አዟሪና አከፋፋዮች ለምን አንድ ለአምስት አይደራጁም? (ጽዮን ግርማ)

ዮን ግርማ

ጽዮን ግርማ
tsiongir@gmail.com

ከአምስት ወራት በፊት ከኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት የስልክ ጥሪ ደረሰኝ፡፡ በሞያው ውስጥ ሰንበት ብያለኹና ከአብዛኞቹ የጣቢያው ዘጋቢዎች ጋራ እንተዋወቃለን፡፡ ጥሪው የደረሰኝም በላይ ኃድጎ ከተባለ ከማውቀው ጋዜጠኛ ነበር፡፡ ለሥራ ጉዳይ በስልክ ሳይኾን በአካል መገናኘት እንደሚፈልግ ነገረኝ፡፡ ባለመመቻቸት ሳንገናኝ ቀናት ቢቆጠሩም በመጨረሻ ተገናኘን፡፡

በአካል መገናኘትን ያስመረጠው ጥብቅ ጉዳይ ከጋዜጠኝነት ሞያ ጋራ ለሚሠራ አንድ ዘጋቢ ፊልም ቃለምልልስ እንድሰጥ ነበር፡፡ በወቅቱ እንደነገረኝም፤ዘጋቢ ፊልሙ የሚሠራበት የማጠንጠኛ ሐሳብ የበርካታ ሚዛናዊ ጋዜጦች ሕትመት መቋረጥና ሥርጭት መቀነስ ዋነኛ ምክንያት፣አከፋፋዮችና አዟሪዎች በሕትመት ውጤቶቹ ላይ በተዘዋዋሪ የሚኖራቸው የይዘት ተሳትፎና በአሣታሚው ላይ ያደርሳሉ የተባለውን ጫና በሚመለከት አስተያየት እንድሰጥ ነበር፡፡

ከስድስት ዓመታት በፊት ተቋቁሞ ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ገበያ ላይ የቆየው ‹‹እንቢልታ ጋዜጣ›› ባለቤትና ዋና አዘጋጅ ስለነበርኩ፣ጋዜጣውም ከሕትመት ውጪ የኾነው አከፋፋዮቹና አዟሪዎቹ በጋዜጣው ላይ በፈጠሩት ጫና ምክንያት መኾኑን መረጃ ስለደረሰው ለቃለ ምልልሱ እንደመረጠኝ ነገረኝ፡፡ ከዛው ጋር በተያያዘም የጋዜጠኝነትን ነባራዊ ኹኔታ አያይዤ አስተያየቴን እንዳካፍል ጠየቀኝ፡፡

ጋዜጣው ከገበያ ውጪ ለመኾኑ በርካታ ምክንያቶች እንዳሉት ገልጬለት፤‹‹እንቢልታ ጋዜጣ›› በአከፋፋዮችና በአዟሪዎች ጫና ምክንያት ከገበያ ወጣ መባሉን ግን ከእርሱ እንደሰማሁ ነገርኩት፡፡አጠቃላይ ሐሳቡን በሚመለከት ግን፤‹‹አከፋፋዮችና አዟሪዎች ጫና ይፈጥራሉ›› የሚለው ሐሳብ ጣቢያው በሚያሠራው ዶክመንተሪ በተደጋጋሚ መነሳቱን፣አሁን ካለው ነባራዊው ሁኔታ ጋር አብሮ የማይሄድ መኾኑን፣ኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እራሱ ይህን ጉዳይ ደጋግሞ መሥራቱ እንዴት እንደማይሰለቸው ተገርሜ ጠይቄው ነበር፡፡ በመጨረሻም በዚህ ጉዳይ ላይ የተሟላ አስተያየት መስጠት የሚያስችል ልምድ ቢኖረኝም ለኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ግን ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልሆንኩ በእርጋታ አስረድቼው ነበር፡፡የ‹‹እንቢልታ›› ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በነበርኩበት ቀደም ባለው ጊዜ ተመሳሳይ ነገር ተጠይቄ ፈቃደኛ እንዳልነበርኩ ነገርኩት፡፡

አስተያየት የማልሰጥበት ምክንያትም ኾን ተብለው ከሚዘጋጁ አስተያየት ሰጪዎች በስተቀር ያለው ተጠያቂ ለሚቀርብለት ጥያቄ የሚሰጠው ምላሽ በቴሌቭዥን ሲቀርብ እጅግ ተቆራርጦና አስተያየት ሰጪው መልስ ከሰጠበት ጥያቄ ጋራ በቀጥታ ግንኙነት እንዲኖረው ተደርጎ ሳይኾን እነርሱ እንዲተላለፍ ከሚፈልጉት ሐሳብ ጋራ አጣብቀው ይሰፉታል የሚል እምነት እንዳለኝ ነገርኩት፡፡ ይህንንም ለቃለ ምልልሱ ፈቃደኛ ብኾን ኖሮ ሊያነሳልኝ የፈለገውን ጥያቄ በምሳሌነት ጠቅሼ አስረዳሁት፡፡
ለምሳሌ ’የጋዜጠኝነት ሞያ በኢትዮጵያ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ምን ይመስላል?’ በሚል ለጠየቀኝ ጥያቄ ልሰጠው እችል የነበረው ምላሽ፤‹‹አሁን በኢትዮጵያ ባለው ነባራዊ ሁኔታ የጋዜጠኝነት ሞያ በራሱ ነጻ አልወጣም፡፡መንግሥት ወደ ራሱ ፍላጎት በመጎተት እስረኛ አድርጎታል፤ተቃዋሚዎችም ሞያውን እንደነርሱ ፍላጎት ይስቡታል፣ባለሃብቶችም እንደሚመቻቸው ሊያሽከረክሩት ይፈልጋሉ፡፡ አንባቢውም ማንበብ የሚፈልገው ብቻ እንዲጻፍለት ይፈልጋል፡፡ በዋነኛነት ለሞያው ነጻ አለመውጣት ተጠያቂው ግን መንግሥት ነው፡፡ ምክንያቱም የእርሱ ጡጫ ስለሚጠነክር ምንም ነገር ተቋቁሞ መቀጠልን እጅግ ከባድ ያደርገዋል›› የሚል እንደነበር ነገርኩት፡፡

እርሱ ደግሞ ይሄን ሲያስተላልፈ ያውም በጨዋ መንገድ ፤‹‹አሁን በኢትዮጵያ ባለው ነባራዊ ሁኔታ የጋዜጠኝነት ሞያ በራሱ ነጻ አልወጣም፡፡‹‹ተቃዋሚዎች ሞያውን እንደነርሱ ፍላጎት ይስቡታል፣ባለሃብቶችም እንደሚመቻቸው ሊያሽከረክሩት ይፈልጋሉ፡፡ አንባቢውም ማንበብ የሚፈልገው ብቻ እንዲጻፍለት ይፈልጋል፡፡›› የሚለውን ብቻ ወስዶ እንደሚኾን በእርግጠኝነት ነገርኩት፡፡ እርሱም ከዛ በላይ ብዙ ሊለልኝ ስላልፈለገ ለስንብት ተነሳ፡፡እናም ከወራት በኋላ እኔን በጠየቀኝ ጋዜጠኛ ስምም ባይኾን በሌላ አዘጋጆች ስም በዚህ ሓሳብ ዙሪያ የሚያጠነጥን ‹‹መንታ መንገድ›› የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም ባለፈው ሣምንት በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ቀርቦ ታየ፡፡ ስለ ፊልሙ ቅድመ ዝግጅት በማወቄ ሳይኾን በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ስለ ሕትመት ሚዲያው ስርጭት የቀረበው መረጃ እውነተኛውን ስዕል የሚያሳይ አይደለም ብዬ ስለማምን አስተያየቴን እንዲህ ጻፍኩ፡፡

ዘጋቢ ፊልሙ
ዘጋቢ ፊልሙ የግሉ ፕሬስ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዐት ግንባታ ያለው አስተዋጾ፣የግሉ ፕሬስ ሚና እና ነባራዊ ኹኔታ፣የፕሬስ ታሪክ፣የፕሬሱ ፈተናዎች፣የጸረ ሽብር ሕጉና ፕሬስ በሚሉ ዋና ርዕሶች ሥር ሌሎች ንዑስ ርእሶችን ለመዳሰስ ይሞክራል፡፡ይህንንም ሐሳብ ለማጠናከር በአጠቃላይ ዘጠኝ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ጋዜጠኞች እንዲሁም ሁለት ሰዎችን አስተያየት አካቷል፡፡ ርእሶቹ ለየብቻቸው በብዙ የሚያወያዩና አንዳንዶቹም ከጋዜጠኝነት መሠረታዊ መርሕ ጋራ የተሳሰሩ በመኾናቸው በተነሱት ሁሉም ሐሳቦች ላይ አስተያየት የመጻፍ ዕቅድ የለኝም፡፡ ነገር ግን የዘጋቢ ፊልሙ ማጠንጠኛና መንግሥት ሊወስደው ያሰበውን ቀጣይ እርምጃ አመላካች ነው ያልኩትን የአከፋፋዮችና የአዟሪዎችን ጉዳይ ለማንሳት እሞክራለሁ፡፡

የመንደርደሪያ ሐሳቡ አሮጌነት
ዘጋቢ ፊልሙ ወደ ተነሳበት ሐሳብ የሚያንደረድረውን አስተያየት ያስጀመረው፤የቀድሞ የፓርላማ አባል፣ በ2002 ምርጫ በቦንጋና አካባቢው ከዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ ጋራ በገጠሙት የምርጫ ጦርነት ተሸንፈው በኋላም በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት የተመደቡትና አሁን የሕግ ባለሞያና መምሕር መኾናቸው በተገለፀው አቶ ብርሃኑ አዴሎ ፕሬስ በአደጉት አገሮች ያለውን ሚና በማስተንተን ነው፡፡

ያለ ነጻ ፕሬስ ከሚኖር መንግሥት ይልቅ ያለ መንግሥት የሚኖር ፕሬስ እንደሚመርጥ የሚናገረው ሦስተኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቶማስ ጀፈርሰን፤ ሕግ አውጪው፣ ሕግ ተርጓሚውና ሕግ አስፈጻሚው የመንግሥት አካላት እርስ በርሳቸው የተነጣጠሉና እርስ በርሳቸው የሚቆጣጠሩ እንዲሆኑ ሲታገል ቆይቶ፤ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ለዜጎች መተኪያ የሌለው መብት ነው የሚለው እምነቱን ለማረጋገጥም ፕሬስ አራተኛው የመንግሥት አካል (The Fourth State) ኾኖ እንዲያገለግል በማድረግ ጥንካሬውን አሳይቷል፡፡ አቶ ብርሃኑም ይህንኑ የጀፈርሰን ሓሳብ አንስተው፤ ፕሬስ ባደጉት አገራት አራተኛው የመንግሥት አስፈጻሚ ክንፍ እንደኾነ በመንገር ነበር አስተያየታቸውን የጀመሩት፡፡ አቶ ብርሃኑ ግን ስንሰማው የኖርነውን የፕሬስን አራተኛ መንግሥትነት ደግመው ከመንገር ውጪ ኢትዮጵያ ውስጥ ፕሬሱ በአራተኛ መንግሥትነት እንዲያገለግል እንደ ቶማስ የታገለ መሪ መኖር አለመኖሩን ሳይነግሩን አልፈዋል፡፡

የዘጋቢ ፊልሙ ሐሳብ በኤቴቪ ተደጋግሞ ከመነሳቱና ከአስተያየት ሰጪዎቹ ውስጥ የተወሰኑት ለዓመታት በአንድ ዐይነት ጉዳይ ላይ ደጋግመው ተመሳሳይ ነገር ከመናገራቸው የተነሳ አቶ ወንደሰን መኮንን የተባሉት በመንግሥት ድጋፍ መቆሙ የሚነገርለት የኢትዮጵያ ነጻ ጋዜጠኞች ፕሬዝዳንት አስተያየት ሲሰጡ፤ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡ ሳይኾን የቴሌቭዥን ፕሮግራም የሚያቀርቡ አንባቢ ይመስሉ ነበር፡፡ ሐሳባቸውንም በአንድ ትንፋሽ በመደዳ ደርድረው ነበር ያጠናቀቁት፡፡
ባነሱት ሐሳብም፤የግሉ ፕሬስ ያላደገው ፕሬሱ ለኢትዮጵያ እንግዳና አዲስ ባሕል መኾኑን በመጥቀስ የዛሬ ሃያ ዓመት የሰጡትን አስተያየት ዛሬም ደግመው ለዕድገቱ መቀጨጭ እንደምክንያት ያስቀምጣሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ የግሉ ፕሬስ በጥፋት ጎዳና ላይ እየተጓዘ መኾኑን በእርግጠኝነት ተናገሩ፡፡ ለዚህም አስተዋጾ ያበረከቱት፤የሕትመት ሚዲያው አጀማመር ላይ በግንባር ቀደምትነት የተሰለፉት ጋዜጠኞች ከደርግ ሥርዐት የተረፉ መኾናቸውን ይነግሩናል፡፡ ለዚህ ንግግራቸው ማልበሻም ይኾን ዘንድ ኢቴቪ የዱሮ ጋዜጦችን ምስል አሳይቶናል፡፡ እውነት ግን ጣቢያውና መንግሥት (ኢሕአዴግ) ስለነዚህ ጋዜጦችና የደርግ ርዝራዥ ስለሚላቸው ሰዎች መቼ ነው ማውራት የሚያቆመው? ምስሉንስ መቼ ነው በሌላ የሚቀይረው? እርሱ የደርግ ርዝራዥ የሚላቸው ሰዎች (ከጥቂቶቹ በስተቀር አብዛኞቹ በደርግ ሥርዐት ወቅት ተማሪዎች ነበሩ) ይታተሙ የነበሩ ጋዜጦች እኮ በተለያ ምክንያት ከገበያ የወጡ፣ በራሱ በመንግሥት ድምጥማጣቸው እንዲጠፋ ተደርገው ከዓመታት በፊት የተዘጉ፣ ባለቤቶቻቸውና ጋዜጠኞቻቸው በእስር የተሰቃዩ፣ የተሰደዱ፣ ሞያ የቀየሩ ፣ በሕይወት የሌሉ እንዲሁም በሌላ ምዕራፍ ታስረው እስር ቤት የሚገኙ ናቸው፡፡

