በታሪክ ትምህርት የሚወሳ “የባሪያ ፈንጋይ ሥርዓት” የሚባል ማኅበረሰብኣዊ ዕድገት የወለደው ጥንታዊ ሥርዓት ነበር፡፡ ያ ሥርዓት በወቅቱ በሰው ዘር መካከል ትልቅ የልዩነት ቋጥኝ ፈጥሮ አንዱን ጌታ ሌላውን ሎሌና ከዚያም አልፎ የጊዜ ማሳለፊያና የመዝናኛ ዕቃ በማድረግ የማይፋቅ ጠባሳ አስቀምጦ ያለፈ ሥርዓት ነው(ሰውን ከአንበሣና ከነብር እያታገሉ በሰው ስቃይ የሚደሰቱ መኳንንትና መሣፍንት ነበሩ)፡፡ ለዚህ ሲያስቡት እንኳን ለሚዘገንን የታሪክ ስብራት አሜሪካ ኅያው ምሥክር ናት – ምንም እንኳ ነገሮች በተወሰነ መልክና ባልተጠበቀ መንገድ ቅርጻቸውን ለውጠው የጉዳቱ ሰለባዎች ለይስሙላም ቢሆን አሁን አሁን መንበረ ሥልጣን የጨበጡ ቢመስሉም የጓዳ ጎድጓዳው ታሪክ አሁንም ብዙ የተለወጠ አይመስልም – በጥቁርና በነጭ የሚታየው የዘር ልዩነት አሁንም ድረስ አልጠፋምና፡፡ አፍሪካውያንና ካሬቢያውያን በተለይም ጋናንና ቤኒንን የመሳሰሉ የባሪያ ንግድ ይጧጧፍባቸው የነበሩ ሀገሮችም ቋሚ ምሥክሮች ናቸው፡፡ የእነኩንታኩንቴ ታሪክ መቼም ቢሆን በኅያውነት ይቆያል፡፡ በኢትዮጵያም እነግንደበረትና እነሰሜን ሸዋ፣ እነቦንጋም ይመስክሩ፡፡ ቋንጃ መቁረጥ፣ የሰውን ልጅ ዛፍ ሥር ኮልኩሎ በወፈረና በከሳ፣ በዕድሜ በገፋና ባልገፋ፣ ባጠረና በረዘመ፣ ከብት ይመስል ጥርሱን በሸረፈና ባልሸረፈ … እየተባለ የሰው ልጅ እንደእንስሳና እንደአሞሌ ጨው በገንዘብ ወይም በዓይነት ይሸጥ ይለወጥ ነበር፡፡ ያ እንግዲህ ዱሮ ነው፡፡ አልፏል፡፡ መልኩን ቀይሮ በኢትዮጵያችን ሊያውም ሰላምን፣ ፍትህን፣ ነፃነትን፣ እኩልነትንና ዴሞክራሲን ከአንደበቱ በማይነጥለው የሕወሓት መንግሥት በዘመናዊ መልኩ አሁንና ዛሬ እውን ሲሆን ግን ምን እንላለን? “ጭቆናና መድሎ አስመርሮኝ ሕዝቤን ነፃ ላወጣ ለትግል በረሃ ወጣሁ” የሚለው ሕወሓት ጥንት የሞተን የባሪያ ፈንጋይ ሥርዓት ነፍስ ዘርቶበትና አቀንቃኝ ሆኖ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ብቅ ሲል በተለይ የድርጊቱ ሰለባዎች ምን ይዋጠን? አሣዛኝ ድርጊት በሀገራችን እየተፈጸመ ነው፡፡ እመለስበታለሁ፡፡
በምሥጋና መጀመር ነበረብኝ፡፡ ይቅርታ፡፡ ብዙም አልረፈደብኝም፡፡
በዚህን ሰሞን “ኑሮ በአዲስ አበባ” በሚል ርዕስ አንድ መጣጥፍ ማቅረቤን ተከትሎ ከወትሮው ለዬት ባለና እኔንም ባስገረመኝ ሁኔታ ብዙ አንባቢያን ልባዊ እርካታቸውን በመግለጽ በግል አድራሻየ መይለውልኛል፡፡ ለሁሉም በወቅቱ መልስ ሰጥቻለሁ፡፡ ግን በዚህ አጋጣሚ ለሁሉም በሁሉም አንባቢያንና በድረገፆቻችን ስም በድጋሚ ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ፡፡ ከውድ ጊዜያቸው ተሻምተው ያን ብሶት-ወለድ ረጂም መጣጥፍ በማንበባቸውና በኑሯችን ከምር አዝነውም ያን የመሰለ ነፍስና ሥጋን የሚያለመልም የሞራል ድጋፍ ከዚያቺው ዕንቁ ጊዜያቸው ሰውተው በመላካቸው አሁንም ምሥጋናየ ድንበር የለውም – ጫት ቤቶችንና መጠጥ ቤቶችን ስታዘብ በኛ ሀገር በኮንቴይነር አሽገን ወደዓለም የጊዜ ገበያ ኢክስፖርት ልናደርገው የምንችለው “ጊዜ” በብዛት እንዳለን ብገነዘብም በውጭ ሀገራት ለሰላምታ እንኳን ጊዜ እጅግ ውድና ብርቅ እንደሆነ እሰማለሁ – ለዚህም ይመስላል ሰዎች በእግር እየተጓዙ በተመሳሳይ ቅጽበት ስልክ የሚያናገሩት፣ ምግብ የሚመገቡት፣ ጽሑፍ የሚያነቡትና… በአካባቢ የሚከናወንን ነገር የሚቃኙት፡፡ አንዲት ደቂቃ ወርቅ ናት፡፡ እንደውነቱ ከሆነ ጽሑፍ መጻፍ ከጀመርኩ ጊዜ አንስቶ ጽሑፌን በማንበብ ይህን ያህል በሀገሩ ጉዳይ ልቡ የተነካ አንባቢ ገጥሞኝ አያውቅም፡፡ በኔ የጋዜጠኝነት ዕውቀት የአንድ ሰው አጸፋ(feedback) በመቶ ሰው ይመነዘራል፡፡ ስለዚህም እስካሁኒቷ ቅጽበት ብቻ በጎ አስተያየታቸውን የላኩልኝ 15 ሰዎች 1500 ሰዎችን እንደሚወክሉና አጻጻፌንና መልእክቴን ክፉኛ ነቅፎ የወቀሰኝ አንድ ሰው ደግሞ በሌላኛው ጎራ 100 ሰዎችን እንደሚወክል በወያኔያዊ ቋንቋ ግንዛቤ ወስጃለሁ፡፡ የዚህኛውን ሰው አስተያየት ለፍርድ እንዲያመች በመጨረሻው ላይ እንዳለ አስቀምጠዋለሁ፡፡ የሌሎችን ግን ሙያ በልብ ነውና በኔው ይቅር፡፡ ግን ግን አይዞን፤ እንደጨለመብን አንቀርም፡፡ የተበተነው የሚሰበሰብበት፣ የተራበ በልቶ የሚጠግብበት፣ ጠግቦ የሚዘል አደብ የሚገዛበት፣ ፍትህ ርትዕ የሚሠፍንበት፣ ፍቅርና መተማመን የሚናኝበት፣ የእህል በረከት የሚበዛበት፣ … እውነተኛ የመኖሪያ ድባብ በሀገራችን በጣም በቅርቡ ይፈጠራል፡፡ እንዲህ ይታየኛል፡፡ ገደሉን ጨርሰን ጫፍ የደረስንም ይመስለኛል፡፡ መመኪያየ ግን ኢትዮጵያን ፈጥሮ የማይረሣት አምላከ ኢትዮጵያ ወአምላከ ኩሉ ዓለም እንጂ ሰው አይደለም፡፡ተስፋችን እሱ ነው፡፡
