የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ፕሬዚዳንት ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ውድቅ ሆነ

“ጉዳያችን በዓለምአቀፍ ፍ/ቤት ችሎት ይታይልን” ተከሳሾች

በአሸናፊ ደምሴ (ሰንደቅ ጋዜጣ)

የጋምቤላ ህዝቦች ንቅናቄ ግንባር በሚል ራሱን በሚጠራው ቡድን ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ነበር ሲል ዐቃቤ ሕግ በሽብር ወንጀል ክስ የመሠረተባቸው፤ የቀድሞ የጋምቤላ ክልል አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሚስተር ኦኬሎ ኦኮያን ጨምሮ ሰባት ተጠርጣሪዎች ያቀረቧቸው አራት የክስ መቃወሚያዎች ፍርድ ቤት ውድቅ አደረገ። ትናንት ነሐሴ 13 ቀን 2006 ዓ.ም በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት ተከሳሾች ድርጊቱን አልፈፀምንም ከማለታቸው ባሻገር ጉዳያችን በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት መታየት እንደሌለበትና መከሰስም ካለባቸው ወደ ዓለምአቀፉ ፍ/ቤት (አይ.ሲ.ሲ.) ችሎት መሄድ ይገባናል በሚል ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

የፌዴራሉ ዐቃቤ ሕግ በክስ ዝርዝሩ እንዳስረዳው ተከሳሾቹ ከላይ በተጠቀሰው ድርጅት ስር በመሆን የጋምቤላ ክልልን በኃይል ከፌዴሬሽኑ ለመገንጠል በማሴር፤ የጦር መሣሪያ አቅም በማደራጀት፤ የብርና የስልጠና ድጋፍ ከውጪ ሀገር በማግኘትና የወንጀል አድማ ስምምነት በመፈፀም ከ2000 ዓ.ም በፊትም በጋምቤላ ክልል ደግ ወረዳ የወርቅ ቁፋሮ በሚያደርጉ ሰዎች ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል በሚልና በተያያዙ የሽብር ወንጀሎች ክስ መስርቶባቸዋል። በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ክሱ የተነበበላቸው ተጠርጣሪዎቹ በተከላካይ ጠበቃቸው በኩል የክስ መቃወሚያዎችን በፅሁፍ አቅርበዋል።

ተከሳሾቹ ያቀረቧቸው አራት የክስ መቃወሚያዎች ዐቃቤ ሕግ በክሱ እንዳስረዳው ከ1996 ዓ.ም እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ ተፈፅሟል ብሎ የጠቀሰው ድርጊት የሽብር አዋጅ አንቀፅ ስር አይወድቅም፤ የጋምቤላ ህዝቦች ንቅናቄ ድርጅት በሽብርተኛ ቡድኖች ስም ዝርዝር ውስጥ ያልተካተተ በመሆኑ የሽብር ቡድን አባላት ተብለን መጠራት የለብንም፤ የወንጀል ድርጊቱን የፈፀሙት የደቡብ ሱዳን አማጽያን ሆነው ሳለ እኛ መጠየቅ የለብንም የሚለውንና የሽብር ክሱ ይቀየርልን የሚሉ መቃወሚያዎችን አቅርበዋል።
በነዚህም የክስ መቃወሚያ ነጥቦች ላይ ዐቃቤ ሕግ መልስ የሰጠ ሲሆን፤ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ የቡድኑ የሽብር ድርጊት ያላቋረጠ በመሆኑ በሽብር አዋጅና በተጠቀሰው አንቀፅ ስር መካተት ይቻላል። የጋምቤላ ህዝቦች ንቅናቄ አሸባሪ ቡድን አይደለም ለተባለው መቃወሚያ ቡድንም ሆነ ግለሰብ ለሽብር ተግባር እንቅስቃሴ ውስጥ ከተገኙ ከተጠያቂነት እንደማይድኑ በህጉ መጠቀሱን ያስታወሰ ሲሆን፤ በመጨረሻም ድርጊቱ ከደቡብ ሱዳን ተነስቶ የተፈፀመ ቢሆንም የሽብር ድርጊት ተጠቂ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት በመሆኑ በሽብር ህጉ አንቀፅ አራት ስር የተዘረዘሩትን ድጋፎች ለመስጠት ተባብራችኋል የሚሉ መከራከሪያዎችን ለፍርድ ቤቱ በፅሁፍ አቅርቧል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የባለስልጣኑ ቤት በቦምብ ተመታ/የጳጳሳት ሹመት ተራዘመ ሰበር መግለጫ

የግራ ቀኙን ሃሳብ የመረመረው ፍርድ ቤቱም በሰጠው ብይን የተከሳሾችን የክስ መቃወሚያ ውድቅ ለማድረግ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ሁሉም ተከሳሾች ድርጊቱን አለመፈፀማቸውን ጥፋተኛ እንዳልሆኑም ከመግለፃቸው ባሻገር፤ 1ኛ ተከሳሽ ሆነው የቀረቡት የቀድሞ የጋምቤላ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ኦኬሎ ኦኮያን በዜግነት ኖርዌያዊ መሆናቸውን በማስታወስ መከሰስ ካለባቸውም በአለም አቀፉ ህግ እንጂ በኢትዮጵያ ህግ ስር መሆን እንደማይገባው ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። ሌላ አንድ ተከሳሽም እኛ የፈፀምነው የግድያም ሆነ የሽብር ወንጀል የለም፤ ወንጀል ፈፅማችኋል ከተባለም በኢትዮጵያ ሳይሆን በአይ ሲ.ሲ ችሎት እንቅረብ የሚል የተቃውሞ ሃሳብ ለችሎቱ አሰምተዋል።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎትም ተከሳሾቹ አሉን የሚሏቸውን መቃወሚያዎችና አቤቱታዎች ለህጋዊ ስርዓትና ለሂደት ማሰማት የሚችሉ መሆኑን በመጥቀስ፤ ዐቃቤ ሕግ አሉኝ የሚላቸውን አራት ምስክሮች ለመስማት ለጥቅምት 19 ቀን 2007 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

Share