ዳዊት ዳባ
Saturday, July 5, 2014
በቅርብ ከአገር ቤት የተመለሰች እህት ምልከታ ታክሎበት።
“When people were hungry, Jesus didn’t say, “Now is that political, or social?” He said, “I feed you.” Because the good news to a hungry person is bread.”
– Desmond Tutu
ሰሞንኛ ስለሆነ ብቻ ወያኔዎች እንኳን ደስ ያላችሁ። ቆራጡን የኢትዮጵያ ልጅ አንድአርጋቸው እጃችሁ ገባ። ሰቆቃ መፈፀም እንደምትችሉ ስታሳዩን የመጀመርያ ጊዜ ባይሆንም እንዲታይላችሁ የለቀቃችሁትን ፊልም አይቼላችሗለው። አንድአርጋቸውን ከመያዙ በፊት ስላየሁት በደንብ እንዳሰቃያችሁት ይታያል። ሞያ ያደረጋችሁት በዜጎች ላይ ሰቆቃ መፈፀም ተሳክቷል ልትሉ ትችላላችሁ። በግሌ እጨብጭቤያለው ብራቮ በሽተኛ ዘረኛ ውላጆች። የንዴት ነው ብላቸሁ ውሰዱት። ደግሞም የንዴት ነው።
እናንተም በማትክዱት አንድአርጋቸው ምን አይነት ሰዎች እጅ ላይ እንደወደቀ ያውቃል። ስትይዙት ግን በፍራቻ አልሞተም። ሞተ እንዴ? ዋናውና ዋናው ጉዳይ ይሄ ነው። ሌላው ሁሉ ግራ ከመጋባት የሚመጣና የተለመደ አካይስትነት ነው። ምን ለማለት እንደፈለኩ ይገባችሗል።
ልታውቁትና ግልጽ ሊሆንላችሁ የሚገባው ዜጎችን በማሰር፤ በመግደልና በማሰቃየት የሚለወጥ፤ የሚለውጠውም ነገር የለም። ለምን ብትሉ አዎ አካይስቶች ነግሳችሁብናል። እናንተ እንደ አንድ ቡድን ተወስዳችሁ አላችሁ። በሌላው ጎራ ተጨቋኞች፤ መከራ የሚወርድብን፤ የተራብንና እኩይ ድርጊታችሁን በዝርዝር የምናውቅ በሚሊዬኖች ደግሞ አለን። ተፈጥሯዊም ስለሆነም ይሆናል መፈራገጣችንና እንቢኝ ማለታችንን ደግሞ የምናቆመው አልሆነም። እውነት ለመናገር እናንተ እስካላችሁ የሚቆምም አይደለም። በዚህ እንኳ ተስማሙኝና የተደጋገመና አርባዎቹን አመታት ያስቆጠረ ጭካንያዊ ድርጊታችሁ የሚያስቆመን ቢሆን ድሮ ሰጥ ለጥ ባሰኝን ነበር። አልሆነም። እንደውም እንቢታው እያደገ፤ እየሰፋና ጉልበት እያገኘ ነው። ሀብታሙ ባደባባይ አውጇል “ እመኑኝ ይወድቃል”። እውነቱን ነው ትወድቃላችሁ። በረግጥም ይህ የታሪካችን ምእራፍ ፍፃሜ ይኖረዋል። ጥያቄ የሚሆነው ፍፃሜ የሚያገኘው እንዴት ነው የሚለው ነው?። እስካሁን እንደታየው እንትናን ዘቅዝቃችሁ ጭስ ስላጠናችሁት፤ እነንትናን አሸባሪ ብላችሁ ሰብስባችሁ ስላሰራችሁ ወይ ብልት ስለምታልቡ አልሆነም። በዚህ ፍፃሜው ሊመጣ ካልቻለ ደግሞ ፍፃሜው በቀረው በሁለተኛው አማራጭ በርግጠኛነት ይመጣል ማለት ይሆናል። ተጨቋኞች እኛ ስናሸንፍ። ሁሌም ሲሆን የነበረውም ይህ ነው። ያ እሲኪሆን እንቢተኛነቱ ይቀጥላል። እኛ የአገሪቷ ዜጎች ሁሉ ስንሆን። እናነተ ጥቂቶች መሆናችሁ ደግሞ ይሰመርበት።
እረሀብ በአገራችን ውስጥ አለ። በዚህ በአሁኑ ሰአት ምግብ ባይናቸው የሚዞር ሰለምግብ የሚብሰለሰሉና እየራባቸው ያሉ ወገኖቻችን ብዙ ሚሊዬን ናቸው። በገበያው ማሻቀብ ምክንያት ኑሮውን ማሸነፍ ያቃተው ደግሞ አገሬው ሆኗል። አዎ አገሬው ነው። አዲስአበባ ካሉ ሆስፒታሎች በአንዳቸው ውስጥ የሚሰራ ዶክተር ምርር ባለ ስሜት ያለኝ። “የሁለት ልጆች አባት ነኝ። መቼም የተንደላቀቀ ኑሮ እኖር ነበር አልልሽም። ሞያተኛ እንደመሆኔ ዘና ያላ ኑሮ ለምን አልኖርኩም ከሚልም እንዳይመስልሽ። ዛሬ የኑሮውን ውድነት በሚከፈለኝ ደሞዝ መቋቋም አልቻልኩም። እንደውም በግልጽ ለምን አልነግርሽም።፡ በቤቴ ውስጥ ምግብ አዎ የምንበላው ችግር የሚሆንበት ጊዜ አለ”
ሌላዋ ሀኪም፤- መድሃኒት የዘዝንላቸው ታካሚዎች ተመለሰው መጥተው “ያዘዛችሁልኝን መዳሀኒት ሊገዛ የሚችል ገንዘብ የለኝም ይቀየርልን” ሲሉ ቁርጥ ባለ ይሉሻል። ይህ በቀን ውስጥ ብዙ ጊዜ የሚያጋጥምሽ እና የተለመደ ሆኗል። አንዳንዴ የላቸውን የገንዘብ መጠን አምስት ብር አስራ አምስት ብር ብቻ ነው ይሉናል። ያላቸው ገንዘብ ሊገዛ በሚችልው መድሀኒት አይነት እንድንቀይርላቸው ይጠይቃሉ። በታካሚዎች ጥያቄ መሰረት ለበሽታቸው እንደማይፈይድ እያወቅን ርካሽ በሆነና ብዙውን ጊዜ በማስታገሻ መድሀኒት እንቀይርላቸዋለን። በአሁኑ ጊዜ የበዙት ታማሚዎች ይታከማሉ እንጂ የትኛውንም ርካሽ የሚባለውንም እንኳ መድሀኒት ስናዝላቸው ስሌላቸው አይገዙትም። የባሰባቸው እግር ላይ ወድቀው ይለምናሉ። ወድቀው ስል ላባባል አይደለም። እግር ላይ ወድቀው ዛሬ እዚህ እረዱኝ ነብስ አይደል ሙጭጭ ይላሉ። በይበልጥ ጀማሪና የቤተሰብ ጣጣ የሌለባቸው ዶክተሮችና የሀኪም ቤቱ ሰራተኞች የበዛውን ደሞዛቸውን ለበሽተኛ መዳኒት በመግዛት ተጨማሪ የኑራቸው አካል አድርገንዋል። መስጠት ያለብን ግን ገንዘብ ብቻ እንዳይመስልሽ። በጠቃላይ በአገሪቷ ውስጥ በገዘፈ የመተኪያ ደም አለመኖር ታማሚያችንን ለማትረፍ ስነል ደማችንንም በተደጋጋሚ መስጠት ግድ ይለናል። እመኚኝ ደም በማጣት ብቻ ብዙ ዜጎች ናቸው የሚሞቱት።
