ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ታሰሩ

አንድነት የፊታችን እሁድ ለሚያደርገው ሰላማዊ ሰልፍ መቀስቀሱን፤ ኢሕአዴግ ማሰሩን ቀጥለዋል

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት እና የአሁኑ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ(አንድነት) ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ መታሰራቸውን ብስራት ወልደሚካኤል ከአዲስ አበባ አዘገበ፡ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ መታሰራቸው የተገለጸው ዛሬ መስከረም 15 ቀን 2006ዓ.ም. ሲሆን ዘ-ሐበሻ ወደ አንድነት ጽህፈት ቤት ደውላ “ዛሬ እስከ ጠዋት ድረስ ሥራ ላይ ነበሩ’ የሚል ምላሽ አግኝታ ነበር። አሁን ይህን ዜና እየዘገብን ባለንበት ወቅት ወደ አዲስ አበባ የአንድነት አመራሮች ጋር ስንደውል ስልኮቻቸውን ያነሱ ሁለት የአንድነት አመራሮች የዶ/ር ነጋሶን በፖሊስ ጣቢያ መቆየት ለዘ-ሐበሻ አረጋግጠዋል።

የፍኖተ ነፃነት ጋዜጠኛ ብስራት “አንድነት ፓርቲ አባላት በጉለሌ ክፍለ ከተማ መስከረም 19 ቀን 2005 ዓ.ም. በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ለተጠራው ህዝባዊ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ በሽሮ ሜዳ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ ሳሉ መታሰራቸውን ተከትሎ የፓርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ያዘዝኩት እኔ ስለሆንኩ ልጆቹን ልቀቁ፤ ከፈለጋችሁ እኔን ማሰር ትችላላችሁ በማለታቸው የጣቢያው ፖሊሶች ዶ/ሩ ነጋሶን ማሰራቸው ተረጋግጧል።” ሲል ቢዘግብም ለዘ-ሐበሻ የደረሰው መረጃ የሚያመለክተው ግን ዶ/ር ነጋሶ የታሰሩት ካልተፈቱ ከፖሊስ ጣቢያ አልወጣም በሚል በፈቃደኝነት ለመታሰር ሄደዋል የሚል ነው።

ፖሊሶች ዶ/ር ነጋሶን ከያዙበት ሽሮሜዳ ወደ ጉለሌ ፖሊስ መምሪያ በፖሊስ መኪና እና በበርካታ ፖሊሶች ታጅበው መወሰዳቸውን የዘገበው ብስራት በቅስቀሳ ላይ እያሉ የታሰሩትን የአንድነት ፓርቲ አባላትን ለማስፈታት ሄደው ዶ/ር ነጋሶ በምትካቸው በመታሰራቸው የተለቀቁት የአንድነት ፓርቲ አባላትም ቅስቀሳቸውን ቀጥለዋል ብሏል።

(የአንድነት አባላት በቅስቅሳ ላይ)
ፎቶ ምንጭ የሚሊዮኖች ድምጽ ለነፃነት
ተጨማሪ ያንብቡ:  አዲሱ አረጋ ከለገጣፎ መልስ የጻፉት ጽሁፍ

በእሁድ መስከረም 19 ቀን 2005ዓ.ም. በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ለሚደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ቅስቀሳ እያደረጉ የሚገኙ ከ28 በላይ ሰዎችን ለማስፈታት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ያመሩት ዶ/ር ነጋሶ ‹ልጆቹ የፈጸሙት ህገ ወጥ ድርጊት የለም፣ ሲቀሰቅሱ የነበሩትም እውቅና የተሰጠውን ሰላማዊ ሰልፍ ነው፡፡ቅስቀሳው ህገ ወጥ ነው የምትሉም ከሆነ እነርሱን የላኳቸው እኔ በመሆኔ እኔን ልታስሩኝ ትችላላችሁ” ማለታቸው ተዘግቧል።

ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ዶ/ር ነጋሶ ከፖሊስ ጣቢያ ያልወጡ ሲሆን የፊታችን እሁድ ለሚደረገው ሰልፍ ቅስቀሳ ላይ ያሉት የአንድነት አባላት በቄራ አካባቢ ሲታሰሩ የሚቀሰቅሱበት መኪናም በፖሊስ ታግቷል።

Share