እንዚህን ጋዜጦች ገዢው ፓርቲና ባለሥልጣናቱ የሚያስታውሳቸውን ያህል ስንትና ስንት መስዋትዕነት የከፈሉላቸው ባለቤቶቹ እንኳን የሚያስታውሷቸው አይመስለኝም፡፡ የፕሬስ ታሪክ ሰፊና ከዓመት ዓመት የተለያየ አካሄድ የነበረው ነው፡፡ ከ1994 ዓ.ም እስከ 1997 ዓ.ም የነበረውን የፕሬስ አካሄድ ብቻ ብንመለከተው በእነዚህ ጊዜያት ትንሽ ለውጥ የታየበት፣ የነፃ ፕሬስ ተቋማትና የሕትመት ውጤቶች በቁጥር ብቻ ሳይሆን በይዘትም ለውጥ ያሳዩበት አዳዲስ ባለሞያዎች ኢንዱስትሪውን የተቀላቀሉበት፣ የጋዜጠኝነት ሞያን ለማዳበር የሚጣጣሩ ጋዜጠኞች የተፈጠሩበት፣ በዕውቀትም በክህሎትም ብቃት ያላቸው ሞያተኞች ሞያውን የተቀላቀሉበት ጊዜ ነበር፡፡ ከ97 በኃላ ደግሞ ሌላ አዲስ ባሕል ይዞ መጥቶ ተመልሶ ጠፍቷል፡፡ አሁን ደግሞ በስደትና በእስር፤ በተፅእኖ፣ በወከባና በሽብርተኝነት ዐዋጅ የተጨነቀ ፕሬስ ተፈጥሯል፡፡

ከዚህ ዘጋቢ ፊልም ያስገረመኝ ሌላው ነገር፤የፖለቲካ ፓርቲ አባላት የነበሩና የኾኑ ግለሰቦች በሕትመት ሚዲያ ላይ የሚጻፉትን ጹሑፎች ከእነ ገጻቸው በምስል እያሳየ የአቶ ብርሃኑ አዴሎን አስተያየት ያቀረበበት ክፍል ነው፡፡ እርሳቸው እንዳሉት ሚዲያው ሥነ ምግባሩን የተከተለ ሥራ ብቻ መሥራት እንጂ በፕሬስ ስም ወንጀል የኾ ድርጊት ላይ ተባባሪ በመኾን ኅብረተሰቡን ለማደናገር መሞከር አግባብ እንዳልሆነ ይገራሉ፡፡ ወንጀል ያሉት ደግሞ በፓርቲ ፖለቲካ ውስጥ ያሉ ሰዎችን እንደ አምደኛ አድርጎ በማቅረብ የእነርሱን የፖለቲካ ፍላጎትና አስተሳሰብ እንዲያንጸባርቁና በመንግሥት በኩል የመጣውን ለውጥ እንደሌለ አድርገው እንዲናገሩ በመፍቀዱ ነው፡፡

የፖለቲካ ፍላጎትና አስተሳሰብን ማንጸባረቅ፣ ‹‹ለውጥ አልመጣም›› ብሎ መከራከርን ማነው ወንጀልና ሽብርተኝነት ያደረገው? ከአንድ ሚዲያ ግዴታዎች አንዱ የተለያየ እምነትና አስተሳሰብ ያላቸውን ሰዎች ሐሳባቸውን የሚገልጹበትን መንገድ በእኩል ማመቻቸት፣ የተለያየ ሐሳብ ያላቸው ሰዎች እንዲከራከሩበት በር መክፈት ነው፡፡ ይህ ለአቶ ብርሃኑ እንዴት ወንጀል ኾኖ እንደታያቸው አልገባኝም፡፡ በዚህ አስተሳሰባቸው ሃያ አራት ሰዓት ሙሉ የኢሕአዴግን ፖለቲካዊ አስተሳሰብ እንዲህ ካሉ ዶክመንተሪዎች ጋራ እያዋዛ ተመልካቹ ላይ የሚጭነውን የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ምነው በሽብር ሳይፈርጁ ዘለሉት? ይኸው የእራሳቸውን ሐሳብ እራሱ እየጫነብን አይደል እንዴ?

