May 25, 2013
19 mins read

በሚኒሶታ ለቤተክርቲያን ሰላምና አንድነት ከቆሙ ምእመናን የተላለፈ ጥሪ

በስመ አብ ወወለወድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ፤ አሜን!

ግንቦት ፳፻፭ ዓ.ም

ባለፉት ፳ ዓመታት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ላይ የደረሱ ጥፋቶችና በደሎች ባጭሩ እና የምንገኝባትን ቤተክርሰቲያን አንድነትና ሰላም አጽንተን ስለመጠበቅ።
ለቤተክርቲያን ሰላምና አንድነት ከቆሙ ምእመናን
ሚኔሶታ

 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ቀኖና በመጣስ በሥርዓትና በምልዐት የተሾሙትን ፓትርያርክ ከመንበራቸው በማውረድና በማባረር
 ወያኔ የራሱን ጉዳይ አስፈጻሚ ጳጳስ በመንበሩ በመሾሙ ምክንያት የቤተክርስቲያኗ አባቶችና ምእመናን በታሪክ ባልታየ ሁኔታ እንዲከፋፈሉ ተደርጓል
 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ለኢትዮጵያ ዳር ድንበር መከበር ለታሪክና ለቅርስ መጠበቅ ያበረከተችው አስዋጽኦ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ነበር። ነበር መባሉ ግን እጅግ አሳዛኙ በዘመናችን በምሬት የምንቀበለው እውነታ ሆኗል።
 የወያኔ ባለስልጣናት በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ የጽርፈት ነገር ሲያስተጋቡ ቤተክርስቲያኗን ይመሩና መንጋዋን ይጠብቁ ዘንድ የተሾሙ አባቶች ድርጊቱን ሳይገስጹና ሳያወግዙ በዝምታ አልፈውታል።
 አቶ ተፈራ ዋልዋ፣ አቶ ስብሐት ነጋ፣ አቶ አባይ ጸሐዬና ሌሎችም ባለሥልጣናት በግልጽ የቤተክርስትያኗን ህልውና ሲያንቋሽሹና ሲያዋርዱ ተሰምተዋል። ለምሳሌም ያህል ኦርቶዶክስ የነፍጠኛ ዋሻ ነች፣ መነኮሳትን የተለየ የፓለቲካ አጀንዳ ያላቸው ናቸው፤መለኪያው ኦሮቶዶክስና አማራ የነበረውን ሥርዓት ሰብረነዋል ወዘተ የሚሉ የድፍረትና የማዋረድ ቃላት ሲነገሩ መስማቱ እንግዳ አይደለም።
 በአባቶች መካከል የተፈጠረውን መለያየትና መወጋገዝ በመፍታት ሰላምና እርቅን ለማምጣት ግድ ያላቸው ውድ የቤተክርስቲያን ልጆች ጥረት በከንቱ ሲመክን የአባቶች ዝምታ እና የዚሁ ሰላምንና አንድነትን የማፍረስ የአመጸኝነት ተግባር አካል መሆን እጅጉን አሳፋሪና አስነዋሪ ክርስቲያናዊ ያልሆነ ተግባር ነው። ይህንን የብዙዎችን ተስፋ ያጨለመ ድርጊት አስመልክቶ በሁለቱም ወገኖች ይሁንታን ካገኘ በኋላ የማደራደር/የማስታረቅ/ ወንጌላዊ ተግባር ሲያከናውን የነበረው የኢትዮጵያ ኦ/ተ/ቤ/ክ የሰላምና አንድነት ጉባዔ ለዓመታት የተለፋበት የሰላምና እርቅ ሂደት አስመልከቶ የካቲት 12/2005 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የእርቅና የሰለም ሂደቱ እንዳይሳካ ያደረጉትን ዋና ዋና ምክንያቶችን ሲገልጽ፦
