የግል ወይም የቡድን   የፖለቲካ ትርፍን እያሰሉ አዋጅ ማወጅ የእውነተኛ ለውጥ ባህሪ አይደለም! – ጠገናው ጎሹ

April 21, 2019
ጠገናው ጎሹ

እንደ መግቢያ

 አስፈላጊነታቸው  ለጊዚያዊ  የፖለቲካ ፍጆታነት ሳየሆን  አገርን እውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የተረጋገጠባት  ለማድረግ የሚደረገውን የትግል ሂደት ለማሳካት ሲባል የግድ የሚሉ ሆነው እስከተገኙ ድረስ የአስቸኳይ (የአስገዳጅ) ጊዜን ጨምሮ ልዩ ልዩ አዋጆችን የማወጅና  ሥራ ላይ የመዋል  አስፈላጊነት  አጠያያቂ  አይደለም ።

ጥያቄ የሚያስነሳው አዋጆች የሚነሱባቸው መነሻዎች፣ የሚፀደቁባቸው ሁኔታዎችና የሚቀመጡላቸው ግቦች በአንድ ወይም በሌላ መንገድ የግል ወይም የቡድን የፖለቲካ ሸፍጥና ሴራ (hypocrisy and conspiracy) ማስፈፀሚያ ሰለባ ሲሆኑ ነው ።  ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ዜጎችን  በየጎሳቸው/በየዘውጋቸው የማንነት ፖለቲካ ከረጢት ውስጥ አስገብተው  ጨርሶ ገደብ በሌለው ኢሰብአዊ ሁኔታ  በመግዛት  በተካኑ የህወሃት/ኢህአዴግ ፖለቲከኞችና ካድሬዎች በስፋትና በጥልቀት የተሠራበት የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ በማያሻማ አኳኋን የሚነግረን ይህንኑ መረር ሃቅ ነው ። እንዲህ አይነቱን እጅግ የከፋና የከረፋ የአገዛዝ ሥርዓታቸውን ለማስቀጠል ያስችለናል በሚል ያላወጁት አዋጅና ያልደነገጉት ህግና መመሪያ አልነበረም ።

ይህ አይነቱ እኩይ  የፖለቲካ ጨዋታ  የተጀመረው  ህወሃቶች /ኢህአዴጎች በጎሳና በቋንቋ ከልለው  እርስ በርስ እያናቆሩ  ለመግዛት የሚያስላቸውን ህገ-መንግሥት  ጨርሶ ሥራ ላይ በማያውሏቸው   (ባላዋሏቸው) ዓለም አቀፋዊ ድንጋጌዎች አጅበው ከተነሱበት ዓላማ አንፃር  እየተረጎሙና እየመነዘሩ መጫወት ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ነው ።

የአሁኖቹ የለውጥ አራማጅ የምንላቸው ፖለቲከኞችም  ከዚያው ተዘፍቀው ከኖሩበት ኢህአዴጋዊ  ክፉ ልክፍት ጨርሰው ባለመላቀቃቸው  አዋጅን ለጊዜያዊ የፖለቲካ ትኩሳት ማስተንፈሻነት ከመጠቀም ክፉ ልማድ የተላቀቁ አይመስልም ።

የሰላምና እርቅ ኮሚሽንን  እና የድንበርና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽንን  ያቋቋሙት  አዋጆች   አላማቸውና  ተግባራቸው  ተብለው በወረቀት ላይ የተቀመጡላቸው ቁም ነገሮች   ቀደሞውንም የህዝብ ጥያቄዎች  ስለሆኑ የሚያወዛግቡ አይደሉም።  ትልቁ ቁም ነገር ያለው አዋጅን ፅፎና አፅድቆ “ያልሰማህ ስማ!” ብሎ ዜና ማስነገሩ ላይ  አይደለም ።  ትልቁ ጉዳይ ያለው ለምን? በማን/በነማን? ለማን/ለነማን? በምንና እንዴት ? የሚሉ ጥያቄዎችን ብቃትን፣ ግልፅነትን ፣ ቅንነትንና አርቆ አስተዋይነትን (ለትውልድ ተጨናቂነትን) በተላበሰ  የሃላፊነት ስሜት ከመመለሱ ላይ ነው ።

እንደ መልካም ዜጋ  በግልፅ መነጋገር ካለብን  አሁንም የምንገኘው ህወሃት/ኢህአዴግን በኦዴፓ/ኢህአዴግ የመተካት  ትዕይተ ፖለቲካ  ውስጥ በመሆኑ አዋጆችንም ሆነ ሌሎች የህግና የደንብ ማእቀፎችን ከፖለቲካ ፍጆታ ሰለባነት አውጥተን የታለመላቸውን ግብ እንዲያስገኙ ለማድረግ አልተቻለንም ። በቀላሉ የሚቻለንም አይመስልም ።

በጎሳ/በዘር አጥንት ማንነት በእጅጉ የተበከለው የፖለቲካ አስተሳሰባችንና አካሄዳችን ዘመናት ያስቆጠረውን  የፖለቲካ  ካንሰር ከማስወገድ ይልቅ እንዲያውም ያልተበከለውን አካል ሁሉ በከፍተኛ ፍጥነትና ስፋት እየበከለ የመቀጠሉ ጉዳይ አስጨንቆን ሳይመሽ የፈውሱን መፍትሄ በጋራ እውን ካላደረግን በስተቀር የትምና ወደ የትም አንደርስም ።   ወደ ውስጣችን ያላስገባነው የዲስኩርና የአዋጅ ጋጋት አንዳችም ፋይዳ አይፈይድም ።

አዎ! በእውነት ከተነጋገርን በየጎሳው/በየመንደሩ እንደአሸን ተፈልፍሎ  አገርን የመተራመሻ (የለየለት የፖለቲካ እብደት መጫወቻ) ሜዳ ያደረገው ፖለቲከኛ ነኝ ባይ  “የሥነ ምግባር ድርሰት መፈራረሜን ታሪካዊ አርበኝነት ብላችሁ ተቀበሉኝ” በሚልባት ምስኪን አገር ውስጥ አዋጆችና ደንቦች የፖለቲካ ተውኔት ሰለባ ቢሆኑ አይገርምም።

ፖለቲከኞቻችን ወይም መሪዎቻችን በሸፍጥ የተለወሰና ስሜት ኮርኳሪ ዲስኩራቸውን ቀንሰው መሠረታዊውን የሥርዓት ለውጥ ጥያቄ በአግባቡ ማስተናገድ ሲሳናቸው የአዋጅና የመመሪያ ድርሰት እያዘጋጁ የድንቁርና እና የግፍ አገዛዝ ያንገፈገፈውን ህዝብ “ለአንተ ስንል የማናውጀው አዋጅ ከቶ አይኖርም”  በሚል የፕሮፓጋንዳ ናዳ ናላውን (የማሰቢያና የማገናዘቢያ ህሊናውን) ቢያዞሩት በእጅጉ ያሳዝን እንደሆነ እንጅ ጨርሶ አይገርምም።

ከሰብአዊ ፍጡር በላይ በሚመስል አኳኋን የዘመናችን ድንቅ ሐዋርያት” ብሎ የተቀበላቸው የዋሁ የአገሬ ህዝብም  አዋጅን ” እንደ ድል ብሥራት በመቁጠር የፖለቲከኞች የሸፍጥ ፖለቲካ ሰለባ ቢሆን ያሳዝን እንደሆን እንጅ   የሚያስገርም አይሆንም። የፖለቲከንና የፖለቲከኞችን አስቸጋሪ ባህሪና አካሄድ  ለማወቅ ወይም ለመረዳት የሚያስችለውን የእውቀት ፣ የመረጃ  አቅምና አቅርቦት እየተፈራረቁ በገዙት ገዥዎች ተነጥቆ የኖረውና አሁንም እየኖረ ያለው የዋህ የአገሬ ህዝብ ፖለቲከኞች የሚያውጇቸው አዋጆችን እንደ የእውነተኛ የለውጥ መድህን አድርጎና ሁሉንም ነገር ለፖለቲከኞች አደራ ሰጥቶ አዎንታዊ ውጤት ቢጠብቅ ከቶ የሚገርም አይሆንም ። አደጋው ግን አሳሳቢ ነው ።

ለነገሩ የኢትዮጵያ ህዝብ እራሱ ሳይማርና ጨርሶ ሳይደላው በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ (በወላጅነት ወይም በግብር ከፋይነት) ያስተማረውና እያስተማረው ያለው ይህ ትውልድ ከዘመን (ከጊዜ) ጋር መዘመን እንኳ ቢያቅተው መሠረታዊ በሆኑ የአንድ አገር ልጅነትና የአብሮነት እሴቶች ዙሪያ መደማመጥና መነጋገር ባልቻለበት የፖለቲካና ማህበራዊ ሁኔታ ውስጥ ዴሞክራሲን መፈለግ በራሱ  የለየለት ቂልነት (ድንቁርና) ነው ።  ከዚህ የባሰ ልብ የሚሰብር ቁልቁል የመውረድ አዙሪት ግን የለም ። ደጋግሞ የመክሸፍ አሳፋሪ  የፖለቲካ ታሪክ መደገም ከሌለበት በገዥው ቡድንም (በመንግሥትም) ውስጥ ሆነ ከሱ ውጭ የሚገኙ  ህሊና ቢስ የጎሳ/የመንደር ፖለቲካ ማንነት ነጋዴዎችን  በግልፅና በቀጥታ  መጋፈጥ የግድ ነው።

አዋጆቹ

  1. የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ለማሸጋገር ግድ ከሚሉና በህዝብ ይጠየቁ ከነበሩ ጥያቄዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል ፦

ሀ) ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በጎሳ/በመንደር ማንነት ላይ የተመሠረተው ሥርዓተ ኢህአዴግ ያስከተለውን እጅግ እኩይ የመለያየት ፣ የጥላቻና እስከ መገዳደል ያደረሰ የፖለቲካ እብደትን አስወግዶ ወደ ፊት ለመራመድ የሚያስችልን የእርቅና ሰላም መንገድ (mechanism) መፍጠር ለነገ የሚባል ጉዳይ እንዳልሆነ የህዝብ ጥያቄ ከሆነ ረጅም ጊዜ አስቆጥሯል ። ለዚህ እውን መሆንም ሁሉም በአግባቡ በሚሳተፍበት የጋራ ምክክር፣ መግባባትና የውሳኔ ሃሳብ ላይ ተመሥርቶ የማስፈፀሚያ እቅድና ስልት  የሚነድፍ አገር አቀፍ የእርቅና የሰላም ጉባኤ ማካሄድ አስፈላጊ እንደሆነ ተደጋግሞ የተሰማ የህዝብ ጠንካራ አስተያየት ነው ።

ለ) ህወሃት/ኢህአዴግ  በጎሳ ላይ የመሠረተውን እኩይ የፖለቲካ ፕሮግራም እውን ለማድረግ በተንቀሳቀሰበት ጊዜ ፣ሁኔታና  ቦታ ሁሉ በህዝብ ላይ  የፈፀመው የፖለቲካና የሰብአዊ መብት ድፍጠጣን ብቻ አልነበረም ።  ነፃ አውጭው ነኝ የሚለውን ክልል ለማስፋፋት ከአጎራባች ክልሎች በተለይም ከአማራ ክልል ሰፋፊ መሬቶች እየነጠቀ የአማርኛ ተናጋሪ ዜጎችን ማንነት ጨርሶ ለማጥፋት የፈፀመው ወንጀል ፈፅሞ በቀላሉ የሚታይ ሊሆን አይችልም ። ይህና በየአካባቢው የሚነሱ የአስተዳደራዊ ወሰን ጥያቄዎች ተገቢውን ፖለቲካዊና ህጋዊ መፍትሄ  እንዲያገኙ የሚለውም የረጅም ጊዜ የህዝብ ጥያቄ ነው ።

የለውጥ አራማጅ የምንላቸው ፖለቲከኞች (መሪዎች) እነዚህን ጥያቄዎች አደናቁረውና አድበስብሰው ለማለፍ የቻሉትን ያህል ሞክረዋል  ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየአካባቢው እየተጓዙ በየአደባባዩና በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ  ስሜትን በሚገዙ የይቅርታና የሰላም አስፈላጊነት ዲስኩሮች (ሰበካዎች) እንዲህ አይነት ጥያቄዎችን  አድበስብሶ ለማለፍ በዋና ተዋናይነት ተጫውተዋል ። ጥርሳቸውን ነቅሎ ያሳደጋቸው ህወሃት የሰሜን ጎንደርንና የሰሜን ውሎን መሬቶች የነጠቀበትን ግልፅና ግልፅ ሴራ   ሀ) እኔ የማውቀው ነገር የለምና በመመካከርና በህገ መንግሥት አግባብ  የሚፈታ ነው የሚሆነው በሚል ደምሳሳ ፖለቲካዊ ምላሽ ያልፉበት ሁኔታ  እንደነበር እውነት ነው ፤ ለ) ለዚህ አይነት እኩይ አጀንዳ ማስፈፀሚያ እንዲሆን ተደርጎ የተሠራውን ህገ መንግሥት መፍትሄ ሰጭ አድርጎ በማቅረብ የህዝብን ትኩረት ቢቻል ለማስቀየር ካልሆነም ለማርገብ ብዙ ተደክሟል ፤ ሐ)   በተራ አባልነት ብቻ ሳይሆን ጉልህነት ባላቸው የተለያዩ የሙያና የሃላፊነት ቦታዎች ያገለገሉበት ገዥ ግንባር (ህወሃት/ኢህአዴግ) ለዘመናት የተከለውና ያስፋፋው የጥላቻና የመናቆር ፖለቲካዊና ማህበራዊ  ደዌ የእርቅና የሰላም ጉባኤ በማካሄድ እውነተኛ ፈውስ እንዲፈለግለት ለቀረበ ጥያቄ  በወቅቱ ምላሽ  ለመስጠት ይቸገሩ እንደነበርም እውነት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመረጡት አካሄድ   እውነተኛ  ዜጋ ሁሉ አሳምሮ  የሚያውቀውን የእርቅና የሰላም  አስፈላጊነት የንግግሮቻቸው (የዲስኩሮቻቸው) ማጠንጠኛና ማሳረጊያ እያደረጉ መስበክን ነበር ።  

