February 21, 2013
25 mins read

የኦርቶዶክስ ቤት ክርስቲያንን አንድ ሊያደርግ የሚችል የመፍትሄ ሃሳብ !

ግርማ  ካሳ
[email protected]
የካቲት 12 2015 ዓ.ም

«በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ ! 

የአቡነ  ጳዉሎስን ሕልፈት ተከትሎ፣  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዉስጥ የተፈጠረዉን መከፋፈል ለማስቀረት፣ በመንፈሳዊ አባቶች መካከል፣ የሰላምና የእርቅ ዉይይቶች ተደርገዋል። ለሃያ አመታት የዘለቀዉ፣ ይህ በቤተ ክርስቲያን ላይ የወረደው የመከፋፈል እርግማን ተወግዶ፣  ቤተ ክርስቲያኒቷ  አንድ ሆና፣  «ሂዱና አሕዛብን እያስተማራችሁ፣ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅድስ ስም እያጠመቃችሁ፣ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸዉ» የሚለዉና  በመድሃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጠዉ፣ ታላቅ ተልእኮን መፈጸም ትችል ዘንድ፣ ሕዝበ ክርስቲያኑ በየአብያተ ከርስቲያናቱ፣ በየጸሎት ቤቱ ፣ በየገዳማቱ ሲጾምና ሲጸል ነበር።

ነገር ግን ከተጠበቀዉና ከተገመተዉ ዉጭ አስደንጋጭና አሳዛኝ መግለጫዎችን አነበብን። የክርስቶስ መድሃኔአለም ስም ተሰደበ። የዲያብሎስ ስም ገነነ። የትህትሃ የፍቅር እራስን የማዋረድ ክርስቲያናዊ መንፈስ ጠፋ። የእልህ የስደብ የመወጋገዛና የትእቢት መንፈስ ሰፈነ።

በአገር ደረጃ ካያን ፣ የከተማ፣   የክልል ፣ የፌደራል መንግስት  ሕጎች ይኖራሉ። ነገር ግን ከህጎች ሁሉ በላይ የሆነ ሕገ-መንግስት የሚባል ሕግ አለ። ፈረንጆች “The Supreme Law of the Land” ይሉታል።

ቤተ ክርስቲያንም የምትተዳደርበት ሕገ ደንብ ወይንም ቀኖና አላት። ካህናት ፣ ገዳማት፣ የሰንበት አስተማሪዎች ወዘተረፈ የሚታዳደሩበት ስርዓት/ሕግ/ቀኖና  አለ። እነዚህ የቤተ ክርስቲያን ሕጎችና ቀኖናዎች የቤተ ክርስቲያኒቱ ዋና መመሪያ የሆነዉን፣ የመድሃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የሚያግዙ እንጂ፣  የሚተኩ አይደለም። ወንጌል ከሁሉም በላይ ነዉ። ለዚህም ነዉ በቅዳሴ ወቅት ወንጌልን ቄሱ በሚያነቡበት ወቅት፣ ምእመኑ በአክብሮትና በፍርሃት ቆሞ የሚያዳምጠው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ  ቤተ ክርስቲያን አባቶችን እያጨቃጨቀ ያለ አንድ ጉዳይ ቢኖር፣  በቤተ ክርስቲያኒቷ የቀኖና መጽሃፍ የተጠቀሱ፣ ፓትሪያርክ እንዴት እንደሚሾምና እንደሚተካካ የሚገልጹ አንዳንድ አንቀጾች ናቸዉ። በዶክትሪን ወይንም በሃይማኖት ጉዳዮች አልተለያዩም። በአስተምህሮ አልተለያዩም። ልዩነታቸው፣ ቅንነትና ትህትና የተሞላ ልብ ካለ፣ በቀላሉ ሊፈታ የሚችል፣   የአሰራርና ማን መሪ መሆን አለበት የሚለዉ ላይ ነዉ።

አራተኛዉ የቤተ ክርስቲያኒቷ ፓትሪያርክ በሕይወት እያሉ አምስተኛ ፓትሪያርክ ይሾማሉ። «አምስተኛዉ ፓትሪያርክ የተሾሙት አራተኛዉ ፓትሪያርክ በፍቃዳቸው ሃላፊነታቸዉን ስለለቀቁ ነዉ» ያላሉ አንዳንዶች። ሌሎች ደግሞ «አይደለም ፤ በአቶ ታምራት ላይኔ ተገደው ነዉ» ሲሉ በፓትሪያርኩ ላይ ተደረገ የሚሉትን  ግፍ በምሬት ይገልጻሉ። ይሄ እንግዲህ ከሃያ አመት በፊት የሆነ ነገር ነዉ።  ጠባሳዉ ግን ለሃያ አመታት ይኸዉ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ጉዳት አደረሰ። ቤተ ክርስቲያኒቷ ተከፈለች። ለሃያ አመታት ጠብ ነገሰ። ተፋቅረን ተያይዘን በአንድ ላይ ወንጌልን ማስፋፋት የሚገባን ክርስቲያኖችን፣ ከፋፍሎና አጣልቶ ሆድና ጀርባ አደረገን።

እንግዲህ አስቡት፣ የመጽሃፍት ሁሉ የበላይ፣ የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነዉ ፣ ወንጌልን ያካተተዉ መጽሃፍ ቅዱስ ነዉ።  መጽሃፍ ቅዱስ የሚያዘው ፍቅርን፣ ይቅር መባባልን፣ አንድነትን፣ ትህትና የመሳሰሉትን ነዉ። የቀኖናዎች ሁሉ የበላይ ከሆነዉ፣ ከማያልፈዉና ከማያረጀዉ ሕያዉ የእግዚአብሄር ቃል ዉስጥ ፣ «እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ የኔ ደቀ መዛሙርት መሆናችሁን ሌሎች ያዉቃሉ»፣ « እራስህን ከሌላ የተሻለ አድርገህ አትቁጠር» ፣ «አንተ የሌላዉን ጉዳፍ ለማወጣት የምትቸኩል በአይን ያለዉ ያለዉን ትልቅ ምሰሶ መጀመሪያ ተመልከት» ፣  ‹‹በመጀመሪያ መባህን በመሰዊያው ላይ ትተህ አስቀድመህ ከወንድምህ ጋር ታረቅ››፣ «ማንም ከነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን የሚያሰናክል ፣ ወፍጮ ባንገቱ ታስሮ ባህር ዉስጥ ቢወረወር ይቀለዋል»፣ «ሌላዉን የሚያሰናክል ከሆነ ስጋ ባልበላ ለዘላለም ልቀር»፣ «እኔ መምህር ና ጌታ ሆኜ ይሄን ካደረኩ ( የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠቡ) እናንተም እንዲሁ አደርጉ» የመሳሰሉትን  ትእዛዛት እናነባለን።

የቤተ ክርስቲያን አባቶች በአንድ በኩል ለክርስቲያናዊ ሕግና ቀኖ ቆመናል  እያልን፣  በሌላ በኩል ከቤተ ከርስቲያን ሕግና ቀኖና በላይ የሆነዉን የጌታ ክርስቶስን ትእዛዝ ወደ ጎን እያደረገን፣  ያለ ይመስለኛል። ቀኖና፣  ወንጌልንም መደገፍ እንጂ ከወንጌል በተቃራኒ መቆም እንደሌለበት የዘነጋን ይመስለኛል። ዋናዉን ረስተን ትንሹ ነገር ላይ ስናከር ነው የሚታየዉ።

እንግዲህ «ንስሐ እንግባ ። ክርስትናችንን ፣ የክርስቶስ ተከታይና አገልጋይነታችንን፣ በምንለብሰው ካባ  ሳይሆን በስራችን አናሳይ» እላለሁኝ። ከወንድሞቻችን ጋር መስማማት አቅቶን፣ ይቅር መባባል ከብዶን፣ «እኔ ነኝ ፓትሪያርክ መሆን ያለብኝ …እርሱ ነዉ መሆን ያለበት ..» እየታባባልን፣ በእልህ  መንፈስ ተሞልተን፣ በአኮቴተ ቁርባን ወቅት ስጋ ወደሙን በእጃቸችን ለመያዝ መቆማችን  መቅሰፍት ነዉ»  እላለሁ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ናት።  እንደ እዉነቱ ከሆነ ፣ ከኛ በኋላ ክርስትናን በተቀበሉ አገሮች የሚኖሩ ዜጎች፣ እምነት የሌላቸውን ክርስቲያን እያደረጉ ባለበት ወቅት፣ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ በምስራቅ አፍሪካ ወንጌልን ለማሰራጨት የበለጠ መነሳት አይገባትም ነበርን ? በሚሊዮን የሚቆጠሩ እራሳቸውን ኦርቶዶክ ክርስቲያን ነን  የሚሉ፣  ነገር ግን የስላሴንና የስጋዌን ሚስጥራትን እንኳን በደንብ የማያዉቁ አሉ።  ብዙ የኦርቶዶስክ ልጆች በሃሺሽ፣ በጫት፣ በተለያዩ ከምእራባዉያን አገራት በመጡ ጸረ-እምነት ተግባራት የተጠመዱ ፣ በስም እንጂ ከክርስትና ጋር በተግባር የማይተዋወቁ ናቸው። አብያተ ከርስቲያናትን ከሚያዘወትሩት ይልቅ፣  የዳንኪራ፣ የጫትና የካቲካላ  ቤቶችን የሚያዘወትሩ በጣም ይበዛሉ።

ታዲያ  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ቤተ ክርስቲያን፣ በሯን ለመንፈስ ቅዱስ  ከፍታ፣ እራሷን ከመንፈሳዊ ባርነት አውጥታ፣ የማያምኑ  አሕዛብን  እንዲያምኑ ማድረጉን ለጊዜው እንተወዉና፣ ኦርቶዶክስ ነን የሚሉትን  እንኳ በቃለ እግዚአብሄርና በእምነት ማጠንከርና ማሳደግ አልነበረባትምን ?  የኦርቶዶክስ አማኞች ፣ ወንጌልን አልፎ አልፎ ቅዳሴ ሲመጡ በሚሰሙት ብቻ ሳይወሰኑ፣  ሌት ተቀን የሚያነቡትና የሕይወታቸው መመሪያ የሚያደርጉት፣ ሳይፈሩም በአደባባይ  የሚያወጁት መሆንስ አይገባምን ?

ነገር ግን መንፈሳዊ አባቶች፣ እረኝነታችንን ረስተን፣  መንጋዉን ለተኩላ ለመስጠት እየተዘጋጀን ያለ ይመስለኛል። ጥል ባለበት እግዚአብሄር የለም። «የትእቢተኞችን ቀስት ይሰብራል፣ ለትሁታን ግን ጸጋን ይሰጣል» እንዳለችዉ እናታችን ቅድስት ማርያም፣ እግዚአብሄር ትእቢትን ይጸየፋል። ትእቢት ባለበት ቦታ እግዚአብሄር የለም። በመሆኑም  የኦርቶዶስክ አባቶች እርቅ መመስረት ካልቻልን፣  ከእግዚአብሄር ክብር ይልቅ የኛን ክብር ካስቀደምን፣ በግልጽ በስራችን የምንናገረዉ፣   እግዚአብሄር ከእኛ ጋር እንደሌለ ነዉ። እግዚአብሄር የሌለበት ቦታ ደግሞ እንዲሁ መቆዘም እንጂ በረከት የለም።

እስቲ ትንሽ ጠለቅ ልበልና፤ ሁለቱ የኦርቶዶክስ ሲኖዶሶች፣  ሊስማሙበት ካልቻሉበት ነጥቦች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰውን ለማየት እንሞክር።

ዉጭ አገር የሚገኘዉ ሲኖዶስ አራተኛው ፓትሪያርክ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው፣  የፓትሪያክነት ሃላፊነታቸዉን እንዲወጡ ይፈልጋል። አዲስ አበባ ያለው ሲኖዶስ ደግሞ «ለሃያ አመት የተሰራዉን ሥራ መቀልበስ ነዉ። አምስት ተብሎ ወደ አራት መሄድ አይቻልም» በሚል አራተኛዉ ፓትሪያርክ ተመልሰው አራተኛ ወይንም ስድስተኛ ሆኖ መቀጠላቸዉን ሊደግፉ አልቻሉም። ‹‹አራተኛው ፓትርያርክ ወደ አገራቸው ተመልሰው ደረጃቸውና ክብራቸው ተጠብቆ፣ የሚያስፈልጋቸው ሁሉ ተሟልቶላቸው በመረጡት ቦታ በፀሎት ተወስነው እንዲኖሩ፣ ነገሮቹም ሆነ በእሳቸው አንብሮተ ዕድ የተሾሙ ቀኖናውን በቀኖና አሻሽሎ ሐዋርያዊ ሥልጣናቸውን ሰጥቶ፣ ስማቸውን መልሶ በሀገረ ስብከት መድቦ ለማሠራት፣ ፈቃደኛ ነዉ» ሲል በአዲስ አበባ ያለዉ  ቅዱስ ሲኖዶስ የመጨረሻ አቋሙን ያሳዉቃል። አሜሪካ ያለዉ ሲኖዶስ መልስ በመስጠት «አቡነ መርቆሪዮስ ፓትሪያርክነታቸውን መቀጠል አለባቸው። የቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖና መጠበቅ አለበት» በሚል አቋሙን በድጋሚ የሚያጸና መግለጫ ያወጣል።

ከሁለቱም ወገኖች ላሉ አባቶች እንግዲህ የምለው ይሄን ነዉ። እግዚአብሄርን እንጂ ሰዉን አንፍራ። አላስፈላጊ መግለጫዎችን  ከመስጠት እንቆጠብ። አለመስማማት፣ ለጊዜዉ መጋጨት ያለ ነዉ። ሐዋርያዉ ጳዉሎስና በርናባስም አንድ ወቅት ተጋጭተዉ ነበር። እግዚአብሄር ለቁጣ የዘገየ በምህረቱ ግን ባለጠጋ የሆነ አምላክ ነዉ። «የልጁ የየሱስ ክርስቶስ ደም ከሐጢያት ሁሉ ያነጻል« ተብሎ እንደተጻፈ፣ ለሰራናቸው ሐጢያቶች እና ስህተቶች እግዚአብሄር ይቅር ይለናል። የትላንትናዉን  ትተን፣ ዛሬ መልካምን ነገር ለማድረግ እንዘጋጅ። ዛሬ እራሳችንን ለፍቃዱ እናስገዛ። ጆሮዎቻችን የጥላቻን እና የእልህ ወሬዎችን ከመስማት የተደፈኑ ይሁኑ። ሁላችንንም ሊያስማማ የሚችል መፍትሄ ማግኘት ይቻል ዘንድ እንመካከር፣ በጋራም አብረን እንጸልይ።

አዲስ አበባ ያለው ሲኖዶስ፣ ፓትሪያርክ የሚሆኑ እጩዎችን ተቀበሎ ስድስተኛዉን ፓትሪያርክ ለማስመረጥ ስራዎችን እየሰራ እንዳለ እያነበብን ነዉ።  በቅርቡም አዲሱ ፓትሪያርክ ማን እንደሚሆኑ እንሰማለን። ይሄ ደግሞ ለሃያ አመታት የነበረዉ  የቤተ ክርስቲያን መከፋፋልና እርግማን እንዲቀጥል ሊያደርገው አይገባም። የእርቁን ሂደት ይረዳ ዘንድ፣ የኦርቶዶክ ቤተ ክርስቲያንን አንድ የሚያደርግ፣  አንዳንድ ሃሳቦችን በትህትና ለማቅረብ እሞክራለሁ። እነዚህን ሃሳቦች ሳቀርብ ፣ አገር ቤት ያሉም ሆነ በአሜሪካ የሚገኙ አባቶች፣ ትንሽ ሊቆረቁራቸው ቢችልም ትኩረት ሰጠዉ ሃሳቤን ያስተናግዱታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

  1. አዲስ አበባ ያሉም ሆነ በዉጭ የሚገኙ አባቶች፣ መግለጫዎችን  ከማዉጣት መቆጠብ ይኖርባቸዋል። መግለጫ ማዉጣት ማንነትን አይሳይም። መግለጫ ማዉጣት ክርስትናን አያሳይም። «በፍሪያችሁ ያውቋቹሃል» ተብሎ እንደተጻፈ ክርስትናችንን፣ የክርስቶስ አገልጋይነታችንን፣ የቤተ ክርስቲያን መሪነታችንን በስራችን ነዉ ማሳየት የሚኖርብን። በስራችን ክርስትና ማለት ምን ማለት እንደሆነ፣ አርዓያ በመሆን፣  ለምንመራው ምእመን ማስተማር አለብን።
  2. በአዲስ አበባ የሚገኘው ሲኖድስ፣ ስድስተኛዉን ፓትሪያርክ በቅርቡ ያሳዉቀናል። አዲሱ ፓትሪያርክ በዉጭ አገር ካለዉ ሲኖድ ጋር በመነጋገር፣ አንድነት የሚፈጠርበትን፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የወረደው እርግምን የሚገፈፍበትን ሁኔታ በቀዳሚነት ማመቻቻት ቀዳሚ ተግባራቸው ሊሆን ይገባል። «ከሁሉም በላይ መሆን የሚፈልግ የሁሉም አገልጋይ ይሁን»  እንዳለ ጌታችን ኢየሱስ ፣ ፓትሪያክነታቸዉ የከፍታ ቦታን ለማግኘት ሳይሆን፣ ለማገልገል፣ የተበተኑትን ለማሰባሰብ፣ የተሰበረዉን ለመጠገን መሆን አለበት።
  3. አቡነ መርቆርዮስ በእድሜ ባለጠጋ የሆኑ አባት ናቸዉ። በርሳቸው ምክንያት ክፍፍሉ መቀጠል የለበትም። ለሰላም ሲሉ ፣ ለቤተ ክርስቲያኒቷ አንድነት ሲሉ፣ ለእግዚአብሄር ክብር ሲሉ፣ እግር ማጠብ ይኖርባቸዋል። እርግጥ ነዉ በቆኖናዉ መሰረት ፓትሪያርክ ሳይሞት ፓትሪያርክ አይሾምም። ከዚህ በፊት ስህተቶች ተሰርተዉ ሊሆን ይችላል። ከዚህ በፊት በደል ተፈጽሞባቸዉ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን አሁን ከዚያ አልፈዉ መሄድ ያለባቸው ይመስለኛል።  ይቅር ማለት መቻል ያለባቸው ይመስለኛል። ከሃላፊነታቸው በፍቃዳቸው ቢለቁና አዲስ ለተመረጡ ፓትሪያርክ እዉቅና ቢሰጡ፣ የዲያቢሎስን ሥራ ነበር የሚያፈርሱት። በመሸነፍም ያሸንፉ ነበር።

እዚህ ላይ በቅርቡ የካቶሊኩ ፖፕ ያደረጉትን መመልከት ሊጠቅም ይችላል። «ቤተ ክርስቲያኔን ለመምራት የአካል ጥንካሬ የለኝም። የኔ ፖፕ ሆኖ መቀጠል ጥሩ አይደለም። በኔ ምትክ ሌላ ሊሰራ የሚችል ፖፕ መመረጥ አለበት» ብለው፣  ለቤተ ክርስቲያን ጥቅም ሲሉ፣ ፖፕ ቤኔዲክት ከሃላፊነታቸው ሊነሱ ነዉ። አቡነ መርቆሪዮስም  እንደ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ጥቅም አስቀድመዉ፣ ቤተ ክርስቲያኒቷን አንድ ለማድረግ፣ የቤተ ክርስቲያኒቷን ቀኖና በጠበቀ መልኩ፣  ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

እንግዲህ እንደ ክርስቲያኖች ትልቅ መንፈሳዊ ዉጊያ ከፊታችን ይጠብቀናል። ጸረ-ወንጌል የሆነው ዲያብሎስ፣ በታሪክ ትልቅ ስራን የሰራች ቤተ ክርስቲያንን ለማዳከም እየጣረ ነዉ። በመሆኑም ሕዝበ  ክርስቲያን ሁሉ ከመቼውም በበለጠ አጥብቆ መጸለይና መጾም ይኖርበታል።  በወጡት፣ ጠቃሚ ያልሆኑ መግለጫዎች ተስፋ መቁረጥ የለብን። ክርስቲያን ተስፋ አይቆርጠም። ከንግስት አስቴር መማር አለብን። አማሌቃዊዉ ሃማ እሥራዔላዉያንን ለመጨረስ አዋጅ አሳወጀ። እነ አስቴር  ጾም ጸሎት አወጁ። በእግዚአብሄር ፊት አነቡ። አዋጅን የሚሽር ሌላ አዋጅ ታወጀ። ሃማ መርዶኪዮስን ለመስቀል ባዘጋጀው እንጨት ላይ ተሰቀለ። ሃሌሉያ።

እንደዚሁም እኛ በእምነት፣  በጾምና በጸሎት እግዚአብሄር  ፊት ከቀረብን፣  ተአምራት ማየት እንችላለን። ቤተ ከርስቲያንን ከመፈራረስ ልናድናት እንችላለን። አንድነቷን ማስጠበቅ እንችላለን። ከርግማን ወጥታ ፈረንጆች ከሚያደርጉት በላይ ለወንጌል መስፋፋት የተሰለፈች ልናደርጋት እንችላለን።

እዚህ ላይ አንድ ትልቅ ቁም ነገር አንርሳ። በቤተ ክርስቲያኒቷ ያሉትን ችግሮች በማባባስ፣ የፖለቲክ ትርፍ ለማግኘት የሚሞክሩ፣ ዲያብሎስ እራሱ እየተጠቀመባቸው  ያሉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ይኖራሉ። በፖለቲካ እንቅስቃሴ ዉስጥ ገብቶ መሳተፍ የራሱ ቦታና ጥቅም ቢኖረዉም፣  በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ግን፣  የእግዚአብሄር ሥራ የሚሰራው በፖለቲካ መድረክ አይደለም። የእግዚአብሄር ሥራ የሚሰራዉ እንደ ወገዛ፣ ስድብ፣ መግለጫ ማዉጣት በመሳሰሉ የፖለቲካ መሳሪያዎችን በመጠቀም አይደለም። የእግዚአብሄር ሥራ የሚሰራዉ በመንፈሱ ነዉ። በቤተ ክርስቲያን ዉስጥ ችግር የሚፈጥሩ ካህንም ሆነ ጳጳስ ካሉ፣ የሚበቀላቸው እራሱ እግዚአብሄር ነዉ። «ፍርድ የኔ ነዉ!» ይላልና የሰራዊት ጌታ እግዚአብሄር።

በመሆኑም የምናቀራርብ፣ የምናስታርቅ፣ ልዩነቶችን የምናጠብ፣ መግባባት ንግግርና መቀባበል እንዲኖር የምናበረታታ ፣ የተሳሳተን በጨዋነት የምንገስጽ፣ የወደቀን የምናነሳ፣ የሚያጠፋን ከጥፋታቸውዉ የምንመልስ እንሁን እንጂ፣ በእሳት ላይ ነዳጅ አናርከፍከፍ።

እግዚአብሄር ልቦናችንን ለፍቅሩ አይምሯችንን ለጥበቡ ይክፈትልን !

 

 

 

Latest from Blog

[ማስታወሻ ከፍል አንድ፣ በዘሐበሻ ድረ ገጽ ላይ ኦፍ ጃዋር አንድ ኢትዮጵያ ተብሎ በእንግልዝኛ ወጥቷል] https://zehabesha.com/of-jawar-and-ethiopia/ ባለፈው ሰሞን፣ ጃዋር መሐመድ ከደረጀ ኃይሌ ጋር  በነገራችን ላይ ክፍል ሁለት ባደረገው ቃለ ምልልስ ላይ ተመስርቼ ገንቢ አስተያየት ጽፌ በኢንግሊዝኛው ዘሐበሻ ድረ ገጽ ላይ አሳትሜ ነበር። አስተያየቴ በዚህ ቃለ ምልልስ ላይ

ስለ ጃዋርና ኢትዮጵያ (ክፍል ሁለት)

January 20, 2025 ጠገናው ጎሹ የአቤ ጎበኛው አልወለድም ለወገኖቹ መብት መከበር ሲል ባደረገው ጥረት ምክንያት እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ ይሙት በቃ በፈረዱበት ጊዜ በምላሳቸው መልካም  አድርጎ ስለ መገኘት እያወሩ በድርጊት ግን ተቃራኔውን የሚያደርጉ ሁሉ

ወዮ ለመከረኛው የአገሬ ህዝብ እንጅ  ታየማ ታየ ነው

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ “ ሰው የሰነፎችን ዜማ ከሚሰማ ይልቅ የጠቢባንን ተግሣጽ መስማት ይሻለዋል። ”   — መክብብ 7፥5 እስቲ ቆም ብለን በማሰብ  ራሳችንን እንፈትሽ ።  እንደ ሰው ፣ የምንጓዝበት መንገድ ትክክል ነውን ? ከቶስ ሰው መሆናችንን እናምናለንን ? እያንዳንዳችን ሰው መሆናችንን እስካላመንን ጊዜ ድረስ ጥላቻችን እየገዘፈ

 ለሀገር ክብርና ብልፅግና ብለን ፤ ቆም ብለን በማሰብ ፤ ህሊናችንን ከጥላቻ እናፅዳ

                                                         ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)                                                       ጥር 12፣ 2017(January 20, 2025) ጆ ባይደን ስልጣናቸውን ለማስረከብ ጥቂት ቀናት ሲቀራቸው በአሜሪካን ምድር በጣም አደገኛ የሆነ የኦሊጋርኪ መደብ እንደተፈጠረና፣ የአሜሪካንንም ዲሞክራሲ አደጋ ውስጥ ሊጥለው እንደሚችል ተናግረዋል።  ጆ ባይደን እንዳሉት በተለይም በሃይ ቴክ

አሜሪካ ወደ ኦሊጋርኪ አገዛዝ እያመራ ነው! ጆ ባይደን ስልጣን ለመልቀቅ ጥቂታ ቀናት ሲቀራቸው የተናዘዙት!!

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
Go toTop