 1. ‘‘ በኢትዮጵያ ያሉ አንዳንድ አባቶች ከቤተክርስቲያን ሰላምና አንድነት ይልቅ ለሢመተ ፓትርያርክ ቅድሚያ በመስጠታቸውና የላኳቸውን ልዑካን ሪፖርት ሳይሰሙ አስመራጭ ኮሚቴ መሰየማቸው፤
 2. የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የሰላምና አንድነት ጉባዔ አባላት በልዑካኑ የስምምነት ውሳኔ መሰረት ወደ አዲስ አበባ ቅዱስ ሲኖዶስ ተሰይመው ከሔዱ በኋላ የተላኩበትን ዓቢይ የቤተክርስቲያን ጉዳይ ለቅዱስ ሲኖዶስ እንዳያቀርቡ እስካሁን ድረስ እንኳን ማንነታቸው ባልታወቁና ባልተረጋገጠ ግለሰቦች ተላለፈ በተባለ ሕገ ወጥ ትእዛዝ ወደ መንበረ ፓትርያርኩ ቅጽረ ግቢ እንዳይገቡ በጥበቃ ሰራተኞች መከልከላቸው፤
 3. ከዚህም በላይ እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ አንደኛውን ልዑክ ካለአንዳች ምክንያት በግዳጅ ከሀገር እንዲወጡ መደረጉ ሁለተኛውንም ልዑክ በማጉላላትና ወደ ቤተክህነት ግቢ እንዳይገቡ በማገድ በቀጠሮ እንኳን ለሚጠብቃቸው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ከላይ የዘረዘርናቸውን የመፍትሔ ሃሳቦች የያዘውን የሰላምና አንድነት ጉባዔ ደብዳቤ አቅርበው እንዳያስረዱና ቅዱስ ሲኖዶስ በጉዳዩ እንዳይመክርበት መደረጉ
 4. ገና ከጅምሩ ጀምሩ እርቀ ሰላሙን የማይፈልጉና በግልጽ ይቃወሙ የነበሩ አንዳንድ አባቶች ፈጽሞ የተዛባና ከእውነት የራቀ መሠረተቢስ መረጃ ለመንግስት ባለሥልጣናትም ሆነ ለኅብረተሰቡ መስጠታቸው
 5. በሐዋሪያዊት ቤተክርስቲያናችን ፍጹም ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን ለማድረግ ላለፉት ሦስት አመታት ሲካሔድ የቆየው የእርቀ ሰላም ጥረት ከዳር እንዳይደርስ በሚፈልጉ ጥቂት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት አማካይነት ቅዱስ ሲኖዶስ እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆኖ የተጀመረው የእርቀ ሰላም ውይይት ለውጤት እንዲበቃ ባለማድረጉ ምክንያት መንግስት በቅዱስ ሲኖዶስ ሉዓላዊ ሥልጣን ላይ ግልጽ ተጽእኖና ጫና በማድረጉ
 6. በመጨረሻም ጥር 8/2005 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚገኘው ቅዱስ ሲኖዶስ ስድስተኛ ፓትርያርክ ለመሾም በችኮላ መወሰኑ የሰላሙን በር ከመዝጋቱም በላይ የእርቀ ሰላሙን ውጤት በጸሎትና በታላቅ ተስፋ ሲጠባበቅ ለቆየው መላው ሕዝበ ክርስቲያን ታላቅ መርዶ ሆኗል።’’ በማለት በዝርዝር አስረድቷል። ከዚህም ሌላ በቅርቡ በቤተክርሰተያኗ ላይ እየደረሰ ያለውን በደል ብንመለከት