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ( አብን ) የጠራው ሰልፍ በመንግስት መከልከሉ የብልፅግናን ከልክ ያለፈ አንምባገነናዊነት ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነው

ከቤተ መንግሥታቸው አካባቢ ጀምሮ በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎቸ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎች ህይወት በጎሳ/በዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ልክፍት ህሊናቸውን በሳቱ ካድሬዎች አብሮ የኖረ የአንድ አገር ሰው ይፈፅመዋል ብሎ ለማመን በሚያስቸግር ሁኔታ በአንድ ሌሊት ወይም ቀን ምስቅልቅሉ ሲወጣ ዝምታን ከመምረጥ አልፎ “ከእኔ ሥልጣንና ተግባር ውጭ ነው “ የሚል አይነት መልስ እየሰጡ ስለ እርቅና ሰላም አብዝቶ መስበክ (መደስኮር) ሌላው ቀርቶ የፅንሰ ሃሳቡን እውነተኛ ትርጉም (እሴትነት) ያኮሰምናል እንጅ አያገዝፍም ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ አይነት አድበስብሶ (አደናቁሮ) የማለፍ ፖለቲካዊ ዘዴ ከምር እየገፋ የመጣውን የህዝብ ጥያቄ ማስቆም እንደማይቻል በመገንዘብ ኮሚሽኖቹን የሚያቋቋም አዋጅ እንዲወጣ ማስድረጋቸው ተገቢ ነው ።

አዋጆቹ የያዟቸው ጉዳዮች ቢያንስ አስተያየት በመስጠት ደረጃ  የህዝብን ሰፊና ንቁ ተሳትፎ የሚጠይቁ ከመሆናቸው አንፃር ከመጀመሪያውም በዚህ ረገድ ድክመት የነበረ ቢሆንም በተለይ ግን በኮሚሽኖቹ አባላት የምልመላና የአመዳደብ ሂደት የታየው ዜሮ ህዝባዊ ተሳትፎ ከአስቀያሚው የፖለቲካ ጨዋታ ለመላቀቅ ገና ረጅምና አስቸጋሪ ፈተና መኖሩን ነው የሚያሳየው ።

በህዝብ አስተያየትና ንቁ ተሳትፎ  የሚታጀብ  አገራዊ የምክክር ፣ የእርቅና የሰላም ጉባኤ  አስተዋፅኦ መሠረት አዋጆቹን ከማውጣትና የኮሚሽኖችን አባላትንም መልምሎ ከመሰየም ይልቅ ገና ከቤተመንግሥት የፖለቲካ ተፅዕኖ ቅዠት ባልተላቀቀው የፍትህ አካል በተረቀቀ አዋጅና በቤተመንግሥት (በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት) ብቸኛ ወሳኝነት  እዚያም እዚህም (hochpoch ) በሆነ ስብጥር (ኮታ)  መልምሎና መድቦ “ታሪካዊ የለውጥ እርምጃ ተብሎ ይመዝገብልኝ” ማለት እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሰማይን ያህል እየራቀበት በተቸገረ ህዝብ ላይ  መቀለድ ነው የሚሆነው ።

ህዝብ  ከመከራውና ከውርደቱ መጠንና ጥልቀት የተነሳና ከዚህ አዙሪት የሚወጣበትን መንገድ እያመቻቼና እየመራ የሚሳየው አማራጭ  የፖለቲካ ሃይል (ንቅናቄ//ህብረት/ድርጅት/ፓርቲ) ማግኘት ወይም መፍጠር ባለማቻሉ ምክንያት ገና ምንም አይነት ጉልህ ወይም ወሳኝ የለውጥ ሥራ ሳያሳዩት በስሜት ኮርኳሪ ዴስኩሮቻቸው ብቻ “ተመስገንና አሜን” ብሎ ስለተቀበላቸው የፈጣሪውን ያህል ሁሉን ነገር ለእነሱ የተወላቸው የሚመስላቸው ፖለቲከኞች ቆም እያሉ እራሳቸውን መጠየቅ ግድ ይላቸዋል ።

አዎ! ስለ እኛው ስለራሳችን በእውነት ስለእውነት ከተነጋገርን አንቅቶና አደራጅቶ  ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን በማድረግ ከሚፈራረቁበት የመከራና የውርደት የፖለቲካ ሥርዓቶች የሚገላግለው ዴሞክራሲያዊ አርበኛ የፖለቲካ ድርጅት (አካል)  የሌለው ህዝብ  ሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞች በቀደዱለት ቦይ እየፈሰሰ ቢቸገር በእጅጉ ያሳዝን እንደሆን እንጅ ከቶ አይገርምም ። በተለይ በሩብ መቶ ክፍለ ዘመን እራስን በራስ (ወገንን በወገን) ላይ እያነሳሱና እያጋጩ መግዛት በሚያስችለው የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ለተካኑ ፖለቲከኞች በዚያው ለመቀጠል ማጣፊያው ባጠራቸው ቁጥር መከረኛውን ህዝብ በድክመቱ እየገቡ ወደ ሚፈልጉት ቦይ እንዲፈስ ለማድረግ የተለየና አድካሚ ጥበብ አይጠይቃቸውም  ።

በዚህ አኳኋን ነበር የህዝብን የተወጠረ ስሜት ለማርገብና   ከሞት አፋፍ የተመለሰውን ህወሃት/ኢህአዴግ በኦዴፓ/ኢህአዴግ ተክቶ በሥርዓት ለውጥ ሳይሆን በማሻሻያ (reform) የፖለቲካ ጨዋታ ለማስቀጠል ያስችሉ ዘንድ ሁለቱ መንታ አዋጆች ማለትም የእርቅና ሰላም ኮሚሽን እና የወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጆች የታወጁት እና አባላት የተመደቡላቸው ።