ድረ ገፆችን በሚመለከት ሁሉንም ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ እነሱ ባይኖሩ የነፃነት ትግላችን በብዙ ማይሎች ወደኋላ ይቀር ነበር፡፡ ችግራችን እንዲሰማ፣ የሌላው ዓለም ሕዝብም እንዲያውቅልን፣ የነፃነት አርበኞች እንዲጠራሩና እንዲወያዩ … በማድረግ ረገድ እየከፈሉ ያሉት ከፍተኛ መስዋዕትነት በታሪክም በፈጣሪም ዘንድ ትልቅ ዋጋ የሚያሰጣቸው ነው፡፡ አምላክ ይጠብቃቸው፡፡
ይህን ስልም ከነህፀፃቸው ነው፡፡ ዓለማችን ምሉዕ በኩልሄ አይደለችም፡፡ ፍጹምነት የለም፡፡ ማንም በምንም ዓይነት መለኪያ ፍጹም አይደለም፡፡ ከዚህ ፍጹምነትን ከመሻት አኳያ ማናችንም ብንሆን በየሥራችን እንዳንታበይ ወንድማዊ ምክሬን መሰንዘር እወዳለሁ፡፡ ያጠፋን ሳይመስለኝ የምናጠፋበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ ዐውቀን የምናጠፋበት ጊዜም እንደዚሁ አለ፡፡ ቂም የምንቋጥር፣ በቡድን ስሜት በመገፋት በግል ያልበደሉንን የምናሣዝን፣ መቻቻልን የማናውቅ፣ በዱሮ በሬ የምናርስና ከረሜላ እንደከለከሉት ሕጻን በቀላሉ የምናርኮፍ፣ ወዘተ. አለን፡፡ ሰዎች እንደመሆናችን አመንነውም ካድነውም እንሳሳታለን፡፡ እኔ በበኩሌ እንደዚህ ነኝ፡፡ እሳሳታለሁ፤ በስህተቴም እጸጸታለሁ፡፡ ይቅር በሉኝ ብዬም የበደልኳቸውን ሰዎች ከልብ በመነጨ ስሜት እለምናለሁ፡፡ እንዲያ ስንሆን ይመስለኛል የሰው ልጅን የዕድገት መሰላል ወደላይ የምንወጣው፡፡ እንዲህ ካልሆን ታጥቦ ጭቃ እንሆናለን፤ ንግግራችንና ተግባራችንም ለዬቅል እንደሆነ ይቀራል፡፡ በንግግር ብዙዎቻችን እጅግ መሳጭ ነን – በምግባር ግን ያን ያህል አንሆንም፡፡ በጸጸትና በንስሃ፣ በመደማመጥና በመግባባት በተመሠረተ ይቅር መባባል መንፈሣዊ ፈውስን ካላገኘን በመጎሻመጥና በመገፈታተር፣ በትዕቢትና በትምክህት የትም አንደርስም – ምናልባት የነዚህ ነገሮች አባትና የክፋት አበጋዝ ወደሆነው የዲያብሎስ ቤተ መንግሥት ልናመራ እንችል ይሆናል – ያ ደግሞ ብዙ ልፋትና ድካም የለበትም፡፡ ቂምንና በደልን ሠርዞ (ልብ በል – ረስቶ አላልኩም! የተረሣ ይታወሳልና፡፡) በአንተ ትብስ በአንቺ ትብሽ በአዲስ መልክ ፍቅርንና መዋደድን መመሥረት ግን ከባድ ከባድ ቢመስልምና ቢሆንም ይቻላል – ባሕርያዊ እልኸኝነትንና ዕብሪትን ማሸነፍ ከጦርነቶች ሁሉ ከባዱ ይመስለኛል፤ ጽጌረዳ ታምራለች፤ ይቅር ባይነትም ሃሤትን የሚያረብብ ዕፁብ ድንቅ ነገር ነው – ወደአምላክም ያስጠጋል፤ ሁለቱም ግን እሾሃማ ናቸው – በቀላል አይገኙም፤ ጽጌረዳዋ እጅን የሚወጋ ጦረኛ እሾህ፣ ይቅርባይነትም ስሜትን የሚፈታተን መግነጢሳዊ ኃይል አላቸው፡፡ እስከማውቀው ድረስ ትዕቢትና እልኸኝነት ማንንም አዋጥተው አያውቅም፡፡ ስሙን ቄስ ይጥራውና ያን የአዳምና የሔዋንን ቀንደኛ ጠላትም ወደታችኛው ዓለም(the netherworld) ከገነት አውጥቶ ያሽቀነጠረው ይሄው ትዕቢት ነው፡፡
