የሕወሓቱ ሱር ኮንስትራክሽን ግየንባታ ማሽነሪዎችን የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች በባህርዳርና ጎንደር ታገቱ

ንብረትነታቸው  የሱር ኮንስትራክሽን ድርጅት የሆኑ የግንባታ ማሽነሪዎችን የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች ከትናንት ጀምሮ በባህርዳርና በጎንደር ከተሞች ታግተዋል።

በምዕራብ ጎንደር በመንገድ ስራ ላይ የተሰማራው  የህወሓቱ ሱር ኮንስትራክሽን  በአካባቢው ለሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች የጦር መሳሪያ ያጓጉዛል የሚል ስሞታ ከቀረበበት በኅላ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቱን አቋርጦ በመውጣት ላይ ነበር።

https://www.youtube.com/watch?v=yJGl1PI8qiY

ከሶስት ሳምንት በፊት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ባወጣው መግለጫ)  “የአሸባሪው የትግራይ ሕዝብ ነፃነት ግንባር/ሕወኃት ንብረት የሆነው ሱር ኮንስትራክሽን ኃብቱ ተወርሶ ፈቃዱ እንዲሰረዝ ይጠይቃል።” ሲል ጠይቆ ነበር::

በዚሁ መግለጫ አብን “በመንገድ ሥራ ሽፋን በሰሜን ምዕራብ አማራ ተሰማርቶ የሚገኘው ሱር ኮንስትራክሽን ድርጅት ራሳቸውን «የቅማንት ኮሚቴ» እያሉ ለሚጠሩ ለጥፋት ኃይሎች የትጥቅና ትራንስፖርት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ደርሰንበታል። ይህ ድርጅት ለግንባታ ሥራ በሚጠቀምባቸው ቦቴዎችና የኮንስትራክሽን መኪናዎች እያጓጓዘ ለእነዚህ የጥፋት ኃይሎች ባቀበላቸው ከባድ የጦር መሣሪያዎችና ተቀጣጣይ ፈንጂዎች በሕዝባችን ላይ ከፍተኛ የሕይወት መጥፋትና ንብረት ውድመት ደርሷል።” ሲል ክሱን በመግለጫው አቅርቦ ነበር::

‘ስለሆነም” አለ አብን “ስለሆነም “ሱር ኮንስትራክሽን ከተቋቋመበት ዓላማ ውጭ ተሰማርቶ በመገኘቱ፤ በኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ መሰረት፤ ድርጅቱና የሥራ ኃላፊዎቹ በሕግ እንዲጠየቁ፤ ላደረሰው በደል ካሳ እንዲከፍል፣ ኃብትና ንብረቱ እንዲወረስ እንዲሁም ፈቃዱ እንዲሰረዝ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ይጠይቃል።”

በሕወሓት እስር ቤቶች ሲሰቃይ የነበረው የቀድሞው የአየር ኃይል ባልደረባ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ በበኩሉ “ሱር ያለፉትን ሁለትና ሶስት አመታት የህወሃትን ድብቅ ተልእኮ ሲፈጽም የቆዬ ድርጅት መሆኑን ሰሞኑን በተከታታይ ለህዝብ ስናሳውቅ ቆይተናል።

ይህ ተልእኮው በፋኖዎቻችን ሲጋለጥ የራሱን ካምፕ (መረጃዎችን) በማቃጠል የአማራን ህዝብ ተጠያቂ አድርጓል። ሌላው ስራው የቅማንት ኮሚቴ ነኝ የሚለውን የህወሃት ክንፍ ሲያሰለጥንና ሲያስታጥቅ እንደቆየ ሙሉ መረጃ አለን (አስፈላጊ ከሆነ ቃለ ምልልሱን ማያያዝ እንችላለን)።ይህንን ድርጊቱን መከታተል ስንጀምር በራሱ ፍላጎት ስራውን በማቆም ከክልሉ መንግስት ጋርም ሆነ ከሚመለከተው አካል ጋር ምንም አይነት ውይይት ሳያደርግ እቃ ማጓጓዝ ጀምሯል። ትናንትና እና ዛሬ ብቻ ከ18 በላይ ማሽነሪ የጫኑ መኪናዎች በጎንደርና በባህርዳር በፋኖዎቻችን እንዲቆሙ ተደርጓል:: ከዚህም በላይ ህገወጥ ተግባሩን ከቀጠለበት ለሚደርሰው ኪሳራ ሃላፊነቱን ይወስዳል። በመጨረሻም በጠፋው የሰው ህይወት፣ በጎደለው የፋኖዎቻችን አካል እና በህዝባችን ንብረት ካሳ ሳይከፍልና ይቅርታ ሳይጠይቅ ንብረት ማንቀሳቀስ የማይችል መሆኑን ማሳወቅ እንወዳለን። ምንም ቢደረግ ከያዝነው ትግል ለደቂቃ የሚያቆመን አይኖርም።” ብሏል::

ተጨማሪ ያንብቡ:  የታሰሩት ባለስልጣናት እና ነጋዴዎች ስም ዝርዝር (ይዘናል)
Share