊ ትስስር እየመጣ ሲሄድ እየተወያዩ ለአካባቢው ጠቃሚ የሆኑ ነገሮችን ሊተገብሩ ይችላሉ፡፡

አዲስ ልሳን፡-  በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የወረደው ሰላም በአፍሪካ ቀንድ ላይ ምን አንድምታ ይኖረዋል?

 

ፕ/ር ተስፋዬ፡-በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የወረደው ሰላም ትልቅ ክስተት ነው፡፡ እንደሚታወቀው ለ20 ዓመታት የዘለቀውን መፋጠጥ ፈረንጆች እንደሚሉት ‹No War-No Peace› ማለትም ጦርነትም  ሰላም የሌለበትን ሁኔታ የለወጠ ክስተት ነው፡፡ ሁለቱም አገሮች ሃያ ዓመታትን አቃጥለዋል – በጦርነት ያጠፉትን ሀብት ለልማት ቢጠቀሙበት ኢኮኖሚያቸውን ትልቅ ደረጃ ማድረስ ይችሉ ነበር፡፡

እንደሚታወቀው የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተጠበቀ ሪፎርም ተካሄዶ ዶክተር አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ፡፡ ይህንን ለውጥ ተከትሎ በአንዳንድ የአካባቢው ሀገሮች ሸምጋይነት ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲሄዱ ተደርጓል፡፡ እዚህ ላይ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ሳውዲ አረቢያ ትልቅ ሚና የተጫወቱ ይመስለኛል፡፡ ይህ የሰላም ስምምነት ለኢትዮጵያና ኤርትራ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ ቀንድ ቀጠና፣ ከዛም አልፎ ለመካከለኛው ምስራቅ ትልቅ እንደምታ ይኖረዋል፡፡ በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ለዘለቄታው ሊያሰፍን ይችላል፡፡ ሰላም ካለ ደግሞ የኢኮኖሚ እድገት ይኖራል እንዲሁም የፖለቲካ መረጋጋት ሊፈጠር ይችላል፡፡

ኢትዮጵያ በሚያሳዝን ሁኔታ ከ100 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት ትልቅ ሀገር ሆና የባህር በር የሌላት ሀገር ሆናለች፡፡ ከኤርትራ ጋር ሰላም መፍጠሩ ኢትዮጵያን አማራጭ የወደብ አቅርቦት በተሻለ ዋጋ ማግኘት የምትችልበት መንገድ ሊከፍት ይችላል፡፡ የኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝብ አንድ ህዝብ ነው፣ ለብዙ ዓመታት አብሮ የኖረ፣ የተዋለደ ህዝብ ነው፡፡ ሰላም ሲኖር የህዝቦችን ነጻ ዝውውር ይፈጥራል፡፡ ሰዎች እንደፈለጉ መዘዋወር፣ ሸቀጥና ካፒታል እንደፈለጉ ማንቀሳቀስ ይቻላል፡፡ ስምምነቱ ለሁለቱም ሀገራት ጠቃሚ ነው፡፡

አዲስ ልሳን፡- ስምምነቱ እንደተጀመረው ወደፊት ተራምዷል ብለው ያስባሉ?

ፕ/ር ተስፋዬ፡- አጀማመሩ ጥሩ ስለነበር እኔ ከዚህ በላይ ነበር የጠበቅኩት፡፡ ነገሮች በፍጥነት ሄደው ድንበሩ ተከፍቶ፣ ነጻ የህዝብ እንቅስቃሴ በአየር ብቻ ሳይሆን በየብስም ይኖራል የሚል ግምት ነበረኝ፡፡ አሁን አንዳንድ ነገሮች ግልጽ አይደሉም፡፡ ለምን በኤርትራ በኩል ድንበሩን ከፍተው እንደገና እንደዘጉት በይፋ የተገለጸ ነገር የለም፡፡ ምክንያት ይኖራቸዋል፡፡ ከህወሃት (ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ) ጋር ብዙ ጊዜ ችግር ላይ ስለነበሩ፣ የኤርትራ መንግስት ያለፈውንም ጦርነት የኢትዮጵያ ህዝብ ሳይሆን ህወሃት እኛን ለማጥቃት ያደረገው ነው ብለው ስለሚያስቡ በዚያ በኩል ድንበሩን ሙሉ በሙሉ ከፍተው ነጻ ማድረጉን የፈለጉ አይመስልም፡፡ ችግሩ የተወሳሰበ ነው፡፡ በኤርትራ በኩል በግልጽ የወጣ ነገር የለም፡፡ በኢትዮጵያ በኩልም ለምን ሁኔታዎች በተጀመረው ፍጥነት አልሄዱም የሚለው እስካሁን በይፋ የወጣ መረጃ ስለሌለ ምክንያቱን አናውቅም፡፡

አዲስ ልሳን፡-  የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ሀገራት በኢኮኖሚው የሚተሳሰሩበትና ወደ ኮንፌዴራላዊ ቀጠና ማደግ የሚችሉበት ዕድል ምን ያህል ነው?

