1/ የ1966ቱ አብዮት ግርግር ሁሉንም በየፈተቱ ከእንጉልቻው እንዲነሳ አድርጎ ግን ሲያልቅ አያምር ሆነና አንድ ትውልድ አስበልቶ በከፋ ሁኔታ ተንኮታኩቶ በመውደቅ ሕዳጣኖች (የባንዳ ትውልዶች) በለስ እንዲቀናቸው አድርጎ አለፈ።በተለይ ኢላማ የነበረው ›አማራውን‹ በሁሉም ዜጎች በኩል ፈላጭ ቆራጭ፤ጨቋኝ ፤ ትምክህተኛ ብሎ በመፈረጅ ከጫፍ እስከ ጫፍ ጠላቶቹ እንዲበዙ የውሸት ትርክት በመተረክ አማራው በጥርጣሬና ስጋት የሚታይ በበሬ ወለደ የፖለቲካ ጫጫታ እውነት አስመስሎ ስሎ በማቅረብ በአራቱም ማእዘን የንጹሐን ደም በከንቱ እንዲፈስ ሆኗል። ዛሬም ያ የቧልተኞች ሙዚቃ እየተስተጋባ ይደመጣል።
‘’ከድርጊቱ ክፋት እራሴን በደረቁ የላጩኝ” አመመኝ አለ እንደሚባለው ያደረጉትን አድርገው በፈጸሙት ጥፋት ማዘንና መቆጨት ሲገባ ያን እኩይ ተግባራቸውንና ያደረሱትን አሰቃቂ ወንጀል እንደ ጀብድ ሥራ ሲሞካሹበትና ይቅርታም አለመጠየቅ ጭካኔያቸው አውሬያዊና ተተኪውንም ገዥ ኃይል የልብ ልብ እንዲሰማው ማድረጉ ማሰቢያ ህሊና አለኝ ለሚል ጀሮ ሲሰማው ይሰቀጥጣል ለዚያም ነው ‘’ኢትዮጵያ ሀገሬ በሞኝነሽ ተላላ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ’’እንዲሉ ያደረገው ። ውብና መልካም ሀገር እያለን ነገር ግን እንደ አለመታደል ሆኖ »ጤናማ መሪና አስተዳደር~ድኻ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ የሚል ጠፍቶ ወገኔ በግራ ዘመሞች ግራ ተጋብቶ እርስ በራሱ ሲጨራረስ ማየት እጅግ በጣም ያማል።
ለዚህ ጦስ ኢትዮጵያውያንን የዳረጉና የሰለባው ፊታውራሪዎች ዳገት መውጣት ወንዝ መሻገር ባይችሉም በያሉበት ተቃርኖው የፈጠረውን ንቃቃት እንዳይሽር በሽምግልናቸው ዘመንም ከመጥፎ ድርጊታቸው መታቀብ አለመቻላቸው ትኩረት ሊሰጥበትና በቃ አሁን ጊዜው አልፎባችኋል ሊባሉ ይገባል ብየ አስባለሁ።ሞኝ ባያፍርም የሞኝ ዘመድ ያፍር ስለሚባል እንዲህ አይነት ኢትዮጵያዊ ትውልድ የግድ እርምት ይሻል።ቢያንስ ሕዝባዊ እምብኝተኝነቱ ያመጣውን የተጋድሎ ውጤት ለደርግ ከማስረከብ ተመሳሳይ ኣላማና ፕሮግራም ከነበራቸው ጋር ሰጥቶ በመቀበልና በመቻቻል የተሻለ የሕዝቡን ትግል አቀናጅቶ ለሚመራ አለማስረከብ ራእይ እንዳልነበራቸውና ይዘውት የተነሱት ሕዝባዊ መፈክርም የእነሱ እንዳልነበር በግልጽ ዛሬ ላይ ሆኖ መተቸት ቀላል ነው።