የሕትመት ሚዲያው ሥርጭት
ሌላው ከዚህ ዶክመንተሪ ውስጥ ያስገረመኝ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ም/ዋና ዳሬክተር አቶ ልኡል ገብሩ የሕትመት ሚዲያ ሥርጭትን በሚመለከት ጥናት ማድረጋቸውን በመግለጽ የሰጡት አስተያየት ነው፡፡ እንዲህ ይላል፤‹‹እነዚህ የሕትመት ሚዲያዎች ከፍተኛ ቅጂ አላቸው ከተባለ አርባና አርባ አምስት ሺሕ ነው፡፡ ከአርባ አምስት ሺሕ ቅጂ ውስጥ በጣም ብዙ ሸጡ ከተባለ ሁለት ሺሕ ኮፒ ብቻ ነው የሚሸጡት፡፡ ሌላውን አርባ ሦስት ሺሕ ቅጂ መጋዘን ውስጥ ያስቀምጡታል፡፡ አንድ የሕትመት ውጤት አትራፊ የሚኾነው አንድም ማስታወቂያ ማግኘት አለበት ወይም ደግሞ የሥርጭት መጠናቸው ከአንድ መቶ ሺሕ መብለጥ አለበት›› አሉ፡፡ የአስተያየታቸው ማጠቃለያም እነዚህ የሕትመት ውጤቶች እንዲህ የሚያደርጉት ሌላ በእነርሱ በኩል የራሱን አጀንዳ ለማስፈጸም ፍላጎት ካለው አካል የገንዘብ ድጋፍ እያገኙ ነው የሚል ነው፡፡

እነዚህ የሕትመት ውጤቶች አርባ አምስት ሺሕ አሳትመው አርባ ሦስት ሺሕ መጋዘን ውስጥ እያስቀመጡ ከኾነ አቶ ልኡል በእውነትም ልክ ናቸው፡፡ እነዚህን የሕትመት ሚዲያዎች የሚያግዝ ረጅምና ፈርጣማ የኢኮኖሚ ክንድ ያለው ሌላ አካል ለመኖሩ እርግጠኛ ኾኖ መናገር ይቻላል፡፡ እውነቱ ግን ይህ አይደለም፡፡ መቼም አቶ ልኡል ይህን ጥናት ራሳቸው ሠርተውታል ተብሎ አይታመንም፡፡ በመጀመሪያ የተጠቀሰው ቁጥር በሣምንት ነው በወር? ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በግንቦት ወር 2006 ዓ.ም ያወጣው መረጃ በስርጭት ላይ የዋሉ ጋዜጦችን ከእነ ሕትመት ብዛታቸው ይዘረዝራል፡፡በዚህ መረጃ መሠረት በሣምንት ውስጥ ከፍተኛውን የሥርጭት መጠን የያዘው መጽሔት አንድ ብቻ ነው፤ እርሱም ዐሥራ ስምንት ሺሕ ቅጂ ነው፡፡ ይህ በአራት ሳምንት ተባዝቶ በወር ቢሰላ ሰባ ሁለት ሺሕ ይመጣል፡፡ የሣምንት ሕትመታቸው በወር ተሰልቶ ሃምሳ ሺሕ ቅጂ የሚያሳትሙት ከሦስት አይበልጡም፡፡ እንግዲህ እኔ ያገኘኹት መረጃ የእርሳቸው መሥሪያ ቤት ካወጣው ሰነድ ላይ ነው፡፡ እርሳቸው ግን ከየት ነው ያገኙት?

የእርሳቸውን መረጃ እንደወረደ እንቀበለውና፤ ሁለት ሺሕ ብቻ ተሸጦ ሌላው አርባ ሦስት ሺሕ ጋዜጣ መጋዘን ያስቀምጣሉ ብለዋል፡፡ ለመሆኑ አቶ ልኡል አርባ ሦስት ሺሕ መጽሔትና ጋዜጣ ከማተሚያ ቤት ሲወጣ ብዛቱን ዐይተውት ያውቃሉ? በስንት ብር እንደሚታተምስ ያውቃሉ? አንድ የሕትመት ውጤት በጣም አትራፊ ቢኾን እንኳን ይህን ያህል ቁጥር ያለው የሕትመት ውጤት ለአንድ ጊዜ ሳይሸጥ ቢመልሰው መልሶ በእግሩ መቆም እንዴት እንደሚከብደው አያውቁም?፡፡ አሁንም እርሶ ያሉትን እንቀበልና የሕትመቱን ኪሳራ ለመሸፈን ደግሞ ከፍተኛ የኾነ የገንዘብ ዝውውር መኖር አለበት፡፡ ጋዜጠኞች የሚጠጡበትን የሻይ ሲኒ በቀለም ለይቶ ለሚያውቀው የእርስዎ መንግሥት እንዲህ ያለ የገንዘብ ዝውውር እያለ እንዴት እስካሁን ሳይደርስበት ቀርቶ ይኾን?

