May 13, 2014
12 mins read

ደቡብ ሱዳን-የሰላም ዉልና ጦርነት

ነጋሽ መሐመድና ተክሌ የኋላ እንዳቀረቡት

 

ባለፈዉ ታሕሳስ አጋማሽ የተጀመረዉ ጦርነት አንዳድ ግምቶች እንደሚጠቁሙት በአስር ሺሕ የሚቆጠር ሕዝብ ገድሏል።ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ አፈናቅሏል።ወይም አሰድዷል።ከሰወስት ሚሊዮን የሚበልጥ ለረሐብ አጋልጧል።ጦርነቱ እስከ መጪዉ የዝናብ ወቅት ከቀጠለ ደግሞ—–

ታሕሳስ ጦርነት ገጠሙ።ጥር የተኩስ አቁም ሥምምነት ተፈራረሙ።ተኩስ ግን አላቆሙም።ባለፈዉ አርብ እንዳዲስ ተኩስ አቁም ዉል ተፈራረሙ።ዛሬም ይቃዋጋሉ።እንዳዲስ ይወነጃጀላሉ።

የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና የአማፂያኑ መሪ የቀድሞዉ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቸር እንደጠላት መሻኮት፤ መወነጃጀል፤ መታኮስ ከጀመሩ ወዲሕ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለፈዉ አርብ አዲስ አበባ ዉስጥ ፊት ለፊት ተያዩ።አምስት ወር ያስቆጠረዉን ጦርነት ለማስቆም ይረዳል የተባለዉን ስምምነትም ፈረሙ።

በአምስት ወር ለሁለተኛ ጊዜ የተፈረመዉ የተኩስ አቁም ዉል ለአዲሲቱ አፍሪቃዊት ሐገር ሠላም በርግጥ ጠቃሚ፤ ከግጭት ጦርነት ሌላ-ሠላም መረጋጋት ለማያዉቀዉ ደሐ ሕዝቧም ተስፋ ሰጪም ነበር።የአፍሪቃ ጉዳይ የፖለቲካ አጥኚ ፕሮፈሰር መድሕኔ ታደሰ እንደሚሉት አርብ የተፈረመዉ ስምምነት ከወረቀት አልፎ ገቢር የሚሆን ከሆነ ይዘቱ ገንቢ ነዉ።

ባለፈዉ ታሕሳስ አጋማሽ የተጀመረዉ ጦርነት አንዳድ ግምቶች እንደሚጠቁሙት በአስር ሺሕ የሚቆጠር ሕዝብ ገድሏል።ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ አፈናቅሏል።ወይም አሰድዷል።ከሰወስት ሚሊዮን የሚበልጥ ለረሐብ አጋልጧል።ጦርነቱ እስከ መጪዉ የዝናብ ወቅት ከቀጠለ ደግሞ እንደ ጎሮጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ከ1980ዎቹ ወዲሕ በአፍሪቃ ታይቶ የማይታወቅ ቁጥር ያለዉ ሕዝብን ለከፋ ረሐብ ያጋልጣል።በደቡብ ሱዳን የአዉሮጳ ሕብረት መልዕክተኛ ጀርመናዊዉ ሴቫን ኩሕን ፎን ቡርግስዶርፍ እንደሚሉት ባለፈዉ አርብ የተደረገዉ ስምምነት እስካሁን የታየዉን ጥፋት፤ ይደርሳል ተብሎ የሚፈራዉን መቅሰፍት ለማስቆምም እጅግ ጠቃሚ ነዉ።

«ሥምምነቱ ለችግር ለተጋለጡ ሰዎች እርዳታ እንዲደርስ የሚፈቅድ በመሆኑ በጣም ጠቃሚ ነዉ።እንደሚገመተዉ በያዝነዉ ዓመት ማብቂያ 4 ሚሊዮን ያሕል ሕዝብ የምግብ ርዳታ ያስፈልገዋል።አንዳድ ባለሙያዎች እንደሚያስጠነቅቁት የምግብ እጥረት ላጋጠመዉ አካባቢ አስቸኳይ ርዳታ ካልደረሰ አስከፊ ሰብዊ ድቀት መከሰቱ አይቀርም። ከሐገሪቱ ስልሳ-ከመቶዉ የመሠረተ-ልማት አዉታር ባልተዘረጋባት ሱዳን (ጦርነት ሲታከልበት) ለችግረኛዉ ሕዝብ ርዳታ ማቅረብ ሲበዛ ከባድ ነዉ።»

ያ ስምምነት የፈነጠቀዉ ተስፋ ዳር መዝለቁ ማጠራጠሩ እንጂ ቀቢፀ ተስፋዉ።ቢያንስ እስካሁን ከወረቀት አላለፈም።ፈራሚዎች ካንጀት ሳሆን-ካንገት፤ ፈልገዉ፤ ተግባብተዉ ሳይሆን ተፅዕኖን ፈርተዉ መፈረማቸዉ – ነዉ ድቀቱ።እንደገና ፕሮፈሰር መድሕኔ።

አሁን ያሉት ክስተቶች-ጦርነት፤ መወጋገዝና እና ያዉ የሰዎች ሞት፤ ስደትና መፈናቀል ናቸዉ።እንደ ፕሮፌሰር መድሕኔ ሁሉ ጀርምናዊዉ ዲፕሎማት ቡርግስዶርፍ ገና ዉሉ እንደተፈረመ የመጀመሪያዉ «ቀና እርምጃ» ብለዉት ነበር።የዚያኑ ያክል ዉሉን ገቢር ማድረጉን «ከባድ» ነዉ ያሉት።

«ትናንት ማታ የተፈረመዉ ስምምነት አንድ ጠቃሚ እርምጃ ነዉ።ከእንግዲሕ ገቢራዊ ማደረጉ ነመከተል አለበት።አስቸጋሪዉም ገቢር ማድረጉ ነዉ።»

የተፋላሚ ሐይላት መሪዎች ሁለተኛዉን የተኩስ አቁም ስምምነት የመፈረማቸዉ ተስፋ-ተነግሮ ሳያበቃ ጦርነቱ መቀጠሉ እየተዘገበ፤ አንዱ ሌላዉን ማዉገዝ መወንጀሉ እየተስማ ነዉ።

በስምምነቱ መሠረት ከቅዳሜ እኩለ ሌት ጀምሮ የሁለቱ ወገኖች ጦር በየአለበት መርጋት አለበት።ስምነቱ ይፀናል በተባለ በሰዓታት ልዩነት ዉስጥ ግን የቀድሞዉ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቼር የሚመሯቸዉ አማፂያን የመንግሥት ጦር ዉጊያ ከፍቶብናል በማለት ወጅሏል።

አማፂያኑ እንዳስታወቁት የመንግሥት እግረኛ ጦር ትናንት ጠዋት ቤንቲዉ እና የላይኛዉ ናይል በተባሉት ሁለት ግዛቶች የሚገኙ የአማፂያኑን ይዞታ በመድፍ ጭምር ሲደበድብ ነዉ-የዋለ ያመሸዉ።የመንግሥት ባለሥልጣናት ባንፃሩ አማጺያኑ ስምምነቱን ጥሰዉ የመንግሥት ጦር ይዞታን እያጠቁ ነዉ በማለት ይከሳሉ።ግጭት መወነጃጀሉ ዛሬም አላባራም።

ለሁለተኛ ጊዜ ያዉም በመሪዎች የተፈረመዉ ስምምነት ለሰዓታት ያሕል እንኳ አለመከበሩ ብዙ ማነጋገሩ እልቀረም።ፕሮፈሰር መድሕኔ ግን የስምምነት ማግስቱ ዉጊያ፤ መወነጃጀል የሚጠበቅ ነበር ባይ ናቸዉ።ምክንያት፤-

በርግጥም ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅቱ የፈራሚዎቹ አካላዊ -ቋንቋ ሁሉኑንም ብሎት ነበር።ፈገግታ የለም።መጨባበጥ የለም።የመግባባት ስሜት-አልተንፀባረቀም።ያም ሆኖ የኣማፂያኑ መሪ ሪክ ማቸር እንደዲፕሎማሲዉ ወግ ቡድናቸዉ ለስምምነቱ እንደሚገዛ ቃል ገብተዉ ነበር።

«ይሕን ስምምነት ሥፈርም፤ ይሕ ግጭት በሰላማዊ መንገድ መወገድ አለበት የሚል መልዕክት ማስተላለፌ ነዉ።ሌለኛዉ ወገንም (ዉሉን የፈረመዉ) ከልቡ ነዉ የሚል ተስፋ አለኝ።»

በፖለቲካ-ዲፕሎማሲዉ፤ በጦር አዉዱም የበሰሉት የኙዊሮቹ ፖለቲከኛ የልባቸዉን በልባቸዉ ይዘዉ ዓለምን ሲሸነግሉ ተቀናቃኛቸዉ ተቃራኒዉን ተናገረዉ የዉሉን ዉል-አልባነት አፈረጡት።የቀድሞዉ ጄኔራል ሰላሳ ዘመን ያስቆጠረዉ የደቡብ ሱዳን ጦርነት ካበቃ በሕዋላ መላዋ ሱዳን በምክትል ፕሬዝዳንትነት-ለአምስት አመት፤ ደቡብ ሱዳን ነፃ ከወጣች በሕዋላ ደግሞ በፕሬዝዳንትነት ለሁለት ዓመት ያክል መረተዋል።

የሰባት ዓመቱ የመሪነት ልምድ ግን ወታደራዊ ስብዕናቸዉን በሐይል የመመካት ባሕሪያቸዉን አልሞረደዉም። ሳልቫ ኪር በአካላቸዉ ያሳዩትን ቁጣ-መኮሳተር በቃላትም ደገሙት።ከኔ ሌላ ደቡብ ሱዳን መሪ የላትም እያሉ አዲስ አበባ ላይ ተገሰሉ።

«እኔ የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ነኝ።በፕሬዝዳንትነት ሥልጣኔ፤ የዚያች ሐገር መሪ እንደሆንኩ እቀጥላለሁ።»

ባለፈዉ ጥር ማብቂያም ሆነ፤ ባለፈዉ አርብ የተደረገዉ ስምምነት በአብዛኛዉ የዉጪ በተለይም የዩናትድ ስቴትስን ግፊት ፍራቻ የተደረገ እንጂ ተፋላሚዎችን ልብ ለልብ ያገናኝ አይደለም። ኪር እንዳሉት የተፋላሚ መሪዎችን ሥልጣን የማጣት ሥጋትን ያስወገድ ወይም ለሕዝብ ፍላጎት መገዛትን እንዲገነዘቡ ወይም እንዲገደዱ ያደረገ አይደለም።

የጎሳ መልክና ባሕሪ የተላበሰዉ ጦርነት በየጎሳዉ መሪዎች ወይም አክራሪ ጎሰኞች ዘንድ ያሳደረዉ የብቀላ ወይም ብቀላን የመቋቋም ስሜትን የሚያስወግድ አይደለም።እና ስምምነቱ እዉነተኛ ስምምነት ለመሆን በፕሪሮፌሰር መድሕኔ አገላለፅ ብዙ ይቀረዋል።

የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ሐይላትን የሚያደራደረዉ የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) የወቅቱ ሊቀመንበር የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚስትር አቶ ሐይለማርያም ደሳለኝ ዛሬ ያልተከበረዉ ስምምነት ባለፈዉ አርብ ሲፈረም ፈራሚዎችን አስጠንቅቀዉ ነበር።እንዲሕ ብለዉ

«እንዳትሳሳቱ።ሰዎች ሲገደሉ አካባቢዉና ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ዝም ብሎ አይቀመጥም።»

ላሁኑ ግድያ፤ ሥደት-መፈናቀሉ አልቆመም።ያካባቢዉ፤ ያለም አቀፉ ማሕበረሰብ እርምጃም አልታየም።

ምንጭ ጀርመን ድምጽ ራድዮ

Latest from Blog

እነዶ/ር ደብረፅዮን እና በጠ/ሚ ዐብይ አህመድ በተሾሙት የትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት መሪዎች እነጌታቸው ረዳ መካከል የነበረው አለመግባባት ተካርሮ ሰራዊቱን ወደውግንና አስገብቷል። የትግራይ ሐይል አዛዦች ትላንት ባወጡት መግለጫ ውግንናቸው ከእነዶ/ር ደብረፅዮን ጋር መኾኑን አስታውቀዋል።

በትግራይ የተፈጠረው ምንድነው?

January 23, 2025
የድሮ መሪዎች ያላደረጉትን ምሁር ጳጳሳቱ ያላስተዋሉትን ከፈረሰች ጎጆ ከባልቴት ቤት ገብቶ ክብሩን ዝቅ አድርጎ ውሀዋን ጠጥቶ ምግቧንም ተጋርቶ ያላለቀሰ ሰው ያንን ትይንት አይቶ ማን ይኖራል ከቶ? በዉሸት ፈገግታ ፊቱን አስመስሎ ፀሀይ የበራበት

ሰው በሰውነቱ – ከ ይቆየኝ ስሜ

የአማራ ፋኖ በጎጃም ምክትል የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የነበረው እና አሁን ላይ በአማራ ፋኖ በጎጃም የሁለተኛ (ተፈራ ) ክፍለጦር ሰብሳቢ የነበረው ፋኖ ዮሐንስ አለማየሁ በክብር ተሰዋ። የአማራ ህዝብ የተጋረጠበትን የህሎና አደጋ ለመቀልበስ ያለ

ከአማራ ፋኖ በጎጃም የተሰጠ የሐዘን መግለጫ ታጋይ ይሰዋል ትግል ይቀጥላል !

January 22, 2025
Go toTop