“ ስጋት የተላበሰው ተስፋ” – ከገዙ በቀለ (ዶ/ር)

ሁለት በጣም የሚጣረሱ ቃላት ጎን ለጎን ማስፈሬ ብቻ ሳይሆን አብረው እንዲጎዳኙ በማድረጌ እብዱ እንዳያሰኘኝ እሰጋለሁ።ስጋት ቁርሴ፣ ምሣዬና እራቴ መሆን ከጀመረ  ከራርሟል፤ ስለሆነም ገና ከጀምሩ አትፍረዱብኝ።  ነገሩ የሚያስደምም አይደለም፤ግርምትም አያስከትልም፤ በርታም አያሰኝም።የሁለቱም ቃላት ፍቺ የሰማይ ርቀት ያህል አንዱ ከሌላውጋር ሲተያይ በእጅጉ ይለያያል። በሰው እለት ተእለት ኑሮ ውስጥ ለስጋት መንሰኤ የሚሆኑ አያሌ ምክንያቶች ለመኖራቸው በመስኩ የተሰማሩ ምሁራን ይገልጻሉ።የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ምክንያቶች ብሎም በዋናነት መመደብ ይቻል ይሆናል።በእነዚህ ዐቢይ ርዕሳነ ጉዳዮችም ሥር ዘርፈ ብዙ ንዑሳን ጉዳዮችን እንዳሉም ይታወቃል።ታዲያ ተስፋ ከስጋት ጋር ምን ቁርኝት አለው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። መልሱን በትክክል አውቄ የማልመልሰው አገራችን ያለችበት ሁኔታ ግርዶሽ ስለሆነብኝ ነው። አገራችንና ሕዝቧ መቼም ቢሆን ስጋት ፈጥረብኝ አያውቁም። ክሩ ፣ አብሮ የሚኖር፣ የሚተጋገዝ ሕዝብ ነው። ጫንቃው ላይ ቁጢጥ ያሉት ግን የዛሬውና የነገውን ተስፋውን ዘወትር  ሊያጨልሙበት ይፈልጋሉ።ስጋቴ እንዳለ ቢሆንም በቅርቡ በአገራችን የታየው የፖሊቲካ ድባብ ተስፋ ሰጪ ነው።

ተስፋ ለሰው ልጅ ከእግዚአብሔር የተሰጠ ልዩ በረከት ነው። ስለሆነም መብትም ጭምር ነው።ትዕይንተ ሕዝብ ማድረግ፤ መሰብሰብ፣ ሃሳብን በነጻነት መግለጽ፣ መጻፍ ለሰው ልጅ ከፈጣሪው የተሰጠው ነው። እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥረው ሙሉ ፍቃድ እንዲኖረው አድርጎ ነው። እምቢና እሽታን ክማንም ሊለገሰው አይገባም፤ አብሮት የተፈጠረ ነው። ሰው በሕይወት ዘመኑ ተስፋ ባያደርግ ኖሮ ጥልመት የሞላው የሰቆቃ ኑሮ እንዲኖር የተፈረደበት ያህል ነው። ተስፋ ለሰው ልጅ ከመሠረታዊ ፍላጎቶች ቀጥሎ ወሳኝ ሚና እንዳለው ይታመናል።ክግል  እስከ ማህበረሰብ የሚደርስ ተስፋ መኖሩን ግልጽ ነው።ይበልጡንም የሥነ አእምሮ ሊቃውንት ብዙ ሊሉበት ይችላሉ። ለዲሞክራሲ መብት ታግለው በእስር ለማቀቁ ወገኖች፣ ተስፋ ሰጪ የጭላጭል ቃል  ቢሱማና ቢያዩ፣ ተስፋው የምሉእ ማህበረሰቡ ይሆናል። አንድም የፖለቲካ እስረኛ የለም በተባለላት አገር በብዙ ሺህ እስረኞች ሲለቀቁ ማየት ጉድ እኮ ነው ያሰኛል።የፖለቲካ እስረኞች መፈታታቸው ደስታው ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ እንዲናኝ አድርጎታል።ሕዝቡ አፍ የሆኑለትን እስረኞች ሲፈቱለት ለመቀበል አዳባባይ ወጣ፤ ሆ ብሎም ተቀበላቸው። ችግሩ ግን ነባሮቹ እስረኞች ሲለቁቁ አዳዲሶች ዘብጥያ መውረዳችው ሂደቱን አስቂኝ ያደርገዋል። ዛሬም በመታደን ላይ ያሉት ወጣቶች ሕያው ምስክር ናቸው።ለዚያውስ ገና መቼ ሁሉም እስረኞች ከእስር ተፈቱ!! አንዳንዶች እንደሚሉት እንዲያውስ አገሬው ሁሉ እስር ቤት አይደል ያለው! ከቀዬው የተፈናቀለው የኦሮም ሕዝብ፣ በልማት ስም ቤት ንብረቱን ያለ ካሣ ያጣው ዜጋ ቤት ይቁጥረው።የጥቂት ዲታዎች ፍላጎት ለሟሟላት ሲባል ቤቱንና ንብረቱን በትንሽ ገንዝብ የተነጠቀውና ተገዶም የተፈናቀለው ሕዝብ ምሬቱን በእንባ ጭምር ሲገለጽ ማየቱ ምንኛ ያሳዝናል። የምጣኔ ኃብቱ ዕድገት በሁለት አኃዝ ጎሞራ በሚባልበት አገር የድሃው ብዛት ቁጥር ስፍር የለውም። የሕንጻ ብዛት፣ የመዝናኛ ስፋራ መበራከትና ሌላ ሌላውም የማህበረሰቡን የእለት ኑሮ ካልለወጠ ጥቅሙ ምን ይሆን? በደዌና በበሽታ የሚማቅቀው፤ በውሃ አቅርቦት ችግር የሚገላታው፤ በኑሮ መጋሸብ የተነሣ የሚበላው ኩርማን እንጀራ ያጣው ሕዝባችን የልማት እድገታችን ጣራ ነክቱዋል ቢባል ለእርሱ ምኑ ነው።ምግብ ማብሰያ ያጣውና መብራት የተነፈገው ምስኪን ሕዝብ እድገት አለ ቢሉት ጆሮ ዳብ ልብስ ማለቱ የት ይቀራል። የማህብረሰቡን ኑሮ የማያሻሻል ዕድገት እርባና የለውም፤ ፋይዳውም ይህ ነው ማለት አይቻልም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኦኖሌ፡-ሀርከ-ሙራ