 

ፕ/ር ተስፋዬ፡- ይኼ የቆየ ጥያቄ ግን እስካሁን መልስ ያላገኘ ነው፡፡ ኮንፌዴሬሽን እንደ አንድ ትልቅ አማራጭ አድርገው የጻፉ ምሁራን አሉ፡፡ አንዱ በዚህ ላይ ብዙ ጹሁፍ ያቀረቡት ፕሮፌሰር ተስፋጽዮን መድሃኔ ይባላሉ፡፡ ኤርትራዊ ናቸው፡፡ የሚያዳምጥ ጠፍቶ ነው እንጂ ብዙ ጽፈዋል፡፡ የእርስ በርስ እንዲሁም የውክልና ጦርነት በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ አለ፡፡ በሀገሮች መካከል አለመግባባት አለ፡፡ ባለፈው ኤርትራ ከኢትዮጵያ፣ ጅቡቲና ሌሎችም አገሮች ጋር ችግር ነበረባት፡፡ በዚህ ምክንያት ኮንፌደሬሽን የሚታሰብ ነገር አልነበረም፡፡ ኮንፌዴሬሽንን ተግባራዊ ለማድረግ በሁሉም ዘንድ ሰላምና መተሳሰብ መኖር አለበት፡፡ ሁሉም ይጠቅመናል ብለው ማመን አለባቸው፡፡ ለምሳሌ የአውሮፓ ህብረት ሀገራት አንድ ከመሆን አልፈው አንድ ገንዘብ ዩሮን ነው የሚጠቀሙት፡፡ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ኮንፌዴሬሽን የማይፈጸምበት ምክንያት የለም፡፡ ይኼን የምልበት ምክንያት በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የባህል ትስስር አለ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካም ትስስርም ያለበት ቀጠና ነው፣ እንዲሁም ችግሮችንም በተለያዩ ደረጃ ይካፈሉታል፡፡ ለምሳሌ ድርቅ ከመጣ ሁሉምጋ ነው የሚመጣው፡፡ ረሃብም እንደዚያው፡፡ የአካባቢ መራቆት፣ ድህነት፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት ካለ ሁሉም ላይ ተጽዕኖ ስለሚኖረው የጋራ ጥረት አስፈላጊ ነው፡፡ የጋራ ጥረት አስፈላጊ ከሆነ የኮንፌዴሬሽን አስፈላጊነትን ያመጣል፡፡ በኮንፌዴሬሽን መተሳሰር የጋራ ጥረትና የጋራ መፍትሔ ማምጣት ይቻላል፡፡

በአሁኑ ወቅት  ኮንፌዴሬሽን በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ለማምጣት ችግሮች ይታያሉ፡፡ በአፍሪካ ቀንድ በተለይም በኢትዮጵያ ጎጠኝነት፣ የሰፈር አስተሳሰብ እና  የሃይማኖት አክራሪነት ይታያል፡፡ ልክ የአውሮፓ ህብረት እንዳደረገው ወደ ኮንፌዴሽን ለመሄድ ጭንቅላትንና አስተሳሰብን ሰፋ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ አንተ ኢትዮጵያዊ ሆነህ ስለሀገርህ ብቻ አይደለም መጨነቅ ያለብህ፡፡ ስለአፍሪካ ቀንድ ከዚያም ባለፈ ስለ አፍሪካም ቀጥሎ ስለአለም መጨነቅ አለብህ፡፡ በሚዲያ ጎርፍ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ ጉዳት አደረሰ ሲባል በሰብአዊነት ታዝናለህ፡፡ በአፍሪካ ቀንድ እና በተለይም ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቁ ችግር በጭንቅላት ላይ ብዙ አልተሰራም፡፡ ፈረንጆች ‘ኮስሞፖሊታን’ የሆነ አስተሳሰብ (cosmopolitan thinking)፣ ማለት ከጎጥህ ወጥተህ ስለዓለም፣ ስለአፍሪካ፣ ስለዓለም፣ ስለ የሰው ልጅ የምታስብበት ግንዛቤ መፈጠር አለበት፡፡

አዲስ ልሳን፡-  ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከጎረቤትና አረብ ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት በጥርጣሬ የተሞላ እና መተማመን የሌለበት እንደነበር ይነገራል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሳውዲ አረቢያን ጨምሮ ከካታርና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር ያለው ግንኙነት እየሞቀ መጥቷልና ይህን  እንዴት ያዩታል?

ፕ/ር ተስፋዬ፡-ቀደም ባሉት ጊዜያት በተሳሳተ መረጃና አስተሳሰብ ከአረብ ሀገራት ጋር ያለን ግንኙነት በጥርጣሬ ላይ የተመሰረተ ነበር፡፡ አንዳንድ የአረብ ሀገራት እና ሌሎችም ኢትዮጵያን እንደ ‘ክርስቲያን ደሴት’ ይወስዷት ነበር፣ በፊት የነበሩ አጼዎችም እንዲህ አይነት ምልከታ ነበራቸው፡፡ እዚህ ሀገር ከአንድ ሶስተኛ በላይ የሚሆነው ህዝብ ሙስሊም ሆኖ ይህ ሀገር የክርስቲያን ሀገር ነው የሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ ነበር፡፡ ኢትየጵያ ከእስራኤል ጋር በተለያዩ ምክንያቶች ወገናዊነት ታሳያለች የሚልም አመለካከት ለብዙ ጊዜ ነበር፡፡ አሁን ነገሮች እየተለወጡ መጥተዋል፡፡ እውነታዎች እየወጡ ሲመጡ ነገሮች እየተስተካከሉ የመጡ ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ ኤርትራና ኢትዮጵያን በማቀራረብና ሰላም እንዲወርድ ትልቁን ሚና የተጫወቱት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችና በመጠኑም ቢሆን ሳውዲ አረቢያ ናቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ስልጣን ላይ ከመጡ በኋላ ብዙ የመካከለኛው ምስራቅ የአረብ ሀገራትን ጎብኝተዋል፡፡ ጉብኝታቸው ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንድታገኝ አድርጓታል፡፡ አንዳንዶቹ በችግር ጊዜ ደራሽ ሆነዋል፡፡ ካዝናዋ ባዶ በነበረበት ጊዜ ድጎማ በማድረግ ለተወሰነ ጊዜ ኢኮኖሚዋ እንዲንቀሳቀስ የረዱት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ናቸው፡፡ ይኼ ለጥሩ ግንኙነት ተምሳሌት የሚሆን ነው፡፡ ኢትዮጵያና መካከለኛው ምስራቅ በመልክአ ምድር አቀማመጣቸው ጎረቤታሞች ናቸው፣ ሃይማኖታዊ ግንኙነታቸው ከፍ ያለ ነው፣  የእስምልናና ክርስትና ሃይማኖቶች የተፈጠሩት መካከለኛ ምሥራቅ ውስጥ ነው፡፡ መካከለኛው ምስራቅ የአየር ጸባዩ ደረቃማ ስለሆነ ብዙም የእርሻ ምርት የላቸውም፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ የእርሻ ምርት ውጤቶች ስላላት መካከለኛው ምስራቅ ትልቅ ገበያ ሊሆናት ይችላል፡፡ ግንኙነቱ ሲታሰብ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ታሳቢ ማድረጉ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡

አዲስ ልሳን፡-  በሌላ በኩል ደግሞ በታላቁ ህዳሴው ግድብ ላይ የአረብ ፓርላማ አባላት የግብጽን አቋም ደግፈው መግለጫ አውጥተው ነበር፡፡ ይሄስ አሁን ከመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ጋር ካለን ግንኙነት አንጻር እንዴት ይታያል?

 

ፕ/ር ተስፋዬ፡- እርግጥ ነው ባለፈው ኦክቶበር መጨረሻ ላይ የአረብ ፓርላማ የግብጽን መንግስት የሚደግፍ መግለጫ አውጥቷል፡፡ መግለጫው ለግብጽ ወገናዊነትን ያሳየና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚፃረር ነበር፡፡ በመግለጫው ብዙም አልተደነቅኩም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ የአረብ ሊግ አባል አይደለችም፡፡ ግብጽ የአረብ ሊግ አባል ነች፡፡ በዚያ ላይ አረብ ሊግን የሚመሩት አህመድ አቡል ጌይት የሚባሉት ግብጻዊ ናቸው፡፡ በቅርቡ እኚህ ሰውዬ የህዳሴው ግድብ የግብጽን የውሃ ደህንነት እንደሚጎዳ ከማሳሰብ አልፈው፣ እኛ ታህሪር አደባባይ (Tahrir Square) ሙባረክን ለመጣል ስንረባረብ፣ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መገንባት ጀመረች በማለት እርግጠኛ ሆነው ሲናገሩ ነበር፡፡ ይኼ በጣም የተሳሳተ አስተያየት ነው፡፡ የግብጽ ህዝብ የሚያገኘው እንዲህ አይነት መረጃ ነው፡፡ ግብጽ ውስጥ ሚዲያ ትልቅ ሚና አለው፡፡ መዋሸትና መዋሸት ግን ባሕል ነው፡፡ ወደ ግብጽ በተለያየ ጊዜያት ሄጃለሁ፤ ኢትዮጵያ ውሃን ልታቆመው ነው፤ ልታስርባችሁ ነው የሚባለው፡፡ የማይደረግ አይነት ፕሮፖጋንዳ የለም፡፡ አንዳንድ ግብፃውያን ናይል ወንዝ እዚያው ግብፅ ውስጥ መንጭቶ እዚያው የሚያልቅ ይመስላቸዋል፡፡ እስከዚህ ድረስ ውሃው የኛ ነው ብለው ያስባሉ፡፡ የአረብ ፓርላማ አባላትም ሆኑ የአረብ ሊግ ዋና ጸሀፊ አስተያየት ወገናዊነትን ለማሳየት እንጂ ይኼን ያህል ተጽዕኖ ያለው አይመስለኝም፡፡ ግብጽን አይዞሽ ለማለትና ለመሸንገል የተደረገ ነው፡፡

