የቀድሞው ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ በፓርላማ ማህበረ ቅዱሳንን “አክራሪ” ሲሉ መግለጻቸው ይታወሳል። ከቅርብ ግዜ ወዲህ ደግሞ የአቶ ኃይለማርያም መንግስት በተለይ የጸረ ጽንፈኝነትን እና አክራሪነትን ለማጥፋት እታገላለሁ እያለ ባለበት ወቅት ማህበረ ቅዱሳንን ደግሞ አክራሪ ሲል መግለጹ ከፍተኛ ቁጣን መቀስቀሱ ይታወሳል። በአዲስ አበባ እየታተመች የምትወጣው እንቁ መጽሔት ሰሞኑን ዲ/ን ዳንኤል ክብረትን አነጋግራ ወጥታለች – በዚህ ጉዳይ። ዘ-ሐበሻ ይህን ቃለ ምልልስ እንደወረደ ለአንባቢ ግንዛቤ ሊሰጥ ይችላል በሚል መንፈስ አስተናገዳዋለች።
ዕንቁ፡- ጽንፈኝነት ምንድን ነው? አክራሪነትስ?
ዲ/ን ዳንኤል ክብረት፡- አንድን ነገር ወደ ጥግ ወይም ወደ መጨረሻው ጠርዝ ላይ መውሰድ ጽንፈኝነት ነው፡፡ በነገራችን ላይ፣ አክራሪነት ይሁን ጽንፈኝነት በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ብዙም ልዩነት ያላቸው ጉዳዮች አይደሉም ፡፡ ልዩነታቸው በአፈጻጸም ላይ ነው ፡፡ ጽንፈኞቹ ‹‹ይሄ እና ይሄ ብቻ!›› የማለት ጠባይ አላቸው፡፡ አክሪዎቹ ደግሞ ‹‹ይሄ እና ያ….. ካልሆነ እንዲህ እናደርጋለን›› ወደሚልና ወደ ተግባሩ ርምጃ የሚያዘሙት ናቸው፡፡ ጽንፈኝነት በየትኛውም ጠባይ ሊኖር ይችላል፡፡ በማንኛውም ጉዳይ በቅርብ ስትመጣ ለዘብተኝነት ፣ ወደ መሀል ሲሆን ወግ አጥባቂነት ፣ ወደ ዳር ሲኬድ ጽንፈኝነት ይኖራል፡፡ በባሕልም ቢኾን ለዘብተኛ ሰው አለ ፤ ማንኛውም ባህል ምንም የማይመስለው፡፡ ባህሉን የሚያጠብቅም አለ ፤ ‹‹ባሕሌን እወደዋለኹ፤ አከብረዋለኹ፤ ለምን ትነካብኛለህ? ለምንስ ትበርዘዋለህ? እንዲሁ ሳይበረዝና ሳይከለስ እንዲሁ እንዲኖርልኝ እፈልጋለኹ. . .›› ብሎ የሚያስብ ሰው አለ፡፡ ወደ ዳር ያለው ደግሞ ‹‹ከዚህ ውጭ ያለውን ፈጽሞ ማየትም ኾነ መስማት አልፈልግም!. . .›› ባይ ነው፡፡ የሌላውን ህልውና የሚክድ ነው፡፡ ይህ ለእኔ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ከባዱ ነገር አክራሪነት ነው፡፡ ወደ አክራሪነት ስትመጣ ‹‹ይሄኛውን ካልተቀበለ…›› ከሚል ይነሣና ርምጃ እስከ መውሰድ ጥግ ድረስ የሚሄድ ይሆናል፡፡
ዕንቁ፡- በኢትዮጵያ ውስጥ አክራሪነት አለ?
ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ፡- በአገራችን ‹‹አክራሪነት የለም›› ብለን መደምደም አንችልም፡፡ በተወሰነ ደረጃ አለ፡፡ የሚለያየው በምን ያህል ደረጃና የት ነው ያለው? የሚለው ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም የመኖሩን ምልክት ሰዎች ከእምነታቸው የተነሣ ሲገደሉ፣ የእምነት ቦታዎች ሲቃጠሉ ፣ የእምነት አባቶች መቃብራትና የተለያዩ ነገሮች እንዲፈርሱ ሲደረጉ አይተናል፡፡ ጽንፈኝነትን ብቻ ሳይሆን ወደ ኃይል ርምጃው የመሄዱን ነገር አይተናል፡፡የዛሬ ሰባት ዓመት ከተመለከትነው የጅማው ድርጊት ብንነሣ እንኳ አክራሪነት መኖሩን እንረዳለን፡፡ እነዚያ የጅማ ክርስቲያኖች የተገደሉት ምንም መጥፎ ነገር አድርገው አልነበረም፡፡ ‹‹ብዙዎች ሆነው ነውጥ ፈጥረው ነው›› እንዳይባል በቁጥራቸው ትንሽ ናቸው፡፡ የነበሩትም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ በገባበት ከኻያ ዓመት በፊት በነበሩት ሰሞናት በአሰቦት ገዳም እነ ጃራ አል ኢስላሚያ የፈጸሙትም በምሳሌነት ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ እነዚያ መነኮሳት ተራራ ላይ በነበረ አንድ ገዳም ይኖሩ የነበሩ ናቸው፡፡ ሌላ ያደረጉት ነገር የለም፡፡ የተገደሉት መነኩሴ ወይም ክርስቲያን በመኾናቸው ብቻ ነው፡፡ ይህ ሲታይ የአክራሪነት ጠባዕያት በአገራችን የለም ለማለት ያስቸግራል፡፡
ዕንቁ፡- ከመቼ ወዲህ ነው ይህ ዝንባሌ በኢትዮጵያ መስተዋል የጀመረው?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ይህ የመገዳደል ሁኔታ ማለትም አንድ ሰው ክርስቲያን በመኾኑ የመግደል፣ ሙስሊም በመኾኑ የመግደል ወይም የሙስሊምን መስጊድ፣ የክርስቲያኑን ቤተ መቅደስ በማቃጠል የሚገለጸው ድርጊት በቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ ከ1980ዎቹ በኋላ መታየት የጀመረ ነው ፤ የተመዘገቡት መረጃዎች እንደሚያሳዩት ፣ ከ1980 ዓ.ም ወዲህ ነው፡፡ ይህም ከአካባቢያዊ ሁኔታዎችና በመላው ዓለም ከተስተዋለው የተከተለና ችግርን የመፍቻ አንድ አማራጭ አድርጎ ከመመልከት የመነጨ ነው፡፡
ዕንቁ፡- በአገር ውስጥ እንዲህ ዐይነት ነገሮች እንዳይከሠቱ ያልተሠሩ ሥራዎች አሉ?
ዲ/ን ዳንኤል፡- አንድ ከመንግሥት ፣ ሁለት ከሃይማኖት ተቋማት ፣ ሦስት ከሌሎች አካላት በኩል ያልተሠሩ ሥራዎች አሉ፡፡ መንግሥት በሕገ መንግሥቱ ‹‹ሃይማኖት እና መንግሥት የተለያዩ ናቸው›› ብሏል ፡፡ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የሃይማኖት ፖሊስ እንኳ የለም፡፡ ይሄ ባለመኖሩ መንግሥት ሃይማኖቶችን እንዴት ነው የሚያያቸው? ለሚለው መልስ ለማግኘት አስቸጋሪ ይኾናል፡፡ ስለዚህ በአንድ በኩል ያለው ለሌላው ያደላል፣ በሌላ በኩል ያለውም ለሌላው ያደላል እያለ እንዲያማርር ኹኔታው በር ከፍቷል፡፡ አሠራሮች ላይ የሚፈጠሩ ነገሮች አሉ፤ በምዝገባውና በሌላውም፡፡ አንዳንዶቹ የተጨቋኝነት፣ ሌሎቹ የጨቋኝነት፣ ደግሞ አንዳንዶቹ የተገላጋይነት ስሜት እንዲሰማቸው የሚያደርጉ ናቸው፡፡የሃይማኖት አስተሳሰቦች የሚመሩትን ብዙኃኑን ሕዝብ እንዴት ነው? በምን መልኩ ነው? እምነቱን ከአገሪቱ ዕድገት፣ ከአገሪቱ የፖሊቲካ አስተሳሰብ ጋራ በማይጣላበት ሁኔታ ጋር ማስኬድ የሚቻለው….. በሚለው ላይ በደንብ የተጠና ፖሊስ በአገሪቱ አልነበረም፡፡ የተሠራ ሥራ አልነበረም፡፡ አሁንም አለ ለማለት ይከብደኛል፡፡ ዛሬ በሃይማኖት ጉዳዮች አንድ የሃይማኖት ‹‹ዳይሬክቶሬት›› ነው ያለው፡፡ ግን አገሪቱ ውስጥ ትልልቅ ቦታ የሌላቸው፣ ታላላቅ ጉዳዮችን የማይወስኑ…. በትልቅ ፖሊሲ፣ በትልቅ ሚኒስቴር ደረጃ ይታያሉ፡፡ ይህ ለቦታው የተሰጠውን ግምት ያንጸባርቃል፡፡ ብዙውን ውኃ በትንሽ ኮዳ ለመያዝ የመሞከር አሠራር ነው የሚስተዋለው፡፡ ስለዚህ በእምነቱ ጉዳይ ከኮዳው አቅም በላይ ሲኾን የሚፈጠሩ ዐይነት ችግሮች እየተመለከትን ነው፡፡
ዕንቁ፡- አክራሪነትን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ አኳያ እንዴት ታየዋለኽ?
