ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመፍጠር የተቃዋሚዉ ጎራ ልብ መቼ ይፈታል? – ሸንቁጥ አየለ 

በርካታ ተቃዋሚዎች ገዥዉንና አምባገነኑን ኢህአዴግን ለዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ አለመፈጠር ይወቅሳሉ:: ሆኖም ገዥነት ወንበር ላይ ቁብ ያለ አምባ ገነን ሀይል መግዛት ስለሚጣፍጠዉ የያዘዉን ወንበር ይዞ ለመቀጠል ሁሉንም ብልጠት የተሞላባቸዉን ነገሮች ማድረጉ አያስደንቅም:: የሚያስደንቀዉ ግን ተቃዋሚዎች በጋራ ሆነዉ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ትፈጠር ዘንድ ተባብረዉ ለመስራት ልባቸዉ አርባ አመት ሙሉ መቋጠሩ ነዉ::

እናም የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች የተቋጠረ ልብ በደንብ ሲመረመር ያስገርማል:: ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በጋራ ለመፍጠር የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ልብ ከጠቆረና ከተቋጠር ይሄዉ 40 አመታትን ፈጀበት:: አንዲት ሀገር ዲሞክራሲያዊት ስትሆን ሁሉም ሀሳቦችን: ሁሉንም ቡድኖችን: ሁሉንም የፖለቲካ ድርጅቶችን: ሁሉንም አይነት የመብት ጥያቄዎችን የማንሸራሸር ብሎም የመመለስ አቅም ይኖራታል::

ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊት ሆና ብትመሰረት የሁሉንም የቋንቋ ጥያቄዎች: የአስተዳደራዊ መዋቅር ጥያቄዎች: የፖለቲካ ፓርቲዎች አስተሳሰብ ማንሸራሸሪያ መድረክን የመመለስ አቅም ይኖራታል:: የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ልብ ግን ዘላለሙን ይሄን ቀላል የዲሞክራሲ ትርጉም አልረዳ ብሎ ለአምባገነነት ህጋዊ ሽፋን እየሰጡ ይኖራሉ::

የየጎሳዉ ፖለቲከኞች ከሌላዉ ጎሳ የተለዬ ምን የዲሞክራሲ ጥያቄ አላቸዉ? እንደ እዉነቱ ምንም የተለዬ ጥያቄ የላቸዉም::ሁሉም የኢትዮጵያ ማህበረሰብ በለዉ : ጎሳ በለዉ; ብሄር በለዉ ወይም ህዝብ በለዉ ጥያቄ አንድ ነዉ:: ይሄዉም ዲሞክራሲ ብቻ ነዉ::

የኦሮሞ ህዝብ ከአማራ ህዝብ የተለዬ ምን የዲሞክራሲ ጥያቄ አለዉ? የሲዳማ ህዝብ ከሶማሌዉ ህዝብ ምን የተለዬ የዲሞክራሲ ጥያቄ አለዉ? የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ ህዝብ መሰረታዊ የዲሞክራሲ ጥያቄዉ አንድ ነዉ:: የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ግን በጋራ በዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ፈጠራ ዙሪያ ለመስራት ገና ልባቸዉ እንደተቋጠረ ነዉ::

ልባቸዉም ተቋጥሯልና ለየብቻቸዉ በመሮጥ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ እያሉ ሲተናነቁ ለአምባገነንነት የህጋዊነት ሽፋንን በደንብ እየሰጡ ይኖራሉ:: አንድም እርስ በእርስ ይጠፋፋሉ:: ወይም አንዱ ተቃዋሚ ሲታሰር አንዱ ከበሮ እየደለቀ ወደ ምርጫ ይገባል:: አንዱ ሲበደል አንዱ ያደፍጣል:: አንዱ የምርጫ ዉጤቴ ተነጠቀ ሲል አንዱ ዝም ይላል::

አንዱ ከምርጫ ሲወጣለት አንዱ ተሽቀዳድሞ ከምርጫ የወጣዉን አባላት ለመሰብሰብና በአንዱ ፓርቲ ኪሳራ አንዱ አትራፊ ለመሆን አፍንጫ ስር የሆነ አስተሳሰብ ዉስጥ ይወሸቃል:: እንዲሁም በፍጥነት በቡድን ተቧድነዉ ለመለያዬት ደባ ይጎነጉናሉ:: አለዚያም ተባበሩ ሲባሉ ሰበብ እየደረደሩ እርስ በእርሳቸዉ አስር ቦታ ጠምደዉ ያደባሉ::