 

አዲስ ልሳን፡- የህዳሴውን ግድብውሃ አሞላልና አለቃቀቅን በሚመለከት ሶስቱ የተፋሰሱ ሀገራት እያደረጉ ባሉት ድርድር ግብፅ በተደጋጋሚ እንደታየው ላለመስማማት የምትስማማው እንዲሁም ችግሩ ከቴክኒካዊ መፍትሔ ይልቅ በዲፕሎማሲ እንዲያልቅ የምትፈልገው ለምንድን ነው?

 

ፕ/ር ተስፋዬ፡-ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ ግብጾች ቴክኒካል ጉዳይ ከመጣ እንደማያዋጣቸው ያውቁታል፡፡ ስለዚህ ቢቻል በዲፕሎማሲ ካልሆነ በማስፈራራት እነሱ በሚፈልጉት መንገድ የግድቡ ውሃ አሞላልና አለቃቀቅ እንዲካሄድ ይፈልጋሉ፡፡ አሁን በቅርቡ የውኃው ሙሊት ከ12 እስከ 20 እንዲሆን ብለው ሀሳብ አቅርበዋል፡፡ ይኼ በጣም የሚያሳዝንም የሚያስቅም ነው፡፡ ከ12 እስከ 20 ዓመት (ግድቡ ይሞላ) ማለት ግድቡ ከጥቅም ውጪ ይሁን እንደ ማለት ነው፡፡ አንድ መኪና አቁመኸው ከአንድ ዓመት በኋላ ብትመጣ ምንም አገልግሎት ስላልሰጠ ዝጎ ብዙ ነገሩ ተበላሽቶ ታገኘዋለህ፣ ሞተርም ሊያስወርድህ ይችላል፡፡ በዚህም ሆነ በዛ የውኃው ማከማቻ ከሞላ በኋላ የአባይ ወንዝ የተፈጥሮ ፍሰቱን ጠብቆ እንዲሄድ ማድረግ አለባችሁ ነው የሚሉት፡፡ እ.ኤ.አ በ1959 ግብጽና ሱዳን ‹የናይል ውሃ ስምምነት› ብለው የተፈራረሙት ኢትዮጵያን ሳያሳትፉ ሁለቱ ብቻ ተቀምጠው ግብጽ 55 ነጥብ 5 በሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ፣ ሱዳን ደግሞ የተቀረውን 18.5 ቢሊዬን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ እንድታግኝ ነው፡፡ ይህንን ኢትዮጵያ ማክበር አለባት ብለው ይወተውታሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ስምምነቱ ኢትዮጵያን አይመለከትም ብሎ በንጉሰ ነገስቱ ዘመን መግለጫ አውጥቷል፡፡ ማስፈራራቱም ሆነ ውሃ በዚህ መጠን መለቀቅ አለበት የሚሉት እነዚህ የግብጽ ሀሳቦች የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ጥቅም የሚጻረሩ ናቸው፡፡ እንደሚታወቀው 85 በመቶ የናይል ውኃ ከኢትዮጵያ ነው የሚሄደው፡፡ ኢትዮጵያ በአባይ ውሃ ሙሉ በሙሉ የመጠቀም መብት አላት፡፡ እርግጥ ነው፤ ሙሉ በሙሉ የመጠቀም መብት ሲኖርህ ግን የሌላውን ሀገር እንዳይጠቀም ማድረግ አለብህ ማለት አይደለም፡፡ ለግብፅ ሕዝብም መታሰብ አለበት፡፡ ይህም ሆኖ ኢትዮጵያ ግብጽ አሁን በምታቀርበው ቅድመ ሁኔታ በምንም ተአምር መስማማት የለባትም፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ውሃ ማከማቸቱ በመጪው ክረምት ይጀምራል፡፡ ከ13 የውሃ ማመንጫ ተርባይኖች ሁለቱ በታህሣሥ 2013 ሀይል ማመንጨት ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ እነዚህ ሥራዎች በፕሮግራሙ መሰረት መካሄድ አለባቸው ነው የምለው፡፡

 

አዲስ ልሳን፡-  በድርድሩ አሜሪካ በታዛቢነት የተጋበዘችው ለምንና በምን ሁኔታ ነው?