ዲ/ን ዳንኤል ፡- በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ አክራሪነት ቦታ የለውም፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ ይዘት፣ ከቀኖናው ስንነሣ ይህች ቤተ ክርስቲያን ለሌሎች ዕውቅና የመንፈግ ችግር አልነበረባትም፡፡ ዕውቅና ስትሰጥ ነው የኖረችው፡፡ የእስልምና እምነት ተከታዮች ወደ አገሪቱ ሲመጡ፣ በወቅቱ የነበሩት ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ምእመናን ባይቀበሉት ኖሮ ንጉሡ ብቻውን ምንም ሊያደርግ ባልቻለ ነበር፡፡ የዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ የነገሥታቱ ሥልጣን፣ ከእምነት አባቶች ተቀባይነት ማግኘት የሚመነጭ በመኾኑ ነው፡፡ ያ ሳይኾን ሲቀር በአገሪቱ የተፈጠሩትን ችግሮች ቀረብ ካሉት ጊዜያት በእነ ዐፄ ቴዎድሮስ፣ በእነ ዐፄ ሱስንዮስ ከኾኑት ድርጊቶች ማየት እንችላለን፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜ ግጭቶች ይፈጠሩ የነበሩት፣ ሌሎች ለእርሷ ዕውቅና መስጠት ሲያቅታቸው ነው፡፡
ለምሳሌ ባለፉት ሁለት ሺሕ ዘመናት ስትቀድስ፣ ስታስተምር የኖረችበትና በ6ኛው መ/ክ/ዘ በእጅ የተጻፈው ወንጌል የተገኘው በዐድዋ እንዳባ ገሪማ ገዳም ነው፡፡ ከእርሱ የቀደመ እስከ አሁን ሊገኝ አልቻለም፡፡ እንደዚህ ያለ የክርስትና ታሪክ የተገኘባትንና አስቀድማ ወንጌል ስታስተምር የነበረችን ቤተ ክርስቲያን ‹‹ወንጌል ስታስተምሪ አልነበረም›› የሚልና ለሥራዋ፣ ለአገልግሎቷ ዕውቅና የመንፈግ ችግር አለ፡፡ ይህን ኃይል በመጠቀም፣ ድንበሯን በመሻገር፣ እርሷው ቤት ድረስ ገብተው ካህናቷ ካሉበት፣ ቅኔ ማሕሌቷና መቅደሷ ውስጥ የመዝለቅ ፍላጎት ያላቸው ሲመጡ ችግር ነው የሚኾነው፡፡
በ17ኛው መ/ክ/ዘ በዐፄ ሱስንዮስ ጊዜ በካቶሊኮችና በኦርቶዶክሶች መሐል የተከሠተው ግጭት መንሥኤው አስቀድሜ የገለጸኹት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሮማ አልሄደችም፡፡ ሮም ናት እዚህ የመጣችው፡፡ እዚህ መምጣቷ ብቻ አልነበረም ችግሩ፣ ‹‹ከዛሬ ጀምሮ ከበሮው፣ ታቦቱም፣ የካህናቱ አልባሳትም ይውጣ! የዘመን አቆጣጠሩም እንደ ጎርጎሮሳውያን ይሁን! በዓላቱም ይቀየሩ! የዓመቱ መጀመሪያ መስከረም መኾኑ ቀርቶ ታኅሣስ ይሁን!›› በሚል በቀጥታ በቤተ ክርስቲያኒቱ ህልውና ውስጥ ገቡ፡፡ ይህን የመሰለው ግፊትና ዕውቅና የመንፈግ ኹኔታ ሲመጣ ወደ ጦርነት ደረጃ ታለፈ፡፡
በስተኋላ የዐፄ ሱስንዮስ ዘመን አልፎ የዐፄ ፋሲል ዘመን ሲመጣና ችግሩ ቆሞ ኢትዮጵያውያን አባቶች፣ እነዚህ ሰዎች ምን ይደረጉ ሲባሉ ‹‹ጉባኤ ይጠራና እንከራከር›› ነው ያሉት፡፡ ጉዳዩን ከጉልበት ወደ ዕውቀት አቅጣጫ ነው የወሰዱት፡፡ ‹‹የሐሳብ ክርክር እናድርግ፤ በጉባኤው የረታ ይሂድ›› አሉ እንጂ ሌላ ነገር አላሉም፡፡ ይህም የሊቃውንቱን ጠባይ የሚያሳይ ነው፡፡ ስለዚህ በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ አክራሪነትን ሊያበቅል የሚችል መሬት አይገኝም፡፡
ዕንቁ፡- በቅርቡ የመንግሥት ወኪሎችና ሌሎች የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት አገር ዓቀፍ የሆነ ጉባኤ፣ አባ ዮናስ የተባሉ ሰው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በተለይ በማኅበረ ቅዱሳን በኩል ‹‹የአክራሪነት ችግር አለ›› የሚል ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ ይህን መነሻ በማድረግ በርግጠኝነት በቤተ ክርስቲያኒቱ የአክራሪነት ችግር ስለመኖሩ ለማሳወቅ የደፈሩ የፖሊቲካ ሰዎችም ነበሩ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የአንተ አስተያየት ምንድን ነው?
ዲ/ን ዳንኤል፡- በቅድሚያ አሁን በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ያሉትን ሰዎች በሦስት ከፍለን ማየት አለብን፡፡ አንደኛ የሌሎች መሣርያ በመኾን መሣርያ ያደረጓቸውን ወገኖች ጉዳይ የሚያስፈጽሙ አሉ፡፡ እነዚህ ሰይጣን ወደ ገነት መግባት በቻለበት ሁኔታና መንገድ ሊታዩ ይችላሉ፡፡ እንደሚታወቀው ሰይጣን ራሱ ወደ ገነት አልገባም፡፡ ወኪል ነበረው፡፡ ወኪሉም እባብ ነበር፡፡ በእባብ ውስጥ አድሮ ነው ወደ ገነት የዘለቀው፡፡ ምክንያቱም የሰይጣን ባሕርይም ጠባይዕም ስለማይፈቅደለት ራሱ ወደ ገነት አይገባምና ነው፡፡ በአባቶቻችን መጽሐፍ እንደሚነገረው፣ እባብ ተንኮለኛ፣ ውብና ትክለ መልካም ነበረች፡፡ ስለዚህ ሰይጣን ክፉ ሐሳቡንና ሤራውን በተዋበውና በማራኪው የእባብ ውበትና ተክለ ሰውነት ሸፍኖ ወደ ገነት ገባ፡፡ ሔዋንም ልትሳሳት የቻለችው የምትነጋገረው ከእባብ ጋራ ስለመሰላት ነው፡፡ ከእባብ ጀርባ ያለውንና የእባብን ሐሳብ የቀየረውን ነገር መመልከት አልቻለችም፡፡ልክ እንደዚሁ ሁሉ ገነት በኾነችው ቤተ ክርስቲያን የሌላውን ሐሳብ ይዘው የመጡ ወገኖች ገብተዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በምንኩስና፣ በቅስና፣ በዲቁና፣ በመምህርነት፣ በዘማዊነት አለባበስ ውስጥ ሁሉ የሚገኙ ናቸው፡፡ ግን ሐሳባቸው የእነርሱ አይደለም፡፡
ሁለተኛ፡- ቤተ ክርስቲያኒቱ ለዘመናት ስትቃወመው የነበረችውን የለዘብተኛ ማለት የሊበራል ክርስትና አስተሳሰብ ተጭነው በመምጣት ያን የሚያራምዱ ሰዎችም አሉ፡፡ ከእኒህ ጋራ ሊታዩ የሚችሉ ግን ደግሞ ለምንም ነገር ግድ የሌላቸው ሰዎችም አሉ፡፡ በአርባና በሰማኒያ ቀናቸው ከመጠመቃቸው በቀር ለምንም ሆነ ለምን ቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ግድ የሌላቸው መኖራቸው አይካድም፡፡
ሦስተኞቹ ደግሞ ፣ ‹‹የለም፣ ይህች ቤተ ክርስቲያን የራሷ የኾነ በጣም ብዙ ጠንካራ ነገሮች አሏት፡፡ በዶግማ፣ በቀኖና፣ በትውፊት፣ በቅርስ፣ በባህል ሀብታም ነች፡፡ በዓለም ላይ የጠፉ ቅርሶችን ጠብቃና ተከባክባ የቆየች ናት፡፡ የዓለም የባህል ሙዝየም ናት. . .›› ብለው የሚያምኑ፣ የሚሟገቱላትም ናቸው፡፡