ለመኾኑ አቶ ልኡል በአዲስ አበባና በመላው ኢትዮጵያ ስንት አከፋፋይና ስንት አዟሪ እንዳለ ያውቃሉ? አንድ አዟሪ በከፍተኛ መጠን የሚሸጠውን ተፈላጊ የሕትመት ውጤት በቀን ስንት እንደሚሸጥ ያውቃሉ? እኔ በግሌ ባያውቁ ነው እንጂ ቢያውቁ እንዲህ አይሳሳቱም ብዬ ገመትኩሎት፡፡

መቼም ሪፖርትር ጋዜጣን ያውቁታል?ሪፖርትር ጋዜጣ ላይ ለሦስት ዓመታት በከፍተኛ ሪፖርተርነት ሠርቻለሁ እናም ጋዜጣው ዐሥረኛ ዓመቱን በኢግዚብሽን ማዕከል ሲያከብር ከመርሐ ግብሩ አንዱ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያሉትን አከፋፋዮችና አዟሪዎችን የፕሮግራሙ ተሳታፊ እንዲኾኑ መጋበዝ ነበር፡፡ እነዚህን አዟሪና አከፋፋዮች ለማግኘት ምን ስልት ተነደፈ መሰሎት? ጋዜጣውን ለማከፋፈል የሚወስዱ ንኡስ አከፋፋዮች ጋራ እየተሄደ አዟሪዎቹ ለመረከብ ሲመጡ ስማቸው እየተመዘገበ ካርድ ተሰጣቸው፡፡ በወቅቱ ከሦስት የማይበልጡ ዋና አከፋፋዮች፣ አርባ የሚኾኑ ንኡስ አከፋፋዮችና አራት መቶ የሚኾኑ አዟሪዎች ተገኙ፡፡

ከስድስት በላይ የሕትመት ውጤቶች ላይ ስለሠራኹ ሌላ በርካታ ምሳሌ ልጨምርሎት እችላለሁ፡፡ ለዛሬ ግን በዚህኛው ምሳሌ ላይ ተንተርሼ ላስረዳዎት፡፡ እነዚህ አከፋፋይና አዟሪዎች ሌላው ቀን ብዙም ገበያ ስለሌለው ከቅዳሜና እሁድ በስተቀር ሁሉም በአንድ ጊዜ አይወጡም፡፡ ቅዳሜና በትንሹ ሁለት መቶ ሃምሳ የሚኾኑት አዟሪዎች ወጥተዋል ተብሎ ይገመታል፡፡ እንደ ቦሌ፣ መገናኛ፣ አራት ኪሎ፣ ፒያሳ….. እያሉ ዋና ዋና ቦታዎች ያሉትን አዟሪዎች ያስታውሷቸው መኪናዎትን ያቁሙና ስርጭቱ ከፍተኛ ነው ያሉትን አንዱን የሕትመት ውጤት ስም ጠርተው ‹‹በቀን ስንት ተረክበህ ስንት ትሸጣለህ?›› ይበሉና ይጠይቁት፡፡ ከዛም እኔ ከምነግሮት ቁጥር ጋራ ያነጻጽሩታል፡፡ ለማንኛውም አንድ ጋዜጣ አዟሪ በአሁኑ ሰዓት ሽያጩ ከፍተኛ ነው የተባለለትን መጽሔት በቀን በትንሹ ስልሳ ይሸጣል፡፡ ሽያጩ ከፍተኛ ሲኾን ደግሞ አንድ አዟሪ እስከ አንድ መቶ ሃምሳ ሊሸጥ ይችላል፡፡ ይህን ቁጥር በሁለት መቶ ሃምሳ ብናበዛው ዐስራ አምስት ሺሕን እናገኛለን፡፡ ከዚያም በአዲስ አበባ አቅራቢያ ያሉትን ጨምሮ ወደየክልል ከተሞች ሲበተን ደግሞ የታተመውን ቁጥር ልክ ይገኛል ማለት ነው፡፡

‹‹አንድ የሕትመት ውጤት አትራፊ የሚኾነው አንድም ማስታወቂያ ማግኘት አለበት ወይም ደግሞ የሥርጭት መጠናቸው ከአንድ መቶ ሺሕ መብለጥ አለበት›› ሲሉ ሰማሁ ልበል፡፡ ሐሳቡን ልክ ኖት ቁጥሩን ግን ተሳስተዋል አቶ ልኡል፡፡ አንድ ጋዜጣም ኾነ መጽሔት ከዐሥር ሺሕ በላይ ያለ ማስታወቂያም ቢታተም ትርፍ ያመጣል፡፡ ከዛ በታች ከኾነ ደግሞ የሥራ ማስኬጃ ወጪውን አመጣጥኖ ራሱን ይችላል፡፡ ይሄም ራሱን የቻለ ስሌት አለው፡፡ እንደ ሥራ ማስኬጃው ወጪ፣ እንደ ገጽ መጡ፣ እንደ ቀለሙና እንደ ማተሚያ ቤቱ ዋጋ ወጪና ገቢው ይለያያል፡፡ እርሶ ስላላወቁ ነው እንጂ አብዛኛው ጋዜጠኛ ለስሜቱ፣ ለፍላጎቱና ለእምነቱ የሚሠራ ነው፡፡ ኑሮውን ቀረብ ብለው ቢያዩት መሳሳቶ የበለጠ ይገባዎት ነበር፡፡ ደግሞ እኮ በእርሶ አባባል ይህ የሚደረገው ሁሌም ነው፡፡ ታዲያ የት ነው የሚቀመጠው? ምን ዐይነት መጋዘን ይኾን የሚችለው? እስቲ ኤቴቪ በነካካ እጁ አንድ አርባ ሦስት ሺሕ ሕትመት የያዘ መጋዘን ያሳየን፡፡

