March 28, 2019
29 mins read

አፍ ባይናገር ሌላው ይናገራል! – በገብረ ክርስቶስ ዓባይ

ሰው የሚወደውንና የሚያከብረውን ጠንቅቆ ያውቃል። ምናልባት ከልብ ከማመኑ የተነሣ መሳሳቱን ሌላ ሰው ቢጠቁመውና ቢመክረው አንኳ የምቀኛ ወሬ ነው በማለት ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ሊዘናጋ ይችላል። ይህም በመሆኑ ጸጸትና ቁጭት ሊያሳድርበት አይችልም። ምክንያቱም አውቆና ሆነ ብሎ የፈጸመው በመሆኑ ነው። ነገር ግን ሲነገረውና ሲጠቆመው የኖረውን ነገር እራሱ በራሱ በግልጽ የተረዳውና የተገነዘበው ጊዜ፤ ያንን ሲያከብረውና ሲኮፍሰው የኖረውን ሰው አያድርገኝ። እንደቆሻሻ እና ‘ሠገራ እንደነካው እንጨት’ ይጠየፈዋል። ቀጥሎም፤ ለከሐዲው ሰው ወዮለት፤ በክብር ፋንታ ውርደት፤ በከፍታ ፋንታ ዝቅጠት ይጠብቀዋልና!

ይህን ካልኩ በኋላ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝን ምክንያት ልጠቁም። እንደሚታወቀው አገራችን አሁን ያለችበትን ወቅት አስመልክቶ አፍቅሮ ኢትዮጵያውያን በሙሉ በከፍተኛ ደስታና ሐሴት ላይ ሲገኙ በአንፃሩም ንፍቀ ኢትዮጵያውያን ግን አንገታቸውን አቀርቅረው ጥልቅ የሤራ ገመድ በመጎንጎን ላይ ናቸው። ለሁለቱም ወገን የመጣው ለውጥ ከሰው አእምሮ በላይ የሆነ ክስተት በመሆኑ በሁኔታው የተሰማን ስሜት ድብልቅልቅ ያለ ነው። እውን የማይመስል ገሐድ ክስተት! በአጭሩ እፁብ ድንቅ የሚባል፤ ለማመን እጅግ በጣም የሚከብድ ጉዳይ ነው። ይሁን እንጂ የለውጡ ሂደት በግልጽ እየታየ ሲሆን፤ የለውጡ ባለቤት ኃያሉ አምላክ መሆኑን በመዘንጋት ሁሉም በየፊናው በቡድን በቡድን ተደራጅቶ ለውጡን ያመጣነው፤ እዚህም እዚያም ‘እኛ ነን’፤ ‘እኛ ነን’ በማለት ዋናውን ጉዳይ ወደጎን በመተው ጉንጭ አልፋ ከርክርና ሙግት ውስጥ ገብተዋል።

ይህ ቅጥ ያጣ ውዥንብር ከምኒልክ ቤተመንግሥት በድንገት የተሰናበተውን እና መቀሌ በመመሸግ በሊዳማ እየቆዘመ ለሚገኘው ወንጀለኛ እና ዘራፊ የአድዋ ቡድን ለተጨማሪ የተንኮልና ሤራ ጥንሰሳ አመቺ ሁኔታ ፈጥሮለታል። ለዚህ ተንኮልና የማያቋርጥ የሤራ መረብ መታታት፤ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ እንደ ጥሩ ነዳጅ በመሆን እያገለገለ ያለው ‘የሀገር ጉዳይ ጥልቅ የመንፈስ ዕውቀት ያልሰረጸበት፤ የዘመኑ ቴክኖሎጂ የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ እምቡር እምቡር ባዩ ወጣቱ ትውልድ ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት የወያኔን የዘር ፖለቲካ ከልጅነታቸው ጀምሮ እንደ ጡጦ እየመጠመጡ ያደጉ በመሆኑ ነው።