ሳልጠቀስ የማላልፈው ወቀሳ አለኝ፡፡ ይህ ወቀሳየ ደግሞ የኔ ብቻ ሣይሆን የብዙ ጸሐፍት መሆኑን እረዳለሁ፡፡ የችግር ትንሽና ትልቅ የለም ብዬ ስለማምን ይህንንም በመጠኑ ማንቀራበጡ አይከፋም ባይ ነኝ – ተገቢ ትኩረት ያልተሰጠው ትንሹ ችግር ነው አድጎ ትልቅ እሚሆን – “እማዬ፣ ምነው በዕንቁላሌ በቀጣሽኝ!” የሚለውን ሥነ ቃላዊ ብሂል እናስታውስ፡፡ አንድን ችግር ሳይብስበት መግለጡ ለመፍትሔው በግማሽ እንደመቅረብም ይመስለኛል፡፡ ‹ኑ እንዋቀስ‹ አልነበር የሚል ያ አላበሳው ተሰቅሎ የሞተ የዓለም መድሓኒት? ብንዋቀስ ምን ወጪ እናወጣለን? ተዋቅሰን ብንታረቅና የሰይጣንን ቀንድ ብንሰብር ተጠቃሚዎች ነን፡፡ ጥቅምን ደግሞ በግድ ከማቴሪያላዊ ጎኑ ብቻ ማየት የለብንም፡፡ እንደችግር ሁሉ የጠብም ትንሽና ትልቅ የለውም፡፡ ለምሳሌ የኔን ተግባርና ጠባይ ልትንቅ ትችላለህ – እኔን ግን ልትንቀኝ አይገባም፡፡ ነውር ነው፡፡ ኃጢኣትም ነው፡፡ እንዳንተው ሰብኣዊ ፍጡር ነኝና አንተ ባንተ ላይ እንዲያደርጉብህ የማትወደውን ነገር ሁሉ በኔ ላይ ልታደርግ አይገባም – ኮንፊውሸስ ተናገረው፣ አሊጋዝ ደገመው እውነቱ ይሄው ነው፡፡
ዝም ብዬ ሳስበው አንዳንድ ድረገፆች ምን እንደሚፈልጉ የሚያውቁ አይመስሉኝም፡፡ የሚፈልጉትን ነገር እንዳለማወቅ የመሰለ አስከፊ በሽታ ደግሞ የለም፡፡ ጅል ባህል ሆኖባት ሣይሆን አይቀርም ያገሬ ሣዱላ በፍቅር የነሆለለላትን ጉብል ንቃ (ባህሉን ስለሚያውቅ ሆን ብሎ እንድትወደው በማሤር የናቃት መስሎ የሚጀነንባትን ጭምር መሆኑን ልብ ይሏል) የሚንጠባረርባትንና የሚጠላትን እንደምታፈቅር ሁሉ አንዳንድ የድረገፅ አዘጋጆችም በፍቅር የሚንሰፈሰፍላቸውን ወገናቸውን ያለመለየት ችግር አይባቸዋለሁ፡፡ በበኩሌ ምን ስጽፍ በየትኞቹ እንደሚወጣና በየትኞቹ እንደማይወጣ አስቀድሜ ዐውቃለሁ – ባብዛኛው፡፡ ይህ ዓይነቱ መለስተኛ ልዩነት የሚለመድ ነው – በቂ ምክንያት ኖረውም አልኖረውም በበኩሌ ለምጀዋለሁና አንዳንዶች ነሸጥ አድርጓቸው ፊት ሲነሱኝ ማቅ አልለብስም፡፡ ደግሞም – በሚገባ አምናለሁ – የዜጎች ሁሉ አስተሳሰብና አመለካከት በግድ አንድ መሆን የለበትም፤ ልዩነት ይኖራል፡፡ ነገር ግን ልዩነት ይኖራል ሲባል በሁሉም ነገሮች በግድ መለያየት አለብን ማለት አይደለም፡፡ ልዩነትን ተገድደን የምንቀበለውና ለማጥበብም ከልብ የምንጥርበት ሊሆን ይገባዋል እንጂ በ“ማን ምን ያመጣል?” የፈግጠው ፈግጪው ሁከተኛ መንፈስ አነሳሽነት በቤተ ሙከራ ተፀንሶ የሚወለድና የሚያድግ በጥባጭ “in vitro son” ሊሆን አይገባም፡፡ አንድ ሊያደርጉን የሚችሉ ነገሮች መኖር አለባቸው፤ ማወቅ ስለማንፈልግ ይሆናል እንጂ የምንጋራቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ተቃዋሚዎችንና ወያኔን አንድ ሊያደርጉ የሚችሉ ነገሮች አይኖሩም ብዬ በበኩሌ አላምንም፡፡ በዚህኛውም ሆነ በዚያኛው ጎራ እንደአለመታደል ሆኖ ሁሉንም ነገር የመቃወም ባህል ስላዳበርን እንጂ በምንስማማባቸው ነገሮች እየተስማማን በማንስማማባቸው ነገሮች ብቻ ብንነጋገር ኖሮ ትልቅ ሸክም ከትከሻችን በወረደልን ነበር፤ ግን አንዱ ስንጥቅ ሌላውን ሸለቆ እየፈጠረ ነገረ ሥራችን ሁሉ ባቢሎን ሆኖ ቀረ፡፡ ልዩነት ደግሞ በባሕርይው ቶሎ ካላጠበቡትና ከነጭርሱ ካላጠፉት እየተምቦረቀቀ የሚሄድ ክፉ ደዌ ነው፡፡ በአሁኑ ሁኔታችን በአንድ ጎራ ውስጥ አሉ በሚባሉ ወገኖች መካከል እንኳን የልዩነት ቀዳዳዎች ሲሰፉ እንጂ ሲጠቡ አይስተዋሉም፡፡ ይህም መረገም ነው፡፡
ከዚህ አኳያ ያ የበቀደሙ ጽሑፍ በተለይ የዘወትር ደምበኛው በሆንኩት አንድ ድረገፅ ላይ ሳይወጣ ሲቀር ደንግጫለሁ፡፡ በተደጋጋሚ ብጠይቅም እነአያ ሰው ጤፉ ፀጥታን መርጠዋል፡፡ የሕዝብ ነፃነት ተሟጋች ማለት እንግዲህ እንዲህ ነው፡፡ ውሸታም በሏቸው፤ እኔም ብያለሁ፡፡ የአንድን ዜጋህን ጥያቄና ብሶት ለመጋራትና ስሜቱን ለመረዳት፣ ተረድተህም ለማረጋጋት ካልሞከርክ፣ ከዚያም ባለፈ በትዕቢት ተወጥረህ ከተጓደድህበት ውሸታምና የይመስል ታጋይ ነህ – “ፑቲካ!”፡፡ አንድ ዜጋ ክቡር ነው፡፡ ትግላችንም ለዚያ ነው፡፡ እኛ ዘንድ የሌለን መከባበርና መደማመጥ እሌላ ቦታ መፈለግ ላም ባልዋለበት ኩበት ለመልቀም እንደመሞከር ነው፡፡
አንድ ወቅት በጣሊያን ሀገር ለውኃ በተቆፈረ የ36 ሜትር ጥልቀት ጉድጓድ ውስጥ አንድ ሕጻን ይገባና መንደርተኛውና ጠበብቱ ሁሉ እንዴት ሕጻኑን ማውጣት እንደሚቻል በጉድጓዱ ዙሪያ ከብበው ይጨነቃሉ፡፡ በዚህ መሀል ወሬውን በተባራሪ የሰማው የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር ይመጣና አብሮ እየተጨነቀና እያዘነ ከሕዝቡ ጋር ሙሾ ያወርድ ገባ፡፡ ሰው ማለት እንዲህ ነው፤ መሪ ማለትም፡፡ ዜጋቸውን እንደትቢያ የሚቆጥሩ ወያኔዎችን የምንታገለው ሌላ የአፈና ሥርዓት አምሮን ሣይሆን የመሰለንንና የምናምንበትን የኛን እውነት በነፃነት መግለጽ እንድንችል ነው፡፡ እርግጥ ነው – አንድ ሰው ወይም አንድ ቡድን የተጻፈው ነገር ትክክል አይደለም ብሎ ሲያምን በዚያው መድረክ በተመሣሣይ መሣሪያ – በብዕር – አጸፋውን በመስጠት የማስተባበልና የማስተማርም ግዴታ አለበት፡፡ ከዚያ ውጪ ወደ አፍ እላፊና እጅ እላፊ እንዲሁም ወደመኮራረፍ መሄድ ከሰውነት ደረጃና ክብር መውጣት ነው፡፡ ሰዎች ወደነዚህ ጅላጅል አማራጮች የሚዞሩት ትግስት በማጣታቸው ብቻ ሣይሆን የእውነት ስንቅ ስለሚያጥራቸው በካፈርኩ አይመልሰኝ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ አዎ፣ እውነት ስታጥረን ሀሰት ከተፍ ትልና የተጓደለውን ነገር በዛቻም፣ በስድብና በጡንቻም ታሟላልናለች፡፡
የኔን ወረቀት ቦጫጭቆ የጣለው ያ ድረ ገፅ ግን አሁንም ድረስ ግራ እንዳጋባኝ አለ፡፡ እንደሰው ድረገፅ ከፍቶ ማስተናገድ ከጀመሩ በኋላ ቀጫጭን ሰበብ እየፈለጉ ተናጋሪን ለማፈን መሞከር ሳቢውን ግረፈው እንዲሉ ነው፡፡ ያበጠው ይፈንዳ – ይህ ዓይነቱ አፈና ከወያኔ ያልተናነሰ ብልግና ነው፡፡ ያ ጽሐፍ በዚያ ድረገፅ የቅርጫት እራት (በኮምቡጠር ቋንቋ የ“Trash” ቀለብ) ሆኖ ይቀራል ብዬ በእውኔ ቀርቶ በህልሜም አላሰብኩትም፡፡ ከናካቴው ያዩትም አልመሰለኝም፤ አይተውት ከሆነና በምንም ምክንት ይን ከተውት ግን በርግጥም የሚዲያ ሥራን አያውቁም፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ችግር ቆሜያለሁ የሚል “የነፃነት ዐርበኛ” ያን የመሰለ ከመስከረም በሉት፣ ከየካቲትም በሉት(በተወሰነ ደረጃም ቢሆን)፤ ከግንቦትም በሉት ከሌላ ማናቸውም ንቅናቄ ምንም ያህል የጠበቀ ግንኑነት የሌለውን ማኅበራዊ ጉዳይ ገሸሽ ሲያደርገው “የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” የሚለውን ክርስቶሳዊ ተማጽኖ ከማስታወስ ውጪ ሌላ ቃልም ሆነ አስተያየት የለኝም፡፡ የሚዲያ ሥራ ሆደሰፊነትን፣ ዕውቀትና ችሎታን፣ ሃቀኝነትን፣ አለማድላትን፣ አለማግለልን፣፣ ሙያዊ ትምህርትና ሥልጠናን፣ በጥቅም አለመደለልን … ይፈልጋል፤ ፈራጅና ዳኛው አንባቢ ወይም አድማጭና ተመልካች እንጂ እሱ የመረጠለትን ብቻ የሚያሣልፍ ከሆነ መጥፎ አሣላፊ ሆነ ማለት ነው፡፡ ጋዜጠኛ በሁለት የተራራቁ ጫፎች መሀል የተቀመጠ የሁለቱም ጫፎች የወል አገልጋይ እንጂ ከሁለቱ ወደ አንድኛው የሚሳብ ሊሆን አይገባም – ሰው ነውና አይሳብ አልልም፤ በሥራው ላይ እስካለ ግን አንዱን በመውደድ ሌላውን በመጥላት ሚዛኑን የሚስት ከሆነ የፓርቲ/የድርጅት ልሣን እንጂ የጋዜጠኝነት ሙያዊ ሥነ ምግባር የሚፈቅደው አሠራር አልተከተለም – ኅሊናውንም አቆሸሸ፡፡ ከዚህ መሠራተዊ መርህ አኳያ ድረገፆቻችን ቢፈተሹ … ለነገሩ ማነው ወንዱ ለመፈተሸ የሚነሣ! ማንስ ሊሰማው፡፡ ለማንኛውም ማንም ደመ ሞቃት ካለበቂ ሙያዊ ዕውቀትና ግንዛቤ ከሜዳ እየተነሣ ጋዜጠኛ ልሁን ቢል ኢቲቪን ከሚያስታውሰን በስተቀር ሊታይና ሊጨበጥ የሚችል የረባ ሥራ አይሠራም፡፡ ዐርፎ እቤቱ ቢቀመጥ ወይም ሌላ ነገር ቢሠራ ነው የሚሻለው፡፡ ከልብ ነው ያዘንኩት፡፡ ሰው ደግሞ በወደደው ያዝናል፡፡ አለበለዚያማ ስንትና ስንት ሺህ ድረገፅ ሞልቶ የለም እንዴ? ደግሞ ለድረገፅ! የኮምፒውተር እናት በድባብ ትሂድ፡፡ እኔም እዚህ ሀገር ውስጥ ቀረቀር ውስጥ አጓጉሊት ተሰንቅሬ ባልገኝ ኖሮ አሥሩን ከፍቼ አራውጠው ነበር፡፡(ብዙ ጊዜ የሚያሣዝነኝ ነገር – ብዙ ነገሮች ወደኢትዮጵያ ሲገቡ ተፈጥሯቸውን ይለውጡና amorphous ይሆናሉ – ቅርጽ አልባ፡፡ ጥሎብን ፖለቲካችንም ሸፋፋ፣ ንግዳችንም ሸፋፋ፣ ዕድገታችንም ኳሻርኳራዊ ምች ያጠናገረው ግንጥል ጌጥ፣ የትምህርት ሥርዓቱ ሸፋፋ፣ መንግሥታዊ ተቋማችን ሸፋፋ፣ የግብርና የቀረጥ አተማመን ደንባችን ሸውራራ፣ መሪዎቻችን የአእምሮ መካኖች፣ አንዳችን ለአንዳችን ያለን አመለካከት ሸፋፋ፣… በአሁኑ ወቅት ምን ያልተንሻፈፈ ነገር አለን? በመጪው ዘመን ስንቱን ሸፋፋ አቃንተን እንደምንዘልቀው ፈጣሪ ይወቅ፡፡)
ወደጥንተ ነገራችን እንመለስ፡፡
ባጭር ባጭሩ ልንገራችሁ፡፡ ዘመናዊ ባርነት በኢትዮጵያ ነግሦኣል፡፡ እንዲህ ስላችሁ ባለፈው ጦማሬ እንደገለጸኩት ብዙዎቻችን የምንጠበስበትን የኑሮ ውጣ ውረድና የፖለቲካ እመቃ ማለቴ አይደለም፡፡ ከዚያም የከፋ የለዬለት ዘመናዊ ባርነት አለላችሁ፡፡(በነገራችን ላይ ባለፈው ጽሑፌ የአንድ ኪሎ ብርቱካን ዋጋ 22 ብር ገደማ ያልኳችሁ በጣም ተሳስቻለሁ – 45 ብር ገብቷል አሉ፤ ልብ አድርግ የአንድ ኪሎ ብርቱካን በችርቻሮ የመሸጫ ዋጋ 45 ብር ብቻ! ጉድ በል ጎንደር ማለት አሁን ነው፡፡)
ሚሚ ስባሃቱን የማያውቅ መቼም አይኖርም፡፡ የማታውቋት ካላችሁ – በቪኦኤ የአማርኛው ክፍል ትሠራ የነበረች፤ ከዚያ ተባርራ ይሁን በራሷ ፈቃድ ወጥታ ወደኢትዮጵያ የገባችና በርሷና በባሏ ስም የመነሻ ፊደላት “ዛሚ” ተብሎ በሚጠራ የኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ በአብዛኛው ወያኔን እያገለገለች የምትገኝ “ጋዜጠኛ” ናት – አንዳንድ ማኅበራዊ ችግሮችን ማንሳቷንም አልክድም፤ ይህንን በጎ ሥራዋን በአወንታዊነት አደንቃለሁ፡፡ … አዜብ መስፍን የምትባለዋን ጉድ ደግሞ የማያውቅ ይኖራል ብዬ አልገምትም፡፡ እንደድንገት የማያውቅ ቢኖር አዜብ መስፍን ወይም አዜብ ጎላ ማለት የቀድሞውንና የዐፅመ-ዕድሜ ልክ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ጨምሮ የብዙዎች ሚስት እንደነበረችና እንደሆነች በብዛት የምትታማና – የአሁን ሁኔታዋን እንጃላት እንጂ – ወንዶችን ብቻ ሣይሆን ንግዱንና የንግዱን ማኅበረሰብ በሞላ እንደፈለገች የምታተረማምስ ሦስተኛዋ ዮዲት ጉዲት እንደሆነች የሚነገርላት ልዩ እስፊንክስ(Sphinx) ናት – ወደመጀመሪያዋ ዮዲት መሄድ ሳያስፈልገን ከሌላኛዋ መበለት ከገነት ዘውዴ ቀጥላ መሆኑ ነው ሦስተኝነቷ፤ ( እንዳለመታደል ሆኖብኝ አንዳንዴ ፈታ ብሎ መናገር ደስ ስለሚለኝ እንጂ ስለዚች ሴትዮ የግል ጠባይ እዚህ መናገሬ ስህተት መሆኑን ዐውቃለሁ፤ ሂሴን ውጫለሁ፡፡) እነዚህ ሁለቱ አዜብና ሚሚ የሚሰኙ ጉዶችና ሌሎች እነሱን የተከተሉ ጥቂት የማይባሉ ባሪያ ፈንጋዮች በሀገራችን የሚሠሩት ተዓምር ልዩ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የዛሬ አሥራ ሦስት ዓመት ገደማ በአንድ ታዋቂ የግል ጋዜጣ አንድ መጣጥፍ ማውጣቴ ትዝ ይለኛል – ሰሚ ግን አልተገኘም፡፡ መጯጯኽ እንጂ መደማመጥ ብሎ ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ ጭራሽ የለም፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ የነሚሚና አዜብም ሆነ የሌሎቹ በሥራ አስቀጣሪነት ፈቃድ አውጥተው በሕዝብ የሚነግዱ ድርጅቶች ሠራተኞችን “ሥራ እናስቀጥራችኋለን” በሚል በየሙያ ዘርፉ ይመዘግባሉ፤ ይመለምላሉ፡፡ የተወሰነ የአጭር ጊዜ ሥልጠናም ሳይሰጡ አይቀሩም፡፡ በተለይ የጽዳትና የጥበቃ ሠራተኞችን፣ የጉልበት ሥራና መሰል አገልግሎት የሚሰጡ ሠራተኞችን የሚፈልጉ መሥሪያ ቤቶች ወደነዚህ ባሪያ ፈንጋዮች ዘንድ በመሄድ የሚፈልጉትን የሠራተኛ ዓይነት እንደፍላጎታቸው መርጠው ይወስዳሉ፡፡ ቀጣሪዎች፣ ደሞዝ ከፋዮች፣ አስጠንቃቂዎች፣ ከሥራ አሰናባቾች፣ … እነዚሁ አስቀጣሪ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ሰዎቹን ወስዶ የሚያሠራቸው ድርጅት ግንኙነቱ ከ“ባሪያዎቹ” ጋር ሣይሆን ከአስቀጣዎቹ ድርጅቶች ጋር ነው፡፡ ይህ ዘመናዊ የባሪያ ፍንገላ አሠራር በሀገር ውስጥ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ መንግሥት የፈቀደላቸው የሚባሉ ወደውጪ ሀገራት በተለይም ወደዐረቡ ዓለም የቤትና የጉልበት ሠራተኞችን የሚልኩ አሉ፡፡ የሚያስከፍሉት ገንዘብ አንጀትን ይመዘምዛል አሉ፡፡ የነሱን የመጓጓዣና የደላላ ወጪ ለመክፈል የሚፈጀው ጊዜ የወላጅንና የተደጓሚ ቤተሰብን አንጀት በርሀብ ያነጥፋል፡፡ በዚያ ላይ አንዴ ከላኳቸው በኋላ ቢቀቀሉ ቢገነተሩ መብታቸውን ለማስከበር ዘወር ብለው አያዩዋቸውም ይባላል፡፡ አበሻ እንዲህ ሆዳምና ጨካኝ የሆንነው ግን ከመቼ ጀምሮ ይሆን እባካችሁ? የነሚሚ ጦስ ድንበር ዘለል ነው፡፡ ገንዘብ ባለበት ወያኔ አለ፡፡ ንግድ ባለበት – እዚህ በተጨባጭ እንደምናየው ሰውም ይሸጥ መሬትና ተንቀሣቃሽ ንብረትም ይሸጥ – ወያኔና የሙስና እናት የምትባለዋ አዜብ አይጠፉም፡፡ ይቺ የመርገም ፍሬ ሴትማ የጉልት ሴቶችን ሳይቀር በሽርክና አስገቡኝ ከማለት አትመለስም ይባላል – ፈጣሪን ምን ብንበድለው ይሆን ግን ለዚህ ለወሬ እንኳን ለማይመች መከራና ስቃይ የዳረገን? ይህችን ሴት ባሰብኩ ቁጥር አንዳርጋቸው ጽጌ(አንዱ) የተናገራት cringe የምትል ቃል ትዝ ትለኛለች፤ አዎ፣ ምን የመሰለ ድንቅ ታሪክ ያለን ሕዝብ ይቺን በመሰለች ሴት ስንታመስ በርግጥም መሸማቀቅ ሲያንሰን ነው፡፡ ለማንኛውም በነዚህ ሴቶችና ተባባሪዎቻቸው መሬት መሸከም የሚከብዳት ግዙፍ ግፍና በደል እየተፈጸመ ነው፡፡ ከፍ ሲል የጠቀስኩላችሁ የሀገር ውስጥ ባሪያ ፍንገላ የደመወዝና የጥቅማጥቅም ነገር ሲነሳ ነው ግፉ ቁልጭ ብሎ የሚታየን፡፡ በጥቂቱ እንየው፡-
እኔን የቀጠረኝ የግል ድርጅት ከነዚሁ የድሃን ደም መጣጮች ነው የጽዳትና የጥበቃ ሠራተኞቹን የተኮናተረው፡፡ እነዚህ ምሥኪን ሠራተኞች ደሞዛቸውን የሚያገኙት ከኛ ድርጅት ሣይሆን ከቀጠራቸው አስቀጣሪ ድርጅት ከነሚሚ ወይም ከነአዜብና መሰሎቻቸው ነው – አንዳች ሳይለፉ በድሃው ጉልበት የማይነጥፍ የነዳጅ ጉድጓድ የቆፈሩ ዘራፊዎች፡፡ የኔ መሥሪያ ቤት ለአንድ ጥበቃ ብር 1100(አንድ ሺህ አንድ መቶ ብር) ለቀጣሪ-አስቀጣሪው ድርጅት ይከፍላል፡፡ አስቀጣው ድርጅት ከዚህ ገንዘብ ውስጥ ግማሹን ለሥራ ማስኬጃ ይቀነድብለትና ግማሹን ብር 550 ለሠራተኛው በየወሩ ይከፍለዋል – በመረጃ የተደገፈ ወሬ ነው የምነግርህ፡፡ ይህ ሠራተኛ የኛ ድርጅት ቋሚ ቅጥር ቢሆን ኖሮ አንደኛ ደሞዙ ከዚህ አሁን ከሚከፈለው ሻል ሊል ይችል ነበር – የኛ ድርጅት ጭንቅላት የለውም እንጂ ቢኖረው ኖሮ ማለቴ ነው፡፡ ሁለተኛ የሕክምና ዋስትና ይኖረው ነበር፡፡ ሦስተኛ የጡረታ ዋስትና(Provident Fund) ይቆረጥለት ነበር፡፡ አራተኛ የሥራ ዋስትናው አሁን ካለበት ሁኔታ በጣም የተሻለ ይሆንለት ነበር(አሁን እንደ ዕቃ ነው፤መናገር፣ ማጉረምረም፣ መውቀስ፣ ምናምኒት አይችልም – ወዲያውኑ ይባረራል፡፡) እኛ ቢያንስ በግል ስንገናኝ የማጉረምረም መብታችን የተጠበቀ ነው፡፡ እነዚህ በወር 550 ብር የሚከፈላቸው የጥበቃና ጽዳት ሠራተኞች ባለፈው ጦማሬ የገለጽኩላችሁን የአዲስ አበባ የኑሮ ውድነት እንዴት ሊቋቋሙት እንደሚችሉ እንግዲህ አስቡት፡፡ የዱሮ ባሪያ ደረጃውን የጠበቀ አይሆን እንደሆነ እንጂ ቢያንስ በሕይወት ሊያኖረውና ሥራውን በአግባቡ እንዲሠራ ሊያደርገው የሚችል ምግብ ይሰጠው ነበር፡፡ የዘመናዊ ባርነት ሰለባዎች ግን የላባቸውን ውጤት የሚበላው ሌላ በመሆኑ ለትራንስፖርትም በማይበቃ ገንዘብ ጉልበታቸው ይበዘበዛል፤ ሥራ አላቸው እንዲባሉ ግን ውለው ይገባሉ፡፡ እነዚህ አስቀጣሪ ድርጅቶች በመያዶችና በዓለም አቀፍ ድርጅቶችም ያስቀጥራሉ፡፡ ከዚያም አካባቢ እንደሰማሁት ባሪያ ፈንጋዮቹ በብዙ ሺዎች ይቀበሉና ለሁለተኛ ዙር ተቀጣሪው ሠራተኛ የሚያቀምሱት በቡና ሥኒ ነው አሉ፡፡ ሰው ሌላ አማራጭ ስለሚያጣ በግዱ ወደነዚህ ድርጅቶች ይሄዳል፡፡ ወደ አሠሪዎቹ ድርጅቶች ሄዶ መቀጠር እንዳይችል እነዚህ የኔን ቀጣሪ ድርጅት መሰል ድርጅቶች ኃላፊነትን ይሸሻሉ፡፡ ከሠራተኛ ቁጥጥር፣ ከጥቅማጥቅም፣ ከሠራተኛና አሠሪ የክስ ውጣ ውረድና ከመሳሰለው የተገላገሉ እየመሰላቸው በእጅ አዙር የሰውን ጉልበት ይበዘብዛሉ፡፡ ግፍ በየዓይነቱ የሚናኝባት ብርቅዬ ሀገር አለችን፡፡
