እንግዳ ታደሰ/ ኖርዌይ
ሆ ! ብለን ጨፍረን መከራ ዘርተናል
በመንሽ አበራይተን ጥይት ሰብስበናል
ንጉስ አጠልሽተን የከፋ አንግሰናል
አገር ሳንሰበስብ ቆርሰን በታትነናል
የሻሞ በትነን ባዶ እጅ ቀርተናል
ኧንደው በጥቅሉ ከስረናል ከስረናል፡፡
« አንድ ለመንገድ ለታሪክ ግብዓት » በሚል ስያሜ በአቶ ተክለማርያም መንግሥቱ የተጻፈ ባለ 351 ቅጠል መጽሃፍ በእጄ ገብቶ ካነበብኩት በኋላ አንድ ነገር ልበል በሚል የመጽሃፉን ይዘት ሳይሆን ክመጽሃፉ ያገኘኋቸውን ገራሚና ፥ አስቂኝ የዚያን ዘመን ክስተቶችን ላካፍል ወደድኩ ፡፡ የጽሁፌ ዋና ዓላማ መጽሃፉን የመሄስ አላማ አይደለም ፡፡ በ 1966 ዓ.ም የፈነዳው ህዝባዊ አብዮት ያስከተላቸውን በረከትና ፥ መርገም ፣ ደራሲው በተዋዛና በማያንጎላጅጅ ብዕር ከትበው ያቀረቡት ታሪክና ሂደት ስላስደመመኝ ነው ፡፡ ከላይ የከተብኩትም ግጥም መጽሃፉን ካነበብኩ በኋላ የተሰማኝን ስሜት ነው በግጥሜ ያስቀመጠኩት ፡፡
በመጽሃፉ መግቢያ ላይ ደራሲው ስለመጽሃፋቸው እንዲህ ይላሉ ፡፡ በአንድ ሀገር በየዘመኑ የተፈጸመውን ታሪክ መዝግቦ ለተከታዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ሁሉ ነገር በተመቻቸበት ዘመን እንኳ ያለመቻሉ ሲታይ አሳዛኝነቱ ጉልህ ነው ፡፡ የበለጠ የሚያሳዝነው ደግሞ የታሪኩ መሪዎች ራሳቸው ጭምር በዚህ ሲወርድ ሲዋረድ በመጣ ይሉኝታና ፍርሀት ተወጥረው እውነቱን ሳይነግሩን ማለፋቸው ፣ በህይወት ያሉትም ባለመቻላቸው ብዙ የህዝብና የሃገር ታሪክ እንደተቀበረ መቅረቱ ነው ይሉናል ጸሃፊው ፡፡
ከላይ ባለው የጸሃፊው አስተያየት መሰረት አንዳንዶቹ የዚያን ጊዜው ባለስልጣኖች ታሪካቸውንና በሂደቱም ውስጥየነበራቸውን ሚና በግልጽ ሳያካፍሉን አሸልበዋል ፡፡ በህይወት ያሉት ደግሞ ዳጎስ ያሉ መጻህፍትን ቢጽፉም ፣ ሩሯን ወደሌላ ሰው ከመወርወር ባሻገር ፣ ዋስ ይቅረብ እንዳይባል እንከኑን በሞተ ሰው ላይ በመለጠፍ ፣ የተስፋዬ ገ/አብ አይነት ስታይል በመጠቀም የጨበጣ ታሪክ ተሞክሮብናል በሚል እልህ ይመስላል እውነቱን ወይም ያልተካተቱ ጉዳዮችን በኮለኔል መንግሥቱም ሆነ ፥ በሻምበል ፍቅረሰላሴ ፥ ከዚያም ሲዘል በኮለኔል ፍስሃ ደስታ መጽሃፍ ውስጥ አልተካተቱም ያሏቸውን ጉዳዮች ሊያስነብቡን የሞከሩት፡፡
