የሲዳማ ዞን እና የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የሰመጉን ሪፖርት ተአማኒነት የለውም አሉ

የሲዳማ ዞን ባህል ቱርዝምና የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መ ምሪያ እና የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ባህል, ቱርዝም የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ:  የሰብአዊ መብቶች ጉባዔ (ሰመጉ) ታህሳስ 24 ቀን 2011 ዓ.ም 146ኛ ልዩ መግለጫ “በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈፀመው የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች” በሚል ሥር ስለ ሀዋሳና ሲዳማ አስመልክቶ ባሠፈረው ሪፖርት ላይ  ምላሽ ሰጥተው;  ሪፖርቱ “የሲዳማ ወጣቶች” ድርጊቱን ፈፀሙት በሚል በጅምላ የፈረጀበት አግባብ ፈጽሞ የተሳሳተ ነው ብለውታል::

https://youtu.be/J8BZqY2t65c

“የተወሰኑ ግለሰቦች የፈፀሙትን ጥፋት በማሳበብ አጠቃላይ በሚሊዮን የሚቆጠረውን የሲዳማን ወጣት መፈረጅ በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የለውም። የሲዳማ ወጣት እንደ ማንኛውም ሀገራችን ወጣቶች የለውጥ ደጋፊ ኃይል እንጂ የጥፋት ኃይል አይደለም።” ያለው ምላሹ “.የምርመራው ውጤት በአመዛኙ ገለልተኛ አካል ሳያካትት በግለሰቦች አቤቱታ ላይ ብቻ የተመሠረተ መሆኑ የሪፖርቱ ተዓማኒነት ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። ከዚህም ባሻገር ተቋሙ የምርመራውን ሥራ በጥራትና በብቃት ለማከናወን የሰው ኃይል፣ የገንዘብና የምርመራ ቁሳቁስ አቅም ውስንነት እንዳለበት በመግቢያ ላይ አስቀምጦ ሲያበቃ በሪፖርቱ ላይ የግለሰቦችን አቤቱታ ብቻ ዋቢ በማድረግ ገለልተኛ አካል ሳያካትት ያቀረበው መረጃ እጅግ የተጋነነና ተዓማኒነት የሚጎድለው ነው።” ብሎታል::

“የሟቾች ብዛትና ማንነት በተመለከተ” ሰመጉ ያወጣውን ሪፖርት የተቃወመው መግለጫው “በዚህ ሰነድ ላይ በጉጂ ኦሮሞና በጌዴኦ በተፈጠረው ግጭት የሟቾች ቁጥርና ብሔር በሠንጠረዥ አስደግፎ የገለፀ ቢሆንም የሀዋሳን ግጭት በተመለከተ ግን ሠንጠረዥ 5 ላይ በዝርዝር አላቀረበም። በግጭቱ ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች ከአንድ ወገን ብቻ እንደሆነ አድርጎ አቅርቧል። ይህ ስህተት ነው። ለአብነት ከቁጥር 14-18 የተጠቀሱት ሟቾች በሻማና ቀዲዳ ገበያ ላይ የወላይታ ተወላጅ በሆነው ግለሰብ የእጅ ቦንብ ተወርውሮ በአሠቃቂ ሁኔታ ሕይወታቸውን ያጡ የሲዳማ ተወላጆች ናቸው። እንዲሁም ደግሞ በዚሁ ሠንጠረዥ በቁጥር 5&7 የተጠቀሱና ሕይወታቸውን ያጡ ወጣቶች የሲዳማ ብሔር ተወላጆች ሲሆኑ ተቋሙ በጅምላ ማቅረቡ ግርታን የሚፈጥር ነው።” ብሎታል::

ተጨማሪ ያንብቡ:  የመሬት ሽያጭ ለልማት ወይንስ ለአገር ጉዳት?

“በሰብአዊ መብት ጉባዔ (ሰማጉ) የቀረበው 146ኛ ልዩ መግለጫው ገለልተኛና ተኣማኒነት የለሌውና ሪፖርቱን በማስረጃ ሳያስደግፍ ያቀረበ በመሆኑ ለቀጣይ ግጭት የሚቀሰቅስ ፣ ጥላቻን የሚፈጥርና ሰላምን ለማደፍረስ የተሠራ ሤራ በመሆኑ በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የለውም።” ሲል በዛሬው መግለጫ ላይ ተገልጿል::

Share