 የታላቁ ሰማዕት የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ከስፍራው ሲነሳ የአባቶች ዝምታ ወይንም የድርጊቱ ተባባሪ መሆን፣
 የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ተቋም በአንድም በሌላም ምክንያት ሲዘጋ የአባቶች ዝምታ ወይም የድርጊቱ ተባባሪ መሆን
 ከሁሉም በላይ ደግሞ አሁን በቅርቡ ለዘመናት በኢትዮጵያ ሕገ-መንግስትና በፍታብሔር ሕግ ውስጥ እውቅናና ሕጋዊ ሰውነት የተሰጣትን ቤተክርስቲያን ሕጋዊ መብቷን ለመግፈፍና ለማፍረስ እንደ ማንኛውም በኃይማኖት ስም እንደተራጁ ድርጅቶች እንደ አዲስ ተመዝግባ ፈቃድ በማውጣትና በማሳደስ ብቻ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባት የሚገልጽ ረቂቅ አዋጅ ወጥቶ ቀርቧል። ይህም ቤተክርስቲያንን የማዳከሙና የማፍረሱ ታላቁ ሤራ አንዱና ትልቁ እቅድ መሆኑ አያጠራጥርም። ይህ ሁሉ ሲደረግም የቤተክርስቲያናችን አባቶች ዝምታ እጁጉን የሚያስደምም ሆኗል።
 ወያኔ በያዘው የጸረ-አማራነትና ጸረ-ኦርቶዶክስ ፖሊሲ በአርሲ፣በጅማ፣በደቡብ ህዝቦች፣ በጎንደር፣በደሴ፣ በአሰቦት፣በዝቋላ፣በ ዋልድባ ገዳማት፣ቤተክርስቲያናት፣ካህናትና ምእመናን ላይ ሞት፣መቃጠል፣ዝርፊያና ውድመት ሲደርስ የቤተክርስቲያኗን መብትና የምእመናንን ደህንነት ለመጠበቅ የተሾሙ አባቶች በማወቅም ሆነ በቸልተኝነት ዝም ብለው በማየት የዚህ ሁሉ በደል ፈጻሚዎችና አስፈጻሚዎች ደጋፊ እና ተባባሪ ሆነው መገኘታቸው በጣም አሳዛኝና ሐዋርያዊ ተልዕኮን መዘንጋት ነው።
 የዋልድባ ገዳም ወደስኳር ፋብሪካት እየተቀየረ ነው። የአባቶች ዝምታ ወይም በድርጊቱ ተባባሪ መሆን ፣
 ዜጎች በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አባላት ያለምንም ወንወጀል ከቤት ንብረታቸው ሲፈናቀሉ፣ለስደትና ለእንግልት ሲዳረጉ የሚያጽናናቸው አባት አጥተው ምስካዬ ኅዙናን የተባለች ቤተክርስቲያንን መጠጊያና መሸሻ ለማድረግ ሲሞክሩ ከቤተክርስቲያን ቅጽር እንዲባረሩ መደረጉ በዘመናችን ያሉ ‘ብጹአን አባቶች’ ታረክ መሆኑ እጅግ ከማሳዘን አልፎ በርግጥም መጽሐፍት እንደሚነግሩን የተመረጡን እስከሚያስት ድረስ ተዐምራትን ያደርጋል የተባለለት የመጨረሻው ዘመን መንፈስ በግልጥ እየሰራ ያለበትን ዘመን መሆኑን የሚያሳስብ ነው።ይህም ለእውነትና ለኃይማኖት፣ለቤተክርስቲያንና ለመንጎቿ የሚገደው አባት ፈጽሞ የጠፋበት ጊዜ ላይ መድረሳችንን የሚያስዳ ነው።
 እንግዲህ በዚህ ሁኔታ ነው በቤተክርስቲያን ላይ ጥቃትና ደባ ከሚፈጽምና ከሚያስፈጽም መንግስት ተብዬ ጎን እንቁም፤ እርሱን ከሚደግፉና የጉዳዩ አስፈጻሚ ከሆኑ አባቶች ጋር አብረን እንሰለፍ እየተባለ የሚሰበከውና የሚነገረው???!!!

