ማለዳ ወግ … በአዲስ አመትም ያላባራው ስቆቃ፣ ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ እነ ልናገረው የከበደኝ ሮሮ !

ከነቢዩ ሲራክ (ጋዜጠኛ)

በግልም ቢሆን አዲሱን አመት በሰላም እና በደስታ መቀበሌ እውነት ነው ! መስከረም ጠብቶ ብዙ ቀናት ሳንቆጥር ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚደርሰኝ የስደተኛ ወገን መከራ ግን ከአዲሱ አመት ዋዜማ ጀምሮ እስከ መባቻው አላባራም … አያንዳንዱን የወገን ስደት ሰቆቃ መከራ ጨክኘ ከመናገር ለመቆጥብ ያደረግኩት ትግል ላንዲት ቀን ቢሳካም ህሊናየ ግን እረፍት አላገኘም ! በተለይ በአዲሱ አመት ዋዜማ “ብሪማን” ተብሎ በሚጠራው የጅዳው ትልቅ ማረሚያ ቤት የደረሰኝ መረጃ ያማል …
ያሳለፍነው ሮመዳን ወር እንደገባ ጅዳ ውስጥ የትዳር ጓደኛውን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሎ በአሳር በመከራ ከተያዘ በኋላ ዘብጥያ የወረደው አዕምሮውን የሳተ ኢትዮጵያዊ ከጤነኛ ታሳሪ ሃበሾች ጋር ነብሰ ገዳይነሰ ከተራ ወንጀለኛ ጋር ደባልቀው በማሰራቸው ደም እንዲፈስ ምክንያት ሆኗል በማለት ታሳሪዎች እያነቡ ገልጸውልኛል ። ይህ ነፍሰ ገዳይ ከአንድ ፍርዱን ጨርሶ በተወካይ ጉትጎታ እጦት ከእምስት ወራት በላይ እስር ይንገላታ የነበረን በእስር ቤቱ ተደብቆ ሲጋራ የሚሸጥን ወጣት ኢትዮጵያዊን ታሳሪ “አንዲት ሲጋራ ለምን አልሰጠህኝም “በሚል ቂም በብረት ዘንግ አይኑን አፍስሶ የመደብደቡ ወንጀል ሊናገሩት የሚከብድ አሰቃቂ እንደነበር ” ተደብዳቢው ከሞት አይተርፍም “ያሉኝ እማኝ ታሳሪዎች በሃዘን ገልጸውልኛል … በአዲሱ አመት ዋዜማ !
በአዲስ አመት መባቻ ዛሬ ምሽት … ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ እና ፍትህ!
ሀገር ቤት የጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ የርሃብ አድማ መምታት ዜና ከአሜሪካ ራዲዮ የግማሽ ሌሊት የሳተላይት ስርጭት እያዳመጥኩ በወጣቷ ጋዜጠኛ የእስር እንግልት ዙሪያ እንደ ዜጋ የሚሰማኝን ለማለት በሃሳብ ላይ ነኝ ፣ ከኮምፒውተሬ ጋር ተፋጥጨ በሃሳብ ከርዕዮት አለሙ አልፊ ከእስክንድር ከውብሸት እና ከአንዷለም የእስር ፈተና ርቄ ፍትህን ፍለጋ ሄጃለሁ …”አሸባሪዎች! ” አልኩ ለራሴ ውስጤ እየተቆጣ ! ግን ዝም አልኩ … ጭጭ … ዝም ! ምን ይባላል !
ወጣቷ ጉብል ትፈታ ግን እላለሁ !

ተጨማሪ ያንብቡ:  አዟሪና አከፋፋዮች ለምን አንድ ለአምስት አይደራጁም? (ጽዮን ግርማ)