ወጣቱ ትውልድ፤ በግብታዊነት በሚያራምደው የጠባብነትና የዘር ፖለቲካ በስፋት ተጠልፏል። በተለይ ቄሮ የሚባለው ኦሮሞ፤ በአድር ባይ ወገኖቹ ተባባሪነት የወያኔን የመቶ ዓመት የቤት ሥራ ይተገብር ዘንድ ከራሱ ፊደል ይልቅ የባዕድ ፊደል እንዲጠቀም ጫና ተደርጎበት ቆይቷል። ከዚህም የተነሳ የተሻለ ዕውቀት አላቸው ተብለው የሚገመቱት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሳይቀሩ ለዚህ የኋላቀርነት አስተሳሰብ ሰለባ ሆነዋል። ዋናው ምክንያት ደግሞ በቋንቋ አለመግባባት እንደሆነ መረዳት አይከብድም።

የዚህን ክፍተት በመጠቀም የወያኔ ወንጀለኞች በፌስቡክ ሠርገው በመግባት ሁለቱን ታላላቅ ብሔረስቦች በተለይ ኦሮሞን እና አማራን ለማቃቃር ተንኳሽ የፈጠራ ትርክቶችን በመፍጠርና ሐሰተኛ የፖለቲካ ቤንዚን በማርከፍከፍ፤ እሳቱም እንዳይጠፋ በማራገብ ላይ ተጠምደዋል። በአንፃሩም አገር እንዳትፈርስ በልበ ሠፊነትና በታጋሽነት በጥበብ እየተንቀሳቀሰ ያለውን የዶ/ር ዓቢይን የለውጥ ቡድን ከደጋፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመነጠል ከፍተኛ ሥራ እየሠራበት ይገኛል።

በሠራው ወንጀል ምክንያት ኅሊናው ሲሞግተው ዕንቅልፍ የተሳነው አካል፤ አልኮል እየተጋተ በቅዠት ባህር እየዋኜ የሚገኘው ወያኔ፤ “እኔ ከሞትኩ ሠርዶ አይብቀል” እንዳለችው እንስሳ፤ ሰይጣናዊ የሆነ የሕዝብ ጥርጣሬና አለመረጋጋት እንዲፈጠር በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የልዩነትና የቅራኔ መርዝ ያለመታከት እየረጨ ነው።

የለውጡ ቡድን እየወሰደው ያለው ጥበብ የተሞላበት አገር የማዳን ተግባር፤ ታጋሽነትና ሆደ ሠፊነት፤ እንደ ደካማነትና የችሎታ ማነስ ተደርጎም እየተራገበ ነው። ወንጀለኛው ወያኔ ቀደም ሲል የዘረፈውን የአገሪቱን አንጡራ ሀብት በየቦታው እየበተነ የለውጡን ቡድን በተናጥልና በኅብረት የስም ማጥፋት ዘመቻ ማናፈሱን የየዕለት ተግባሩ አድርጎ ቀጥሏል።

ለዚህ የስም ማጥፋት ዘመቻ ዋነኛ ተባባሪ በመሆን እየሠሩ ያሉት ከተጋሩ በላይ በጃዋር መሐመድ የሚመራው የኦሮሞ ሜዲያ ኔትወርክ እና ወያኔ እንደ ሮቦት የሚጠቀምባቸው የኦነግ ዓባላት ናቸው። ወያኔ ይህንን ስትራተጂ የያዘበት ዋናው ምክንያት ከትግራይ በስተቀር ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ በግልጽ ድጋፋቸውን የሰጡ በመሆኑ፤ ‘ልጡ ተርሶ ጉድጓዱ ተምሶ’ የኅልፈተ ሕይወት ተራውን እየተጠባበቀ ያለው የእነ አቦይ ስብኀት ቡድን ወደዚህ ‘ኢትዮጵያ ሱሴ ናት’ ባዩ ቡድን ውስጥ ለመግባት የሚያመች ዕድል አልገጠመውም ለማለት ይከብዳል። ሙከራው እንኳ ቢኖር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያመረረ በመሆኑ በቀላሉ እንደሚጋለጡ ያውቃሉ።

