የዳያስፖራዎች ቤት ግብዣ | በእውቀቱ ስዩም

/

.
ከዘፋኞች ቡድን ጋር አሜሪካ በገባን ማግስት ዘፋኞች በዶላር ከበሩ፡፡

እኔ አጥብቄ ተቸገርኩ፡፡

በወይዘሮ የሺሻ-ወርቅ ናይት ክለብ ውስጥ፤ ፋሲል ደመወዝ የጣውላ ክላሹን አነግቶ “አረሡት የሁመራን መሬት” ብሎ ዘፍኖ ሁመራን ለመሸመት የሚበቃ የሽልማት ዶላር ይዞ ሲወርድ እኔ ግጥም ለማንበብ ወደ መድረክ እወጣለሁ፡፡

ከዚያ በግጥም ደብተሬና በእኔ መሃል የቆመውን ወፍራም የሺሻ ጭስ ባይበሉባዬ ገለል አድርጌ…

“ዓለማዊ ልቤ ለበሰልሽ ዳባ ምናኔ ተመኘ
በእናቴ ቀብር ላይ የጠፋብኝ እምባ ፊቴ ላይ ተገኘ“
…ብየ ስጀምር አያስጨርሱኝም፡፡

“ምናኔ ደሞ ምንድነው”? ትለኛለች ከጥግ ቁጭ ብላ ሺሻ የምትጠባ ደንበኛ፡፡

ብልጭ ይልብኛል ! ግጥሜን ላንብብ ወይስ አንቺን አማርኛ ላስተምር?

“አቦ ይሄ ልጅ ያስቃል ሲባል አልነበረ እንዴ ? ምንድነው እዚህ ”ቀብር“ ምናምን እያለ የሚያለቃቅስብን ?”ይላል ሌላው የሚወረወር ነገር ባካባቢው እየፈለገ፡፡

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከኢትዮጵያ ያስመጣኝ ፕሮሞተር በኔ ተስፋ ቆረጠ፡፡ ጥረህ ግረህ ብላ ብሎ ጥሎኝ ጠፋ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ምግብ አማርጥ የነበርኩት ሰውዬ አሜሪካ ውስጥ ያለ ፈቃዴ በተከታታይ እፆም ጀመር፡፡

ጠዋት የቤቴን በር ስከፍት ከነ ጃንቦ ጆቴ ክፍል መአት ዓይነት የፕላስቲክ አገልግል፤ የሰርዲን ጣሳ፤ ድርብ ሰረዝ የመሰለ በርገር፤ እንዲሁም የቢራ ጠርሙስ እየተጠረገ ሲወጣ አያለሁ፡፡

ሲብስብኝ ማንኛውንም የምሳ ግብዣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መቀበል ጀመርኩ፡፡

ዘፋኞቹ ”ተጋባዡ ገጣሚ“ በማለት ይፎትቱኝ ጀመር፡፡

አንድ ቀን ቨርጂንያ አውራ ጎዳና ዳር ቆሜ በጥሞና ሳሰላስል ፊቴ ላይ የሚታየውን ጥልቅ ጥሞና የተመለከተ ሰው ስለ ቀጣይ ያገራችን እጣ ፈንታ እንጂ ስለ ቀጣዩ ምሳ እያሰበ ነው ብሎ አይገምትም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጥሪ ዱር ቤቴ ላላችሁት ፋኖዎች በያላችሁብት ክፍለ ሀገራት፣ አዉራጃዎች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች!

”ሃይ በእውነቱ“ የሚል የሴት ድምጽ ካሳቤ አባነነኝ ፡፡

አንዲት ያገሬ ልጅ መኪናዋን አቆመችልኝ፡፡

ትንሽ ከተደናነቅን በኋላ ”ለምን ምሳ አብረን አንበላም?“አለቺኝ፡፡

ገና ”ለምን ምሳ… “ የሚለው አርፍተ ነገር ባየር ላይ እያለ መኪናዋን ከፍቼ ከኋላ ወንበር ቁጭ ብያለሁ፡፡

ትንሽ እንደ ሄድን መኪናዋን ካንድ ጥግ አቁማው የሆነ ዐራት ማእዘን ሰውዬ ገብቶ አጠገቧ ተቀመጠ፡፡

ከዚያ ዞር ብሎ “የማን አባቱ ጉቶ ነው” በሚል አይነት ገላመጠኝ ፡፡

ወድያው ግን በድጋሚ ከተመለከተኝ በኋላ
“አጅሬ! አንተነህ እንዴ?ለመሆኑ ወደ ሥነጽሁፍ ዓለም እንዴት ገባህ“ እያለ በባዶ ሆዴ ያደርቀኝ ጀመር፡፡

ቤት ገብተን ልጅት ምሳ ለመሥራት ወደ ጓዳ ገባች፡፡

ሰውየው የፍቅርና የትዳር ታሪኩን ባጭሩ ለሁለት ሰዓት ያህል ተረከልኝ፡፡

አዲሳባ ውስጥ በፍቅር እንደኖሩ፤ ከዚያ እሱ ወደ አሜሪካ እንደተሰደደና እሷን በስንት ውጣውረድ እንዳመጣት ነገረኝ፡፡ በቅጡ አልሰማሁትም፡፡

ከሰውየው ትረካ በላይ ጥርት ብሎ የሚሰማኝ ከጓዳ የሚመጣው የመክተፍያ ድምጽ ነበር፡፡

ልጅቷ በያይነቱ ሠርታ ጨረሰች፡፡ ግን ቶሎ አልቀረበም፡፡

እኔን ራብ እየሞረሞረኝ ባልና ሚስቱ ስለኣቀራረብ ስታይል ይራቀቃሉ፡፡

“ስንግ ቃርያው የሚቀመጠው ከቲማቲሙ በስተቀኝ በኩል ነው በስተግራ በኩል ነው”? በሚለው ዙርያ ለሃያ ደቂቃ ያክል ተከራከሩ፡፡

እኔ ወደ ማእዱ ለመሄድ ትንሽ ሲቀረኝ ማእዱ ከፊቴ ቀረበ፡፡

”ይገርምሃል ለመጀመርያ ጊዜ ሲዲህን የሰማሁት ደሳለኝ ቤት ሆኜ ነው” አለችኝ ከጠረጴዛው ላይ ብርጭቆ የሞላ ውሀ እያስቀመጠች፡፡

”ደሳለኝ? ደሳለኝ ማን ነው?“አለ ሰውየው የህጻን ብርድልብስ የሚያክል እንጀራ ሰሀኔ ላይ እያነጠፈ፡፡

”ደሳለኝ፡፡ ተከራይቶ የሚኖር ልጅ ነበር፤ እኛ ግቢ”
”ኦኬ ምን ልትሠሪ ቤቱ ገባሽ?“ ባሉካ ባረቀ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በአፍሪካ ውስጥ በቅዠት የሚባንኑት እነማን ይሆኑ ?

”ቲቪ ላይ ነዋ ! የደሳለኝ ብቸኛ ሀብቱ ግዙፍ ቴሌቪዥኑ ነበር፡፡ ይገርምሀል ቤቱ ውስጥ ወንበር እንኳ አልነበረውም” አለች ወደኔ ዞራ፡፡

“ወንበር ከሌለው ታድያ ምን ላይ ተቀምጠሽ ቲቪውን ዓየሽው?” ሰውየው አፈጠጠ፡፡

“እምም አልጋው ጫፍ” አለች ፈገግታዋ እንዳያመልጣት ከንፈሯን እየጨቆነች፡፡

ሰውየው ለመደባደብ ያሟሙቅ ጀመር፡፡

ብድግ ብዬ ”ተው እንጂ! ነውር ኣይደለም እንዴ?” ምናምን እያልኩ በማሃላቸው ገባሁ፡፡

“ነውር ኣይደለም እንዴ? አትሊስት ምሳዬን እስክበላ ድረስ ለምን አትታገስም?“ አልኩ በልቤ፡፡

”አሜሪካ እንዳለህ አትርሳ፡፡ ጫፌን አትነካኝም!“ አለች ከመጤፍ ሳትቆጥረው፡፡

እውነቷን ነው፤ አሜሪካ ውስጥ የሴትን ጫፍ መንካት ትልቅ ወንጀል ነው፡፡ ወንዶች ንዴታቸውን የሚወጡት ግድግዳ በቴስታ በመምታትና የመኪና ጎማ በካልቾ በመጠለዝ ነው፡፡

ሰውየው በንዴት አረፋ እየደፈቀ ዞር ሲል ከግድግዳ የተሻለ ንዴቱን ማስተንፈሻ ተመለከተ፡፡

ቁልቁል ዐየኝ፡፡

ቀጥሎ የተከሰተው ብዙ ነገር ትዝ አይለኝም፡፡
ብቻ…

“አቦ ወደዛ ዞርበልልኝ” ሲልና የመጥረቢያ ዛቢያ የመሰለውን ክርኑን ወደ አንገቴ ሲሰነዝር ትዝ ይለኛል፡፡

አንገቴ ወደ ቀድሞው ጤንነቱና ውበቱ ለመመለስ ላንድ ሳምንት ያህል የፒትልስ ሹራብ ኰሌታ የመሰለ ጄሶ ድጋፍ ማግኘት ነበረበት፡፡

እና እስከዛሬ ድረስ ”አንገት ከሚሰበር ባይበላስ ቢቀር“ የሚለውን የቴዲ አፍሮ ዘፈን በሰማሁ ቁጥር ይሄ ልጅ የኔን ታሪክ ማን ነግሮት ይሆን ? እላለሁ፡፡
.

6 Comments

  1. ያንን የኢትዮዽያ ኦርቶዶክ ተዋህዶ እምነት የሚያራክሰውን መጽሃፍ ጥፈህ ባስመረቅህ ሰሞን
    በውቀቱ በዳዳ እያሉ ሲጠሩህ ነበር ፣ ታዲያ በውቀቱ ስዩም ነው የሚባለው ስላቸው አባቱ
    ስዩም ሳይሆን በዳዳ ነው አሉኝ ፣ ለምን ስል እርሱ ያውቃል ለምን እንደቀየረ አሉኝ ፣ የሰው
    ልጅ ውሃ ውስጥ እንደገባ ጨው እየሟሟ ለምን እንደሚሄድ እንቆቅልሽ ሆነብኝ ፣ አሁን ደግሞ
    ይችን መጣጥፍህን ስመለከት ተወዳጁንና ስለሀገር የሚያቀነቅነውን አርቲስት ፍሲል ደመወዝን
    “የጣውላ ክላሹን አንግቶ” አረሱት የሁመራን መሬት ብሎ ሲዘፍን ብለህ ታላግጥበታለህ !
    መስንቆውን የጣውላ ክላሽ አልከው ስትሳለቅበት! ከተስፋየ ገ/አብ ጋር መቼነው አብራችሁ
    ቡራኬ የተቋረሳችሁት ? ወጣ ወጣና እንደ ሸንበቆ ተንከባለለ እንደሙቀጫ ነበር ያሉት
    አቶ አነሰ ሰው !!

  2. @wezerow ketaw,relax man. The guy got amazing talent.baddada or seyom both are nice ethiopian names.

  3. Bewketu you are extraordinarily talented and gifted I believe that you won’t be distracted even for a minute ,from your beautiful literature and a sense of humor that no one hasso far in the contemporary Ethiopia, because of the millions extras found everywhere like waste.
    Semere Habte

  4. ሁልጊዜ እንደበሳል ጸሀፊ,ጽሁፍ ትጀምራለህ እና ምን ሊያስነብበን ነው ብዬ ማንበብ ስጀምር አፍህ የካደው ነገር ግን ብዕር ስታነሳ አይምሮህ የሚያምነውን ሀሳብ ስትዘባርቅ ይሄ ሰው ከሀይማኖት እና ከአማራነት ውጪ እውቀት የለውም ወይስ ፈሪ ፀሀፊ? ምን እንደሆንክ አላቅም ቢሆንም አሁንም ጸሀፊ ነህ…በሌላ መጣጥፍ ወጣ ያለ ጹሁፍ ትምክራለህ ብዬ እጠብቃለሁ ፡፡ አድናቂህ አደለሁም ተቃዋሚም ለወደፊት ከሁለት አንዱን እሆናለሁ፡፡

Comments are closed.

Share