ለምሳሌ፡- ሰንበቴ ይህች ቤተ ክርስቲያን ይዛው የቆየችው የዓለም ባህል ነው፡፡ የዓለም ክርስትና ሲጀመር ሰንበቴ ነበር፡፡ ሲጠፋ ግን ጠፋ፡፡ እርሷ ዘንድ ግን አለ፡፡ ጽዋ በሌላም ቦታ ነበር፤ ግን ጠፋ፡፡ ዛሬ የአውሮፓን ካታኮምብ (ጥንታዊ ከርሰ መቃብሮች) ቁፋሮ ሲካሄድ የሚገኙ ሥዕሎች ሰንበቴ ተሰብስበው ሲበሉ፣ ጽዋ ሲጠጡ የሚታዩባቸው ናቸው፡፡ እነርሱ አሁን የድሮ ክርስቲያኖች እንዲህ ነው የሚበሉት፣ የሚጠጡት ይሉኻል እንጂ ዛሬ ህልውናው የለም፡፡ እኛ ጋራ ግን ከነሕይወቱ ተጠብቆ ታገኘዋለህ፡፡ ሌላ ምሳሌ እንውሰድ፤ መስቀል እኛ ጋራ አልነበረም የተጀመረው፡፡ ሌሎች ጋራ የነበረ ነው፡፡ ግን እኛ ጋራ ነው ሕያው ኾኖ የሚገኘው፡፡ በሌሎች ቦታዎች ታስቦ ነው የሚውለው፡፡ ጥምቀትም ታስቦ ነው የሚውለው፡፡ የግብጽን ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ስታይ፣ እስከ ስምንትና ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ጥምቀትም መስቀልም በአደባባይ ይከበር ነበር፡፡ ዛሬ ግን አልኾነም፡፡ ይኸው እኛ ጋራ ግን በህልውናው አለ፡፡ ስለዚህ ነው ይህች ቤተ ክርስቲያን የራሷ ብቻ ሳትኾን የዓለም ባለ አደራ ናት የምንለው፡፡ ከዓለም ከኦሪት ታቦታቱን፣ ከሐዲስ መስቀሉን ጠብቃ በአደራ አስቀምጣ የቆየች አደራ የማትበላ ናት፡፡
‹‹ይህች ቤተ ክርስቲያን አደራዋን እንደጠበቀች፣ ሃይማኖትን እንደ አባቶቻችን፣ አሠራሩን እንደ ዘመናችን አድርጋ መሄድ አለባት›› የሚሉ ወገኖችም ያሏት በመሆኑ ፣ በእነዚህ ወገኖችና የሌላውን ሐሳብ ተጭነው በሚመጡ ሰዎች መሐል ትግል አለ፡፡ ክርክር አለ፡፡ ሰውዬውን በአካል ባላውቃቸውም ሲናገሩ ባላዳምጥም አሉ የተባለውን ሰምቻለሁ ፡፡ ምናልባት ስማቸው የተነሣው አባት የተባለውን ሐሳብ ይዘው መጥተው ሊሆን ይችላል ብዬ አምናለኹ፡፡
የሆነው ሆኖ፣ የሌላውን ሐሳብ ይዘው የሚመጡ ሰዎች ትልቁ ችግራቸው ምንድን ነው? ዘመኑን ከመዋጀት ይልቅ (መጽሐፉ ‹‹ዘመኑን ዋጁ›› ይላልና) ዘመኑን የመጠቀም ስልት መከተላቸው ነው፡፡ የኮሚዩኒስት ሐሳብ ሲራመድ ካዩ፣ ራሳቸውን ኮሚዩኒስት ሌላውን ካፒታሊስት ያደርጋሉ፡፡ የካፒታሊስት ሐሳብ በዘመኑ ሲራመድ ሲያዩ ደግሞ ራሳቸውን ካፒታሊስት ሌላውን ኮሚዩኒስትነት ፈርጀው ማስመታት ይፈልጋሉ፡፡ ይህን መሰል ተግባርም በየዘመኑ ይፈጽማሉ፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ከተመሠረተ ወደ ሃያ ዓመት በላይ ኾኖታል፡፡ ከመጀመሪያው ጀምሮ ይሰጡት የነበረውን ስሞች ብንመለከት የሚያስገርምና የሚያስደንቅ ነው፡፡ መአሕድ በአገሪቱ ትልቅ መነጋገርያ በኾነበት ጊዜ ‹‹መአሕድ ነው›› ተባለ፡፡ አገሪቱ ቅንጅት፣ ቅንጅት በምትሸትበት ጊዜ ደግሞ ‹‹ቅንጅት›› ተባለ፡፡
ዕንቁ፡- ለምንድን ነው እንደዚህ የሚባለው?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ምክንያቱ አስቀድሜ ባቀረብኹት ምሳሌ መሠረት በዘመኑ የመጠቀም ፍላጎት ካላቸው ሰዎች ጠባይና ባሕርይ የሚመጣ ነው፡፡ አንተ በሐሳብ ስትሸነፍ ማስመታት መቻል አለብኽ፡፡ በእኛ አገር የተለመደ ሦስት ዐይነት አሠራር አለ፡፡ አንድን ነገር መጀመሪያ ታውቀዋለህ ፡፡ ቀጥለህ ስም ትሰጠዋለኽ፡፡ ሠልሰህ ትመታዋለህ፡፡ ስም ካላወጣህለት አይመታልህም፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ለምን ነበር ‹‹መአሕድ›› ይባል የነበረው? የሚያደርገው እንቅስቃሴ በመታወቁ ነው፡፡ እንደዚህ የሚወነጅሉትም ሰዎች እኮ ያውቁታል፡፡ ግን ለመምታት የሚያስችላቸውን ስም ማውጣት አለባቸው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ግን እስከ አሁን ድረስ አክራሪ ሆኖ ያመጣው ነውጥ፣ ያስነሳው ነገር፣ የደበደበው፣ የገደለው ሰው፣ ያቃጠለው ቤተ እምነት የለም፡፡
ዕንቁ፡- ሰው ሕይወቱን፣ እምነቱን፣ ትምህርቱን፣ የዕውቀትና የኑሮ ምርጫውን በተመለከተ የራሱ ሐሳብና ከሐሳቡም የሚመነጭ ውሳኔ አለው፡፡ የሌላውን መብት እስካልተፃረረ ድረስ በራሱ ለራሱ የመመራት መብት ባለቤት ነው፡፡ ‹‹ለምንድን ነው እኛ ወዳደራጀነው ተቋም፣ ማእከል የማትመጣው›› የሚሉ ‹‹አልመጣም›› ሲል በአክራሪነት ወይም በሌላ የሚፈርጁ ሰዎችና ቡድኖች ደግሞ አሉ፡፡ ይህን ኹኔታ በጠራና የተሻለ ግንዛቤ በመፍጠር ደረጃ ለኅብረተሰቡ ማስተማር የሚቻልበት መንገድ አለ?
ዲ/ን ዳንኤል፡- አስቀድሜ ለማንሣት እንደፈልግኹት፣ ለዘብተኛው አካል መሥዋዕትነት ለመክፈል ወይም ደግሞ አንዳች ሱታፌ ለማድረግ ፍላጎት የለውም፡፡ ያኛው ደግሞ የሌላው ወኪል ነው፡፡ ምክንያቱም ይህች ቤተ ክርስቲያን እኮ በሦስት ደረጃ ማለትም ወይ ለማፍረስ! ወይ ለመጠምዘዝ (ከምትሄድበት አቅጣጫ ወደ ሌላ መሥመር ለመውሰድ) ይህ ካልኾነ ደግሞ ለማደንበሽ ብዙ ጥረት ተደርጓል፡፡ ማደንበሽ ማለት ምንም እንቅስቃሴ እንዳታደርግ፣ ዝም ብላ እንድትኖር ማድረግ ማለት ነው፡፡ ለአንድ ሰው ምግብ፣ ልብስ፣ መጠለያ ተሰጥቶት ግን በአእምሮው ምንም ዕውቀት እንዳይኖረው የማድረግ አይነት ነው፡፡ እንደዚህ አይነቱ ሰው አንድ ሰፈር ውስጥ ቁጭ ብሎ የፈለገውን ፊልም፣ የፈለገውን ሙዚቃ እያየና እያደመጠ፣ በዚህ ብቻ እየተደሰተና እየጨፈረ እንዲኖር ቢደረግ ይህ ኑሮ አይደለም፡፡ ያ ሰው ምንም የሚያስበው፣ የሚሠራው፣ የሚፈጥረው ነገር የለውም፡፡ በቃ ሰፈሩ ብቻ መኖርያው ነው፡፡ የምግብ፣ የልብስ ችግር የለበትም፡፡ እንግዲህ ይሄ ነው መደንበሽ የሚባለው፡፡
በእኒህ በሦስቱ የማጥፊያ ስልቶች ይህች ቤተ ክርስቲያን ተሞክራለች፡፡ ግን የእግዚአብሔር ኃይል፣ የቅዱሳን ጸሎት በውስጧ ስላለ የተመኙላትን ልትኾን አልቻለችም፡፡ በርግጥ የተወሰኑ ሰዎችን መማረክ ይቻል ይኾናል፤ ግን ይህች ቤተ ክርስቲያን ከማናችንም ኃይል በላይ ናት፡፡ ያልታወቀና ማንም የማይደርስበት ኃይል ያላት ነች፡፡ ባትሆን ትጠፋ ነበር፡፡ ግራኝ አንድ ዐሥረኛ ምእመኗ እስኪቀር ጭፍጨፋ አካሂዶባታል፡፡ ብዙዎቹን መቅደሶቿን አቃጥሎባታል፤ ግን አልጠፋችም! ፋሽስት ኢጣልያ ብዙ ነገር አድርጓል፡፡ የፋሽስት ኢጣልያ ወራሪ ጦር እንደገባ ወደ አራዳ ቅ/ጊዮርጊስ በመሄድ የቤተ ክርስቲያኑን ቅጽር በወታደሮች ነው ያስከበበው፡፡ ቀጥሎም የቅ/ጊዮርጊስ ታቦት ‹‹ወታደራዊ ፍርድ ቤት›› በሚለው ችሎት እንዲቀርብ በማድረግና ‹‹ሞት ሊፈረድበት ይገባል!›› የሚል ውሳኔ በማስወሰን ዙሪያውን ተኩስ እንዲከፈትበት አድርጓል፡፡ የተኩሱ አሻራ አሁንም ድረስ በቤተ ክርስቲያኑ ቅጽር ውስጥ አለ፡፡ ግን ይህ ለምን ተደረገ?….. የሚለው ነው ዋናው ጥያቄ፡፡ ታቦቱ አገር በመጠበቁ ካልኾነ ምን ወንጀል ነበረበት? ከአራዳ ጊዮርጊስ አልፈው ደብረ ሊባኖስ በመሄድ መነኮሳቱን የገደሉት ለምንድን ነው? ቅርሷንስ ጭነው የሄዱት? ያኔ ብዙ መነኮሳት ተገድለዋል፡፡ ከሞቱት መሐል እነ አቡነ ጴጥሮስ የዚህች ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ራስ ናቸው፡፡ ግን የሚጠብቃት ኃይል ስላለ ምንም ሊያደርጓት አልተቻላቸውም፡፡