ስለዚህ ያሏቸው ሁለት አማራጭች ሲሆኑ አንደኛው በቅማንት ስም የሚንቀሳቀሱ ትግራይ በቀል ወዶ ዘማቾችን አስርጎ በማስገባት የአማራውን ሰላም ለማወክና የለውጡን መንፈስ ለማራከስ የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ ይገኛሉ። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በቲም ለማና በዶ/ር ዓቢይ አህመድ አመራር ምንም ጥርጣሬ አልነበረውም። ነገር ግን ሠይጣናዊው ወያኔ በኦነግ አማካይነት የመርፌ ቀዳዳ የምታክል ቀጭን በር ዛላንበሳ ላይ ለመሸንቆር ዕድል በማግኘቱ በዚያች ሽንቁር በመጠቀም መላዋን ኢትዮጵያ ለማተራመስና እርስ በእርሱ ለማጋጨት የማይቧጥጡት ተራራና የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም።

ኦነግ ከነበረበት የስደት ቦታ ሆኖ ለሃያዎቹ ዓመታት በሻብዕያ ምፅዋዕት ሲተዳደር የቆየ ለመሆኑ በግልጽ ይታወቃል። ይሁን እንጂ ተሰነይ ላይ ያጸደቀው፤ አማራን ያገለለ የጭቦ ሕገመንግሥት አብሮ ያዘጋጀ ቢሆንም እንኳ፤ህወሀት ወያኔ ከሽግግር መንግሥቱ በዘዴ ገፍትሮ ሲያስወገደው ሊታደገው እንዳልቻለ የሚዘነጋ አይደለም።

ነገር ግን ይህ ሁሉ ግፍ ተሠርቶበት፤ የኦነግ መሪ ነኝ የሚለው ኅሊና ቢሱ ዳውድ ኢብሣ፤ ለሁለተኛ ጊዜ በገንዘብና በጦር መሣሪያ በመታለል የወያኔን ሥውር ጉዳይ አስፈጻሚነቱን ተሹሞ ወደ ሀገሩ ሲመለስ፤ ይህንን ያልተረዳው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከኦሮሞ ወንድሞቹ ጋር በመሆን እንኳን ለሀገራችሁ በሰላም ገባችሁ በማለት የጀግና አቀባበል አድርጎለታል። “…. እና ሽንፍላ ቢያጥቡት አይጠራም” እንደሚባለው ዳውድ ኢብሳ ያከበረውን እና ወደ እናት ሀገሩ እንዲገባ መስዋዕት የከፈለለትን ሕዝብ በመናቅ፤ ከሃያ ዓመታት በላይ ሲጫወትበት እና ሲሳለቅበት ለነበረው ሕወሃት በመንበርከክ በሪሞት ኮንትሮል የሚሰጠውን ትዕዛዝ እየተቀበለ ድብቅ አጀንዳውን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።

ለነገሩ ይህንን ሤራ የዶ/ር ዓቢይ መንግሥትም ይሁን ቲም ለማ አያውቀውም ለማለት ይከብዳል። ምክንያቱም ይህንኑ የሚያረጋግጡ አንዳንድ አንኳር ፍንጮች አሉና! አንደኛው አጋሚዶው ዳውድ ኢብሣ፤ ከጋዜጠኞች በተደረገለት ቃለ ምልልስ ወቅት ስለትጥቅ ተጠይቆ ‘ትጥቅ ያስፈታ የለም፤ እኛም አልፈታንም ለምን እንፈታለን’ በማለት መናገሩ አይዘነጋም።

ሲጀመር ከኤርትራ ሲነሣ ትጥቁን አስረክቦ ጀሌውን መምጣቱ በግልጽ ሲታወቅ፤ እንደታጠቀ ወደ ሀገሩ የገባ ለማስመሰል ሞክሮአል። ዛላአንበሳ ላይ ከህወሃት ጋር በነበረው ግብዣ ወቅት በተደረገው ስምምነት መሠረት ሀገር ለማተራመስ የሚያስችል፤ጠቀም ያለ ገንዘብ እንደተቀበለና መሣሪያ ደግሞ በቤንሻንጉል አካባቢ በሄሊኮፕተር ከህወሃት ወያኔ እንደተራገፈለት የዓይን ምስክሮች አሉ።