2/ ጠባብነት ፤ ባንዳነት ፤ የመገንጠል አባዜና የቅጥረኝነት ዳንዳ የሆኑ ቡድኖችም እርጉምና እኩይ ተግባራቸውን አንግበው ነውረኝነትን አሳፋሪ ተግባርን በባዕዳን ተክነው የተነሱትም ይህችን በመሪና በፍትሃዊ አስተዳደር የተጎዳች ሀገርን ሕዝብ ለመበታተን ሲያደቡ የከረሙ አስተሳሰበ ድኻዎች ደርግ ወደ ሥልጣን በመጣበት ስሌት የኢትዮጵያ ሕዝብ ደርግ ባደረሰበት ውስጣዊ ብሶትና እንግልት ጅምላ ጭፍጨፋ ምክንያት ከዚህ የከፋ ሊመጣ አይችልም በማለት ታግሎ ካዳከመው በኋላ በሩን ከፍቶ በማስገባቱ በለስ የቀናቸው ደርግን ታግለናልና መቶ አመት መግዛት አለብን ያሉት ሃሳበ ስንኩላን አድማሰ ጠባቦች እንደ አውሬ ከጫካ ከወጡ በኋላ ያለ አስተዳደርና ፖሊስ ራሱን በራሱ ሲመራ የኖረን ሕዝብ እኛ ነን ገዥህ ብለው ሥልጣን ላይ ከወጡ በኋላ ክህሎቱ ስለ አልነበረ በለመዱት የውንብድና እና የጫካ ሕግ እንምራህ በማለት ሲጀምሩ ሀብት ንብረት በመዝረፍ፤ እርስት በመውረስና በማፈናቀል ፤ በማሰርና በመግደል ፤ዘርን በማጽዳትና በማጥፋት ፤ወላዶችን በማምከን በተለይም የጣሊያን አባሽ አጎንባሽ ለባሽና ሹማሽ ልጆች ከወላጆቻቸው እና ከጸረ-ኢትዮጵያ ኋይሎች በወረሱት የፈጠራ ትርክት የትግሬ ጠላት አማራ ነው ብለው አሰልጥነው አደቁነውና አቀሥሰው ከጀርባ ድጋፋቸውን እየለገሱ ስለ አስገቧቸው በአማራው ላይ ናዚዎች በይሁዳውያን ላይ ከፈጸሙት ፋሽስታዊ ጭፍጨፋ ባልተናነሰ አማራውን ጨፍጭፈዋል።
የራሳቸውን ሀገር እንደ ባእዳን አገር በመቁጠር ወረሩ ሀብት ዘረፉ በአንድ ጀምበር ከበሩ ፤ የሀገሪቱን ሀብት ቅርሳቅርሶች ወርቅ የውጭ አገር ገንዘብ ፤ መርከብና አውሮፕላን ሳይቀር ዘረፉ ሀገሪቱን ከቀበሌ እስከ ፌደራል ተብየው ከአንድ አናሳ ብሄር በተሰባሰቡ ቡድኖች የፖለቲካው ፤ የኢኮኖሚውና ማህበራዊ ተቋማቱ ተያዙ ምዝበራው ኢ-ፍትሃዊ አስተዳደር ከጥዋው አልፎ ፈሰሰ ፤ የዜግነት ደረጃ ወጥቶለት ትግሬ አንደኛ ተባለ ሌሎች ሁለተኛ ሆኑ »አማራ የሚባል« ከኢትዮጵያዊ ዜግነት ተፋቀ~ ሀብት ንብረቱ እርስቱ ገቢ ተደረገ~ለምን ብሎ የጠየቀ እጣ ፈንታው እሥራት ሞትና ስደት ብቻ ሆነ**የሰሜን ወሎ እና የሰሜን ጎንደር በርካታ ወረዳዎች ብትግሬ ተነጠቁ**ምዕራብ ጎጃም የመተከል አውራጃ ለቤንሻንጉልና ጉምዝ ስጦታ ተበረክቶ ክልል ተባለ~ውሃ ገብና ለሙ የጎንደር መሬት ከትግሬዎች አልፎ ለሱዳን ውለታ ተከፈለ~በመላ ሀገሪቱ ማናቸውም የንግድና ሥራ እድል ሆዳም አማራ ካልሆነ በሀገር ሠርቶ መብላት የማይቻልበት ጊዜ ደረስን~ሳያፍሩም ሴቶቻችሁንና መሬቱን እንጅ እናንተን(ወንድ አማራዎችን) አንፈልጋችሁም ብለው ነገሩን።
