በቤኒሻንጉል ጉሙዝና አካባቢው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታወጀ፣ | ኮማንድ ፖስት ተቋቁሟል

በቤኒሻንጉልና በኦሮሚያ ክልሎች አጎራባች አካባቢዎች ባለፉት ሦስት ወራት በተከሰተ የጸጥታ ችግር ከ100 በላይ ሰዎች ሲሞቱ፣ በ10 ሺህ የሚቀጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡ ይህ ችግር ከእለት ወደእለት እየተባባሰ ከመምጣቱም በላይ በትላንትናው እለት በህዝብ ትራንስፖርት ሚኒባስ ላይ ቦምብ ፈንድቶ በርካታ ዜጎች ለህልፈት መዳረጋቸውን ዘግበናል፡፡ በዛሬው እለት ችግሩን ለመቅረፍ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ አካባቢውን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስተዳደር እንደተጀመረ ሰምተናል፡፡ ኮማንድ ፖስቱ ከፌደራልና ከሁለቱ ክልሎች መንግሥታት፣ የአገር መከላከያ ሠራዊትና ፌዴራል ፖሊስ የተዋቀረ ሲሆን በአካባቢው የመሸገውን የታጠቀ ኃይል ለመቆጣጠር መቀመጫውን በአሶሳ ከተማ አድርጎ ከሱዳን የጸጥታ ኃይሎች ተባብሮ እንደሚሰራ ለመረዳት ችለናል፡፡ በአካባቢው ጥቃት የሚፈፅመው ሃይል ማንነት እስካሁን በውል ያልታወቀ ሲሆን የቤኒሻንጉል ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ሰይፈዲን በክልሉ የተሰማራው የታጠቀ ኃይል የክልሎቹን ሕዝቦች እንቅስቃሴ ከመገደብ ጀምሮ ያለልዩነት ጥፋት ሲፈጽም እንደነበር ዛሬ በሰጡት መግለጫ አስታውሰዋል።

ይህ የታጠቀ ኃይል በአቋራጭ ሥልጣን የመያዝ ፍላጎት ያለውና ኪራይ ሰብሳቢ እንደሆነ የገለጹት የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት አባል የሆኑት አቶ ሰይፈዲን ሲናገሩ ‹‹ዋነኛ ዓላማውም አገራዊ ለውጡን ማደናቀፍ ነው፡፡ ታጣቂው ኃይል

 ከየትኛውም ብሔርና የፖለቲካ ድርጅት ግንኙነት እንደሌለውም ተደርሶበታል›› ብለዋል፡፡ 

ሕዝብና መንግሥት የጥፋት ኃይሉ ወደ ሠላማዊ መንገድን ይመለሳል በሚል ለወራት በትዕግስት መጠበቃቸውን ያስታወሱት አቶ ሰይፈዲን፣ የጥፋት ኃይሉ በድርጊቱ እንዳይቀጥል ኮማንድ ፖስቱ መቋቋሙን አስታውቀዋል። በበጀት፣ በቁሳቁስና በሌሎች ሎጂስቲክሶች የተደራጀው ኮማንድ ፖስት፣ በአጭር ጊዜ የአካባቢውን ጸጥታ ወደ ነበረበት ለመመለስ እንደሚሰራና ሕገ-መንግሥቱን መሠረት በማድረግ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሳይፈም ሥራውን እንደሚያከናውን አስታውቀዋል፡፡ በዚህ መሰረት በካማሽና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች በሚገኙ አዋሳኝ በ25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከተፈቀደላቸው የጸጥታ ኃይሎች በስተቀር የጦር መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስ የማይቻልበት ቀይ መስመር አድርጎ እንደተወሰነ ገልጸዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሸንጎ 2ኛውን መደበኛ ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቁን ገለጸ

https://www.youtube.com/watch?v=HYrXgK5KjTY

Share