መሣሪያውን እንዳገኘም ንቃት የጎደላቸውን የተለያዩ የኦረሞ ወጣቶች በመመልመል በማሠልጠንና በማስታጠቅ ከጌታቸው አሰፋ የሚሰጠውን መመሪያ እየተቀበለ በምዕራብ ወለጋ የሚኖረውን ኦሮሞ ያልሆነውን ሰላማዊ  ሕዝብ በመዝረፍ፤ በማፈናቀልና በመግደል ከአካባቢው የማጽዳቱን ተግባር ተያያዘው።

ለዚህም እንደ ተጨማሪ ማጠናከሪያ በመሆን እያገለገለ ያለው በጀዋር ሞሐመድ የሚመራው የኦሮሞ ሜድያ ኔትወርክ ሲሆን፤ የዶ/ር ዓቢይን መንግሥትና የቲም ለማን የለውጥ ሂደት፤ኦሮሞን ያገለለ አፍቅሮ ኢትዮጵያ እየሆነ ነው በማለት፤ የኦሮሞን ሕዝብ ለማሸፈት ብዙ ብዙ የማጥላላት ዘመቻ ሲያራምድ ቆይቷል። ለዚህም ውለታው የወያኔ ጉዳይ አስፈጻሚ እንደሆነ በሚነገርለት የቅርብ ጓደኛው አሉላ ሰሎሞን አማካይነት ጠቀም ያለ ገንዘብ እንደተሰጠው አሳማኝ ፍንጮች አሉ።

ከዚህም የተነሳ ‘ጥሩ መንግሥት መጣልን’ በማለት ገላቸውን ሰደው በነፃነት እየኖሩ ያሉትን፤ በምዕራብ አዲስ አበባና በቡራዩ አካባቢ ይኖሩ የነበሩትን ኢትዮጵያውያንን በጠራራ ፀሐይ ሕገወጥ የሆነ የመንጋ የማፈናቀልና አረመኔያዊ ግድያም ተፈጽሟል። የዚህ ዘመቻ ዋናው አቀነባባሪና ተዋናኝ የሆነውን ጃዋር ደፍሮ የጠየቀው የለም። በዚህ ብቻም አላበቃም በምዕራብ ወለጋ ያሉ የፖሊስ ጣቢያዎች ላይ የጦር መሣሪያ ዘረፋ ተፈጽሟል። የመንግሥት ጸጥታ አስከባሪ ፖሊሶችም የኦነግ ዓባል ባለመሆናቸውና ኃላፊነታቸውን በመወጣት ላይ እንዳሉ ያለአግባብ መስዋዕት ሆነዋል።

ቀጥሎም እጅግ በጣም የሚገርም ተግባር ተፈጸመ ይኸውም 18 ባንኮች በተመሳሳይ ጊዜና ሰዓት በኦነግ ታጣቂዎች መዘረፋቸው ይፋ ሆነ። በዚህ ጊዜ ሁኔታው ያልጣማቸው አብዛኛው የዶ/ር ዓቢይ ደጋፊ ኢትዮጵያውያን ከለውጡ ባቡር ወራጅ አለ ማለት ጀመሩ። “እንኳን ይችን የዝንብ ጠንጋራም እናውቃለን!” በማለት በተለይ የፌስ ቡክ አክቲቪስቶች የለውጡን ሂደት በጥልቀት መመርመር ተያያዙት።

በእርግጥ ግልጽ ያሉ ፍንጮች ታይተዋል፤ ለምሳሌም የአዲስ አበባ ም/ከንቲባ ተብሎ የተሾመው ኢጅነር ታከለ ኡማ ጉዳይ አንደ አንድ ጉልህ ማስረጃ ሆኖ ሊወሰድ ይቻላል። ምክንያቱም በዘር መስፈርት ካልተመዘነ በስተቀር፤ በእውነት  በልምድም ሆነ በዕውቀት ከእርሱ የተሻለ ሰው ጠፍቶ ነውን? በማለት ይጠይቃሉ። በአጠቃላይ ደጋፊውን ሕዝብ ለማማለል ይረዳ ዘንድ የማስመሰል ፖለቲካዊ ድራማ ሲሠራ ወራቶች አልፈዋል።

ጃዋር በተለያየ ሜዲያ እየቀረበ እንደፈለገ አፉን ሲከፍት ቆይቷል። አቋሙ ግልጽ ሳይሆን አራቦ እና ቆቦ እየረገጠ አንዴ የለውጡ ደጋፊ ሲመስል፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ በግልጽ ተቃዋሚ እየሆነ ቴአትር ሲተውን እንደነበር አይዘነጋም። ይልቁንም የመደመርን ፍልስፍና ቀመር ለዶ/ር ዓቢይ የሰጠሁት እኔ ነኝ እስከ ማለትም ደርሷል። ይህ ሁሉ ሆኖ እያለ እንደገናም በኦነግና በኦዴፓ መካከል ተፈጠረ የተባለውን አለመግባባት “ዓይናችሁን ጨፍኑና ላሞኛችሁ” ድራማ በአባ ገዳዎች አማካይነት ለማስማማት በሚል በተተወነው መድረክ ጃዋር ሞሐመድ በጸሐፊነት እንዲሰየም መደርጉ ሌላው ሁለተኛው የጥርጣሬ መነጽር ድርጊቱን ፍንትው በማድረግ አስመሳዮቹን እርቃናቸውን እንዲቆሙ አድርጓቸዋል በማለት ይከሳሉ።

አክቲቪስቶቹ ሌላም ተጨማሪ ፍንጭ ይመዛሉ፤ ይኸውም የኦሮሞ ሜዲያ ኔትወርክ በአዲስ አበባ የተደራጀው ዶ/ር ዓቢይ ወደ አሜሪካ ከመሄዳቸው በፊት እንደሆነ አስረግጠው ይናገራሉ። ይህም ማለት እየዘመርንለት ያለው የዶ/ር ዓቢይ እና የቲም ለማ ቡድን ከመጋረጃ ጀርባ ‘ቁጭ በሉ’ ተጫውተውብናል በማለት ይቆጫሉ። እነዚሁ አፍቃሪ ኢትዮጵያውያን በዚህ አላበቁም፤ ያለፈውን የህወሃት ታሪክ ዋቤ በማድረግ ያነፃጽራሉ።

ወያኔ ህወሃት አዲስ አባባን በተቆጣጠረ ማግሥት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን እና የንግድ ባንክን በመዝረፍ ነበር፤ ኤፈርትን ለመመሥረት እንደመቋቋሚያ የተጠቀሙበት። እንደዚሁ ሁሉ የዶ/ር ዓቢይ እና የቲም ለማ የለውጥ ቡድን (አዴፓን አይጨምርም) “በልጅ አመካኝቶ ይበላሉ አንጉቶ” እንዲሉ በኦነግ አሳቦ 18 ባንክ በአንድ ቀን እንዲዘረፍ የተደረገው ቅንብር ኦዴፓን በኢኮኖሚ ለማፈርጠም እንደሆነ መጠራጠር አይቻልም በማለት ይሞግታሉ።

ጸሐፊው የአክቲቪስቶችን ጥርጣሬና ግምት እንደ ነፃ አመለካከት ቢያከብርላቸውም፤ ዶ/ር ዓቢይም ሆነ አቶ ለማ መገርሣ በእንደዚህ ያለ የተዋረደ ተግባር ላይ ይሳተፋሉ የሚል ዕምነት የለውም። ምክንያቱም “የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ” ነውና እንዲህ ያከበራቸውን እና ያመናቸውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ይከዳሉ የሚል ቅንጣት ታህል ጥርጥር የለውምና ነው። ነገር ግን አንድ ነገር መጨመር ተገቢ ይሆናል። ይኸውም “መጀምሪያ ባልዘፈንሽ፤ ከዘፈንሽ ደግሞ ባላሳፈርሽ” እንዲሉ ቲም ለማ ጥርት ያለ ቁርጠኝነት እንደሚጎለው ይስተዋላል።

“ሁለት እግር አለኝ ተብሎ በአንዴ ሁለት ዛፍ ላይ መውጣት አይቻልም” እንዲሉ፤ ቲም ለማም፤ ወይ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን መቆም፤ ወይም ደግሞ ከኦነግና ከጀዋር ጎን መቆም አለበት። ሁለቱንም ላለማጣት ብሎ ውሀ ላይ እንደወደቀ ኩበት የሚዋልል ከሆነ ከመበስበስ የሚታደገው አንዳች ኃይል አይኖርም። ሠፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሃያ ሰባት ዓመታት የህወሃትን ግፍና መከራ እየታገለ፤ ያላሰለሰ መስዋዕትነት ሲከፍል ቆይቶ ያመጣውን የለውጥ ድል፤ የሻዕቢያን አዝመራ ሲኮድድና ከብት ሲያግድ የቆየው ኦነግ፤ ከስደት ወደ ሀገር ቤት እንዲገባ መደረጉ መጥፎ ባይሆንም፤ ነገር ግን የኢትዮጵያውያንን ድል እንዲነጥቅ የተቀነባበረ ክኅደት ተፈጽሟል።

የድሉ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳያውቀውና ግልጽ ባልሆነ ድርድር፤ ኦነግ በዛላአንበሳ ተስለክልኮ ወደ መሃል አገር ገብቶ በለውጡ ኃይል ላይ እንደዘንዶ ተጠምጥሞበታል፤ ጃዋር መሐመድም በኦሮሞ ሜዲያ ኔትወርክ እየታገዘ የኢትዮጵያውያንን አንድነት ለመሸርሸር፤ በቀጥታ የወያኔን የመከፋፈያ ፕሮፓጋንዳ እንደ እባብ መርዝ፤ በኦሮሞ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብም ላይ የሚያሳድረው ጥርጣሬና የጥላቻ ፖለቲካ በቀላሉ መታየት የለበትም።

ከእነዚህና ሌሎች ተመሳሳይ ድርጊቶች ተነስቶ አፍቃሪ ኢትዮጵያውያን ቢጠራጠሩ ሊፈረድባቸው አይገባም። “እባብን ያዬ በልጥ ይደነግጣል” እንደሚባለው የሃያ ሰባት ዓመት የህወሃት ወያኔ የዘር ፖለቲካ ያንገፈገፈው ኢትዮጵያዊ የለውጡን ደስታ አጣጥሞ ሳይጨርስ፤ ተስፋን የሚያጨልም መንፈስን የሚፈታተን ጉዳይ፤ ዕለት በዕለት ሲተገበር እያዬ ሰውነቱ ቢቆጣ፤ ደሙ ቢፈላ ተገቢ ነው። ይህንን ሁኔታ አግባብ አይደለም በማለት የሚያጥላሉት እነጃዋር ብቻ ናቸው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀደም ሲል በተማሪዎች አማካይነት የተገኘውን አብዮት በደርግ ተቀምቷል፡ ለደርግ መውደቅ ሲታገል የቆየው የኢትዮጵያ ሕዝብ በወያኔ ጠባብ ከሐዲዎች ተነጥቆ በጥቂት የአድዋ ዘራፊ ቡድን ሲንገላታ መቆየቱ የማይታበል ሐቅ ነው። አሁንም ከሃያ ሰባት ዓመታት ሥቃይ የበዛበት ትግል በኋላ በህወሃት ላይ የተገኘው ለውጥ በአፍቅሮ ኦነግ ከሐዲዎች አማካይነት ድሉን ሊነጠቅ በቋፍ ላይ ይገኛል።

እዚህ ላይ ቲም ለማ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ወደ ኦነግ ተሸብልሏል ለማለት ያስደፍራል። ምክንያቱም አጀማመራቸውና አካሔዳቸው፤ አነጋገራቸውና ተግባራቸው፤ ቃልኪዳናቸውና እምነታቸው ፈጽሞ ሊጣጣሙ አልቻሉም። ለዶ/ር ዓቢይም በጎ ራዕይ ጥሩ ምልክት እንዳልሆነ ማንም የሚገነዘበው ጉዳይ ነው። “ከተልባ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ” እንዲሉ የዶ/ር ዓቢይ መንግሥት እንደ ሳንድዊች አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። እጅግ በጣም የሚያሳዝን ጉዳይ ነው። ሕዝብ ምን ጊዜም አሸናፊ መሆኑን አምኖ መቀበል ብልህነት ሲሆን፤ ይህንን በመናቅ በኃይል ተማምኖ በዕብሪት መወጠር ግን ለሒትለርና ለሙሶሊኒም አልበጃቸው።