ተጨማሪ ያንብቡ:  የታሪክ አዙሪት? (ከአሁንገና ዓለማየሁ)

አንዴ በብሄር ሲያሰሉ: አንዴ በዘመነ መሳፍንት ፈረስ ላይ ተቀምጠዉ ወንዝ ሲቆጥሩ: ሌላ ጊዜ በኢትዮጵያ አፈጣጠር ላይ ላባቸዉ እስኪንጠባጠብ ከበሮ እየደለቁ ከንቱ ጉዳይ አንስተዉ እየፈተፈቱ ሲለያዩ : እንዲሁም አንዱ እራሱን ብቻ ጀግናና አዋቂ በማድረግ ሌላዉን በካልቾ ብሎ ስለመጣል ሲያዉጠነጥን ይሄዉ አርባ አመታት ሙሉ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መፍጠር ተስኗቸዉ እርስ በእርስ ይጓተታሉ::

ሌላዉ ቀርቶ በሰለጠነዉ እና ዲሞክራሲ በገባዉ አለም ሄደዉ እየኖሩም የዲሞክራሲ ትርጉም አልገባ ብሏቸዉ በጎሳና በመንደር ተከፋፍለዉ ለአምባገነን ስርዓት ህጋዊ ሽፋን ይሰጣሉ:: ዉጭ ሀገር ቁጭ ብለዉ የፖለቲካ ፓርቲ መስርተናል እያሉ በጎን ግን ከአምባገነኑ ገዥ ጋር በዲሞክራሲ ላይ ይደራደራሉ:: አንዳንዱ ምላሱ ስለሀገር ይለፈልፋል:: ሆኖም ህሊናዉ ስለ ግል ትርፉ ያሰላል:: አንዳንዱ ስለዲሞክራሲ ይናገራል:: ሆኖም ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለሁሉም ኢትዮጵያዉያን ከመፍጠር ይልቅ የእርሱ ብሄር እንዴት እንደሚጠቀም ያንሰላስላል::

አንዲት ሀገር ዲሞክራሲያዊት ስትሆን ሁሉም ሀሳቦች ወደ መድረክ መጥተዉ: የሀሳብ ፍጭት ተደርጎባቸዉ : የጋራ ዉሳኔ የሚወሰንባቸዉ መሰረታዊ ጉዳዮችን በጋራ መወሰን መቻል ከዚያም ሌሎች የሀሳብ ልዩነቶችን በመቻቻል ማራመድ እንዲቻል የዲሞክራሲ ማዕቀፍ መፍጠር ጎሳና ዘር: ወንዝና ሰፈር የሚያስቆጥር ጉዳይ አልነበረም:: አንዲትን ሀገር ዲሞክራሲያዊት እንድትሆን ለማድረግ የጎሳ ፓርቲዎችም : የህብረ ብሄር ሀሳብ አራማጅ ፓርቲዎችም በጋራ መስራት መቻል ነበረባቸዉ::

የኢትዮጵያ ህዝብ ድሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለማዬት ዘላለሙን ስለሚጓጓ ለዲሞክራሲ ተባበሩ እያለ ሁሌም በጥልቁ ዉስጥ ሆኖ ይጮሃል::ሆኖም ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ በጋራ የተቃዋሚዎች ትብብር ትፈጠር ዘንድ ተቃዋሚ ተብዬዎቹ ስሌታቸዉ ሁለት ብቻ ሆኖ ይገኛል:: አንደኛዉ ስሌት አንዱ አንዱን እንዴት ዉጦ እርሱ ታላቅና ብቸኛ ፓርቲ ሆኖ እንደሚወጣ ማስላት ነዉ:: ሁለተኛዉ ስሌት ወደ አምባገነን ገዥዉ ጠጋ ብሎ የተሻለ ተቀባይነት ያለዉ ፓርቲ እንዴት መሆን እንደሚቻል ማንሰላሰል ነዉ::

ተጨማሪ ያንብቡ:  አማራን የማሽመድመዱ ዕኩይ ተግባር ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው - አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ)

አንዱ አንዱን ለመዋጥ በርካታ የእርስ በእርስ ትግል ያደርጋሉ:: በርካታ የስም ማጥፋት ዘመቻ ይደረጋል:: የፓርቲ አባላት በወንዝና በጎጥ ይጠራራሉ:: አንድ ቡድን ከአንዱ ፓርቲ ይነጠላል:: ወደ ሌላዉ ቡድን ይዋሃዳል::

አንዱ በኢህአፓነት ብቻ ካለሆነ ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ አይመጣም ብሎ በሚቋቋሙ ፓርቲዎች ዉስጥ እየገባ ስለኢህፓ አሁንም እንዲዘመር ይፈልጋል:: ሌላዉ ስለ መኢሶን ብቻ እንዲወጋለት ይባትታል:: አንድኛዉ ሁሉን ኋላቀር ሲል ኢዴፓን ብቻ ዘክሩልን ይላል:: እንዱ ተነስቶ አንድነት ካልሆነ ሌላዉ ምሁር የለዉም ሲል እንዴት አለምን በእጁ እንዳደረግ ይናገራል:: አንድኛዉ ከመኢአድ ዉጭ ወጥም አይጣድ ጥንሥም አይጠነሰስ የሚል ታሳቢ ላይ ቆሟል:: አንዱ በ40 አመታታ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዉስጥ ከሰማያዊ ፓርቲ በቀር የፖለቲካ ፓርቲ አልተነሳም ሲል እራሱን ብቸኛ ታጋይ አድርጎ የዲሞክራሲዉን ወርቅ ይወስዳል:: አንዳንዱም ኢትዮጵያን ያፈርሱ ሀይሎች ጋር ገና ለገና ተጠግቼ ዱላ ጨብጫለሁ ብሎ ከግንቦት ሰባት ዉጭ ያለዉ ተቃዋሚ ሁሉ ካገሪቱ ይነቀል: ድምጹም በፈጠርነዉ ሚዲያ አይሰማ የሚል አስተሳሰብ ያራምዳል::

የብሄር ፖለቲካ ፓርቲ ነን የሚሉት ደግሞ ዲሞክራሲን በራሳቸዉ ብሄር ዙሪያ አጥረዉ በጋራ ስለመስራት ልባቸዉ ተቛጥሯል:: ህዝባቸዉን በጋራ የዲሞክራሲ አዬር እንዳይተነፍስ ትልልቅ የጥርጣሬ ተራራ ገንብተዉለታል:: በኦሮሞ ድርጅት ስም ወይም በአማራ ድርጅት ስም የተደራጀ ሰዉ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ መጀመሪያ ትፈጠር ዘንድ የጋራ የዲሞክራሲ መሰረት ላይ መስራት ሲኖርበት የሚሰራዉ ልዩነቱና ጥላቻዉ ላይ ነዉ:: ኢትዮጵያ በልዩነት እና በጥላቻ ብትለበለብ የእርሱን ብሄር የማይነካዉ ይመስል ከበሮ የሚደልቀዉ ስለጥላቻ ነዉ::

ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ሁሉንም ኢትዮጵያዉያን በእኩል ማስተናገድ የምትችል ታላቅ መሰረት ላይ የቆመች ሀገር ትሆን ዘንድ በጋራ እየተመካከሩ ከመስራት ይልቅ እንደ ጫዉቴ ዝንጀሮ እኔ ስለዚህኛዉ ብሄር ነዉ የምቆረቆረዉ እኔ ደግሞ ስለዚያኛዉ ብሄር ነዉ የምቆረቆረዉ በማለት አፋፍ አፋፉን ይራወጣል:: ከዚህም የከፋ ድንቁርና በአለም የፖለቲካ መድረክ ላይ ታይቶ አያዉቅም:: ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ማለት ለዚህኛዉ ብሄር የምትመች ለዚያኛዉ ብሄር የማትመች አድርጎ በማሰብ ሁሉም ልቡን ቋጥሮ እርስ በእርሱ ይባላል:: ይጠባበቃል::

ተጨማሪ ያንብቡ:  በሚጠበቀው እና በሚሆነው መካከል ያለው ልዩነት ዜሮ ካልሆነ የእርስ በርስ ጦርነት ያሰጋናል (Expectation - Actual= 0) (የጉዳያችን ማሳሰቢያ)

እና በዚህ መሀል ሀገር በእጁ ላይ የወደቀችለት አምባገነን ሀይል ስልጣኑን ለማን ብሎ ነዉ በፈቃዱ አሳልፎ ለሌላ ወገን የሚሰጠዉ? ይሄ ሁሉ የተቃዉሞ ጎራ እርስ በእርሱ ሊጠፋፋ በድንቁርና በጥላቻ ዉስጥ ታጅሎ ሲተረማመስ አምባገነን የሆነዉና በበላይነት ስሜት የተወጠረዉ ሀይል ስለምን ብሎ ነዉ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲያደርግ የሚጠበቅበት? ወይ ቀልድ !!!

የኢትዮጵያ ህዝብ ተቃዋሚዎች የሀሳብ ልዩነታቸዉን ጠብቀዉ በመከባበር ተባብረዉ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ይፈጥሩለት ዘንድ ከገባበት ጥልቅ አዘቅት ዉስጥ ሆኖ ይጮሃል:: ተቃዋሚ ተብየዎች ግን እንደ ጫዉቴ ዝንጀሮ ለየብቻቸዉ ይራወጣሉ:: የጫዉቴ ዝንጀሮ ባህሪ ምንድነዉ? ነጥቆ መሄድ: የሰዉ ማሳ ማጥፋት: ደግሞሞ ድዱን በሌላዉ ላይ መገልፈጥ ነዉ::

ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመፍጠር ዘርህ: ጎጥህ: ሀይማኖትህ: የፖለቲካ አመለካከትህ: በጎሳ ፖለቲካ ወይም በህብረ ብሄር ፖለቲካ ማመንህ ልዩነት ሊሆንብህ አይችልም:: ምክንያቱም እንያንዳንዱ ልዩነትን መሸከም የምትችል ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ከተፈጠረች ሁሉም ሀሳቡን በዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ማዕቀፍ ዉስጥ ማራመድ ይቻላልና:: በዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ማእቀፍ ዉስጥ ሆኖ ማንኛዉም ቡድን ሁሉንም ሀሳቦች ማንሸራሸርና ማራመድ ይቻላልና::

ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንዳትፈጠር ግን የተቃዋሚ ፖለቲከኞች ልብ ተቋጥሯል:: ባህሪያቸዉም እንደ ጫዉቴ ዝንጀሮ ሆኗል:: ስለሆነም እያንዳንዱ ተቃዋሚ በዚህ ወይም በዚያ መልክ ስራዉ ሁሉ ለአምባገነነት የሚሰጥ የህጋዊነት ሽፋንስ ሆኖ ቀጥሏል::

ተቃዋሚ ለተቃዋሚ ሲደባባና ሲጠፋፋ ወይም ብልጥ ተቃዋሚ የሆነ መስሎት በገዥዉ የጨዋታ ቀመር የተሻለ እስክስታ ወራጅ ሆኖ ለመታዬት ሲባትት ሁሉም ተቃዋሚ በዚህና በዚያ ሲፈስ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በመፍጠር ላይ ከማተኮር ይልቅ አንዱን በመበተን : ያንን በማፍረስ ወይም ደግሞ ከሌላዉ ይልቅ ይበልጥ ተደማጭ ስለመሆን ብቻ በሚቀመሩ ቀመሮች ጉልበትና ጊዜ ይባክናል::

በመጨረሻም ለአምባገነ አገዛዝ ህጋዊ ሽፋን ሰጭ መሆን ይከተላል:: ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንዳትፈጠር የተቃዋሚ ፖለቲከኞች ልብ ተቋጥሯል:: ባህሪያቸዉም እንደ ጫዉቴ ዝንጀሮ ሆኗል::

እናም በኢትዮጵያዉያን ህሊና ጥያቄ ይነሳል:-ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመፍጠር የተቃዋሚዉ ጎራ ልብ መቼ ይፈታል?

1 Comment

  1. Dear Shenqut,
    The article shows the true and real problems of all oppositions of Ethiopian political parties,you hit the nail on the head. They should learn from this article if they need true democracy.God bless you

Comments are closed.

Share