(ዘ-ሐበሻ) በየዓመቱ በዚህ ወቅት የሚጀረገው የኢትዮጵያውያን የስፖርትና የባህል ፌስቲቫል በሳንሆዜ ትናንት በድምቀት ተከፈተ። በክብር እንግድነት የተገኙት ኢትዮጵያን ከ31 ዓመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ያበቁት አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በሰረገላ በሕዝቡ መሃል ሲያልፉ በእልልታና በጭብጨባ ከፍተኛ ክብር ተሰጥቷቸዋል።
ለአንድ ሳምንት ያህል የሚቆየው ይኸው የኢትዮጵያውያን ስፖርት ፌስቲቫል መከፈቱን ያበሰሩት የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ተስፋዬ ይህን ፌስቲቫል ለመታደም የመጣውን ሕዝብ አመስግነው፤ ከጎናችን በመቆማችሁና በሄድንበት ቦታ ሁሉ እየተከተላችሁ የምታሳዩን ድጋፍ ለበለጠ ሥራ የሚያነሳሳ ነው ብለውታል። ከስፖርት ውድድሩ በተጨማሪ የሙዚቃ ኮንሰርቶች ከረቡዕ ምሽት ጀምሮ እንደሚኖሩ ያስታወቁት አቶ ጌታቸ ቴዎድሮስ ታደሰ፣ ቴዲ አፍሮ፣ ጃኪ ጎሲ፣ ፋሲል ደመወዝ፣ ሸዋንዳኝ ሃይሉ፣ ሚካኤል በላይነህ የሚገኙበት ኮንሰርቶች ዝግጅቱን ያድምቁታል ብለዋል። አርብ የኢትዮጵያ ቀን ሲከበርም የተለያዩ ባህላዊና ዘመናዊ ሙዚቃዎች በስታዲየሙ እንደሚኖር ተገልጿል።
ከአሜሪካና ከካናዳ የተለያዩ ከተሞች የመጡት የእግር ኳስ ተጫዋቾች በመክፈቻው ዝግጅት ላይ በሕዝብ መሃል በመዘዋወር የተዋወቁ ሲሆን ሁሉም በራሳቸው መንገድ የኢትዮጵያን ዳንስና ሙዚቃዎችን እየጨፈሩ ያሳዩት እንቅስቃሴ በጣም የሚያስደስትና በየዓመቱ የሚናፈቅ ነው።
በስታዲየሙ ውስጥ በተተከሉ ድንኳኖች ውስጥም ምግብ፣ ጌጣጌጦች፣ አልባሳት፣ ሙዚቃዎች፣ ባንዲራዎች እየተሸጡ ሲሆን የተለያዩ ድርጅቶችም ድንኳን በመያዝ ከሕዝብ ጋር እየተዋወቁ ነው።
የሳንሆዜው የመክፈቻ ዝግጅት ላይ የታደመውን ሕዝብ ፎቶ ይመልከቱ፦ ተጨማሪ ፎቶዎችን እና ዘገባዎችን ይዘን እንመለሳለን።
ሳምንቱን ሙሉ የዘ-ሐበሻ ወኪሎች በሳንሆዜ ስለሚገኙ ዘገባዎችን ይዘን እንቀርባለን።
ሚኒሶታን ወክሎ ሳንሆዜ የተገኘው የኒያላ ቡድን