March 18, 2015
4 mins read

በፊንጫ ስኳር ቃጠሎ የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉ ታወቀ

(ሰንደቅ ጋዜጣ) ፊንጫ ስኳር ፋብሪካ መጋቢት 5 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ 5 ሰዓት ገደማ የሸንኮራ አገዳ ገለባ (ባጋስ) ማቀጣጠያ ክፍል በተነሳ ቃጠሎ የአንድ ሠራተኛ ሕይወት ሲያልፍ በአስራ ስድስት ሠራተኞች ላይ ከባድና ቀላል የመቁሰል አደጋ ማድረሱን የኮርፖሬሽኑ የኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት የሚዲያ ግንኙነት የቡድን መሪ ለሰንደቅ ጋዜጣ አረጋገጡ።

የሚዲያ ግንኙነት ቡድን መሪው አቶ ጋሻው አይችሉም ስለቃጠሎው ከሰንደቅ ጋዜጣ ተጠይቀው ሲያስረዱ፣ “የሸንኮራ አገዳ ገለባ (ባጋስ) ማቀጣጠያ ክፍል ለፋብሪካው አማራጭ የኃይል አቅርቦት የሚሰናዳበት ክፍል ሲሆን ለማቀጣጠያ ግብአትነት የሚውለው የአገዳ ገለባ ደረቅ በመሆኑ በቀላሉ ቃጠሎ ሊነሳበት የሚችልበት እድል ሰፊ ነው። የተነሳውን የእሳት ቃጠሎ ለማጥፋት በተደረገው ርብርብ የአንድ ሰራተኛ ሕይወት ሲያልፍ፣ በአስራ ስድስት ሠራተኞች ላይ ከባድና ቀላል የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል። ቀላል አደጋ ከደረሰባቸው ሠራተኞች መካከል አምስቱ በፋብሪካው የሕክምና ማዕከል ተገቢውን እርዳታ ተደርጎላቸው በጥሩ ጤንነት ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ አስራ አንዱ ግን በቤቴል ሆስፒታል ተኝተው እየታከሙ ናቸው” ብለዋል።

በፋብሪካው የተነሳው የእሳት ቃጠሎ በዕለቱ በቁጥጥር ስር መዋሉን የቡድን መሪው ጠቁመው፤ የፋብሪካው ሰራተኞች፣ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ መከላከያ ሰራዊት፣ ፌደራል ፖሊስ፣ እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እሳቱን በማጥፋት ከፍተኛ ድርሻ ነበራቸው። እንዲሁም ሁለት ሂሊኮፕተሮችም ተሳታፊ እንደነበሩ ጠቅሰዋል።

ለቃጠሎው መነሳት ትክክለኛ ምክንያቱን እየተጣራ መሆኑ የገለፁት አቶ ጋሻው፣ የደረሰውም ውድመት ምን ያህል እንደሆነ ግምቱ እየተሰራ ነው ብለዋል። ለጊዜው ግን ለቃጠሎው መነሻ ምክንያት ያለው ግምት የአካባቢው ሙቀት ሳይሆን አይቀርም ሲሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ ቃጠሎው ከደረሰበት ቅዳሜ መጋቢት 5 እስከ መጋቢት 7 ቀን 2007 ዓ.ም ድረስ ስራ ለማቆም የተገደደ ሲሆን፤ ከማክሰኞ መጋቢት 8 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ አገዳ መፍጨት በመጀመሩ ከ16 ሰዓታት በኋላ ስኳር ያመርታል ተብሎ ይጠበቃል።
የፊንጫ ስኳር ፋብሪካ በተደረገለት አዲስ የፋብሪካ ማስፋፊያ ግንባታ የመፍጨት አቅሙን በቀን ወደ 10ሺ ኩንታል ማሳደጉ ይታወቃል። በሙሉ አቅሙ መስራት ሲጀምር በቀን 12ሺ ኩንታል ያመርታል ተብሎ ይጠበቃል።3⁄4

Previous Story

ድርጅት በሕዝብ ካልተደገፈ የመርካቶ ሱቅ ነው – አማኑኤል ዘሰላም

Next Story

“በመጪዎቹ ሳምንታት በቦይኮት እና ህዝባዊ እምቢተኝነት ላይ ያተኮሩ መርሃ ግብሮች ይኖሩናል” – ድምጻችን ይሰማ

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop