ከእጅ አይሻል ዶማ?!! – የአማራ ባለሙያዎች ማህበር (አምባ)

ከሐይለገብርኤል አያሌው

በተለምዶ የተማረ ይግደለኝ ይላል የሃገራችን ሰው። ይህ ሲባል በደፈናው ፊደል ለቆጠረ ዲግሪ ለጫነና ምሁር የተባለውን አድርባይ ፈሪና ጥቅም አሳዳጁን ሳይሆን በእውቀትና በእውነታ ላይ የተመሰረተ ስብእና ያለውን ነው:: አርቆ አስተዋይነት፣ ሚዛናዊነት፣ ፍትሓዊነትን የተከተለ ህዝባዊ ወገንተኝነትንና ሰብኣዊ ርህራሄን ላነገበ ባሉባልታ የማይነዳ በማስረጃ የሚያምን በክርክርና በሃሳብ የበላይነት የሚመራን ምሁር ላቅ የሚያደርግና የሚያከብር ምሳሌዊ ጥቅስ ነው::

በሃገራችን የምሁራን ሚና እጅግ አስፈላጊና ጠቃሚ ቢሆንም የሚፈለገውን ያህል ከልሂቃኑ ተሳትፎንና መፍትሄን አላገኘችም:: ሕዝባችን ላቡን አንጠፍጥፎ ከርሃብና ከድህነት ጋር ታግሎ ካፈራው ጥሪት እየተወሰደ አያሌ ትውልድ በነጻ ማስተማር ቢቻልም ውጤቱ ወርቅ አበድሮ ጠጠር ከመቀበል አልተለየም::

ገበሬው ትላንት ከሚኖርበት የመከራ ሕይወት ሳይላቅቅ አያት ቅድመ አያቶቹ ሲያርሱበት ከነበረ ማረሻና ቀምበር አላቆ ቢያንስ ትላንት ከባርነት ነጻ ወጥተው ሃገር ከሆኑ አፍሪካዊያን በተሻለ የእለት ጉርሱን እንኳ መሸፈን ሳይችል 21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ደርሷል::

ከገበሬው አብራክ የተገኘው አብዛኛው ምሁር ለክብር ያበቃውን ቤተሰብ የተወለደበትን ቅዬ እረስቶ ለምቾት ሕይወት ትኩረት የመስጠት የግለኝነትና እራስ ወዳድነት ቁራኛ በመሆኑ ዛሬ ለደረስንበት ፍትህ አልባና እስፈሪ የኑሮ ጭለማ ምክንያት ሆኗል::

በተለይ የአማራው ሕዝብ ሲዘንብበት ከኖረው የመከራ ዶፍ ሊታደግ አደባባይ የተገኘ ምሁር እጅግ በጣም በጣም ጥቂት እንደነበር መግለጽ ለቀባሪው ማርዳት ነው:: አማራው በማንነቱ ብቻ እየተመተረ ከያለበት ሲሳደድ ሊደርስለት የሚችል ቀርቶ ዳር ሆኖ እንኳ የሚጮህለት ብርቅ ነበር:: ካለፋት ሶስት አመታት ወዲህ የተቀጣጠለው ሕዝባዊ ቁጣ አማራው በሚችለውና ባለው አቅም ጠላቶቹን ለመታገል መነሳቱ የዳር ተመልካች ሆኖ የኖረው ምሁር ብዙም ባይሆን ትግሉን ተቀላቅሏል::

የአማራው ምሁር በሃገር ውስጥ የተለያዩ እደርጃጀቶች ውስጥ በመሪነትና በተሳታፊነት እያሳየ ያለው እንቅስቃሴ ብዙ ጉድለቶች ቢኖሩበትም ከዘርፈ ብዙው የሃገራችን ሁኔታ አንጻር ሲታይ ባያስመካም ለክፉ አይሰጥም::

ተጨማሪ ያንብቡ:  የጂብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል ፤ የሟች ችኩል ገዳይን ይከተላል !