ዕንቁ፡- ይህ ‹‹አክራሪ›› የሚባለው ስያሜ የመነጨው ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማፍረስ፣ ለመጠምዘዝ ወይም ለማደንበሽ ከሚፈለገው መንፈስ ነው ማለት ይቻላል?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ታድያስ! እርሱ እኮ ነው ‹‹ይህችን ቤተ ክርስቲያን እንጠብቅ›› የሚሉትን የሚፃረረው፡፡
ዕንቁ፡- ‹‹መንፈሱ መኖር አለበት›› በሚሉና ‹‹መንፈሱ መኖር የለበትም›› በሚሉ መካከል ነው ትግሉ ያለው?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ነው!. . .ትግሉ እርሱ ነው፡፡ ‹‹ይህች ቤተ ክርስቲያን ተጠብቃ፣ ሥርዐቷን ይዛ ወደሚቀጥለው ትውልድና ዘመን መሻገር አለባት›› የሚሉትን አካላት ነው አሁን ‹‹አክራሪ›› ማለትና ዝም ማሰኘት የሚፈለገው፡፡ እነዚህን ሰዎች ዝም ማሰኘት ግን አይቻልም፡፡ ሃይማኖት የህልውና ጉዳይ ነው፡፡
ዕንቁ፡- ዝም ማሰኘት ካልተቻለ ግቡ ምን ሊኾን ነው?
ዲ/ን ዳንኤል፡- እርሱን በሂደት የምናየው ነው፡፡ የዚህችን ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ማንም በዕቅድ፣ በስትራተጂ፣ በምን ሊተምነው አይችልም፡፡ ታሪኳ የእግዚአብሔር ሥራ ውጤት ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹እገሌ ነው እርሷን የሚመራት›› ሊባል አይችልም፡፡ አስተዳደራዊ አመራር ይኖራታል እንጂ መንፈሳዊ አመራሯን ከፈጣሪ የምታገኝ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ስለዚህ እኛ የተባሉት ሰው…. ይህን ዓላማ ይዘው መጥተው ተናግረውት ካልኾነ በቀር ማኅበረ ቅዱሳንን አክራሪ ለማሰኘት የሚያበቃ ምንም፣ አንድም መከራከሪያ ሊያመጡ አይችሉም፡፡ ለነገሩ እርሳቸውም ቢሆኑ ማስጠንቀቂያ ሰጡ እንጂ ይሄ፣ ይሄ፣ ይሄ ብለው በዝርዝር ያመጡት ምንም ነገር የለም፡፡ ከሳቸውም በፊት የነበሩት ሌሎች ሰዎች እንደ እርሳቸው ብለዋል፡፡ ማናቸውም ግን ማስረጃ ብለው የሚያቀርቡት ነገር የላቸውም፡፡
በበኩሌ አራት፣ አምስት ነገሮች ሲነገሩ እሰማለኹ፡፡ ‹‹አንዲት አገር አንዲት ጥምቀት››፤ ‹‹አንድ አገር አንድ ሃይማኖት›› ብለዋል የሚል፡፡ ይህን ከብዙኀን መገናኛ እሰማዋለኹ እንጂ ከየትኛውም የቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ላይ ተጠቅሶ አይቼ አላውቅም፡፡እንዴ ‹‹አንድ አገር አንድ ሃይማኖት›› የሚለው እኮ ከራሷ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ ጋራ የሚጋጭ ነው፡፡ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 1 ቁጥር 8 ላይ የሚለው ‹‹በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳ፣ በሰማርያ እስከ ዓለም ዳርቻ አስተምሩ›› ነው፡፡ አንድ አገር ውስጥ ተቀመጡ አላለም፡፡ የሚባለውን የማንቀበለው ከእኛ አስተምህሮ ጋራ ስለሚጋጭ ነው፡፡ ቢቻል ጅቡቲ፣ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ሶማልያ፣ ታንዛንያ፣ ጋና፣ ጃማይካ ሄደን አስተምረን ክርስቲያን ማድረግ ነው የሚጠበቅብን፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታይ የኾኑ አሜሪካውያን፣ ጃማይካውያን፣ እንግሊዛውያን፣ ጀርመናውያን አሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ እንዴት ወደ አንድ አገር መጥቅለል ይቻላል? ሊሆን አይችልም፡፡ ፈጽሞ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ ጋራ የማይሄድ ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቱ በዜግነት ኢትዮጵያውያን ያልኾኑ የእምነት አባቶች ያሏት ነች፡፡ የመጀመሪያው ጳጳስ አቡነ ሰላማ ግሪካዊ ነው፡፡ ዘጠኙ ቅዱሳን የሶርያ፣ የግሪክ፣ የሮም ሰዎች ናቸው፡፡ ወደዚህ ቀረብ ስንል አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ግብጻዊ ናቸው፡፡ የደብረ ሊባኖሱ 11ኛው ዕጨጌ አቡነ ዕንባቆም የመናዊ ነው፡፡ እንዴት ተደርጎ በአንድ አገርና በአንድ ሕዝብ መወሰንና ማስተማር የሚቻለው፡፡ በዚህች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እኮ ዕድሉ የለም፡፡
ዕንቁ፡- ጽንፈኝነትን ይኹን አክራሪነትን የሚያበረታታ ታሪካዊ መሠረት በአገራችን ታሪክ አለ?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ከዚህ ጥያቄ አንጻር ሦስት ነገሮችን ማየት ያለብን ይመስለኛል፡፡ አንደኛ፡- የእምነቶቹ ግንኙነት በመተዋወቅና በመግባባት እንዲኾን የተሠራ ሥራ የለም፡፡ ይሄ ባለመሠራቱ አንዳንድ ወገኖች ሁልጊዜ የተጨቋኝነት ስሜት እንዲሰማቸው የሚያደርጉ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ግን እነዚህን በቀላሉ ማጥፋት የሚቻልበት መንገድ፣ እርስ በርስ የሥነ ምግባር መመሪያ እንዲኖራቸው የማድረጉ ዕድል አለ፡፡
ለምሳሌ አንዱ ስለሌላው ሲናገር መሆን ስለሚኖርበት ኹኔታ ተቀራርቦ በመወያየት አንድ የሚያግባባ ነጥብ ላይ መድረስ ይቻላል፡፡ በመሠረቱ ስለሌላው እምነት ማስተማር ተፈጥሯዊ ነው፡፡ አንተ ‹‹እኔ ትክክል ነኝ›› ስትል ሌላው ‹‹ስሕተት ነው›› ማለት በፍጹም ችግር ያለበት ጉዳይ አይደለም፡፡ አንድ ሙስሊም ‹‹እስልምና ትክክለኛ የመዳን ሃይማኖት ነው›› እስካለ ድረስ ‹‹ክርስትና ስሕተት ነው›› ብሎ ስሕተት ናቸው ብሎ ስለሚያምንባቸው ነገሮች ቢያስተምር ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ለምን ይህን አደረግኽ ልንለው አንችልም፡፡ አለበለዚያ ‹‹ክርስትናም እስልምናም ትክክል ነው›› ማለት መቻል አለበት፡፡ አንድ ክርስቲያንም ስለ እስልምና ‹‹ቁርዓን እዚህ ጋራ ተሳስቷል፤ ነቢዩ መሐመድ እዚህ ላይ ተሳስተዋል፤ አካሄዳቸው ስሕተት ነው›› ቢል ለእኔ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ግን እርሱ አይደለም ችግሩ፡፡ ይህን ስታስተምር ምን ዓይነት ሥነ ምግባራዊ መርሕ መከተል አለብህ፤ አንዱ ወደ አንዱ እንዲመጣ ሳይሆን አንዱ በሌላው ላይ የጥላቻ ስሜት እንዳያድርበት ማድረግ የሚቻልበት ዕድል አለ፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ መንግሥት የሃይማኖት ተቋማትን የሚያይበት አሠራር መስተካከል አለበት ባይ ነኝ፡፡ በአንድ ሚኒስቴር ሥር የሃይማኖት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ነው ያለው፡፡ ፖሊሲ የለውም፡፡ አሁን ተቋቋመ የተባለው ጉባኤ በራሱ ሲታይ ሕዝቡ በሚገባ የተረዳው አይነት አይደለም፡፡ የምንመሠርታቸው ተቋማት ለምን እንደ ሐበሻ መድኃኒት ድብቅ እንደሚኾኑ ይገርመኛል፡፡ ሲኾን እንደዚህ ዐይነቱ ተቋም መቋቋም የሚገባው በላይኛው አካል አልነበረም፡፡ ከታች ከአጥቢያ ጀምሮ አብያተ ክርስቲያንና መስጊዶች ባሉበት አካባቢ የሚገኙ ምእመናን ተሰብስበው ‹‹እንዴት ነው ሁሌ ከምንቧቀስ፣ ከምንጋጭ በጋራ በሚያገናኝን ጉዳይ ላይ የማንነጋገረው? የሚያስማማን ኹኔታ የማንፈጥረው?›› የሚለውን ጥያቄ በማንሣት መወያየት ይኖርባቸዋል፡፡ የምንለያይበት ነገር ቢኖርም የጋራችን በኾነው ጉዳይ መነጋገር፣ የተለያየንበትን በየራሳችን አስቀምጠን ጊዜ የሚፈጅ ቢኾንም የፈጀውን ያህል ጊዜ ፈጅቶ ይሄን፣ ይሄን፣ ይሄን እያልን ወደላይ መድረስ አለብን፡፡
ምንም ነገር ቢሆን ሊሰምር የሚችለው በእኛ በኢትዮጵያውያን ጠባይ ከታች ወደላይ ሲሆን ነው፡፡ እምነት ከታች ወደላይ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ምእመናን ያለጳጳስ ኖረው ያውቃሉ፡፡ ያለምእመናኑ ግን ጳጳሳቱ ኖረው አያውቁም፡፡ ስለዚህ ወሳኞቹ ምእመናን ናቸው፡፡ ያለ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ብዙ ሙስሊሞች ኖረዋል፡፡ የእስልምና ጉዳዮች ጠ/ም/ቤት የተቋቋመው በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ብዙ ሙስሊሞች ነበሩ፡፡ ሙስሊሞች ባልነበሩበት ዘመን የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ኖሮ አያውቅም፡፡ ስለዚህ ወሳኞቹ ሙስሊሞቹ ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት የእምነቱ ነገር ከታች ወደላይ እንጂ ከላይ ወደታች ኾኖ አይኾንም፡፡ በቃ አይኾንም! የኢትዮጵያ እምነት ጠባዩ እርሱ አይደለም፡፡ ይህን ጠባይ እኛ እንሻገረው ብንል ብሎኑ ጭራሽ አይገጥምም፡፡ የሚመጣው ስድስት ቁጥር ብሎን ነው፤ ማስገባት የሚፈለገው ግን አራት ቁጥር ብሎን ነው፡፡ ና ግባ፤ ቢባል እሺ አይልም፡፡ ስለዚህ ምን ይደረጋል. . . ልኬቱ መመጠን አለበት፡፡ ቀዳዳውን ላስፋው ሲሉ ግን ግጭቱ ይፈጠራል፡፡
ዕንቁ፡- በኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹የሃይማኖት መቻቻል›› አለ ትላለህ?
ዲ/ን ዳንኤል፡- እኔ ከመቻቻል ያለፈ መገንዘብ ነበረ እላለኹ፡፡ ‹‹መቻቻል›› የሚለውን አልቀበለውም፡፡ ለምን? አሁን ባልና ሚስትን ብዙ ጊዜ ስናስታርቅ ‹‹እኔኮ ችዬው ነው የኖርኩት›› ብለው ሲሉ ተስማምቶኝ ነው ማለታቸው አይደለም፡፡ ምን ይደረግ ብዬ፤ ልጅ ለማሳደግ ብዬ፤ ችዬው፣ ተሸክሜው እያሉ ነው የተበደሉት ሚስቶች፡፡ አንደኛው ተሸካሚ ኾኖ እህህ…ብሎ የመቻል ነው፡፡ ጭነት የበዛበት ነው፡፡ የማይፈለግ ነገር ያለበት ነው፡፡ ቻለው ተብለህ የምትኖረው ኑሮ ማለት ነው፡፡ መገንዘብ ማለት ግን አንዱ የሌላውን ችግር፣ ብርታት ተገንዝቦ በዚያ ውስጥ መኖር ማለት ነው፡፡
ዕንቁ፡- ይኼ የምትለው መገናዘብስ አለ?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ኢትዮጵያ ውስጥ በብዙ ሕዝብ ዘንድ አለ፡፡ አሁን አለና የለምን በቃላት ደረጃ ስናገረው ተግባራዊ መመዘኛው በኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል የእስልምና እምነት፣ ምን ያህልስ የክርስትና እምነት ተከታዮች አሉ ብለን ስንጠይቅ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ የእነዚህ ሁለት እምነት ተከታዮች ቁጥር ከኢትዮጵያ ሕዝብ አብላጫው ነው፡፡ በአብዛኛው ማኅበረሰብ ዘንድ ይኸው መገናዘብ አለ፡፡ በርግጥ በጥቂቶች ዘንድ ላይኖር ይችላል፡፡ ለምሳሌ አንድን ሙስሊም ‹‹እንኳን ለመውሊድ በዓል አደረሰኽ›› ስትለው ተገንዝበህዋል ማለት ነው፡፡ በዚያ በዓል ላይ ተስማምተህ ላይኾን ይችላል፡፡ እንደውም ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያ ብዙኀን መገናኛዎች ለሙስሊሞች ‹‹እንኳን ለዒድ አል አረፋ በዓል አደረሳችኹ››፤ ለክርስቲያኖች ‹‹እንኳን ለጥምቀት በዓል አደረሳችኹ›› ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ግን ለምንድን ነው እንዲህ የሚሉት? እኔ በኢትዮጵያዊነቴ የሙስሊም ወገኔን በዓል ገዝቼዋለኹ፡፡ ሙስሊሙም የእኔን በዓል ገዝቶታል፡፡ እርሱም በእኔ እምነት እድናለኹ፤ እኔም በእርሱ እምነት እድናለኹ፤ አላልንም እንጂ በባህላችን አንዳችን የሌላችንን በዓል ገንዘብ አድርገነዋል፡፡
ስለዚህ በብዙኀን መገናኛ በኩል መባል የሚኖርበት ‹‹ለኢትዮጵያውያን በሙሉ እንኳን ለዒድ አል አረፋ፤ እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ በዓል አደረሳችኁ›› ነው፡፡ ለምን ሚዲያው ይለየናል? እኛ ያልተያየነውን ለምን የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት የሚለያየን እላለኹ፡፡ ብዙውን ጊዜ እኔ ጓደኛዬን ‹‹እንኳን አደረሰን›› ነው የምለው፡፡ ለምሳሌ እርሱ የመውሊድን በዓል ሲያከብር የሚያገኘው ሃይማኖታዊ በረከት እንዳለ አስቦ ነው፤ ልክ እኔ ጥምቀት በማከብርበት ጊዜ እንደማደርገው፤ ግን እርሱን እንኳን አደረሰኽ ስለው እርሱ በዓሉን ሰላማዊ ኾኖ፣ ነጻ ኾኖ፣ ደስ ብሎት የሚያከበርበትን ከባቢያዊ ኹኔታ መፍጠር ግዴታዬ ነው፡፡
ዕንቁ፡- ‹‹እንኳን አደረሰህ›› እና ‹‹እንኳን አደረሰን!›› በሚለው መሀል ልዩነት አለ እያልኽ ነው?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ስንኾን አዎ፣ ልዩነት አለው፡፡ ለምን? እኔም አስተዋፅኦ አድርጌአለሁ፡፡ ሙስሊሙ ሃይማኖታዊ በዓሉን ደስ ብሎት፣ ነጻ ኾኖ እንዲያከብር፡፡ በዚህም ደስተኛ ነኝ፡፡ እኔም የጥምቀት በዓሌን ደስ ብሎኝ በሰላማዊ ሁኔታ ለማክበሬ የሙስሊሙ አስተዋፅኦ አለበት፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ‹‹እንኳን ለመውሊድ፣ እንኳን ለብርሃነ ልደቱ አደረሰን፤ አደረሳችሁ›› ማለት ወይም መባባል ነው ያለብን፡፡ የሁላችንም አስተዋፅኦ ያለበት ነገር እኮ ነው፡፡እስኪ ፈጣሪ ያሳይህ. . .ለጥምቀት፣ ለፋሲካ. . .ቀን በግ ይዞ የሚመጣውን ሰው ሙስሊም ይሁን ክርስቲያን በምን ታውቀዋለኽ? ለይተህ የምታውቅበት ልዩ ዘዴ አለህ እንዴ? እርሱ ይዞ ባይመጣ አንተ ከየት ነበር የምታገኘው? ይህ ሰው እኮ ለፋሲካ ይህን ነገር ማድረስ አለብኝ ብሎ ከሠራ ትልቅ ተግባር ነው ያከናወነው፡፡ እና የእነዚህ ወገኖቻችን አስተዋፅኦ በእኛ በዓል አከባበር ላይ አለበት፡፡ ለምን ታድያ የሥራውን ቀን ዝግ እናደርጋለን? የማይገባኝ ነገር እርሱ ነው፡፡ ጥምቀት ዕለት ሙስሊም ወገናችን ለምን ሥራ እንዲገባ አይደረግም? የመውሊድ ዕለትስ እኛ ሥራ እንዳንገባ የሚደረገው ለምንድን ነው? መገናዘቡ የለም ከተባለ፣ አንዱ ለሌላኛው ያበረከተው አስተዋፅኦ የለም አልነበረም የሚባል ከኾነ ሥራው ሲዘጋ በከፊል ነው መዘጋት የሚኖርበት፡፡ የመውሊድ በዓል ሲሆን ሙስሊም የሆናችሁ ወደ ሥራ አትምጡ፤ የስቅለት ዕለት ሲሆን ደግሞ ክርስቲያን የሆናችሁ ወደ ሥራ አትግቡ፤ ሌሎቻችሁ ግን ወደ ሥራ መግባት አለባችሁ መባል ነበረበት፤ በዓሉ የእነርሱና የእኛ ብቻ ከሆነ፤ ግን የሁላችንም ነው፡፡ በሕግ ደረጃ ብሔራዊ በዓል ነው ተብሎ ከተደነገገ በኋላ በሚዲያ በኩል ልዩነቱ ለምን ይመጣል? ይሄ ነው በተግባር መልስ ማግኘት ያለበት፡፡ ኢትዮጵያውያን ከሥር ሆነን ያዳበርነው ከወደላይ ትልቅ ችግር ይፈጠርበታል፡፡ አስቀድሜ እንደተናገርኹት በኢትዮጵያ ውስጥ እምነት ከታች ወደላይ ነው፡፡ ታች ያለው ያለ በላዩ መኖር ይችላል፡፡ በስተላይ ያለው ግን ያለ በታቹ መኖር አይችልም፡፡
ቤተ ክህነት መኖሯን ሳያውቁ የሚኖሩ ብዙ ምእመናን አሉ፡፡ ጋምቤላ፣ ጎጃም፣ አሶሳ ጠረፍ ሄደህ፣ ጎንደር ገጠር ወርደህ ፤ .ፓትርያርኩ ማን ናቸው? ብለኽ ጠይቅ፤ የት ያውቃል! የእስልምና ጉዳዮች ሰብሳቢ ማን ቸው? ብትለው እስኪ የት ያውቅልሃል! እግዚአብሔርን ፣ የአጥቢያውን ታቦት፣ ቃዲውን ነው የሚያውቀው፡፡ ወይም ደግሞ በሰፈሩ ያለውን ዑሏማ ‹‹አሏህ ወ አክበር›› የሚያሰኘውን ሰው ነው የሚያውቀው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋራ፣ ከአላህ ጋራ የሚያገናኘው ያ በቅርቡ ያሉት የሃይማኖቱ ተጠሪ ናቸው፡፡ እርሱ ካለለት በቂ ነው፡፡ ከዚያ በላይ ያለው ትርፍ ነው፡፡ እኔ ታች ያሉት ከተግባቡ ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ችግር የለም ባይ ነኝ፤ የሃይማኖት መሠረቶች እነርሱ ናቸውና፡፡ ሌላው ዓለም ስንሄድ ከላይ ወደታች ነው፡፡ ለዚህም ነው ለኢትዮጵያውያን በሃይማኖታቸው ጸንተው መኖር እምነቱ ከታች መኾኑ ዋነኛው መሠረት ነው፡፡
ዕንቁ፡- እምነቱ ከላይ ወደታች ቢኾን ምን ችግር ይገጥመዋል?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ግብጽ ስንት ጊዜ ጳጳስ ስታስቀር ምን ይውጠን ነበር? በዚህ ሁሉ ጭቅጭቅ፣ በዚህ ሁሉ ክርክር በንጉሡም በደርግ ዘመንም እንይ፤ አሁንም እንመልከት፡፡ ስለ እምነት ተቋማት የተለያየ አመለካከት ነው የነበረው፤ ያለውም፡፡ በየዘመኑ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች ከመንግሥት ጋራ ናቸው አይደሉም የሚለው ክርክር አለ፡፡ ይህ ክርክር ግን ታች ያለውን ሰው አይነካውም፡፡ ጥፍጣፊው አይደርስበትም፡፡ ለምን? ብለን ስንል ጉዳዩ ከላይ ነው፡፡ እርሱ ከታች አንድ የንስሐ አባት፣ አንድ ቁርዓን የሚያስቀራው ካለ በቂው ነው፡፡ ታቦቱ አጠገቡ ካለ እዚያው ሄዶ ያስቀድሳል፤ ክርስትና ያሥነሳል፤ ሲሞት እዚያው ይቀበራል፡፡ እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ አለ የምለው መገናዘብ፣ መግባባት ይህን ነው፡፡
ዕንቁ፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ህልውና ለመጠበቅ፣ እሴቶቿን በነበረበት ለማቆየት የሚደረገውን መንፈሳዊ ትግል ወይም ይህን የመሰለውን ተነሣሽነትና መንፈሳዊ አስተምህሮ እንደ አክራሪነት ተግባር የሚመለከቱትን ለመከላከል ምን መደረግ ይኖርበታል?
ዲ/ን ዳንኤል፡- አንደኛ መገንዘብ አለባቸው! በደንብ ስለማውቀው ክርስትና ልናገር፡፡ ክርስትና የሚጠይቅህ አንተ አምነህ ፣ ተጠምቀህ ብቻ እንድትኖር አይደለም፡፡ ይሁዳ በመልእክቱ ቁጥር ሦስት ላይ ‹‹ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እመክራችኋለኹ›› ነው ያለው፡፡ እንድትጋሉ እንጂ አምናችሁ፣ ተጠምቃችኹ እንድትቀመጡ አላለም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በላከው መልእክት ላይ ‹‹ሩጫዬን ፈጽሜአለኹ፤ ሃይማኖቴን ጠብቄአለኹ፤ መልካሙን ገድል ተጋድዬአለኹ›› ብሏል፡፡ ስለዚህ ሃይማኖት መጠበቅ አንድ ነገር ነው፡፡ ብዙ ሰው እንደሚለው ግን ይህ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ መልካሙን ገድል መጋደል ደግሞ ይኖርብናል፡፡ ያ መልካሙ ገድልም ደግሞ ከሦስት አካላት ጋራ የሚደረግ ነው፡፡ አንደኛ፡- ከራስ ጠባይዕ ጋራ፣ ሁለተኛ፡- ከሰይጣን ጋራ፣ ሦስተኛ፡- ከተለያዩ አካላት ማለትም ሃይማኖትኽን፣ ቤተ ክርስቲያንህን ወይም እምነትህን ለማፍረስ ከተነሡ ወገኖች ጋራ፣ ከመናፍቃን፣ ከከሐድያን፣ ከአላውያንና ከሌሎች አካላት ጋራ የምታደርገው ተጋድሎ ነው፡፡
ለምሳሌ፡- መናፍቃን ከውስጥ የሚወጡ ናቸው፡፡ አላውያን የምንላቸው ኃይልና ሥልጣን ተጠቅመው የሚመጡ ሲኾኑ ፤ ከሐድያን ደግሞ ወጥተው የሚሄዱ ናቸው፡፡ መልካሙ ገድል የሚባለውም ከእኒህ ጋራ የሚደረግ ተጋድሎ ነው፡፡ ይሄ ከሌለ ተጋድሎ አለ ሊባል አይችልም፡፡ ስለሆነም በክርስትና የመጋደል ግዴታ አለ፡፡ ስለዚህ የክርስትና ተጋድሎ በሚሰጠው ግዴታ ውስጥ አንድ ክርስቲያን አንዱን የተጋድሎ ዐይነት መምረጥ ይኖርበታል፡፡ ‹‹ቀኝኽን ለሚመታኽ ግራኽን ስጥ›› የሚል ክርስትናን የምንከተል በመኾናችን እስከ አሁን አባቶቻችን ሞተዋል እንጂ አልገደሉም፡፡
ሃይማኖትን የመጠበቅና የመጋደል ግዴታ በክርስትና አለ፡፡ በዚህ መሠረት የሚጋደሉትን አክራሪ የሚሉ ሰዎች ካሉ ያልተገነዘቡት ነገር አለ፡፡ አክራሪነት ይሄ ከኾነ በክርስትና አክራሪነት የሚጀምረው በቅዱስ ጴጥሮስ ዘመን ከነበሩት ሐዋርያት ነው ማለት ነው፡፡ እነዚያ ሁሉ አክራሪዎች ከኾኑ የምናወራው ስለ ክርስትና ነው ማለት ነው? ስለዚህ ስም በሌላው ላይ ከመለጠፋቸው በፊት ማወቅ፣ መገንዘብ ይኖርባቸዋል፡፡በተለይ ማኅበረ ቅዱሳንን በተመለከተ የሚሰነዘሩ ሐሳቦች ምንጫቸው መታየት አለበት፡፡ ለምንድን ነው ያ ሰው እንደዚያ ያለ ሐሳብ ያቀረበው፤ በምን ፍላጎት ላይ ተመርቶ ነው የሚለው መጤን ይኖርበታል፡፡ ከዚህ በፊት መንግሥት ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት›› የሚል ትልቅ አጀንዳ አንሥቶ በነበረ ጊዜ የሆኑ አካላት ተነሥተው ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን ኪራይ ሰብሳቢ ነው›› ብለዋል፡፡ እንደነዚህ ያሉ አካላት ነገ ሌላ ስም ቢመጣ የመጣውን ስም ከማለት አይመለሱም፡፡
ዕንቁ፡- ማኅበረ ቅዱሳን እንደዚህ ዐይነቱን ነገር ለመከላከል ምን ማድረግ አለበት?
