/

በእውቀቱ ስዩም ስለ ድምፃዊዉ ኢዮብ መኮንን

ከበእውቀቱ ስዩም

ከጥቂት አመታት በፊት ባንድ የበጎ አድራጎት ትርኢት ላይ ለመሳተፍ፣ከዘፋኞች ጋር ወደ ደሴ ተጉዠ ነበር፡፡የተሣፈርንበት አውቶብስ ጉንጫቸውን በጫት አሎሎ በወጠሩ ዘፋኖች ተሞልቷል፡፡ ዘፋኞቹ ሲሻቸው ይተራረባሉ፣ ሲሻቸው ይጮሃሉ፣ይጨፍራሉ፡፡የአውቶብሳችን ሽማግሌ ሹፌር ሳይቀር፣ አልፎ አልፎ መሪውን እየለቀቀ በማጨብጨብ በ‹‹ቅወጣ›› ከዘፋኞች እንዳማያንስ በማሳየት ላይ ነበር፡፡በጫቱም፣ በጭፈራውም የሌለበት ድምጻዊ ኢዮብ መኮንን ብቻ እንደሆነ ተመለከትሁ፡፡ በርጋታ ተቀምጦ፣ ባውቶብሱ መስኮት አሻግሮ፣ የሚሮጡ የግራር ዛፎችን ይመለከታል፡፡ልዩነቱ ግልጽ ነበር፡፡
ድሮ ድሮ፣ኢዮብ መኮንን አቤሴሎም የሚዘናፈል ረጅም ጸጉር ያለው ጎልማሳ ነበር፡፡ድንገት ጸጉሩን ተሸለተ፡ከጸጉሩ ጋር የጥንት ባህርይውን አራገፈ፡፡ጭምት መንፈሳዊና በመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር የነደደ ምእመን ሆነ፡፡
በተገናኘን ቁጥር፣ኢዮብ ስለ ስለ እምነት እንድንወያይ ይፈልጋል፡፡ብዙ ጊዜ እምነት የሚያጠብቅ ሰው አንዳች ችግር ይኖርበታል ብየ አስብ ነበር፡፡ኢዮብ ግን እጅግ መልካም ሊባል በሚችል ሕይወቱ ይሄንን አመለካከቴን ውድቅ አድርጎብኛል፡፡
የዛሬ ሳምንት ገደማ ኢዮብ ዘፈን በመሥራት ላይ ነበር፡፡እና ላንድ ዜማው ግጥም እንደሠራለት ጋበዘኝ፡፡ከዚህ በፊት የሞርኳቸው የዘፈን ግጥሞች ስለከሸፉብኝ ግብዣውን ለመቀበል አመነታሁ፡፡ግን ደሞ ወድያው፣ በኢዮብ ድምጽ ግጥሜን ተዘፍኖልኝ ለማየት ጓጉዋሁ፡፡ውሀ ልማት አካባቢ፣ ሌክስፕላዛ ሕንጻ ሥር መኪናው ውስጥ ቁጭ ብለን ዜማዎችን ማድመጥ ጀመርን፡፡ዘፈኑ ውስጥ ያሉት ሐሳቦች አብዛኞቹ ወደ መዝሙር ያዘነብላሉ፡፡ ኢዮብ ዘፈኑን ለፈንጠዝያ ሳይሆን ለስነምግባር ግንባታ ሊጠቀምበት ፈልጓል፡፡አንድ በጣም ልብ የሚበላ የሶማሌ ዘፈን አስደመጠኝ፡፡
‹‹ሶማሊኛ ትችላለህ እንዴ?>>
‹‹አዎ፣ትግርኛም አውቃለሁ!››
‹‹የት ተማርከው?>>
‹‹አስመራ፣የወታደር ልጅ መሆኔን አትርሳ››
ከዘፈን ውጭ ምን ታደርጋለህ?
‹‹ኦን ላይን፣ ጊታር እየተማርሁ ነው፡፡ቆይ ላሳይህ››…ላፕቶፑን ለኮሰና ጥቂት አስጎበኘኝ፡፡ከዛ ከመኪናው ስወርድ የመኪናው እጀታ ስለማይሠራ ወርዶ ከውጭ ከፈተልኝ፡፡ኢዮብ ብዙ ብሮችን መቆጠር የሚችል ልጅ እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ይሁን እንጂ እንኳን መኪናውን የመኪናውን እጀታ ማስቀየር አልፈለገም፡፡ምናልባት፣ዓመት በአልን ጠብቆ ልብስ የሚቀይር ብዙ ሰው ባለበት አገር ውስጥ፣ መኪና መቀያየሩን እንደ ኃጢአት ቆጥሮት ይሆናል፡፡
ከጥቂት ቀናት በኋላ ልኡል የተባለ ዘፋኛ ጓደኛየ የኢዮብን በድንገት መውደቅ ሲነግረኝ ወደ ቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል ሄድኩ፡፡ዘፋኞችና አዘጋጆች መጠበቂያው ክፍል ላይ ተደርድረው ይተክዛሉ፡፡ዘሪቱ፣ዳግማዊ አሊ፣እቁባይ በርሄ፣አጃቸውን አገጫቸው ላይ ጭነው፣ተቀምጠዋል፡፡የኢዮብ ባለቤት ወድያ ወዲህ እየተንቆራጠጠች ታነባለች፡፡
ዛሬ ደግሞ ይሄው ሞቱን ሰማሁ፡፡ለካ፣ወደ ደሴ የሚሄደውም አውቶብስም ሆነ፣ሌክስ ፕላዛ ሕንጻ ስር፣ የቆመው ቪታራ መኪናው መዳረሻቸው አንድ ነው፡፡መቃብር!!
ኢዮብ!!! በጠፈሩ ውስጥ፣ ያለ ግብ ከሚዞሩ ኮረቶች፣ያለ ምክንያት ከሚበሩ ኮከቦች በቀር ምንም የለም ብየ እንደማምን ታውቃለህ፡፡ይሁን እንጂ ለዛሬ እንኳ፣ የኔ እምነት ከሽፎ ያንተ እምነት እውነት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡በምድር ለገጠመህ መራራ እጣ ሰማያዊ ካሳ(ጉማ) እንድታገኝ እመኛለሁ፡፡