ከምሳ የተረፈችንን ራት አድርገን ከባለቤቴ ጋር እየቀማመስኩም ርዕዮትን አስታውሸ ፍትህን ፍለጋ በሃሳብ ነጉጃለሁ … ምሽት ላይ አብረውኝ ሲጫዎቱ ያመሹትን ሁለት ታዳጊ ግረምሳ ልጆችን በአመት በአል ተጠራርተን በአሉን ያደመቁ ዘምድ ጓደኛ ጎረቤቶችን አንዳፍታ ከእን ርዕዮት ጋር አዛምጀ ሳያቸው አመመኝ! በአውደ አመት ከልጅ ወላጅ ወዳጅ ዘመድ ተራርቀው የከረሙ እና እንዲከርሙ የተፈረደባቸው ወንድም እህቶች ጉዳይ በእርግጥም ያሳስባል ያማል! የሰረቀ ፣ የገደለ በምህረት በሚፈታበት ሃገር የህዝብን በሶት በተነናገረ መቀመቅ መውረድ አግባብ አይደለም ማለቱ በዘመኑ ባያዋጣም ፣ ይቅርታ ምህረት ጠይቆ መነፈግ ልብ የሚሰብረውን ያህ ስብራት አጣሁለት! የእነ ርዕዮትን ስቅየት ፣ እስራት! የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ ! ሰላማዊ እርቅ ይበጀናል እላለሁ !
መንገድ ላይ ተጥላ የተገኘችው የኮንትራት ሰራተኛ …
ብዙ ርቄ ስጓዝ ስልኬ አቃጭሎ ከነጎድኩበት ሃሳብ ተመለስኩ … ከአንድ ወዳጀ የደረሰኝ የስልክ ጥሪ አዲሱን አመት ዳግም በአሳዛኝ መረጃ ቅበላ እንድጀምር አስገደደኝ :( እየተኮላተፈ አማርኛ የሚናገር ወዳጁ መንገድ ላይ አንዲት አትዮጵያዊት በአሰሪዎቿ ተጥላ እንዳገኘና ሃበሻ የሚያውቅ እሱን በመሆኑ እንዲረዳት መረጃ አቀብሎት ይህችን እህት እንዴት መርዳት እንደሚቻል” የተሻለ መረጃ ካለህ ” ብሎ ሊያማክረኝ መደወሉን አጫወተኝ! እኔም ከሁሉ አስቀድሞ የጅዳ ቆንስል ሃላፊዎችን እንዲያነጋግር በመምከር አድራሻ ጭምር አቀበልኩት እና በጉዳዩ ዙሪያ አማክሬው ስልኩን ዘጋን …
ወዳጀ በደረቁ ሌሊት መልሶ ደውሎ የደረሰበትን መረጃ አቀበለኝ … ወደ ጅዳ ቆንስል ሃላፊዎች ደውሎ ቆንስል ሙንትሃን በማግኘት ችግሩን አስረድቶ መፍትሔ ጠየቀ ። ከዚያም ቆንስል ሙንትሃ ልጅቱን ወደ ቆንሰሉ መጠለያ በመውሰድ ለመጠለያው ሃላፊ ለወሮ አዜብ እንዲያስረክባት መክረውት ወደ ጅዳ ቆንሰል መጠለያ መሄዱን ገለጸልኝ ፣ በቆንስላው ሲደርስ የተባሉት የመጠለያ ሃላፊም ሆኑ የሚመለከታቸው በቦታው አለማግኘቱን ወዳጀ በአግራሞትና በብስጭት የሆነውን ሁሉ ገልጾልኛል! ለመጠለያውን እና ለኮሚኒቲውን ጠባቂዎች ጉዳዩን በማስረዳት ይህች መንገድ ላይ ተጥላ ያገኟት እህት የቀሩትን ከ140 የዘለቁ ተፈናቃዮች ለመቀላቀል ይቻላት ዘንድ የቆንስል ሃላፊዋን መልዕክትና ቃል ቢገልጹም ከጠባቂዎች ጋር መግባባት አልተቻለም! ይህች ምስኪን እህት ለሃገር ምድሩ ባዳ በሆነችበት ሰማይ ስር መንገድ እንደመጣሏ ወገኖቿ የደረሱላት መሆኑ ቢያስደስትም ወደ መጠለያው ለመግባት ፈቃድ አለማግኘቷ የሰበሳጨው መረጃውን ያቀበለኝ ወንድም እልህ እና ቁጭት እየተናነቀው ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ስልክ ደውሎ እንዲህ ነበር ያለኝ ” አቶ ነቢዩ ዘበኞት አትገባም አሉን ፣ወደ ጅዳው ቆንስለወ ሃላፊ አቶ ዘነበ ደወልን ስልካቸው ዝግ ነው! መልሰን ለቆንስል ሙንትሃ ደወልን ፣ ቅድም ውሰዷት እና ለወሮ አዜብ አስረክቧት ያሉኝ እመቤት ደጋግምን ብንደውልም ስልካቸውን አያነሱም ፣ ምን ማድረግ ይቻላል? ግን … ወገናችን ይህን መከራ ላለማየት እህታችን ሜዳ ላይ አይተን እዳላየን በጭካኔ ጥለን መሄድ ነበረብን ? … ” ብሎ አጠየቀ ! ብዙ ተነጋግረን ስልኩ ተዘጋ … አደንደምንም በግል አስጠግቶ አሳድሮ ነገ የሚሆነውን ለማድረግ ተስማምተን ከተሰነባበትን በኋላ መልሸ አሁንም የደረሰበትን ሁኔታ ለመረዳት ስደውልለት መልካም የምስራች አበሰረኝ ፣ እንዲህ ሲል ” አዎ ተሳካ! የቆንስል ሃላፊዎች ስልካቸውን ማንሳት ባይችሉና የምናደርገው ጠፍቶን ብንንገላታም በፍቃድ ማግኘት ያልቻሉትን ወደ መጠለያ የማስጠጋት ሙከራ ሰው በሰው (በዋስጣ) ይህች አንጀት የምትበላ እህት ወደ ቆንስሉ መጠለያ ልትገባ ችላለች! ” ብሎኛል !
በየሜዳው እየተጣሉ ያሉ የኮንትራት ሰራተኛ እህቶቻችን ከችግር ብዛት እስከ ማበድ ራሳቸውን እስከ ማጥፋት እንዳደረሳቸው እያየን ነው ! ሰብዕናው ቢገደን ገጽታችን እንዳያጠፉት እህቶቻችን ወደ መጠለያ በመሰብሰቡ ረገድ የጅዳ ቆንስል ሃላፊዎች ዛሬም ድምጻችን ሰምተው ሳይሆን ግፉአኑን ከደጃቸው ተመልክተው አንድ ቢሉን መልካም ነው !
የአዲሱ አመት የማለዳ ወግ በመራራው ሮሮ ጀመርኩት …በአዲስ አመትም ያላባራው ሰቆቃ እና ልናገረው የከበደኝ ሮሮ ! አልኩት … ልተንፍሰው በሚል ከብዙ ጥቂቱን ነካክቸ …
ምን ላድርግ ! የአረብ ሃገር ስደት ኑሯችን እንዲያ ሆኗል!
እሰኪ ቸር ያሰማን !
ነቢዩ ሲራክ
መስከረም 2. 2006 ዓ .ም

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሁላችንም የእግዚአብሔር ንብረቶች የሆንን  ሰዎች እንጂ ቋንቋ አይደለንም - መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ
Share