በሚከተሉት ነጥቦች አስተያየቴን ይበልጥ ግልፅና ቀጥተኛ ላድርግ፦

  • ለመሆኑ ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የመከራና የውርደት ምንጭ የሆነውን ሥርዓት እንዲያገለግል በበጎ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ታጅቦ ሥራ ላይ የዋለውና ይኸውና እስከአሁንም ለንፁሃን ዜጎች መከራና ውርደት ምክንያት የሆነው ህገ መንግሥት እየሠራ ባለበት መንግሥታዊና ድርጅታዊ መዋቅሮች ከሥልጣን ብልግና በሚገኝ ጥቅም በሰከረ የኢህአዴግ ካድሬ  ተጠርንፈው በሚገኙበት ሁኔታ እና በተግበሰበሰ የኮታ አይነት አመላመልና ምደባ በተቋቋሙ ኮሚሽኖች ሁለቱን እጅግ ትልልቅ ጉዳዮች እንዴት ውጤታማ በሆነ ሁኔታ መፍታት ይቻላል ? የመከራና የውርደትን  አውራ  ሰንሰለት ሳይሆን ከእሱው ጋር የተያያዙ ቁርጥራጭና የሰንሰለትነቱን ህልውና የማይወስኑ ሰንሰለቶችን የማስወገድ  የፖለቲካ ጨዋታ ከቶ የትም አያደርስም ።እየሆነና እየተደረገ ያለው ግን በተግበሰበሰና ከዚያም ከዚህም (hochpoch) በሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ ዘመን ጠገቡን የመከራና የውርደት ሥርዓተ ፖለቲካ የመለወጥ  ከንቱ ሙከራ ነው ።
  • እነዚህ አዋጅ የታወጀላቸው ሁለት ትልልቅ ጉዳዮች ህዝብ ለረጅም ጊዜና ያለመታከት ሲጮህላቸው የነበሩ እንደሆኑ በግልፅና በሰፊው ይታወቃል ። ታዲያ በሂደቱ በተለይም የኮሚሽኖችን አባላት ምንነት ፣ ማንነት፣ ታማኝነት ፣ ገለልተኝነት፣ የትምህርትና የሙያ ብቃት ፣ የሥራ ወይም የተግባር ወይም የእደሜ ተሞክሮ ፣ ከአድርባይነት ልክፍት ነፃ የመሆን ፣ እና በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ህዝብና በተለይ ደግሞ በሚሠሩበትም ሆነ በሚኖሩበት አካባቢ ያላቸው (የሚኖራቸው) አወንታዊ አንድምታ ጨርሶ ባልተጠየቀበትና ባልታወቀበት ሁኔታ መልምሎ “አትጨቅጭቁን  ይኸውላችሁ” ማለት የፖለቲካውን ሸፍጥ ከማረጋገጥ ያለፈ ፋይዳ የለውም ።
  • የአባላቱ ስብጥር የኢህአዴግን ድርጅታዊ አሠራር ተከትሎ ለኢህአዴግ የተሃድሶ የፖለቲካ ጨዋታ እንዲያግዝ በሚያስችል አኳኋን የተካሄደ የመሆኑ ጉዳይ

ለኮሚሽኖች ተልኮ መሳካት ከጠቀሚታው (asset) ይልቅ ጎጅነቱ (liability) ሊያመዝን እንደሚችል ለመገንዘብ የተለየ ችሎታና ምርምር አይጠይቅም ። የአባላቱ ስብጥር  ፖለቲከኞችን ፣ የቀድሞ ከፍተኛ የኢህአዴግ ባለሥልጣናትን ፣ ምሁራንን ፣ ጋዜጠኞችን ፣ የኬነ ጥበብ ባለሙያዎችን፣ የሃይማኖት ተቋማት ሰዎችን ፣ ስፖርተኞችን ፣ የህግ ባለሙያዎችን ፣ ታዋቂ ግለሰቦችን ፣ ሽማግሌዎችን (አዛውንቶችን) ፧ አክቲቪስቶችን ፣ የቀድሞ ፓርላማ አባላትን ፣ ዲፕሎማትን ፣ የጤና ባለሙያዎችን፣ በግብረ ሰናይ ሥራ የተሠማሩ ግለሰቦችትን ፣ የወጣት ተወካይን ፣ ደራሲያንን ፣ አንትሮፖሎጅስትትን እና የአካል ጉዳተኛን እንዲያካትት መደረጉን  በጥሞና ለታዘበ (ለሚታዘብ)  የአገሬ  ሰው ነገርየው አውደ ጥናት  (symposium )  እንጅ እጅግ ውስብስብና የሆኑና የሙያዊና የአጠቃላይ ሰብዕና ልዕልናን የሚጠይቁ አገራዊ ጉዳዮችን አጥንተውና መርምረው  ለዘላቂ ፖለቲካዊና ማህበራዊ የጋራ መፍትሄ ሃሳብ ለማቅረብ የተቋቋሙ አካላት (ኮሚሽኖች)  አካል ጨርሶ አይመስሉም።  በዚህ አኳኋን  ሰዎች የተመደቡላቸው አዋጆች ከተፃፉበት ወረቀት ወደ መሬት ወርደው ወይም የፖለቲካ ፍጆታ ከመሆን አልፈው ለእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ለውጥና ለዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እውን መሆን ጉልህ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል ብሎ መከራከር ጨርሶ ከአፍንጫ ሥር የፖለቲካ አስተሳሰብ አያልፍም ።

 

ምናልባትም “የተቀዋሚ (አሁን ተፎካካሪ በሚል የፉገራ ስም ይጠሯቸዋል) ድርጅቶች አባላትም እኮ አሉበት” የሚሉና ከቅንነት የሚነሱ አስተያየቶች ሊሰነዘሩ ይችላሉ ። በእውነት ከተነጋገር ግን ለዜግነት (ለአገራዊ) የፖለቲካ ሥርዓት እንታገላለን የሚሉትና አንፃራዊ ተስፋ ተጥሎባቸው የነበሩ ፖለቲከኞችም ነፃነታቸውን (independenc / self reliance) ዝቅ አድርገው የለውጥ አራማጅ የምናላቸውን ፖለቲከኞች የቤት ሥራ ወደ መሥራት እና “ያለ እናንተ አሸጋጋሪ የለንም” እስከማለት ወርደዋልና ብዙም የሚያስኬድ ክርክር አይደለም ። የመሠረታዊ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን መሆን ለሚናፍቅ ቅን ዜጋ ግን በእጅጉ ልብ ይሰብራል ።

 

  • በየጎሳው/በየመንደሩ ተቧድነው “የእኔ ሉዓላዊ ክልል ወይም መንደር ጨርሶ አትነካም” ከሚል የፖለቲካ እብደት ጨዋታ ለመውጣት የተሳናቸው ፖለቲከኞች የተካተቱባቸው ኮሚሽኖች እውነትን በግልፅና በቀጥታ ተጋፍጠው እና ከልብ የመነጨ ይቅር መባባልን እውን አድርገው ገንቢነትና ዘላቂነት ወደ አለው ዴሞክራሲያዊ የሥልጣን አያያዝና ፍትሃዊ  የሃብት ተጠቃሚነት የሚያሸጋግር የመፍትሄ ሃሳብ  ያስገኛሉ ብሎ መጠበቅ ከባዶ ተስፈኝነት አያልፍም።  በሌላ አገላለፅ በእውነት ላይ ብቻ የተመሠረተ አስተሳሰብና አካሄድ የግድ ለሚለው አገራዊ የእርቅና የሰላም ጉዳይ (ጥያቄ) የጎሳ/የመንደር ማንነት የፖለቲካ ጨዋታን የአስተሳሰባቸውና የአካሄዳቸው መሠረት ያደረጉ ፖለቲከኞች በታደሙባቸው ኮሚሽኖች እውነተኛ መፍትሄ አስገኛለሁ ማለት ወይ የፖለቲካ ልፍስፍስነት ወይም ሸፍጥ ካልሆነ ሌላ ሊሆን አይችልም።
ተጨማሪ ያንብቡ:  የኦሮሞ ብልፅግናና ትህንግ የአማራ አፅመ ዕርስቶችን እና ፀጋዎቹን የመውረር አባዜ ለምንና እውነታው (ተዘራ አሰጉ)