ከናቴ ጋር ቤተ ክርሲቲያን ደርሰን ስንመለስ ስኳር መግዛት አለብኝ አለች። እቦታው ስንደርስ ወረፋው ለጉድ ነው። ዝናብ መዝነብም እየጀመረ ስለነበር ይቅርብን የሚያስጨምረውን ጨምረን ከውጪ እንገዛ አልኳት። የደላሽ ገንዘቡ ብቻ መቼ ሆነ ቸግሩ የት አግኝተሽ ነው የምትገዥው አለችኝ። ስኳር ሱቆች ውስጥ የለም? ብዬ ጠየኩ። ባጭሩ የለም ነበር መልሷ። ሁሉም ዜጋ የሸማቾች ማህበር አባል ነው። አውቃለው ከሶስትና ሁለት አመት በፊት አገር ቤት የነበራችሁ እንኳ ለማመን ይቸግሯችሗል። የዛሬይቷ አገራችን ግን ይህን ነው የምትመስለው። ባለራሽን። ዳቦው፤ ስኳሩ፤ ዜይቱ ትራንስፖርቱ ሁሉ ነገር በራሽንና በሰልፍ ነው። ህዝቡ እነዚህን ሰለፎች ብሶት መግለጫ ይላቸዋል። ሄጄ ብሶቴን ልግለጽ ብሎ ነው ዳቦ ሊገዛ የሚሄደው። ወደ ስራ ሲሄድ ብሶቴን ገልጬ ካዛ ወደ ስራ እሄዳለው ብሎ ይሰናበታል። ትራንስፖርት አጥቼ አይልም። ብሶት ስገልጽ ነው የሚለው።ሌላው በጣም በጣም የተለወጠው ነገር ህዘቡ ችግሩን ይናገራል። አገዛዙን በግላጭ ይቃወማል። ነገ ከነገ ወዲያ እነዚህ ሰልፎች ላይ መፈክር ይዞ መጠበቁ ስለማይቀር እንዳይገርመን።
የአዲስ አባባ ወና መንገዶች በሙሉ ለባቡር ግንባታ ተብሎ ተዘግተዋል። ይሄንኛውን መንገድ ብቻ አፍርሰን እዚህ የሚሰራውን ስራ ከጨረስንና መንገዱን ላገልግሎት ከተከፈተ በሗላ ያንኛውን መንገድ ደግሞ እንዘጋለን። እስከዛውም ጊዜያዊ አማራጭ መንገድ ሊሆን እንዲችል ብሎ የሚጨነቅ ለህዘብ ከበሬታ ያለውና ጠያቂ ያለበት መንግስት ነው። ስላልታደልን ያሉን ስለ ስልጣናቸው ብቻ የሚጨነቁና አልመቸን በሎ የምንቃወማቸውን ዜጎች ያፍንልን ይሆናል ብለው ሶቆቃ ስለሚፈፅሙበት መንገድ የሚብሰለሰሉ ናቸው።
ለማንኛውም በአንደኛው ቀን የታክሲው ሹፌሩ ወናዎቹ መንገዶች በሙሉ ስለተቆፈሩ ዙሪያ ጥምጥም በሆነ መንገድ መንደር ለመንደር ያዞረናል። የኮረኮንች መንገዱ ጎርበጥባጣነት ከመጨቅየቱ ጋር ምቾት ያለሰጣት ዘነጥ ያለች ተሳፋሪ “ይህ የሰፈሩ ሰዎች ስንፍና ነው። ምን አለ አዋጥተው ኩብል እስቶን ቢያስነጥፉ” ስትል በቀናነት ሀሳቧን ትሰጣለች”። በሞላው ሚኒ ባስ ውስጥ ያሉት ተሰፋሪዎች በሙሉ ድርሻ ባደረጉበት አቢዬት አካሄዱባት ብል አላጋነንኩም። ከስንፍና ጋር ምን አገናኘው? በሚል ጥያቄ ጀመሯት። እየራበው ያለ ህዝብ ኬት አምጥቶ መንገድ ይስራ ብለሽ ነው?