መፍትሔው ምን ይሁን ትላላችሁ? መፍትሔው እንደኔ የአስተሳሰብ ለውጥ ነው፡፡ የወያኔ ዓይነቱ ትውልድን አምካኝ የትምህርት ሥርዓት ሣይሆን ሥጋንና ነፍስን የሚያስታርቅ መንፈሣዊና ዓለማዊ ትምህርት ያስፈልገናል፡፡ በኢትዮጵያችን የሞራል ዕሤቶች ታጥበው ገድል ከገቡ በኋላ ይመስለኛል ይህ ዓይነቱ የጅብ ባሕርይ ወደ ሰዎች የተጋባው፡፡ እንጂ አምስት መቶ ብር ለውሻው የወር ባጀት እንደማይሆን የሚረዳ አንድ ሀብታም “ኢትዮጵያዊ” ዜጋ እንዴት አንድ መሰል ዜጋውን በዚህ ደሞዝ ያሠራል? ምን ዓይነት ደደብነት ነው? በተዘዋዋሪ ቀጥሮ የሚያሠራቸው ድርጅትስ ቢሆን ምናለበት ይህን ችግር ተገንዝቦ ራሱ በቀጥታ ቢቀጥራቸውና ያን አላግባብ የሚመዘበር ገንዘብ ለነሱ ቢያደርገው? ምን ዓይነት ሁልአቀፍ የሆነ የአስተሳሰብ ስንኩልነት ነው እየታዘብን የምንገኘው? አእምሮ ወዴት ገባ? ወዴት ሸፍቶ ይሆን? እዚች ላይ ትንሽ እንጸልይ መሰለኝ፡-“ አቤቱ የሰማዩ አባታችን እግዚአብሔር ሆይ፣ በሞራ የተሸፈነ ኅሊናችንን ግለጥልንና እውነቱን እንድናይ አድርገን! ለሰዎችም እንድናዝን የርህራሄና የመተሳሰብን መንፈስ በላያችን አሳድርልን፡፡ ለይቶልን ሳንጠፋ ጭል ጭል በምትለዋ እስትንፋሳችን ላይ ሞልቶ ከሚፈሰው የማያልቅ ቸርነትህ ላክልንና ወደየልቦናችን ተመልሰን እንድንተዛዘን፣ እንድንፈቃቀድም አድርገን፡፡ ጨርሰን ሳንጠፋብህ በመሀከላችን ገብተው የሚያበጣብጡንን የፍቅረ ንዋይና የአምልኮተ ንዋይን መንፈስ፣ የዘረኝነትና የሙስናን ደዌያት አስወግድልን፡፡ አሜን፡፡”
ችግርን ከማውራት የምገላገልበትን ጊዜ በጣም ናፍቄያለሁ፡፡ ሁልጊዜ ስለችግር ስለማወራ ራሴኑ ጭምር እንደችግር ማየት ከጀመርኩ ቆይቻለሁ፡፡ ከዚህ ቅኝት ለመውጣት ወደፊት ትልቅ ትግል ሳይጠብቀኝ አይቀርም፡፡
ወደ ሌላ ችግር፡፡ ሰሞኑን የወያኔው መንግሥት 37ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በዕጣ ማከፋፈሉ ይታወሳል፡፡ ዕጣ አወጣጡ ራሱ ችግር እንዳለበት ሰምቻለሁ፡፡ እመለስበታለሁ፡፡
ዕጣ ያልወጣላቸው ሰዎች “እንኳንስ ዕጣ አልደረሰኝ!” እያሉ የሚደሰቱበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ምክንያቱም አስቀድሞ የሚከፈለው ገንዘብ ከየት መጥቶ ይከፈል? ዕጣ የደረሳቸው አንዳንድ ጓደኞቼ “ምን ቅብጥ አድርጎኝ ነው የተመዘገብኩት”እያሉ ሲያማርሩ ታዝቤያለሁ፡፡ ምዝገባው የተካሄደው ቀደም ሲል ነው፡፡ ሰው ደግሞ ሲመዘገብ አንዳንዱ ለደራ ነው – ዕድሉን ለማየት፡፡ አንዳንዱ – እንዲያውም ብዙው ከመኖሪያ ቤት ችግሩ አንጻር ነው፡፡ አንዳንዱ ለትርፍ ነው – ቤት እያለው ግን ኮንዶምንየሙን ሸጦ ትርፍ ለማግኘት፡፡ አቤት የመጥፎ ጠባያችን አበዛዙ! ስንትና ስንት ሌላ አማራጭ እያለው ለዚች የአንድና የሁለት ክፍል ጎጆ ከድሃው ጋር ሙሉ ቀን ተሠልፎ የድሃውን ዕድል የሚያሰነካክል ሀብታም ታያለህ፡፡ በሚስቱም በልጁም በዘመዱም ስም ብዙ ቤት እያለው ለዚች ትንሽዬ ነገር የድሆችን ዕድል ሲያጨነግፍ የምታየው ገብጋባ ሰው አለ፡፡ ብዙ ችግር እኮ ነው ጓዙን ጠቅልሎ ወደሀገራችን የገባው፡፡ ለሰው ደግ መመኘትና “ይህ ለኔ በቂ ነው፤ ይህም የሌላቸው አሉና ለነሱ ይሁን” ብሎ ማሰብ ቀርቷል፡፡ እናላችሁ አዳሜ ዕድሏን ለመፈተንና “ከዚህ ወይ ከዚያ በማገኘው ገንዘብ አሟልቼ ቅድሚያ ክፍያውን እከፍላለሁ፣ ከዚያም እኔ በአነስተኛ ገንዘብ እከራይና ቤቱን በትልቅ ዋጋ አከራይቼ ወይ ሸጬ በማገኘው ትርፍ ዕዳየን በቶሎ አጠናቅቃለሁ” ብላ አስባ ስታበቃ አሁን ዕጣው ሲወጣላት ጊዜ ምኑን ከምን ታ’ርገው? ለምሳሌ በምዝገባው ወቅት 60ሺህ ብር ገደማ ተብሎ የተነገረው የባለ ሁለት መኝታ ቤት ኮንዶምንየም የቅድሚያ ክፍያ አሁን በወቅቱ የገንዘብ ምንዛሬ ተሻሽሎ ከ80ሺህ ብር በላይ ሆኗል፡፡ አንዱ ጓደኛየ የዚሁ ቤት ዕጣ ደርሶት ዕጣው ከወጣበት ዕለት ጀምሮ የሌት እንቅልፉንና የቀን ሰላሙን አጥቷል፡፡ የርሱ ደሞዝ ከዕለታዊ መጠነኛ ኑሮ አያልፍም፡፡ በዕቁብም ሆነ ወደፊት የሚከፈል ተብሎ በብድር መልክ ከሰው ማግኘት የሚታሰብ አይደለም – ከመነሻው ድሃን አምኖ የሚያበድረውም የለም፡፡ ብድርና ቁጠባ ቢል ያጠራቀመው በጣም ጥቂት ነው፡፡ ፒኤፍ ቢጠይቅ እሺ አልተባለም – ቢፈቀድለት እንኳን አይሞላለትም፡፡ ሥራውን ለቅቆ ፒኤፉን እንዳይወስድ በዛሬ ጊዜ በመከራ የሚገኝና በዘመድ አዝማድ በተቆላለፈ ማኅበረሰብ ውስጥ ሌላ ሥራ መፈለጉ መድሓኒት የሌለው ትልቅ ራስ ምታት ነው፡፡ እናም እንዲሁ እየዋተተ አለ፡፡ በዚህ ሁኔታ የሚቸገሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ይህ አጋጣሚ ደስታ ሀዘንን ሲወልድ ያየሁበት ልዩ አጋጣሚ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይህን የኮንዶምንየም ቅድሚያ ክፍያ በሴከንድ ውስጥ የሚከፍሉ ግን ባለአነስተኛ ደሞዝተኞች አሉ፡፡ እነዚህም የሙስናው ሞተር አሽከርካሪዎችና ልየ ልየ የጎን ገቢ ያላቸው ናቸው፡፡ ሙስና ካለ እንኳንስ ኮንዶምኒየም ኦሮጵላንም ይገዛል፡፡ ይብላኝ ዙሪያ ገባው ለጨለመበት ተራው የመንግሥትና የግል ድርጅቶች ሠራተኛ! ይብላኝ በረንዳዎችን ሙጥኝ ብሎ ለሚገኘው በመቶ ሺዎች ለሚገመተው ዜጋ፡፡ ስለወቅቱ የሥራ አያያዝ ሁኔታ ግን ትንሽ ላውራችሁ፡፡
በዛሬ ጊዜ ይገርማችኋል ወርቅ የሆነ የሥራ ችሎታና ወርቅ የሆነ ጠባይ ቢኖርህ ሰው የሚቀጥርህ ዘርህን ጠይቆ ነው፡፡ የሀገራችን ሠራተኛ ያሣዝናችኋል፡፡ በየጠላና አረቂ ቤቱ ስዘዋወር የምሰማው የዘረኝነት መዘዝ የፈጠረው ብልሹ አሠራር ዕበድ ዕበድ ነው የሚለኝ፡፡ ምን የመሰለ የግምበኝነትና የአናፂነት ሙያ እያለው ትግሬ ወይም ኦሮሞ ባለመሆኑ ብቻ የሚቀጥረው አጥቶ ሲንቀዋለልና በየቁንድፍት ቤቱ ጉበቱን ሲያቃጥል የሚውለውንና የሚያመሸውን ዜጋ በቤቱ ይቁጠረው ብቻ የምንተወው ሣይሆን እኔም ያቅሜን ተዘዋውሬ ተመልክቻለሁና እስክሞት የማይረሳኝ ዕድሉ ከገጠመኝም ምሥክርነቴን በኃያሉ አምላክ ፊት ሣይቀር የምሰጥለት የሀገራችን የወቅቱ ነቀርሣ ነው፡፡ ከዘበኝነት አቅም ዘርህና ጎጥህ ተቆጥሮና ማንነትህ ተጠንቶ ነው የምትቀጠረው – በር እየከፈተ መኪናን ማስወጣትና ማስገባትም ከቁም ነገር ተጥፎ እንዲህ ያለ መድሎ ይታያል፡፡
በዕጣው አወጣጥ ችግሮች እንደነበሩበትም ይነገራል፡፡ ወያኔ ለማስመሰል ድራማው በዕጣው ቤት ይደርሳቸዋል ተብለው ከማይጠበቁ ዜጎች ከዚህም ከዚያም ለአንዳንዶች ጣል ጣል አደረገ እንጂ የአንበሳ ድርሻውን ለራሱ ካድሬዎችና ለሚፈልጋቸው ወገኖች በዕጣ አስመስሎ እንደሸለማቸው በስፋት ይወራል፡፡ ለምሳሌ በአንድ መሥሪያ ቤት ለብዙ የሥራ ሂደት ባለቤቶችና የፖለቲካ ሠራተኞች እንደደረሰና ያን የመሰለ አጋጣሚ እንዴት በዕጣ ሊወጣ እንደቻለ መነጋገሪያ እንደሆነ ከቅርብ ሰው ተረድቻለሁ፡፡ ለነገሩ በህዳሴው ግድብ ሥራ ማስጀመሪያ የመጀመሪያዋ ዕለት እንደተወለደና ስሙም ህዳሴ ለተባለ ሕጻን የህዳሴው የስልክ ሎተሪ ዕጣ የመኪና ሽልማት እንደደረሰ በሚነገርባት ሀገር፣ አንዲት የ14 ዓመት ታዳጊ ወጣት በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቷ ባሳየችው የበጎ አድራጎት ሥራ የተመሰጡት ትምህርት ቤቷና ሌላ ድርጅት በጋራ ሆነው የኢትዮጵያን ዓመታዊ አጠቃላይ በጀት ሊሆን የሚዳዳው የ20 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት እንደተቀበለችና ያንንም ገንዘብ – ድምቡሎ ሣታስቀር(እንዴት ያለ ቱጃር ቤተሰብ ነው ያላት ጃል!) ለትምህርት ቤት ግምባታ ልታውለው ለመንግሥት እንዳበረከተች በሚነገርባት የወያኔ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ዕጣ ሸር የለበትም ብሎ መቀበል ከየዋህነትም የዘለለ ሞኝነት ነው፡፡
በመጨረሻም አስቀድሜ እንደጠቆምኩት ትዝናኑበት ዘንድ አንድ ወንድም ከቦስተን ማሳሹተስ የላከልኝን ኢሜይል እንዳለ በኮፒ/ፔስት ከሥር አስቀምጣለሁ፡፡ “ያልተነካ ግልግል ያውቃል” ይባላል፡፡ እኔ በመምህር የሚታረም የፈጠራ ድርሰት የጻፍኩ ይመስል ስለ አጻጻፍ ሥልቴ አይረቤነት ያወራል፡፡ ችግራችንን ዘረዘርኩ እንጂ ሥነ ጽሑፍ አልጻፍኩም፡፡ ችግርን ለመናገር ደግሞ አንድ ሰው በልምድም ይሁን በትምህርት የሚያውቀው (አነስተኛም ቢሆን) የንግግርና የጽሑፍ ችሎታ በቂው ነው – መራቀቅና ተቺየ እንደሚለው coherence, cohesive device ቅብጥርስ እንዲያውቅ አይጠበቅበትም፡፡