 

  • ሲሆን በተጠያቂነት ቢያንስ ግን በሥርዓቱ ውስጥ ተዘፍቀው ዓመታትን እንደማስቆጠራቸው የሚያውቁትን መሪር እውነት ከምርና በዝርዝር ይናገሩ (ይመሰክሩ) ዘንድ መጠየቅ ያለባቸው የቀድሞው ፕረዝደንቶች ልክ እንደገለልተኛና ንፁህ ዜጋ አባል የሆኑባቸው ኮሚሽኖች የሚሳዩን ጤናማ ካልሆነ የፖለቲካ ጨዋታ ለመውጣት ፈተናው ምን ያህል ከባድና ውስብስብስብ እንደሆነ ነው ።

 

  • በተለይም ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስተርና የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ የነበሩት አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ አባል የሆኑበት ኮሚሽን  ምን ያህል የሸር ፖለቲካ ጨዋታ ሰለባ እንደሆን ለመረዳት ብዙ ማሰብን አይጠይቅም ። ህዝባዊ  የለውጥ ፍለጋ እንቅስቃሴው አይበገሬ እየሆነ በመጣበት እጅግ ወሳኝ ወቅት ቀጭን ትእዛዝ በመስጠት ንፁሃንን ማስደበደቡ ፣ ወደ ማጎሪያ ቤት ማስወረወሩና ማስገደሉ ሳያንሳቸው ትእዛዛቸውን ተቀብለው የፈፀሙትን ሃይሎች ለአገር ዳር ድንበር ሉአላዊነት ታላቅ ገድል የፈፀሙ ይመስል ከፍተኛ ምሥጋና እና ሙገሳ የመለገሳቸው ጉዳይ  ገና ቀለሙ ያልደረቀ የትናንት እጅግ አሳዛኝ ዜና ነው።

ታዲያ የእንዲህ አይነት ሰዎች የእርቅና ሰላም ከሚሽን አባል ሆኖ መመልመልና መመደብ አዋጀች የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ ሰለባ  መሆናቸውን ካልነገረን ሌላ ማን ይነግረናል

 

“ስለጉዳዩ (ስለችግሩ) ብዙ ስለሚያወቁ ነው” የሚል መከራከሪያ ማቅረብ ለመሪሩ እውነታ ጨርሶ የማይመጥን ብቻ ሳይሆን ህይወታቸው በግፍ በተቀጠፈ ንፁሃን ዜጎች ላይ መሳለቅ ነው የሚሆነው ። የሚያውቁትንና የሠሩትን ሁሉ በተገቢው አቀራረብና ሥነ ሥርዓት እንዲያስረዱ በኮሚሽኑ  እንደማነኛውም ተጠያቂ ዜጋ ይጠየቃሉ እንጅ እንዴት የጠያቂውና የመርማሪው አባል ይሆናሉ ?  ምን አይነት የእውነትና የእርቅ አፈላላጊነት አካሄድ  ነው ለዚህ ትውልድ እየነገርነው ያለነው  ይህች አገር የተከበረች ዴሞክራሲያዊት አገር ሆና እኛም በነፃነትና በክብር እንኖር ዘንድ አያሌ ንፁሃን ዜጎች መስዋእትነት መክፈላቸውን በየአደባባዩ እየደሰኮርን እንዲህ አይነት ትልልቅ ጉዳዮችን በእንዲህ አይነት ፖለቲከኞች አማካኝነት “እውነተኛ መፍትሄ አስገኝላችኋለሁ” ማለት ግልፅ የሆነ የፖለቲካ ሸፍጥ ነው ።  

በተለይ በልዩ ልዩ ሙያ ተማርኩና ተመራመርኩ ወይም እየተማርኩና እየተመራመርኩ ነው የሚለው የአገሬ ሰው በዚህ ረገድ የደረሰበት ቀውስ በእጅጉ አሳፋሪና አስቀያሚ ነው ።  አዎ! ተማርኩና ተመራመርኩ ወይም እየተማርኩና እየተመራመርኩ ነው የሚለው የአገሬ ሰው ልክ ያልሆነውን ልክ አይደለም በማለት ልክ በሆነው  እንዲስተካከል በግልፅና በቀጥታ ከመናገር ይልቅ ከዚያም ከዚህም በሚቃርመው ቲዎሪ (ንድፈ ሃሳብ) የሸፍጠኛ ፖለቲከኞችን አተረጓጎም ቆንጆ ለማስመሰል  ሲደክም ማየትና መስማት በእጅጉ ያሳፍራል ።

እያልኩ ያለሁት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትርም ሆነ ሌሎች ባለሥልጣኖች   ይቆረጡና ይፈለጡ አይደለም ። ከተፈፀመ ስህተት ወይም ወንጀል ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግኑኝነት ያለው ሰው አግባብ ባለው የፖለቲካና የህግ አቀራረብ  ሊጠየቅ ይገባል ነው ።

