“…አወቅሽ ።አወቅህ።”ሥንላቸው ፣መፅሐፍ እያጠቡ ያሉትን የሚያንጓልልን ከሆነ የመደመር ፍልስፍናን እንደግፋለን። – መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

 “አወቅሽ፣አውቅሽ ቢሏት የባሏን መፅሐፍ አጠበች”
በድሮ ጊዜ ነው አሉ ፣ አንድ ያለማወቋን የማታውቅ ሆና  አውቃለሁ የምትል ሴት ነበረች።ይህቺ ሴት   ከሠፈሯ ካለው ምንጭ፣ ውሃ ለመቅዳት፣ የሚመጡትን  ሴቷች ሁሉ፣ከሰላምታ በፊት በወሬ ነበር  የምትቀበላቸው ።  ሥራ ፈት ሥለሆነችም ከምንጩ ዳር አትታጣም።  ውሃ ለመቅዳት የሚመጡትንም ሴቶች  በተለያየ ወሬ  እየነተርከች ታሥቸግራቸው ነበር።
        አንድ ቀን ለመንደሩ እንግዳ የሆኑ፣ “በእህል ውሃ አሥገዳጅነት ” ወደ አካባቢው የመጡ ሁለት ጎረቤታም ወይዛዝርቶች ውሃ ለመቅዳት ሲመጡ አየች።ከተቀመጠችበት ተነሥታም ወደእነሱ ሄደች።በእግዜር ሰላምታ ፋንታም የዕውቀቷን ልክ መቀባጠር ጀመረች።
      “እናንተዬ ! የዚህ መንደር ሰዎች ያዋቂ ምክር አይሰሙም።የሚያውቅ ከሚመክራቸው አላዋቂ ቢሰድባቸው ይመርጣሉ።አያችሁ፣እኔ ዕውቀት አለኝ።ደሞም ሴት ወይዘሮ ነኝ።የምሰራው ዶሮ ወጥ  ጣት ያሥቆረጥማል። ዶሮ ወጥ ሥሠራም  ሽታውን ለማጥፋት ከሎሚ ጋር እንዶድ ቀላቅዬ ነው።ይህንን ዘዴ ተመራምሬ ነው የደረሥኩበት።  ” ምራቋን ለመዋጥ ንግግሯን ለአፍታ አቋረጠችና  እንደእብድ መቀባጠሯን ቀጠለች።
     ” በሎሚው ጭማቂ  ላይ አንድ ዘለላ እንዶድ ጨምሮ ማጠብ ደግሞ እንዴት እንደሚያፀዳው ብታውቁ ትገረማላችሁ። ” በማለት ወሬዋን አይኗን  በሴቶቹ  አይን ላይ እያቁለጨለጨች  ነዝታ ጨረሰች።
  ወሬዋን እንደጨረሰች፣  ወይዛዝርቱ  ” በእርጎ ዝንብነቷ”  ተገርመው ፣በጨዋ ደንብ “ይህንን እኛ አናቅም።ይህ እውነት ከሆነ መቼም የጠቆምሽን  ዕውቀት የሚያስደንቅ ነው።” በማለት፣አመሥግነዋት ወደቤታቸው ሄዱ። በማግሥቱም ያለቻቸውን  በተግባር ሲሞክሩት የአረፋው መኩረፍረፍና የሎሚው ከእንዶዱ ጋር የፈጠረው ሽታ ፣ አፍንጫቸውን በመሰርሰር ያሥነጥሥና ይሰናፍጣቸው ጀመር።…
  ቶሎ ብለው፣   ውሃ በብዛት በመጨመር፣ የእንዶድና  እና የሎሚው ውህደት የፈጠረውን መጥፎ ሽታ  አስወገዱ ና በሌላ ንፁህ ዕቃ አድርገውም ሎሚ በመጨመር ፣ እንደገና   የዶሮውን ሥጋ አጥበው መጥፎ ሽታውን አስወገዱ።…
    በሣምንቱ ፣ውኃ ለመቅዳት ወደ ምንጭ   ወረዱ።ወሬኛው ሴትዮም  ፣እንደልማዶ ከምንጩ ውሃ ዳር ፣ቁጢጥ ብላ አገኟት።ዛሬም እንደልማዶ ፣ ሣታውቅ አውቃለሁ እያለች ፣ እንዳታውቅም ጆሮዋን ጠርቅማ ያለማቋረጥ ትለፈልፋለች።  ቅጥፈት ና ሐሰቱን፣ በድፍረት ትዘባርቃለች ። ሴቶቹ ወደ እርሷ ሲመጡ ሥታይ እርሷም ተነሥታ ወደነሱ ሄደች።
     አጠገባቸው እንደደረሰች፣ ሥላለፈው ያላወቂ ሃሳቧ ሊነግሯት አፋቸውን ሲያሞጠምጡ:-
    ” እኔን ሥሙኝ ! እኔን በቅድሚያ ሥሙኝማ ! ይሄውላችሁ ወደዚህ ከመምጣቴ በፊት የባሌ ዳዊት እጅግ ቆሽሾ ሥላገኘሁት በእንዶድ አጥቤው ፣ፀሐይ ላይ አሥጥቼው መጣሁ።” አለቻቸው።ይህንን የአዋቂ ሣይሆን የጅል ተግባር ሲሰሙ ሆዳቸውን ይዘው በሳቅ ጦሽ አሉ።
       “ቂቂቂቂቂቂቂቂቂቂቂቂ…..አወቅሽ አወቅሽ ቢሏት ይኽቺ ጅል የባሏን መፅሐፍ በእንዶድ አጠበች። ይገርማል!! ” ብለው፣ ድርጊቷ ማንነቷን ሥለከሰተላቸው ያላዋቂ ምክሯ ያደረሰባቸውን ችግር ሳይነግሯት እየተገረሙ ውሃቸውን ቀድተው ሄዱ።…
     በተረቱ ውስጥ እንዳለችው ወሽካታ ና ጅል  ሴትዮ ዓይነቶች   በዚች ሀገር እያደር እየበዙ መጥተዋል።
     በማሥተዋል መነፅር ሥንመለከት ፣በፖለቲከኛው ና በአክቲቪሥቱ ጎራ ሣያውቅ አውቃለሁ ባዩን እና የቆርጦ ቀጥሉ ብዛት እያደር እየጨመረ መጥቷል።  እናም በዚች ምሥኪን ሀገር ” አወቅህ !አዋቀሺ !” ሥንላቸው፣ ሳያፍሩና  ሣይፈሩ መፅሐፍ ሲቆሽሽ መታጠብ አለበት የሚሉን እየበዙ  ነው።
   እሥቲ በማሥተዋል የእያንዳንዱን አገልግሎት ሰጪ  የዕውቀት ና የተግበር ችሎታ  የእውነትና የምር” ይፈተሽ ቢባል ፣ ብቃቱ መፀሐፍ ከማጠብ የከፋ አገልግሎት ሰጪ አይገኝምን??
     ዕውቀት ችሎታ፣ብቃት ና ትጋት ከቶም የሌላቸው፣ በየደረጃው ና በየፈርጁ ፣ረብጣ ብር እየተከፈላቸው በመሥራት ፣ አያሌዎችን  የጎዱ  እና እንዲጎዱ ምክንያት የሆኑ እንደሉ፣በድፍን ሀገር ቢወራም   በማሥረጃ ማረጋገጥ ባለመቻሉ  ፣እነዚህ በለዲግሪ ማይማን መፀሐፍ ማጠባቸውን ቀጥለዋል።
     ሙያተኞች እንደደረጃቸው፣አገልግሎት እየሰጡ ነው ወይ?ህዝብን በእውቀታቸው ደረጃ እያገለገሉ ነው ወይ?   … የሚል ጠያቂ ፣ መርማሪ ና አሥቀጪ ተቋም በፌደራል ደረጃ  ባለመኖሩ ፣ያላዋቂዎች መፀሐፍ እያጠቡ ነው። …
      እድሜ ለኢህአዴግ  የትሞህርት ፖሊሲ ይበሉ ና በገዙት  ዲፕሎማና ዲግሪ ፣ ማሥትሬት ና ዶክተሬት ፣በሌላቸው እውቀት አንዳችም ፋይዳ ያለው ቱግባር ሳይፈፅሙ ሆኖም በማሥመሠል ፣ መፅሐፍ እያጠቡ እንኳን የማወደሱ አሉ።
     በሁሉም የሙያ ዘርፍ
    ከጥበብ በራቁ ግን ዲግሪ በተሸከሙ፣ለተገልጋዩ ሰው ሳይሆን ለገንዘብ ና ለቋንቋ ብቻ  የሚጨነቁ  ባለሙያዎች ዛሬም “ሠርቶ በላውን ” እያማረሩት፣”ወሮ በላውን” እየጠቀሙት ነው።ይህ ብቻ አይደለም ከሰው ጤና ጋር የተያያዘ ሥራ ያላቸው ባለሙያዎች ሁሉ ጥራት ና ብቃት አላቸው ብለን ለመናገር አንደፍርም።ይህ ሀገር ያወቀው፣ፀሐይ የሞቀው እውነት ነው።የጤና ጥበቃም የህክምና ጥራትን ለመጠበቅ ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ  ነው።በመንግሥት ጤና ጣብያዎች እና ሆስፒታሎች ውስጥ እያየን ያለው ለውጥ ቢያሥደሥተንም፣የግሉ የህክምና ተቋም አሰራር ግን ያሳስባል።
      ተገልጋዩ የደረሰበትን የማይቀለበሥ የህክምና ሥህተት በማሥረጃ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በግልፅ ሥላወራ አልደግመውም፣ነገር ግን ቀዳሚ ትኩረታቸው ሰው ማዳን ላይ ያልሆነ፣ አንዳንድ የግል ሆስፒታል ባለቤቶች አልፈው ተርፈው ምንም የተግባር ዕውቀት በሌለው ነጭ ህብረተሰቡን ለመበዝበዝ ሲዳዱ አሥተውያለሁና የጤና ጥበቃ ሚኒሥቴር እነዚህ ላይ ልዩ   ትኩረት እንዲያደርግ እጠቁማለሁ።በእኛ ሀገር እኮ በየዘርፉ   የላቀ ዕውቀትና ችሎታ ያላቸው ኃኪሞች አልጠፉም።አዲሥ ከሚመረቁትም የሀገር ተሥፋ የሆኑ አራት ዓይናማዎች አሉ።እነዚህን ማበረታታትና የነፃ ትምህርት በአውሮፖ የሚያገኙበትን መድረክ ማመቻቸት ያሥፈልጋል።ምክንያቱም እነዚህ ጥበበኞች የሀገር ብቻ ሣይሆን የዓለም ተሥፋዎች ናቸውና።በእርግጥ በሁሉም የሳይንሥ ትምህርት ዘርፍ መሰል ወጣቶች እንዳሉ ምሥክር አያሻውም።እንደ “አንድሮ ሜዳ” የጄቲቪ ኢትዮጵያ ፕሮግራም፣ በየትምህርት ቤቱ እነዚህን ለማግኘት ና በሚዲያ ለማቅረብ ጥረት አልተደረገም እንጂ።
    እነዚህ ወደፊት  የሚያሥጉዙን ፣የፈጣሪ ሥጦታዎቻችን ናቸው።ፀጋዎቻችንን በጊዜና በወቅቱ በመጠቀም ፣ከመሞታችን በፊት ለሀገር ዕደግት ና ብልፅግና ማብቃት ሲገባን ፣ ሆዳችንን በማፍቀር፣ለምቾት ተገዝተን፣ ምቾታችን ዘላለማዊ ይመሥል ፣ ባልጠግባይነት ሥንባዝን፣ አንዳችም እርካታ ሣናገኝ ድንገት ወደመቃብር መግባታችን ያሳዝናል።
      ዓለም ከተፈጠረችበት እና ሰው በምድር ላይ ፣ ምናልባትም ሁለት ወይም አራት ወይም ሥድሥት ወይም አሥር ወይም … ሆኖ ከኖረበት ጊዜ ጀምሮ ፣ አሁን ካለው ቢሊዮን  ሰው ይልቅ መቃብር የገባው፣ በቢሊዮን ሊበልጠ ይችላል።
    እውነት ነው ፣ትላንት ብዙ የምናውቃቸው ሰዎች ሞተዋል።ዕድሜ ለሞት ይሁንና የሁሉም ሞች  መጠሪያ ግን አንድ ነው።ዓለም ባወጣችለት ሥም አይጠራም።ሬሣ ነው የሚባለው።ሲሞትም ሙት ወቃሽ አያድርገኝና እንዴት ዓይነት ክፉ ሰው ነበር ?! ነው የሚባለው።
     አሥከሬኑ ወደቀብር ሥፍራ ሲመጣም፣  የሟችን አሥከሬን ማንም ሰው ” ያ ኦሮሞ መጣ፣ያ ትግሬ መጣ፣ያ አማራ መጣ ወዘተ ።” ብሎ አይጠራም።
       ፖለቲካችን ሰውን የሚጠራበት አጠራር፣ከውልደትና  ከሞት አጠራር ያነሰ ነው።ፓለቲካችን አሣታፊ ወይም ደማሪ አይደለም።አግላይና ቀናሽ ነው። አትደረሱብኝ “እዛው በፀበላችው።” ባይ ነው። የሥሥታም እና የሆዳም መገለጫ ባህሪዎች ዛሬም በፖለቲካችን ውስጥ አሉ። የእገሌ ነን እንጂ የብዙሃን አይደለንም ባይ ከመቶ በላይ ፓርቲዎች ይህቺን የብዙሃን ሀገር ለመምረት ሲፎካከሩ ያሥቁኛል።የእኔ እና የእኔ ወገን ይቅደም የሚል ሥሥታምና ሥግብግብ ሀገርን ያፈርሳል እንጂ ሀገርን አይመራም። በእኔነት የሠከረ ፖለቲከኛ  ሀገር መምራት ፈፅሞ አይችልም። እኔ እና የእኔ ወገን ባይ ፓርቲ ሁላ ፣ የመደመር ጠር ነው።
    በመሆኑም ሥልጣን ቢይዝ   የገዘፈ አእምሮ ያላቸውን ለሥልጣን የሚፎካከሩ  ወጣቶችን ገና ለገና ሥልጣኔን ይነጥቁኛል ፣ቅንጦቴንም ያጎድሉብኛል ብሎ በመፍራት በእሥር እና በግድያ ከተፎካካሪነት ይቀንሣቸዋል እንጂ አይደምራቸውም።
    የራሳቸው  የተለየ ሃሳብ ያላቸውን እና እውነትን የያዙ ጎምቱ ምሁራንንም ያገላል እንጂ አያቅፍም። ካላቀፈ ደግሞ ቀናሽ እንጂ ደማሪ አይደለም።ደሞም በተግባር ከእኔ ብላይ የሚያውቁ ሀገርን በፍፁም ቅንነት ማገልገል የሚችሉ ዜጎች አሉ ብሎ የማያምን ግብዝ ነው።
    በመደመር ፍልስፍና ሳትቀንስ ፣ሣትሰርቅ ለመሥራት፣እንዱምሳሌ የሆኑ ግለሰቦች በአዲስ አበባ ተገኝተዋል። በራሳቸው ቀጥተኛ ተሳትፎ፣አምሳቲም በካሽ ሳይሰጡ ፣ የህዝብና የመንግሥት ሀብቶችን ማለትም ትምህርት ቤት ና ሆስፒታሎችን አድሰዋል።
      ጠቅላይ ሚኒሥቴራችንም በመደመር ፍልሥፍናቸው የሚኒሊክን ቤተመንግሠትን ልዩ፣ልዩ ጥንታዊ ህንፃዎችንን  እና በኢህድሪ መንግሥት የተሰራውን ህንፃ ለቢሮ በሚሆን መልኩ አሳምረው ለማሳደሥ  የመደመር ፍልስፍናቸው ጠቅሟቸዋል።
   በሚያሳዝን መልኩ፣በተቃራኒው፣   በየክልሉ ለተረጂዎች አዋጡ እየተባለ ገንዘቡ በግለሰቦች ይበላ ነበር። ዛሬም መሰል አሰራር የለም ማለት አይቻልም።… እናም፣ የላይኛው ከታችኛው ጋር ወይም ፌደራል ከክልል ጋር ካልተደመረ ፣ የመደመር ፍልስፍናን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል?!
      በበኩሌ “የመደመር ፍልስፍና እውን የሚሆነው ኢህአዴግ የተባለው ፓርቲ እሥከናካቴው ሲከስም ብቻ ነው።” ባይ ነኝ። ሌላ ዴሞክራሲያዊ የሆነ አዲስ ፓርቲ ፣ከሌሎች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲዎች ጋር ተደምሮ መፍጠር አለበት። አብዮትንም ልማትንም የሥሙ ተቀጥላ ባያረጋቸው መልካም ነው።በእውነት  ዴሞክራሲያዊ ከሆነ ተራማጅም ይሆናል ልማትንም በተግባር ለመላ ህዝቦ ያዳርሳል( …)።
    እናም በግሌ እንዲህ ብዬ እመክርሃለሁ፣ ” ኢህአዴግ ሆይ፣     በአሮጌ አቁማዳ አዲስ ወይን ስትጨምር የሚያጋጥምህ ምን እንደሆነ ድርጊቱን ሥትፈፅመው ታውቀዋለህ።መፀሐፍ አጠባ ማለትም ምን ማለት እንደሆነ ይገባሃል።”
   በሀገራችን፣ ከዘበኛ ና መዝገብ ቤት ጀምሮ መፅሐፍ ማጠባቸው ሣያንሥ ኪሥ የሚያጥቡ ጥቂት እንደማይባሉ የለውጥ መሪው አሳምሮ ያውቀዋል።
        በሲቪል ሰርቪሱ ውሥጥ  በቅጥር የሚሰሩት (በሁሉም ክልል) ቀበሌ፣መዘጋጃ፣አገር ውሥጥ ገቢ ወዘተ ያሉ ቁልፍ ቦታ ይዘው የባሉጉዳዩን ዶሴ በመደበቅ፣ጊዜውን በመግደል፣ቀጠሮ ና ያለአሥፈላጊ ማሥረጃ እንዲያቀርብ በማሥገደድ ” አሥቀድመህ ፀጉር ለሌለበት መላጣ ሚዶ መግዛት ነበረብህ።”  በማለት የሚያዱናግሩ ፣መላጣው ግራ ተጋብቶ  ” ሚዶውን ግዛ ያሉኝ እነዚህ ሰዎች  ለምንድነው? “በማለት  ሰው ሲያማክር “ላለብህ የመረጃ ክፍተት ማሞያ የሚዶውን ጥርስ ቆጥረህ ኖት፣ኖቱን ከች አደርግ ነው፣የሚሉህ።”በማለት ቅኔውን እንደሚፈቱለትም ይገነዘባል።
    እነዚህ  ፣ ኪሳቸውን ለመሙላት ሲሉ አገልግሎት ተቀባዩን በማሥደንገጥ ፣ተገልጋዩ  “ምን መንግሥት አለና?” በማለት ፣በመንግሥት ላይ እንዲያማርር የሚያደርጉ ፣መሆናቸውን ቢያውቅም፣ ዛሬም፣” የኔን ፓርቲ የሚደግፉ እስከሆኑ ና ብዙዎቹም በፓርቲዬ እሥተታቀፉ ጊዜ ድረሥ  ተገልጋዩን ቁም ሥቅሉን ቢያሳዩት ና “ኤሎሄ…. !”  በማለት የጣር ድምፅ ቢያሰማ መሥሜያችን ድፍን ነው።”የሚሉ ዙሪያውን ከከበቡት ምን ማድረግ ይችላል።
     መንግሥት ፣እንደመንግሥት  በራሱ መዋቅር ውሥጥ ያለን ሌባ የሚቀጣበት አርጩሜ (stick ) ከሌለው ፣ አዳሜ “በመንግሥት ካባ ውሥጥ ተወሽቆ “ህዝብ ማሥለቀሱን አይተውም ና  ኢህአዴግ ፈርሶ ተደምሮ አዲስ ሆኖ ካልመጣ  በነፃ፣ ገለልተኛ፣ፍትሃዊ ና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንድም ተገልጋይ ለገዢው ፓርቲ ድምፁን ሰጥቶ ይመርጠዋል ብሎ ማሰብ ፣ፀሐይ በምሥራቅ ሳይሆን በምዕራብ ትወጣለች ብሎ ከመጠበቅ አይተናነሥም።…
      ዛሬ፣በየክልሉ ያለ አገልግሎት ሰጪን “ወራዳ ሌብነት (pity corruption ) እንተው ና ህግ አሥፈፃሚዎቹ አቃቢ ህግና ፖሊሥ ራሳቸው ለህግ ተገዢ ሆነው እየሰሩ ነው ወይ?? በእውነት ፣ሥለእውነት ለፍትህ እና ለርዕትህ የቆሙ  “ሥልጣን ያላቸው ” ፖሊሶች ና አቃብያን ህጎች ዕውን ከቁጥር የሚገቡ ናቸውን??????
       የህግ መፀሃፍትን እያጠቡ ፣ ፍርድን በማጣመም ና ፣ፍትህን በማዛባት…ከቀበሌ እስከ ክልል በሥርዓት ማሥተዳደር ና ህግን ማሥከበር ሳይሆን ኪሳቸውን በማሥከበር …  ሠርክ፣ ዳቢት ከሻኛ፣ውሥኪ ከቮድካ እያማረጡ ፣በጠራራ ፀሐይ ፣ ያለአንዳች ሀፍራት ፣በደሃው ህዝብ ላይ የሚያጋሱ የበዙ አይደሉም ወይ??? የነዚህ ማፈሪያዎች ፈፃሚያቸው  ያምራልን???
      በኢትዮጵያ ፣ ሥለህግ  በየፈርጁ” ሀ ” ተብሎ ትምህርት መሠጠት አለበት።ትምህርቱም  ለህግ  በተገዛ ና ለሃቅ ና ለእውነት በቆመ  ተቋም  እሥካልተሰጠ ና ህግና ፍትህ በማያከብር ላይ ተገቢ ቅጣት ተግባራዊ እስካልሆነ ጊዜ ድረስ  ፣ ህግም ሆነ ፍትህ “በእኔእነት” ለተደራጁ እንጂ  “ለእኛ” ለዜጎች የማይሰራ መሆኑ ባለፉት 27 ዓመታት  በተግባር ታይቷል።
       ” ቋንቋዊ  ክልል ካለህ ፣  ትልቅና ትንሽ ሥልጣን  እንዲሁም እንዳሻህ የምታዘው  የራስህ ፖሊሥ እና አቃቢ ህግ   ካለህ፣ አንተ ራሥህ እግዜር ነህ።” አለኝ ፣ አንድ በዜግነቱ ብቻ ማግኘት ያለበትን የቀበሌ መታወቂያ ፣ በጎጥ በተቀነበበ ህጋዊ ባልሆነ ምሥክር ወረቀት ብቻ ነው የሚሰጥህ የተባለ ዜጋ በምሬት።እውነቱን ነው። ከሠላሣ ዓመት በላይ በዛው ቀበሌ መኖሩ ና የግል ማህደሩም በቀበሌው መዝገቤት ማንነቱን እየመሰከረ በአሥር ብር ሁለት ገፅ ፎርም ገዝቶ ፣ወደ ጎጥ ኃላፊዎች ጋር መሄድ ና መጉላላት አልነበረበትም።
      በነገራችን ላይ ፣ የዜግነት  መታወቂያ ወይም የኗሪነት መታወቂያ  ለማግኘት የተቀመጡ መሥፈርቶች  በየቀበሌው ግልፅ ሆነው ፣ በማሥታወቂያ ሰሌዳ ሊወጡ ይገባቸዋል። ተከራይተውም ሆነ በግል ቤት የሚኖሩ ፣ መታወቂያ ሊያገኙ የሚችሉት በተቀመጠው ህጋዊ መሥፈርት እንጂ ህጋዊ እውቅ ና በሌለው ፣የጎጥ አመራር በሚሰጠው ምሥክር ወረቀት መሆን የለበትም። ሁለት ገፅ ፎርም አዘጋጅቶ  በአሥር ብር መቸርቸርም ፣ ፍትሃዊ አይደለም። ይህም በራሱ መፅሐፍ ከማጠብ ይቆጠራል።
     ይህቺ ሀገረ፣ ጥርት ባለ ፣ሥርዓት፣ደንብና መመሪያ መመራት እስካልጀመረች ና ከቀበሌ ጀምሮ ፍትህ የሚነግሥበትን ፣ ግልፅ አሰራር፣ ከቅን አገልጋይ ገር ደምረን እስካላሰፈንን ጊዜ  ድረስ፣ህዝብ ፣ሲያወሩ ውለው፣ሲያወሩ በሚያድሩ ና ከቶም በማይደክማቸው፣በተግባር ግን መፅሐፍ አጣቢ በሆኑ ግለሰቦች መሰቃየቱ አይቀሬ ነው።
   እናም   ሀገርን ና ህዝብን ከእነዚህ ቆርጦ ቀጥሎች እና የራሳቸው ሃሳብ ሳይኖራቸው በቀቀናዊ በሆነ ወሬያቸው በመሰሎቻቸው አወቅህ።አወቅሽ።ከሚባሉ  መፅሐፍ አጣቢዎች ለመገላገል “ይበቃል።”ማለት “ይበቃል።”ነው።ባይ የእውነት፣የፍትህ ና የርዕትህ   ድምር ፍልሥፍናን ይህቺ ሀገር ትሻለች።
    መደመር ከመቀነስ ጋር ብርሃን ለመፍጠር ሢል እንደሚጋባ ማወቅም ፣የመደመርን ለመልካም ነገር ፍቃደኝነትን ያሳያል ና ለሰው ልጅ የሚጠቅመውን ሁሉ እየደመረ ሀገርን እና ህዝብን የሚያገዝፍ የመደመር ፍልስፍና  ይህቺ ሀገሬ እንደሚያሥፈልጋት አምናለሁ።
      በይሉንታ፣በፍርሃት ና ባለማወቅ  ” አወቅህ። አወቅሽ።” እያልናቸው መፅሐፍ እያጠቡ ያሉትን የሚያንጓልል እስከሆነ ድረስ የመደመር ፍልስፍናን እንደግፈዋለን።…
ተጨማሪ ያንብቡ:  በራስ መረብ ግብ በማስቆጠር ኦሮሙማን የሚስተካከል የለም!!! - ዳግማዊ ጉዱ ካሣ
Share