የዲፕሎማሲው ተግዳሮቶች | ክንፉ አሰፋ

  የሰቆቃውን ምዕራፍ ዘግተን ተስፋ ወደሰነቅንበት ሌላ ምዕራፍ ለመሻገር አንድ ብለን ስንጀምር፤  ከኋላ ጥለናቸው የመጣናቸውን ቅርሻቶች የምንጎትትበት እሳቤ ግልጽ አይደለም።  “በፖለቲካ ድድብና እንደ ስንኩልና አይታይም” የሚለውን የናፖሊዮን ቦናፓርት ምጸታዊ ተረብ የምር አድርገን ካልወሰድነው በስተቀር፤ ሁለተኛ ግዜ ለመሳሳት አንዘጋጅም። መለወጥ ማለት መቀየር ማለት ነው። መቀየር ደግሞ በበጎም ሆነ በክፉ ሊከሰት ይችላል።

https://www.youtube.com/watch?v=rEsGsXV75_k&t=6s

        የውጭ ጉዳይ ፖሊሲውና አሰራሩን በወፍ በረር ስንቃኝ ይህንን ግራጫ ቀለም እናያለን።  በጥቅል ምስሉ ውስጥ የምናየው የአብዮታዊ ዲሞክራሲን ትሩፋቶች ብቻ አይደለም። የንዋይ ምርኮኞች ሆነው በክራር እና በመሰንቆ ሲያጅቡ የነበሩትም፤ የለውጡ ተደማሪ ሆነው ፊት-ለፊት ተሰልፈዋል።

            የአንድ ሃገር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሮኬት ሳይንስ አይደለም። ምስጢረ ስላሴም አይሆንም። የስርዓቱ ርዕዮተ-ዓለም ነጸብራቅ ነው- በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ሲገለጽ። የዲፕሎማሲ ሳይንስ አስተምሮት የሚነግረንም የአንድ ሃገር የውጭ ፖሊሲ የሚቀዳው ከሃገር ውስጥ ፖሊሲ ነው። የውስጥ ፖሊሲ በአለም መድረክ ላይ ሲተገበር የውጭ ፖሊሲ ይሆናል። የህወሃት ምርኩዝ የሆነው አብዮታዊ ዲሞክራሲ ቢያንስ ላለፉት ሩብ ምዕተ አመታት ከሃገር አልፎ በአለም መድረክ ተሰብኳል። ትርክቱ እንደ ሃገር አለምን የምናይበት መነጽር ነበር።  ይህንን የበሰበሰ ርዕዮት ተሸክመው ወደ ውጭ ይላኩ የነበሩ እንደራሴዎችም ቫይረሱን በሌሎች ላይ በማስተላለፍ ረጅም ርቀት ተጉዘዋል።

        ርዕዮቱ ከአፈጣጠሩ በአገር ሉዓላዊነትንና ብሄራዊ ጥቅም ላይ ደንታ አልነበረውም። ዲያስፖራውን በጠላት ከመፈረጅ አልፎ ለዘመናት የተገነባውን ኢትዮዽያውንን ትስስር በመበጣጠስ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። በሃገር ውስጥ እንደሚተገብረው ሁሉ፤ በውጭም ግጭቶች አዋላጅ ነበር።

        ይሾሙ የነበሩ ዲፕሎማቶችም ቢሆኑ፤  ሃገሪቱ ከውጭው ዓለም ጋር ሊኖራት ስለሚገባው ግኑኝነትፍንጭም ሆነ ራዕይ አልነበራቸውም። ዲፕሎማሲው የአኩራፊዎች ግዞት፣ የፓርቲ ጡረተኞች መሾምያና መሸለሚያ ነበር።

        አብዛኞቹ ዲፕሎማቶች ስራቸው ላይ ማጠፍያው የሚያጥራቸው በችሎታ ሳይሆን በውለታ ተመርጠው፡ በተላላኪ ሚና ስለሚሾሙ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አሸባሪዉ ኢህአዴግና የፀረሽብር ህጉ መወገድ አለባቸዉ

        የአንዳንዶቹ ዲፕሎማቶቻችን ተግባር እጅግ ከማሳሰብ አልፎ ይሰቀጥጣል። ጆሯቸው ቢቆረጥ የውጭ ቋንቋ የማይሰሙ ዲፕሎማቶች ገጥመውናል፣ ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ዲፕሎማቶችም ተመልክተናል። የጎረምሶች ክለብ ገብተው በሴት የሚደባደቡ፣ አደንዛዥ እጽ ላይ ተሰማርተው ሃገር ያሰደቡ ዲፕሎማቶች ገጥመውናል። በሰለጠነ አለም ላይ ተቀምጦ ወገኑ ላይ ሽጉጥ የተኮሰ ዲፕሎማትም አጋጥሞናል። ካሰራችሁኝ በኢትዮጵያና በቱርክ መካከል ጦርነት ይነሳል ብሎ የዛተ ዲፕሎማትም በዜና ሰምተናል። ችግሮቹ ብዙ ናቸው። አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት ብለን ቆጥረን የምንዘልቃቸው አይደሉም። ፉክክር በበዛበት ዓለም ኢትዮጵያ ከአለም ዲፕሎማሲ መድረክ ተነጥላ ወደ ኋላ ባትቀር ነበር የሚገርመን።