፤ ለጆቻችንን እንመግብ መንገድ እንስራ?። የደላሽ አሁን አዎ አሁን እኔ እየራበኝ ነው። ላባይ አዋጡ እያሉ ያስርቡናል አንቺ ደግሞ መንገድ ካልሰራችሁ በይ ምን አለብሽ፤ የማይገባኝ መንገድም እኛ የምንሰራ ከሆነ ለምንድን ነው ታክስ እያሉ የሚዘርፉን። ያልሰማሁት ውግዘትና የምሬት አይነት የለም። ልጅቷ መነሻ ሆነች እንጂ ምሬቱ አገዛዙ ላይ ነው ያነጣጠረው። ተሳፋሪዎቹን ገመገምኳቸው ከወጣት እስከ አዛውንት አሉበት። ሴቶች እንበዛለን። እርቦኛል ያለው ወንድሜ ሲወርድ ያለ ፌርማታዬ ተከትዬው ወረድኩ። አለቀሰ።
ካፌ ውስጥ ጨዋታ የጀመርኩት ቻይናዊ በጫወታ ጫወታ አገር ምድሩን ስላጥለቀለቁትና ገላቸውን ሸጠው ስለሚኖሩ ወገኖቼ መብዛት ያወራኝ ጀመረ። የሰው አገር ዜጋም ስለሆነ ሴትም ስለሆነኩ በመከላከል አይነት ኩሩ ህዝቦች ነን። ችግሩ የኑሮው መክፋትና በተበላሸ መንግስታዊ አስተዳደር ምክንያት እንደገዘፈ በተቆርቋሪነትና በተከላካይነት አወራው። አስጨርሶኝ ያለኝ ያስደነገጠኝ ነበር። አውቃለው። ችግሩ አንቺ ችግር ከምትይው ግን የከፋ ነው።እንዳላበሰጫሽ እንጂ የበዙት ከመራብ ስለሆነ ጥያቄያቸው ብዙውን ጊዜ ከምግብ የሚያልፍ አይደለም። መንግስታችሁ የውጪ ምንዛሪ ማስገኛ አድርጎ እንደሚያየው ደግሞ አውቃለው። ይህቺ ከተማ በውጪ አገር ዜጎች ለስብሰባ ተመራጭነቷ ለምን ያደገ ይመስልሻል?። እያላገጠ ስለተሟላ አገልግሎት እናደይመስልሽ መብራትና ውሀ የሌለበት ከተማ። ሁሉም ከስራ ግዚያቸው በላይ ቀን ጨምረውና እረፍት ወስደው እነደሚመጡም አውቃለው። መሪዎቻችሁ ያልገባቸው እንዳልኩሽ የልጆቹ ጥያቄ ብዙውን ጊዜ ከምግብ አያልፍም። ከፈለግሽ ጥሩ ምግብ ለመብላት ብለሽ ውሰጂው። መንግስት አንደኛውን እንደታይዋን በመስታወት ውስጥ ቢያቆማቸው ይሻል ነበር። ደግሞም ታያለሽ በቅርብ ይህ መሆኑ አይቀርም አለኝ። ታይዋን ውስጥ መንግስት በመስታወት እንደሚያቆማቸውም አላውቅም። ሁሌ ብሰማውም ሴክስ እንዱስትሪ ተብሎ የሚጠራበት ምክንያትም እስከዛሬ ዞሮልኝም አያውቅም። ይህን ከሰማው በሗላ ዝም ማለትንና መሰናበትን ነው የመረጥኩት። ምንስ ላወራ እችላለው።
ድግግሞሽ እንዳይሆን ብዬ ነው እንጂ በኑሮው ውድነት የተነሳ ስለሚራቡ ዜጎች የመንግሰት ሰራተኛው ጋር፤ አስተማሪው ጋር፤ ወታደሩ ጋር፤ ተማሪው ጋር ሂዱ የሚሰማው በግልፅ ይህን መከረኛ ሆድ መሙላት አልቻልንም የሚል ብሶት ነው። እሮሮው በዝቷል። ዜጎች ሊሸከሙት ከሚችሉት በላይ ስለሆነ ደግሞ በግልጽ ነው መራባቸውንና አገዛዙ ላይ ያላቸውን ጥላቻ የሚናገሩት። እንደድሮው ካጥር ውጪ ሆኖ እንዲሰማ ድምፅን ከፍ አድርጎ የሚለምን የለም። ሁሉ በተቸገረበትና በራበው አገር ሲደክማቸው ይሄዳሉ ብላችሁ ዝም ልትሉ ነዋ። በር ይንኳኳል ሲትከፍቱ እርቦናል የሚሉ ዜጎች ናቸው። ወጣቶች፤ ሱፍ ለባሾች፤ አሮጊቶች፤ ህጻናት ሁሉንም አይነት ዜጎች አሉበት። በር መክፈት አስፈሪ ሆኗል። አሳቢ ለሆነ ዜጋ ይህ ጉዳይ ወዴት እንደሚያመራ ለመገመት ከባድ አይሆንም። እኔ እግዚያብሄር ይርዳን ነው የምለው።
ተመስገን ደሳለኝ ህዝባዊ ቁጣው ከቀጣዩ አመት መስከረም የሚያልፍ አይመስለኝም ይላል። በነገራችን ላይ በቅርብ ይታሰራሉ ብዬ ካሰብኳቸው ውስጥ ተመስገንና ይልቃል ቀርተዋል። መቼም ተረስተው አይደለም። ለምን ብለን እንድንጠራጠር መሆኑ ነው። እስከዛሬም እኛም ያው እየሆንን እንጂ የወያኔ ነገር ትናንትም ለከርሞም ያው ነው። ለማንኛውም ቸኩዬ ሳይሆን ከምቃርመው የዜጎች ችግርና ምሬት ተነስቼ ይህ ጉዳይ እስከዛ ጊዜ የሚቆይ አልመሰለኝም። ተጨማሪ ሊሆኑ በሚችሉ ሌሎች ምክንያቶች ለምሳሌ- የቀጣዩ ምርጫ የተቃዋሚዎች እንቅስቃሴ መጠናከር፤ ቃታ መሳብ የጀመሩት ቁጥራቸው እየጨመረ መሄድ። የእስልምና እምነት ተከታይ ዜጎቻችን የጀመሩት ትግል ወይ ንቅንቅ መሆኑ። ያበረ ባይሆንም አማራና የኦሮሞ ክልሎች ውስጥ የሚታየው ከስርና መሬት የረገጠ መነቃነቅ። ስልጣኑን እንዲጠብቁለት መሳርያ ያስያዛቸውን ጨምሮ ከራሱ ከውስጡ የሚሰሙት ጉርምርምታዎች መጨመር። ህዝብ በራሱ ጊዜ ውሀ አጣን። መብራት እያገኘን አይደልም። የኑሮውን ውድነት መቋቋም አልቻልንም። ቤታችንን አታፈርሱም። እያለ ብሶቱን አደባባይ ይዞ መውጣትና መተናነቅ መጀመሩ። ወያኔ አቶ አንዳርጋቸውን በማፈኑ ምክንያት ህዝቡ ውስጥ ከተፈጠረው ያልተገመተ አይነት የመጠቃትና የቁጣ ንቅናቄ ተጨማሪ ሊሆኑ በሚችልበትና የትግል ጓዶቻቸው ጦር ከማደራጁቱ ጎን ለጎን ህዝብን ማንቀሳቀስና መምራቱን እንዲሁ የተጨቆኑ ዜጎችን ለጋራ ግብ ሲባል መመራትን ማለማማዱ ወሳኝ ስለሆነ መላውን እያሰደጉት በመሆኑ በሌሎችም ብዙ ምክንያቶች ተደማምረው ጊዜውን ከመስከረም ሊያፈጥኑት ይችላል።
ለማሳሰብ ያህል ለለውጥ በሚደረግ ትግል ወሳኝና ዋነ የሆነውን ምሬትና ቁርጠኛነት ከምርጫ 97 በሗላ በነበሩት አመታት በነበረው የዜጎች በቀላሉ የማይንበብና የማይገለፅ ፈዛዛ ስሜት ተንተርስን ጊዜና ዝግጅት ለሚፈልግ ትግል እያቀድን ያለን የሮሮው ደረጃ ጋር እኩል እየሄድን አይደለም። የዜጎች የምሬት ደረጃ መብዛት መጽአዊ በሆነ ሁኔታ ሊያስነሳ ለሚችለው ቁጣን ለመምራት ተመጣጣኝ ዝግጅት ያላደረግን በድጋሚ ስህተት እንዳንሰራ። በይበልጥ በውጪ ያላችሁ አሁንም መምራቱን መረከባችሁ ግድ ካለ ባስፈላጊው ሁኔታ ዝግጁ በቶሎ ሁኑ። ከአመት ወይ ከስድስት ወር በፊት ባለ መረጃም እንኳ እየሰራችሁ ካላችሁ የምሬቱ ፈጣን እድገትና የችግሩ መክፋት እንደወረርሽኝ በየቀኑ በፍጥነት እየጨመረ እየሄደ ስለሆነ በቂ ዝግጅት ሳይደረግበት እንዳይፈነዳ። አገር ቤት ያላችሁም አብራችሁና ውስጡ ስላላችሁ እንደ ህፃን እድገት ወጣ ገባ እያለ የምሬቱን ደረጃና ስፋቱን በቀላሉ ሊያይ እንደሚችለው ዜጋ ያህል በበቂ ላይታያችሁ የሚችልበት ሁኔታ እንዳይፈጠር።
በትክክል ሁሉ ነገር ወደሰላማዊ ህዝባዊ እንቢታ እያመራና እንዲሁ ሁሉ ነገር ለዚሁ አጋዥና ተጨማሪ ጉልበት እየሆነ መሄድ ቀድሞ የታያቸውና እየወተወቱ ያሉ ዜጎች አሉ። ሰላማዊ ህዝባዊ እንቢታ ሌላ ምንም አይደለም። ሰዎቹ ቤተመንግስት እንደተቀመጡ ቀርቅበናቸው በሌላ መመራት መጀመር ነው። አለቀ ይህው ነው። በዚህ ሂደት መሪዎቻችን አዛው ሆነው ሊመሩን እስከቻሉ እንመራለን። ዘሬ ይህን አድርጉ ይሉናል እናደርጋለን፤ ነገ ደግሞ ይህን አታድርጉ ይሉናል ሁላችንም አናደርግም።
ዜጎች በዋናነት አብረን ግንዛቤ ልንወስድበት የሚገባ ቁም ነገር ግን መጀመሩና መመራቱ ብቻ ሳይሆን ከምንታገለው ሀይል አፋፋሽነት አኳያ እንዴት ይቀጥል የሚለው ቁም ነገር ነው። መሪዎቻችን በግላጭ እዛው ሆነው አርጉ ያሉንን እንደምናደርግ። ሳይመች ቀርቶ ህቡ ገብተው ሲሉንም እንዲሁ እናደርጋለን ማለት ነው። ለዚህም አላመች ብሎ ደግሞ ውጪ ላሉ ድርጅቶች አመራሩን ካቀበሉት ወይ ከተቀበሉት እንደዛው ባለ አደራ መሪዎች አድርጉ ሲሉን ማድረግ እንዳለበን ማወቁ የዋና ዋና ነው። ያሄ ነው ትግሉን አስቀጥሎ ከሚፈለገው ግብ የሚያደርሰን። ተመራጩ ባንድ ያበረ ሁሉ ዜጋ ሊታዘዘው የሚችል ድርጅት ቢሆንም አስፍተነው አመኔታችንን የሰጠነው ግለሰብም ወደ ነጻነት ሊመራን ይችላል ብለን እናስብ።
እኔም ግጥም አድርጌ አንድአርጋቸው ነኝ።