አዟሪና አከፋፋዮች ለምን አንድ ለአምስት አይደራጁም?
የዘጋቢ ፊልሙ የመጨረሻው ማጠንጠኛ ችግሮቹን አዟሪና አከፋፋዮች ላይ የሚደመድም ነው፡፡ የሕትመት ሥርጭቱን የማከፋፈል ሥርዐት በሚመለከት ወጥ የኾነ አሠራር ስለሌለ አከፋፋዮቹ እንደፈለጋቸው የሚያሽከረክሩት ነው የሚል መልዕክትም ተላልፏል፡፡ እነዚህ አከፋፋዮች አፍራሽ ተልኮ ካላቸው ከተወሰኑት ሕትመቶች ጋራ ትስስር ስላላቸው የተወሰነው አሣታሚ እንዳይሸጥለትና ገበያ ውስጥ እንዳይቆይ የማድረግ ኃይል አላቸውም ተብሏል፡፡

‹‹በፕሬስ ውጤቶቹ ላይ ትልቅ ተጽዕኖና አፈና እየፈጠሩ ያሉት አከፋፋዮቹ ናቸው፡፡›› በማለት በዘጋቢ ፊልሙ ላይ አስተያየት የሰጡት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር ዴታ አቶ እውነቱ ብላታ፤ እነዚህ አከፋፋዮች የፕሬሱን ይዘት ሳይቀር እየወሰኑ ሚዛናዊ የኾነው ከገበያ እንዲወጣ እንደሚያደርጉ፣ ይሄም መንግሥት ባለበት አገር በጠራራ ጸሐይ እየተፈጸመ ያለ ፀረ ፕሬስ ዕድገት መኾኑን በመግለጽ በመንግሥት በኩል ይህን ችግር መፍታት እንደሚኖርባቸው ሲናገሩ አድምጠናቸዋል፡፡

አቶ እውነቱን እኔ ብኾን የጠየኳቸው ኖሮ፤ ‹‹ለመኾኑ የትኞቹ ጋዜጠኞች በዚህ ምክንያት ከገበያ ወጡ? የትኞቹ አከፋፋዮችና አዟሪዎች ናቸው ይህ ኃይል ያላቸው?›› ብዬ እጠይቃቸው ነበር፡፡ እርግጥ ነው ከ1994 ዓ.ም እስከ 1997 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ እነ አቶ ሽመልስ ከማል በፊት ለፊትና በእጅ አዙር ኒሻን፣ ኢፍቲን፣ ኔሽንና የመሳሰሉትን ጋዜጦች በሚያሳትሙበት ጊዜ እንዲህ ያለ ምክንያት ይሰጡ ነበር፡፡ በግላቸውም ከጓደኞቻቸው ጋር ኾነው ‹‹እንዲህ ያለውን ሰንሰለት እንሰብራለን›› በማለት ይዝቱም ነበር፡፡ በ97 ምርጫም ይህ ነገር ተደጋግሞ ይነገር ነበር፡፡ ያን ግዜ የሕትመት ሚዲያው ብዛት ስለነበረው ስርጭቱም ከፍተኛ ስለነበር ወሬው እውነት ይሁን አሉባልታ ሳይታወቅ አልፏል፡፡አሁን ግን ባለሥልጣናቱ እንዳከበዱት ሳይኾን ካሉም ‹‹እነ እከሌ›› ናቸው ብሎ መጠቆም ይቻላል፡፡እስቲ እነ እከሌ በሉ፡፡

እነዚህ አከፋፋይና አዟሪዎች እኮ ከአንድ ጋዜጣ ላይ የሚያገኙት ከሽርፍራፊ ሳንቲም አይበልጥም፡፡ የእነርሱ ገቢ የሚጨምረው ሕትመቱ በተሸጠ ቁጥር ነው፡፡ እንኳን ሊያፍኑ ቀርቶ ገቢ ስለማይሞላላቸው አከራይተው ገንዘብ ሲያገኙ ያላየ አንባቢ ይኖር ይኾን? አብዛኞቹ አከፋፋይና አዟሪዎች የሕትመት ውጤት በማይወጣበትና የሥርጭት መጠኑ አነስ ያለ ሲኾንባቸው እንደ ጫማ መጥረግ፣ ሎቶሪ መሸጥና የመሳሰለውን የቀን ሥራ ሠርተው ወደ ቤታቸው የሚገቡ ናቸው፡፡