ብሩህ ተስፋ ከቅርብ ዓመታት የታየው ቄሮው፣ ፋኖው ብሎም ክልጅ እስከ አዋቂ ሳይቀር በነቂስ ሕዝቡ ያለውን ሥርዐት አሻፈረኝ በማለቱ ነው።በአገርና በውጭ ያሉትን ታዛቢዎችን ቀልብ የሳበው ሕዝባዊ እምቢተኝነት አልደፈርም ባዩን መንግሥት ተሸክሞት ይዞር የነበረውን የፖለቲካ አንቀልባ  ባዶ መሆኑን  አሳይቶበታል።መንግሥት በፖለቲካው መስክ ተበልጡዋል፤ እንደ ቀድሞው ላሞኛችሁ የሚልበት ዘዴውም አብቅቱዋል። ዛሬ ወዳጆች ሳይቀሩ እየተቃወሙት ይገኛሉ። አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ሲዊድንና የአውሮጳ ማህበረሰብ አስችኳይ ጊዜያዊ አዋጁን በጽኑ ተቃወሙታል።በዚህም የተነሳ ገዥው ፓርቲ በሥልጣን ላይ ለመቆየት ወታደራዊ አገዛዝ መምረጡ ላይገርም ይችል ይሆናል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ በፈለጉ ማግስት አስቸኳይ አዋጅ ለምን እንዳስፈለገ ጥልቅ ምርምር የሚያስፈልገው አይደለም። የለውጥ ሂደቱን የሚቃወሙ ወገኖች ይህ መንገድ መምረጣቸውን ታሳቢ ማድረግ ይቻላል።ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ነበራቸው ወይ? ወደው ለቀቁ ወይስ ተገደው? የእሳቸው ሥልጣን መልቀቅ ምን አንደምታ አለው? ይህ መንግሥት ዛሬም በማን የሚዘወረው? የሚሉት ጥያቄዎች አነጋጋሪ ሆኑ። ማህበረሰቡ ይህን በማውጣትና በማውረድ ላይ ሳለ፣ ጊዜዊ አስቸኳይ አዋጅ ታወጀ።ብሩህ ተስፋ እንዲጨልም ተሞከረ። አገሪቷ በወታደራዊ አስተዳደር ሥር ወደቀች።  በተስፋ ግለት የጦዘውን ሕዝብ መልሶ እንዲቀዘቅዝ ዶፍ ቸለሱበት።በሰላም ለውጥ ለማምጣት የነበረውን ተስፋ ቀነሰው።ይሁን እንጂ ሕዝቡና አንዳንድ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉ ለውጥ ፈላጊ ወገኖች የሰላማዊ ትግሉን ቸል ሊሉት የሚገባ አይመስለኝም። የለውጥ ጉዞው መራራ ቢሆንም፣ አንዳችም ኃይል ከሕዝብ ሊበልጥ አይችልም። ስለዚህ ምንም ያህል ስጋት ቢኖር፣ የድል ተስፋ ግን በማማው ላይ ከፍ ብሎ ይታያል።

 

 

 

 

Share