  • ለመሆኑ ስንቶቹ የኮሚሽኖቹ አባላት ናቸው በየሙያቸው የየራሳቸውንና የየቤተሰቦቻቸውን ኑሮ ስኬታማ ለማድረግ የሚያደርጉት ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ እራሳቸውን ልክ በሌለው ራስ ወዳድነትና አድርባይነት ላለማስለከፍ በመታገል የዚህ ህዝብ መከራና ውርደት ያበቃ ዘንድ የሚታይና የሚጨበጥ አስተዋፅኦ ያደረጉ ? ስንቶችስ ናቸው ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን አገርን ምስቅልቅሉን ያወጣውንና ንፁሃን ዜጎችን የመከራና የውርደት ቀንበር ተሸካሚ አድርጎ የዘለቀውንና አሁንም መልሶ ወደ ዚያው ሊዘፍቀን የሚተናነቀንን የኢህዴግ የፖለቲካ ካንሰር እንደ አንድ መልካም ዜጋ በድፍረት በመተቸትና ገንቢ የመፍትሄ ሃሳብ በመሰንዘር የሚታወቁት ?  ስንቶቹስ ናቸው በህዝብ አስተያየት ማሰባሰቢያ መድረክ ወይም ሌላ የመገናኛ ዘዴ  ማንነታቸውና ምንነታቸው ለህዝብ ግልፅ የሆነው ? በተለይ ደግሞ ስንቶቹ  የኮሚሽኖቹ አባላት የሆኑ  ምሁራን ናቸው የጎሳ/የዘር አጥንት ማንነት ፖለቲካ ንፁሃን ዜጎችን ሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ሙሉ ከሰብአዊ ፍጡራን በታች እንዲውሉ ሲያደርጋቸው ቢያንስ ከራሳቸው ልጆች ፊት  በአርአያነትና በኩራት  ለመቆም ሲሉ የሚችሉትን የዜግነት ግዴታ ለመወጣት ጥረት ወይም ሙከራ ያደረጉት ?
  • ከየሃይማኖቶች የተውጣጡ ሰባት ሰዎች በእርቅና ሰላም ኮሚሽን   አባልነት ተመድበዋል ። እርቅና ሰላም የሃይማኖታዊ እምነት አስተምህሮ ማዕከል ከመሆኑ አንፃር ተገቢነቱ የሚያጠያይቅ አይደለም ። የሚያጠያይቀው ላለፈው ሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በህዝብ ላይ  የመከራና የውርደት ዶፍ ሲወርድ እንደ ሰማዕታት  ቀርቶ እንደማነኛውም የወገኑ መከራና ውርደት እንደሚያሳስበው የሃይማኖ ሰው በሚሰብኩበት አዳራሽ ወይም አደባባይ ላይ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ግፈኞችን “በህግና በሰብአዊ ፍጡር አምላክ!” ብለው ያላሰሙ የሃይማኖት መሪዎች አሁን ከልብ ተፀፅተው መከረኛውን ምእመን (ህዝብ) ሊክሱ ከምር ተነስተዋል ወይ ? የሚለው ነውበዚህ የነፃነትና የፍትህ ፍለጋ ሂደት እየታዘብን ያለነው እውነታ ግን ይህን አይነት የአርበኝነት ሰብዕና ትርጉም ባለው ሁኔታ አያሳየንም ። የሚሊየኖች ህይወት ከገዛ አገራቸው (ቀያቸው) የጎሳ/የዘር ፖለቲካ ማንነት ልክፍተኛ በሆኑ የፖለቲካ ነጋዴዎች  ብቻ ሳይሆን በመንግሥት ባለሥልጣኖች ጭምር  ምስቅልቅሉ ሲወጣ ከተለመደ አስልች መግለጫና “እግዚኦ! በሉ” ከማለት የዘለለ ፟ቁም ነገር አላየንም። እናም ከዚህ አይነቱ የራስ (የውስጥ/የመንፈስ) ድቀት ነፃ ለመውጣት ትርጉም ያለው ጥረት ሳያደርጉ እጅግ ትልልቅ ለሆኑ አገራዊ ጉዳዮች የመፍትሄ አካል ሆኖ መሰየም በራሱ ምን ፉይዳ አለው ? ብሎ እራስን መጠየቅ (መሞገት) የመልካም ዜግ ሃላፊነትና ግዴታ ነው ።
  • የተሰጣቸውን ድንቅ ተሰጥኦ በእውቀት አጎልብተው በእጅጉ በሚያኮራ አኳኋን ሰው ከዋለበት ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ የዋሉ እንደ ወ/ት  (የማእረግ አጠራር ከተሳሳትኩ ይቅርታ) የትነበርሽ ንጉሤ  የመሳሰሉ ሴቶችን ማየት በእጅጉ ያስደስታል  ወይም ያኮራል ።

ይህ ድንቅ የስኬታማነት ሰብእና ግን ለፖለቲከኞች በስሜት ከመነዳት የታቀበና ገንቢ የሆነ ሂሳዊ ድጋፍ ከመስጠት ይልቅ ወደ ፍፁምነት (ወደ ማምለክ) የተጠጋ ሙገሳ ለማዥጎድጎድ  አሳማኝ ምክንያት ( convincing execuse) ሊሆን አይችልም ። የፖለቲከኞች ባህሪና አካሄድ በታቀደ ፣ በተቀናጀ፣ አሳታፊ በሆነ ፣ የትውልድ ተሻጋሪነት ባለው አኳኋን ስለመመራቱ  ጥያቄ ሳያንሱ እዚያም እዚህም ብልጭ ድርግም የሚል የለውጥ ብልጭታ ላይ ተመሥርቶ “እኔ አምኛለሁና እናንተም እመኑ” የሚል አይነት ጥሪ ማስተጋባት በአጠቃላይ የገሃዱ ዓለም ፖለቲካ ነፀብራቅ አይደለም ፧ በተለይ ደግሞ  ለእንደ እኛ አይነቱ በቡድንና በጎሳ ፖለቲካ ማንነት ምስቅልቅሉ ለወጣ ማህበረሰብ ጨርሶ አይመጥንም ።

በመሠረቱ ሁለቱም ኮሚሽኖች የምር ወይም የእውነት ከሆኑ  ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሌሎች  ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የአስከፊው ሥርዓት አባላት ሆነው የቆዩት ባለሥልጣናት ቢያንስ እውነቱን ዘርዝረውና  ጠለቅ አድርገው እንዲያስረዱ ሊጠየቁ ይገባል ። “እነሱን መጠየቅ ለውጡን ማደናቀፍ ነው” የሚል መከራከሪያ ከልጆች ጨዋታ በታች  እጅግ  የወረደ  የፖለቲካ አስተሳሰብ ነው ።  ወ/ት የትነበርሽ የለውጡ ሂደት ከአወንታዊ ነገሮች ይልቅ አደገኛ በሆኑ የጎሳ/የዘር አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ሸፍጠኞችና ነጋዴዎች እየተናጠ ባለበትና የለውጥ አራማጅ የምንላቸው ፖለቲከኞችም በአንድ ወይም በሌላ መልክ የዚሁ ሰለባ እየሆኑ የመሆናቸው ጉዳይ የአደባባይ ሚስጥር እየሆነ በመጣበት ሁኔታ ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ  የኖቤል ተሸላሚነት አጥብቃ ስትጨነቅ (ስታልም) መስማት የአገራችን ፖለቲካ ውስብስብና በሸፍጥ የተሞላ ስለመሆኑ ያለን ግንዛቤ (አረዳድ) ገና ከእንጭጭነትና ከስሜታዊነት ( emotional and infantile political thinking) ብዙም ያልራቀ መሆኑን ነው የሚነግረን ።  እናም እንዲህ አይነት ወደ ፍፁምነት የተጠጋ ሙገሳና ምኞት የሚያቀርቡ እንደ ወ/ት  የትነበርሽ የመሳሰሉ  እህቶች  በኮሚሽኖች አባልነት (ምክትል ሰብሳቢነት)  መሰየማቸው የአዋጆቹን የወረቀት ነብርነት እንጅ  መሬት ላይ ወርደው  የለውጥ ሂደት አጋዥ ግብአት የመሆናቸውን ብቃት አይደለም ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጸረ-ሴማዊ ጽንፈኝነት በኢትዮጵያ፡ የኦሮሙማ አዲስ አሰላለፍ

 

 

  1. ሰሞነኛው ረቂቅ አዋጅ

ከሰሞኑ የጥላቻ ንግግርንና የሃሰት መረጃን ለመቆጣጠር የሚል ረቂቅ አዋጅ በህግ ተርጓሚው የመንግሥት አካል (በጠቅላይ አቃቤ ህግ) ተዘጋጅቶ በሚኒስትሮች ምክር ቤት (በህግ አስፈፃሚው) እንዲፀድቅና የቀረበለትን ሁሉ እጅ አውጥቶ ከማፅደቅ (rubber stamp) ያለፈ ሥራ ለሌለው ፓርላማ ቀርቦ እንዲፀድቅ   በሂደት ላይ መሆኑ ተነግሯል ። ረቂቁም ለሚዲያ ይፋ ሆኗል ።

በመሠረቱ ሆን ተብሎ የሚደረግ የጥላቻ ንግግርንና የሚሰራጭ ጎጅ የሃሰት መረጃን ለመቆጣጠር ወይም ለመከላከል ምንም አይነት ህግ (አዋጅን ጨምሮ) አያስፈልግም ማለት ትክክለኛ የመከራከሪያ መነሻ ሃሳብ አይደለም ።

የዚህ ረቂቅ አዋጅ አነሳስና አካሄድ መሬት ላይ እየሆነ ካለው እውነታ አንፃር ሲታይ  ግን ያሳካል ተብሎ ከተቀመጠለት ዓላማ ይልቅ ለፖለቲካ ፍጆታነት የመዋሉ እውነታ በእጅጉ ያመዝናል ። ይህን ለመረዳት ብዙ ሃተታና ትንታኔ የሚጠይቅ ባለመሆኑ አስተያቴን የምሰነዝረው በሚከተለው ጥያቂያዊ አቀራረብ ነው ።

  • ዋነኛው የአገር ምስቅልቅል ምክንያት (ምንጭ) ሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በጎሳ/በዘውግ ማንነት ከፋፍሎና በጥላቻ አናክሶ ለመግዛት ሥራ ላይ የዋለውና አሁንም በጭራሽ አይነካም እየተባለለት ያለው ህገ መንግሥት ተብየ መሆኑን ለተፈፃሚነቱ በርትተው ሲሠሩ የነበሩትና አሁን የለውጥ አራማጆች የምንላቸው ፖለቲከኞች አሳምረው አያውቁትም እንዴ?
  • ኢህአዴግ ህዝብ መብቱን በጠየቀ ቁጥር ከጠረጴዛው መሳቢያ እየመዘዘና ከሃሰት ውንጀላ ጋር እያስማማ ንፁሃን ዜጎችን ሲያሳድድበት ፣ የቁም ስቃይ ሲያሳይበት፣ ሲያስርበትና ሲገድልበት የኖረውን ህገ መንግሥት ተብየ አሁንም የሙጥኝ እያሉ የጥላቻ ንግግርን በአዋጅ እቆጣጠራለሁ ማለት በህዝብ የእውቀት ችሎታ ላይ መቀለድ አይሆንም እንዴ?
  • በአገራችን እያስተዋልነው ያለነው በጎሳ/በዘውግ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ላይ ተመሥርቶ የንፁሃን ዜጎችን ህይወት በአሰቃቂ ሁኔታ ምስቅልቅሉን እያወጣ ያለው የፖለቲካ እብደት እውን በጥላቻ ንግግርና የሃሰት መረጃ ምክንያትና ግፊት ነው እንዴ?
  • የኦሮሚያ (ኦዴፓ) ባለሥልጣትና ካድሬዎች ሚሊዮኖች ንፁሃን ዜጎችን በገዛ አገራቸው ለዓመታት ከኖሩበት ቀየ መጠጊያቸውን (ቤታቸውን) እያፈራረሱ ታይቶ ለማይታወቅ ሰቆቃ የዳረጓቸው በጥላቻ ንግግርና በሃሰት መረጃ ስርጭት ነበር (ነው) እንዴ? ይህ አይነቱ አስከፊ ድርጊት ከንግግርና ከሃሰት መረጃነት በላይ የአደገኛ ጥላቻ ምንጭ ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል ?
  • የጎሳ/የዘር ፖለቲካ ማንነት የወለደው አስቀያሚ የፖለቲካ ሰብእና ወገን በወገኑ ላይ የሚፈፅመውን እጅግ ኢሰብአዊ ድርጊት እንኳን ለማውገዝና በህግ አግባብ ለማስኬድ የደም እንባ የሚያነቡትን ዜጎች ጩኸት ሰምተው ባለጌና ጨካኝ ካድሬዎቻቸውን ነውር ነው ብለው ለመገሰፅ የሞራል ብቃት የከዳቸው የለውጥ አራማጅ የምንላቸው ፖለቲከኞች የጥላቻ ንግግርን ልክ የሚያስገባ ታሪካዊ አዋጃችን “እልልልል! ብላችሁ ተቀበሉን” ሲሉን ምን ማለታቸው ነው?
  • ለሁሉም ተቀዋሚ ነኝ ባይ ከተደረገው ወደ አገር ቤት ገብቶ በሰላም የመታገል ጥሪ በተለየ አሥመራ (ኤርትራ) ድረስ በመሄድ ለህዝብ ባልተገለፀ ስምምነት ወደ አገር ቤት በገባና አቀባበል በተደረገለት ማግሥት ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ውስጥ የገባው ኦነግ ምክንያቱ የጥላቻ ንግግርና የሃሰት መረጃ ስርጭት ነበር (ነው) እንዴ ? እስከአሁን ይህን ክፉና አደገኛ አባዜ አግባብነት ባለው ህግና ፖለቲካ አደብ ማስገዛት የተሳናቸው (ያልፈለጉ) የለውጥ አራማጅ የምንላቸው ፖለቲከኞች ለጥላቻ ንግግርና ለሃሰት መረጃ ስርጭት የአዋጅ ድርሰት ቢጤ ደርሰው ሁላችንም በየኪሳችን ይዘን ከመናገራችን በፊት እንድናነበው ሊነግሩን ሲቃጣቸው  ምን ማለታቸው ነው?
  • በማእከላዊና በሰሜን ምራብ ጎንደር ወደ መቶ ሽ የሚጠጉ ንፁሃን ዜጎችን ያፈናቀለውና ለሰቆቃ የዳረገው ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ቅፅበታዊ ሳይሆን ቀደም ብሎ የሚታወቅ መሆኑን አሳምሮ እያወቀ የመከላከል እርምጃ መውሰድ የተሳነው (ያልፈለገው)   የቀድሞው ብአዴን የአሁኑ አዴፓ  ተብየውስ “የውድመቱ ምክንያት የጥላቻ ንግግርና የሃሰት መረጃ ነውና አዋጁን በሆታ ተቀበሉልን” ሲል ምን ማለቱ ነው?   ፍፁም ሰላማዊ በሆነ አግባብ መብታቸውን ለማስከበር የተንቀሳቀሱ ንፁሃን ዜጎች በጋጠ ወጥ ቡድኖች (ምናልባትም ፖለቲከኞች ነን ባዮች) ግንባራቸው በጋለ የቡና ጀበና ሲበረቀስ እና በጠራራ ፀሃይና በአደባባይ በጦር መሳሪያ በታጀበ አመፅ ሲዋከቡ (ደሴና ባህርዳር ላይ የሆነውን ያስታውሷል) ምን ይሠራ ነበር ? ታዲያ እንዲህ አይነቶቹ “የለውጥ ሃዋርያት” የጥላቻ ንግግርንና የሃሰት መረጃን ለመቆጣጠር የምናፀደቀውን አዋጅ “ታሪካዊ እያላችሁ እንድትታዘዙለት” ሲሉን ምን ማለታቸው ነው ? በእንዲህ አይነት የበሰበሰና የከረፋ የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ ስለምን አይነት እውነተኛ ለውጥ ነው  የምናወራው ?
  • ደህዴንስ (የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ) በጎሳ ወለድ ፖለቲካና በኑሮ ከባድነት ናላቸው በዞረ ሥርዓተ አልበኛ ወጣቶች የሚታመሰውን እና የአያሌ ንፁሃን ዜጎች ምስቅልቅሉ የወጣበትን ክልል መቆጣጠር (በቅጡ ማስተዳደር) የተሳነው እውነት በጥላቻ ንግግርና በሃሰት መረጃ ምክንያት ነው ?
  • ህወሃት “ሉአላዊት ትግራይ” ላይ ሆኖ ያዙኝና ልቀቁኝ እያለ እነ ዶ/ር አብይን ያስቸገረውና አገርን እያወከ ያለው እውን በጥላቻ ንግግርና በሃሰት መረጃ ምክንያት ነው?