ፕ/ር ተስፋዬ፡-አሜሪካ እንድታደራድራቸው የተማጸኑት የግብጹ ፕሬዝዳንት አልሲሲ ናቸው፡፡ በተለያዩ ታሪካዊ ምክንያቶች ግብጽና አሜሪካ ከካምፕ ዴቪድ ስምምነት ጊዜ ጀምሮ ጠበቅ ያለ ግንኙነት ነው ያላቸው፡፡ እንደሚታወቀው በዓለም ላይ ከፍተኛ የአሜሪካ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ እርዳታ የሚያገኙት አንደኛ እስራኤል ስትሆን፣ ሁለተኛዋ ግብጽ ናት፡፡ በዚህም ምክንያት የግብጹ አልሲሲ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ከኢትዮጵያ ጋር  እንዲያሸማግሉዋቸው ስለተማጸንዋችው ነው የገቡበት እንጂ ሰውዬው (ዶናልድ ትራምፕ) ስለናይል ብዙ የሚያውቁት ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ሰው ሸምጋይ ለማድረግ ኢትዮጵያ በምን እሳቤ እንደተስማማች ለእኔ ግልጽ አይደለም፡፡ ይመስለኛል በግብጾች እሳቤ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ብዙ እርዳታ ስለምታገኝ ተጽዕኖ ልታደርግ ትችላለች ወይንም አሜሪካን ሲያዩ የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ሊፈሩ ይችላሉ ብለው ገምተው ሊሆን ይችላል፡፡ ግብጾች ካይሮ፣ ካርቱም አዲስ አበባ እያልን ከምንመላለለስ ኃያሏ አገር አሜሪካ የዓለም ባንክ እና የገንዘብ ሚኒስትር ባለበት ብንደራደር የተጨበጠ ውጤት ያመጣል ብለው ወደ አሜሪካ የወሰዱት ይመስለኛል፡፡

 

አዲስ ልሳን፡-  በናይል ተፋሰስ ሀገራት አሁንና ወደፊት ሊፈጠሩ የሚችሉ የውሃ ፓለቲካ ግጭቶችን ለማስቀረት ምን መሰራት አለበት?

ፕ/ር ተስፋዬ፡- ይህንን ለማድረግ ሁሉም አሸናፊ የሚሆኑበትን ነገር (win-win solution) መፈለግ ያስፈልጋል፡፡ አንዱ ወገን የራሱን ጥቅም በማስከበር ሌላው እንዲጎዳ ከሞከረ (win-lose solution) አንዱ ተሸናፊ ሌላው አሸናፊ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም በመጨረሻ ውጤቱ ሁሉም ተሸናፊ የሚሆኑበት (lose-lose) ይሆናል፡፡

ናይል የጋራ ሀብት ነው፣ ድንበር አቋራጭ ወንዝ ነው፡፡ የጋራ ሀብትና ድንበር አቋራጭ ወንዝ ላይ ልክ እንደ ሌሎች ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ለምሳሌ ያህል ሴኔጋል፣ ኮሎራዶና ሚኮንግ ወንዞች ሁሉም ተነጋግረው ተስማምተው ሁሉም አሸናፊ የሚሆኑበትን መንገድ መፈለግ አለባቸው፡፡ እንዲህ ከመሆን ፈንታ እኔ ነኝ የተሻለ አቅም ያለኝ፣ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት አለኝ፣ በታሪክ ተጠቃሚ ነበርኩ እናንተን አላውቃቸሁም ከተባለ ችግር ይፈጠራል፡፡ አሁን በአባይ ላይ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ በሚያሳዝን ሁኔታ ይህንን ይመስላል፡፡

መፍትሄ ከተፈለገ ከኢትዮጵያ ይልቅ ብዙ ነገር በግብጽ ሜዳ ላይ ነው ያለው፡፡ ግብጽ አጨቃጫቂ የሆኑትን ከቅኝ ግዛት በፊትና በኋላ የነበሩ የናይል ወንዝ ስምምነቶችን ልክ ናቸው ተግባራዊ መሆን አለባቸው የሚል ግትር አቋሟን ሙሉ በሙሉ መለወጥ አለባት፡፡ መፍትሔው የዛሬ አስር ዓመት አካባቢ የተዘጋጀ የናይል ተፋሰስ ትብብር ማዕቀፍ (Nile Basin Cooperative Framework) – ባጭሩ CFA – የናይል ቤዝን ኢኒሽዬቲቭ ጽሕፈት ቤት  የሚገኝበት እንትቤ (ዩጋንዳ) የተቀመጠውን ሰነድ መፈረም ነው፡፡ ስድስት ሀገራት ማለትም ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ዩጋንዳ፣ ብሩንዲ እና ሩዋንዳ ፈርመዋል፡፡ ከእነዚህ ሀገራት ሶስቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለፓርላማዎቻቸው አቅርበው አጸድቀውታል፡፡ ግብጽና ሱዳን እስከዛሬ ባለመፈረማቸው ሰነዱ ፀድቆ ስራ ላይ ሊውል አልቻለም፡፡ በጥሞናና በሰከነ መንገድ ካሰቡበት ሰነዱ ለሱዳንም ሆነ ለግብጽ በጣም ጠቃሚ የሆነ ስምምነት ነው፡፡ ያለነው 21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ነው፡፡ የህዝብ ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡ አዳዲስ ችግሮች በየጊዜው እየተፈጠሩ ነው፡፡ ሁኔታዎች እንዲህ ባሉበት ሁኔታ የቆየና ሁሉም ያልተስማሙበትን ስምምነቶች ተቀበሉ ማለት አያዛልቅም፡፡

ግብጽ ከሁሉም የናይል ተፋሰስ ሀገሮች በአንፃራዊ መልኩ ያደገች ነች፡፡ አቅሙም ሀብቱም ያላት ሀገር ስለሆነች ናይል ረጅም ወንዝ ቢሆንም ትንሽ ውሃ ይዞ የሚሄድ በመሆኑ እሱ ላይ ብቻ ከማተኮርና ከመፋጠጥ ሌሎች የውሃ ምንጮችን መጠቀም ይችላሉ፡፡ እስራኤሎች የታወቁበትን የጠብታ መስኖ መጠቀም ብዙ ውኃ ለመቆጠብ ይረዳል፤ አጠገባቸው ሜዴትራኒያን ባህር፣ ቀይ ባህር አለ ከዛ ውኃ ጨለፍ አድርጎ ጨዋ አልባ በማድረግ መጠቀም ይችላሉ፤ ውኃ እንደገና አጣርቶ የመጠቀም አቅሙም አላቸው፤ እንዲሁም የከርሰ ምድር ውሃ ብዙ ስላላቸው እነዚህን አጎልብተው ቢጠቀሙ ለእነሱም ለሌሎችም የተፋሰስ ሀገሮች የሚበጅ መፍትሄ ይመስለኛል፡፡

አዲስ ልሳን፡-  ከዚህ ቀደም ለውጡን ተከትሎ ከዓመት በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ስምንት የሚደርሱ ተግዳሮቶች እያጋጠሙ እንደሆነ ጠቅሰው ነበር፡፡ ባለፈው አንድ አመትስ የነበረውን ሁኔታ እንዴት እያዩት ነው? ተግዳሮቶቹ እየቀነሱ ነው ወይስ እየጨመሩ?

 

ፕ/ር ተስፋዬ፡-ከዚህ ቀደም የዛሬ ዓመት አካባቢ ለውጡን እየገጠሙ ያሉ ስምንት የሚደርሱ ተግዳሮቶችን ጠቅሼ ነበር፡፡ አሁን ላይ አንዳንዶቹ ችግሮች ረገብ ብለዋል፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ብሰዋል፡፡ ካለምንም ጥርጥር መናገር የሚቻለው ኢትዮጵያ መስቀለኛ መንገድ ላይ መሆኗን ነው፡፡ አንዳንዶቹን ለመጥቀስ ያህል፡- ለምሳሌ ማህበራዊ ሚዲያውን አግባብ ባልሆነ መንገድ አፍራሽ ለሆኑ ተግባራት መጠቀም የሚለው አንድ እንደ ትልቅ ተግዳሮት እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አለመምጣቱን ነው፡፡ እንደእኔ ግንዛቤ እየባሰ እንጂ እየቀነሰ የመጣ አይመስለኝም፡፡ ደረጃቸው ቢለያይም ብዙ ሀገራት በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የውሸት ዜና ችግር ሰለባዎች ናቸው፡፡ በሀሰት ህዝብን ከህዝብ፣ አንዱን ብሔር ከሌላው ብሔር ጋር በማጋጭት የሚረኩ ሰዎች ባሉበት ሀገር ይኽ ችግር በአጭሩና በቀላሉ ይቀረፋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ የጭንቅላት ማለት የአስተሳሰብ ዕድገት ይፈልጋል፡፡ በዚህ ሀገር ትልቁ ክፍተት ጭንቅላት ላይ አለመሰራቱ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ቢኖር ጊዜውን የውሸት ዜና በመልቀቅ የሚያቃጥል ግለሰብ ወይንም ቡድን ባልኖረ ነበር፡፡

ጋዜጠኝነትና እና ፖለቲከኝነት በተሳሳተ መንገድ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ሆነዋል ያልኩትም እየባሰ የሄደ ይመስለኛል፡፡ ባሁኑ ወቅት በነፍስ ወከፍ ብናሰላው እንደ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ተንታኝ ያለበት ሀገር ያለ አይመስለኝም፡፡ የፖለቲካ ተንታኝ ተብለው የሚቀርቡት ብዙ ጊዜ የፖለቲካ ዕውቀቱ የሌላቸው እና ወገንተኛ የሆኑ ሰዎች ናቸው፡፡ ህብረተሰቡ ውስጥ ውዥንብር የሚፈጥሩትም እነኚህ እውቀት አልባ ‹የፖለቲካ ተንታኞች› ናቸው፡፡

