ፋሲል የኔአለም
ገዢዎቹ፣ ቀብረነዋል ያሉት ኢትዮጵያዊነት መልሶ ሊቀብራቸው መሆኑን ሲያውቁ ያወዳድሱት ጀምረዋል። ኢትዮጵያዊነት ከብሄር ፖለቲካ ጋር ፍጹም ተጻራሪ ነው። ኢትዮጵያዊነት የጋራ ታሪክንና ማንነትን መሰረት አድርጎ፣ፍቅርና መቻቻልን እያጎለበተ፣ በጎውን እየያዘ ፣ ስህተትን ደግሞ እያረመ አሁን ካለንበት ደረጃ ደርሷል።
የብሄር ፖለቲካ በተቃራኒው ያጋራ ታሪክን በማፍረስ፣ ጥላቻን በማራገብና አንድን ህዝብ ( አማራውን) የጥላቻ ማእከል አድርጎ ሲገነባ የኖረና በመገንባት ላይ ያለ አፍራሽ ሂደት ነው። የብሄር ፖለቲካ ከመልካም ስራዎች ይልቅ በስህተቶች ላይ ብቻ የሚያተኩር፣ ወደ ፊት ሳይሆን ወደ ሁዋላ መጓዝን የሚመርጥ ለመገንባት ሳይሆን ለማፍረስ ያለመ “ተመላሽ ሂደት” ነው። ኢትዮጵያነትን ተቀብያለሁ ካልክ፣ በጋራ የተሰሩ ታሪኮችን ( በጎውንም ክፉውንም) መቀበል ግድ ይልሃል። የጥላቻ ማእከል ያደረከውን ህዝብ ይቅር በለኝ ልትለውም ግድ ይልሃል። ወደ ሁዋላ የምታየው ወደ ፊት ለመጓዝ እንጅ ወደ ሁዋላ ላለመንዳት መሆኑን አምነህ መቀበልም አለብህ።
ስታንቋሽሻቸው የነበሩትን ነገስታት መልሰህ ስለዘከርክ ብቻ የኢትዮጵያውያንን ልብ አማልላለው ብለህ ካሰብክ ተሳስተሃል። የሚኒልክን ልጆች እየገደለክ፣ ሚኒሊክን ብታወደስ ኢትዮጵያዊነት አይገነባም። የዲነግዴን ልጆች እየገደልክ ዲነግዴን ብታወድስም እንዲሁ። በርግጥም ኢትዮጵያዊነት እምነት ነው፣ ለፖለቲካ ትርፍ ብለህ ሳይሆን ከልብህ አምነህ ልትቀበለው የሚገባ። የዚህ ዘመን ኢትዮጵያዊነት በሂደት የጋራ ታሪክና ማንነትን ከመቀበል በተጨማሪ ሌሎች መስፈርቶችንም ይዞ መጥቷል።
ዜጎች ነጻነት፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ይፈልጋሉ። የሚገድላቸውን ሳይሆን ነፍስና ስጋቸውን የሚያከብር ስርዓት ይፈልጋሉ። የዚህ ዘመን ልጆች ብልጦች ናቸው። እነዚህን መሰረታዊ መብቶች ሳይሟሉላቸው የአባቶቻቸውን ታሪክ ብቻ ስላወደስክላቸው ኢትዮጵያዊ ነው ብለው አይቀበሉህም። ከፊል ኢትዮጵያዊነት ብሎ ነገር አይገባቸውም፤ ያለፈውን ታሪካቸውንና የአሁን መብታቸውን እንድታከብርላቸው ይፈልጋሉ። አንዱን አንስተህ ሌላውን ስትጥል ሲያዩህ ይሳለቁብሃል እንጅ አይከተሉህም።
አሮጌ ስርዓት አሮጌ ነው፤ አዲስ አስተሳሰብን መቀበል አይችልም። አዲሷ ኢትዮጵያ ደግሞ ወደፊት በሚወለድ ስርዓት እንጅ እየሞተ ባለ ስርዓት ላይ አትገነባም።