ራያ ኮረም አላማጣ ቆቦ ወልቅይት ጠገዴና ጠለምት ትግሬ ናችሁ ተብለን ተገደድን አማራ ነን ያልን ለቃችሁ ሂዱ ካልሄዳችሁ ወይም ይህን አማራ ነን የምትሉትን ካልተዋችሁ ምርጫችሁ ሞት ነው አሉን ተሰደን በሕይወት የምንገኝ በጣም በአነሰ ቁጥር ነው~እርስታችን ከትግራይና ሱዳን የነበረ የትግሬ ተመላሽ ወገን የሚባል ወርሶታል።እንግዲህ ይህንና የመሳሰሉት አበይት ጉዳዮች ናቸው የ2007 እና ከዚያ በኋላ ከአንደኛው ጫፍ ወደ ሌላኛው ጫፍ እየተቀጣጠለ ሂዶ በመላ ሀገሪቱ አመጽን ወልዶ ሙሉ በሙሉ ሥሩ ባይነቀልም የትግሬ ወያኔ(ትህነግ)ሥርዎ መንግሥት ወደ መቀሌ እንዲከትም ያደረገው። ታዲያ አሁን ምን ተገኘ የሚል ጥያቄ ሲነሳ ከዚህ በታች ያለኝን አስተያየት በአጭሩ ለመስቀመጥ እሞክራለሁ።
3/ ከዚህ ከፍ ብሎ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት **በትህነግ** (የትግሬ ወያኔ) ጨኻኝ አፓርታይድ አገዛዝ በዜግነት ፤ በማንነት አፈና ክፉኛ የተጎዳው አማራው ነው አማራው ደግሞ ከዚህ የባሰ ምን ሊመጣ ይችላል በሚል በጀመረው ማንነቱን የማስከበርና ዜግነቱን እንዲከበርለት ትግሉን ጀመረ ትግሉን ሲጀምር ግን ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ ይሆናሉ ብሎ እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል።ካሳለፋቸው የትግል ልምዶች በቀሰመው እውቀት አደረጃጀቱን **ፋኖ ፤ እና የጎበዝ አለቆችን**መጠሪያ ራሱን አጠናክሮ በመውጣት በመላ ሀገሪቱና በውጭው ዓለምም ወሸኔ ሊባል የሚችል እንቅስቃሴ አድርጎ ሥርአቱን አስጨንቆ ሁለት ጎራ እንዲኖር አድርጓል=- ይኸውም የለየላቸው የሕዝብ ጠላቶችና የሕዝብ ወገን ነኝ የሚሉትን ለይቷል። የሕዝብ ወገን ነኝ የሚሉት ነገር ግን የዚያ ቆሻሻ ሥርዓት ባለመዋሎች የሕዝባዊ ተጋድሎውን እሳት እያሟሟቁ **በሪፎርም ስም** በጡረታና በዘራፊነት በመፈረጅና በተለያዩ ምክንያቶች ወንበር አንለቅም ያሉ ሽማግሌዎችን »የቀን ጅቦች« በማለት ከሥልጣን አግልለው ራሳቸውን ወደ ሥልጣን ማማ አወጡ። አዲሶቹ ሥልጣን ከያዙ እና የያዙትም እንዳሉ **ራሳቸውን** የለውጥ አራማጅ ወይም ሐዋርያ ነን ያሉት በመጀመርያዎች አምስትና ስድስት ወራት ውስጥ በመተዋወቂያ ወቅታቸው ብዙ ቃል ገቡ የተስፋ ዳቦም አስጋመጡን። ጀግኖቹን ያጣ ሕዝብ ግን ለውጡ ሌላ ነውጥ እንደሚያመጣ ትንሽም አልተዘናጋም ነበርና ዛሬም እነዚያን የመብትና የዜግነት የማንነቴ ይታወቅልኝ ጥያቄዎች ከፍ አድርጎ ይዞ ለመታገል ወደ ኋላ የሚል አለመሆኑን አስረግጦ እየተናገረ ነው ስለሆነም ትግሉ ይቀጥላል እንጅ ማን ባቀናው ሀገር ማን ባይተዋር ይሆናል? ሲጀመር ኢትዮጵያ ያለ አማራው አማራው ያለ ኢትዮጵያ እንዴት ብሎ? ኢትዮጵያስ የማን ሀገር ሆነችና ነው አማራው ይጥፋ የተፈረደበት??
ነፍጥ ያነሳም ያላነሳም በውጭ የነበረ የተቃዋሚ ኃይል መቶም ይግደል አንድሽህ በምህረት ይግባ ተባለ ገባ ፤ ሁለት የነበረው የኦርቶዶክሷዊት ቤተክርስትያን ሲኖዶስ አንድ ላይ ሆነ ፤ የእሥልምናም እንዲሁ፤ ብዙ የሕሊና እስረኞችና ጋዜጠኞች ተፈቱ ፤ ዝግ የነበረው የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ተከፈተ(ደጺ)አሁን ዘጋው ሲባል ሰምቻለሁ ፤ከሌሎች የጎረቤት ሀገሮች ጋር መልካም ግንኙነት ተጀመረ ፤በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች እንዲገቡ ተፈቀደ …ወዘተ ይህ አበረታች ነው ሊቀጥል ይገባዋል።ዳሩ ግን የአሁኑን ካቢኔ ወደ ሥልጣን ያመጣው አመጽ የቀሰቀሰው ጥያቄ ሌላ ጦስ ይዞ ሲመጣ ሃይ አለማለት ፤ ሰላምና መረጋጋት አለመኖር ፤ የደፈረሰን ጸጥታ ለመፍታት የሚያስችል አቅም ማጣት አስነዋሪ ነገር ሆኖ እየታየ ነው። ሸክሙን ሲፈሩ መደላድሉን እንዲሉ የመጣ የሄደው አማራውን ሲያይ የልቡ ምት ሲጨምር የኣይኑ ቀለም ሲቀየር ማየት ምን ማለት ይሆን? በተለይ ጠቅላይ ሚንስትር ተብየው »በእንደመር ስም« ሁሉንም አግበስብሶ ሲያስገባ የራሴ የሚለውን ካቢኔ ለማስገባት የራቀውን ለማቅረብ እንጅ እውን ኢትዮጵያዊነት ሲሞቅ የሚወልቅ ሲበርድ የሚደረብ አይደለም ሲል ሊያጃጅለን ማሰቡ ንቀት አይሆንም ወይ? ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው ሲሉን የተኛውን ኢትዮጵያዊነት ይሆን?
ጠቅለል ብሎ ሲታይ የሀገሪቱ ርእሰ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ እየሆነ ያለውና የሚታየው አሳፋሪ ነው አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ ነውና ሀገር ሰላም ሳትሆን መረጋጋት ሳይሰፍን የነበረውን ቁርሾ ይዞ ኢትዮጵያን እመራለሁ ማለት ከንቱ ቅጀት ነው። “የቄሳሩን ለቄሳር” እንዲሉ ማንም ይሁን ማን አማራው ተደራጅቶ በተመጣጣኝ ደረጃ እስካልተገኘ ድረስ ዛሬም ጥርስ እንደተነከሰበት ያለ መሆኑ ቢገባኝም ሌሎችን እንኳን አስማምቸ እገዛለሁ የሚለውን ምናብ አለመያዝ ውድቀትን እንደሚያከፋው ደፍሮ መናገር ይቻላል የሚገርመው ደግሞ ሆዳሙ አማራ ነው ለራሱ ሆድ ካደረ ይሁን ግን ምንም ትርፍ ለማይኖረው ጉዳይ በአማራው ስም መሸቀጥ ብዙ ዋጋ እንደሚያስከፍል መገንዘብ የሚሻ ይመስለኛል።ሰሞኑን በምእራብ ጎንደር የተፈጠረውን ችግር የእለት ክስተት አድርገው የሚያስቡ ሊኖሩ ይችላሉ ይህ የዋህነት ነው።በረከትና አዲሱ መመላለስ ሲያበዙና ጎንደር ላይ ሲከትሙ የማንቂያ ደወል ደውየ ነበር ያኔ እዚህ ግባ ያለው አልነበረም እናም ከላይ እስከ ታች ያለው የመንግሥት መዋቅር በንቃትና እያወቁ የሆነ ነው።
አዲስ አበባን እና ሌላም ለኦሮሞ ይገባል ያሉትን ለማና አብይ ከማድረግ እንደማይመለሱና በዚህ ምክንያት የሚፈጠረውን ሁከትም ወደ ዲክታተርነት(አምባገነንነት) ሽፍት ሊያደርጉት እንዳሰቡም ግልጽ ነው ይህን በውል መገንዘብ ጠቃሚ ይመስለኛል~ለውጡ ከትህነግ ሥርዎ መንግሥት ወደ ኦህዴድ ሥርዎ መንግሥት መሻገሩ ካልሆነ ለውጥ አለ ብሎ አፍን ሞልቶ የሚናገር ቢኖር የአዲሱ ሥርዎ መንግሥት ተስፈኛ ብቻ ነው የሚሆነው~ይህ በዚህ እንዳለ ከትህነግ ጋርም ጠብና ጥላቻ አለመኖሩን የሚያሳዩ ብዙ አመላካች ነገሮች ይታያሉ ምናልባትም የመቀሌውና የአዲስ አበባው እንደ ቅርጫ ሥጋ ላይቀራመቱን ምን ዋስትና አለን?ሁለቱም ግባቸው አንድ ነውና።
የዛሬውን ከዚህ ላብቃ በቀጣይ እንገናኝ
አማራ ተነስ ተደራጅ ተሰባሰብ ምከር መክት ራስህን አድን ልትበላ ነው!!
(አንተ