ጅብ በማያውቁት ሃገር ሄዶ ቁርበት አንጥፍሉኝ አለ | ከገብረመድህን አርአያ

ኢትዮሚዲያ በ26/09/2016 ከግደይ ዘርአፅዮን ጋር ያካሄደውን ቃለ ምልልስ አንብቤዋለሁ። ግደይ ዘርአፅዮንን የማውቀው ገና ትግሉ ሳይጀመር በፊት ነው። ግደይ በጥሩ ቤተሰብ ያደገ ግለሰብ ነው። ትገሉ ሳይጀመር በመስከረም 1967 አዲስ አባባ ውስጥ ማገበትን መሰረቱ። የመሰረቱትም አረጋዊ በርሄ፣ ገደይ ዘርአፅዮን፣ አባይ ፀሃየ፣ ሥዩም መስፍን፣ ዘርኡ ገሰሰ፣ ሃይሉ መንገሻና አስፍሃ ሃጎስ ናቸው። ከዚያ በኋላ እነ መለስና ስብሃት ወዘተ. ተቀላቀሉ። ግደይ ስለእኔ፤ ገብረመድህን፤መስራች አልነበረም ብሎ ነው የተናገረው። ያለው ትክክል ነው፤ እኔ የማገበት – ተሓህት መስራች አልነበርኩም። ማገበት እንደተመሰረተ በተራ አባልነት ተመልምዬ ከማገበት ጀመሮ ትግሉን ለማጠናከር ስንቀሳቀስ የነበርኩ ተራ አባል ነበርኩኝ እንጂ መስራች አይደለሁም። ስለ ተሓህት – ህወሓት ማንነትን ግን ከግደይ ዘርአፅዮን ያላነሰ እውቀት አለኝ። ልክ እንደ እኔ፣ በወቅቱ የነበርው ታጋይ የህወሓትን እኩይ ሥራ ያውቃል። የህወሓት አመራር ፀረ-ኢትዮጵያ፣ ዘረኛ፣ የአማራውን ዘር ለማጥፋት የተነሳ ወዘተ መሆኑን አስምሮበት ያለፈ ታጋይ ነው።

በትግርኛ አንድ ተረት አለ። እሱም “መባእያ እንዳ አባገሪማ ዝበለእስ ባእሉ ይለፋለፍ” ይባላል። ይህ ማለት፣ የአባ ገሪማ መባእ፣ የሰረቀ ሌባ ራሱ ይናዘዛል እንደማለት ነው።
ግደይ ዘርአፅዮን ትልቅ ትኩረት የሰጠው ከኢሳት ሰብአዊ መብት ተሟጋች ESAT Human Rights, May 13, 2016 –May 15, 2016 ባካሄድኩት በሁለት ክፈል ኢሳት ባስተላለፈው ቃለ ምልልስ፣ ስለ 06 ሓለዋ ወያኔ ሁኔታ ነበር። 06 ሓለዋ ወያኔ የገዳይ ማእከል ነው። በዚሁ ቃለ ምልልስ ላይ እኔ ገብረመድህን አርአያ፣ የነበሩ ሓለዋ ወያኔ ብዛት ከመሬት በታች ሁለት ሜትር ተቆፍሮ፣ ነፋስ መግቢያ የሌለው ማጎሪያ ውስጥ ስለተገደሉት፣ ትግሬና አመራ መሆናቸውን በዝርዝር የገለጽኩበት ቃለ ምልልስ ነው። ግደይ ዘርአፅዮን ከኢቲዮ ሚዲያ ጋር ባካሄደው ቃለ ምልልስና በጽሁፍም የተዘረጋው ባጣም አንዶታል፣ ክንክኖታልም። በዚህም ምክንያት ይመስላል ብዙ ስድቦችን አውርዶብኛል። ግደይ የተናደደበት ዋናው ምክንያት፣ ምስጢራችንን በዝርዝር አውጥቶ አጋለጠን ብሎ ነው። ይህም ይመስላል ወደ ተራ ስድብና ውሸት የከተተው። የትግራይን ሕዝብ አጸያፊ ስድብ ተሳደበ ብሎም ወንጅሎኛል። እኔ ማን ሆኜ ነው የትግራይን ወላጆችና ወንድሞቼን የምሰድበው? ሃቅ ነው ካለስ፣ የተሳደብኩትን ስድብስ ለምን አልተናገረም? ግደይና ግብረአበሮቹ የህወሓት አመራር የትግራይ ሕዝብ ፊውዳል፣ ሸዋዊ አማራ ትግሬ፣ ፀረ- ህወሓት ወዘተ እያላችሁ የገደላችሁት አንተና ጓደኞችህ አልነበራችሁም ?እኔ የነበሩትን፣ 06 ሓለዋ ወያነ፣ በነሱ ውስጥም ስንት የሰው ፍጡር፣ አማራና ትግሬ – አማራው በዝቶ የተገደለበት – ቦታዎች መሆናቸውን ነው በትክክል የገለጽኩት። ቅንጣት ውሸት አልጨመርኩበትም። ግደይ ከፈጸመው ውንጀል ነፃ የሚወጣ መስሎታል። እውነት በውሸትና በማስመሰል አትጣጠፍም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በፊደራል ደረጃ  ልዩ ትኩረት የተደረገበት  የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፣ የ 2015 ዓ/ም የ12ኛ ክፍል መልቀቅያ  ፈተና ልዩ መረጃ  -  በመኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