በውጪ አገራት ያሉ ቤተክርስቲያናትን አስተዳደርና አመሰራረት በተመለከተ

 በውጪ አገራት ያሉ ቤተክርስቲያናት የሚቋቋሙበት ሕግና ሥርዐት በሚገኙበት አገር የቤተክርስቲያናትና ሌሎች ከታክስ ነጻ ለመሆን የሚመሰረቱበት ሕግና ደንብን ተከትሎ መሆኑን ባለመረዳት በቤተክርስቲያናት መካከል ልዩነት ያለ ይመስል እኛ ከቤተክርስቲያን ተገልለናል እነዚያ በዚህኛው እነዚያ በዛኛው ሲኖዶስ ሥር ናቸው ሲባል ይሰማል።
 ነገር ግን ሁሉም ቤተክርስቲያናት የሚተዳደሩት ባሉበት አገር ህግና ተቀባይነት ባለው መተዳደሪያ ደንብ ወይንም ባይ ሎው መሰረት በቦርድ አመራር ሰጪነት ከቀረጥ ነጻ የሚያደርጋቸውን ሕግ የሚያከብሩ ሲሆኑ ነው። ቤተክርስቲያናቱም ያለልዩነት በቦርድ ኦፍ ትረስቲስ ነጻ አገልጋዮች ብቻ የሚመሩና በየአመቱ ከቀረጥ ነጻ የሚያደርጋቸውን ቅጽ እየሞሉ የእድሳት ፈቃድ እያወጡ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው። አሁን ያለውን የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ቃለ-አዋዲ የውጪ አገር መንግስታትና ሕጎቻቸው የማያውቁትና በውጪ አገር ሊሰራበት የማይችል ነው። ስለሆነም ወደ እናት ቤተክርስቲያን ይሁን በስደት ባለው ሲኖዶስ ሥር እንሁን የሚለው አካሔድ ከምኞት የማያልፍ ነባራዊ ሁኔታን ያለመረዳት ነው። ምክንያቱም ሁሉም በአንድ አይነት ሕግ ብቻ የሚመሰረቱና የሚተዳደሩ በመሆናቸው።
ስለሆነም ልዩነት ያለው ወገንተኝነትን ከመግለጽ አኳያ ብቻ ነው። ይህም ከመንበራቸው የተባረሩትን ወይም በወያኔ የተሾሙትን ፓትሪያርኮች ስም በመጥራትና ባለመጥራት የሚገለጽ ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ ጉዳዩን በመረጃ በተደገፈ ማጣራት የጉዳዩን ወይም የልዩነቱን መንስዔ በትክክል አውቆ ለመወሰን አስቸጋሪ ሁኔታ በመፈጠሩ ምክንያት ሁለቱ ወገኞች በሰላምና በእርቅ ሂደት ወደ አንድነት እስካልመጡ ድረስ እንደ ክርስቲያን የችግሩን ውል በሚገባ ሳያውቁ ለዚህኛው ወይንም ለዛኛው ወገን ወግኖ መገኘት ኢክርስቲያናዊ በመሆኑ የሁለቱንም ወገኖች/ፓትርያርኮች ስም ከመጥራት በመቆጠብ ወደ ሰላምና አንድነት የሚመጡበትን መንገድ መደገፉ ትክከለኛ አማራጭ መሆኑ የታመነ ነው።
 በየደብረሰላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ሁሉም ወገኖች የቤተክርስቲያኑን አቋም እስካከበሩ ድረስ መጥተው መባረክ፣ ማስተማርና መቀደስ አልተከለከሉም።
 በዚህም መሰረት በኢትዮጵያ ሲኖዶስ ስር ያሉም ሆኑ በውጪው ያሉ እንዲሁም ከሁለቱም ወገን ያልሁ አባቶች በተለያየ ጊዜ መጥተው ቀድሰዋል፣ አስተምረዋል ፣ቡራኬ ሰጥተዋል።
 ከላይ እንደተጠቀሰው መለያየቱ ያሳሰባቸው ውድ የቤተክርስቲያኗ ልጆች በከፍተኛ ጥረት የሰላምና እርቅ ኮሚቴ አቋቁመው ለሦስት ዙር ያህል ጥረት አድርገው ውጤቱም በግልጽ በዚሁ ኮሚቴ እንደተገለጸው ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ አንዳንድ ለስልጣን በቋመጡ አባቶችና አይዟችሁ ባዩ መንግስት ተብዬ እንዲጨናገፍ ሆኗል። በእግዚአብሔር ተስፋ አይቆረጥምና አሁንም ቢሆን ወደዚሁ የእርቅና ሰላም ሒደት እንደሚመለሱ ተስፋ እናደርጋለን።
 ይህም በእግዚአብሔር ፈቃድ እስኪፈጸም ድረስ ወገንተኝነትን ለቤተክርስቲያን ብቻ በማድረግ በእውነትና በእምነት መጽናት አማራጭ የሌለው መንገድ ነው። በጭፍን ከዚህኛው ወይንም ከዚያኛው ወገን መወገን ግን ለሥርዓተ ቤተክርስቲያን መጣስ፣የእርቅና ሰላም ሒደት እንዳኖር፣ ለሕሊናና ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለጥቅምና ለወገኔ ይድላው በማለት ከኃይማኖት መውጣት ነው።
 ስለዚህ የምንገኝበትን ቤተክርስቲያን ሰላምና አንድነት አጽንተን በመጠበቅ በተስፋ እየኖርን ለእግዚአብሔር መንግስት ለመብቃት እንዘጋጅ።

የሰላም አምላክ ሰላምን ያድለን
አንድነታችንን ይጠብቅልን አሜን!

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop