ሙስሊም ወጣቶች ከደቡብ ወሎ እየተሰደዱ ነው

(ፍኖተ ነፃነት ኒውስሌተር) በደቡብ ወሎ ወረባቡ ወረዳ በኃይማኖት ሰበብ በርካታ ወጣቶች እየታሰሩ በመሆኑ ብዙዎች ከኢትዮጵያ እንዲሰደዱ እንደሆነ የጥቃቱ ሰለባ ወጣቶች በተለይ ለፍኖተ ነፃነት ገለፁ፡፡ በተለይ ከሙስሊሙ የኃይማኖት ነፃነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የአካባቢው የእስልምና ኃይማኖት ተከታይ ወጣቶች ያለምክንያት እየታሰሩ በዋስ
እንደሚለቀቁም ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡
የመንግስትን እስርና እንግልት ሸሽተው ከሚሰደዱ ወጣቶች መካከል የወሎ ዩኒቨርስቲ ተመራቂ ተማሪም እንደሚገኝበት ተገለፀ ሲሆን ከሀገር ተሰደው የመን ከገቡት መካከል የወሎ ዩኒቨርስቲ 4ኛ ዓመት ተማሪ እና የአንድነት ፓርቲ አባል ወጣት አሊ ሰይድ የመን በሚገኙ አጋቾች ታግቶ እንደሚገኝ ምንጮቻችን በተለይ ለፍኖተ ነፃነት ገልፀዋል፡፡
ሌላው ወጣት ከድር መሐመድ በወረባቡ በሚገኝ መስጂድ ለፀሎትና ስግደት ቢሄድም በመስጂዱ ውስጥ የኮሚቴው ተጠሪ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሼህ “እጅህን ስጥ” በሚል ተኩስ ከፍተውበት ጉዳት ሳይደርስበት እንዳመለጠም ተጠቁሟል፡፡
በዚህም ምክንያት የወጣት ከድር መሐመድ እናትና አባት ታስረው በዋስ እንደተለቀቁ ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ የአካባቢው የአንድነት ፓርቲ አባል ወጣት ሰለሞን ፀጋዬም ታስሮ በ 5,000 ብር ዋስ ተለቋል፡፡ ይህን እስከዘገብንበት ሰዓት ድረስም በርካታ የአካባቢው ወጣቶች የተሰወሩ ሲሆን ከነዚህ መካከልም
– ወጣት ከካሊድ ተስፋዬ፣
– ሙስጠፋ ዑመር፣
– ሀቢብ ኢብራሂም፣
– ቢላል አየለ፣
– አብዱራህማን ማህሙድ፣
– መሐመድ አብዶ፣
– ከድር እንድሪስ፣
– በድሩ፣ አብዱልከሪም የት እንዳሉ አይታወቅም፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የወረዳው ፖሊስ ኢንስፔክተር መስፍን እኔ ታምሜ እቤት ተኝቻለሁ፣ ጉዳዩ ገና በምርመራ ላይ ያለ በመሆኑ ከእኔ ሌላ የሚተባበርህ ሰው ልሰጣችሁ አልችልም፤ ከፈለጋችሁ በሌላ ጊዜ በአካል መጥታችሁ ዝርዝር መረጃውን መውሰድ ትችላላችሁ ሲሉ ምላሽ ሰጥተውናል፡፡ (ምንጭ ፍኖተ ነፃነት ኒውስሌተር)

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአማራ ወጣት ቅድምያ መከላከያን ተቀላቀል!! = ቹቹ አለባቸው
Share