በመጨረሻ
ኤቴቪና ባለሥልጣናቱ በዚህ ዘጋቢ ፊልም ማጠቃለያ ላይ ለፕሬሱ ዕድገት ተቆርቋሪ ለመምሰል ሞክረዋል፤ ፕሬሱ ያለበትን የማተሚያ ቤት ችግር፣ የባለሞያ ችግር፣ የቢሮና የመሠረታዊ መገልገያ ዕቃዎች ችግር፣ የማስታወቂያ ችግር እንዲሁም የአዟሪና አከፋፋይ ችግር ለመፍታት የተነሳ አስመስሎ አቅርቧል፡፡ በፕሬሱ ላይ እነዚህ ሌሎች ችግሮች እንዳሉበት ማንም አይክድም፡፡ ዋናው ችግር ግን ይሄ አይደለም፡፡ መንግሥት ዋናውና መሠረታዊ የኾነውን የፕሬስ ነጻነት አንቆ ይዞ በጭፍጫፎው ላይ አዛኝ ለመምሰል የሚያደርገው ሙከራ ‹‹ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ…›› ያስመስልበታል፡፡ እንደ ባለሥልጣናቱ ገለጻ መንግሥት እነዚህን አዟሪዎችና አከፋፋዮችን በጎንዮሽ በቁጥጥር ሥር የማድረግ ፍላጎት እንዳለው አሳይቶበታል፡፡ እኔ ደግሞ ሐሳብ አለኝ፤ መንግሥት በነጻ ፕሬስ ጉዳይ እንዲህ እንቅልፍ አጥቶ ከሚያድር አከፋፋዮቹና አዟሪዎቹ ለምን በአንድ ለአምስት አደራጅቶ እርፍ አይልም?

 tsiongir@gmail.com

(ቅዳሜ ሐምሌ 12 ቀን 2006 ዓ.ም በወጣው ፋክት መጽሔት ላይ የታተመ)

1 Comment

  1. ጽዮን እጅግ ደስ የሚልና ሚዛኑን የጠበቀ አስተያየት ነው ያስቀመጥሽው:: ይህን ኢትዮጵያን ሊያዩት የሚችሉበት ግዚ በጣም ሩቅ ይመስለኛል:: ለሁሉም አምላክ ይህን አይንት ሰላም: ነጻነት: ያለበት ኢትዮጵያ ለማየት ያብቃን::

Comments are closed.

020
Previous Story

Look for the Union Label when you are buying a coat, dress, or blouse. Remember

Next Story

ግንቦት 7 ለብሔራዊ አንድነትና ነፃነት ህወሓትን ከትግራይ ሕዝብ መነጠል ያስፈልጋል አለ

Latest from Blog

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ የውጪ ግንኙነት የቤተክርስቲያኒቱን የሺሕ ዘመናት ታሪክ እና እሤቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርባታል!!

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) (ለሪፖርተር ጋዜጣ እንደጻፈው) እንደመንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው ጽሑፌ መነሻ የሆነኝ- ባሳለፍነው ሳምንት በአፍሪካ ኅብረት ኔልሰን ማንዴላ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለአንድ ቀን የተካሄደው፤ ‹‹የአፍሪካ  መንፈሳዊ ቀን/The African Spiritual

የአበባው ታደሰ እና የአረጋ ከበደ ፍርጠጣ | ስለአማራ ክልል ከነዋሪዎች የተሰማው | አበባው ጉ’ድ ሆነ – “አበባውን ሳትይዙ እንዳትመጡ”|“በባህርዳር ተከበናል፣ ከፍተኛ አዛዦች ተመተዋል” | “ፋኖ መንግ’ስት ሆኗል” ጄ/ሉ |

የአበባው ታደሰ እና የአረጋ ከበደ ፍርጠጣ አበባው ጉ’ድ ሆነ – “አበባውን ሳትይዙ እንዳትመጡ”|“በባህርዳር ተከበናል፣ ከፍተኛ አዛዦች ተመተዋል”| “እጅ ከመስጠት ውጭ አማራጭ አይኖረንም” ፊ/ማ “ፋኖ መንግ’ስት ሆኗል” ጄ/ሉ |

ከውጭ በተላከ ገንዘብ ሀብት አፍርቶ የተላከበትን ደረሰኝ ያላቀረበ ንብረቱ እንዲወረስ የሚደነግግ አዋጅ ቀረበ

ዮሐንስ አንበርብር በጥፋተኝነት ላይ ያልተመሠረተ ንብረት የመውረስ ድንጋጌም በአዋጁ ተካቷል አዋጁ የሚፀድቅ ከሆነ 10 ዓመት ወደኃላ ተመልሶ ተፈጻሚ ይሆናል ከውጭ በተላከ ገንዘብ ሀብት አፍርቶ የተላከበትን ደረሰኝ ያላቀረበ ሰው ወይም ሊታወቅ ከሚችል ገቢው በላይ ሀብት አፍርቶ ምንጩ ሕጋዊ መሆኑን ማረጋገጥ ያልቻለ ሰው፣ ንብረት በመንግሥት እንዲወረስ የሚፈቅድ ድንጋጌ የያዘ
Go toTop