ግደይ ዘርአፅዮን ሲናገር፣ 06 ሓለዋ ወያኔ ከመሬት በታች ሁለት ሜትር መሆኑን በቃሉ አምኖበታል። ማመኑ ጥሩ ነው። ነገር ግን ዋሻም እንጠቀማለን ያለው ውሸት ነው። ይህንንም የምናደርገው የጦር ቀጠና ስለሆነ ነው ብሏል። ይህም ትክክል አይደለም። የህወሓት አመራር ሰውን ነፋስ በማይገባበት ጉድጓድ ውስጥ እያሸጉ የስንት ንጹሃን ኢትዮጵያዊያኖችን፣ ህፃን፣ ሽማግሌ፣ ወጣት፣ ወንድ፣ ሴት፣ እርጉዞችን ጭምር አጥፍተዋል፣ ግድለዋል። ሲፈጸም የነበረውንም ቶርቸር አንተ ራስህ፣ ግደይ ዘርአፅዮን፣ ቡምበትና ሱር ሓለዋ ወያኔ የፈጸምከውን ዘግናኝ ግድያ አምነህ መቀበል ይኖርብሃል። ኢትዮጵያን ለችግር ይዳረጋችኋት አንተና አረጋዊ በርሄ ናችሁ። በአማራው ላይ በዘር ማጥፋት ወንጀል የተሰማራችሁት አንተና ጓደኞችህ መሆናቸውን አምነህ ተቀበል።
ስለምርኮኛዎችም ተናግረሃል። መናገርህ ጥሩ ነው። የነበሩት ምርኮኞች ከሻእቢያ የመጡ ናቸው እንጂ ተሓህት -ህወሓት የማረካቸው አልነበሩም። አሻግራችሁ ወደየመጡበት ሸኙአቸው እየተባለ ተሓህት – ህወሓት እየተቀበላችሁ ትገድሏቸው ነበር። ይህንንም ሁሉም የድርጅቱ ታጋይ በወቅቱ የሚያውቀው ሃቅ ነበር። ግደይ፤ ታጋቅዮች በአይናቸው ያዩትን እና የተናገሩትን ሃቅ በአንተ በኩል በዚያ ወቅት የፈጸምከውን ላንሳልህ፡፡ 300 (ሶስት መቶ) ከሻእቢያ በህዳር 1971 የተላኩትን ምርኮኞች ምን ፈረድክባቸው? በጥይት ተረሽነው እንዲገደሉ አደርግሃቸው። ለዚህም በውጭ ሃገር የሚኖሩ በርካታ የቀድሞ ታጋዮች የዓይን ምስክሮች አሉ። የተረሸኑትም ሌላ ሃጢያት ሳይኖራቸው አማራ በመሆናቸው ብቻ ነው።

እናንተ የህወሓት አመራሮች የፈጸማችሁት ስንት ከባድ ወንጀል ተሸፋፍኖ እያለ፣ ይፋ ከሆነ የሚገጥማችሁ እስራት ብሎም ግድያ ይጠብቀናል በሚል ፍርሃቻ አካላችሁ ስለተወረረ፣ ከዚያ ለመላቀቅ ጥፋታችሁን ለሕዝብ ተናዛችሁ ይቅርታ ብትጠይቁ ይሻላችሁ ነበር። ግደይ፣ እኔ ፖሊት ቢሮ ስለነበርኩኝ የምናገረው ሁሉ ተአማኒነት አለው ብለህ ታስባለህ፣ ግን ስተሳስተሃል። ህወሓት ለምርኮኞች ብዙ እንክብካቤ ሲያደርግ እንደ ነበርም ተናግረሃል። የተናገርከው ግን ሙልጭ ያለ ውሸት ነው። ህወሓት የዚህ ዓይነት ባህሪ የለውም።

ግደይ ሲናገርም ገብረመድህን የትግራይ ሕዝብ አማራን ይጠላል ይላል ብሏላ። እኔ የምናገረውን አውቃለሁ። ግደይ የዘነጋው ነገር ግን አለ። ተሓህት – ህወሕት ገና ከጅምሩ በየቦታው እየተንቀሳቀሰ አማራ የትግራይ ሕዝብ ደመኛ ጠላት ነው እያላችሁ ስትሰብኩ እንደነበር የማይካድ ሃቅ ነው። ለዚህም የትግራይ ሕዝብ የሰጣችሁን መልስ አትዘነጋውም። ላስታውስህና፣ የትግራይ ሕዝብ ያለው አማራ ጠላታችን አይደለም፣ ወንድማችን፣ ደማችን፣ አጥንታችን፣ ኢትዮጵያዊ እንጂ ነው ያለው። ለትግራይ ሕዝብ የውሸት ስም እየሰጣችሁ፣ ትግራዋይ ሸዋዊ ብላችሁ፣ በምክንያት ስንት ሺዎች የትግራይን ሕዝብ ገድላችኋል፣ ንበርቱን ዘርፋችኋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሕወሐትና የኢትዮጵያ ጦርነት  - አንድነት ይበልጣል - ሐዋሳ

በየካቲት 1968፣ ተሓህት – ህወሓት፣ ፕሮግራሙን ሲያሰራጭ የትግራይ ሕዝብ አንቀበልም በማለቱ በተከታታይ እያሳደዳችሁ በመግደል ወንጀል ፈጽማችሁበታል። በሓለዋ ወያኔ 06 እያሰራችሁ ፍዳውን አሳይታችሁታል። ፈዳያን አጥፍቶ ጠፊ አሰማርታችሁ የከተማውን ሕዝብ እየገደላችሁ ደሙ በየፒያሳው መጠጥ ቤት እንዲፈስ አድርጋችኋል። ይህንን የፈጸማችሁት ደግሞ፣ አረጋዊ በርሄ፣ ግደይ ዘርአፅዮን፣ አባይ ፀሃየ፣ ስብሃት ነጋ፣ ሥዩም መስፍን እና መለስ ዜናዊ ናችሁ። ምስክሬ የትግራይ ሕዝብ ነው።

ይህንን ሁሉ ግፍ ሲያስፈጽም የነበርረው ግደይ ዘርአፅዮን ለትግራይ ሕዝብ ተቆርቋሪ መስሎ የትግራይን ሕዝብ ሰደበ የሚለኝ፣ ስሰድብ የተቀረጸ የድምጽ ምስክርነት ካለው ያቅርብ። ኢሳትም ይህን ብለህ ነበር ብሎ በማለት ለሕዝብ ያጋልጠኝ። የትግራይን ሕዝብ የጨፈጨፈ ግደይ እንጂ እኔ አይደለሁም። ግደይ ዘርአፅዮን በኢሳት ላይ ባለው ጥላቻ ኢሳትን ውሽታም እያለ በሰው ሕዝብ ያሰድባል ማለቱ በጣም አስገራሚ ነው። ኢሳት ሕዝብን የሚሳደቡ ማሰባሰቢያ የመገናኛ ብዙሃን አይደለም። ግደይ ኢሳት ለኢትዮጵያ ሕዝብ የቆመ ሚዲያ መሆኑም አልተረዳውም። ኢሳትን መስደብና ማንቋሸሽ የኢትዮጵያን ሕዝብ መስደብና ማንቋሸሽ ነው። አሁንም እንደዱሮው በሕዝብ ላይ ያለው ንቀት አልለቀቀውም።

ግደይ ዘርአፅዮን ስለወልቃይት ሲናገር እንዲህ ብሏል፣ “ትግሉን ስንጀምር ትግራይ የሚባለው ያኔ የትግራይ ጠቅላይ ግዛት የነበረው ከአለወሃ መለስና ወልቃይት ያለው ትግርኛ ተናጋሪ የሚኖርበትን ያጠቃለለ ነው” ይላል። (ሰረዙ የኔ ነው)። እንዲህ ብሎ መናገሩ ከእውነት የራቀ ነው። ያልነበረውን ነበረ ማለት ያልተላቀቀውና ያደገበት የህወሓት መርህ ነው።

