የሽንጎው ከፍተኛ የአመራር አካል ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን አካሄደ

ሸንጎ ለዘ-ሐበሻ የላከው ጋዜጣዊ መግለጫ

ነሃሴ ፯ ቀን ፳፻፭
Aug 13, 2013
የኢትዮጰያ ህዝብ የጋራ ትግል ሽንጎ ከፍተኛ የአመራር ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን ቅዳሜ ነሃሴ 4 ቀን፣ 2005 (August 10, 2013) በተሳካ ሁኔታ አካሄደ።
ይህ ስብሰባ የሽንጎው ሁለተኛ ጉባኤ ያስተላለፋቸውን ውሳኔዎችና የተለማቸውን የትግል አቅጣጫዎች በሀገር ውስጥና በውጭ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያሰችሉ የተግባር መመሪያዎችን የሰጠ ሲሆን ይህንንም እውን ለማድረግ አስፈላጊ የሆኑ ኮሚቴዎችን መስርቷል፣ የሰው ሀይልም መድቧል።
ምክር ቤቱ በሀገሪቱ ውስጥ እየተከሰቱ ያሉትን ወቅታዊ ሁኔታዎች በመመርመር ገዥው ህወሓት/ኢህአዴግ በተከታታይ ሲያደርግ እንደቆየው ሁሉ ህዝብን የማሸበር ተግባሩን በመቀጠል፣ በኢትዮጵያውያን ሙሰሊሞች ላይ በኢድ አል ፈጥር ያካሄደውን ድብደባና ማንገላታት በታላቅ ሀዘን ተገንዝቧል፣ ድርጊቱንም በጥብቅ አውግዟል።
በሰላማዊ መንገድ መሰረታዊ የእምነት ነጻነት እንዲከበርና መንግስትም በሃይማኖት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብነቱን እንዲያቆም፣ የታሰሩ የሀይማኖት መሪዎችም እንዲፈቱ የቀረበን ሰላማዊ ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ሙስሊሙን ማህብረተሰብ በጀምላ በሽብርተኛና አክራሪነት የመወንጀል ዘመቻ መቀጠሉ እጅግ ሀላፊነት የጎደልውና አደገኛ እርምጃ እንደሆነ በመገንዘብ ገዥው ህወሓት/ኢህአዴግ ከዚህ አይነት እኩይ ተግባሩ ተቆጥቦ ለሙስሊሙ ማህብረተሰብ ጥያቄዎች ባስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥ አሳሰቧል። ከህዝበ ሙስሊሙ ጋር ያለውን የትግል አንድነት በድጋሜ ገልጿል።
ከዚህም ሌላ በቅርቡ በአንድነት ፓርቲ ፣ በመድረክ፣ በሰማያዊ ፓርቲና በመኢአድ አባላት ላይ ገዥው ህወሓት/ኢህአዴግ እያካሄደ ያለውን እስራት፣ ወከባና ድብደባ ባሰቸኳይ እንዲያቆም፤ የህዝብንም መሰረታዊ መብቶችንና የህግ የበላይነትን እንዲያከብር በጥብቅ አሳሰቧል።
ሽንጎው እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ፣ የህዝባችንን መብት ለማስከበር ቆራጥ ትግል በማካሄድ ላይ ከሚገኙት ከነዚህ የተቃዋሚ ድርጅቶችና አባሎቻቸው ጋር ያለውን የትግል አንድነት በድጋሜ አረጋግጧል።
በመጨረሻም፣ ትግሉ ውጤታማ ለመሆን የተቃዋሚዎችን መተባበር የግድ የሚል መሆኑን በመገንዘብ በኢትዮጵያ አንድነትና በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ምስረታ ላይ ጽኑ እምነት ያላቸው ሁሉ አሁንም ሽንጎውን እንዲቀላቀሉ ቀጣይ ጥሪ አቅርቧል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በመቀሌ ምድር ባቡር ፕሮጀክት በጥበቃ ላይ የነበሩ የፌደራል ፖሊስ አባላት የተቃጣባቸውን ወንጀል በመፋለም ማምለጥ መቻላቸውን ገለፁ

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ

Share