ታሪካዊው የቴዲ አፍሮ ኮንሰርት በአዲስ አበባ ተካሄደ

/

_

ላለፉት 5 ዓመታት በአዲስ አበባ ምንም ዓይነት ኮንሰርቶች እንዳያካሂድ በተለያዩ ምክንያቶች ሲታገድ የቆየው ቴዲ አፍሮ በትናንትናው ዕለት በአዲሱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተሰጠው ፈቃድ በሚሊኒየም አዳራሽ አካሄደ:: 25 ሺህ ሕዝብ የታደመበት ይኸው ኮንሰርት ታሪካዊ ሆኖ ማለፉን በኮንሰርቱ የታደሙ ወገኖች ገልጸዋል::

በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ አንድ ዘፋኝ ለብቻው የሙዚቃ ኮንሰርት አዘጋጅቶ 25 ሺህ ሰው ገብቶለት አያውቅም; የቴዲ ግን ልዩ ነው የሚሉት ታዳሚዎች አምስት እና ስድስት ዘፋኞች ሆነው እንኳን ኮንሰርት ቢያዘጋጁ ይህን ያህል ታዳሚ እንደማያገኙ ይናገራሉ::

ከአምስት ዓመት በኋላ ኮንሰርቱ ተፈቅዶለት ለማከናወን የቻለው ቴዲ አፍሮ ሕዝቡ በት ዕግስት እስከዛች ዕለት ድረስ ስለጠበቀው ምስጋናውን አቅርቧል::

በሕወሓት የአገዛዝ ዘመን እንዳይዘፈን ተከልክሎ የነበረው ጃ ያስተሰርያል ዘፈንንም ቴዲና ሕዝቡ በጋራ አቀንቅነውታል::

ኮንሰርቱን ከታደሙት መካከል ዳግማዊ የተባሉ ግለሰብ ያቀረቡትን አጭር ዘገባ እንደሚለተለው እናቀርበዋለን::

11 ሰአት አካባቢ ነበር ወደ ሚሊኒየም አዳራሽ የገባሁት! ከዋናው አስፓልት ጀምሮ አዳራሽ ውስጥ እስክንገባ ድረስ አራት ግዜ ተፈትሸናል!

ፍተሻውን አልፈን አዳራሽ ውስጥ ከገባን በኋላ ህዝቡ በዲጄው በሚከፈቱ ሙዚቃዎች እየተዝናና እና እየጨፈረ መጠበቅ ጀመረ! በመሀል ውሀ ለመግዛት ከጓደኞቼ ጋር ተያይዘን የሄድን ሲሆን ባልጠበቅነው መልኩ ግማሽ ሊትር የታሸገ ውሀ በሀያ አምስት ብር ሲሸጥ ተመልክተናል! እኛም በዛ ዋጋ ለመግዛት ተገደናል!

ሶስት ሰአት አካባቢ ይመስለኛል የአቦጊዳ ባንድ አባላት ወደ መድረኩ በመውጣት ቦታ ቦታቸውን ይዘው ቆሙ። ብዙም ሳይቆይ ታዳሚው ሁሉ በጉጉት ሲጠብቀው የነበረው ቴዲ አፍሮ መድረክ ላይ ተከሰተ! በዛች ቅፅበት ህዝቡ ቴዲን ለማየት የነበረው ግፊያና መንጠራራት ይሄ ነው ብሎ ለመግለፅ እጅግ እጅግ ከባድ ነበር!

ቴዲ አፍሮ ጥቁር ሆኖ ወርቃማ ጥለት ነገር ያለው ቲሸርት ለብሶ አንገቱ ላይ ረዘም ያለች ቀጭን የወርቅ መስቀል አድርጎ “ኦ አፍሪካ” የተሰኘውን ሙዚቃ እየተጫወ ወደ መድረኩ ብቅ አለ! ሚሊኒየም አዳራሽ ከአቅሙ በላይ እስኪሆን ድረስ በጩኸት ተደበላለቀ!

ሁሉም ነገር ልዩ ነበር! ብላቴናው በጥቁር ሰው እምዬን አወደሰ… ኢትዮጵያን አዚሞ አዳራሹን አናወጠው!
ካሳ ካሳ የቋራው አንበሳ
ዳኘን ዳኘን አንድ ህልም አሳየን!… እያለ ታዳሚውን በቁጭት ልጓም ይዞት ወደኋላ ሸመጠጠ! አዳራሹን ከዛ አፄ ቴዎድሮስ ከተባለ የአንድነት መንፈስ ጋር አላተመው!

ጃ ያስተሰርያል ሲል ዛሬም ይቅር ተባባሉ ሲል አዜመ! በፊዮሪና አስመራ ላይ ተክዘን! ቀላል ይሆናል… አነኛቱ… ሔዋን እንደዋዛ… አቦጊዳ… ማራኪዬ… ሰንበሬ… ሼመንደፈር… ግርማዊነቶ… ሁሉም በቅደም ተከተላቸው እንደ ወንዝ ፈሰሱ!

ቴዲ አፍሮ ለባንድ አባላቶቹ የሚያሳየው ክብር እጅግ አስገራሚ ነበር! ቴዲ ቴዲ እያለ ለሚዘፍነው ህዝብም “ማርያምን እወዳችኋለው” ሲል አፀፋውን መልሷል! ከምሽቱ 6:40 ይመስለኛል የዝግጅቱ ማሳረጊያ ሆነ! ቴዲ በቀኝ በመሀል እና በግራ በኩል እየሄደ ጎንበስ በማለት ህዝቡን በክብር ተሰናበተ! የቴዲን ማናጀር ጨምሮ የአቦጊዳ ባንድ አባላትም መድረክ ላይ ተሰብስበው ጎንበስ በማለት እጅ ነሱ!

ምሽቱ እንዲህ አለቀ! እጅግ አስገራሚ የድምፅ ጥራት… እጅግ ድንቅ የመብራት ቅንብር… ህዝቡና ብላቴናው በአስገራሚ ሁኔታ የተናበቡበት ታሪካዊ እለት ነበር!
https://www.youtube.com/watch?v=urrQCDkbbQE&t=489s

ተጨማሪ ያንብቡ:  ድምፃዊት አስቴር ከበደ - ከ25 ዓመት በኋላም ዝናዋ ናኝቷል
Share