የለውጡ ሀይል በዋልታ ረገጥ ሀይሎች መካከል መገኘት ያልኩትም እየባሰ እንጂ እየቀነሰ የመጣ አይመስለኝም፡፡ ይኼንንም በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን የሚቀርቡ ሰዎችን በማየት በቀላሉ ማወቅ ይቻላል፡፡ እነዚህ ሰዎች ለጥፋት የተሰለፉ ናቸው፡፡ እንዲህ አይነት ሁኔታ እስከ ምርጫውና ከዚያም በኋላ ሊቀጥል ይችላል፡፡ ህብረተሰቡ ማን ምን እንደሚፈልግና ማን ሊጠቅመው እንደሚችል በመገንዘብ እነዚህ ዋልታ ረገጥ የሆኑ ኃይሎችን/ ጽንፈኞችን አሁኑኑ ውሎ ሳያድር በቃችሁ ማለት አለበት፡፡ ባጭሩ ሊያንጓልላቸው ይገባል፡፡

ጤናማ ያልሆነ የኢኮኖሚ ስርዓትና ስራ አጥነት በከፍተኛ ደረጃ መጨመር እንደተግዳሮት ጠቅሼው ነበር፡፡ የዋጋ ግሽበቱ እንዳለ ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱም እየጨመረ ነው፡፡ የአለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ተቋም፣ በሁለትዮሽ ግንኙነት፤ የአውሮፓ ህብረት እና የተለያዩ ሀገራት በአገሪቱ ላይ በጎ አመለካከት እየፈጠሩ ስለመጡ፣ ከአለም ባንክና የአለም የገንዘብ ተቋም 3 ቢሊዮን ዶላር ይገኛል ተብሏል፡፡ በዚህ ኢኮኖሚው ትንሽ በመጠኑም ቢሆን ሊረጋጋ ይችላል፡፡ ሌሎቹንም የገንዘብ ምንጮች ጨምሮ እስከ 8 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ይገኛል ነው የተባለው፤ ገንዘቡ  ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት፣ የዋጋ ግሽበትንና የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ፣ ሥራ ለመፍጠር እና የህዝቡን ደህንነት ለማረጋገጥ መጠቀም አለብን፡፡

ዞኖች “ክልል እንሁን” የሚለው ሌላው ተግዳሮት ነው ብዬ አንስቼ ነበር፡፡ የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ተመልሷል፡፡ አሁን በደቡብ ክልል ወደ አስር የሚሆኑ ዞኖች የክልል እንሁን ጥያቄ አንስተዋል፡፡ በእኔ እምነት የክልልነት ጥያቄ ኢኮኖሚያዊ፣ ስነ ልቦናዊ እና ከማንነት ጥያቄ ጋር የሚያያዝ ይመስለኛል፡፡ ለእነዚህ ጥያቄዎች መፍትሔው ተከታታይ ውይይቶችን በማካሄድ ኢኮኖሚያዊና ስነ-ልቦናዊ ጥያቄዎችን መቅረፍ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ ጥያቄውንም ሊያረግበው ይችላል፡፡

ወደኋላ እያዩ ወደ ፊት ለመሄድ የሚፈልጉ ግለሰቦችና ቡድኖች መኖር የለውጡ ተግዳሮት እንደሆነ ያነሳሁትም፤ በአንዳንድ ወገኖች ፓርቲ መር ሆኖ የመንቀሳቀሻ አጀንዳ እየሆነ ነው፡፡ በታሪክ ብዙ ስህተት ተፈጥሮ ሊሆን ይችላል፤ ተፈጥሯልም ብዬ አስባለሁ፡፡ ይኼ ግን ኢትዮጵያ ላይ ብቻ የሆነ አይደለም፡፡ ጀርመን፣ እንግሊዝ፣ሩስያ የትም ሀገር ሂድ በታሪክ ጥሩም መጥፎ ነገር ተፈጥሯል፡፡ የቀድሞ መሪዎች እንዲህ አደረጉ፤ አላደረጉም የሚል ክርክር የሚጠቅም አይመስለኝም፡፡ በታሪክ ከዚህም በላይ ተፈጥሮ ሊሆን ይችላል፡፡ ጭቅጭቁን በማለዘብ፣ ካለፈው ትምህርት በመውሰድ ጠቃሚ ጠቃሚውን በማጎልበት፣ ቆሻሻውን ድርጊት ኮንኖና ድጋሚ እንዳይመጣ ማድረግ ነው የሚጠበቅብን፡፡

ጀርመን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ዐመድ የሆነች ሀገር ነበረች፡፡ ያለፈውን ችግራቸውን ወደ ጎን ትተው፤ ሙዚየም ውስጥ ከተው፣ ወደፊት በማየት አሁን ምን የመሰለ ሀገር ገንብተዋል፡፡ የጃፓንም አካሄድ እንደዚያው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ይኼንን መከተል ያለባት ይመስለኛል፡፡

አዲስ ልሳን፡- በአገራችን ላይ የእርስበርስ ግጭትና የመፍረስ አደጋ እንዳዥበበ የተለያዩ አካላት ይናገራሉና ይህንን እንዴት ይመለከቱታል?

 

ፕ/ር ተስፋዬ፡- ያንዣበበ ግጭት፣ የመፈራረስ አደጋ አለ የሚባለው ማስፈራሪያ ሳይሆን እውነትነት ያለው ይመስለኛል፡፡ ዋልታ የረገጡ ሀይሎች ጫፍና ጫፍ ሆነው ገመድ ጉተታ ውሰጥ ነው ያሉት፡፡ ገመድ ጉታተው መጨረሻ ላይ እነሱን ጨምሮ ሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ይዞ ነው የሚጠፋው፡፡ አሸናፊ አይኖርም፤ ሁሉም ተሸናፊ ነው የሚሆነው፡፡ የጽንፈኞች ዋና ዓላማቸው ወክለነዋል በሚሉት ብሔረተሰብ ስም ስልጣን ላይ መውጣት ነው፡፡ አፈ ታሪኩን ከትክክለኛው ታሪክ ጋር በመደበላለቅ የህዝቡን ስሜት በመቀስቀስ ብቻ የሥልጣን ማማ ላይ የሚወጣ ይመስላቸዋል፡፡ የተማረው ክፍል፣ ኢትዮጵያ እንድትድን የሚመኝ ሕዝብ በሙሉ እውነታውን ከማሳወቅ ወደኋላ ማለት የለበትም፡፡

አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ በግልጽ የሚታየው ዋልታ ረገጥ ኃይሎች ሲጨፍሩ፣ ከ90 በመቶ በላይ የሆነው አብዛኛው ማለት ብዙሃኑ ህዝብ (the Silent Majority) ዝም ብሎ ተመልካች ሆኗል፡፡ ይህ አሁኑኑ መለወጥ አለበት፡፡ ሜዳውንም፣ ወሬውንም፣ መሳሪያውንም፣ ቃላቱንም ለጽንፈኞች ትቶ ሌላው ፀጥ ብሎ እየተመለከተ መሆኑ ከፍተኛ አደጋ ሊያመጣ ይችላል፡፡ ብዙሃኑ ዝም ያለው ህዝብ ራሱንም ሀገሪቱንም ለማዳን ዛሬውኑ መንቀሳቀስ መጀመር አለበት፡፡ ንዑስ ከበርቴው (የእኔ አይነቱ) አንድ ቤት ካለው ሁለተኛ ቤት ለመስራት፣ አንድ መኪና ካለው ሌላ መኪና ለመጨመር የተጨነቀ (obssesed) የሆነ ይመስለኛል፡፡ ግጭትና ጦርነት ከመጣ ቤትም፣ መኪናም፣ ገንዘብም፣ ልጆችም፣ ቤተሰብም ሁሉም ነገር ዱቄት ይሆናል ይጠፋል፡፡ መፍትሔው ህዝቡ ራሱን ማደራጀት አለበት፡፡ በሀገር ደረጃ፣ በከተማ፣ በገጠርም ራሱን ከጽንፈኛ ሀይሎች ለመከላከል መደራጀት አለበት፡፡

አዲስ ልሳን፡- አፍሪካዊያን ችግሮቻቸውን በውስጥ አደረጃጀታቸው የመፍታት ልምዳቸው ምን ያህል እየጎለበተ መጥቷል?

ፕ/ር ተስፋዬ፡- የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካዊያን መፍትሔ መስጠት (African Solutions to African Problems) የሚል ጥሩ መፈክር አንግቧል ፡፡ ይህ ነገር መጎልበት አለበት፡፡ ለምሳሌ የናይልን ያልተፈቱ ችግሮች ይዞ አትላንቲክን አቋርጦ ዋሽንግተን ዲሲ ድረስ ይዞ መሄድ ለእኔ አይታየኝም፡፡ የናይል ወንዝ ያለው እዚህ ነው፡፡ ለምን እዚያ እንሄዳለን? ይኼ መፍትሄ ማግኘት ያለበት ወንዙ ከሚፈስባቸው ሀገሮች ጋር በመነጋገር ነው፡፡ ዋሽንግተን ዲሲ መሄድ የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካዊያን መፍታት ከሚለው መርህ በተፃራሪ የቆመ ነው፡፡ ለአፍሪካ ህብረትም የሚያሳፍር ነው፡፡ ለምሳሌ አሁንም እልባት ያላገኘው የናይል ድርድር በዚህ ወር መፍትሔ ካላገኘ ጠ/ሚ ዓቢይ ደቡብ አፍሪካ ለጉብኝት ሄደው ፕሬዚዳንት ራማፎዛን ቃል ባስገቡት መሰረት ደቡብ አፍሪካ እንድትሸመግል ማድረጉ የአፍሪካ ሕብረትን መፈክር ተግባራዊ ማድረጊያ ጥሩ ምሳሌ ይሆናል፡፡

አዲስ ልሳን፡- ውድ ጊዜዎን ሰውተው ስለሰጡን ሰፋ ያለ አስተያየት እናመሰግናለን

ፕ/ር ተስፋዬ፡-እኔም አመሰግናለሁ፡፡

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop