ካልፎሂያጁ ማስታወሻ የተቀነጨበ (በ.ሥ)

አሪፍ የፍቅር ግጥም ጽፌ ለመለጠፍ አስቤ ነበር፡፡ ግን ብለው ብሠራው “ እኔ እምልሽ ውዴ” ከሚለው ቃል ውጭ ጠብ ሊልኝ አልቻለም፡፡
እኔ እምልሽ ውዴ!
ብለው ሳይጀምሩ- ስለፍቅር መጻፍ አይቻልም እንዴ?
አንዳንድ ባለንጀሮቼ በውስጥ መሥመር ይሄን ድብርታም ዘመን እንዴት እያሳለፍከው ነው ምናምን እያሉ ይጠይቁኛል፡፡ ለጊዜው ቲቪ በማየትና አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ለማሣለፍ እየሞከርኩ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ፤ የመንግሥትን ቲቪ ዜና ስከታተል ፤ የጋዜጠኛውን ዐማርኛ ወደ ራሴ ዐማርኛ በመመለስ ወደ እውነታው ለመድረስ ጥረት አድርጋለሁ፡፡ ለምሳሌ፤
ጸጥታ አስከባሪ= ጸጥ የሚያሰኝ፤ ንግግርን አዋርዶ ጸጥታን የሚያከብር ታጣቂ
ማረምያ ቤት= እሥረኛ እንደ አረም የሚታረምበት ቤት፡፡
አርብቶ አደር= ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ልጅ የሚያስወልድ ገበሬ
አንዳንድ ያዲሳባ ነዋሪዎች= አንዳንድ ያዲሳባ አስ-ነዋሪዎች
ችግሩን ለመፍታት በሂደት እየተንቀሳቀስን ነው=ችግሩ ካቅማችን በላይ ነው፡፡
ገለጹ=ተቀደዱ
ወዘተረፈ፡፡

ዲሼ ላይ ርግብ ጎጆ ሠርታበት ስለተበላሸ ዐልፎ ዐልፎ ጎረቤት እየሄድኩ የቃና ቲቪ እሾፋለሁ ፡፡ ፊልሙን ከማይበት ይልቅ ባልና ሚስቱ በፊልሙ ምክንያት በተጣሉ ቁጥር በመገላገል የማሳልፈው ጊዜ ይበልጣል፡፡ በቀደም ለት ሶፋው ላይ ተደርድረን ፊልም እያየን ሚስትዮዋ “ወይኔ ኦ-ማር! ዛሬ ደሞ እንዴት አባቱ እንደሚያምር!”ስትል፤ ባል ድል በተመታ ድምጽ ”አሁን ይሄ መጥረቢያ ፊት ምኑ ያምራል!”ብሎ ቀወጠው፡፡ ሚስት ምናለች” ኦማርን የሚመስል መጥረቢያ ቢኖር ኖሮ ዛፎች በቆረጣ ሳይሆን በፍቅር ይወድቁ ነበር :: “ ኧረ ሴቱ እንዴት እንዴት ይፈላሰፋል ጎበዝ!ለዚህ አባዋራ ኢትዮጵያ ሶርያ ትሆናለች የሚለው ሥጋት የኦማርን ፊት ያክል አያስጨንቀውም፡፡
አካላዊ እንቅስቃሴ አደርጋለሁ ያልኩት እንኳ ስቀደድ ነው፡፡ በርግጥ አሜሪካ እያለሁ ረጅም እድሜ ለመኖር ስል ባመት ሁለቴ ሮጫለሁ፡፡ የመጀመርያው፤ ፋሲል ደሞዝ በጥቁር ማጅራት መችዎች በተደበደበ ማግስት አምሽቼ ወደ ቤቴ ስመጣ፤ መታጠፊያው ላይ ግብዳ ጥቁር አይቸ የሮጥኩት ሩጫ ሲሆን ፤ ሁለተኛውን ረስቸዋለሁ፡፡ (በማግስቱ ሳጣራ፤ መታጠፊያው ላይ ቆሞ ያስቦካኝ ነገር ወይም ኒገር የማልኮም ኤክስ ሀውልት ኑሯል)፡፡
ያሜሪካ ውስጥ ሩጫ ቢያምርህ የሩጫ መንገድ አለልህ ፡፡ ሳይክል ቢያምርህ የሳይክል መንጃ መንገድ አለልህ፡፡ ቀዘፋ ቢያምርህ ሀይቁ በየደጅህ አለልህ፡፡ አየ!ሰው ካሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ይሰደዳል?
አዲሳባ ውስጥ ሳይክል አይመርህ እንጂ ካማረህ አውሮፕላን ተሣፍረህ ወደ ባህርዳር መሄድ አለብህ፡፡ ስማ! እዚህ ሃያሁለት ማዞርያ ረፋድ ላይ ለመሮጥ ብትፈልግ በየትበኩል ልትሮጥ ትችላለህ፡፡ ትንሽ ሮጥ ሮጥ እንዳልክ መንገድህ ላይ በቆሎ የሚጠብሱ አሮጊት ይገጥሙሀል፡፡ ከነምድጃቸው ዘለሃቸው ታልፋለህ፡፡ ትንሽ ሮጠህ የለማኝ ምርኩዝ ትዘላለህ፡፡ ትንሽ እንደሮጥህ በኮንትሮባንድ የገባ የጫማ ክምር ትዘላለህ፡፡ እንዲህ እየኖርን በመሰናክል ሩጫ ወርቅ አለመብላታችን ይገርመኛል፡፡
በእኛ ሠፈር በእኩልነት ተፈጥረው በኩሊነት እንዲኖሩ የተፈረደባቸው ብዙ ብሄረሰቦችን እናገኛለን ፡፡ እኛ ሠፈር ሰማይ ጠቀስ ፎቅ ለመሥራት የታደለ ጎጄ አይገኝም ፡፡ ግን ብዙ ጎጄዎች ሰማይ ጠቀስ የመጽሐፍ ክምር ተሸክመው ሲያዞሩ ታያለህ፡ያዳም ረታን “ ግራውንድ ፕላስ ዋን” ልቦለድ ተሸክሞ አዲሳባን በግር ማካለል ምን ያህል ከባድ እንደሆነ አስበው፡፡ እንኮኮ የማለት እድሉ ባይኖረኝም ፤ ራሱ አዳም ረታ የመጽሐፉን ያክል የሚመዝን አይመስለኝም፡፡ ለነገሩ ፤ይሄን ሁሉ የሚያናግረኝ ኮምብሌክስ ሳይሆን አይቀርም፡፡ አንባቢ ሆይ !የኔ አምስት መጽሐፎች ተደማምረው፤ ያዳም አንድ ምራፍ በመጠን ሲበልጣቸው ዝም ብየ የማይ ይመስልሃልን??
እኛ ሠፈር ያሉ ብዙዎቹ ፎቆችና ቢዝነሶች የሙስና ውጤት ናቸው ይባላል፡፡ እንዲያውም የኛ ሠፈር መንግስታዊ ሀብታሞች ቅሌት አንድ ሳላስቀር ብዘከዝክ ደስ ይለኝ ነበር፡፡፡ ይሁን እንጂ የሀብታሞቹን ጉድ በዘከዘክሁ ማግሥት “በሃያ ሁለት ማዞርያ ኮንደሚኒየም ሁለተኛ ብሎክ ላይ በትናንትናው ምሽት ምነቱ ባልታወቀ ምክንያት በተነሣው እሣት ቃጠሎ፤ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ፡፡ በጭስ ታፍነውና ተረጋግጠው ለህልፈት ከተዳረጉ ሰዎች መካከል፤ በእውነቱ ሥዩም የተባለ ተከራይ ይገኝበታል፡፡ በዚህ አጋጣሚ መንግሥት ለደረሰው የንብረት ውድመት የተሰማውን ልባዊ ሀዘን ይገልጻል“ የሚል ዜና ለመስማት እንደማትፈልጉ ስለገባኝ ትቸዋለሁ፡ አያድርገውና እኔ ቤት ውስጥ እሣት ቢነሣ፤ የሣት አደጋ መቆጣጠርያ ግብረኃይል ደውየ የምጠራ አይመስለኝም፡፡ ከነበልባሉ አምልጨ ብሮጥ እንኳን የሣት አደጋ መኪናው እስከፒያሳ አባሮ የሚገጨኝ ይመስለኛል፡፡
እኛ ሠፈር ከመንግሥት ጋር ሳይሞዳሞድ ሚሊኒየር የሆነ ሰው ቢኖር ሙሳ ብቻ ነው፡፡ ሙሳ ከሊስትሮነት ተነስቶ እንዴት የአምስት ኮከብ ሆቴል ባለቤት እንደሆነ መተረክ ላንባቢ መነቃቃት የሚፈጥር ይመስለኛል ፡፡ ሙሳ ጫማ እየቀባ አስር አመት ሠርቷል፡፡ አንድ ቀን የናይጄሪያ አምባሳደር፤ ለሙሳ በርሚል እግሩን አሳልፎ ሰጥቶ ጫማ እያስቀባ በመንገድ የሚያልፉ ቆነጃጅቶችን ፈዞ ሲያይ ቆይቶ በዶላር የተሞላ ሳምሶናዊቱን ረሥቶ ሄደ፡፡ ሙሳ ሳምሶናይቱንና ይዞ ካካባቢው ሽል አለ ይባላል፡፡ከሁለት አመት በኋላ ይሄው መለስተኛ ሆቴል ከፍቷል፡፡ ሙሳ ሆቴሉን“ የመለስ ራእይ ሆቴል ”ብሎት ነበር፡፡ ባለፈው አመጹ ሲበረታ የሆቴሉ ስም“ የዮሐንስ ራእይ ”ተብሎ እንዲቀየርለት ማመልከቻ አስገብቷል ይባላል፡፡
በነገራችን ላይ እኛ ሠፈር ፊታውራሪ አመዴ ለማ ያለሙት ጫካ አለ፡፡ መንግሥት ጫካው ላይ አንድ ሁለት የጽድ ችግኞች ጣል ጣል ካረገበት በኋላ የመለስ ፓርክ ብሎ ሰይሞታል ፡፡ በፓርኩ ውስጥ የቆመውን የመለስ ሀውልት ባየሁ ቁጥር ሳቄ ይመጣል፡፡ መለስን በሁለት ባህርዛፎች መሀል ቆሞ ስታየው የሆነ የደበረው ደን ጠባቂ ነው የሚመስለው፡፡
ከፓርኩ ፈንጠር ብሎ ባለው አውራጎዳና ዳር ፤ቆሻሻ ከረጢት ካብ ተዘርግቶ በሃያሁለት ማዞርያና በካዛንቺስ መካከል የበርሊን ግንብ ሠርቷል፡፡ የመጀመርያ ቀን ግማቱን ስላልቻልኩት አፍንጫየን እና አፌን አፍኘ ወደቤቴ ሸሸሁ፡፡ ምስጋና ላዲሳበባ ከንቲባ ይሁንና ፤የሰው ልጅ አፍና አፍንጫ ለሃያ ደቂቃ አፍኖ በህይወት መቆየት የሚችል ፍጡር መሆኑን ተረዳሁ፡፡ ከሦስት ቀን በኋላ በቦታው የተለመደው የጥንብ ሽታ ሳይሸተኝ ቀረ ፡፡ አሃ !ከሰንዳፋዎች ጋር ተደራድረው ቆሻሻው አስወግደውታል ማለት ነው ብየ ዞር የጥንቡን ካብ በነበረበት ቦታ አየሁት፡፡ ለካስ የተወገደው ቆሻሻው ሳይሆን የማሽተት ችሎታየ ኑሯል፡፡
ባለፈው እነ ጃዋር መሀመድ የሚላስና የሚቀመስ ወደ አዲሳባ እንዳይገባ የገበያ ማእቀብ ጥሪ ማስተላለፋቸው ይታወሳል ፡፡ አዲስአበቤስ ምኑ ሞኝ ነው ፤አስቀድሞ አስርኩንታል አስፈጭቶ ፤ ፍሪጁንም በመብልና በመጠጥ ሞልቶ ፤ ሲጠብቅ ስለነበር ያብዮቱን ሂደት በፌስቡክ መከታተሉን ቀጠለ፡፡ የእቀባው ጫና የተጫወተብን እኔንና ብጤዎቼን ነው፡፡ በቀደም ለት የሆነ ምግብ ቤት ገባሁና ምሳ አዘዝኩ፡፡ እንጀራው ከመሳሳቱ የተነሣ ” ተች እስክሪን” ነው፡፡ በልቸ ጨረስኩ አስተናጋጁ መቶ ኣምሳ ብር እንከፍል ፈረደብኝ፡፡
“ምነው ምን ጉድ መጣ! ትናንትኮ ከማርቆስ ተሳፍሬ ስመጣ ፍቼ ላይ ምን የመሰለ ምስር ወጥ በሃያ አምስት ብር በልቻለሁ”አልሁ በምሬት፡፡
አስተናጋጁ ቱግ ብሎ ምን መለሰኝ መሰላችሁ ፤
“እና ሁኔታው እስኪረጋጋ ድረስ ለምን ፍቼ እየሄድክ አትበላም?

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጭራቅ አሕመድን በሕይወት መያዝ ላማራ ሕልውና ያለው ወሳኝነት
Share