መጽሃፉ ከደርግ አመሰራረት እስከ ፍጻሜው ድረስ ያሉትን ጉዳዮች በዝርዝር ስለሚዳሥስ በዚያን ወቅት በአፍላ እድሜ ውስጥ ሆነው በተቀጣጠለው አብዮት የነገሮችን ጥልቀት ሳይገነዘቡ አሁን በስድሳ ፈሪ እድሜ ውስጥ ላሉ ማስታወሻ ወይም የኋልዮሽ እንዲያዩ የሚያደርግ ፥ በዚያን ወቅትም ላልተፈጠሩ አዲስ ትውልዶች ደግሞ የቀደማቸው ትውልድ ላመነበት ጉዳይ ምን ያህል ርቀት ሂዶ እስከ ሞት እንደደረሰ የሚያሳይ መጽሃፍ ነው ፡፡ ለዚህም ነው ደራሲው « የጻፍኳትም ከደርግ ጋር እንደ ተዋናይም እንደተመልካችም ሆኜ በሠራሁባቸው ዓመታት የገጠሙኝን አንዳንድ ክስተቶች ለታሪክ ግብዓት እንዲሆን ለአንባቢዎቼ ለማሳወቅ እንደሆነ ለማስታወስ እፈልጋለሁ » ያሉት ፡፡
የነገሌ ሠራዊት ታሪክና ደራሲው በነበሩበት ቦታ ፕሬዝዳንት መንግሥቱ የሠሩት የማሸማቀቅ ታሪክ
ከ እለታት በአንዱ ቀን እንዲህ ሆነ ፡፡ አስመራ ቤተመንግሥት ውስጥ ፕሬዝዳንቱና ሌሎች ባለስልጣኖች በተገኙበት በተደረገው የእራት ግብዣ ላይ ፣ ጨዋታው ደርቶ ሞቅ ባለበት ሰአት ጄ/ል መርዕድ ጣልቃ ገብተው « የነገሌን ሠራዊት ከኋላ ሆኜ የምገፋው እኔ ነበርኩ ይላሉ » ፡፡ ከዚያም ፕሬዝዳንት መንግሥቱ በቁጣ ገንፍለው ዝም በል ! ለዚህ ነዋ አሁንም ኢህአፓ ልጆችህን የምታዘምትብን ? ቢሏቸው ጄ/ል መርዕድ ወንበራቸው ውስጥ ሰምጠው ዝም ሲሉ ተመልክቻለሁ ፡፡ ለነገሩ በወቅቱ ፕሬዝዳንት መንግሥቱ እንደመበለጥ ስላዩትና ታሪክ ለመሻማት ካልሆነ ጄ/ል መርዕድ ያሉት ትክክል እንደንበረ በትግላችን መጽሃፋቸው ገጽ 129 ራሳቸው ሊቀመንበሩ ጽፈዋል ይላሉ የመጽሃፉ ደራሲ ፡፡
የመንጌ ኪሲንግ
በዚያው ዕለት ምሽት ፕሬዝዳንት መንግስቱና ጄ/ል ተስፋዬ በቤተ መንግሥቱ ምድር ቤት ከረምቦላ እየተጫወቱ ሳለ ፣ ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ጄ/ል ተስፋዬን በጨዋታ በልጠው ያሸንፋሉ ፡፡ ፕሬዝዳንት መንግስቱ ጄ/ል መርዕድን እንደወረፉት ሁሉ ጄ/ል ተስፋዬንም አልማሯቸውም ፡፡ በአብሮ አደግነት ጊዜ የተደረገችውን አንድ አስቂኝ ታሪክ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ጄ/ ተስፋዬ ከአብሮ አደግህ ጋር አትሰደድ ነውና ላጥ ያደርጋሉ ፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው በደራሲው አገላለጽ መሠረት ፡፡
ሌ/ኮ መንግሥቱ በኢትዮጵያውያን መለኪያ ድንክ ባይባሉም አጭር ናቸው ፡፡ የፊታቸው ቀለም የኑግ ልጥ-ልጥ የመሰለ እንደ ባለሙያ እንጀራ ጠቃጠቆ የበዛበት ፣ የታችኛው ከንፈራቸው በንክሻ ( የወጣትነት ባልደረቦቻቸው ኪሲንግ kissing በሚሉት ) ምክንያት ትንሽ ወደ ግራ ያጋደለ ነው ፡፡ የታችኛው ከንፈራቸው ወደ ግራ እንዲያዘነብል ምክንያት ስለሆነው ጦሰኛው ኪሲንግ እነሆ ፡፡ ነገሩን ለደራሲው ያጫወቷቸው የደራሲው የታላቅና ታናሽ ልጆች ከሆኑት አንዱ ሜ/ጄ ስዩም መኮንን ነበሩ ፡፡ ይሄ ኪሲንግ የተባለው ድራማ የተፈጸመው ሌ/ጄ ተስፋዬና ፕ/ት መንግሥቱ የመቶ አለቆች ሆነው ጂጂጋ ተመድበው በሚሰሩበት ወቅት ነበር ፡፡