በውጪ ያለው የአማራው ምሁር ካለው አንጻራዊ ነጻነትና የኢኮኖሚ አቅም አንጻር ብዙ መስራት ሲችል አብዛኛው በግለኝነትና በምንቸገረኝነት ተቸንክሮ ቆይቷል:: የቀረው ጥቂቱም የሃገሪቱን ፖለቲካና የዘውግ አደረጃጀቱ አማራውን ለይቶ ማጥቃቱን በቅጡ ካለመረዳት የሕብረ ብሄር ፖለቲካ እናራምዳለን ለሚሉ የአየር ባየር የፖለቲካ ነጋዴዎች የጥገት ላም ሆኖ ገንዘቡንና እውቀቱን ትርጉም ለሌለው ትግል በከንቱ ሲገብር ቆይቶ በምን እንደተጠናቀቀ በቅርቡ ያየነው አይዘነጋም::

የወገናቸው ጉዳይ አሳስቧቸው ቀና አስተዋጽዖ ለማድረግ ከተቋቋሙ ማህበራት የአማራ ባለሙያዎች ማህበር (አምባ) አንዱ ነው:: ይህ ስብስብ የአማራውን ሕዝብ ትግል ከፍ ወዳለ ደረጃ እንዲሸጋገር የተበታተነው የድርጅት ሃይል ተሰባስቦ ለወገን ድምጽ የመሆን ቁመና ላይ እንዲደርስ ለማስቻል የበኩሉን አስተዋጽዖ ለማድረግ በመነሳቱ ሊመሰገን ይገባል::

አምባ እና ሌሎች በግል እንደ ተከበሩ ሻለቃ ዳዊት ወልደጎርጊስ የተከበሩ ፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻውና እንዲሁም የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ በጋራ አንድና ጠንካራ የአማራ ሕዝብ ድምጽ የሚሆን ተቋም ለማቋቋም ከአንድ አመት በላይ ብዙ ግዜ ጉልበትና ወጪን የጠየቀ ብዙ ጥረት ተደርጏል:: ውጤቱ አሳዛኝና ፍጻሜው አሳፉሪ በመሆኑ ስለዚህ ጥረት ክሽፈት ምንም ሳይባል ቆይቷል::

ዛሬ ላይ ማንሳት ያስፈለገው የአማራ ባለሙያዎች ማህበር(አምባ) ”የአማራን ሕዝብ ትግል ያለፈውን መፈተሽ ወቅታዊ ሁኔታውንም መገምገምና የወደፊቱን መተለም” በሚል መሪ እርዕስ ሕዝባዊ ውይይት ጠርቷል:: የውይይቱ አጀንዳ ወቅታዊና አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን በእውነትና በምሁራዊ ስነምግባር የታገዘ የራስንም ድክመትና ስህተት መመልከቻ እንዲሆን ለመጠቆም ነው::

የአማራ ባለሙያዎች ማህበር (አምባ) ከብዙሃኑ የተሻለ የአካዳሚና የእውቀት ደረጃ ላይ የደረሱ አባላትን ያቀፈ ስብስብ እንደመሆኑ የሚጠበቅበትም ተሳትፎ የዚያኑ ያህል ከፍ ያለ ይሆናል:: ከአምባ ጋር በጋራ ለአንድ አመት ያህል የአማራ ድርጅቶችን አንድ አድርጎ ጠንካራ አደረጃጀት ለመፍጠር በተደረገው ጥረት ውስጥ አምባ እንደ ምሁራን ተቋምነቱ ሃሳብ የማመንጨት አቅጣጫን የማሳየትና መርሕን የተከተለ ተጽዕኖ የማሳደር አቅም ብቃትና ዝግጁነት አጥቶ ያሳየው ልፍስፍስና የተከታይነት አቋም በምሁሮቻችን ላይ እምነት እንድናጣና ተስፋ እንድንቆርጥ ማድረጉን መሸሸግ አልፈልግም::