ታዲያ የእነዚህ የጋራ ማእከል በሆነው ኢህአዴግ የሚመራው መንግሥት  “ስጋት ላይ የጣለኝ የጥላቻ ንግግርና የሃሰት መረጃ በመሆኑ ለዚህ መድህን ነው ያልኩትን አዋጅ በፀጋ ተቀበሉና ተገዥው ሁኑ ፥ ያለዚያ አይቀጡ ቅጣት ይጠብቃችኋል” ሲለን አሜን! የምንል ከሆነ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከቶ የእኛ ሊሆን አይችልም ።

 

ለማጠቃለል

ሥልጣን ላይ ያሉ ፖለቲከኞች የሚያውጇቸው  አዋጆች መሬት ላይ ያለውን ዒላማቸውን እየሳቱ የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ ጨዋታ አካል ለመሆናቸው ተጠያቂዎች ፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ቅን አሳቢ ዜጋ በተለይ ደግሞ ተማረኩና ተመራመርኩ (ልሂቅ የሚል ግዙፍ ፅንሰ ሃሳብ በቅፅልነት የተሸከመው) እና በመማር ላይ ያለው የህብረተሰብ ክፍል መሆኑ በፍፁም መዘንጋት የለበትም ።

ለውጥ ሳይሆን ለለውጥ መሳካት የግድ የሚሉ አንዳንድ በጎ ኩነቶች በታዩበት በዚህ ወቅትም ተማርኩና ተመራመርኩ ወይም እየተማርኩና እየተመራመርኩ ነው ከሚለው የህብረተሰብ ክፍል የምንሰማውና የምናየው  በጭራሽ የሚያበረታታ አይደለም ። ይህ የህብረተሰብ ክፍል   በድንቁርና በታወሩና ከተበላሸ የፖለቲካ ሥርዓት እንጠቀማለን በሚሉ ሸፍጠኛና ሴረኛ የጎሳ/የመንደር ፖለቲከኞች እጅግ የከፋና የከረፋ የፖለቲካ ጨዋታ ሰለባ እየሆነ መቸገሩን በጥሞና እና በቅንነት ተገንዝቦ የሚመጥነውን ሚና በመጫወት ፖለቲከኞችን ከተለከፉበት በጎሳ/በዘር አጥንት ቆጠራ ከሚዘወር የፖለቲካ ጨዋታ ይወጡ ዘንድ ሊያግዛቸው ይገባል ።

አዎ ! በትክክለኛው አተረጓጎም ፊደል መቁጠር (መማር) ማለት እንኳን የራስ ወገን ሰው የሆነ ፍጡር ሁሉ ከችግርና ከመከራ ይላቀቅ ዘንድ ፈጣንና ውጤታማ መፍትሄ የመፍጠርና የማበርከት ፈቃደኝነትና አቅም ባለቤትነት  ማለት  ነው ።   ተወደደም ተጠላ አፍጥጠውና አግጥጠው እየተናነቁ ወደ ፊት አላንቀሳቅስ ማለት ብቻ ሳይሆን ወደ ባሰ አዙሪት መልሰውና መላልሰው እየዘፈቁን ካሉት መሪር እውነቶች መካከል ይኸ ተምሮ ወይም እየተማሩ የመውደቅ አባዜ አንዱ ነውና ልብ እንበል ። ያለዚያ ፖለቲከኞችም ለፖለቲካቸው ጨዋታ መቀጠል ይጠቅመናል ያሉትን ዘዴ ሁሉ እየተጠቀሙ ይቀጥላሉ ፣ ህዝብም ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ከኖረበት የመከራና የውርደት ሥርዓት ብዙም በማይሻል ሁኔታ ውስጥ ሲዳክር ይኖራል ወይም በፖለቲከኞች ልክ የሌለው ሸፍጥና ሴራ ተጎትቶ  ወደ ባሰ አዘቅት ውስጥ ይገባል ። ጊዜ የለምና አሁንኑ የሚበጀውን መምረጥና ማድረግ ግድ ይላል ።

 

1 Comment

  1. We can learn a lot from Derg’s first few years and the declaration of land use Derg announced .

    “ደርግ ሥልጣን ሲይዝ መንግሥት አልነበረም ቢባልም ሥርዓት አልባነትን የመቆጣጠሪያ ጉልበትና ቁርጠኛነት ነበረው”. Professor Mesfin Woldemariam wrote on the link below.

    -Derg. killed 60 Ministers without any judicial process.
    -Derg confiscated money in bank accounts and confiscated other assets without judicial process just to spend it on alcohol and women..
    -Derg ordered mass capital punishment/red.terror without judicial.process.
    -Derg is what started the ሥርዓት አልባነትን we see going on till today. Even Hailesselasie himself deserved to stand trial but the ሥርዓት አልባ Derg didn’t even charge him with a crime officially.
    -Derg just burried Hailesselasie alive and built an office on top of him.

    Now trying to get added and return to Ethiopia Derg came up with new history about what happened to Hailesselasie. The New info from Derg is released lately claiming ,”Hailesselasie burried himself like Sadam Hussein trying to escape from derg prison and fell into a deep whole where he was found dead.”. Derg is saying he didn’t kill Hailessealsie . Noone will believe it but derg is claiming it from Zimbabwe. Nomatter what Mengistu says The whole country knows Derg is a group of cannibals that ate Ethiopia and drunk Ethiopians blood worse than the Hailesselasie regime. The Hailessealsie regime wasn’t perfect actually it was far from perfect, but it was so much better than derg.
    Famine, starvation , disease , civil unrest and terror weren’t part of Ethiopians daily life that occur year after year 45 years ago, all these became common after 1974.

    Derg = ሥርዓት አልባ

Comments are closed.

Share