በኮለኔል ካሳ ገ/ማርያም የሚመራ አንድ የኮማንዶ ቡድን ጄ/ል ስዩምም ያለበት ለሥራ ተልከው ወደ ሀርጌሳ ለማለፍ ጅጅጋ ባደሩበት ዕለት በእንግድነታቸው እንዲዝናኑ ተብሎ ከጓደኞቻቸው ጋር ከተማ ባመሹበት ዕለት የተፈጸመ ኪሲንግ ነበር ፡፡ የጅጅጋዎቹ ሌ/ጄ ተስፋዬና ፕ/ት መንግሥቱ ከሃረር ከመጡት እንግዶች ጋር ሆነው ቡና ቤት ገብተው እየተጎነጩ በመዝናናት ላይ እያሉ የአውራጃው ፖሊስ አዛዥ የነበሩ ሌ/ኮ መጥተው ይቀላቀሏቸዋል ፡፡ በወታደር ቤት አንድ የበላይ የሆነ ሰው የበታቾቹ በሚዝናኑበት ሥፍራ ደፍሮ ከገባ መጋበዝ ይጠበቅበታልና ኮለኔሉ እንደደረሱ ሁሉኑም ተጋበዙ ፣ ጠጡ እያሉ ይለምኗቸዋል ፡፡ ባልተገለጸ ምክንያት መንግሥቱ ኃይለማርያምን ብቻ ሳይጋበዙ ዝም ይሏቸዋል ፡፡ ቆይተው ቆይተው – አንተም ጠጣ – ይቺም ፊት ሆና ደግሞ ያኮሳትራታል በማለት የፖሊሱ አውራጃ አዛዥ በንቀት የታጀበ ግብዣ ይወረውራሉ ፡፡
መንጌ አሁንስ በዛ ብለው ነው መሰለኝ የያዟትን « ዘቬሎስ ኮኛክ » ኮለኔሉ ፊት ላይ ይደፉና ኮለኔሉ ሲደናበሩ በቦክስ ሲመቷቸው ኮለኔሉ ይወድቃሉ ፡፡ የተደናገጡት ኮለኔል በሆነ ታምር የመንግሥቱን ከንፈር በጥርሳቸው ለቀም ያደርጋሉ ድብድቡ ይጦፋል ፡፡ ሁለቱም መድከማቸውን ይመለከቱና ይገላገሏቸዋል ፡፡ድራማው በዚህ ይፈጸማል ፡፡ በማግስቱ የፕ/ት መንግሥቱ ከንፈር በንክሻው ምክንያት አንዳች አክሎ ይገኛል ፡፡ በዚህም ጓደኞቻቸው በተለይም ሌ/ጄ ተስፋዬ ከሌሎች ጋር ሆነው የትናንትናው ኪሲንግ ጉዳት አደረሰ እያሉ ማውካኪያ ያደርጓቸዋል ፡፡ በዚያ ኪሲንግ ምክንያት ይመስላል የታችኛው ከንፈራቸው ትንሽ ወደ ግራ ዘንበል እንዳለ ቀርቷል ፡፡ ይህን በማስታወስ በከረንቦላ ጨዋታ የተሸነፉት ጄ/ል ተስፋዬ መንጌን ለማብሸቅ ሲሉ ፣ ስዩሜ ! ያ ኪሲንግ እንዴት ነው ? በማለት የልጅነት ጊዜ ጨዋታውን ሲያነሱ መንጌ በሽቀው ጨዋታውን አቋርጠው ይሄዳሉ ይሉናል ደራሲው ፡፡
ደራሲው ለደርግ ስልጣን መያዝ ያገዙ አመቺ ሁኔታዎች በማለት ባስቀመጡት ከዚያን ጊዜ የሚሊተሪ የታሪኩ ተዋንያኖች ውጭ ከሲቢሉ ማህበረሰብ የተገኙት ምሁራኖችንም ጭምር ሚና በዝርዝር አስፍረዋል ፡፡ ይበልጥ የሚገርመው በቅርብ ጊዚ ጭምር በኢሳት ቴሌቪዥን ኢንተርቪው ያደረጉት ሰው ታሪክ ሁሉ በደግ ሳይሆን በአሉታዊ ጎኑ በደራሲው ተጽፏል ፡፡ ጥሩነቱ እንዲህ ያለው መጽሃፍ ሰዎቹ ሳይሞቱ በመወቃቀስ እውነቱን ማግኘት ስለሚረዳ ለመጪው ትውልድ ታላቅ ትምህርት ስለሚሰጠው ሰዎች ሞተው ሳይሆን ሳይሞቱ ታሪክ ማጥራቱ የደግ ነው ፡፡
በቅድመ አብዮት ዶክተር ሰናይ ልኬ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በደብረዘይት ስለተማረና ፣ አሜሪካ ለትምህርት ሄዶ ከተመለሰም በኋላ የሰናይ ልኬ ታናሽ ወንድምና አንድ የአየር ኃይል መኮንን ሚስት እህትማማቾች በመሆናቸው የተነሳ በተገኘ ቅርርብ ሁኔታ ሰናይ ልኬ ከአየር ኃይሎች ጋር የመቀራረብ እድሉን ስላገኘ ከ 1966 አብዮት በፊት ጀምሮ መኮንኖችን በህዋስ በማደራጀት እንደተጠቀመበት ደራሲው ይጠረጥራሉ ፡፡ ዶ/ር ሰናይ ጀብደኛም ጭምር በመሆኑ በአንድ ወቅት ፣ በሃገር ሰላም ስም ኡዚ ተሸክሞ የሚዞር ጠመንጃ ነካሽ ግለሰብ ነበር፡፡ ከዕለታት አንዱን ቀን ንጉሱ የመገናኛ ሚንስቴርን ህንጻ ሲጎበኙ እንደ አጋጣሚ ሠናይ ልኬ ፖስት ራንዴቩ አካባቢ ነበርና ሲያያቸው ለጓደኞቹ ኡዚውን እያገለባበጠ « ይቺን ሽማግሌ መግደል ለካ ቀላል ነው! እያለ ሲጋበዝ እንደነበር በወቅቱ አብረውት የነበሩ ሰዎች አጫውተውኛል ይላሉ ደራሲው ፡፡
ደርግና ሶሻሊዝም
ደርግ ጊዚያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ተቋም ከመሆኑ በፊት እነማን ያማክሩት እንደነበረ ባይታወቅም በተለይ ግራ ዘመምነቱን ይፋ ካደረገ በኋላ በ 1968 ዓ/ም የህዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ/ቤትን በሟቋቋም ልዩ ፥ ልዩ መምህራን በይፋ በመሰብሰብ መሥራቱ እውን ነው ፡፡ ምክርም ከነርሱ እያገኘ እነርሱ የመረጡትን ሥርአት ማራመድ መጀመሩም ግልጽ ነበር ይሉናል ደራሲው ፡፡ ኢትዮጵያ በህዝባዊ ዲሞክሪያሳዊ አብዮት በኩል ወደ ሶሻሊስት አብዮት እንደምታቀና ወታደራዊ ደርጉ ይፋ ያደረገውም በነዚሁ በህዝብ ድርጅት ጽ/ቤት ምሁራንና ፈር አስያዥነት ነበር ማለት ይቻላል ይላሉ ደራሲው፡፡
የኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት ጣኦስ/ peacock ምልኪ
በደርግ ስብስብ ውስጥ በጣት የሚቆጠሩ እስልምና ወይም ክርስትና ተከታዮች ሊኖሩ ቢችሉም አብዛኞቹ ኃይማኖትን እንደአስፈላጊነቱ የሚጠቀሙ አልፈውም በራዕይና በህልም የሚያምኑ ሰዎች ነበሩት ፡፡ የመጽሃፉ ደራሲ በተገኙበት ኮለኔል ደበላ ዲንሳ ደርግ የተመሰረተበት ሰኔ 21 ቀን በቤተ መንግሥት ሲከበር ጃንሆይን ለማውረድ ቤተ መንገሥት በሄዱ ጊዜ የደረሰባቸውን ቆመው የተናገሩትን እንዲህ ያወሱታል ደራሲው ፡፡ ኮለኔል ደበላ በተሰጣቸው ትዛዝ መሰረት ከ4ኛ ክፍለጦር ተነስተው ወደ ኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት ቡድኑን እየመሩ ሲደርሱ በስፍራው መገኘት የነበረባቸው ጋዜጠኞች ቡድን በሰአቱ ስላልደረሰ መጠበቅ ነበረባቸውና እየተንጎራደዱ ግቢው ውስጥ የነበሩትን አቦ ሸማኔና ጣዎስች / ፒኮክስ መጎብኘት ይጀምራሉ ፡፡በጉብኝቱ ላይ አንዷ ጣኦስ እየተገለባበጠች የሆነ ጂምናስቲክ ትሰራለች ፡፡ ደበላ ዲንሳ የጣዎሷ ሁኔታ ጥሩ ሚልኪ/ ገድ እንዳልሆነ ነፍሳቸው ይነግራቸውና ጥበቃ ላይ የነበረውን የክብር ዘበኛ ጠጋ ብለው ወፏ ምን ሆና ነው ? ብለው ይጠይቁታል ፡፡ያው እንደሚያዩዋት ትገለባበጣለች ይላቸዋል ፡፡ ሁልግዜም እንዲሁ ታደርጋለች ? ይሉታል መልሰው በጥርጣሬ ፡፡ኧረ ፈጽሞ ያለ ዛሬ እንዲህ ስትሆን አይቻት አላውቅም ይላቸዋል፡፡ እሳቸውም ይመልሱና ታድያ ዛሬ እንዲህ የምትሆነው በምን ምክንያት ይመስልሃል ? ብለው መልሰው ይጠይቁታል – እኔ እንጃ ብቻ ዛሬ አንድ መጥፎ ነገር ይኖራል ብዬ እገምታለሁ ይላቸዋል ፡፡በዚህ ጥያቄና መልሱ ይቆምና በድንጋጤ እነኚህ ሰዎች እኔን እንደዚህ ያለ እሳት ውስጥ የሚከቱት በምን ምክንያት ነው እያሉ ከራሳቸው ጋር ሲሟገቱ የዘገየው የጋዜጠኞች ቡድን ደርሶ ይገላግላቸዋል ፡፡ ወዲያው ቤተመንገሥት ንጉሱ ጋር ቀርበው ካስረዱ በኋላ ንጉሱን ይዘው ወደ አራተኛ ክፍለጦር ይሄዳሉ ፡፡
ፕሬዝዳንት መንግሥቱም ንጉሱን ይዘው እንዲመጡ የተላኩት ሰዎች ከተጠበቀው በላይ በመዘግየታቸው ደንግጨ መታጠቢያ ቤት ገብቼ ምርር ያለ ጸሎት ለእግዚአብሄር አቀረብኩ ፡፡ ልመናዬንም ሰምቶ ነው መሰለኝ የተላከው ቡድን ንጉሱን ይዞ በሰላም ተመለሰ ሲሉ ሰምቻለሁ ይላሉ ደራሲው ፡፡ ደርግ ሶሻሊዝምን እንደ ስርአተ ማህበር ከልብ አምኖበት የተቀበለው ስራት ያለመሆኑን የሚያሳየው ደግሞ በአብዮቱ አፍላ አመታት ሶሻሊዝምና ኮሚኒዝም የሚል ቃል በማንኛውም የመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣ ፥ ሬድዮና ቲቪ እንዳይነሳ አደራ ጭምር ለደርግ ማስታወቂያና መረሃ ብሄር ሚንስቴር በጽሁፍ ትዛዝ ማገዱ ነበር ፡፡ እንዲያውም የሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 64/68 የታወጀው ኢህአፓ ሠራተኛውን የምትቀሰቅስበትን የህብረተሰባዊነት ጥሪ ከአፋቸው ለመንጠቅ የተጮኽ ጩኽት እንጅ ለአሰሪውም ለሰራተኛውም ያልበጀ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ በጅጉ የጎዳና የሠራተኛውን የሥራ ሥነ- ምግባር ያበላሸ አዋጅ ቢሆንም ደርግ ደጋፊዎቹን ለማብዛትና ተቃዋሚዎቹን ለመሸርሸር ነጋሪት የመታበት አዋጅ ነበር ይሉናል ደራሲው ፡፡