ተጨማሪ ያንብቡ:  በሬየን አልሸጥም - አጭር ወግ - በሄኖክ የሺጥላ*

የአምባ ተወካዮች ለሶሻል ሚዲያ ጀብራሬዎችና የአማራን ሕዝብ መከራ የኑሮ መደጎሚያ ያደረገ የፖለቲካ ነጋዴ የሶስት ድርጅት ማህተም በኪሱ ይዞ ያደረሰውን ነውርና ለብዙን ሃሳብ ተገዢ ያለመሆን አጉራዘለልነት ላይ ቆራጥና መርህን የተከተለ አቋም አምባ ከመያዝ ይልቅ በልመናና በምልጃ ያሳዩት መልፈስፈስ ብዙ የተደከመበት አላማ ከዳር እንዳይደርስ ሃላፊነታቸውን መወጣት አልቻሉም:: ከዛም አልፎ አንዳንድ የአምባ አባላት በወንዝ ልጅነትና በጽዋ ማህበርተኝነት ተይዘው ያደረጉት አይነት ባልቴታዊ ባህል መዘርዘር ባልፈልግም ምሁራዊም መንፈሳዊም ያልሆነ ነውረኛ ተግባር እንዳይደገም ሊያደርጉ ይገባል::

ትላንት ለአማራው ድምጽ ሊሆን የሚችል ተቋም እንገንባ ብለን ከልባችን ስንጥር ቃላት ይሰነጥቁ አጀንዳ ይበውዙና የእነከሌ አይን ስላላማረን እነሱ ክተገኙ አንመጣም የሚሉ የድርጅት መሪ ተብዬ ሕዝባቸውን እረስተው እራሳቸውን ያነገሱ ነውረኞች እንደቀለዱ እንዲኖሩ እንደነገዱ እንዲቀጥሉ የማያስችል ሁኔታ ድንገት በመፈጠሩ ከአደባባዩ እንደጉም በነው ሲጠፉ አይተናል::

በሙያቸው በእውቀትና ተሞክሯቸው ትግሉን እንዲያስተባብሩ ምክርና ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ በአምባ ተጋብዘው የመጡት ሻለቃ ዳዊትና ፕሮፌሰር ጌታቸው በክብር እንደተጠሩ በክብር መሸኝት ሲገባቸው በስብዕናቸው ላይ የተካሄደው ስም የማጠልሸት ነውር አምባ አለማውገዙ ተጠያቂ ያደርገዋል::

ሻለቃ ዳዊት ወልደጎርጊስ ከፍተኛ ወጪ ከሚጠይቀው ከሚኖሩበት ደቡብ አፍሪካ ከ20 ግዜ በላይ እየተመላለሱ ፕሮፌሰር ጌታቸው ከችካጎ ድረስ እየመጡ የአማራን ሕዝብ ትግል ለማጠናከር ላደረጉት ወደር የለሽ ትጋት ግዜ ታሪክና ትውልድ በክብር ያኖረዋል:: ነገር ግን በገዛ ወገናቸው የተካሄደው የመንጋ ስድብ የአሉባልታ ዘመቻ የስም ማጥፊያ የሃሰት የቪዲዮ ዶክመንተሪ የነሻለቃ ዳዊትን ክብር ቅጣት ሊቀንስ ባይችልም:: የአማራው ትግል ምራቅ የዋጡ አስተዋይ ስዎች ከመድረኩ ገፍቶ የወጠጤ መራገጫ የእርስ በእርስ መናጫ እንዲሆን ገና ከማለዳው ነውርንና ሃሰትን መታገልና ለመርህ መቆም የነበረበት : የአማራ ባለሙያዎች ማህበር አይቶ እንዳላየ በማለፉ ዛሬ ላይ ለደረስንበት የትግል መቀዛቀዝ ግራ መጋባትና መበታተን ጉልህ ድርሻ ይይዛል:: አምባ ጠርቶ ለነውረኞች ጭዳ ያደረጋቸውን አንጋፉ ምሁራን አስቀድሞ በአደባባይ ይቅርታ መጠየቅ ይኖርበታል:: በዚህም እራሱን ከፍ ለትግሉም ተሃድሶን ይጠቅማል::