ዲ/ን ዳንኤል፡- የተለየ ነገር ማድረግ አለበት ብዬ አላምንም፡፡ እያደረገ ያለውን መቀጠል ነው፤ ምክንያቱም ለሚነሣው ሁሉ መልስ በመስጠት ራስን ከሠራተኛነት ወደ ተዋጊነት መለወጥ አያስፈልግም፤ እውነት ነውና የሚያሸንፈው፡፡ በአገራችን ይትበሃል ‹‹ቂጣም ከኾነ ይጠፋል፤ ሽልም ከኾነ ይገፋል›› እንደሚባለው በተያዘው ሐቅ መቀጠል ነው፡፡ አንድ ሰው እርግዝና መኾኑን ባወቀው ጉዳይ ‹‹አይ ይሄ ቦርጭ ነው›› ላሉት ሰዎች ሁሉን ለማስረዳት በመድከም ጨጓራውን መላጥ የለበትም፡፡ ሲወለድ ይታወቃል፤ ያኔ ይደርሳል፡፡
በበኩሌ አንድ የተባለ ነገር ብቻ አውቃለኹ፡፡ በዓለም ላይ ተከሥቶ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን አላደረገውም›› የተባለውን ነገር፡፡የመስከረም 11 የአሸባሪዎች ተግባር ማኅበረ ቅዱሳን አደረገው አልተባለም፡፡ ከዚህ ውጭ ያሉት ነገሮች ግን ተመልክተውታል፡፡ እናም ክፉ ነገር ሲመጣ መለጠፍ ለሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ መልስ መስጠት አይቻልም፡፡ ግን የሚመለከታቸው አካላት ጊዜ ሰጥቶ፣ መዛግብቱን ይዞ ማስረዳት ይኖርበታል፡፡ እንደውም ማኅበሩ አንድ የሚጎድለው ነገር ቢኖር ማስረዳት ነው፡፡ መልስ መስጠት እንጂ ቀድሞ የማስረዳት ነገር ውስጥ ብርቱ አይደለም፡፡ ስለዚህ ቀድሞ ጉዳዮቹን የማስረዳት፣ የመንገር ሓላፊነት አለበት፡፡ የሚያስረዳውም ሰዎች እንዲገባቸው ብቻ አይደለም፡፡ መረዳት፣ አለመረዳት ግን የእነዚያ አካላት ድርሻ ነው፡፡
ዕንቁ፡- በቤተ ክርስቲያኗ ላይ ወንጃይ ጣቶች የሚቀሰሩት ለምንድን ነው?
ዲ/ን ዳንኤል፡- ቤተ ክርስቲያን ከሃይማኖታዊ ዕሴቷ በተጨማሪ ለብዙ ዘመናት ሁለት ለአገሪቱ የሚጠቅሙ ዕሴቶችን ይዛ የኖረች ነች፡፡
አንደኛ፡- የኢትዮጵያዊነት ዕሴት ማለትም አገርን የመውደድ፣ አገርን ከአጥቂዎች የመከላከል፣ የአገር ፍቅር ስሜት በደም ሥር እንዲዘዋወር የሚያደርግ፣ ለአገር የመሞት እሴትን የያዘች ነች፡፡ ይሄ በግልጽ ይታያል፡፡ በተለያየ ዘመን የመጡ የአገሪቱ ጠላቶች መጀመሪያ ማፍረስ የሚፈልጉት ይህችን ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያትም አገሪቱ በጠላቶቿ ስትወረር ከግንባር ቀድማ የምትደርሰው ይህች ቤተ ክርስቲያን ነች፡፡ ለምን? ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይኾን አገራዊ አደራንም የተረከበች ቤተ ክርስቲያን በመኾኗ፡፡
ሁለተኛ፡- የአገር፣ የታሪክ፣ የባህል፣ የእምነት፣ የቅርስ ባለአደራ ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱን ያቃጠለውና ብዙ ምእመን የፈጀው የግራኝ መሐመድ ካባ የሚገኘው በመርጡለ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ያንን ካባ ያስቀመጠችው እርሱን በመሳምና በመሳለም በረከት ይገኛል ብላ እንዳልኾነ ይታወቃል፤ ግን የአገር ታሪክ ነው፡፡ የብዙ ነገሥታት፣ የአያሌ መኳንንት፣ የሚወዷትና የሚጠሏት ሰዎች ቅርስ ያለው በቤተ ክርስቲያኗ ነው፡፡ ባለአደራ ስለኾነች፣ እርሷን የሚመለከቱም የማይመለከቱም መጻሕፍት ይገኙባታል፡፡ በጭራሽ ከእርሷ ጋራ የማይሄዱ የእነአርስቶትል፣ የእነሶቅራጥስ የእነፕሌቶ መጽሐፎች ሁሉ አሉ፡፡ ይህችን አገር የማድከም ፍላጎት ያለው፣ በዓለም ላይ አንገቷን ቀና አድርጋና ከፍ ብላ እንድትሄድ የማይፈልግ ማንኛውም ኃይል መጀመሪያ መምታት ያለበት ይህችን ቤተ ክርስቲያን ነው፤ ምክንያቱም አገሪቱን አገር የሚያሰኟት ሁለት ትልልቅ ዕሴቶች ውስጧ ያሉ በመኾኑ፡፡
በብዙ ዓለም አገሮች ዞሬአለሁ፡፡ በኢትዮጵያ የሚደሰቱ አላየሁም፡፡ አንድ ምሳሌ ልጥቀስ፡፡ በእኛው አገር ውስጥ አንድ የውጭ ማኅበረሰብ ት/ቤት አለ፡፡ ይህ ት/ቤት ከውጭ በሚመጣ የትምህርት ቁሳቁስ እየተረዳ የትምህርት ሥርዐቱን የሚያስኬድ ነው፡፡ በታሪክ ማስተማርያ መጽሐፉ ላይ(አንድ ተማሪ አምጥቶ እንዳሳየኝ) ስለ አፍሪካ በሚገልጸው ክፍል ‹‹ኢትዮጵያና ላይቤሪያ ቅኝ አልተገዙም›› ይልና ምክንያቱን ሲያብራራ ‹‹ላይቤሪያ በአሜሪካ የበላይ ጠባቂነት ሥር ስለነበረች ሲኾን ኢትዮጵያ ደግሞ መሬቷ አስቸጋሪ ስለኾነ ነው›› ይላል፡፡ አየኽ! ያን ሁሉ ከዐድዋ የተጀመረ የፀረ ቅኝ አገዛዝ መሥዋዕትነት ድምጥማጡን አጥፍተውታል፡፡
ይህን የሚለው የትልቋ አገር የአሜሪካ የታሪክ ማስተማርያ መጽሐፍ ነው፡፡ እነርሱ ሳያውቁት ቀርተው ነው ማለት ይቻላል፡፡ ኾን ብለው ኢትዮጵያን የማንኳሰስ ዘመቻ ግን በብዙ ቦታ ይታያል፡፡ የቀደመውን ተወው፤ ሰሞኑን የኾነውንና የአንድ ሳምንት ዕድሜ ብቻ ያስቆጠረውን ጉዳይ በምሳሌ ላምጣልኽ፡፡ ኃይሌና ቀነኒሳ ከሞ ፋራኅ ጋራ ያደረጉትን ልዩ ውድድር አስታውሱ፡፡ ቢቢሲ ይህን ውድድር ምን ብሎ ዘገበ…‹‹ሞ ፋራኅ ተሸነፈ›› አለ፡፡ እንዲህ ያለው ቀነኒሳ አሸነፈ ላለማለት ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም የሚገርመው ራሱ ቢቢሲ ‹‹የኬንያው አትሌት ቀነኒሳ አሸነፈ›› አለ፡፡ ይህ ትልቅና ዓለም አቀፍ ተሰሚነት ያለው የዜና ማሰራጫ ተቋም እንዴት ነው ቀነኒሳን ኬንያዊ የሚያደርገው? ‹‹ኢትዮጵያዊ›› የሚለው መጠሪያ፣ መለያ እንዴት ሊጠፋው ቻለ? ከዚህ ጀምሮ ስታይ ይህችን አገር ኾን ብሎ የማዳከም ነገር እንዳለ በብዙ መንገዶች እንዳለ ትገነዘባለኽ፡፡
እኔ ከፍተኛ ድጋፍ የምሰጠው ‹‹ይህችን አገር በምንም በምንም ብለን በኢኮኖሚውም ይኹን በሌላው ራሷን የቻለች አገር ማድረግ አለብን›› የሚለውን የዚህን መንግሥት አቋም ነው፡፡ ከሕዳሴው ግድብ ጀምሮ ያለውን ነገር ሁሉ የማንንም ድጋፍ ሳንጠይቅ መሥራት አለብን የሚለው ይስማማኛል፡፡ ለምን? ማንም በጎአችንን አይፈልግም፡፡ የትም ስለኢትዮጵያ ተብሎ የሚሰጠውን ትምህርት እንመልከት፤ በሁለት የአውሮፓ አገሮች የታሪክ ማስተማርያ መጻሕፍት አይቻለኹ፡፡ ስለአፍሪካ የሚገልጸው ንኡስ ክፍል ‹‹ግብጽ›› ይልና ‹‹መርዌ›› ይመጣል፡፡ በጭራሽ ስለ አክሱም ማውራት አይፈልግም፡፡ ለምን? ምን አደረገች? የኾነ ነው፡፡ የሐቅ ጥያቄ ነው፡፡ የምርጫ ጥያቄ አይደለም፡፡
ዕንቁ፡- እንደ ጀርመን የግዕዝን ቋንቋ በትምህርት ሥርዐታቸው ውስጥ ያስገቡትስ አገሮች?
ዲ/ን ዳንኤል፡- እርሱ በጣም ጥቂት በኾኑ በጎ አድራጊዎች የኾነ ነው፡፡ እንደዚያም ቢኾን ያ የተደረገበት የራሱ ምክንያት አለው፡፡ ለእኛ ተብሎ የተደረገ አይደለም፡፡ ከዚህ የሚሄድና የሄደ ስንት ጥበብ አለ፤ ነበር፡፡ ግእዙ የሄደውና የሚሄደው ጥበብን የመፍቻ ቁልፍ ስለኾነ ነው፡፡ እንደ ‹‹ባየር›› ያሉ የመድኃኒት ፋብሪካዎች ከየት ተነሥተው የመድኃኒት ማምረቱን ሥራ አሐዱ እንዳሉት፣ ምንን ወስደው አስተርጉመው እንደጀመሩት ይታወቃል፡፡ ያ ለራስ ጥቅም ሲባል የተደረገ ነው፡፡ የዚህችን አገር የዕድገትና የብልጽና ከፍታ የሚያመጣ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያን ከፍታ የሚያመጣ ነገር ሲሞከር ግን፣ አገራችን ስትመታ ነው የሚታየው፡፡ ኢትዮጵያ በኢጣልያ ስትወረር ማን አብሯት ነበር? በወቅቱ የነበረው እውነት ጠፍቷቸው ነው? አይደለም፡፡ እና ይህችን ቤተ ክርስቲያን ከዚህች አገር ጋራ የማየት ጉዳይ ስላለ ምንጊዜም ቢኾን ሰበብ ፈጥረው መምታት ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ደግሞ በውጭዎቹ ብቻ የሚፈጸም አይደለም፤ ወኪሎችም አሏቸው፡፡ ትግሉ ከሁለቱ ጋራ ነው የሚኾነው፡፡ ዓላማቸው መበተን ሳይኾን ይህችን ቤተ ክርስቲያን ማጥፋት ነው፡፡ ይህን ካልቻሉ ማደንበሽ!
ዕንቁ፡- በኢትዮጵያ ያለው የፖሊቲካ ነው የሃይማኖት አክራሪነት?
ዲ/ን ዳንኤል፡- እኔ የሁለቱም አለ ብዬ አምናለሁ፡፡ የእምነት አለ፡፡ የፖሊቲካ እንኳ ባንል የአስተሳሰብ አክራሪነት ይኖራል፡፡ በእኛ አገር የተለመደው የፓርቲ ፖሊቲካ ነው፡፡ አንዱም ትልቅ ችግር እርሱ ነው፡፡ ይህ ስላለ ‹‹እገሌ እንደዚህ ነው›› ሲባል ‹‹እገሌ መአሕድ ነው››፣ ‹‹እገሌ እንደዚህ ብሏል›› ሲባል ‹‹ኢሕአዴግ ነው፤ ቅንጅት ነው›› ይባላል፡፡ ለስላሳ ወይም ቢራ ይመስል የኾነ ሣጥን ውስጥ ካልገባኽ ብቻኽን አስተሳሰብኽን ሊመዝነው ወይም ሊያደምጠው አይፈልግም፡፡
በነገራችን ላይ እንዲህ ዐይነቱ ጠባይዕ ከባህላችንም የመጣ ነው፡፡ በገበያው ላይ ያታያል፡፡ የኾነ ነገር ለመግዛት ስትጠይቅ ‹‹በደርዘን ካልኾነ፣ ከነሣጥኑ ካልወሰድኽ፤ የጠርሙስ ማስያዣ ካላመጣኽ ወይም ይህን ያህል ክፈል›› ይልኻል፡፡ ነጥሎ ማየት አይወደድም፡፡ ጠቅልሎ የማየት በሽታ አለብን፡፡ ስለዚህ ከመኖር የመጣ የአክራሪነት አመለካከት አለ፡፡ አክራሪ ሰዎችም አሉ፡፡ ከጠቅላላው ማኅበረሰብ አንጻር ሲታዩ ግን ኢምንት ናቸው፡፡ ኾኖም አንዳንዴ የማኅበረሰቡን ሐሳብ የማግኘት ዕድል ያላቸው ሲኾኑ፣ ይህንንም ዕድል የምናመቻችላቸው እኛው ነን፡፡ ሰዎቹ አቅም ኖሯቸው አይደለም፡፡ በማንኛውም ሰዓት በአቅራቢያው ጉንፋን አማጭ ቫይረስ ሊኖር ይችላል…ያ ሰው ሲደክም፣ በጉዞ ወይም በከባድ የሥራ ጫና ሊኾን ይችላል በዚያን ጊዜ እርሱ በሽታ ኾኖ ይመጣል፡፡ የሰውዬው መድከም ነው ለበሽታው መከሠት አስተዋፅኦ ያደረገው፡፡ ሰውዬው ጠንካራ ከኾነ ግን በአካባቢው የፈለገው ነገር ቢኖር ምንም ሊያደርገው አይችልም፡፡ የአክራሪነትን ጉዳይ የማየው እንደዚህ ነው፡፡
በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ጠንካራ አመኔታ ያለው የዕምነት ተቋም የለም፤ ጠንካራ እምነቶች ግን አሉ፡፡ ጠንካራ የእምነት ተቋምና አስተዳደራዊ ኹኔታዎች የሉም፤ አንዱ ትልቁ ችግር ይህ ነው፡፡ ተአማኒነት ያለው ተቋም አለመኖር፡፡ ቤተ ክህነቱንም የእስልምና ጉዳዮችንም ፕሮቴስታንቱንም በምሳሌነት ብንወስድ ምእመናኑ በፍርሃት በጥርጣሬ የሚያዩት እንጂ የሚወዱት የሃይማኖት ተቋም የለም፡፡ ከምእመናኑ ጋራ በጣም ተቀራርቦ የሚሠራ የሃይማኖት ተቋም አይታይም፤ ምክንያቱም በዚህች አገር ላይ ብዙዎቹ ምእመናን ናቸው፡፡ ጳጳሳቱ ኀምሳ ያህል ናቸው፡፡ ካህናቱ ተሰፍረው ወይም ተቆጥረው የሚደረስባቸው ናቸው፡፡ ሕዝቡ ግን ብዙ ነው፡፡ ከላይ እስከ ታች በሚገባ፣ በታማኝነት፣ ከሙስና፣ ከዘረኝነት፣ ከፖሊቲካ አቋም የጸዳና ግልጽና ተጠያቂነት ያለው ጠንካራ የሃይማኖት ተቋም ቢኖር ኖሮ አሁን አሉ የምንላቸውን የአክራሪነት ዝንባሌዎች በጣም እንቀንሳቸው ነበር፡፡ ይህ ባለመኖሩ ከሃይማኖት ተቋሙ የሚነሣውን የአስተዳደር ችግር በሙሉ ሰውን የመገፋት፣ የመጨቆንና አደጋ ውስጥ የመግባት ስሜት እንዲያድርበት አድርጎታል፡፡ ይህ ለእነማን ዕድል ይሰጣል? የአክራሪነት ስሜት ላላቸው አካሎች ነው፡፡ ስለዚህ ትልቁ ነገር፣ የእምነት ተቋማት ተጠያቂነት፣ ግልጽነት ባለበት ኹኔታ በየራሳቸው ሃይማኖት ሥርዐት መሠረት የሚኾንና በሌላ የማይቀየር፣ የእምነቱን ታሪክ መነሻ ያደረገ፣ ግን ለማንኛውም ሰው ግልጽ የኾነ ራሳቸውን በራሳቸው ማረምና ማስተካከል የሚያስችላቸውን አሠራር መዘርጋት ይኖርባቸዋል፡፡ ዛሬ ስለእምነት ተቋማት ጉዳይ ተነሥቶ ጨዋታ ሲጀመር ምእመናኑ ፤ ስለሙስና፣ ስለገንዘብ፣ እገሌ በዘመድ ተሾመ፣ እገሌ ገንዘብ ተቀበለ፣ እገሌ የእነ እገሌ ወገን ነው የሚለውን ነው አብዝተው የሚናገሩት፡፡ እና ነገሩ ይጽዳ፤ ይወገድ ከተባለ ከዚህ ነው መጀመር የሚኖርበት፡፡