ሶስት መቶ አምሳ አንድ ገጽ የያዘን መጽሃፍ ታሪክ ለተደራሲው ካነበብኩት ለማቋደስ አይቻልም ፡፡ የመጽሃፉ ደራሲንም ድካም እጅ ሰባራ ላለማድረግ ይህን ስንት ያልተሰማውን ጉዳጉድና የአብዮቱን ታሪክ ፣ በደርግ መንገስትም ውስጥ ወያኔ አሰርጋ አባላቶቿን ገብታ ከኮለኔል ተስፋዬ ወልደ ስላሴ ጋር የሰሩትን ደባ ሁሉ መጽሃፏ ግልጥልጥ አድርጋ የምታስነብበን ሲሆን ፣ በስተመጨረሻም ደራሲው በወያኔ በተማረኩ ጊዜ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስቴር ታምራት ላይኔ በምርኮው ወቅት ይዛቸው የምትሄደውን የሴት ተጋዳሊት ማን እንደሆነ ጠይቋት ? የኢሰፓ ሰው እንደሆነ ለታምራት ስትነግረው ታድያ ምን ይዘሽ ታዞሪዋለሽ ወደ ገደል ወስደሽ ድፊው ብሏት እንደሄደና በዚያ ሁሉ ሁኔታ አልፈው ዛሬ ይህን መጽሃፍ እንደጻፉ ደራሲው ያወጉናል ፡፡ ወያኔ በሽሬ ላይ ያለውን ሠራዊቷን የኢትዮጵያ ሠራዊት ሙልጭ አድርጎ ከጨረሰባት በኋላ እጅ መስጠት በደረሰችበት ወቅት የሻብያ ጦር ደርሶ ከልቂት እንዳዳናት ሁሉ መጽሃፉ ይገልጻል ፡፡ ዛሬ በተገላባጭ ወያኔ የምትነግረን ተራራ የማንቀጥቀጥ ድርሰቷ በሻብያ ድጋፍ እንጂ ለሚኒልክ ቤተ መንግሥትም እንደማይደርሱ ነው ክመጽሃፉ የምንረዳው ፡፡
ለማጠቃልል ደራሲው በአስራ ሰባቱ አመታት የደርግ የመጠፋፋት አብዮት ውስጥ ተዋንያን የነበሩ ሰዎችን ታሪክ የሞቱትንም ሆነ በህይወት ያሉትን እንደየሥራቸው ደካማነታቸውንም ሆነ ብርታታቸውን በራሳቸው በደራሲው ላይ ጭምር ወደ ሞት ሸለቆ እንዲነዱ ሸር የጎነጎኑባቸውን አሁን በህይወት ያሉትም ላይ ሆነ ባለፉት ላይ ይህን አድርገውብኝ ነበር በሚል የባህላችን ጥላቻ አካሄድ ሳይሄዱ የሰዎቹን ጠንካራ ችሎታ በግልጽ የገለጹበት ፥ ክፋታቸውንም ሳይሸሽጉ ያሳዩበት መጽሃፍ ነው ፡፡ ይህ መለመድ ያለበት ነገር ነው ፡፡ ደራሲው ባነሷቸው ጉዳዮች ላይ በህይወት ያሉት እውነት ውይም ዉሸት ብለው በጽሁፍ እንደሚያስነብቡን ተስፋ አለን ፡፡ ይህ መጽሃፍ በብዛት ሳይሆን በአነስተኛ ቁጥር ለስዎች እንደደረሰ ተረድቻለሁ ፡፡ ደራሲው በብዛት አሳትመው ወደ ህዝብ ቢያወርዱት ባገራችን ላይ የወረደውን መአት አንባቢው ህዝብ ተረድቶ ህዝቡ እንደየሃይማኖቱ ምህላ ይዞ ፥ ወይም ማስተሰርያ ክብት አርዶ ለአንዴና መጨርሻ ያን ከመሰለ የመተራረድና በተዋረድም እየደረሰብን ካለው አገር የማጣት እንቅስቃሴ ይገላግለን ዘንድ እመኛለሁ ፡፡