        የአውራው ፓርቲ ገዢ ሃሳብ በራሱ ምዕራቡን አለም በኒዮ-ሊብራል ይፈርጃል። ህወሃት አለምንየምታይበት ይህ የተንሸዋረረ መነጽር የመዕራቡን አለም ሙሉ በሙሉ ባያገልለውም፤ ጉዳቱ ግን ቀላል አልነበረም። ፖሊሲው ከምዕራቡ አለም ይገኝ የነበረውን ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ ተስኖት ፤የራስ ጥቅምን ብቻ በሚሹ ውስን አገሮች ትኩረት በመስጠቱ አቅጣጫውን ወደ “ዶላር ዲፕሎማሲ” ቀይሮታል። ደቀ መዝሙሮቹም ብሄራዊ ጥቅምን ወዲያ አሉትና ትኩረታቸውን ሁሉ የግል ጥቅም ላይ አደረጉት።

        አሁን የለውጥ ጉዞ ላይ ነን። በዚህ ጉዞ ሂደት የታሰረው ዲፕሎማሲም ይፈታ ካልን መጀመርያ እርምጃ አብዮታዊ ዲሞክራሲን እስከወዲያኛው መሰናበት ግድ ይላል። ርዕዮቱ ማየትና መስማት ተስኖት አርጅቷል።  ውስብስቡን የአለመችን ጉዳይ አጥርቶ የሚመለከትበት አይን የለውም። ሊበራል ኢኮኖሚ ርዕዮትና አዳዲስዓለም አቀፍ ሁነቶችን መስማትም ተስኖታል።

        የለውጥ ሂደቱ አለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኝ ከተፈለገ ደግሞ ምስጢሩ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት እንደሆነ በስፋት ይነገራል። በአሮጌ አቁማዳ አዲስ ወይን ከማኖር ይልቅ አስተሰሳቡን ለአዲሱ ትውልድ ማሳተፍ ላይ ምንም አልተሰራም።

        የዶ/ር ዐብይ አህመድ መንግስት “ጠንካራ ዲፕሎማት ለመፍጠር” በሚል “ጠንካራ” ናቸው ብሎ ከሾማቸው ዲፕሎማቶች መካከል የአሮጌው ስርዓት ካድሬዎች በምን ሂሳብ እንደ እንደተሸነቆሩ ግልጽ አይደለም። 

ተጨማሪ ያንብቡ:  በ1ኪሎ ቁርጥ ሥጋ እና በ12 ድራፍት ብርጭቆ - እውነትና ከሕደት………(ከ ይድነቃቸው ከበደ)

        የአምባደርነቱ ሹመት ልክ እንደ ሚኒስትሮች ሁሉ ከጎሳ ድርጅቶች ጋር በሚደረግ የኮታ ድርድር ከሆነ ቀኝኋላ ዞረናል። እውቁ ኢኮኖሚስት ጆን ኬኔዝ “በካፒታሊዝም ስርዓት ሰውን የሚበዘብዘው ሰው ነው።በኮሚኒዝም ደግሞ ተቃራኒው ነው” እንዳሚለን፤  ተመሳሳይ ግን ውዥንብር አይነቱ አሰራር “ሃገር የማዳን” የሚለው ዋና ጉዳይ ወደጎን በማሽቀንጠር፤ ትርፍን የማወራረድ ፖለቲካ ይመስላል።

        ሀገሪቱ የምሁር መካን የሆነች ይመስል ቢያንስ ለሩብ ምዕተ አመታት በዋና ተዋናይነትም ባይሆን የሎሌ ሚና ተላብሰው ይተውኑ የነበሩትን አምጥቶ ፕ/ር መረራ እንደሚሉት እንደ ገና ጥቅም ላይ ማዋል (ሪሳይክል ማድረግ) ያስፈለገበት ምክንያት ግልጽ አይደለም። 

        አቶ ተሾመ ቶጋካሳ ተክለብርሃን እና ሽፈራው ሽጉጤን ሪሳይክል ማድረግ የተፈለገው በእርግጥ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ዘርፍ እውቀትና ልምድ ያካበተ ባለሙያ አጥታ አይደለም። ይልቁንም ብቃታቸው በተግባር ተፈትኖ ውድቀትን ያስከተሉ ጡረተኞችን ሃላፊነት መስጠት መንግስታዊ ስላቅ ነው።

        አቶ ተሾመ ቶጋ የፓርላማ አፈ-ጉባኤ በነበሩበት ወቅት የተቃዋሚዎችን መብት በማፈን የአድርባይነት ጥግ አሳይተውናል። ሚናቸው ከእልፍኝ አሽከርነት ባያልፍም፤ አምባሳደር ተብለው ረጅም ግዜ ውጭ ተቀምጠዋል። ስራቸውን በቅርብ እንከታተል ከነበርነው በላይ ስለሳቸው የሚመስክር ካለ ላሳር ነው። በዘር አጥር የተከለለ ኤምባሲ ውስጥ ቁጭ ብለው ወገኖችን ከማሰለለ ያለፈ ምን ሰሩ?   ስንት ኩባንያዎችን በኢንቨስትመንት ወደ ኢትዮጵያ አስገብተዋል? የሃገር ውስጥ ምርትን በማስተዋወቅና በመሸጥ ስንትሚሊየን የውጭ ምንዛሪ አስገኝተዋል?  ስንት ቴክኖሎጂዎችን አሸጋግረዋል?

        ሰዎቹ በፈጠሩት መጥፎ ምስል ከፖለቲካ እይታ ሲርቁ እፎይ ብለን ነበር። እነዚህ ሰዎች “ይታሰሩ፣ ተዘቅዝቀው ይሰቀሉ”  አላልንም። ይራቁ ነው። ሰዎቹ የደደቢቱ ማልያቸውን ስለመቀየራቸው የሚያመለክት ምንም ማረጋገጫ የለም። የመደመሩን ሂሳብ አስልተው ኮት መቀየራቸው ግን ግልጽ ነው። አዲስ ተሿሚዎቹ በመሆን እጃቸውን አጣጥበውና ሲመጡ የዲፕሎማት ሞያው አሁንም የጡረተኞች ምሽግ ከመሆን ሊወጣ ያለመቻሉ ያመለክተናል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ይህ ስርዓት በፍጹም አይድንም

        የውጪ ግንኙነት ስህተት የሚጀምረው እኛ የውጩን አለም የምናይበት እና ውጩ አለም ደግሞ የእኛንውስጥ የሚመለከትበትን መስመር አጥርቶ ካለማውቅ ብቻ አይደለም። እኛን ይወክላሉ የምንላቸው ሰዎች መልካም ስነ ምግባር፣ ችሎታና እውቀት ትልቅ ስፍራ ሊሰጠው ይገባል። ሪፎርም ይደረግ ከተባለ ደግሞ የዲፕሎማቶች ሹመት መመዘን የሚገባው በታማኝነትና በመደመር ስሌት መሆን የለበትም።

         ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በለውጡ ውስጥ ማሳተፍ ከተፈለገ የዲፕሎማሲውን መንገድ ከዚህ አንጻር መፈተሹ ወሳኝ ነው። ዲያስፖራ ተሳትፎ ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ ለማወቅ ፊሊፒንስን እንደ ናሙና መውሰድ ይቻላል። ፊሊፒንስ በምትከተለው ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ፣  አስራአራት በመቶ የሚሆነውን የሃገር ውስጥ ገቢ የሚሸፍነው ዲያስፖራው ነው። ከዲያስፖራው የሚገኘውየውጭ ምንዛሪ በአለም አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ከህንድ፣ ቻይና እና ሜክስኮ ቀጥሎ ማለት ነው።

        የውጭ ምንዛር ችግር እንደ ግመል የገዘፈባት ሃገር፤ ለዲፕሎማቲክ ሚሽን ወጪዎችን መሸፈን ፈተናመሆኑ አዲስ ነገር አይሆንም። ኢትዮጵያ ውጭ ካሏት 44 ኤምባሲዎችና 48 ቆንስላ ጽ/ቤቶች  መቀነስ እና ማሸጋሸግ ሲገባት ሌሎችን መጨመርዋ ችግሩን ያብሰዋል።

        ዲያስፖራው ገንዘብ እውቀት እና ቴክኖሎጂዎች በማሻገር ረገድ አምባሳደሮቹ የበለጠ ቀረቤታ፣ እውቀትና ችሎታ አለው። ፖሊሲው ቀለም አልባ እና አሳታፊ እንዲሆን ከተፈለገ፤ የመደመር ካርድ መዝዞ በአሮጌው ከመጫወት ይልቅ አዲስ አስተሳሰብ አዲስ ሃይል ማሳተፍ ነው መፍትሄው።

        አለምን እያቀራረበ ካለው ግሎባላይዜሽን አብሮ የማይሄ፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን ከለት ተለት ተግባሩ ማዋሃድ ያልቻለ ዲፕሎማት ሸክም ብቻ ከመሆን አያልፍም። የሳይበሩ አለም በአለም አቀፍ ግንኙነቱ ላይየሚኖረው ተጽእኖ ብዙ ትኩረት አልተሰጠውም።

        ትኩረት ቢሰጠው ኖሮ፤ ከዚህ ቀደም ሲሰልሉት የነበሩ ካድሬዎች ኮት ቀይረው አይመጡበትም ነበር። የትረስት ፈንዱ የኤሊ ጉዞ ምስጢርም ይኸው ነው። ጥርጣሬ!

1 Comment

Comments are closed.

Share