ከኢህአዴግ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የተሰጠ መግለጫ

ኢህአዴግን ከግንባርነት ወደ አንድ ህብረ ብሄራዊ ውህድ ፓርቲ የማሸጋገር ጉዳይ በ1996 ዓ.ም ከተካሄደው 5ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ጀምሮ በተከታታይ በተካሄዱት የድርጅቱ ጉባዔዎችና የተለያዩ ድርጅታዊ መድረኮች ሲነሳ የቆየ ጥያቄ እንደሆነ ይታወቃል። በሁሉም የኢህአዴግ መድረኮች በውህደቱ አስፈላጊነት ላይ ስምምነት እየተያዘበት የሄደ ሲሆን በየጉባዔዎቹ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ውህደቱን በጥናት ላይ ተመስርቶ ለመፈፀም የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ቆይተዋል። ይልቁንም በቅርብ ጊዜያት በተካሄዱ ጉባዔዎች ይነሳ የነበረው ቁልፍ ችግር በአፈፃፀሙ ላይ የታየው ከፍተኛ መጓተት ነበር። በተለይ ባለፈው አመት በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው 11ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ የጥናት ስራው በቶሎ ተጠናቆ የኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ውህደት ፈጥረው አንድ ጠንካራ ሀገራዊ ፓርቲ እንዲፈጠር ውሳኔ ተላልፏል። በሂደቱ የአጋር ድርጅቶችም ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ ተቀምጧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የውህደቱ አቀንቃኝ ሆኖ ውህደቱን ሲመራ የነበረው ህወሃት በአሁኑ ወቅት ውህደቱን በተመለከተ አሉታዊ ገፅታ ያላቸው ተደጋጋሚ መግለጫዎችን በማውጣት ላይ ይገኛል። ምንም እንኳን ጉዳዩ በሂደት ላይ ያለና ያልተቋጨ በመሆኑ በዚህ ወቅት መግለጫ መስጠትም ሆነ በሚወጡ የተሳሳቱ መግለጫዎች ላይ መልስ መስጠት አስፈላጊ አይደለም በሚል እምነት ጉዳዩን በዝምታ ለማለፍ የተሞከረ ቢሆንም የተሳሳቱ መረጃዎች ተደጋግመው ሲወጡ ችላ ማለት ደግሞ ህዝቡ ውስጥ መደናገርን ሊፈጥር የሚችል መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ለህዝቡ ጠቅለል ያለ መረጃ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።

ህወሃት እንደ ድርጅትም ሆነ በአንዳንድ አመራሮቹ በተደጋጋሚ የሚሰጣቸው መግለጫዎች በሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች ስህተት ሆነው እናገኛቸዋለን። የመጀመሪያው ስህተት ከድርጅት አሰራርና ዲስፒሊን ጋር የተያያዘ ነው። በድርጅቱ አሰራርና ህገ ደንብ መሰረት የግንባሩ አባል ድርጅቶች በማንኛውም አጀንዳ ላይ ውይይትና ክርክር ካደረጉ በኋላ የመሰላቸውን አቋም መያዝና በአቋማቸውም ላይ ተመስርተው ክርክራቸውን መቀጠል የተለመደ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በኩዌት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ አሳሳቢ ሆኗል

በ2011 ዓ.ም በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው 11ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ ህወሃትን ጨምሮ ሌሎች አጋርና አባል ድርጅቶች ጥናቱ በአፋጣኝ ተጠናቆ ወደ ተግባር እንዲገባ ያለልዩነት ወስነዋል። በውሳኔው መሰረት ተጠንቶ በቀረበው ሃሳብ ላይ ደግሞ ሁሉም ድርጅቶች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፤ ጥናቱ እንዲዳብርም የበኩላቸውን ተሳትፎ አድርገዋል። በአሁኑ ሰዓት እየተካሄዱ ያሉ ውይይቶችም ከውሳኔ በፊት ጥናቱን የሚያዳብሩ ሃሳቦችን የማሰባሰብ ሲሆኑ በዚህ ደረጃ በተካሄዱ የአመራር ውይይቶች ህወሃትም ሆነ ሌሎች አባልና አጋር ድርጅቶች ተሳትፈዋል፤ አስተያየታቸውንም ሰጥተዋል። የተሰጡት አስተያየቶች ጥናቱን ለማዳበር ወይም ያልታዩ ጉዳዮች በአግባቡ እንዲዳሰሱ ለማድረግ እንጂ የውሳኔ ወይም የአቋም ጉዳይ ሆነው የሚቀርቡ አልነበሩም። በመሆኑም ይህ አጀንዳ ገና በጥናት ውጤቱ ላይ ውሳኔ ያገኘበት ደረጃ ላይ አልደረሰም። የመጨረሻ የውህደት ውሳኔም አሰራሩን ጠብቆ ወደፊት የሚታይ ይሆናል። ጉዳዩ በዚህ ደረጃ ባለበትና የመጨረሻ ውሳኔ ተሰጥቶ የሁሉም ድርጅቶች አቋም ባልተገለፀበት ሁኔታ ህወሃት አስቀድሞ ለብቻው በተደጋጋሚ መግለጫ መስጠቱ የድርጅት አሰራርና ዲሲፒሊንን የጣሰ እንዲሁም ወቅቱን ያልጠበቀ በመሆኑ መታረም ያለበት ነው።

የመግለጫው ሁለተኛው ስህተት ደግሞ ይዘቱ ነው። ህወሃት በተለያዩ መግለጫዎቹ ደጋግሞ የሚያነሳው ውህደቱ አሃዳዊ መንግስት ለመመስረት የታቀደ አስመስሎ ማቅረብ ነው። ፓርቲው ወደ አንድ ወጥ ፓርቲ በሚቀየርበት ወቅት ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብታቸው እንደሚገፈፍና ፌዴራላዊ ስርዓቱ ፈርሶ አሃዳዊ ስርዓት እንደሚመስረት አድርጎ የሚያቀርበው ሃሳብ ለማደናገሪያ ካልሆነ በስተቀር ለመከራከሪያ የሚሆን ተጨባጭ ነገር የለውም። በመሰረቱ የአንድ ሀገር የመንግስት አወቃቀር የሚወሰነው በሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎና በኢትዮጵያ ህዝብ ውሳኔ እንጂ በአንድ ፓርቲ ፍላጎት ብቻ ሊሆን አይገባውም። ስለዚህ የኢህአዴግ ውህደት ለብቻው የአገሪቱን የፌዴራል ስርዓት የሚያፈርስ አድርጎ ማቅረብ ውሃ የሚቋጥር መከራከሪያ አይደለም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  እኔ የምለው.....ክፍል 5 - ጠቅላይ ሚኒስትሩ እውን ሀገሪቱን ተቆጣጥረዋልን? - Anchor Media

ኢህአዴግ ወደ ውህደት መጥቶ ጠንካራ ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ ቢሆን ሀቀኛ ፌዴራሊዝምን እውን በማድረግ እኩልነትና ፍትህ የነገሰባት፣ አንድነቷ የተጠናከረና የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ይታገላል እንጂ የብሄር ብሄረሰቦችንንና ህዝቦችን መብት የሚሸራርፍበት ምንም ምክንያት የለውም።

ጥናቱን ያስጠኑት ህወሃትን ጨምሮ ሁሉም የኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ሲሆኑ የውህደቱ መነሻ ሃሳብም ሆነ የጥናቱ ውጤት ከአሃዳዊ ስርዓት ጋር ፈፅሞ ግንኙነት እንደሌለው ሁሉም ድርጅቶች በግልፅ የሚያውቁት ጉዳይ ነው። ስለሆነም ጉዳዩን ሁሉም የግንባሩ አባልና እህት ድርጅቶች በግልፅ የሚያውቁትና ወደፊት ውህደቱ ቢፈፀም ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች በግልፅ የሚገነዘቡት ሆኖ ሳለ እንዲህ አይነት የተዛባ መረጃ መስጠት መሰረታዊ ስህተት ነው።

ሌላኛው የመግለጫው ችግር የውህደት አጀንዳውን አሁን ያለው የለውጥ አመራር በድንገት ያመጣው በሚያስመስል መልኩ ማቅረቡ ነው። ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው የውህደት አጀንዳው መነሳት የጀመረው ረዘም ካሉ አመታት በፊት እንደሆነ ይታወቃል። ይህ ደግሞ በድርጅቱ ጉባዔዎች፣ ምክር ቤትና ስራ አስፈፃሚ ስብሰባዎች ቃለ ጉባዔዎች ላይ ተመዝግቦ የሚገኝ እውነታ ነው። ሌላው ቀርቶ በአሁኑ ሰዓት ተጠናቆ ለውይይት የቀረበው ጥናት የተጀመረው አሁን ያለው አመራር ወደ ሃላፊነት ከመምጣቱ በፊት እንደሆነ በግልፅ የሚታወቅ ነው። አሁን ያለው የለውጥ አመራር የሰራው ነገር ቢኖር ለረጅም አመታት በልዩ ልዩ ምክንያት ሲጓተት የቆየውን ጥናት እንዲጠናቀቅ በማድረግ ለውሳኔ የሚቀርብበት ደረጃ ላይ ማድረስ ብቻ ነው። ስለሆነም በድርጅቱ ስም በሚወጡ መግለጫዎችም ሆኑ አንዳንድ አመራሮች በሚሰጧቸው ማብራሪያዎች የውህደቱን ሃሳብ አዲሱ የለውጥ አመራር በስልጣን ላይ ለመቆየት ሲል እንዳመጣው አስመስሎ ለህዝብ ማቅረብ የተሳሳተ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በምዕራብ ሃረርጌ የታሰሩት ሼህ ሃሰን በእስር ቤት ሕይወታቸው አለፈ

በአጠቃላይ ኢሕአዴግን ወደ አንድ ህብረ ብሄራዊ ውህድ ፓርቲ የመቀየሩ ሃሳብ ዋነኛ ምክንያቶች አሁን ያለው የግንባሩ አደረጃጀት አባል ድርጅቶች የጋራ አሰራርን በሚጥሱ ጊዜ የድርጅቱ የውስጥ ጥንካሬ አደጋ ላይ የሚወድቅ መሆኑ፣ የግንባሩ የተጠናከረ ሀገራዊ አንድነት በመፍጠር አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመፍጠር ግቡን በተሟላ ሁኔታ ማሳካት አለመቻሉ፣ አጋር ተብለው የሚጠሩ ድርጅቶችን ከውሳኔ ሰጪነት ያገለለና የሚመሯቸውን ክልሎችና ህዝቦች አቃፊ ባለመሆኑ፣ ማንኛውም የሀገሪቱ ዜጋ በቀጥታ የድርጅቱ አባል ሆኖ መታገል የሚችልበትን እድል የሚሰጥ ያለመሆኑን እና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል አደረጃጀት እንዲኖር ታሳቢ በማድረግ እንጂ ህወሃት በመግለጫዎቹ ባስቀመጣቸው ምክንያቶች እንዳልሆነ መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች እንደሚገነዘቡት እንተማመናለን።

በተጨማሪም ከዚህ አጀንዳ በተያያዘ በቀጣዮቹ ጊዜያት በየደረጃው የሚገኙ የድርጅቱ መዋቅሮች (መድረኮች) የሚወስኗቸውን ውሳኔዎች የድርጅቱ አሰራር በሚፈቅደው ዲሲፒሊን መሰረት ለመላው የድርጅታችን መዋቅርና ለሀገራችን ህዝቦች መረጃዎችን የምንሰጥና ግልፅ እያደረግን የምንሄድ መሆናችንን በዚሁ አጋጣሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን።

1 Comment

  1. Ere fexarii bitintinachiwun yawuxa. Yaxifachiw, yigersisaachiw. TPLF na telalakiwochun anfeligim. Demachinin yemexexuu hulla. GOD xifatachiwun yafaxin. OPDO yenefxenya shintim keoromiya na itophiyaa midir yaxifah. Wushoch. Ahun yih hulu girigirri yezerefachihutin lemadan new. Bezerefa yetegenye habtim inantem atidinum. Min ale beleny, tixefalachiw.

Comments are closed.

Share