ግደይና ጓደኞቹ በረሃ ከመውጣታቸው በጣም ቀደም ብሎ፣ ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት፣ ስቲት ሁመራ፣ በጎንደር ጠቅላይ ግዛት፣ በተከዜ ወንዝ ድንበርነት አማራ መሆናቸው በታሪክ የተረጋገጠ ነው። አለወሃ መለስ ወልዲያ፣ ራያና ቆቦ፣ አፍላደራ ወዘተ በወሎ ጠቅላይ ግዛት ውስጥ መሆናቸው ታሪክ ያረጋግጣል። ግደይ ዘርአፅዮን የወልቃይት አማራን በሁለት ከፍሎታል። ትግርኛ ተናጋሪ ወልቃይትና አማራ ተናጋሪ ወልቃይት በማለት ሰንጥቆታል። በታሪክም ሆን በአፈ ታሪክ ይህ አይነቱ አነጋገር ተሰምቶም አያውቅም። የወልቃይት ሕዝብ አማራ እንጂ ትግሬ አይደለም። ግደይ ስለሬፈረንደምም ለመዘባረቅ ሞክሯል። ጠገዴ አንተና የወያኔ መሪዎች በጉልበት ነጥቃችሁ ዘሩን እያጠፋችሁት እያለ፣ አንተ በምትቀባጥረው አይነት ሳይሆን ነገ ሕዝቡ በፈለገውና በመረጠው ዘዴ ማንነቱን ያስከብራል፣ መሬቱንም ወደቀድሞው ይዞታው ያስመልሳል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኮረና በኢትዮጵያ ከባድ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ሁሉም ያስብበት – ሰርፀ ደስታ

ግደይ ይህን ሃሳብ ያነሳው የወልቃይት ሕዝብ ለጥቃት ከፋፍሎ እየሰጠው ነው። የአንድን አውራጃ ሕዝብ ለሁለት ከፍሎ ትግርኛ ተናጋሪና አማርኛ ተናጋሪ ብሎ ሕዝብ ላማጋጨትና አለመተማመን እና ጥርጣሬን ለመፍጠር አልሞ የተነሳ ነው። ይህ ደግሞ ወያኔ አሁን የሚጠቀምበት ዘዴ ነው። ታዲያ ግደይና ወያኔ ምን ልዩነት አላቸው? በታህሳስ 1972፣ ህወሓት መሬት ለመውረር በተነሳበት ጊዜ የህወሓት ፖሊት ቢሮ እየተመራ በሕዝቡ ላይ ጦርነት አወጀ። የግል ንብረታቸው በሕወሓት ተወረሰ፣ ተዘረፈ። በዚህም የተነሳ በርካቶች ለስደት ተዳረጉ። በሺዎች የሚቆጠሩም ወደ 06 ሓለዋ ወያነ እየተጋዙ ተገደሉ። የዚህ ሁሉ እልቂትና ዘር ማጥፋት ዋናው ተዋናይ ግደይ ዘርአፅዮን ነበር። አሁንም በአማራው የሚካሄደው የዘር ማጥፋት እንደቀጠለ ነው። የመሬት ወረራ በተጀመረበት ወቅት ግደይ ዘርአፅዮን የመጀመሪውያው ፖሊት ቢሮ ም/ሊቀመንበር ነበር። የሓለዋ ወያኔ እስር ቤቶች ሁለት ሜትር ወደ መሬት ጠልቀው እንዲሠሩ ትእዛዙን ያስተላለፈ መሪ ነበር። በትእዛዙም መሠረት ተፈጸመ። ነፋስ መግቢያ የሌለው፣ እርጥብ እንጨት “ዓየ” ተብሎ የሚታወቅ ዛፍ እየተቆራረጠ በማቃጠል ጪስ እየተለቀቀ የአማርውና የትግሬው ሕዝብ በአየር እጦት እየታፈነ አልቋል። የዚህም ፈላስፋግደይ ዘርአፅዮን ነበር።

ገደይ ወልቃይት ስንገባ ሕዝቡ አልተቃወመንም ብሏል። ይህ አነጋገር ቅንጣት ያህልም ሃቅነት የለውም። የወልቃይት ጠለምት ጠገዴ ሕዝብ ወራሪ መጣብን ብሎ እልህ አስጨራሽ በሆነ መልክ መሳሪያ አንስተው ፀረ ወያኔ ትግል ማቀጣጠላቸው በጋሃድ ይታወቃል። ከፋኝ የሚባለውና ህወሓትን ያስጭነቀው ፀረ-ወያኔ ድርጅት የተፈጠረውም በዚያ ጊዜ ነበር።
ግደይ ዘርአፅዮን የፖሊት ቢሮ አባል ሆኜ እንኳን ስለ 06 ብዙም የማላውቀው ነገር አለ ብሏል። ታዲያ የህወሓት ፖሊት ቢሮ ም/ሊቀመንበር ሆኖ ሳለ ድርጅቱን በሞግዚትነት ነበር የሚያስተዳድረው? (ይቀጥላል)
የመሪዎቹ ስም ዝርዝርና ገበናቸው ቀጥሎ ይቀርባል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ ገብረመድህን አርአያ 02 ኦክቶበር 2016

Share