የሚኒስትሮች ምክርቤት ከስልጣኑ በላይ ያፀደቀው ሰነድ አወዛገበ

(በፍሬው አበበ)

የኢፌዲሪ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሃግብር የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት እንዲያጸድቀው መቅረቡ አግባብነት ላይ አንዳንድ አባላት ጥያቄ አነሱ።

በሚኒስትሮች ም/ቤት ታይቶ ትላንት ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የቀረበው የብሔራዊ ሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሃግብር በሰነዱ ላይ “በሚኒስትሮች ም/ቤት የጸደቀ” በሚል መቅረቡ አንዳንድ የኢህአዴግ የፓርላማ አባላትን የሰነዱ ለፓርላማው መቅረብ ፋይዳ ጥያቄ እንዲያነሱ አስገድዷቸዋል።

በፓርላማ አባላቱ የተነሱት የድርጊት መርሃግብር በፓርላማ መጽደቅ አለበት ወይ?ፓርላማውስ እንዲህ ዓይነት ሰነድ የማጽደቅ ሥልጣን አለው ወይ? ሰነዱ በሚኒስትሮች ም/ቤት ከጸደቀ ፓርላማው እንደገና ማጽደቁ ምን ፋይፋ እንዳለውና ሰነዱ ቀደም ብሎ ባለመሰራጨቱ ዝርዝር አስተያየት ለመስጠት መቸገራቸውን የሚጠይቁ ነበሩ።

በሰነዱ ላይ አጭር ማብራሪያ ያቀረቡት በፓርላማ የመንግስት ተጠሪ ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መለስ ጥላሁን “ሰነዱ የተሰራጨው ትላንት ነው። በቂ ጊዜ አልነበረም በሚል የቀረበው ኀሳብ ትክክል ነው” ሲሉ አምነዋል። ነገር ግን ሰነዱን ፓርላማው መመልከት አለበት ወይስ የለበትም የሚለውንም ጉዳዩ የሚመራለት ቋሚ ኮሚቴ ቢመለከተው የሚል ኀሳብ አቅርበው ሌሎችም አዋጆች በሚኒስትሮች ም/ቤት ጸድቀው ወደፓርላማ እንደሚቀርቡ እግረመንገዳቸውን አስታውሰዋል።

አቶ አባዱላ ገመዳ የፓርላማው አፈጉባዔ በሰነዱ ላይ “በሚኒስትሮች ም/ቤት የጸደቀ” በሚል የተጻፈው በስህተት ነው፤ የሚያጸድቀው ፓርላማው ነው በማለት ማስተካከያ እንዲደረግ አሳስበዋል። አያይዘውም ሰነዱ ዓለምአቀፍ ስምምነትን መሰረት አድርጎ ተዘጋጀ መሆኑን፣ ዓለምአቀፍ ስምምነት ያላቸው ጉዳዮች በሙሉ በፓርላማ መጽደቅ ስላለባቸው ሰነዱ ወደፓርላማው መመራቱ ትክክል ነው ብለዋል።

የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር የማዘጋጀቱ ጉዳይ እ.ኤ.አ በ1993 ዓ.ም በተካሄደው ሁለተኛው የቪየና ዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት ኮንፈረንስ ላይ ትኩረት ተሰጥቶት በሃገራት መካከል መግባባት መደረሱን ተከትሎ የተዘጋጀ ሰነድ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢትዮጵያ በመጪው ጊዜዎችዋ ከባድ ደመናን ያዘለ የርስ በርስ መጠፋፋት ዝናብ እንዳጃበባት አንድ ጥናት አመለከተ

ከ2005-2007 ዓ.ም ሥራ ላይ ይውላል የተባለው ግን ገና የመጀመሪያውን ግምሽ ዓመት በረቂቅ ደረጃ ያጠናቀቀው ይኸው ሰነድ ያስፈለገበት ዋንኛ ምክንያት በሕገመንግስት የተረጋገጡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አተገባበር ይበልጥ እየተጠናከረና እያደገ የሚሄድበት ሁኔታ ማመቻቸት ሲሆን ኢትዮጽያም ከነሃሴ ወር 2003 ዓ.ም ጀምሮ ሰነዱን ወደማዘጋጀቱ መግባቷ የሚታወስ ነው።

Source: Sendek Newspaper

Share