ተጨማሪ ያንብቡ:  ግልፅ ደብዳቤ ለክቡር ጠቅላይ ሚኔስቴር ዶ/ር አቢይ አህመድ

ይህን ሁሉ የምለው እንድም ከትላንት ስህተታችን ተምረን እንድንቆም::ሁለትም የነውረኞችን ስድብና አሉባልታ ፈርቶ ለራቀው ምሁር እድል እንዲያገኝ:: ሶስትም የሕዝባችን ነባር ባህልና ትውፊት እንዲጠበቅ የሃሳብ የበላይነትና የውይይት ባህል እንዲዳብር አራትም አማራው ከደረሰበት የህልውና አደጋ በጥንካሬና በአንድነት ብእጭር ግዜ ሰብሮ እንዲወጣ ያግዛል ከሚል ነው::

ግዜ ሚዛኑ ምርትና ገለባውን ሃቀኛና መልቲውን ታጋዩንና ነጋዴውን ለክቶ ይህው ዛሬ ላይ አድርሶናል:: ግዜ ከማንም በላይ ምስክር ስለመሆኑ የአምባ አባላት ይረዳሉ ብዬ እገምታልሁ:: ያ ለያዥ ለገራዥ ያስቸግር የነበረ ታጋይ ነኝ ባይ ዛሬ ከአደባባይ ላለመኖሩ ከኔ የተሻለ ትረዳላችሁ ብዬ አስባለሁ:: ይህን ትችት በደፈናው ከማቅረብ ይልቅ ባለፍንበት ሂደት የነበሩ የሰነድ ማስረጃዎች ይዞ መቅረብ ይቻል ነበር:: ነገር ግን ተቋሙ ላይ ላቀርብ የፈለጉት ትችት እራሱን መመልከቻ እንዲሆን ከማሰብ አንጻር ነው::ሕልውናውም ከቀጠለ ይህን መሰል ጉድለት እንዳለበት ተረድቶ ለወደፊቱ እንዲስተካከል ነው::

ተቋም መመስረት ለስም ከሆነ ትርጉም የለውም:: ማንኛውም ስብስብ ከመሰረቱ ሊመራበት የሚገባ መርሕና ዋጋ ሊከፍልለት የሚችለው እውነት ሊኖረው ይገባል:: እውነት ስትጨነግፍ ሃሰት ስትነግስ ጎጠኝነት ሲሰርጽ ስርዐት አልበኝነት ሲስፉፉ አይቶ እንዳላየ ማለፍ እንኳን ከምሁራን ከማንም አይጠበቅም:: አለያ ያገራችን ሰው ከእጅ አይሻል ዶማ እንዳለው ምሁር ተብሎ በባልቴት ተግባር መጠመድ ነውርም ሃጢያትም ይሆናል::

 

እግዚአብሄር አስተዋይነቱን ያድለን!!!

1 Comment

  1. ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነው:: ወያኔያዊ የጥላቻ የጭቃ ጅራፍህ የሚጨምረው አይኖርም ከትዝብት በስተቀር አንተ እንደ አማራ ምሁር ከሆንክ ለዚያውም አማራ ለዚያውም ምሁር ምን የጨመርከው ነገር ይኖራል? ሰድቦ ለተሳዳቢ የሚለቀልቁ ወናፎች ያሳዝኑኛል:: እኔ በበኩሌ አማራ በሙሉ በአንድ አዳራሽ ተሰብስቦ ሲመክር እጅግ ነው ያስደሰተኝ:: ምነው በዶክተር አስራት ጊዜ የዛሬ 20 አመት ላይ ታች ስንባክን ይህ ሁሉ የተለያየ ወገን ቢሰባሰብ የወያኔ እድሜ ያጥር ነበር::

Comments are closed.

Share