በተለይ በአሁኑ ወቅት አንዳችም ነገር ምስጢር ባልሆነበት የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የዲጂታል ጊዜ፤ ችግሮችን በማፈን ሳይሆን ለባለጉዳዩ ለሠፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ በግልጽ አቅርቦ መወያየቱ ጠቃሚ ይሆናል። ከቀን ወደ ቀን ተዓማኒነቱ እየተሸረሸረ ያለው የቲም ለማ ቡድን እንደ ሕወሃት ያለ የሕዝብ ምላሽ የሚጠብቅ ከሆነ ታላቅ ስህተት ነው። የአዲስ አበባ ሕዝብ አንድ ቀን የተነሳ እንደሆነ ታላቅ ሃፍረትና ውርደት እንደሚፈጠር መገመት አይከብድም። ነገር ግን ታምቆ ታምቆ የፈነዳ ጊዜ የተቆጣውን የሕዝብ ማዕበል የሚገድብ አንዳችም ኃይል አይኖርም። ይህ ከመሆኑ በፊት ከሽንገላና ከመጋረጃ በስተጀርባ የሚካሄደውን ስውር አጀንዳ በማቆምና ይቅርታ በመጠየቅ፤ ወደፊትም ሕዝብን የሚያሳትፍ ግልጽ ውይይት በማድረግና በመተማመን መንቀሳቀስ ተገቢ ይሆናል።

የአዲስ አበባ ጉዳይ ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ የወያኔ ቦምብ መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው። ‘ወስፌ ሲለግም ቅቤ አይወጋም’ እንደሚባለው ካልሆነ በስተቀር ዶ/ር ዓቢይም ሆነ አቶ ለማ መገርሣ የሚስቱት አይደለም። ስለሆነም የአዲስ አበባንም ሆነ ማንኛውንም ጉዳይ ለማስፈጸም ታሪክን መሠረት ማድረጉ ለማንም አይበጅም። የታሪክ ሰበዝ እንምዘዝ ከተባለ ግን ወደማያስፈልግ ክርክርና ፍጥጫ የሚመራን ስለሆነ ያለፈውን በመተው አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ተመርኩዘን፤ ለወደፊቱ ምን ብናደርግ ይሻላል? በሚለው አጀንዳ ላይ ትኩረት ማድረጉ ሰላምና ዕድገትን ያመጣል እንጂ፤ወደ ኋላ ተመልሰን የባላባትና የጢሰኛውን ሥርዓት ጊዜ የምንተርክ ከሆነ በተለይ ለኦሮሞ ሕዝብ አይጠቅምም።

ስለዚህ የማይጨበጥ ተስፋ መስጠት የአብሮነት ሰላማችንን ከማደፍረስና ሕዝባችንን ለእርስ በእርስ ፍጅትና ዕልቂት የሚዳርግ ከመሆኑ በስተቀር ጠቃሚ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሎ አይታሰብም። እግዚአብሔር አገራችንን ኢትዮጵያን ይባርክ!

-//-

1 Comment

  1. “……….ወጣቱ ትውልድ፤ በግብታዊነት በሚያራምደው የጠባብነትና የዘር ፖለቲካ በስፋት ተጠልፏል። በተለይ ቄሮ የሚባለው ኦሮሞ፤ በአድር ባይ ወገኖቹ ተባባሪነት የወያኔን የመቶ ዓመት የቤት ሥራ ይተገብር ዘንድ ከራሱ ፊደል ይልቅ የባዕድ ፊደል እንዲጠቀም ጫና ተደርጎበት ቆይቷል።…….”

    You are really adding benzene to the problem on the ground. By saying this, you will not save your FIDEL, Ethiopia, andinet, …..bla-bla. You are pushing the Oromo people more inches towards the our freedom.
    Nagaatti moortu.

Comments are closed.

Previous Story

የሱሪ በአንገት አውልቅ አስገዳጅና ጠማማ ሃሳብ  በጎሠኝነት ላይ ያጠነጠነ የአድማ ፓለቲካ

Next Story

ጢሰኛ ባለ እርስት የሆነባት ሀገር ኢትዮጵያ! (በገ/ክርስቶስ ዓባይ)

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop