ድምጻዊያን አምና በዳላስ ዘንድሮ በሜሪላንድ

/

http://www.youtube.com/watch?v=levsOdg5j48
ጥበቡ ተቀኘ
ባለፈው አመት የአሜሪካን እትዮጵያዊያን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለሁለት በተከፈለበት ጊዜ ብዙ አርቲስቶቻችን ጥሩ ጥሩ ዳጎስ ያለ ብር በአላሙዲን ተከፍሏቸው ዲሲ ሲመጡ ያዩትን ውርደትና ቅሌት እነሱም ብሩን የሚያፈስላቸውም የማፍያ ግሩፕ የሚረሱት አይመስለኝም:: በተቃራኒው ደግሞ ዳላስ የነበረውን ዋናውን ፌዴሬሽን ለማገዝ ጥበብን ከህዝብ ጋር ካልሆነ በምንም አይነት ለብር አንገዛም በማለት የፈጣሪ ስጦታቸውን ተጠቅመው ህዝቡን ያዝናኑት እና ከጎኑ የቆሙት ያዩትን ደስታ እና አለም ታሪክ ሁልጊዜ በመልካም ሲያነሳው ይኖራል::
የጥበብ ባለሙያዎች ከህዝብ ውጭ ሌላ ምንም ሃብት እንደሌላቸው የታወቀ ነው:: ሲዲያቸውን የሚገዛው ኮንሰርታቸውን የሚታደመው በጭብጨባ የሚያበረታታቸው ህዝብ ብቻ ነው:: አላሙዲን የሚባለው ክፉ ጦስ ኪሳቸውን በጉርሻ ሲያሳብጠው ህዝብ ምን ያደርጋል? ብለው ለሃብታሞች ብቻ ለመዝፈን መወሰናቸው በጣም የሚያሳፍርና የሚያኮላሽ ተግባር ነው:: ዛሬ እንዲህ አይነት ተራ አስተሳሰብ ይዘው የሚጓዙትን እድሜ ይስጠንና እናያቸዋለን ነገ ስራዬን አድምጡልኝ ማለታቸው አይቀርምና::
ባለፈው አመት ዳላስ ከህዝባቸው ጎን በመቆም መከፋፈልን ሳይሆን አንድነትን ሲዘምሩና ሲዘፍኑ ከነበሩት ስመ ጥር ድምጻዊያን መካከል ማህሙድ አህመድ ጸሃይ ዮሃንስ አብዱ ኪያር እና ጎሳዬ ተስፋዬ ይጠቀሳሉ:: እነዚህ ታላላቅና ዝነኛ የኪነ ጥበብ ሰዎች የሚከፈላቸው ተራ የአላሙዲን ጉርሻ ሳያዝጎመዣቸው ህዝቡን ሲያዝናኑና አደራቸውን ሲወጡ ምን ያህል ክብርና ፍቅርን እንደሚያካብቱ ማሰብ የሚከብድ አይመስለኝም:: አንዳንዶቹ ድምጻዊያን ደግሞ ከሁለቱም ኳስ አንወግንም ብለው እንዳልሰሩ የማይካድ ሃቅ ነው ዛሬ ግን ድል ከህዝቡ ጋር እንደሆነ አውቀው ተቀላቅለውናል እናከብራቸዋለን:: ለክፉ ጊዜ ባይሆኑም ከመሰሪው አላሙዲን ጋር ባለመሆናቸው አስደስቶናል::
http://www.youtube.com/watch?v=odN5e8mwrS4
ዘንድሮ ያለፈውን ውርደት ለመድገም ወደ ዲሲ የመጡት ድምጻዊያኖችም ዲሲ አካባቢ በነጻነት የሚዟዟሩ አይመስለኝም ምክንያቱም ግልምጫውንና ስድቡን የሚችል አቅም ያላቸው ስለማይመስለኝ ነው:: ለነገሩ እንኳን እነሱ ዋና አዘጋጆቹም ቢሆን የአበሻውን ተቃውሞ እንደ ጦር እየፈሩ እንደሚጓዙ በአይናችን እያየነው ነው:: እንደውም እዚ ጋር አንድ ወዳጄ ያጫወተኝ ትዝ አለኝ:: ባለፈው መለስ ዜናዊ እዚህ አሜሪካ በአበበ ገላው ድምጽ እንደደነገጠ በዛው ሞቷል አሁን ደግሞ አላሙዲን ይሰደብና ደንግጦ አገር ቤት ሲመለስ ይሞታል ተብሎ እነደሚቀለድ ነግሮኛል:: ይህ መቼም የሚያሳየው ሰዎቹ ምን ያህል ህዝብን አንቀጥቅጠው እንደሚገዙ ነው አንድ ሰው እነሱን ክፉ መናገር አይፈቀድለትም:: ወይኔ ያገሬ ሰው!!
የኔ እምነት ማንም ሰው የፈለገውን የመደገፍና የመቃወም መብት እንዲሰጠው ነው ግን 30 አመት ያደረገን አንድ የኢትዮጵያውያን መገናኝ ኳሳችንን ለመበተን ለመከፋፈል እና ለወያኔ አላማ ለማዋል የሚደረገውን ጥረት እቃወማለሁ:: የሚደግፉትም አምነውበት ከሆነ ግድ የለኝም ውጤቱ እንዲህ 30 ሺ ለ ዜሮ መሆኑን ሲያውቁት ስህተት መሆኑን ሊረዱት ይገባል ባይ ነኝ::
የመደገፍና የመቃወም መብቴንም እያየሁት ያለሁት እዚህ አሜሪካ ነው እንጂ አገር ቤትማ ያለው ኢትዮጵያዊ በሙሉ ይህን እድል አላገኘውም የኢህአዴግ ደጋፊ ወይም አባል ካልሆነ አይማርም ቢማርም አይመረቅም ቢመረቅም ስራ አያገኝም ቢያገኝም አያድግም…. ኢህአዴግን መቃወም ሙሉ በሙሉ ወንጀል በመሰለበት በዚህ ጊዜ የአገር ውስጡ አልበቃ ብሏቸው ውጭ አገር ያውም አሜሪካ መጥተው ያልንህን ታደርጋለህ በሚል ማን አለብኝነት ሊበትኑን እና አፋችንን ሊያዘጉ ሲፈልጉ በጣም ይገርመኛል:: ታዲያ እነዚህን በመናቅና በብዙ ሚሊዮን ዶላር ያዘጋጁትን ድግስ ባለመሄድ ኢትዮጵያዊው ሁሉ ሲቀጣቸው ማየትና የታሪክ ምስክር መሆን እንዴት ደስ ይላል?
የተቆጣን እና በአላሙዲን የክፋት ተግባር የተናደድን ህዝቦች በመተባበር የምናደርገው ነገር ሁሉ ስሜት የሚነካ ነው ባለፈው አመት ዳላስ ላይ ስታዲየሙ በህዝብ ሞልቶ ሆ ሲል በአይኔ አይቻለው አሁን ደግሞ ሜሪላንድ የመክፈቻውን ስነስርአት የነበረው ዝናብና የተፈራው ስቶርም ሳይበግረው ይሄ ሁሉ ህዝብ ባንዲራውን ለብሶና ይዞ ሲከታተለው አይቻለው:: በጣም የሚይስደንቅና በቃላት ሊገለጽ የማይችል ከባድ የአገር ፍቅር ስሜትም ተሰምቶኛል::
መቼም ፈጣሪ ለኪነጥበብ ሰዎች የሰጣቸው የተፈጥሮ ስጦታ ይገርመኛል:: ያንን ሁሉ ሺ ህዝብ እያስደሰቱ መኖር ምን ያህል መታደልን እንደሚጠይቅ መቼም ለሁሉም ግልጽ ነው:: ባለፈው አመት ዳላስ ላይ ገጣሚ የዜማ ደራሲ እና ድምጻዊው አብዱ ኪያር እየዘፈነ የተሰማኝን ስሜት በምንም መልኩ ልገልጸው አልችልም:: መላ አካላቴን ውርር አድርጎኝ እንባ እንባ ይለኝም ነበር:: ህዝቡ በሙሉ ከዘፈኑ ጋር ያሳየው የነበረው እንቅስቃሴ ሁሉ አይኔ ላይ አለ::
ያልገቡበት የለም ያልገቡበት የለም
ሙቀትና ብርዱን ችለው በዚች አለም
ይቺ ቀን ታልፋለች እያሉ በማለም
ስትጣሪ ያልመጡት ጠልተውሽ አይደለም
እናቱን ሚጠላ ካንቺ አልተፈጠረም

ተጨማሪ ያንብቡ:  በቅርቡ የሚሆነውን ልንገርህ!! - ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

የከዳማ እናቱን
እንጃ አበሻነቱን…..
ዘንድሮ ደግሞ በሜሪላንድ የመክፈቻው ስነ ስርአት ላይ እነዛን በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ አርንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም ያላቸው አፉፋዎች የባህል ቡድኑ ወደ ሰማይ ሲለቋቸው ሳይ ይኸው ከባድ የአገር ፍቅር ስሜት መልሶ ነፍሴን ሲተናነቃት ይታወቀኝ ነበር:: ስሜቴን ደግሞ ይባስ ያወጣው የድምጻዊው ብርሃኑ ተዘራ(ያምቡሌ) የዘፈን ግጥም ነበር
ይሄ ሰው አማራ እረ ሚለው ማነው
ይሄ ሰው ኦሮሞ እረ ሚለው ማነው
ይሄ ሰው ከትግራይ እረ ሚለው ማነው
ይሄ ሰው ከደቡብ እረ ሚለው ማነው
ቢለያይም ቋንቛው ደማችን አንድ ነው

በናቴም አንድ ነኝ ባባቴም አንድ ነኝ
ከኢትዮጵያ አገሬ የለም የሚለየኝ….
የጥበብ ሰዎች ይህን ሁሉ የአምላክ ስጦታ ይዘው ከህዝባቸው ጎን ካልቆሙ በጣም የመሸማቀቅና የውርደት እድሜ እንደሚገፉ በታሪክ ያየነው ነው:: አላሙዲንም ወያኔም ያልፋሉ ያኔ ከህዝብ ፊት እንዴት ልትቆሙ ነው ምንስ ልትሉ ነው ማለት ይኖርብኛል ብዬ አምኛለሁ::
ይሄንን ጽሁፌን ከማጠቃለሌ በፊት ኳስና ዘፈን እንዲህ የህዝቡን ልብ ማማለል ከቻሉ ፖለቲከኞቻችንም ይህንን ጥበብ ሊካኑት ይገባል ባይ ነኝ:: መልካም የፍቅር እና የደስታ ኳስ ያርግላችሁ::

ጥበቡ ተቀኘ
July 01 2013

1 Comment

  1. this is what i call ethiopiawinet.
    much love for the true ethiopians. alamudin is going to die soon.

Comments are closed.

Share