(24/10/2014)
ሞረሽ ወገኔ የባህል ማህበር በስዊድን
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ከሸገር ራዴዮ ጣቢያ ጋር በ09/08/2014 ያደረጉት ቃለ መጠይቅ ምንም እንኳ አማራውን አስመልክቶ የሰጡት ማብራሪያ እርስ በራሱ የተምታታ ቢሆንም፣ አማራውን ህዝብ የለም ከማለት አልፈው በአርባ ጉጉ በአማራው ህዝብ ላይ የተፈጸውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ክደዋል። የፕሮፌሰር መስፍን ክህደት ’እስላም ኦሮሞዎች ክርስቲያን ኦሮሞዎችን ነበር የገደሉት’ ለማለት ከሆነ፣ ሀቁና መረጃዎቹ ከፕሮፌሰር መስፍን ክህደት ጋር እንደማይጠጣሙ በተከታታይ መረጃዎችን እየመዘዝን የአርባ ጉጉን እልቂት ለማቅረብ እንሞክራለን። ወይም ጉልበታቸው ለፈረጠመ ወንጀለኞች መውጫ ቀዳዳ በመፈብረክ የተለመደው የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ”የወንድ በር እንስጥ” ፍልስፍናም ከሆነ በአማራው ህዝብ ላይ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ያልተፈጸመና ያልተደረገ አያደርገውም ልንላቸው እንገደዳለን። ከአባሎቻችንና ከደጋፊዎቻችን ጋር ለመወያየት የግብዣ ወረቀት ከላክን በሗላ፣ ከስብሰባው በፊት በአማራው ህዝብ ላይ በአርባ ጉጉ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ፕሮፌሰሩ መካዳቸው ብዙዎችን እንዳስቆጣቸው መልክት ሲደርሰን፣ እኛም አንድን ሰው ከሀዲ ከማለታችን በፊት መረጃዎችን አቅርቦ ፍርዱን ለአንባቢ ለመተው፣ በጊዜው የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት ለኢህአዴግ፣ ለውጭ መንግስታት ዲፕሎማቶችና ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲደርስ ያወጣውን የአቋም መግለጫ ከሞላ ጎደል ይህን የመስላል።
የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት ’መአህድ’ ኢህአዴግ በካድሬዎቹ አማካኝነት በአማራው ላይ የሚያካሂደውን የእልቂትና የሽብር ዘመቻ እያፋፋመው የአማራ ህዝብም ከፋሽስቶች ዘመን በባሰ ሁኔታ እያለቀ መሆኑን ባወጣው የአቋም መግለጫ አብራርቷል።
የመአህድ ፕሬዜዳንት ለሽግግር መንግስቱ ምክር ቤትና ለልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ባቀረቡት መግለጫ ላይ እንዳብራሩት በአማራው ህዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለው ግፍና በደል ”ሰብአዊ አእምሮ ሊሸከመው የማይችል ነው” በተለይ ከግንቦት 26 ቀን 1984 ዓም ጀምሮ ጭፍጨፋው በከፋ መልኩ እንዲቀጥል ተደርጎ የጭፍጨፋው ሰለባ የሆነው አማራ ሬሳው በገደል ውስጥ እንዲጣልና በቤት ውስጥ እንዲቃጠል እየተደረገ ነው። ይላል
”ከግንቦት 26 ቀን 1984 ዓም ጀምሮ በአማራው ላይ ከፍተኛ ጭፍጨፋ የተካሄደው በአርሲ ክፍለ ሀገር በአንቦሳ ከተማና በአካባቢው ነው። ኢህአዴግ በዚህ ስፍራ የሚኖሩ ተወላጆችን ሰብስቦ ’በነዚህ መንደሮች የሚኖሩ አማሮች ይገደሉ ብላችሁ ፈርሙ’ በማለት ትእዛዝ ሰጠ።
በማግስቱ ግንቦት 27 ቀን 1984 ዓም አቡሌ የተባለውን መንደር በኦህዴድ (የኦሮሞ ህዝብ ዲሞክራቲክ ድርጅት) የታጠቀ ወታደር ተከቦ ተኩስ ከተከፈተ በሗላ መንደሩ በላውንቸር መደብደብና ማቃጠል ሲጀመር ህዝቡ ህይወቱን ለማዳን ህዝቡ በየአቅጧጫው መሸሽ ጀመረ። ከሚሸሹት መካከል 30 ህጻናት ቤተክርስቲያን ቅጽር ግቢ እንደተጠጉ ከቤተክርስቲያኑና ከካህናቱ ጋር ተቃጥለዋል። አከታትሎም 150 የአማራ ነዋሪ ቤቶች እንዲቃጠሉ ተደርጓል።
የአውራጃው የኢህአዴግ ተወካይ አቶ ዲማ ጎርሜሳ ለወራሪው ሰራዊት ”አማራን መጨረስ ዛሬ ነው” የሚል መፈክር በማሰማት አበሳ የሚባለው የአማሮች መንደር እንዲከበብ አስደርገው ህዝብ ከቤቱ ሳይወጣ መንደሩ እንዲቃጠል ተደርገ። በመንደሩ ከነህይወታቸው በቤት ውስጥ እንዳሉ የሞቱት ቁጥር የማይታወቅ ሲሆን የቤቶቹ ጠቅላላ ብዛት 150 ነው። ከቃጠሎው የተረፉት 50 ሰዎች ተይዘው በጥይት ተረሽነዋል።
በሌላም አሼ በተባለ መንደር በአማራ ተወላጆች በአካባቢው የሚፈጸመውን ሰቆቃ እየተመለከቱ የመንግስት ሃይል ያድነናል ብለው ሲጠብቁ 25 ሰዎች የኢህአዴግ ሰራዊት ፈጅቷቸዋል።
በጉና ወረዳ አዲስ አለም በተባለ ቦታም 150 ቤቶችን ከነነዋሪዎቹ ከማቃጠላቸውም ሌላ ሁለት የአገር ሽማግሌዎች እጅ እግራቸውን አስረው አቃጥለዋቸዋል።
ዋቄንትራ ከተባለው መንደር 100 ቤቶችን ከነነዋሪዎቹ አቃጥለዋቸዋል።
መሶ የተባለውን መንደር በጦር እንዲከበቡና 100 ቤቶች እንዲቃጠሉ ተደርጓ ከቃጠሎው የዳኑት 80 ሰዎች እጃቸው ታስሮ በኦህዴድ (የኢህአዴግ አንዱ ክፍል) ተረሽነው ሬሳቸው ቆሬ ከሚባል ገደል ውስጥ እንዲጣል ተደርጓል። አንድ ሰው በተአምር ከዚህ መአት ተርፏል።
እንደሴ ባዩ የሚባለው መንደር ነዋሪ የሆኑ አማሮች በተመሳሳይ ሁኔታ በኦህዴድ ሰራዊት እነዲከበቡ ከተደረገ በሗላ ከመንደሩ ነዋሪዎች መካከል 80 የሚሆኑት እጅ እግራቸውን ታስረው ተወስደዋል። ወደ ገደል እንደተወረወሩም ይወራል።
ስድስት ቤተ-ክርሲቲያናት በዚህ አካባቢ ተቃጥለዋል። ይህ ሁሉ የተፈጸመው ግንቦት 27 ቀን 1984 ዓም በአንድ ቀን ነው ሲል የመአህድ መግለጫ አብራርቷል።
እንግዲህ ፕሮፌሰር መስፍን በሸገር ራዲዮ ጣቢያ የካዱት ይሄንን በአማራው ህዝብ ላይ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው።
[email protected]